የይሖዋ ሰማያዊ ሠረገላ ወደፊት ይገሰግሳል
“መንኮራኩሮቹም እኔ እየሰማሁ ጌልጌል (የሚሽከረከሩ) ተብለው ተጠሩ።”—ሕዝቅኤል 10:13
1. ይሖዋ እንዴት ያለ መጓጓዣ አለው?
በጣም የተራቀቁ ጄቶት ባሉባቸው በእነዚህ ቀኖች የዓለም መሪዎች በጉዞ ቅልጥፍና ረገድ የመጨረሻውን ደረጃ እንዳገኙ ይሰማቸው ይሆናል። ይሁን እንጂ ከ2,600 ዓመታት በፊት ይሖዋ አምላክ ምንም መሐንዲስ አይቶት የማያውቅ ዓይነት ከሁሉ የበለጠ መጓጓዣ እንዳለው አሳይቷል። እርሱም በጣም ትልቅና አስፈሪ ሠረገላ ነው! የጽንፈ ዓለሙ ፈጣሪ ሠረገላ መሳይ በሆነ ተሽከርካሪ ላይ የሚጓዝ መሆኑ እንግዳ ነገር ይመስላልን? አይመስልም። ምክንያቱም የይሖዋ ሰማያዊ ተሽከርካሪ ከማንኛውም በሰው ከታየ ወይም ከታሰበ ተሽከርካሪ የተለየ ስለሆነ ነው።
2. ሕዝቅኤል ምዕራፍ 1 የይሖዋን ሰማያዊ ሠረገላ እንዴት አድርጎ ይገልጸዋል? ነቢዩስ ትኩረታችንን በመጀመሪያ የሚስበው ወደ እነማን ነው?
2 በሕዝቅኤል ትንቢት ምዕራፍ 1 ላይ ይሖዋ በአንድ በጣም ትልቅ ሰማያዊ ሠረገላ ላይ ተቀምጦ እንደሚነዳ ሆኖ ተገልጿል። ይህ ባለ አራት ጐማ የሆነ አስገራሚ ተሽከርካሪ በራሱ ኃይል የሚሽከረከርና አስደናቂ ነገሮችን መሥራት የሚችል ነው። ሕዝቅኤል በ613 ከዘአበ ከጥንቷ በባቢሎን ወንዞች በአንዱ ሳለ ይህንን ሰማያዊ ሠረገላ በራእይ ተመለከተ። ነቢዩ በመጀመሪያ ያንን የይሖዋን ሰማያዊ ሠረገላ ወደሚያጅቡት ትኩረታችንን ይስበዋል። ማብራሪያውን ስናነብ ሕዝቅኤል ያየውን በዓይነ ህሊናችን ለማየት እንሞክር።
አራት ሕያዋን ፍጥረታት
3. የአራቱ ኪሩቤሎች አራት አራት ፊት ምን ያመለክታሉ?
3 ሕዝቅኤል እንዲህ በማለት ይገልጽልናል፦ “እኔም አየሁ፤ እነሆም ከሰሜን በኩል ዐውሎ ነፋስና ታላቅ ደመና የሚበርቅም አሳት መጣ። ከዙሪያውም ፀዳል ነበረ። . . . ከመካከልም የአራት እንስሳት [ፍጥረታት (አዓት)] አምሳያ ወጣ።” (ሕዝቅኤል 1:4, 5) እነዚህ አራት ፍጥረታት ወይም ኪሩቤሎች እያንዳንዳቸው አራት አራት ክንፍና አራት አራት ፊቶች ነበራቸው። የይሖዋን ፍትሕ የሚያመለክት የአንበሳ ፊት፣ የአምላክን ኃይል የሚያመለክት የበሬ ፊትና ጥበቡን የሚያመለክት የንስር ፊት ነበራቸው። በተጨማሪም የይሖዋን ፍቅር የሚያመለክት የሰው ፊት ነበራቸው።—ዘዳግም 32:4፤ ኢዮብ 12:13፤ ኢሳይያስ 40:26፤ ሕዝቅኤል 1:10፤ 1 ዮሐንስ 4:8
4. ኪሩቤሎቹ ለምን አራት አራት ፊት አላቸው? በፍጥነት ረገድ ኪሩቤሎቹ እንዴት ነበሩ?
