የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w91 3/15 ገጽ 13-18
  • ከይሖዋ ሰማያዊ ሠረገላ ጋር እኩል ተራመዱ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ከይሖዋ ሰማያዊ ሠረገላ ጋር እኩል ተራመዱ
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ተልእኮውን ተቀብሎ ፈጸመ
  • የአምላክን ቃላት ወደ ልብ ማስገባት
  • ሰዎቹ ግድየለሽ መሆናቸው ተስፋ አላስቆረጠውም
  • እኩል ለመራመድ መነሣሣት
  • እኩል መራመዳችሁን ቀጥሉ
  • የይሖዋ ሰማያዊ ሠረገላ ወደፊት ይገሰግሳል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
  • ይሖዋ አገልግሎታችንን እንድንፈጽም የሚረዳን እንዴት ነው?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2022
  • የሕዝቅኤል መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች—ክፍል 1
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2007
  • “አምላክ የገለጠልኝን ራእዮች ማየት ጀመርኩ”
    የይሖዋ ንጹሕ አምልኮ መልሶ ተቋቋመ!
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
w91 3/15 ገጽ 13-18

ከይሖዋ ሰማያዊ ሠረገላ ጋር እኩል ተራመዱ

“ቢሰሙ ወይም ባይሰሙ ቃሌን ትነግራቸዋለህ።”​—ሕዝቅኤል 2:7

1, 2. ሕዝቅኤል ምን ንጉሣዊ መጓጓዣ ተመለከተ? ምን ተብሎስ ተነገረው?

የይሖዋ ሰማያዊ ሠረገላ በአሁኑ ጊዜ በአገልጋዮቹ ፊት ቆሟል። በእምነት ዓይናቸው የሠራዊት ጌታቸውን የክብር መጓጓዝ ይመለከታሉ። ክብራማ ነው፤ አስፈሪና ግርማዊ ነው።

2 ያው ንጉሣዊ ሠረገላ ከ2,600 ዓመታት በፊት በራእይ በአምላክ ነቢይ በሕዝቅኤል ፊት ቆሞ ነበር። የአምላክ መንፈሳዊ ፍጡራን ሰማያዊ ድርጅት ከሆነው ከዚህ ዙፋን ተሸካሚ ሠረገላ ይሖዋ ለሕዝቅኤል ይህን አስደናቂ ትዕዛዝ አወጣ፦ “እነሱ ፊታቸው የተጨማተረ ልባቸው የደነደነ ልጆች ናቸው። እኔ ወደነሱ እልክሃለሁ። አንተም ከፍ ያለው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል በላቸው። እነሱ አመጸኛ ቤት ናቸውና ቢሰሙ ወይም ባይሰሙ ነቢይ በመካከላቸው እንዳለ ያውቃሉ።”​—ሕዝቅኤል 2:4, 5

3. በዚህ ዘመን ሕዝቅኤልን የሚመስል ማን ነው?

3 ሕዝቅኤል በመለኮታዊ እጅ ውስጥ እንደ አንድ ብቸኛ መሣሪያ በመሆን ተልዕኮውን በቁርጥ ሐሳብ ፈጽሟል። ዛሬም አምላክ የሚቆጣጠረው አንድ ብቸኛ ድርጅታዊ መሣሪያ አለው። የሕዝቅኤል ቡድን የሆኑት ቅቡዓን ቀሪዎች የ“ሌሎች በጐች” ክፍል በሆኑት “እጅግ ብዙ ሰዎች” እየታገዙ የመጨረሻውን ምሥክርነት በመስጠቱ ሥራ ግንባር ቀደም ናቸው። (ራእይ 7:9, 10፤ ዮሐንስ 10:16) ሁለቱም ቡድኖች አንድ ላይ መልካሙ እረኛ ኢየሱስ ክርስቶስ ከታላቁ የሠረገላው ተቀማጭ ከይሖዋ አምላክ የበላይ ገዥነት ሥር የሚመራቸው “አንድ መንጋ” ሆነዋል።

4, 5. የሚታየው የአምላክ ድርጅት ወደ ኅልውና የመጣው እንዴት ነው? ይህስ ድርጅት ከኢሳይያስ 60:22 ጋር የሚስማማ ምን ሁኔታ በራሱ ላይ ደርሷል?

