እውነተኛ ሰላም—ከየት ይገኛል?
“[ይሖዋ] እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ጦርነትን ይሽራል።”— መዝሙር 46:9
1. በኢሳይያስ ትንቢት ውስጥ ምን አስደናቂ የሰላም ተስፋ እናገኛለን?
“የጽድቅም ሥራ ሰላም፣ የጽድቅም ፍሬ ለዘላለም ጸጥታና መታመን ይሆናል። ሕዝቤም በሰላም ማደሪያ በታመነም ቤት በጸጥተኛ ማረፊያ ይቀመጣል።” (ኢሳይያስ 32:17, 18) እንዴት ያለ አስደሳች ተስፋ ነው! ይህ አምላክ ስለሚያመጣው እውነተኛ ሰላም የሚገልጽ ተስፋ ነው።
2, 3. እውነተኛ ሰላም ማለት ምን ማለት እንደሆነ ግለጽ።
2 ይሁንና እውነተኛ ሰላም ምንድን ነው? የጦርነት አለመኖር ማለት ብቻ ነውን? ወይም ብሔራት ድምፃቸውን አጥፍተው ለጦርነት ዝግጅት የሚያደርጉበት ጊዜ ነውን? እውነተኛ ሰላም የሕልም እንጀራ ነውን? ለእነዚህ ጥያቄዎች ትክክለኛ መልስ ማግኘት ይኖርብናል። በመጀመሪያ ደረጃ እውነተኛ ሰላም የሕልም እንጀራ አይደለም። አምላክ ስለ ሰላም የሰጠው ተስፋ ይህ ዓለም ሊገምተው ከሚችለው ከማንኛውም ነገር የላቀ ነው። (ኢሳይያስ 64:4) ለጥቂት ዓመታት ወይም አሥርተ ዓመታት ብቻ የሚቆይ ሰላም አይደለም። ለዘላለም የሚዘልቅ ሰላም ነው! ሰማይንና ምድርን፣ መላእክትንና የሰው ልጆችን በሙሉ የሚያቅፍ እንጂ የታደሉ ጥቂት ግለሰቦች ብቻ የሚያገኙት ሰላም አይደለም። ለሁሉም ብሔራት፣ ነገዶች፣ ቋንቋዎችና ዘሮች የሚዳረስ ሰላም ነው። በድንበር፣ በክልል ወይም እንቅፋት በሚሆኑ ሌሎች ነገሮች የሚገደብ ሰላም አይደለም።— መዝሙር 72:7, 8፤ ኢሳይያስ 48:18
3 እውነተኛ ሰላም ማለት እያንዳንዱን ቀን በሰላም ማሳለፍ ማለት ነው። በየዕለቱ ጠዋት ጠዋት ስትነሱ ጦርነት ይኖራል የሚል ሥጋት አያድርባችሁም፤ እናንተም ሆናችሁ ልጆቻችሁ ወይም የልጅ ልጆቻችሁ ወደፊት ስለሚያጋጥማችሁ ሁኔታ መጨነቅ አያስፈልጋችሁም ማለት ነው። የተሟላ የአእምሮ ሰላም ማግኘት ማለት ነው። (ቆላስይስ 3:15) የአምላክ ሰላም ማለት ወንጀል፣ ሁከት፣ የቤተሰብ መለያየት፣ መጠለያ የሌላቸው ሰዎች፣ በረሐብ አለንጋ የሚገረፉና በእርዛት የሚሠቃዩ ሰዎች አይኖሩም፤ ጭንቀትና ተስፋ መቁረጥም የተረሱ ነገሮች ይሆናሉ ማለት ነው። ከዚህም በላይ የአምላክ ሰላም ማለት በሽታ፣ ሕመም፣ ሐዘንና ሞት በሌለበት ዓለም ውስጥ መኖር ማለት ነው። (ራእይ 21:4) ይህ ለዘላለም እውነተኛ ሰላም አግኝቶ የመኖር እንዴት ያለ ታላቅ ተስፋ ነው! ሁላችንም የምንናፍቀው እንዲህ ያለውን ሰላምና ደስታ ለማግኘት አይደለምን? ልንጸልይለትና ለማግኘት ልንጣጣርለት የሚገባን ሰላም ይህ አይደለምን?
ያልተሳካው የሰው ልጅ ጥረት
4. ብሔራት ሰላም ለማምጣት ምን ጥረቶችን አድርገዋል? ውጤቱስ ምንድን ነው?