4 እያንዳንዱ ኪሩብ ወደ አራቱ አቅጣጫዎች የሚመለከቱ ፊቶች ነበሩት። ስለዚህ ኪሩቦቹ ወደተፈለገው አቅጣጫ የሚመለከተውን ፊት ጐዳና ለመከተል በፍጥነት መንገዳቸውን ሊለውጡ ይችላሉ። ታዲያ የእነዚያ ኪሩቦች ፍጥነት እንዴት ነበር? በመብረቅ ፍጥነት ሊወረወሩ ይችሉ ነበር! (ሕዝቅኤል 1:14)ሰው ሠራሽ የሆነ የትኛውም ተሽከርካሪ እስከ አሁን ወደዚህ ፍጥነት አልደረሰም።
5. ሕዝቅኤል የሠረገላውን መንኮራኩርና የመንኮራኩሩን ዙሪያ የገለጸው እንዴት ነው?
5 በድንገት የሠረገላው እግሮች (ጐማዎች) ታዩ። እንዴት የተለዩ ናቸው! ቁጥር 16 እና 18 “ሥራቸውም በመንኮራኩር ውስጥ እንዳለው መንኮራኩር ነበር። ቁመታቸውም የረዘመና የሚያስፈራ ነበር። የአራቱም ክበብ ዙሪያው በዓይን ተሞልቶ ነበር” ይለናል። በእያንዳንዱ ኪሩብ አጠገብ አንዳንድ መንኮራኩር ካለ በአራቱ ኪሩቦች አጠገብ አራት መንኮራኩሮች ነበሩ ማለት ነው። መንኮራኩሮቹ እያንዳንዱ ቢረሌ እንደሚባለው አንፀባራቂ አረንጓዴ ወይም ቢጫ ክቡር ድንጋይ ያበሩ ነበር። ይህም ለዚህ አስደናቂ ራእይ ብርሃንና ውበት ይጨምርለታል። መንኮራኩሮቹ “ዙሪያቸውን በዓይኖች ተሞልተው” ስለነበር እንዲሁ ያለ አቅጣጫ የእውር ጉዞ አያደርጉም ነበር። መንኮራኩሮቹ ወይም ጐማዎቹ በጣም ትልቅ በመሆናቸው በእንዝርታቸው ላይ አንዴ ሲሽከረከሩ ከፍተኛ ርቀትን ሊሸፍኑ ይችሉ ነበር። እንደ አራቱ ኪሩቦች ሁሉ እነሱም በመብረቅ ፍጥነት ይንቀሳቀሱ ነበር።
በመንኮራኩር ውስጥ መንኮራኩር
6. (ሀ) ሠረገላው መንኮራኩር በመንኮራኩር ውስጥ የነበረው እንዴት ነው?(ለ) ጐማዎቹ የእንቅስቃሴአቸውን አቅጣጫ ከምን ጋር ያቀናጁት ነበር?
6 እንግዳ የሆነ ሌላም ነገር ነበር። እያንዳንዱ መንኮራኩር በውስጡ ተመሳሳይ መንኮራኩር ነበረው። ውስጠኛው መንኮራኩር በመስቀለኛ ቅርጽ የተገጠመ ነበር። በዚህ መንገድ ብቻ ነበር መንኮራኩሮቹ “በየአራቱ ጐድናቸው ይሄዱ ነበር” ሊባል የሚችለው። (ቁጥር 17) ወደየአቅጣጫው መሽከርከር የሚችል የመንኮራኩሩ ጐን ስለነበረ መንኮራኩሮቹ በቅጽበት አቅጣጫ ሊቀይሩ ይችሉ ነበር። መንኮራኩሮቹ የጉዞ አቅጣጫቸውን ከኪሩቦቹ አቅጣጫ ጋር ያስማሙ ነበር። አንድ ትልቅ ጀልባ በአየር ግፊት በውሃ ላይ እንደሚንሳፈፍ ሁሉ የአምላክ ሠረገላም በአራቱ መንኮራኩሮች ላይ ወደላይ ተደግፎ ይሄድ ነበር።
7. ለመንኮራኩሮቹ የኃይል ምንጭ ምን ነበር?
