በዛሬው ጊዜ አምላክን በመሐሪነቱ ምሰሉት
“ምሕረቱ ብዙ ነውና [በይሖዋ (አዓት)] እጅ እንውደቅ።”—2 ሳሙኤል 24:14
1. ዳዊት ስለ አምላክ ምሕረት እንዴት ተሰምቶታል? ለምንስ?
ንጉሥ ዳዊት ይሖዋ ከሰዎች ይበልጥ መሐሪ መሆኑን ከተሞክሮ ተገንዝቦ ነበር። የአምላክ ጎዳናዎች ወይም መንገዶች ከሁሉ የሚበልጡ ስለ መሆናቸው እርግጠኛ ስለነበረ ዳዊት መንገዶቹን ለመማርና በእውነቱ ለመመላለስ ይፈልግ ነበር። (1 ዜና 21:13፤ መዝሙር 25:4, 5) አንተስ ዳዊት እንደተሰማው ያለ ስሜት ይሰማሃልን?
2. ኢየሱስ በማቴዎስ 18:15-17 ላይ ከባድ ኃጢአትን በተመለከተ ምን ምክር ሰጠ?
2 መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አምላክ አስተሳሰብ ጠለቅ ያለ ማስተዋል ይሰጠናል። ለምሳሌ አንድ ሰው በእኛ ላይ ኃጢአት ቢሠራ ልናደርጋቸው ስለሚገቡን ነገሮች እንኳ ሳይቀር ጥልቅ ማስተዋል ይሰጠናል። ኢየሱስ ከጊዜ በኋላ ክርስቲያን የበላይ ተመልካቾች ለሚሆኑት ሐዋርያቱ “ወንድምህም ቢበድልህ፣ ሄደህ አንተና እርሱ ብቻችሁን ሆናችሁ ውቀሰው፤ ቢሰማህ ወንድምህን ገንዘብ አደረግኸው” ብሏቸው ነበር። እዚህ ላይ የተገለጸው በደል እንዲሁ ተራ የግል ስህተት አልነበረም፤ እንደ ማጭበርበር ወይም ስም ማጥፋት ያለውን ከባድ ኃጢአት የሚመለከት ነበር። ይህ እርምጃ ለችግሩ መፍትሄ ካላመጣና ምስክሮች የሚገኙ ከሆነ በደል የተፈጸመበት ሰው በደሉን ለማረጋገጥ ምሥክሮቹን ይዟቸው መሄድ እንደሚገባው ኢየሱስ ተናግሯል። ይህ በመጨረሻ ላይ የሚወሰድ እርምጃ ነውን? አይደለም። ኃጢአተኛው “እነርሱንም ባይሰማ፣ ለቤተክርስቲያን [ለጉባኤ (አዓት)] ንገራት፤ ደግሞም ቤተ ክርስቲያንን ባይሰማት፣ እንደ አረመኔና እንደ ቀራጭ ይሁንልህ።”—ማቴዎስ 18:15-17
3. ኢየሱስ ንስሐ የማይገባ ኃጢአተኛ ‘እንደ አረመኔና ቀራጭ ይሁንልህ’ ሲል ምን ማለቱ ነበር?
3 ሐዋርያት አይሁዳውያን ስለሆኑ አንድን ኃጢአተኛ “እንደ አረመኔና እንደ ቀራጭ” አድርጎ መመልከት ምን ማለት እንደሆነ ይገባቸዋል። አይሁዶች አረመኔ ከሆኑት አሕዛብ ጋር ግንኙነት ከማድረግ ይርቁ ነበር፤ የሮም ግብር ሰብሳቢዎች በመሆን ይሠሩ የነበሩትን አይሁዶችም ይጸየፉ ነበር።a (ዮሐንስ 4:9፤ ሥራ 10:28) ስለዚህ ኢየሱስ ጉባኤው አንድን ኃጢአተኛ ካስወጣው ደቀመዛሙርቱ ከእርሱ ጋር መተባበራቸውን ማቆም እንዳለባቸው መምከሩ ነበር። ታዲያ ይህ ኢየሱስ አልፎ አልፎ ከቀራጮች ጋር አብሮ ከመዋሉ ሁኔታ ጋር እንዴት ይስማማል?
4. ኢየሱስ በማቴዎስ 18:17 ላይ ያሉትን ቃላት ከተናገረ ከአንዳንድ ቀራጮችና ኃጢአተኞች ጋር እንዴት ሊገናኝ ቻለ?
