በኢየሱስ አሟሟት ላይ የተነሳው ውዝግብ
በ33 እዘአ በዋለው የማለፍ በዓል ዕለት ሶስት ሰዎች ተገደሉ። ሞት የተፈረደባቸው ሶስት ሰዎች ከኢየሩሳሌም ቅጥር ውጭ ወደሚገኝ ሥፍራ ተነድተው ተወሰዱና በጣም በሚያሰቃይና በሚያዋርድ ሁኔታ ቀጥ ባለ የእንጨት ምሰሶ ላይ ተሰቅለው ሞቱ። እንዲህ ያለው አገዳደል በሮማውያን ዘመን በጣም የተስፋፋ ስለነበረ ይህ በማለፍ በዓል ዕለት የተፈጸመው ግድያ ተረስቶ መቅረት ነበረበት። ይሁን እንጂ ከተገደሉት ሰዎች መካከል አንዱ ኢየሱስ ክርስቶስ ነበር። የእርሱ መገደል ታላቅ ሃይማኖታዊ ለውጥና ውዝግብ አስከትሎአል።
አሁን ይህ ድርጊት ከተፈጸመ 2,000 ዓመት ሊሞላው ስለተቃረበ ይህ ተራ የሆነ ጥንታዊ ታሪክ ነው ብለህ ታስብ ይሆናል። ይሁን እንጂ በዚያ ጊዜ የተነሳው ውዝግብ አሁንም ቢሆን ገና ጸጥ አለማለቱን ታውቃለህን?
በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ኢየሱስ ለእነርሱ ሲል መሞቱን እንደሚያምኑ ታውቅ ይሆናል። ቤዛና የኃጢአት ሥርየት የሚገኘው በክርስቶስ ሞት እንደሆነና በዳን የሚቻለው በሞቱ በማመን እንደሆነ ብዙ ሰዎች በጋለ ስሜት ይናገራሉ። ይሁን እንጂ ይህ የተወደደ እምነት “በችግር ላይ እንደወደቀ” የአንግሊካን ቲዎሎጂካል ሪቪው ገልጾአል።
አንግሊካን ቲዎሎጂካል ሪቪው እንዲህ በማለት ያብራራል፦ “የሥርየት መሠረተ ትምህርት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማስረጃዎቹ አጠያያቂ ስለሆኑ፣ የትምህርቱ አመሰራረት ጠባብ አስተሳሰብ የሞላበት ስለሆነ፣ . . . በመንፈሳዊ ሕይወት ውስጥ በሚገለጥበት ጊዜ የስሜት ግንፋሎትና ራስን የማጽደቅ ዝንባሌ ስለሚታይበት በክርስትና አስተሳሰብ ውስጥ ችግር አጋጥሞታል።” በእውነትም የፕሮቴስታንትም ሆነ የካቶሊክ ሃይማኖታዊ ሊቃውንት የኢየሱስ ክርስቶስ ሞት ትርጉም አለው ቢሉ እንኳን ስለሚኖረው ትርጉም ስምምነት ላይ መድረስ አልቻሉም።
ምናልባት ይህ ጉዳይ የእኔን የግል ሕይወት የማይመለከት ጥቂት ሃይማኖተኞች ብቻ የሚጨቃጨቁበት ጉዳይ ነው ብለህ ታስብ ይሆናል። ይሁን እንጂ ስለሚከተለው ቁምነገር አስብ። የኢየሱስ ሞት በአምላክ ፊት ከሚኖርህ አቋምና ከዘላለም ሕይወት (በሰማይም ሆነ በማንኛውም ሌላ ሥፍራ) ተስፋህ ጋር ግንኙነት ያለው ነገር ከሆነ ይህ ውዝግብ የሚያሳስብህ ነገር ይሆናል ማለት ነው።
ሃይማኖታዊ ምሁራን እስከአሁን ድረስ በዚህ ጉዳይ ላይ የሚከራከሩት ለምንድን ነው? ለምሳሌ ያህል የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያንን እንውሰድ። ስለ ነፍስ ዘላለማዊነትና ስለ ሥላሴ የተብራራ መሰረተ ትምህርት አላት። ይሁን እንጂ በክርስቶስ ሞት አማካኝነት ደህንነት ስለማግኘት ቤተክርስቲያን ያላት አቋም የተቆረጠና ግልጽ የሆነ አይደለም። ዘ ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፒድያ እንዲህ ይላል፦ “የሰው ልጅ እንዴት ከኃጢአት ክፋት ነፃ ወጥቶ ወደ አምላክ ጸጋ እንደደረሰ ለማስረዳት ዓይነታቸው ብዙ የሆኑና የተለያዩ ማብራሪያዎች ቀርበዋል። . . . ይሁን እንጂ አንዳቸውም ቢሆኑ ሙሉ በሙሉ አልተሳካላቸውም። . . . የመቤዠት መንፈሣዊ ትምህርት አሁንም ቢሆን ምንነቱ በከፊል አልተደረሰበትም። ወደፊትም የመንፈሣዊ ትምህርት ችግር እንደሆነ ይቀጥላል።”
ስለዚህ በግለት ኢየሱስ ሞቶልናል ከሚሉት በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች መካከል ይህ አባባላቸው ምን ትርጉም እንዳለው የሚረዱት በጣም ጥቂቶች መሆናቸው ሊያስደንቅህ አይገባም። አንግሊካን ቲዎሎጂካል ሪቪው እንደሚለው “አማኙ ክርስቲያን በጥያቄ ተወጥሮ ሲያዝ ስለ መሰረተ ትምህርቱ ማስረጃ ከመጽሐፍ ቅዱስ ሊጠቅስ ወይም እንዴት እንደሚሰራ ሊያብራራ አይችልም።” የአብያተ ክርስትያናት ተሳላሚዎች ሊረዱትም ሆነ ሊያስረዱ የማይችሉት መሰረተ ትምህርት ስለተጫነባቸው የክርስቶስ መሞት ከሕይወታቸው ጋር ምን ዝምድና እንዳለው መረዳት ችግር ሆኖባቸዋል።
ሕዝበ ክርስትና ስለመቤዠት ግልጽ የሆነ መሰረተ ትምህርት ለማቅረብ አለመቻልዋ የክርስትናን መልእክት ለአይሁዶች፣ ለሂንዱዎች፣ ለቡድሂስቶችና ለሌሎች ለማድረስ የምታደርገውን ጥረት አሰናክሎባታል። ከእነዚህ ሰዎች ብዙዎቹ አብዛኞቹን የኢየሱስ ትምህርቶች የሚያደንቁና የሚያከብሩ ቢሆኑም በኢየሱስ ሞትና ሞቱ ስላለው ትርጉም የተፈጠረው ግራ መጋባት ለማመን እንቅፋት ሆኖባቸዋል።
የኢየሱስ ሞት ትርጉምና ዓላማ ከሰው የመረዳት ችሎታ ውጭ የሆነ ምሥጢር ነውን? ወይስ ምክንያታዊ የሆነና የመጽሐፍ ቅዱስ ጭብጥ ያለው ማብራሪያ አለው? መጽሐፍ ቅዱስ ‘በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት ያገኛል እንጂ አይጠፋም’ ስለሚል እነዚህ ጥያቄዎች ልታስብባቸው የሚገቡ ናቸው።—ዮሐንስ 3:16