4 ሰዎችም ሆኑ ብሔራት ለበርካታ መቶ ዘመናት ስለ ሰላም ተናግረዋል፣ ስለ ሰላም ተከራክረዋል፣ በመቶ የሚቆጠሩ የሰላም ውሎችንም ተፈራርመዋል። ታዲያ ውጤቱ ምን ሆነ? ባለፉት 80 ዓመታት በብሔራት ወይም በቡድኖች መካከል ውጊያ ያልተደረገበት ጊዜ ኖሮ አያውቅም። ሰላም ከሰው ልጆች የራቀ መሆኑ ግልጽ ነው። ስለዚህ አሁን የሚነሳው ጥያቄ የሰው ልጅ ዓለም አቀፍ ሰላም ለማምጣት ያደረገው ጥረት በሙሉ ሳይሳካ የቀረው ለምንድን ነው? የሰው ልጅ ዘላቂ የሆነ እውነተኛ ሰላም ለማምጣት የማይችለውስ ለምንድን ነው? የሚል ነው።
5. የሰው ልጅ ለሰላም ያደረጋቸው ጥረቶች ሳይሳኩ የቀሩት ለምንድን ነው?
5 መልሱ ቀላል ነው፤ የሰው ልጅ እውነተኛውን ሰላም ከትክክለኛው ምንጭ ለማግኘት ጥረት አላደረገም። የሰው ልጆች በስግብግብነታቸውና በምኞቶቻቸው፣ በራሳቸው ድክመቶችና መጥፎ ባሕርያት፣ ለሥልጣንና ለዝና ባላቸው ጥማት ተሰናክለው የሚወድቁ ድርጅቶችን በሰይጣን ዲያብሎስ መሪነት አቋቁመዋል። የከፍተኛ ትምህርት ተቋሞቻቸው እንዲሁም ያቋቋሟቸው የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና የጥናትና ምርምር ተቋሞች ያስተማሯቸው ተጨማሪ ጭቆናና ጥፋት የሚያስከትል ነገር ብቻ ነው። የሰው ልጆች በምን ላይ እንዲያተኩሩ ተደርገዋል? ተስፋ ያደረጉትስ ማንን ነው?
6, 7. (ሀ) የቃል ኪዳኑ ማኅበር ያስመዘገበው ታሪክ ምንድን ነው? (ለ) የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትስ?
6 ወደ 1919 መለስ ብንል ብሔራት ዘላቂ ሰላም ያመጣል ብለው የተማመኑት በመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበር ላይ ነበር። ይህ ተስፋ ግን በ1935 የሙሶሎኒ ሠራዊት ኢትዮጵያን በወረረ ጊዜና በ1936 ደግሞ በስፔይን የእርስ በርስ ጦርነት በተነሣ ጊዜ ከመሠረቱ ተናጋ። በ1939 ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ሲፈነዳ የቃል ኪዳን ማኅበሩ ድምጥማጡ ጠፋ። ያን ያህል የተወራለት ሰላም 20 ዓመት እንኳን አልቆየም።
7 ስለ ተባበሩት መንግሥታት ድርጅትስ ምን ማለት ይቻላል? በመላው ምድር ላይ ዘላቂ ሰላም እንደሚያሰፍን ተጨባጭ ተስፋ ሰጥቷልን? በፍጹም። የተባበሩት መንግሥታት ከተቋቋመበት ከ1945 ወዲህ ከ150 የሚበልጡ ጦርነቶችና የትጥቅ ትግሎች ተካሂደዋል! ስለ ጦርነትና መንስዔው ጥናት የሚያደርጉት ካናዳዊው ግዌን ዳየር የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን እንደሚከተለው ሲሉ መግለጻቸው ምንም አያስገርምም:- “አዳኞች የአራዊት ደህንነት ጠባቂዎች የሆኑበት፣ የቅዱሳን ስብሰባ ሳይሆን ወሬ ብቻ የሚወራበት ተጨባጭ እርምጃ የማይወስድ ድርጅት ነው።”— ከኤርምያስ 6:14ና ከ8:15 ጋር አወዳድር።
8. ብሔራት ስለ ሰላም ቢለፍፉም ምን ሲያደርጉ ቆይተዋል? (ኢሳይያስ 59:8)