4 ሉቃስ 15:1 “ቀራጮችና ኃጢአተኞችም ሁሉ ሊሰሙት ወደ እርሱ ይቀርቡ ነበር” ይላል። በዚህ ቦታ ሁሉም ቀራጮች ወይም ኃጢአተኞች ነበሩ ማለት አይደለም፤ እዚህ ላይ “ሁሉ” የሚለው ቃል ብዙዎች ማለት ነው። (ከሉቃስ 4:40 ጋር አወዳድር) እነዚህ እነማን ናቸው? ኃጢአታቸው ይቅር እንዲባልላቸው የሚፈልጉት ናቸው። ከእነዚህ ውስጥ አንዳንዶቹ ቀደም ብለው ወደ ዮሐንስ የንስሐ ስብከት የተሳቡ ነበሩ። (ሉቃስ 3:12፤ 7:29) ስለዚህ ሌሎቹ ወደ ኢየሱስ ሲመጡ ለእነርሱ መስበኩ የማቴዎስ 18:17ን ምክር የሚቃረን አልነበረም። “ብዙ ቀራጮችና ኃጢአተኞች [ኢየሱስን ሰምተው] ይከተሉት” እንደነበር አስታውስ። (ማርቆስ 2:15) እነዚህ ምንም እርዳታ አንፈልግም ብለው በመጥፎ አኗኗር ለመቀጠል የፈለጉ ሰዎች አልነበሩም። ከዚህ ይልቅ የኢየሱስን መልዕክት ሰሙ፤ ልባቸውም ተነካ። አሁንም ገና ኃጢአት በመሥራት ላይ ቢሆኑም እንኳን (እርግጥ ለውጥ ለማድረግ እየሞከሩ መሆናቸው የማይቀር ነው) “መልካሙ እረኛ” ለእነርሱ በመስበኩ የመሐሪውን አባቱን ምሳሌ ተከትሏል።—ዮሐንስ 10:14
ይቅር ባይነት፣ የክርስቲያን ግዴታ ነው
5. ይቅርታ ማድረግን በተመለከተ አምላክ ያለው መሠረታዊ አቋም ምንድን ነው?
5 አባታችን ይቅር ለማለት ፈቃደኛ ስለመሆኑ የሚከተሉት ሞቅ ያሉ ማረጋገጫዎች ተሰጥተውናል፦ “በኃጢአታችን ብንናዘዝ ኃጢአታችንን ይቅር ሊለን ከዓመፃም ሁሉ ሊያነጻን የታመነና ጻድቅ ነው።” “ኃጢአትን እንዳታደርጉ ይህን እጽፍላችኋለሁ። ማንም ኃጢአትን ቢያደርግ ከአብ ዘንድ ጠበቃ አለን እርሱም ጻድቅ የሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።” (1 ዮሐንስ 1:9፤ 2:1) አንድ የተወገደ ሰው ይቅርታ ሊያገኝ ይችላልን?
6. አንድ የተወገደ ሰው ይቅርታ ሊደረግለትና ወደ ጉባኤው ሊመለስ የሚችለው እንዴት ነው?
6 አዎን ይችላል። አንድ ሰው ንስሐ ባለመግባቱ ምክንያት በሚወገድበት ጊዜ ጉባኤውን የሚወክሉት ሽማግሌዎች ንስሐ ለመግባትና የአምላክን ይቅርታ ለማግኘት እንደሚችል ይገልጹለታል። በመንግሥት አዳራሹ በሚደረጉት ስብሰባዎች ላይ ሊገኝ ይችላል። በዚያም ንስሐ ለመግባት የሚረዱትን የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎችን ሊያዳምጥ ይችላል። (ከ1 ቆሮንቶስ 14:23-25 ጋር አወዳድር) ውሎ አድሮም ወደ ንጹሑ ጉባኤ እንደገና ለመመለስ ይፈልግ ይሆናል። ሽማግሌዎቹ ከእርሱ ጋር ተቀምጠው ሲያነጋግሩት ንስሐ ገብቶና የኃጢአት መንገዱን ትቶ እንደሆነ ለማወቅ ይሞክራሉ። (ማቴዎስ 18:18) ንስሐ ገብቶ ከሆነ በ2 ቆሮንቶስ 2:5-8 ላይ በሚገኘው ምሳሌ መሠረት ወደ ጉባኤው ሊመለስ ይችላል። ከተወገደ ብዙ ዓመት አልፎት ከሆነ እድገት ለማድረግ የተጠናከረ ጥረት ማድረግ ያስፈልገዋል። ከዚያም በኋላ ቢሆን በመንፈሳዊ ጠንካራ ክርስቲያን ለመሆን የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀቱንና አድናቆቱን ለመገንባት ከፍተኛ እርዳታ ሊያስፈልገው ይችላል።
ወደ ይሖዋ መመለስ
7, 8. በምርኮ ላይ ከነበሩት ሕዝቦቹ ጋር በተያያዘ አምላክ ምን ምሳሌ ትቶልናል?
