በአሸባሪ ዓለም ውስጥ የወንጀልን ጥቃት መቋቋም
ማታ ወደ ውጭ መውጣት ትፈራለህን? በመዝጊያና በመስኰትህ ላይ ሁለትና ሦስት መቀርቀሪያ ያስፈልግሃልን? መኪናህ ወይም ብስክሌትህ ተሰርቆብህ ያውቃልን? ከመኪናህ ውስጥ ሬድዮህን አውልቀው ወስደውብሃልን? በአንዳንድ አካባቢዎች ስትሄድ ስጋት ይሰማሃልን?
እነዚህን ጥያቄዎች አዎን ብለህ የምትመልስ ከሆነ በአሸባሪ ዓለም ውስጥ የወንጀልን ጥቃት ለመቋቋም እየሞከርክ ነው ማለት ነው። ታዲያ ከጥቃቱ ራስህን ለማዳን ምን ለማድረግ ትችላለህ? መጽሐፍ ቅዱስ ችግሩን እንድትቋቋም ሊረዳህ ይችላልን?
የወንጀለኝነት አስተሳሰብና ፍትሕ
በወንጀል ዓለም ውስጥ ሦስት መሠረታዊ ክፍሎች አሉ፤ እነርሱም ወንጀለኞች፣ ፖሊስና ወንጀል የሚፈጸምባቸው ሰዎች ናቸው። አንተ ወንጀል ሊደርስብህ ይችላል? ታዲያ ወንጀልን ለመቋቋም ምን ያስፈልግሃል? ከእነዚህ ከሦስቱ ክፍሎች ውስጥ የአንዱን ሐሳብ ለማስለወጥ ትችላለህን? ለምሳሌ ወንጀለኛውን መለወጥ ትችላለህን?
ብዙ ወንጀለኞች ወንጀልን ቋሚ ሥራቸው አድርገውታል። እንደቀላል አኗኗር አድርገው መርጠውታል። ፍልስፍናቸው ‘ሌሎች ሠርተው ባገኙት መተዳደር ከቻልክ ለምን ትሠራለህ?’ የሚል ይመስላል። ዘራፊዎቹ አብዛኛው ተጠቂ ገንዘቡን ወይም ገንዘቧን ያለአንዳች ትግል እንደሚሰጡ ያውቃሉ። ተይዘው ወደ እስር ቤት ከመወሰድ የማምለጥ አጋጣሚያቸው ከፍተኛ ስለሆነ ወንጀል ጥቅም ያለው ሆኖ ይሰማቸዋል።
ከዚህም በላይ የፍርድ ቤት የክስ አያያዝ የተወሳሰበና ጊዜ የሚፈጅ ነው። በብዙ አገሮች ያሉት ፍርድ ቤቶች፣ ዳኞችና እሥር ቤቶች ጥቂት ናቸው። የወንጀለኛው የክስ ፋይል ለፍርድ ቤቶች በጣም ይበዛባቸዋል። ፍርድ ቤቶቹ ቶሎ ውሳኔ ስለማይሰጡ መጽሐፍ ቅዱስ ከሦስት ሺህ ዓመት በፊት የገለጸው የሚከተለው ሁኔታ ይታያል፦ “በክፉ ሥራ ላይ ፈጥኖ ፍርድ አይፈረድምና ስለዚህ በሰው ልጆች ውስጥ ልባቸው ክፉን ለመሥራት ጠነከረ።” ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ሥርዓት እንደሚያመለክተው የወንጀለኞችን ቁጥር በመቀነስ ወይም የወንጀለኞችን አስተሳሰብ በመለወጥ መፍትሔ ሊገኝ ስለመቻሉ ያለው ተስፋ በጣም አነስተኛ ነው።—መክብብ 8:11
ሁለተኛው የወንጀል ዓለም ክፍል የሆነው ፖሊስስ? ፖሊሶች ሁኔታውን በቁጥጥር ሥር እንደሚያውሉት ተስፋ አለን? እነሱ ራሳቸው የሚሰጡት መልስ እንደሚከተለው ነው፦ ሕጉ በአመዛኙ ለወንጀለኛው መብት የሚሰጥ በመሆኑ፣ ሕሊናቸው የማይወቅሳቸው ጠበቆች ጥፋተኛውን ለማስለቀቅ ሕግን እንደፈለጉ ስለሚጠመዝዙት፣ ኅብረተሰቡም የእስር ቤቶችን ቁጥርና መጠን ከፍ ለማድረግ የሚያስፈልገውን ከፍተኛ ወጭ ለመሸፈን ፈቃደኛ ስለማይሆንና የፖሊሶች ቁጥር አነስተኛ በመሆኑ መጠኑ እጅግ ከፍተኛ የሆነውን የወንጀል አድራጎት ለመግታት ምንም ማድረግ አይቻልም።
እንግዲህ አሁን የሚቀረው ክፍል ወንጀል የሚፈጸምበት ሕዝብ ነው። ይህንን ሥርዓተ አልበኛ የሚመስል ሁኔታ በተሻለ መንገድ ታግለን ራሳችንን ለመርዳት ማድረግ የምንችለው ነገር ይኖራልን?