8 ብሔራት ስለ ሰላም ብዙ ቢለፍፉም የጦር መሣሪያዎችን መፈልሰፋቸውንና ማምረታቸውን አላቆሙም። ብዙውን ጊዜ የሰላም ጉባኤዎችን የሚያዘጋጁት የጦር መሣሪያዎችን በማምረት ረገድ በቀዳሚነት የሚጠቀሱ አገሮች ናቸው። በእነዚህ አገሮች ከመሣሪያ ንግድ የሚገኘው ጥቅም በጣም ከፍተኛ በመሆኑ በየዓመቱ 26,000 ሰላማዊ ሰዎችንና ሕፃናትን የሚገድሉትንና የአካል ጉዳተኛ የሚያደርጉትን ዲያብሎሳዊ ፈንጂዎች ጨምሮ በርካታ ቀሳፊ የጦር መሣሪያዎች ይመረታሉ። ለዚህ ሁሉ ምክንያቱ ስግብግብነትና ሙስና ነው። ዓለም አቀፉ የጦር መሣሪያ ንግድ ከጉቦ ጋር እጅና ጓንት ነው። አንዳንድ ፖለቲከኞች ጉቦ በመቀበል ራሳቸውን ያበለጽጋሉ።
9, 10. ዓለማዊ ጠበብት ጦርነቶችንና የሰው ልጅ ያደረጋቸውን ጥረቶች በተመለከተ ምን ነገር ተገንዝበዋል?
9 በታኅሣሥ ወር 1995 ፖላንዳዊው የፊዚክስ ሊቅና የሰላም ኖቤል ተሸላሚ፣ ጆሴፍ ሮትብላት ብሔራት የጦር መሣሪያ እሽቅድድማቸውን እንዲያቆሙ ተማጽነው ነበር። “[አዲስ የጦር መሣሪያ እሽቅድድም] እንዳይፈጠር ለማድረግ ብቸኛው መንገድ ጦርነትን ሙሉ በሙሉ ማጥፋት ነው” ብለው ነበር። እንዲህ ማድረግ የሚቻል ይመስልሃል? ከ1928 ወዲህ 62 ብሔራት በመካከላቸው የሚነሳውን አለመግባባት በጦርነት ላለመፍታት በመስማማት የኬሎግ ብሪያንድን ውል ፈርመዋል። ይሁን እንጂ ይህ ውል ከሰፈረበት ወረቀት የበለጠ ዋጋ እንደሌለው በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ተረጋግጧል።
10 ጦርነት በሰው ልጆች ታሪክ ጎዳና ላይ በተደጋጋሚ የሚያጋጥም ጋሬጣ መሆኑ አይካድም። ግዌን ዳየር እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “ጦርነት የሰው ልጅ ሕይወት ዋነኛ ገጽታ ሆኖ ከመኖሩም በላይ በዕድሜውም ቢሆን ከሰው ዘር ታሪክ ጋር እኩል ነው።” አዎን፣ በከፍተኛ አክብሮትና አድናቆት የሚታዩ የራሱ ወታደራዊ ጀግኖች፣ የራሱ ቋሚ ሠራዊት፣ የራሱ የጦር ሜዳ ጀብዱዎች፣ ተጋነው የሚታዩ የራሱ ወታደራዊ ማሠልጠኛዎችና የጦር መሣሪያ ክምችት ያልነበረው ሕዝብ ወይም ግዛት ኖሮ አያውቅም። ቢሆንም ይህ የኛ መቶ ዘመን ከማንኛውም ሌላ መቶ ዘመን ይበልጥ በአውዳሚነታቸውም ሆነ በሕይወት አጥፊነታቸው አቻ የማይገኝላቸው ጦርነቶች የተካሄዱበት ዘመን ሆኗል።
11. የዓለም መሪዎች ሰላም ለማምጣት ጥረት ቢያደርጉም ምን መሠረታዊ ነገር ችላ ብለዋል?
11 የዓለም መሪዎች በኤርምያስ 10:23 ላይ የተገለጸውን መሠረታዊ ጥበብ ፈጽሞ ችላ እንዳሉ ግልጽ ነው:- “አቤቱ የሰው መንገድ ከራሱ እንዳይደለ አውቃለሁ፣ አካሄዱንም ለማቅናት ከሚራመድ ሰው አይደለም።” አምላክ የሌለበት ሰላም እውነተኛ ሰላም ሊሆን አይችልም። ታዲያ እንዲህ ሲባል የሠለጠነው ኅብረተሰብ ከጦርነት ነጻ ሊሆን አይችልም ማለት ነውን? ሰላም፣ አዎን እውነተኛ ሰላም ፈጽሞ ሊገኝ የማይችል የሕልም እንጀራ ነው ማለት ነውን?