7 ነገር ግን ሽማግሌዎቹ የተወገደው ሰው ሳይጠይቃቸው ራሳቸው ተነሳስተው ሊያነጋግሩት ይችላሉን? አዎን ይችላሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ምሕረት የሚገለጸው አፍራሽ የቅጣት አቋም በመያዝ ብቻ ሳይሆን ብዙውን ጊዜ አዎንታዊ እርምጃዎችን በመውሰድም ጭምር እንደሆነ ያሳያል። ለዚህ ይሖዋ ምሳሌ ይሆነናል። ታማኝነት የጎደላቸውን ሕዝቦቹን ወደ ምርኮ እንዲሄዱ ከማድረጉ በፊት እንደገና የመመለስ ተስፋ እንዳላቸው በትንቢት አስነግሮ ነበር፦ “ያዕቆብ ሆይ፣ አንተም እስራኤል፣ ባሪያዬ ነህና ይህን አስብ፤ . . . መተላለፍህን እንደ ደመና፣ ኃጢአትህንም እንደ ጭጋግ ደምስሼአለሁ፤ ተቤዥቼሃለሁና ወደ እኔ ተመለስ።”—ኢሳይያስ 44:21, 22
8 ከዚያም በምርኮ ላይ በነበሩበት ጊዜ ይሖዋ አዎንታዊ በሆነ መንገድ በመነሳት ተጨማሪ እርምጃዎችን ወሰደ። እስራኤላውያን እርሱን ‘እንዲፈልጉትና እንዲሹት’ ለመጋበዝ ወኪሎቹ የሆኑትን ነቢያት ይልክ ነበር። (ኤርምያስ 29:1, 10-14) በሕዝቅኤል 34:16 ላይ ራሱን ከአንድ እረኛ ጋር የእስራኤልን ሕዝብ ደግሞ ከጠፉ በጎች ጋር አመሳስሎ ገልጿል፦ “የጠፋውንም እፈልጋለሁ የባዘነውንም እመልሳለሁ።” ይሖዋ በኤርምያስ 31:10 ላይም ራሱን የእስራኤላውያን እረኛ እንደሆነ አድርጎ ገልጿል። እርሱ የጠፋው በግ ተመልሶ እንዲመጣ በበረቱ ቆሞ እንደሚጠብቅ እረኛ አድርጎ ራሱን አልገለጸም፤ ከዚህ ይልቅ የጠፉ በጎችን እንደሚፈልግ እረኛ እንደሆነ አሳይቷል። ሕዝቡ በአጠቃላይ ንስሐ ባለመግባታቸው ምርኮኞች ቢሆኑም አምላክ ቀዳሚ በመሆን እንዲመለሱ ጥረቶችን እንዳደረገ ልብ በል። በሚልክያስ 3:6 መሠረት አምላክ በክርስቲያናዊው ዝግጅትም ውስጥ ቢሆን ለሕዝቦቹ የሚኖረውን አቋም አይለውጥም።
9. የክርስቲያን ጉባኤ የአምላክን ምሳሌ የተከተለው እንዴት ነበር?
9 ታዲያ ይህ አሁን ተወግደው ያሉትንና ንስሐ መግባት የሚፈልጉትን አንዳንድ ሰዎች ለመርዳት ቀድመን እንድንነሳሳ ምክንያት ሊኖር እንደሚችል አያመለክትምን? ሐዋርያው ጳውሎስ ክፉውን ሰው ከቆሮንቶስ ጉባኤ እንዲያስወጡት መመሪያ ሰጥቶ እንደነበረ ትዝ ይበላችሁ። በኋላም ሰውየው ንስሐ ስለገባ ፍቅራቸውን እንዲያረጋግጡለት ጉባኤውን አሳሰበ፤ ንስሐ መግባቱ ወደ ጉባኤው እንዲመለስ የሚመራው ሆኗል።—1 ቆሮንቶስ 5:9-13፤ 2 ቆሮንቶስ 2:5-11
10. (ሀ) የተወገደን ሰው ቀርቦ ለማነጋገር ገፋፊው ምክንያት ምን መሆን አለበት? (ለ) ክርስቲያን ዘመዶች ቀድመው ግንኙነት ለማድረግ መነሳሳት የማይኖርባቸው ለምንድን ነው?