ተግባራዊ ጥበብና አስተዋይነት
የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የምሳሌ መጽሐፍ እንደሚከተለው ይናገራል፦ “መልካም ጥበብና ጥንቃቄን ጠብቅ ለነፍስህም ሕይወት ይሆናሉ። ለአንገትህም ሞገስ። የዚያን ጊዜ መንገድህን ተማምነህ ትሄዳለህ። እግርህም አይሰናከልም።” ይህ ምክር አንድን ሰው የወንጀል ተጠቂ ሊያደርጉት በሚችሉ ሁኔታዎች ላይ ይሠራል። ታዲያ በዚህ ረገድ ተግባራዊ ጥበብ ሊረዳን የሚችልባቸው አንዳንድ መንገዶች ምንድን ናቸው?—ምሳሌ 3:21-23
ወንጀለኞች እንደ ነጣቂ አውሬ ያደባሉ። በቀላሉ ሊጠቃ የሚችለውን ይፈልጋሉ። በቀላሉ ማጥቃት ከሚችሉት ሰው የፈለጉትን ነገር ማግኘት እስከቻሉ ድረስ ከሰው ጋር መታገልና መያዝ በሚችሉበት ሁኔታ ውስጥ መግባትን አይፈልጉም። ስለዚህ የሸመገሉ፣ የታመሙ፣ ለአካባቢው እንግዳ የሆኑና አደገኛ ሁኔታ መኖሩን ያላወቁ ሰዎችን ለማጥቃት ያደባሉ። ወንጀለኞቹ ለማጥቃት የሚያመቻቸውን ጊዜና ቦታ ይመርጣሉ። እዚህ ላይ ነው ተጠቂዎች ተግባራዊ ጥበብ ሊጠቀሙ የሚችሉት።
መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚገልጸው ክፋትን የሚወዱ ሰዎች ሥራቸውን የሚሠሩት በጨለማ ሽፋን ነው። (ሮሜ 13:12፤ ኤፌሶን 5:11, 12) ዛሬም ቢሆን በሰዎችና በንብረት ላይ ብዙ ወንጀሎች የሚፈጸሙት ማታ ማታ ነው። (ከኢዮብ 24:14፤ ከ1 ተሰሎንቄ 5:2 ጋር አወዳድር) ስለዚህ ጥበበኛ ሰው በተቻለ መጠን በአደገኛ አካባቢዎች በማታ ከመዘዋወር ይቆጠባል። በወንጀል በተወረረው የኒውዮርክ ከተማ ብዙ ሰዎች የሚዘረፉት ከመሸ በተለይ ደግሞ ከአራት ሰዓት በኋላ ወደ አፓርታማቸው ሲመለሱ መሆኑን ዕለታዊው የፖሊስ መዝገብ ያሳያል። ነጣቂዎቹ ንጥቂያዎቻቸውን ለማካሄድ ጭር ባሉት ጐዳናዎች ላይ ይሠማራሉ። ስለዚህ አውቶብስ ወይም ታክሲ ጠብቀህ መጓዝ ወይም በአደገኛ አካባቢ በእግርህ መሄድ አማራጮች ከሆኑ አውቶቡስ ወይም ታክሲ እስኪመጣ ድረስ ብትጠብቅ ይሻልሃል። አለበለዚያ የሚያጋጥምህ ነገር አሰቃቂ ሊሆን ይችላል።