የችግሩን መንስኤ ማወቅ
12, 13. (ሀ) መጽሐፍ ቅዱስ በዓይን ስለማይታየው ቀንደኛ የጦርነት መንስኤ ምን ይላል? (ለ) ሰይጣን የሰው ልጆች በዓለም ውስጥ ላሉት ችግሮች እውነተኛ መፍትሔ ላይ እንዳያተኩሩ ያዘናጋቸው እንዴት ነው?
12 ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት የጦርነት መንስኤዎች ምን እንደሆኑ መረዳት ያስፈልገናል። መጽሐፍ ቅዱስ ዓመፀኛው መልአክ ሰይጣን የመጀመሪያው “ነፍሰ ገዳይ” እንዲሁም “ሐሰተኛ” እንደሆነና “ዓለምም በሞላው በክፉው እንደ ተያዘ” በግልጽ ያመለክታል። (ዮሐንስ 8:44፤ 1 ዮሐንስ 5:19) ዓላማውን ለማራመድ ምን አድርጓል? በ2 ቆሮንቶስ 4:3, 4 ላይ እንዲህ እናነባለን:- “ወንጌላችን የተከደነ ቢሆን እንኳ የተከደነባቸው ለሚጠፉ ነው። ለእነርሱም የእግዚአብሔር ምሳሌ የሆነ የክርስቶስ የክብሩ ወንጌል ብርሃን እንዳያበራላቸው፣ የዚህ ዓለም አምላክ [ሰይጣን] የማያምኑትን አሳብ አሳወረ።” ሰይጣን ዓለማችን ለተደቀነበት ችግሮች ብቸኛው መፍትሔ የአምላክ መንግሥት መሆኑን የሰው ልጆች እንዳይገነዘቡ የተቻለውን ሁሉ ያደርጋል። ሰዎች የአምላክን አገዛዝ አስፈላጊነት እንዳያስተውሉ በሚከፋፍሉ ማኀበራዊ፣ ፖለቲካዊና ሃይማኖታዊ ጉዳዮች እንዲዘናጉ በማድረግ ያሳውራቸዋል። ለዚህ አንዱ ምሳሌ የሚሆነን በቅርቡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ብሔራዊ ስሜት መስፋፋቱ ነው።
13 አንድ ብሔር፣ ዘር ወይም ጎሣ ከሌላው ይበልጣል የሚለውን የዘረኝነት እምነት ወይም ብሔራዊ ስሜት የሚያስፋፋው ሰይጣን ዲያብሎስ ነው። ለብዙ መቶ ዘመናት ተዳፍኖ የኖረ ሥር የሰደደ ጥላቻ እንደገና በማንሰራራቱ ምክንያት አዳዲስ ጦርነቶችና ግጭቶች ተቀስቅሰዋል። የዩኔስኮ ዳይሬክተር የሆኑት ፌደሪኮ ማዮር ስለዚህ አዝማሚያ ሲያስጠነቅቁ እንዲህ ብለዋል:- “መቻቻል ሰፍኖ በኖረባቸው አገሮች እንኳን ባዕዳንን የመጥላት አዝማሚያ እየተስፋፋ መጥቷል። የተረሱ ነገሮች ናቸው ያልናቸው ወገናዊነትንና የዘር የበላይነትን የሚያንጸባርቁ አነጋገሮች መዘውተር ጀምረዋል።” ይህስ ምን አስከትሏል? በቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ የተደረገው አሠቃቂ ጭፍጨፋና በሩዋንዳ ጎሣዎች መካከል የተፈጸመው ደም መፋሰስ የዓለምን የመገናኛ ብዙሐን ትኩረት ከሳቡት መሰል ክስተቶች መካከል ይገኛሉ።
14. ራእይ 6:4 በዘመናችን የሚታየውን ጦርነትና ጦርነቱ የሚያስከትለውን ውጤት የሚገልጸው እንዴት ነው?