10 ቀደም ሲል ተጠቅሶ የነበረው ኢንሳይክሎፔዲያ እንዲህ ብሏል፦ ‘የማስወገድ መሠረታዊ ምክንያቱ የቡድኑን የሥርዓት ደረጃ ለመጠበቅ ነበር፤ “ጥቂት እርሾ ሊጡን ሁሉ ያቦካልና።” (1 ቆሮ. 5:6) ይህ መንፈስ በአብዛኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስም ሆነ ከዚያ ውጭ በሚገኙ ጽሑፎች ውስጥ በግልጽ ይታያል፤ ሆኖም ከውገዳውም በኋላ ቢሆን ለግለሰቡ አሳቢነት ማሳየት በ2 ቆሮ. 2:7-10 ላይ የሚገኘው የጳውሎስ ልመና መሠረት ነበር።’ እንግዲያው ይህን የመሰለውን አሳቢነት ዛሬም ያሉ የመንጋው እረኞች ቢያሳዩት ተገቢ ይሆናል። (ሥራ 20:28፤ 1 ጴጥሮስ 5:2) የቀድሞ ጓደኞችና ዘመዶች የተወገደው ሰው እንደሚመለስ ተስፋ ያደርጋሉ፤ ቢሆንም በ1 ቆሮንቶስ 5:11 ላይ የሚገኘውን ትዕዛዝ በማክበር ከተወገደው ሰው ጋር አይተባበሩም።b ይህ ሰው ለመመለስ ፍላጎት እንዳለው ለመገምገም እርሱን ቀርቦ የማነጋገሩን ሥራ ለሽማግሌዎቹ ይተዉታል።
11, 12. ሽማግሌዎችም እንኳን ቢሆኑ ሊገናኙአቸው የማይፈልጉት ምን ዓይነት የተወገዱ ሰዎችን ነው? ሆኖም ምን ዓይነት የተወገዱ ሰዎችን መጎብኘት ይኖርባቸዋል?
11 ሆኖም እንደ ከሃዲዎች ያሉትን ‘ደቀመዛሙርትን ወደ ኋላቸው ይስቡ ዘንድ ጠማማ ነገርን የሚናገሩ ሰዎችን’ ቀድሞ ማነጋገሩ ለሽማግሌዎችም ቢሆን ተገቢ አይሆንም። እነዚህ ‘የሚያጠፋ ኑፋቄን አሹልከው ለማግባት የሚሞክሩና ጉባኤውን በሐሰት ቃላት የሚበዘብዙ ሐሰተኛ አስተማሪዎች’ ናቸው። (ሥራ 20:30፤ 2 ጴጥሮስ 2:1, 3) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ በንዴት የሚናገሩትን ወይም ኃጢአት መሥራትን የሚያበረታቱትን ግለሰቦች ለመፈለግ ምንም መሠረት አይሰጥም።—2 ተሰሎንቄ 2:3፤ 1 ጢሞቴዎስ 4:1፤ 2 ዮሐንስ 9-11፤ ይሁዳ 4, 11
12 ይሁን እንጂ የተወገዱ ብዙ ሰዎች እንደዚህ አይደሉም። ምናልባት አንድ ሰው ለመወገድ ምክንያት የሆነውን ከባድ ኃጢአት አቁሞ ይሆናል። ሌላው ደግሞ በፊት ሲጋራ የሚያጨስ ወይም ከመጠን በላይ የሚጠጣ የነበረ ይሆናል፤ አሁን ግን ሌሎችን ወደ ኃጢአት የሚመራ ላይሆን ይችላል። በምርኮ ሥር የነበሩት እስራኤላውያን ወደ አምላክ ከመመለሳቸው በፊት እንዲመለሱ እነርሱን ለማሳሰብ ወኪሎቹን ይልክ እንደነበረ ትዝ ይበልህ። ሐዋርያው ጳውሎስም ይሁን በቆሮንቶስ ጉባኤ ውስጥ የነበሩ ሽማግሌዎች ተወግዶ የነበረውን ሰው ራሳቸው ጀማሪ በመሆን ያነጋገሩት ስለመሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ አይናገርም። ያ ሰው ንስሐ ሲገባና የብልግና ድርጊቱን ሲያቆም ጉባኤው እንዲመልሰው ጳውሎስ መመሪያ ሰጠ።
13, 14. (ሀ) አንዳንድ የተወገዱ ሰዎች በምሕረት ስሜት ለሚደረጉላቸው ጥረቶች አዎንታዊ ምላሽ እንደሚሰጡ የሚያመለክተው ምንድን ነው? (ለ) የሽማግሌዎቹ አካል ከተወገደው ሰው ጋር ለመገናኘት ዝግጅቶችን ማድረግ የሚችለው እንዴት ነው?