7 መንኮራኩሮቹ የእንቅስቃሴ አቅጣጫቸውን ከአራት ኪሩቦች እንቅስቃሴ ጋር ለማቀናጀት ኃይል ያገኙት ከየት ነው? ሁሉን ከሚችለው አምላክ ቅዱስ መንፈስ ነው። ቁጥር 20 እንዲህ ይላል፦ “መንፈሱ ወደሚሄድበት ሁሉ እነርሱ ሄዱ፤ [የሕያዋን ፍጥረታቱ (አዓት)] መንፈስ በመንኮራኩሮቹ ውስጥ ነበርና። በኪሩቦቹ ውስጥ የነበረው ያው የአምላክ ፈጣን ኃይል በመንኮራኩሮቹም ውስጥ ነበረ።”
8. መንኮራኩሮቹ ምን ስም ተሰጣቸው? ለምንስ?
8 መንኮራኩሮቹ “የሚሽከረከሩ” በሚል ስያሜ ተጠቅሰዋል። (ሕዝቅኤል 10:13) ይህም እያንዳንዱ መንኮራኩር በሚሠራው ሥራ የተነሣ እንደሆነ ግልጽ ነው። መንኮራኩሩ ይሽከረከራል ወይም ይዞራል። ይኸኛውን የሰማያዊ ሠረገላ ክፍል በዚህ መንገድ መጥራት ይህ ሰማያዊ ሠረገላ የሚንቀሳቀስበትን ፍጥነት ያስታውሳል። መንኮራኩሮቹ በከፍተኛ ፍጥነት ቢሽከረከሩም በዓይን የተሞሉ ስለሆኑ ምን ጊዜም መንገዳቸውን ማየት ይችሉ ነበር።
9. በከፍተኛ ፍጥነት ከሚሽከረከሩት የሠረገላው ጎማዎች በላይ ምን እንደነበረ ነው ሕዝቅኤል የገለጸው?
9 አሁን ደግሞ ከእነዚህ በሚያስፈራ ሁኔታ ረዣዥምና በከፍተኛ ፍጥነት ተንቀሳቃሽ ከሆኑት መንኮራኩሮች በላይ ምን እንዳለ እንመልከት። ሕዝቅኤል ምዕራፍ 1 ቁጥር 22 እንዲህ ይላል፦ “[ከሕያዋን ፍጥረታቱ (አዓት)] ራስ በላይ የሚያስፈራ በረዶ የሚመስል የጠፈር አምሳያ በራሳቸው ላይ ተዘርግቶ ነበር።” ጠፈሩ ጠጣር ቢሆንም እንደ በረዶ ብርሃን የሚያስተላልፍ ነበር። በብዙ ሺህ የሚቆጠር አልማዝ ጸሐይ ሲመታቸው እንደሚያብለጨልጩት ዓይነት ነበር። እውነትም ፍርሃት የሚያሳድር ግርማ ነበር።
ክብራማው የሠረገላ ነጂ
10. (ሀ) ዙፋኑና በእርሱ ላይ የተቀመጠው የተገለጹት እንዴት ነው? (ለ) የሠረገላው ጋላቢ ክብር የለበሰ መሆኑ ምን ያመለክታል?
