የዓለም ሰላም ከአድማስ እየታየ ነውን?
በታሪክ ዘመናት ሁሉ ቢያንስ አንድ ዓይነት የሰላም ዕቅድ ወይም የሰላም አዋጅ ያልነበረበት ጊዜ የለም። ይሁን እንጂ ይህን ሁሉ ከንቱ የሚያደርጉ የዚያኑ ያህል ጦርነቶች ተደርገዋል። የሰላም ስምምነቶችንና አዋጆች ቢኖሩም አብዛኞቹ ሰዎች በእነዚህ ላይ ብዙ ትምክህት መጣል እንደማይገባቸው ተገንዝበዋል።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት ግን ብዙ ተመልካቾችና የዜና አጠናቃሪዎች አንድ ለየት ያለ ነገር እየተከናወነ እንዳለ እየተሰማቸው መጥቷል። ምንም እንኳ የአገር ውስጥ ችግሮች ቢኖሩም በአሁኑ ጊዜ ለዓለም ሰላም መድረኩ ሊዘጋጅ እንደሚችል ገልጸዋል። የስቶክሆልሙ ዓለም አቀፍ የሰላም ተቋም “ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ካሉት ከሌሎቹ ዓመታት ሁሉ ግጭቶችን በሰላም ለመፍታት ከአሁኑ የተሻለ መሠረት ያለው ተስፋ ኖሮ አያውቅም” ብሏል። አንድ ታዋቂ ጋዜጠኛ በምሥራቅ አውሮፓ በመከናወን ላይ ያሉትን በፍጥነት የሚጓዙ ክንውኖች በመመልከት እንዲህ ብሎ ለመናገር ተገፋፍቷል፦ “ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ በምድር ላይ ሰላምን ለማስፈን ሁኔታው የአሁኑን ያህል አመቺ ሆኖ አያውቅም።” ዘ ቡለቲን ኦፍ ዘ አቶሚክ ሳይንቲስትስ የተባለው ጋዜጣም ይህንን ስሜት አንፀባርቋል። ለእኩለ ሌሊት ሦስት ደቂቃ እንደቀረው ያመለክት የነበረውን ዝነኛውን የእልቂት ቀን መተንበያ ሰዓቱን ተቋሙ በ1988 ለእኩለ ሌሊት ስድስት ደቂቃ እንደቀረው እንዲያመለክት ወደኋላ መልሶት ነበር፤ ከዚያም ሚያዝያ 1990 ላይ አሁንም እንደገና ወደኋላ በመመለስ ለዕኩለ ሌሊት አሥር ጉዳይ ላይ አድርጎታል።
ይህ ሁሉ በመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት ከመፈንዳቱ በፊት ስለ ወደፊቱ ጊዜ የብሩህ ተስፋንና የእፎይታን ስሜት የሚቀሰቅስ ሆኖ ነበር። ይሁን እንጂ ከዚያም በኋላ ቢሆን አንዳንድ ሰዎች ቀዝቃዛው ጦርነትና በኃያላን መንግሥታት መካከል የሚደረገው የመሣሪያ እሽቅድምድም አክትሟል እያሉ እየተናገሩ ነው። አንዳንዶችም መንግሥታት ወታደራዊ ወጪ በመቀነሱ ምክንያት የተገኘውን ትርፍ ገንዘብ ምን ቢደረግበት እንደሚሻል እያሰቡበት ነው። ታዲያ ዘላቂ ሰላም በእርግጥ የሚገኝበት ጊዜ አሁን መጥቶ ይሆን እንዴ? ብሔራትስ በእውነት “ሰይፋቸውን ማረሻ ጦራቸውንም ማጭድ ለማድረግ” መቀጥቀጥን እየተማሩ ይሆንን? (ኢሳይያስ 2:4) ማስረጃዎቹ የሚያሳዩት ምንድን ነው?