4 በይሖዋ አመራር ሥር በመሆን ይህ ዓለም አቀፍ ድርጅት ከትንሽ አጀማመር ተነስቶ “አምላክን ፍሩ ክብርንም ስጡት የፍርዱ ሰዓት ደርሷልና” የሚለውን ድንጋጌ የሚያውጅ ኃያል ድርጅት እስከመሆን አድጓል። (ራእይ 14:7) ሕዝቅኤል ብድግ ብሎ ራሱን ነቢይ አድርጎ እንዳልሾመ ሁሉ የሚታየው የአምላክ ድርጅትም ራሱን አላቋቋመም ወይም አልሾመም። ከሰው ፈቃድ ወይም ጥረት የመነጨ አይደለም። መለኮታዊው የሠረገላ ተቀማጭ ነው ይህን ድርጅት ወደ ሕልውና ያመጣው። በአምላክ መንፈስ ኃይል ሰጪነትና በቅዱሳን መላዕክት እርዳታ የይሖዋ ሕዝቦች እጅግ አስደናቂ ዕድገት ስላገኙ “ታናሹ ለብርቱ ሕዝብ” ሆኗል።​—ኢሳይያስ 60:22

5 ከአራት ሚልዮን በላይ የሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥቱን መልዕክት በ212 አገሮች እያወጁ ነው። በልዩ ልዩ ክልሎችና በወረዳዎች መልክ በተደራጁ ከ63,000 በላይ በሆኑ ጉባኤዎች ተሰብስበዋል። በድርጅቱ ዋና መሥሪያ ቤት በአስተዳደር አካሉ ማዕከላዊ አመራር ሥር ሰፋፊ ቅርንጫፍ ቢሮዎችና የማተሚያ ፋብሪካዎች ሥራቸውን በማካሄድ ላይ ናቸው። ሁሉም እንደ አንድ ሰው በመሆን የምሥራቹን በመስበክ፣ ፍላጐት ያላቸውን ሰዎች በማስተማርና የመሰብሰቢያ በታዎችን በመሥራት ወደፊት እየተራመዱ ናቸው። አዎን የሚታየው የይሖዋ ድርጅት ከሰማያዊው ሠረገላና ከተቀማጩ ጋር እኩል በመራመድ ላይ ነው።

6. ከሚታየው የይሖዋ ድርጅት ጋር እኩል መራመድ ምን ምን ነገሮችን የሚያጠቃልል ነው?

6 ከይሖዋ ምሥክሮች አንዱ ከሆነክ ከሚታየው የአምላክ ድርጅት ጋር እኩል እየተራመድክ ነውን? ይህን ማድረግ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች የመካፈልና በአገልግሎት የተወሰነ ጊዜ የማሳለፍ ጉዳይ ብቻ አይደለም። በመሠረቱ እርምጃ ሲባል መሻሻልና መንፈሳዊ ዕድገት ማድረግ ማለት ነው። ይሆናል፣ ይቻላል የሚል ብሩህ አመለካከት መያዝ፣ ቅድሚያ ሊሰጣቸው ለሚገቡ ነገሮች ቅድሚያ መስጠትና በወቅቱ ካለው ሁኔታ ጋር እኩል መሄድ ማለት ነው። ከይሖዋ ሰማያዊ ሠረገላ ጋር እኩል የምንራመድ ከሆነ አኗኗራችን ከምናውጀው መልእክት ጋር የሚስማማ ይሆናል።

7. ሕዝቅኤል የአምላክ ነቢይ በመሆን ያደረጋቸውን ነገሮች መመርመር የሚገባን ለምንድን ነው?