10 ነጂው ሕዝቅኤልን ለማናገር ሳይሆን አይቀርም ሠረገላው ቆም ይል ነበር። ከጠፈሩ በላይ መልኩ ደማቅ ሰማያዊ የሰንፔር ድንጋይ የሚመስል የዙፋን አምሳያ ነበር። በዙፋኑም ላይ የሰው ልጅ የሚመስል ነገር ነበር። ሕዝቅኤል ይህን መለኮታዊ መግለጫ ይበልጥ ለማስተዋል ሊረዳው የሚችለው ያ የሰው አምሳያ ነበር። ይሁን እንጂ ያ የሰው አምሳያ በሚያንጸባርቅ የብርና የወርቅ ቅልቅል መልክ ያበራ ስለነበረ ክብር ለብሶ ነበር። እንዴት ያለ የሚያንቀጠቅጥ ግርማ ነው! ይህ አሸብራቂ ክብር ከዚህ የሰው አምሳያ ወገብ በላይና በታችም ይገኛል። በመሆኑም አጠቃላይ ቅርጽ በክብር የተከበበ ነበር። ይህም ይሖዋ በቃላት ሊገለጽ ከሚችለው በላይ ክብራማ መሆኑን ያመለክታል። ከዚህም ሌላ የሠረገላው ተቀማጭ ውብ በሆነ ቀስተ ደመና ዙሪያውን ተከቧል። ከባድ ዝናብ ከጣለ በኋላ ቀስተ ዳመና መታየቱ እንዴት ያለ የጸጥታና የመረጋጋትን ስሜት ያሳድራል! ይሖዋ ይህን እርጋታ ይዞ የጥበብ፣ የፍትሕ፣ የኃይልና የፍቅር ባሕርዮቹን በፍጹም ሚዛናዊነት ይጠብቃቸዋል።
11. ሕዝቅኤል የይሖዋን ሠረገላና የዙፋኑን ራእይ ካየ በኋላ እንዴት ተሰማው?
11 የይሖዋ ሠረገላና ዙፋን በብርሃንና ውብ በሆኑ ሕብረ ቀለማት ተከበዋል። የጨለማና የስውር ነገር መስፍን የሆነው የሰይጣን ሁኔታ ከዚህ እንዴት የተለየ ነው! ሕዝቅኤልስ በዚህ ሁሉ እንዴት ተነካ? “ባየሁም ጊዜ በግምባሬ ተደፋሁ። የሚናገርንም ድምጽ ሰማሁ” ሲል ይነግረናል።—ሕዝቅኤል 1:28
ሠረገላው ምን ያመለክታል?
12. የይሖዋ ሰማያዊ ሠረገላ ምን ያመለክታል?
12 ይህ አስደናቂ ሠረገላ የሚያመለክተው ምንድነው? የይሖዋን ሰማያዊ ድርጅት ነው። የይሖዋ ሰማያዊ ድርጅት የተገነባውም በማይታየው ዓለም ባሉ ቅዱሳን መንፈሳዊ ፍጡሮቹ ማለትም በሱራፌሎች፣ በኪሩቤሎችና በመላእክት ነው። ይሖዋ ከሁሉም በላይ የሆነ አምላክ ስለሆነ መንፈሳዊ ፍጡሮቹ ሁሉ ለሱ ተገዥዎች ናቸው። በደግነት ስለሚገዛቸውና ዓላማውን ለማስፈጸም ስለሚጠቀምባቸው በላያቸው ላይ ተቀምጦ እንደሚጋልብ ያህል ነው።—መዝሙር 103:20
13. (ሀ) ይሖዋ በድርጅቱ ላይ ተቀምጦ ይጋልበዋል ለማለት የሚቻለው ለምንድን ነው? (ለ) አራት ጐማዎች የነበሩት የይሖዋ ሠረገላ ወደፊት እየተንቀሳቀሰ ስለመሆኑ የሚገልጸው ራእይ እንዴት ይነካሃል?
13 ይሖዋ ልክ በሠረገላ ላይ እንደተቀመጠ ያህል ይህን ድርጅት ይጋልበዋል፤ ድርጅቱ መንፈሱ ወደሚገፋፋው አቅጣጫ ይንቀሳቀሳል። ያለ ቁጥጥር ወይም ያለ ብልኅ ተቆጣጣሪነት እንዲሁ አይፈረጥጥም። ይሖዋ ይህን ድርጅት ወደፈለገው አቅጣጫ እንዲሄድ አልፈቀደለትም። ከዚህ ይልቅ የሱን መመሪያዎች ይከተላል። አንድ ላይ ሁሉም በኅብረት የይሖዋን ዓላማዎች ሙሉ በሙሉ ለማስፈጸም ወደፊት እየገሰገሱ ነው። በዚህ ተንቀሳቃሽ የይሖዋ ሰማያዊ ባለ አራት መንኮራኩሮች ሠረገላ የተገለጸው ሰማያዊ ድርጅት እንዴት አስደናቂ ነው! ከዚህ ጋር በመስማማት የይሖዋ ድርጅት ፍጹም ሚዛናዊ ለመሆኑ ባለ አራት ማዕዘን እንደሆነ ተደርጎ ተገልጿል።
ጠባቂ ወይም ጉበኛ ሆኖ መሾም
14. ነቢዩ ሕዝቅኤል የእነማን ምሳሌ ነው?