13 በቅርብ ጊዜ አንድ ሽማግሌ ከአንድ የተወገደ ሰው ጋር የተገናኘባቸው ሁኔታዎች አጋጥመዋል።c ተገቢ ሆኖ ሲያገኘው እረኛው እንደገና ለመመለስ ሊወሰዱ የሚገባቸውን እርምጃዎች በአጭሩ ይገልጽለታል። በዚህ መንገድ አንዳንድ ሰዎች ንስሐ ገብተው ተመልሰዋል። እንደዚህ ያሉ አስደሳች ውጤቶች ምናልባት እረኞቹ በምሕረት መንፈስ ቢቀርቧቸው የተወገዱ ወይም ራሳቸውን ያገለሉ አንዳንድ ሰዎች እርምጃ ሊወስዱ እንደሚችሉ ያሳያሉ። ነገር ግን ሽማግሌዎቹ እንዲህ ያለውን ጉዳይ ማከናወን የሚችሉት እንዴት ነው? ቢያንስ በዓመት አንድ ጊዜ የሽማግሌዎች አካል እንደነዚህ ያሉ ሰዎች በክልላቸው ውስጥ እንዳሉ መመርመር ያስፈልገዋል።d ሽማግሌዎቹ ትኩረት የሚያደርጉት ከተወገዱ አንድ ዓመት ባለፋቸው ላይ መሆን ይኖርበታል። ሁኔታው በሚፈቅደው መሠረት አስፈላጊ ከሆን ይህንን ግለሰብ ለመጎብኘት ሁለት ሽማግሌዎችን (ስለ ሁኔታው የሚያውቁ) ይመድባሉ። ሆኖም በጣም የሚተችና አደገኛ አቋም እንዳለው ለተረጋገጠበት ወይም እርዳታ እንደማይፈልግ ላሳወቀ ሰው ጉብኝት አይደረግም።—ሮሜ 16:17, 18፤ 1 ጢሞቴዎስ 1:20፤ 2 ጢሞቴዎስ 2:16-18
14 ሁለቱ እረኞች አጭር ጉብኝት ሊያደርጉለት እንደሚፈልጉ በስልክ ለመጠየቅ ወይም በተስማሚ ጊዜ ላይ ጐራ ብለው ለማነጋገር ይችላሉ። በጉብኝቱ ወቅት መኮሳተር ወይም ቀዝቃዛ መሆን አያስፈልጋቸውም፤ የምሕረታዊ አሳቢነታቸውን በጋለ ስሜት ማንጸባረቅ ይገባቸዋል። ያለፈውን ጉዳይ አንስተው እንደገና ከመወያየት ይልቅ እንደ ኢሳይያስ 1:18 እና ኢሳ 55:6, 7 እንዲሁም ያዕቆብ 5:20 የመሳሰሉትን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች እየጠቀሱ ሊያወያዩት ይችላሉ። ሰውየው ከአምላክ መንጋ ጋር ለመቀላቀል ፍላጎት ካሳየ በደግነት መጽሐፍ ቅዱስንና የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ጽሑፎችን እንደማንበብና በመንግሥት አዳራሹ በሚደረጉት ስብሰባዎች እንደመገኘት ያሉትን እርምጃዎች መውሰድ እንዳለበት ይገልጹለታል።
15. ከተወገደ ሰው ጋር የሚገናኙት ሽማግሌዎች ምን ነገር በአእምሮአቸው መያዝ አለባቸው?