የተረሱት ጦርነቶች
“የቀዝቃዛው ጦርነት ማብቃትና በምሥራቁና በምዕራቡ መካከል ያለው ግንኙነት መሻሻል አንዳንዶች ሰላም የዘመናችን ሥርዓት ነው ብለው እንዲያምኑ አሳስቷቸዋል” በማለት ዘ ኤኮኖሚስት የተባለው የለንደን ጋዜጣ ገልጿል። ‘ሁኔታው ግን እንደዚያ አይደለም። አንድ ትልቅ የውጥረት ምንጭ ቢወገድም፤ ዓለም አሁንም ብዙ ትንንሽ ውጥረቶች ይቀሯታል።’ እነዚህ “ትንንሽ” ውጥረቶች ወይም ግጭቶች ምንድን ናቸው?
ሌንስ የሰላም ጥናት ላቦራቶሪ የተባለ በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የሚገኝ አንድ ራሱን የቻለ የምርምር ድርጅት ከመስከረም 1990 ወዲህ እንኳ በዓለም ዙሪያ ቢያንስ 15 ጦርነቶች በመካሄድ ላይ ነበሩ ሲል ዘግቧል። ዘገባው እስከዚያን ጊዜ ድረስ በየዓመቱ ቢያንስ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች የተገደሉባቸውን ጦርነቶች ብቻ የሚቆጥር በመሆኑ ይህ ሪፖርት ኢራቅ ኩዌትን መውረርዋን አይጨምርም። ከእነዚህ ጦርነቶች ውስጥ አንዳንዶቹ ለ20 ወይም ከዚያ ለሚበልጡ ዓመታት ሲካሄዱ የቆዩ ናቸው። እነዚህም አንድ ላይ ተጠቃለው 2,900,000 ሕይወት አጥፍተዋል። ከሞቱትም አብዛኞቹ ሲቪሎች ናቸው። ይህ ቁጥር በቅርብ ዓመታት እንደ ኡጋንዳና አፍጋኒስታን በመሳሰሉት አገሮች ውስጥ እንዲሁም በኢራንና በኢራቅ መካከል ተደርገው ባበቁበት ደም አፋሳሽ ጦርነቶች የተገደሉትን ሰዎች አይጨምርም።
ዓለም ሰላም ሆናለች እየተባለ በሚነገርበት ጊዜ ወደ ሦስት ሚልዮን የሚጠጉ ሰዎች ተገድለዋል! ይህ ራሱ በጣም አሳዛኝ ነገር ነው። ይሁን እንጂ ከሁሉም በላይ አሳዛኝ የሆነው ከእነዚህ ውስጥ አብዛኞቹ ጦርነቶች የተካሄዱት ሌላው ዓለም ልብ ሳይላቸውና አሳዛኝነታቸውን ሳያውቅ መሆኑ ነው። እነዚህ የተረሱ ጦርነቶች ተብለው ሊጠሩ ይችላሉ፤ ምክንያቱም አብዛኞቹ የመንግሥት ግልበጣዎች፣ የእርስ በርስ ጦርነቶችና አብዮቶች የሚደረጉት በተለያዩ ያላደጉ አገሮች ውስጥ ነው። በሃብታምና በኢንዱስትሪ በበለፀጉ አገሮች ውስጥ ለሚገኙ ለአብዛኞቹ ሰዎች በሱዳን ውስጥ ግማሽ ሚልዮን የሚሆኑ ሰዎች መገደላቸው፣ ወይም በአንጎላ የሚልዮን ሲሦ የሚሆኑ ሰዎች ማለቃቸው ብዙም ትኩረት የማይሰጡት ጉዳይ ነው። በበለጸጉት አገሮች መካከል ጦርነት ስላልተደረገ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ዓለም አይታው በማታውቀው የሰላም ዘመን ላይ ኖራለች ብለው የሚከራከሩም አሉ። ከፍተኛ ውጥረት የነበረባቸው ጊዜያት ቢኖሩና የመሣሪያ ክምችት ቢደረግም ኃያላን መንግሥታት እርስ በርስ ውጊያ አላካሄዱም።
ለሰላም ተስፋ አለን?