7 እኩል በመራመድ ረገድ ዘመናዊ የይሖዋ አገልጋዮች ከሕዝቅኤል ምሳሌ ብዙ ትምህርት ሊያገኙ ይችላሉ። ሕዝቅኤል ነቢይ ሆኖ የተሾመው በራሱ በይሖዋ ቢሆንም ሰብዓዊ ስሜቶች እንዲሁም የሚያሳስቡትና የሚያስፈልጉት ነገሮች ነበሩት። ለምሳሌ ገና በቅርብ ያገባ ወጣት ሰው ሆኖ ሳለ ሚስቱን በሞት በማጣቱ ኀዘን ደርሶበታል። ሆኖም የይሖዋ ነቢይ ሆኖ እንዲሠራ የተሰጠውን ተልዕኮ አልዘነጋም። በሌሎች ነገሮችም ሕዝቅኤል ሕይወቱን እንዴት እንደመራ ስንመለከት ከሚታየው የአምላክ ድርጅት ጋር ጐን ለጐን ለመራመድ ራሳችንን ልናጠናክር እንችላለን። ይህም ከማይታየው ድርጅቱም ጋር ጐን ለጐን እንድንራመድ ያስችለናል።

ተልእኮውን ተቀብሎ ፈጸመ

8. ሕዝቅኤል በተሰጠው ተልዕኮ በኩል ምን ጥሩ ምሳሌ አሳይቷል?

8 ተልእኮውን በመቀበልና በመፈጸም ሕዝቅኤል ጥሩ ምሳሌ ትቶልናል። ይሁን እንጂ ይህን ተልእኮ ለመፈጸም ታዛዥነትና ድፍረት አስፈልጐታል። ምክንያቱም እንዲህ እናነባለን፦ “አንተ የሰው ልጅ ሆይ ኩርንችትና እሾህ ከአንተ ጋር ቢኖሩም አንተም በጊንጦች መካከል ብትቀመጥም አትፍራቸው። ቃላቸውንም አትፍራ። አንተ ቃላቸውን አትፍራ ከፊታቸውም የተነሣ አትደንግጥ። እነርሱ አመጸኛ ቤት ናቸውና። እነርሱ አመጸኛ ቤት ናቸውና ቢሰሙ ወይም ባይሰሙ ቃሌን ትነግራቸዋለህ። አንተ ግን የሰው ልጅ ሆይ የምነግርህን ስማ። እንደዚያ እንደ አመጸኛው ቤት አመጸኛ አትሁን።”​—ሕዝቅኤል 2:6-8

9. ሕዝቅኤል ከደም ዕዳ ነጻ መሆን የሚችለው ምን በማድረግ ብቻ ነው?

9 ሕዝቅኤል ተልእኮውን እንዲፈጽም ሁልጊዜ ጉትጐታ የሚያስፈልገው ዓይነት ግድየለሽ ወይም ፈሪ መሆን አልነበረበትም። ከደም ተጠያቂነት ነጻ ለመሆን የሚለው በፈቃደኝነትና በድፍረት የይሖዋን ቃል ከተናገረ ብቻ ነበር። እንዲህ ተብሎ ተነግሮታል፦ “ነገር ግን አንተ ኃጢአተኛውን ብታስጠነቅቅ እርሱም ከኃጢአቱና ከክፉ መንገዱ ባይመለስ በኃጢአቱ ይሞታል፤ አንተ ግን ነፍስህን አድነሃል።”​—ሕዝቅኤል 3:19

10. የሕዝቅኤሉ ቡድን ልክ እንደ ሕዝቅኤል ሆኖ የተገኘው እንዴት ነው?

10 ሕዝቅኤል እንዳደረገው ሁሉ የተቀቡ የሕዝቅኤል ክፍል የሆኑትም አምላክ የሰጣቸውን ተልእኮ ተቀብለው እየፈጸሙት ነው። የይሖዋ ምሥክሮች ከሆንን ሕይወታችንና የሌሎች ሕይወት የተመካው በታዛዥነታችን ላይ መሆኑን ማስታወስ ይኖርብናል። (1 ጢሞቴዎስ 4:15, 16) እያንዳንዱ ምሥክር ከይሖዋ ድርጅት ጋር ጐን ለጐን መራመድ ይኖርበታል። አምላክ ከሠረገላው ጋር በገመድ አሥሮ አይጐትተንም። ግድየለሽነትና ሁለት ልብ መሆን የሰረገላውን ነጂ ያቃልለዋል። ስለዚህ የሚታየው የይሖዋ ድርጅት መለኮታዊ ፍላጐቶችን የሕይወታችን እምብርት እንድናደርግ አጥብቆ ያሳስበናል። ለዚህ ጥብቅ ማሳሰቢያ የምንሰጠው የማያቋርጥ የእሺታ ምላሽ ከአምላክ ድርጅት ጋር እኩል ለመራመድ ያስችለናል፤ ቅዱስ አገልግሎታችንንም እንዲሁ በዘልማድ ብቻ የሚፈጸም ከመሆን አድኖ ከፍ ያደርግልናል። በእርግጥም የአምላክ ሕዝቦች በአጠቃላይ አስደናቂ የአምልኮ ፍቅርና ታማኝነት ያሳያሉ። በግል የእያንዳንዳችን ድርሻችን የእርምጃችንን ፍጥነት መጠበቅ ነው።