14 በነቢዩ በሕዝቅኤል የተመሰለውስ ምንድነው? ከታሪክ ማስረጃ እንደሚታየው በመንፈስ የተቀቡ የይሖዋ ምሥክሮች አካል ከሰማያዊው ሠረገላ ጋር እንደተባበሩ ግልጽ ሆኗል። በመሆኑም ሕዝቅኤል ከ1919 ጀምሮ የነበሩትን የይሖዋ ምሥክሮች ቅቡዓን ቀሪዎችን ያመለክታል። በመላው ዓለም ለይሖዋ ምሥክሮቹ እንዲሆኑ ሕይወትን ይሰጣቸው ዘንድ የአምላክ ሰማያዊ ድርጅት በዚያ ዓመት ከቅቡዓን ቀሪዎች ጋር በመንፈሳዊ ሁኔታ ተገናኝቷል። (ከራእይ 11:1-12 ጋር አወዳድር) እንደ አሁኑ ጊዜ ሁሉ ያን ጊዜም ያ ሠረገላ መሰል ድርጅት እየተንቀሳቀሰ ነበር። እንዲያውም መንኮራኩሮቹ አሁን ከምን ጊዜው በበለጠ ፍጥነት በመሽከርከር ላይ ናቸው። ይሖዋ በፍጥነት ወደፊት ይገሰግሳል!
15. የሰማያዊው ሠረገላ ጋላቢ ድምጽ ምን አለ? ሕዝቅኤልስ ምን ተልዕኮ ተሰጠው?
15 ሕዝቅኤል ሰማያዊ ሠረገላ እርሱ ወዳለበት ስፍራ መጥቶ ለምን እንደቆመ ለማወቅ ፈልጎ ነበር። በሠረገላው ላይ ከተቀመጠው ድምጽ በመጣለት ጊዜ ምክንያቱን ሊያውቅ ችሏል። ሕዝቅኤል በዚህ አስፈሪ ግርማ ተውጦ በግምባሩ ተደፋ። የሰማያዊ ሠረገላ ተቀማጭ ሲናገር ስሙ፦ “የሰው ልጅ ሆይ በእግርህ ቁም። እኔም እናገራለሁ።” (ሕዝቅኤል 2:1) ከዚያም ይሖዋ ሕዝቅኤልን ጠባቂ እንዲሆን አመጸኞቹን የእሥራኤል ቤት እንዲያስጠነቅቅ ላከው። በመለኮታዊ ስም ሳይቀር እንዲናገር ተላከ። ሕዝቅኤል የሚለው ስሙ “አምላክ ያጠነክራል” ማለት ነው። ስለዚህ የሕዝቅኤልን ቡድንም ለሕዝበ ክርስትና ጠባቂ ይሆኑ ዘንድ ያጠነከራቸውና ሾሞ የላካቸው አምላክ ነው።
16, 17. (ሀ) የሰማያዊው ሠረገላ ራእይ ሕዝቅኤልን የረዳው እንዴት ነበር? (ለ) በዘመናችን ስለ ሰማያዊው ሠረገላ የተገኘው ማስተዋል የሕዝቅኤልን ክፍልና እጅግ ብዙ ሰዎችን የነካቸው እንዴት ነው?