14 መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ሥርዓት ፍጻሜ ዘመን የጦርነት ምሳሌ የሆነ ቀይ ፈረስ በመላው ምድር እንደሚጋልብ በግልጽ ተንብዮአል። በራእይ 6:4 ላይ እንዲህ እናነባለን:- “ሌላም ዳማ ፈረስ ወጣ፣ በእርሱም ላይ ለተቀመጠው ሰላምን ከምድር ይወስድ ዘንድ ሰዎችም እርስ በርሳቸው እንዲተራረዱ ሥልጣን ተሰጠው፣ ታላቅም ሰይፍ ተሰጠው።” ከ1914 ወዲህ ይህ ምሳሌያዊ ፈረስ ‘ሰላምን ከሰው ልጆች ሲወስድ’ ተመልክተናል፤ እስከ ዛሬ ድረስም ብሔራት እርስ በርስ መዋጋታቸውንና መጣላታቸውን ቀጥለዋል።
15, 16. (ሀ) በጦርነቶችና በጭፍጨፋዎች ውስጥ ሃይማኖት ምን ሚና ተጫውቷል? (ለ) ይሖዋ ሃይማኖቶች ያደረጉትን ነገር የሚመለከተው እንዴት ነው?
15 በእነዚህ ጦርነቶችና ጭፍጨፋዎች ሃይማኖት የተጫወተው ሚና በቸልታ የሚታለፍ አይደለም። የሰው ልጅ ታሪክ በደም የተጨማለቀ የሆነው በአብዛኛው የሐሰት ሃይማኖት በሰጠው የተሳሳተ አመራር ምክንያት ነው ሊባል ይቻላል። የካቶሊክ ሃይማኖታዊ ምሁር የሆኑት ሐንዝ ኩንግ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “[ሃይማኖቶች] በጣም ከፍተኛ የሆነ አሉታዊና ጎጂ አስተዋጽኦ እንዳበረከቱና አሁንም በማበርከት ላይ እንደሚገኙ መካድ አይቻልም። ሁለቱን የዓለም ጦርነቶች ጨምሮ . . . በጣም በርካታ ለሆኑ ውጊያዎች፣ ደም ያፋሰሱ ግጭቶችና ‘ሃይማኖታዊ ጦርነቶች’ በኃላፊነት የሚጠየቁት ሃይማኖቶች ናቸው።”
16 ይሖዋ አምላክ በሚካሄዱት ጭፍጨፋዎችና ጦርነቶች ውስጥ የሐሰት ሃይማኖት ስለተጫወተው ሚና ምን ይሰማዋል? በራእይ 18:5 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘው አምላክ በሐሰት ሃይማኖት ላይ ያስነሳው ክስ “ኃጢአትዋ እስከ ሰማይ ድረስ ደርሶአልና፣ እግዚአብሔርም ዓመፃዋን አሰበ” ይላል። የሐሰት ሃይማኖት በደም አፍሳሽነት ወንጀል ተጠያቂ እንዲሆንና ኃጢአቱም እንዲቆለል ያደረገው ከዓለም ፖለቲካዊ ገዥዎች ጋር በማበሩ ነው፤ አምላክ ደግሞ ይህን እንዲሁ ችላ ብሎ ሊያልፈው አይችልም። እውነተኛ ሰላም እንዳይገኝ እንቅፋት የሆነውን ይህን ማሰናከያ በቅርቡ ጨርሶ ያስወግደዋል።— ራእይ 18:21
ወደ ሰላም የሚመራ ጎዳና
17, 18. (ሀ) ዘላለማዊ ሰላም ሊመጣ ይችላል ብሎ ማመን የሕልም እንጀራ የማይሆነው ለምንድን ነው? (ለ) ይሖዋ እውነተኛ ሰላም ለማምጣት እስካሁን ምን አድርጓል?