የአምላክን ቃላት ወደ ልብ ማስገባት

11. የአምላክን ቃላት በተመለከተ ሕዝቅኤል ምን ምሳሌ አሳይቷል?

11 ከዚህም በተጨማሪ ሕዝቅኤል የአምላክን ቃል በልብ ውስጥ በማኖር ረገድም መልካም ምሳሌ ትቶልናል። በታዘዘ ጊዜ አምላክ የሰጠውን የመጽሐፍ ጥቅልል በላ። “በአፌም ውስጥ እንደማር ጣፈጠ” በማለት ሕዝቅኤል ተናገረ። ጥቅልሉ “በኀዘን በዋይታና በልቅሶ” የተሞላ ቢሆንም የይሖዋን ወኪል የመሆን ክብሩን ስላደነቀ ለሕዝቅኤል ጣፋጭ ሆኖለታል። ለነቢዩ አምላክ የሰጠውን ሥራ መፈጸሙ ጣፋጭ ተሞክሮ ነበር። አምላክም እንዲህ ብሎ ነገረው፦ “የሰው ልጅ ሆይ የነገርኩህን ቃሌን ሁሉ በልብ ተቀበል። በጆሮህም ስማ።” (ሕዝቅኤል 2:9 እስከ 3:3, 10) እነዚያ ያያቸው ራእዮች አምላክ ሕዝቅኤልን ተካፋይ እንዲሆንበት የፈቀደለትን ነገር በከፍተኛ ሁኔታ እንዲገነዘብ አድርገውታል። ከይሖዋ ጋር የነበረውን ዝምድናም አጠንክረውለታል።

12. ሕዝቅኤል ነቢይ ሆኖ ባሳለፋቸው ከሃያ የሚበልጡ ዓመታት ምን አድርጓል?

12 ለሕዝቅኤል ለተለያዩ ዓላማዎችና ለተለያዩ ሕዝቦች የሚያገለግሉ ራእዮችና መልዕክቶች ተቀብሎ ነበር። በጥንቃቄ ማዳመጥና በተሰጠው መመሪያ መሠረት መናገርና መሥራት ነበረበት። ሃያ ሁለት ዓመታት በሚሆኑ የነቢይነት ዘመኖቹ ወቅት አዳዲስ መግለጫዎችና የአሠራር ሥርዓቶች ደረጃ በደረጃ ይገለጡለት ነበር። አንዳንዴ ሕዝቅኤል ልዩ አነጋገር ያለበት መልእክት ይናገር ነበር። በሌሎች ጊዜያት ኢየሩሳሌምን በሚመለከት ጡብ ፊት መተኛት በመሰሉ በሰውነት እንቅስቃሴ በሚታዩ ነገሮች ተጠቅሟል። (ሕዝቅኤል 4:1-8) በግል ጉዳዮቹ ረገድም ለምሳሌ ሚስቱ ስትሞት ያሳየው ሁኔታ መልእክት አዘል ነበር። (ሕዝቅኤል 24:15-19) ሁልጊዜ ተገቢውን መልእክት በማቅረብ፣ ተገቢውን እርምጃ በተገቢው ጊዜ በመውሰድም ወቅቱን የጠበቀ መሆን ነበረበት። ሕዝቅኤል ከይሖዋ ጋር ደረጃውን በመጠበቅ በሚሠራ ቅርብ ዝምድና ተሣሥሮ ነበር።

13. ከይሖዋ ጋር የተቀራረበ ግንኙነት መመሥረት የምንችለው እንዴት ነው?