16 የሰማያዊው ሠረገላ ራእይ ስሜትን የሚመስጥና ሕዝቅኤልን የሚያስደነግጥ ነበር። ይሁን እንጂ መጪውን የኢየሩሳሌም ጥፋት ማስጠንቀቂያ እንዲናገር ለጠባቂነት ተልዕኮውም አዘጋጅቷል። በአሁኑ ጊዜም በጠባቂው ቡድን ላይ ተመሳሳይ ነገር ተፈጽሟል። በእንቅስቃሴ ላይ ያለውን የይሖዋን ሰማያዊ ሠረገላ ራእይ ማስተዋላቸው ቅቡአኑን በኃይል ነክቷቸዋል። ቪንድኬሺን ጥራዝ አንድ በተባለው መጽሐፍ ላይ እንደተገለጸው በ1931 ስለ ሕዝቅኤል ራእይ ይበልጥ አወቁ። በዚያን ጊዜ በተመስጦ ከመሞላታቸው የተነሣ ከጥቅምት 15, 1931 እትም ጀምሮ እስከ ነሐሴ 1, 1950 ድረስ መጠበቂያ ግንብ በፊት ለፊቱ ሽፋን ላይ የሕዝቅኤልን ራእይ ሰማያዊ ሠረገላ በስተቀኝ ባለው የላይኛው የመጽሔቱ ማዕዘን ላይ የአንድ ሰዓሊ ንድፍ ሥዕልን በተከታታይ ይዞ ይወጣ ነበር። ስለዚህ የሕዝቅኤል ቡድን የተሰጣቸውን ተልዕኮ አከናውነዋል። መለኮታዊውን ማስጠንቀቂያ በማሰማትም እንደጠባቂ ሆነው ሲያገለግሉ ቆይተዋል። በሰማያዊው ሠረገላ ላይ ከተቀመጠው ከይሖዋ በሕዝበ ክርስትና ላይ እሳታማ ጥፋት የሚመጣበት ጊዜ እንዲህ ቀርቦ አያውቅም!
17 በአሁኑ ጊዜ በግ መሰል የሆኑ “እጅግ ብዙ ሰዎች” ከቅቡዓን ቀሪዎች ጋር ተባብረዋል። (ራእይ 7:9) ሁለቱም ቡድኖች በአንድነት በሕዝበ ክርስትና በዚህ ዲያብሎሳዊ ጠቅላላ የነገሮች ሥርዓት ላይ የሚመጣውን የጥፋት ማስጠንቀቂያ እያሰሙ ነው። ያ የማስጠንቀቅ ሥራ በከፍተኛ ፍጥነት እየተካሄደ ነው፤ ራእይ 14:6, 7 እንደሚያመለክተው መላእክትም እየደገፉት ነው።
ከሰማያዊው ሠረገላ ጋር መጓዝ
18. የመላእክት እርዳታ እንዲቀጥልልን ከፈለግን ምን ማድረግ ያስፈልገናል? ለምንስ ነገር ንቁ መሆን አለብን?
18 ታዛዦቹ መላእክት የአምላክ ሰማያዊ ድርጅት በመሆን በኅብረት ይጓዛሉ፤ በዚያውም ላይ የይሖዋ ምድራዊ አገልጋዮች መለኮታዊውን የፍርድ ማስጠንቀቂያ ለማወጅ ተልዕኳቸውን በሚፈጽሙበት ጊዜ ይረዷቸዋል። የእነዚህን ኃያል የአምላክ መላእክታዊ አገልጋዮች የማያቋርጥ ጥበቃና አመራር ለማግኘት ከፈለግን እኛም ከምሳሌያዊው የመንኮራኩር መሽከርከር ጋር እርምጃችን በማስተካከል በሕብረት መራመድ አለብን። ከዚህም ሌላ ከይሖዋ ሰማያዊ ሠረገላ ጋር እኩል የሚራመደው የይሖዋ የሚታይ ድርጅት ክፍል በመሆን ለአምላክ መንፈስ አመራር በፍጥነት ምላሽ የምንሰጥ መሆን አለብን። (ከፊልጵስዩስ 2:13 ጋር አወዳድር) የይሖዋ ምሥክሮች ከሆንን ከሰማያዊው ሠረገላ ጋር በአንድ አቅጣጫ መራመድ አለብን። የሠረገላውን ዓላማ የሚቃረን ነገር ለማድረግ እንደማንፈልግ የተረጋገጠ ነው። ሠረገላው በዚህ አቅጣጫ መሄድ አለባችሁ ሲለን እኛም እሺ ብለን መከተል ያስፈልገናል። በዚህ መንገድ ጉባኤው አይከፋፈልም።—1 ቆሮንቶስ 1:10
19. (ሀ) የሰማያዊው ሠረገላ መንኮራኩሮች ዙሪያቸውን ዐይኖች እንዳሏቸው ሁሉ የይሖዋ ሕዝብ ለምን ነገር ንቁዎች መሆን አለባቸው? (ለ) በእነዚህ በሁከት በተናወጡ ጊዜያት ውስጥ አካሄዳችን እንዴት መሆን አለበት?