17 ሰዎች እንደተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባሉት ድርጅቶቻቸው አማካኝነት እውነተኛና ዘላቂ የሆነ ሰላም ለማምጣት ካልቻሉ እውነተኛ ሰላም ሊመጣ የሚችለው ከየትና እንዴት ነው? ዘላለማዊ ሰላም ይመጣል ብሎ ተስፋ ማድረግ እውን ሊሆን የማይችል ቅዠት ይሆን? ፊታችንን ወደ ትክክለኛው የሰላም ምንጭ ዞር ብናደርግ ተስፋችን ቅዠት አይሆንም። ይህ ትክክለኛ የሰላም ምንጭ ማን ነው? መዝሙር 46:9 ይሖዋ “እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ጦርነትን ይሽራል፣ ቀስትን ይሰብራል፣ ጦርንም ይቆርጣል፣ በእሳትም ጋሻን ያቃጥላል” በማለት መልሱን ይነግረናል። ይሖዋ አሁንም እንኳ ጦርነትን አጥፍቶ እውነተኛ ሰላም የሚያቋቁምበትን ሂደት ጀምሯል። እንዴት? ክርስቶስ ኢየሱስን ሕጋዊ መብቱ በሆነው ንጉሣዊ ዙፋን ላይ በ1914 በማስቀመጥና በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ ሆኖ በማያውቅ መጠን የሰላም ትምህርት ዘመቻ በማካሄድ ነው። የኢሳይያስ 54:13 ትንቢታዊ ቃላት “ልጆችሽም ሁሉ ከእግዚአብሔር የተማሩ ይሆናሉ፣ የልጆችሽም ሰላም ብዙ ይሆናል” በማለት ማረጋገጫ ይሰጡናል።
18 ይህ ትንቢት በምክንያትና በውጤት መካከል ያለውን ግንኙነት ማለትም እያንዳንዱ ውጤት ምክንያት አለው የሚለውን መሠረታዊ ሥርዓት ይገልጻል። በዚህ ረገድ ምክንያት የሆነው የይሖዋ ትምህርት ጦርነት ወዳድ የነበሩትን ሰዎች ለውጦ ከአምላክ ጋር ሰላም ያላቸው ሰላም ወዳድ ሰዎች አድርጓቸዋል። ሰዎችን ሰላም ወዳድ እንዲሆኑ የሚያደርጋቸው የልባቸው መለወጥ ደግሞ ውጤቱ ነው። ይህ የሰዎችን ልብና አእምሮ የሚለውጠው ትምህርት በአሁኑ ጊዜ እንኳን በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ‘የሰላም ገዢ’ የሆነውን የኢየሱስ ክርስቶስን አርዓያ በመከተላቸው ምክንያት በመላው ምድር በመሰራጨት ላይ ነው።— ኢሳይያስ 9:6
19. ኢየሱስ ስለ እውነተኛ ሰላም ምን አስተምሯል?
19 ኢየሱስ ስለ እውነተኛ ሰላም ምን አስተምሯል? እርሱ በብሔራት መካከል ስለሚኖረው ሰላም ብቻ ሳይሆን በሰዎች የእርስ በርስ ግንኙነት መካከል ስለሚኖረው ሰላምና ከጥሩ ሕሊና ስለሚመነጨው ውስጣዊ ሰላም ተናግሯል። በዮሐንስ 14:27 ላይ ኢየሱስ ለተከታዮቹ የተናገራቸውን ቃላት እናነባለን:- “ሰላምን እተውላችኋለሁ፣ ሰላሜን እሰጣችኋለሁ፤ እኔ የምሰጣችሁ ዓለም እንደሚሰጥ አይደለም። ልባችሁ አይታወክ አይፍራም።” የኢየሱስ ሰላም ዓለም ከሚሰጠው ሰላም የተለየ የሆነው እንዴት ነው?
20. ኢየሱስ እውነተኛ ሰላም የሚያመጣው በምን አማካኝነት ነው?
20 በመጀመሪያ ደረጃ የኢየሱስ ሰላም ከመንግሥቱ መልእክት ጋር በቅርብ የተሳሰረ ነው። ኢየሱስና 144,000ዎቹ ተባባሪ ገዥዎች የሚገኙበት ጻድቅ ሰማያዊ መንግሥት ጦርነትንና ጦርነት ናፋቂዎችን ጨርሶ እንደሚያጠፋ ያውቃል። (ራእይ 14:1, 3) አጠገቡ ተሰቅሎ ለሞተው ክፉ አድራጊ የሰጠውን ተስፋ እውን በማድረግ ሰላም የሰፈነበት ገነታዊ ሁኔታዎችን እንደሚያመጣ ያውቃል። ኢየሱስ ለዚህ ክፉ አድራጊ “እውነት እልሃለሁ ዛሬ፣ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ” አለው እንጂ በሰማያዊው መንግሥት ቦታ እንደሚሰጠው አልተናገረም።— ሉቃስ 23:43 NW
21, 22. (ሀ) እውነተኛ ሰላም ምን አስደናቂና ብርታት ሰጪ ተስፋን ያካትታል? (ለ) ለዚህ በረከት የዓይን ምሥክሮች ለመሆን ምን ማድረግ ይኖርብናል?