13 እኛም በተመሳሳይ ከይሖዋ ጋር የምንሠራ በመሆን ከሱ ጋር የተቀራረበ ዝምድና መሥርተንና ያንንም ዝምድና ጠብቀን ለመኖር የአምላክን ቃል ወደ ልባችን ማስገባት አለብን። (1 ቆሮንቶስ 3:9) በዚህ ረገድ ከሚታየው የአምላክ ድርጅት ጋር ጐን ለጐን መራመድ በወቅቱ የሚቀርበውን መንፈሳዊ ምግብ በዚያው ጊዜ መከታተልን ይጠይቅብናል። (ሶፎንያስ 3:9) የሚወጡትን ጽሑፎች በወቅቱ የምንከታተል ከሆነ ብቻ ነው ለሠረገላው ነጂ መመሪያ በታዛዥነት ምላሽ ልንሰጥ የምንችለው።

14, 15. ከይሖዋ ድርጅት ፍጥነት ጋር እኩል ለመሄድ ምን ዓይነት ልማድ አስፈላጊ ነው?

14 ለዚያም ሲባል ጥሩ የሆነ የግል ጸሎት፣ የግል ጥናትና በቅዱሱ የምሥራቹ አገልግሎት የመካፈል ልማድ ያስፈልገናል። (ሮሜ 15:16) የአምላክን መልእክት የያዘውን ጥቅልል በመብላት ሕዝቅኤል የተወልንን ምሳሌ አስታውሱ። ሕዝቅኤል የበላው የጥቅልሉን ከፊል ሳይሆን መላውን ጥቅልል ነው። ለግል ስሜቱ የበለጠ ተስማሚ የሆኑ ቁራሾችን ወደመምረጥ አላዘነበለም። እኛም በተመሳሳይ የግል የመጽሐፍ ቅዱስና የክርስቲያናዊ ጽሑፎች ጥናታችን በየጊዜው ከሚቀርበው መንፈሳዊ ምግብ ጋር እኩል ለመራመድ እንዲያስችል ታስቦ መደረግ አለበት። በመንፈሳዊ ማዕድ ላይ የቀረበልንን ሁሉ ጥልቅ የሆኑትን እውነቶች ጭምር መመገብ አለብን።

15 የጠንካራውን ምግብ ትርጉም ለማግኘት ጸሎት የታከለበት ጥረት እናደርጋለንን? “ወተት የሚጋት ሁሉ ሕፃን ስለሆነ የጽድቅን ቃል አያውቅምና ጠንካራ ምግብ ግን መልካሙንና ክፉውን ለመለየት በሥራቸው የለመደ ልቡና ላላቸው ለፍጹማን (ለጐለመሱ) ሰዎች ነው” የሚል ሐሳብ ስለምናነብ በየወቅቱ ከሚወጣው ትምህርት ጋር እኩል ለመራመድ ዕውቀታችንና ማስተዋላችን ከመሠረታዊ ትምህርቶች አልፎ መሄድ ይኖርበታል። (ዕብራውያን 5:13, 14) አዎን መንፈሳዊ መሻሻል ማድረግ ከአምላክ ድርጅት ጋር ጐን ለጐን ለመራመድ እጅግ አስፈላጊ ነው።

ሰዎቹ ግድየለሽ መሆናቸው ተስፋ አላስቆረጠውም

16, 17. ሕዝቅኤል የሕዝቡን ግድየለሽነት፣ ፌዝና እምቢ ባይነት እንዴት ተቋቋመ?