19 በአምላክ ሠረገላ መንኮራኩሮች ዙሪያ ያሉት ዓይኖች ንቃትን ያመለክታሉ። ሰማያዊው ድርጅት ንቁ እንደሆነ ሁሉ እኛም የይሖዋን ምድራዊ ድርጅት ለመደገፍ ነቅተን መጠባበቅ አለብን። በጉባኤ ደረጃ ያንን ድጋፍ የምናሳየው ከጉባኤው ሽማግሌዎች ጋር በመተባበር ነው። (ዕብራውያን 13:17) በእነዚህ ተነዋዋጭ ጊዜያት ክርስቲያኖች ከይሖዋ ድርጅት ጋር መጣበቅ አለባቸው። ለነገሮች የራሳችንን ፍቺ መስጠት አንፈልግም፤ ምክንያቱም እንደዚያ ካደረግን ከይሖዋ ሰማያዊ ሠረገላ ጋር አንራመድም ማለት ይሆናል። ሁልጊዜ ራሳችንን “ሰማያዊው ሠረገላ የሚጓዘው በየትኛው አቅጣጫ ነው?” ብለን እንጠይቅ። ከምድራዊው የይሖዋ ድርጅት ጋር በአንድ አቅጣጫ የምንጓዝ ከሆነ ከማይታየው ድርጀትም ጋር እየተጓዝን ነው ማለት ነው።
20. ሐዋርያው ጳውሎስ በፊልጵስዩስ 3:13-16 ላይ ምን ጥሩ ምክር ሰጥቷል?
20 ይህን በሚመለከት ጳውሎስ እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “ወንድሞች ሆይ እኔ ገና እንዳልያዝሁት እቆጥራለሁ። ነገር ግን አንድ ነገር አደርጋለሁ፤ በኋላዬ ያለውን እየረሳሁ በፊቴ ያለውን ለመያዝ እዘረጋለሁ። በክርስቶስ ኢየሱስ ከፍ ከፍ ያለውን የእግዚአብሔርን መጥራት ዋጋ እንዳገኝ [ወደ ግቡ (አዓት)] እፈጥናለሁ። እንግዲህ ፍጹማን [የጐለመስን (አዓት)] የሆንን ሁላችን ይህን እናስብ። በአንዳች ነገርም ልዩ አሳብ ቢኖራችሁ ይህን ደግሞ ይገልጥላችኋል። ሆኖም በደረስንበት በዚያ [በዚያው ልማድ (አዓት)] እንመላለስ።”—ፊልጵስዩስ 3:13-16
21. ምን ዓይነት ልማድ በመከተል ነው ከአምላክ ድርጅት ጋር በመንፈሣዊ ወደፊት መራመድ የሚቻለው?