21 በተጨማሪም ኢየሱስ መንግሥቱ በእርሱ ለሚያምኑ በሐዘን የተዋጡ ሰዎች ሁሉ መጽናናት እንደሚያመጣ ያውቅ ነበር። የኢየሱስ ሰላም አስደናቂና ብርታት ሰጪ የሆነውን የትንሣኤ ተስፋ ይጨምራል። በዮሐንስ 5:28, 29 ላይ የተናገረውን አበረታች ቃል አስታውሱ:- “[“በመታሰቢያ፣” NW] መቃብር ያሉቱ ሁሉ ድምፁን የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል፤ መልካምም ያደረጉ ለሕይወት ትንሣኤ ክፉም ያደረጉ ለፍርድ ትንሣኤ ይወጣሉና በዚህ አታድንቁ።”
22 ይህን ጊዜ በናፍቆት ትጠባበቃላችሁን? የምትወዷቸውን ሰዎች በሞት አጥታችኋል? እንደገና ልታይዋቸው ትናፍቃላችሁ? እንግዲያው ኢየሱስ የሚሰጠውን ሰላም ተቀበሉ። “በመጨረሻው ቀን በትንሣኤ እንዲነሣ አውቃለሁ” ስትል ለኢየሱስ የተናገረችው የአልዓዛር እህት ማርታ የነበራት ዓይነት እምነት ይኑራችሁ። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ለማርታ ምን የሚያስደስት መልስ እንደሰጣት ልብ በሉ:- “ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል፤ ሕያው የሆነም የሚያምንብኝም ሁሉ ለዘላለም አይሞትም፤ ይህን ታምኚያለሽን?” ብሏታል።— ዮሐንስ 11:24-26
23. እውነተኛ ሰላም ለማግኘት በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን ትክክለኛ እውቀት መቅሰም የግድ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
23 እናንተም በዚህ ተስፋ ልታምኑበትና ከተስፋው ልትጠቀሙ ትችላላችሁ። እንዴት? በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን ትክክለኛ እውቀት በማግኘት ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ ለትክክለኛ እውቀት ትልቅ ትኩረት እንደሰጠ አስተውሉ:- “እኛ ደግሞ . . . የፈቃዱ [“ትክክለኛ፣” NW] እውቀት መንፈሳዊ ጥበብንና አእምሮን ሁሉ እንዲሞላባችሁ እየለመንን፣ ስለ እናንተ ጸሎትን አልተውንም፤ በበጎ ሥራ ሁሉ ፍሬ እያፈራችሁ በእግዚአብሔርም [“ትክክለኛ፣” NW] እውቀት እያደጋችሁ፣ . . . በነገር ሁሉ ደስ ልታሰኙ ለጌታ እንደሚገባ ትመላለሱ ዘንድ እንለምናለን።” (ቆላስይስ 1:9-12) ይህ ትክክለኛ እውቀት የእውነተኛ ሰላም ምንጭ ይሖዋ አምላክ መሆኑን ያሳምናችኋል። እንደ መዝሙራዊው “በሰላም እተኛለሁ አንቀላፋለሁም አቤቱ አንተ ብቻ በእምነት አሳድረኸኛልና” ማለት ትችሉ ዘንድ አሁን ምን ማድረግ እንደሚኖርባችሁ ያሳውቃችኋል።— መዝሙር 4:8
ልታብራራ ትችላለህን?
◻ የሰው ልጅ ሰላም ለማስፈን ያደረጋቸው ጥረቶች በተደጋጋሚ ጊዜያት ሳይሳኩ የቀሩት ለምንድን ነው?
◻ ዋነኛው የጦርነት መንስኤ ማን ነው?
◻ ዘላቂ ሰላም የሕልም እንጀራ የማይሆነው ለምንድን ነው?
◻ የእውነተኛው ሰላም ምንጭ ምንድን ነው?
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
እውነተኛ ሰላም የሕልም እንጀራ አይደለም። አምላክ ቃል የገባው ተስፋ ነው
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ምሳሌያዊው የዳማ ፈረስ ጋላቢ ከ1914 ወዲህ ሰላምን ከምድር ላይ ወስዷል
[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሃይማኖትና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሰላም ሊያመጡ ይችላሉን?
[ምንጭ]
UN photo