16 ሕዝቅኤል ግድየለሽነት ወይም ፌዝ ቢያጋጥመውም ለተስፋ መቁረጥ ቦታ ሳይሰጥ ታዛዥ በመሆንም መልካም ምሳሌ ትቶልናል። እኛም በተመሳሳይ ከንጹሑ ልሣን ዕድገት ጋር ጐን ለጐን በመጓዝ የንጉሣዊው ሠረገላ ነጂ ከሚያደርገው ወቅታዊ አመራር ጋር እንራመዳለን። በዚህ መንገድም እርሱ የሚሰጠንን ትእዛዞች ለመስማትና ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል ሁኔታ ይኖረናል። የይሖዋን የፍርድ መልእክት በምንነግራቸው ሰዎች ግድ የለሽነት ስሜት ወይም ፌዝ ላለመበገርም ጥንካሬ ይኖረናል። በሕዝቅኤል ላይ እንደደረሰው አሁንም አንዳንድ ሰዎች ግንባረ ጠንካራና ልበ ደንዳና በመሆን ተቃውሞአቸውን በተግባር እንደሚያሳዩ አምላክ አስቀድሞ አስጠንቅቋል። ሌሎች ደግሞ ይሖዋን ማዳመጥ ስለማይፈልጉ እኛንም አይሰሙም። (ሕዝቅኤል 3:7-9) ገና ሌሎች ደግሞ ሕዝቅኤል 33:31, 32 እንደሚገልጸው ግብዞች ይሆናሉ፦ “ሕዝብ እንደሚመጣ ወዳንተ ይመጣሉ። እንደ ሕዝቤም በፊትህ ይቀመጣሉ። ቃልህንም ይሰማሉ። ነገር ግን አያደርጉትም በአፋቸው ብዙ ፍቅር ይገልጣሉ፤ ልባቸው ግን ስስታቸውን ትከተላለች። እነሆ አንተ መልካም ድምጽ እንዳለው እንደሚወደድ መዝሙር ማለፊያም አድርጎ በገና እንደሚጫወት ሰው ሆንህላቸው።”

17 ውጤቱስ ምን ይሆናል? ቁጥር 33 በመጨመር እንዲህ ይላል፦ “እነሆ ይህ ይመጣል። በመጣም ጊዜ እነርሱ ነቢይ በመካከላቸው እንደነበረ ያውቃሉ።” እነዚህ ቃላት ሕዝቅኤል ከሕዝቡ የእሺታ ምላሽ በማጣቱ ተስፋ እንዳልቆረጠ ያሳያሉ። የሌሎች ግድየለሽነት እሱንም ግድየለሽ አላደረገውም። ሰዎቹ ይስሙም አይስሙ አምላክን ታዞ ተልእኮውን ፈጽሟል።

18. ራስህን ምን ምን እያልክ ልትጠይቅ ትችላለህ?

18 የሚታየው የይሖዋ ድርጅት በአሁኑ ጊዜ ሁሉም ሰዎች አምላክን እንዲፈሩና ክብርን እንዲሰጡት የሚያሳስበውን አዋጁን እያጠናከረው መጥቷል። ታዲያ አንተስ የመንግሥቱን ምሥክርነት ለመስጠት የማያወላውል አቋም በመውሰድህና በአኗኗርህ ንጹሕ ሥነ ምግባር ጠባቂ በመሆንህ ስትነቀፍ በአቋምህ ትጸናለህን? ደም ባለመውሰድህ፣ ብሔራዊ አርማዎችን ባለማምለክህ ወይም ዓለማዊ ክብረ በዓሎችን ባለማክበርህ የተቃውሞ ዒላማ ስትሆኑ ጸንተህ ትቆማለህን?​—ማቴዎስ 5:11, 12፤ 1 ጴጥሮስ 4:4, 5

19. መመሪያዎችን በተመለከተ ከሰማያዊው የይሖዋ ሠረገላ ጋር እኩል ለመራመድ ከፈለግን ምን እናደርጋለን?

19 ይህ አካሄድ ቀላል ባይሆንም እስከ መጨረሻው የሚጸኑት ይድናሉ። (ማቴዎስ 24:13) ከይሖዋ እርዳታ ጋር የዓለም ሰዎች እንደነሱ እንዲያደርጉንና ከይሖዋ ሰማያዊ ሠረገላ ጋር ከመራመድ እንዲያስተዉን አንፈቅድላቸውም። (ሕዝቅኤል 2:8፤ ሮሜ 12:21) ከሠረገላ መሰሉ መላእክታዊ ድርጅት ጋር ጐን ለጐን እየተራመድን ከሆነ በሚታየው የአምላክ ድርጅት አማካኝነት የሚደርሱንን መመሪያዎችና ትእዛዞች በፍጥነት እንከተላለን። በእምነታችን ላይ፣ የሕይወትን ቃል አጥብቀን መያዛችንን እንድንተውና ዓይኖቻችንን በንጉሣዊው ሰማያዊ ሠረገላ ነጂ ላይ ባተኮረ መንፈሳዊ እውነታዎች ላይ እንዳናሳርፍ የሚቃጡብንን ጥቃቶች ለመቋቋም የሚያስፈልጉንን ነገሮች ሁሉ ይሖዋ ያቀርብልናል።

እኩል ለመራመድ መነሣሣት

20. የአረማመድ ፍጥነታችንን እንዳንቀንስ የሚረዱን ሕዝቅኤል የጻፋቸው አንዳንድ ነገሮች ምንድን ናቸው?