15 ሽማግሌዎቹ የንስሐ ምልክት መኖሩንና ተመልሶ መጠየቁ ጥሩ መሆኑን ለማወቅ ጥበብና ማስተዋል ያስፈልጋቸዋል። አንዳንድ የተወገዱ ሰዎች ‘ለንስሐ ፈጽሞ እንደማይነቃቁ’ ማስታወስ ይኖርባቸዋል። (ዕብራውያን 6:4-6፤ 2 ጴጥሮስ 2:20-22) ከጉብኝቱ በኋላ ሁለቱ ሽማግሌዎች ለጉባኤው የአገልግሎት ኮሚቴ አጭር የቃል ሪፖርት ያቀርባሉ። እነርሱም ደግሞ በሚቀጥለው ስብሰባቸው ላይ ለሽማግሌዎቹ አካል ያሳውቃሉ። ሽማግሌዎቹ የሚያቀርቡት ምሕረት ያዘለ ግብዣ የሚከተለውን የአምላክን አስተሳሰብ ያንጸባርቃል፦ “ወደ እኔ ተመለሱ፣ እኔም ወደ እናንተ እመለሳለሁ፣ ይላል የሠራዊት ጌታ [ይሖዋ (አዓት)]።”—ሚልክያስ 3:7
ሌላው የምሕረት እርዳታ
16, 17. የአንድን የተወገደ ሰው ክርስቲያን ቤተሰቦች እንዴት ልንመለከታቸው ይገባናል?
16 እኛ የበላይ ተመልካቾች ያልሆንነውና ለተወገዱት ሰዎች እንደዚህ ያሉትን የቅድሚያ እርምጃዎች የማንወስደውስ? ከዚህ ዝግጅት ጋር በመስማማትና ይሖዋን በመምሰል ምን ልናደርግ እንችላለን?
17 አንድ ሰው እስከተወገደና እስከተገለለ ድረስ “ወንድሞች ከሚባሉት አንዱ ሴሰኛ ወይም ገንዘብን የሚመኝ ወይም ጣዖትን የሚያመልክ ወይም ተሳዳቢ ወይም ሰካር ወይም ነጣቂ ቢሆን ከእርሱ ጋር እንዳትተባበሩ” የሚለውን መመሪያ መከተል ያስፈልገናል። (1 ቆሮንቶስ 5:11) ይሁን እንጂ ይህ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መመሪያ ከተወገደው ሰው ጋር ለሚኖሩት የክርስቲያን ቤተሰብ አባሎች ያለንን አመለካከት ሊነካብን አይገባም። የጥንት አይሁዶች በቀራጮች ላይ ከፍተኛ ጥላቻ ስለነበራቸው ጥላቻቸው የቀራጩን ቤተሰብ እስከመጨመር ደርሶ ነበር። ኢየሱስ ይህንን አልደገፈም። እርዳታ አልፈልግም ያለው ኃጢአተኛ “እንደ አረመኔና ቀራጭ ይሁንልህ” አለ እንጂ የክርስቲያን ቤተሰቦች እንደዚያ መታየት አለባቸው አላለም።—ማቴዎስ 18:17
18, 19. ለአንድ የተወገደ ሰው ታማኝ ቤተሰቦች ክርስቲያንነታችንን ልናሳይ የምንችልባቸው አንዳንድ መንገዶች ምንድን ናቸው?
18 በተለይ ታማኝ ክርስቲያኖች የሆኑትን የቤተሰብ አባላት መደገፍ ይኖርብናል። መንፈሳዊ ጥረታቸውን ከሚያንቋሽሽባቸው የተወገደ ሰው ጋር አብረው በመኖራቸው ሥቃይና እንቅፋቶች አጋጥመዋቸው ሊሆን ይችላል። ምናልባትም ክርስቲያኖች ወደ ቤቱ እንዳይመጡ ይከለክል ይሆናል፤ ወይም ታማኝ የሆኑትን የቤተሰብ አባሎች ሊጠይቁ ሲመጡ ዘወር በማለት አክብሮት አያሳይ ይሆናል። እንዲሁም ቤተሰቡ ወደ ሁሉም የክርስቲያን ስብሰባዎች ለመሄድ የሚያደርጉትን ጥረት ለማጨናጐል ይጥር ይሆናል። (ከማቴዎስ 23:13 ጋር አወዳድር) በዚህ መንገድ መብታቸውን ያጡ ክርስቲያኖች በእውነትም ምሕረት ልናሳያቸው ይገባል።—2 ቆሮንቶስ 1:3, 4