21 እዚህ ላይ ‘ልማድ’ የሚለው ቃል ራሳችንን ልናወጣ የማንችልበት አሰልቺ የሆነ ተደጋጋሚ ሥራ ማለት አይደለም። የይሖዋ አገልጋዮች መንፈሳዊ መሻሻል የሚያደርጉበት መልካም ልማድ አላቸው። እየመላለሱ የሚያደርጉት ይህ ልማድ የግል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የማድረግ፣ በጉባኤ ስብሰባዎች የመገኘት፣ የመንግሥቱን ምሥራች አዘውትሮ የመስበክና የአምላክን ሰማያዊ ድርጅት ባሕርያት የማንጸባረቅ ልማድ ነው። እንደዚህ ያለ ልማድ የይሖዋን ሰማያዊ ሠረገላ መሰል ድርጅት አመራር እንዲከተሉ ያስችላቸዋል። በዚህ ሁኔታ ከቀጠልን ግባችንን እንጨብጣለን፤ ይህም በሰማይ የማይሞት የሕይወት ሽልማት ወይም በገነት ምድር ላይ የዘላለም ሕይወት ማግኘት ነው።
22. (ሀ) ቅቡዓን ቀሪዎችና የሌሎች በጎች ክፍል የሆኑት እጅግ ብዙ ሰዎች በኅብረት እንዲደራጁ ከተፈለገ ምን መደረግ ይኖርበታል? (ለ) ከይሖዋ ዐይኖች የማያመልጠው ምንድን ነው?
22 ዮሐንስ 10:16 እንደሚያመለክተው “ሌሎች በጐች” እና የሕዝቅኤል ቡድን አንድ ላይ ይደራጃሉ። እንግዲያው በይሖዋ ድርጅት ውስጥ ያሉ ሁሉ ከአምላክ ሰማያዊ ሠረገላ ጋር በኅብረት መራመድ ከፈለጉ በሕዝቅኤል ምዕራፍ 1 ላይ የተመዘገበው ራእይ ሙሉ ትርጉምና ቁም ነገር እንዲገባቸው ያስፈልጋል። የሠረገላው ራእይ ከሚታየውም ሆነ ከማይታየው የአምላክ ድርጅት ጋር በአንድ መሥመር መራመድ እንዳለብን እንድንገነዘብ ይረዳናል። ከዚህ ሌላ “ይሖዋ ልቡ በእርሱ ዘንድ ፍጹም የሆነውን ያጸና ዘንድ ዐይኖቹ በምድር ሁሉ” የሚመለከቱ መሆናቸውን አትርሱ። (2 ዜና 16:9) ይሖዋ የማያስተውለው ነገር በተለይ ደግሞ የጽንፈ ዓለም የበላይ ገዥነቱን ለማረጋገጥ ያለውን ዓላማውን በሚመለከት ሳያስተውለው የሚያልፍ አንዳችም ነገር የለም።
23. ሰማያዊው የይሖዋ ድርጅት ወደፊት ሲገሰግስ እኛስ ምን ማድረግ አለብን?
23 በእውነትም በአሁኑ ጊዜ የይሖዋ ሰማያዊ ሠረገላ ወደፊት በመገስገስ ላይ ነው። በቅርቡ ሁሉም ነገር ከሰረገላው ጋላቢ ክብር ጋር በሚስማማ መንገድ ክብር ይለብሳል። ይህም እሱ የጽንፈ ዓለሙ የበላይ ገዥ መሆኑን ያረጋግጣል። በታላቁ ዓለም አቀፍ የስብከት ሥራችን የይሖዋ ሱራፌሎች፣ ኪሩቤሎችና መላእክት እየረዱን ነው። እንግዲያውስ ከይሖዋ ሰማያዊ ድርጅት ጋር ወደፊት እንራመድ። ይሁን እንጂ ከዚያ ፈጣን ሰማያዊ ሠረገላ ጋር እኩል ልንራመድ የምንችለው እንዴት ነው?
እንዴት ትመልሳለህ?
◻ ሕዝቅኤል ያያቸው አራት ሕያዋን ፍጥረታት ለየትኞቹ ጠባዮች የቆሙ ናቸው?
◻ ሰማያዊው የይሖዋ ሠረገላ ምን ያመለክታል?
◻ በነቢዩ ሕዝቅኤል የተመሰሉት እነማን ናቸው?
◻ የሕዝቅኤል ክፍል የሆኑትና እጅግ ብዙ ሰዎች የይሖዋን ሰማያዊ ሠረገላ ምንነት መረዳታቸው እንዴት ነክቷቸዋል?