20 የሕዝቅኤል ራእዮች በእርምጃችን ወደኋላ እንዳንቀር ሊያነሣሡን ይገባል። እሱ በእሥራኤል ላይ ሊመጣ የነበረውን የአምላክ ፍርድ ማወጅ ብቻ ሳይሆን እሥራኤላውያን ወደ አገራቸው ተመልሰው ነገሮች ወደ ቀድሞ ሁኔታቸው እንደሚመለሱ የሚያመለክቱ ትንቢቶችን መዝግቧል። ሕዝቅኤል የተወሰነው ጊዜ ሲደርስ በይሖዋ ዙፋን ላይ ስለሚገዛው ሕጋዊ ባለ መብትም አመልክቷል። (ሕዝቅኤል 21:27) ያ ንጉሣዊ ባሪያ “ዳዊት” የአምላክን ሕዝቦች እንደገና አሰባስቦ እረኛቸው ይሆናል። (ሕዝቅኤል 34:23, 24) በማጐጉ ጐግ ጥቃት ቢደርስባቸውም አምላክ ይታደጋቸዋል፤ ጠላቶቹ ወደ ጥፋት በሚሄዱበት ሰዓት “ይሖዋን ለማወቅ” ይገደዳሉ። (ሕዝቅኤል 38:8-12፤ 39:4, 7) ከዚያ ወዲያ የአምላክ አገልጋዮች በመንፈሳዊ ቤተመቅደስ ውስጥ በሚከናወን የንጹሕ አምልኮ ሥርዓት ፍጻሜ የሌለው ሕይወት ያገኛሉ። ከመቅደሱ ወጥቶ የሚፈስስ የሕይወት ውሃ የምግብና የፈውስ ምንጭ ይሆናል፤ የመሬት ውርሻም በማግኘት ይባረካሉ።​—ሕዝቅኤል 40:2፤ 47:9, 12, 21

21. በዚህ ዘመን ያሉት የይሖዋ ምሥክሮች የሥራ ድርሻ፣ ከሕዝቅኤል ሥራ የሚበልጠው ለምንድን ነው?

21 ሕዝቅኤል እነዚያን ትንቢቶች ሲመዘግብ እንዴት በደስታ ተውጦ መሆን አለበት! ሆኖም የዘመናዊ የይሖዋ ምሥክሮች የሚያከናውኑት ሥራ የበለጠ ነው። ከእነዚያ የሕዝቅኤል ትንቢቶች አንዳንዶቹ እየተፈጸሙ ባሉበት ዘመን እንኖራለን። እንዲያውም በአንዳንዶቹ ትንቢቶች አፈጻጸም ላይ ንቁ ተሳትፎ እናደርጋለን። እኛ በግለሰብ ደረጃ ሕጋዊ ባለ መብቱ ኢየሱስ አሁን በመግዛት ላይ እንዳለ እንደምናምን ባኗኗራችን እናሳያለንን? ይሖዋ በቅርቡ ራሱን እንደሚቀድስና ከድርጅቱ ጋር ጐን ለጎን የሚራመዱትን አድኖ ወደ ራሱ አዲስ ዓለም እንደሚያስገባቸው በግላችን እናምናለንን? (2 ጴጥሮስ 3:13) የእምነት ሥራዎች የታከሉበት እንዲህ ዓይነቱ እምነት በእርግጥም ከይሖዋ ሰማያዊ ሠረገላ ጋር እኩል እየተጓዝን መሆናችንን ያሳያል።

እኩል መራመዳችሁን ቀጥሉ

22. ግልጽ የሆነ መንፈሣዊ እይታ ይዘን ለመኖር እንቅፋቶችን ለማስወገድ ምን ሊደረግ ይችላል?