19 ልባዊ ምሕረት ከምናሳይባቸው መንገዶች አንዱ ‘በሚያጽናና ቃል መናገር’ እና በቤተሰቡ ውስጥ ካሉት ከእነዚህ ታማኞች ጋር የሚያበረታቱ ውይይቶችን ማድረግ ነው። (1 ተሰሎንቄ 5:14) በተጨማሪም ከስብሰባዎች በፊትና በኋላ፣ በመስክ አገልግሎት ላይ፣ ወይም በሌሎች ጊዜያት ስንገናኝ ድጋፍ ለመስጠት የምንችልባቸው ጥሩ አጋጣሚዎችም አሉ። ስለ ውገዳ መጥቀስ ባያስፈልገንም ስለሚያንጹ ብዙ ነገሮች ልንወያይ እንችላለን። (ምሳሌ 25:11፤ ቆላስይስ 1:2-4) ሽማግሌዎቹ በቤተሰቡ ውስጥ ያሉትን ክርስቲያኖች በእረኝነት መጠየቃቸው የማይቀር ሲሆን፤ እኛም ብንሆን ከተወገደው ሰው ጋር ግንኙነት ሳናደርግ ልንጠይቃቸው እንችላለን። ልንጎበኛቸው ስንሄድ ወይም ስልክ ስንደውል ከተወገደው ሰው ጋር ብንገናኝ በአጭሩ የምንፈልገውን ክርስቲያን እንዲያገናኘን ልንጠይቀው እንችላለን። አንዳንድ ጊዜ ክርስቲያን የሆኑት የቤተሰብ አባሎች አብሮ ለመጫወት እቤታችን በምናደርገው ግብዣ ላይ ሊገኙ ይችሉ ይሆናል። እዚህ ላይ ለመግለጽ የተፈለገው ነጥብ፦ ወጣትም ሆኑ በዕድሜ የገፉ ሰዎች ሁሉ ከእኛ ጋር የሚያገለግሉ ስለሆኑ ሊገለሉ የማይገባቸው የተወደዱ የአምላክ ጉባኤ አባላት ናቸው የሚል ነው።—መዝሙር 10:14
20, 21. አንድ ሰው ከውገዳ ሲመለስ ምን ሊሰማንና ምን ማድረግ ይገባናል?
20 ሌላው ምሕረት የምናሳይበት ሁኔታ አንድ የተወገደ ሰው እንደገና በሚመለስበት ጊዜ ነው። ኢየሱስ የተናገረው ምሳሌ ‘አንድ ኃጢአተኛ ንስሐ ሲገባ’ በሰማይ የሚኖረውን ደስታ ጎላ አድርጎ ይገልጻል። (ሉቃስ 15:7, 10) ጳውሎስ ተወግዶ ስለነበረው ሰው ለጉባኤው ሲጽፍ “እንደዚህ ያለው ከልክ በሚበዛ ኀዘን እንዳይዋጥ፣ ይልቅ ተመልሳችሁ ይቅር ማለትና ማጽናናት ይገባችኋል። ስለዚህ ከእርሱ ጋር ፍቅርን እንድታጸኑ እለምናችኋለሁ” ብሏል። (2 ቆሮንቶስ 2:7, 8) ይህንን ምክር የተወገደው ሰው እንደገና ከተመለሰ በኋላ ባሉት ቀኖችና ሣምንታት በጭምትነትና በፍቅር በሥራ ላይ እናውለው።
21 ስለ አባካኙ ልጅ ኢየሱስ የተናገረው ምሳሌ ልንጠነቀቅበት የሚያስፈልገንን አንድ አደጋ ይገልጻል። ታላቅ ወንድሙ አባካኙ ልጅ በመመለሱ ደስ በመሰኘት ፋንታ ተናዶ ነበር። እኛም ባለፈው ስለተሠራው ኃጢአት መጥፎ አስተሳሰብ በአእምሮአችን በመያዝ ወይም ሰውየው ስለተመለሰ በመናደድ እንደ ትልቁ ልጅ አንሁን። ከዚህ ይልቅ ግባችን ለይሖዋ አቀባበል ምሳሌ ተደርጎ እንደቀረበው አባት መሆን ይኖርበታል። አባትየው የጠፋውና እንደሞተ ያህል የነበረው ልጁ ስለተገኘ ወይም ሕያው ስለሆነ ተደስቶ ነበር። (ሉቃስ 15:25-32) እንግዲያው እኛም ብንሆን እንደገና የተመለሰውን ወንድም ሳንሸሸው እናነጋግረዋለን፤ በሌላም መንገድ እናበረታታዋለን። አዎን፣ ይቅር ባዩና መሐሪው ሰማያዊ አባት እንደሚያደርገው እኛም ምሕረት እያሳየን መሆናችን በግልጽ መታየት ይኖርበታል።—ማቴዎስ 5:7
22. ይሖዋ አምላክን መምሰላችን ምን ነገሮችን ይጨምራል?