ዓለም አቀፍ የኑክሌር ጦርነት አለመደረጉ እንደ ሰላም ተደርጎ ከተቆጠረ የዓለም መንግሥታት ለሰላም ያደረጉት ጥረት ተሳክቶላቸዋል ብሎ መከራከር ይቻል ነበር። ኃያላን መንግሥታትን እስከ አሁን ድረስ ጦርነት ከማድረግ የገታቸው እርስ በርሳቸው ላለመጠፋፋት ያወጡት የጋራ ፖሊሲ ነው። ይሁን እንጂ ይህ በእርግጥ ሰላም ነውን? ሰዎች ድንገተኛና አጠቃላይ የሆነ እልቂት ሊደርስብን ይችላል እያሉ በፍርሃት እየኖሩ ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የብዙ ሰዎች ሕይወት ተበላሽቶ፣ መተዳደሪያቸውን ማግኘት ተስኗቸውና ትርጉም ያለውና የተሳካ ኑሮ ለመኖር ያላቸው ተስፋም በትልልቆቹም ይሁን በትንንሾቹ ጦርነቶች ተሟጦ እያለ እንዴት ስለ ሰላም ለመናገር እንችላለን?
የኖቤል ሽልማት አሸናፊ የነበሩት ኤሊ ዋይሰል አንድ ጊዜ እንዲህ በማለት ጽፈው ነበር፡- “ልናስታውሰው ከማንችለው ከጥንት ዘመን ጀምረው ሰዎች ስለ ሰላም ሲናገሩ ቆይተዋል። ሆኖም አላገኙትም። የጎደለን ነገር ተሞክሮ ነውን? ስለ ሰላም እያወራን ጦርነት እናደርጋለን። እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ ጦርነትን የምናደርገው በሰላም ስም ነው። . . . ጦርነት ከታሪክ ጋር በጣም የተሳሰረ ነገር ስለሆነ ለመቼውም ሊጠፋ አይችልም።”
በቅርቡ በመካከለኛው ምሥራቅ የተከሰተው ጦርነት የሰላምን ሕልም እንደገና አጨልሞታል። ችግሩ የሰው ልጅ ሰላምን ከተሳሳተ ምንጭ ለማግኘት መሞከሩ ይሆን?
[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
“ይህ በምድር ላይ ያለ የሰዎች ትውልድ በሥልጣኔ ታሪክ ውስጥ ሊቀለበስ የማይችል የሰላም ጊዜ ሲመጣ በዓይኑ ይመለከት ይሆናል።”—የሶቪየት ፕሬዝዳንት ሚካኤል ጎርባቼቭ፣ ግንቦት 1990 በዋሽንግተን ዲ ሲ ዩ ኤስ ኤ በተደረገው ልዩ ስብሰባ ላይ የተናገሩት ቃል
[ምንጭ]
UPI/Bettmann Newsphotos
[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
“ከፊታችን አዲስ የነፃነት ዓለም እየመጣ ነው . . . ሰላም የሚጸናበት፣ ንግድ ውስጥ ኅሊና የሚገባበት፣ የሚቻል የሚመስለው ነገር ሁሉ የሚቻልበት ዓለም እየመጣ ነው።”—የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆርጅ ቡሽ ሐምሌ 1990 በሂውስተን ቴክሳስ ዩ ኤስ ኤ በተደረገው ልዩ የኢኮኖሚ ስብሰባ ላይ የተናገሩት ቃል
[ምንጭ]
UPI/Bettmann Newsphotos
“በአንድ ወቅት ሕዝቦችንና አስተሳሰቦችን አፍነው የነበሩት ግድግዳዎችን እየፈራረሱ ነው። አውሮፓውያን የራሳቸውን ዕድል በመወሰን ላይ ናቸው። ነፃነትንም መርጠዋል። የኢኮኖሚ ነፃነትን እየመረጡ ነው፤ ሰላምንም እየመረጡ ነው።”—ሐምሌ 1990 በለንደን ኢንግላንድ በተደረገ ልዩ ስብሰባ ላይ ኔቶ ያወጣው መግለጫ
[በገጽ 2 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
Cover photos U.S. Naval Observatory photo (stars); NASA photo (earth)