22 “በእጃችን እርፍ ይዘን” ይህ ዓለም ሊሰጠን ወደሚችል ወደ ማንኛውም ነገር በናፍቆት ወደኋላ መመልከት የለብንም። (ሉቃስ 9:62፤ 17:32፤ ቲቶ 2:11-13) ስለዚህ ማንኛውም በምድር ላይ መዝገብ የመሰብሰብ ዝንባሌ እንግታና የዐይናችንን እይታ ሳናወሳስብ በመንግሥቱ ላይ አተኩሮ እንዲኖር እናድርግ። (ማቴዎስ 6:19-22, 33) አኗኗራችንን ቀላል ማድረግ፣ በተቻለ መጠን ሥጋዊ ሸክማችን ከላያችን ማውረድ ከይሖዋ ድርጅት ጋር አብረን እንድንራመድ ይረዳናል። (ዕብራውያን 12:1-3) ሐሳብ የሚከፋፍሉ ወይም የሚበታትኑ ነገሮች ሰማያዊው ሠረገላና ነጂው ቁልጭ ብለው እንዳይታዩን እይታችንን ያደበዝዝብናል። በእርሱ እርዳታ ግን እንደ ሕዝቅኤል ብሩህ የሆነ መንፈሳዊ አመለካከትን ይዘን መኖር እንችላለን።

23. ታማኝ ምሥክሮች አዲሶችን ለመርዳት ምን ሊያደርጉ ይችላሉ?

23 በይሖዋ ምሥክርነታችን ካሉብን ኃላፊነቶች አንዱ ብዙ አዳዲስ ሰዎችን ከአምላክ ሰማያዊ ሠረገላ ጋር እኩል እንዲራመዱ መርዳትን ይጨምራል። በ1990 አሥር ሚልዮን የሚሆኑ ሰዎች በኢየሱስ ክርስቶስ ሞት መታሰቢያ በዓል ላይ ተገኝተዋል። ከእነዚህ ውስጥ ብዙዎቹ ግለሰቦች በጥቂቶቹ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች የሚገኙ ሊሆን ይችላል፤ ሆኖም ከሚታየው የይሖዋ ድርጅት ጋር ወደፊት የመግፋትን አስፈላጊነት መገንዘብ ያስፈልጋቸዋል። ታማኝ ምሥክሮች በመሆን በምናሳየው መንፈስና በምንሰጠው ማበረታቻ ልንረዳቸው እንችላለን።

24. በእነዚህ ማጠቃለያ ጊዜያት ምን ማድረግ አለብን?

24 አሁን ያለንባቸው ጊዜያት የማክተሚያ ጊዜያት ናቸው። በእምነት ዓይን ሰማያዊው ሠረገላ ከፊታችን ሲቆም አይተናል። ክብራማው የሠረገላ ነጂ በመጨረሻው ይሖዋ ማን መሆኑን አሕዛብ ያውቁ ዘንድ ለእነርሱ የመስበክን ተልእኮ ለሚታየው ድርጅቱ ሰጥቷል። (ሕዝቅኤል 39:7) ከሰማያዊው የይሖዋ ሠረገላ ጋር አብራችሁ በመራመድ የይሖዋን የበላይ ገዥነት ለማረጋገጥና ቅዱስ ስሙን ለማስቀደስ በሚያስችለው በዚህ ታላቅ አጋጣሚ ተጠቀሙበት።

እንዴት ትመልሳለህ?

◻ ሕዝቅኤል በተሰጠው ተልዕኮ ረገድ ምን ምሳሌ ትቶልናል?

◻ ከአምላክ ድርጅት ጋር እኩል መራመድ ምን ማለት ነው?

◻ ሕዝቅኤል የይሖዋን ቃላት የተመለከተው እንዴት ነው?

◻ የሰዎችን ግድየለሽነት በመቋቋም ረገድ የሕዝቅኤልን ምሳሌ ለመከተል የምንችለው እንዴት ነው?

◻ የይሖዋ አገልጋዮች ከሰማያዊ ሠረገላው ጋር እኩል ለመራመድ ሊገፋፋቸው የሚገባው ምንድን ነው?

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከሰማያዊው የይሖዋ ሠረገላ ጋር እኩል ለመራመድ ምን ያስፈልጋል?

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሕዝቅኤል ከአምላክ የተሰጡትን መብቶች አድንቋል። አንተስ?

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