22 አምላካችንን ለመምሰል የምንፈልግ ከሆነ ከትዕዛዛቱና ከፍትሑ ጋር በሚስማማ መንገድ ምሕረት ማሳየት እንደሚገባን ምንም አያጠያይቅም። መዝሙራዊው ስለ እርሱ እንዲህ ይላል፦ “[ይሖዋ (አዓት)] ርኅሩኅና መሐሪ ነው፣ ከቁጣ የራቀ፣ ምሕረቱም ብዙ ነው፤ [ይሖዋ (አዓት)] ለሚታገሡት ቸር ነው። ምሕረቱም በሥራው ሁሉ ላይ ነው።” (መዝሙር 145:8, 9) ይሖዋ ዛሬ ያሉት ክርስቲያኖች ሊመስሉት የሚገባ እንዴት ያለ ፍቅራዊ ምሳሌ ነው!
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a “ቀራጮች በፍልስጥኤም ይኖሩ በነበሩ የአይሁድ ሕዝብ በተለይ ይጠሉ የነበሩት በተለያዩ ምክንያቶች ነበር፦ (1) የእስራኤልን ምድር ለያዘው የውጭ ኃይል ገንዘብ ይሰበስቡ ነበር፤ በዚህም በተዘዋዋሪ ለዚህ ግፍ ድጋፋቸውን ይሰጡ ነበር፤ (2) በደንታ ቢስነታቸው ምክንያት መጥፎ ስም ነበራቸው፤ የገዛ ሕዝባቸው በሆኑ በሌሎች ሰዎች ሐብት የሚበለጽጉ ነበሩ፤ እንዲሁም (3) ሥራቸው ከአሕዛብ ጋር ዘወትር እንዲገናኙ የሚያደርጋቸው ነበር፤ ይህም በሥነ ስርዓት እንዲረክሱ ያደርጋቸዋል። ለቀራጮች ሰዎች የነበራቸው ንቀት በአዲስ ኪዳን ውስጥም ሆነ በራባይ ጽሑፎች ውስጥ ተጽፎ ይገኛል። . . . [በራባይ ጽሑፍ] መሠረት ጥላቻው ለቀራጩ ቤተሰብም የሚተርፍ ነበር።”—ዘ ኢንተርናሽናል ባይብል ኢንሳይክሎፔዲያ
b በክርስቲያን ቤት ውስጥ አንድ የተወገደ ዘመድ ካለ በተለመዱት የዕለት ተዕለት ግንኙነቶችና እንቅስቃሴዎች ተካፋይ ሆኖ ይቀጥላል። ይህም በቤተሰብ መልክ መንፈሳዊ ጽሑፍ በሚጠናበት ጊዜ መገኘትን ሊጨምር ይችላል።—መጠበቂያ ግንብ 22-109 ገጽ 19-20 ተመልከት።
c የ1991 የይሖዋ ምስክሮች የዓመት መጽሐፍ ገጽ 53-54 ተመልከት።
d ማንም የይሖዋ ምስክር ከቤት ወደ ቤት በሚሰብክበት ጊዜ ወይም በሌላ መንገድ በክልሉ ውስጥ አንድ የተወገደ ሰው መኖሩን ካወቀ ለሽማግሌዎቹ ማስታወቅ ይኖርበታል።
እነዚህን ነጥቦች አስተውለሃቸዋልን?
◻ አይሁድ ቀራጮችንና ኃጢአተኞችን እንዴት ይመለከቱ ነበር? ታዲያ ኢየሱስ ከእነዚህ ሰዎች መካከል ከአንዳንዶቹ ጋር ግንኙነት ያደርግ የነበረው ለምንድን ነው?
◻ ጠፍተው የነበሩትን በምሕረት ተገፋፍቶ ለማነጋገር ምን ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረት አለ?
◻ የሽማግሌዎች አካል በተወገደው ሰው ሳይጠየቅ በራሱ ተነሳስቶ እንዴት እርዳታ ሊያደርግ ይችላል? ለእነማንስ?
◻ ከውገዳ ለተመለሱትና ለተወገዱ ሰዎች ዘመዶች ምሕረት ልናሳይ የሚገባን እንዴት ነው?
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
በአንድ ወቅት የንፁሁና የደስተኛው የአምላክ ጉባኤ አባል የነበረ አሁን ግን የተወገደ ወይም የተገለለ ሰው ባለበት ሁኔታ መቀጠል የግድ አያስፈልገውም። ከዚህ ይልቅ ይህ ሰው ንስሐ ሊገባና ከጉባኤው ሽማግሌዎች ጋር ለመገናኘት ቀድሞ እርምጃ መውሰድ ይችላል። ለመመለስ በሩ ክፍት ነው።
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
Garo Nalbandian