አንድ ክርስቲያን ከምሽቱ በአራት ሰዓት አካባቢ አውቶብስ መጠበቅ ሲችል ጨለምለም ባለ ቦታ ጥቂት እንደተራመደ በአሰቃቂ ሁኔታ ተደበደበና ተዘረፈ። በጐዳናው ላይ ሌሎች ሰዎችም ነበሩ። ወንጀለኞቹ ግን ያልተጠራጠረውን አጠመዱት። ለንጥቂያ ዒላማ ሊሆን የሚችል ሰው በጐዳናው ላይ ሲያቀና አንዱ ለሌሎቹ ምልክት ሰጣቸው። ቃል ሳይተነፍሱ ተጠቂውን ደበደቡትና ዘረፉት። ዝርፊያው በጣም ፈጣን ከመሆኑ የተነሣ በአካባቢው የነበረው ሰው እንኳን ጣልቃ ለመግባት ጊዜ አልነበረውም። ተጠቂው በኋላ “ለወደፊቱ አውቶቡስ እጠብቃለሁ” በማለት ጥፋቱን አምኗል።
በቻርልስ ዲክንስ ኦሊቨር ትዊስት የተሰኘው ልብ ወለድ መጽሐፍ የተገለጸው አጭበርባሪ ወጣት ኪስ አውላቂ በአሁኑ ጊዜ በጐዳናው ላይ ላሉት ወንጀሎች መጥፎ ምሳሌ ነው። የዛሬዎቹ ሌቦችና ዘራፊዎች ከዚያ አጭበርባሪ ኪስ አውላቂ የተለዩ ናቸው። ዕድሜ ሳይለይ ጠመንጃ ወይም ጩቤ ይይዛሉ፤ ይጠቀሙበታልም። መንገድ የጠፋው አገር ጐብኚ፣ እንግዶችና ግርግር በበዛበት ከተማ ውስጥ ዙሪያ ገባውን የሚቃኙ ሰዎች ለእነዚህ ይሉኝታ ቢስ ወንጀለኞች ቀላል ዒላማዎች ናቸው። ዓይንህን አንዴ ሳትጨፍን እነርሱ የተገኘውን ነገር ይሠርቃሉ። የሌባን ልብ ምት የሚጨምረው ነገር ምን ሊሆን ይችላል? በሚታይ ሁኔታ የወርቅ ሰንሰለት ወይም ውድ ጌጥ አድርጎ መሄድ ሊሆን ይችላል። ወይም በአገር ጐብኚ አንገት ላይ የተንጠለጠለ ካሜራ ሊሆን ይችላል። “ኑና ንጠቁኝ” የሚል ምልክት እንደመሄድ ያህል ነው። ስለዚህ ጥንቃቄ ያስፈልጋል። ማንኛውንም ጌጣ ጌጥ ደብቁ፤ ካሜራችሁንም ግልጽ ባልሆነ መንገድ ለምሳሌ ከገበያ የተገዛ ዕቃ በምትይዙበት ቦርሳ ውስጥ ያዙት። ይህ ተግባራዊ ጥበብ ነው።
ወንጀልን ለመቋቋም ሌላው መንገድ ንቁ መሆን ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “የጠቢብ ዓይኖች በራሱ ላይ ናቸው። ሰነፍ ግን በጨለማ ይሄዳል” በማለት ይናገራል። (መክብብ 2:14) ይህን ማስጠንቀቂያ በወንጀል ችግር ላይ በሥራ መተርጐም አንድን ሰው ያለ አንዳች ዓላማ በመንገድ ላይ የሚንቀዋለሉ ሰዎችን በጥርጣሬ እንዲመለከት ያደርገዋል። የእግር መንገዱን ይዘህ ስትሄድ ከኋላህ መጥተው ቦርሳህን ሊነጥቁህ ከሚችሉ ሌቦች ጠንቀቅ በል። አንዳንዶች ብስክሌት እየነዱ ከሚጋፉ ሰዎች ንብረት ነጥቀው ስለሚበሩ በተለይ ማንኛውም ዓይነት የልብስ ሻንጣ ወይም የእጅ ቦርሳ ይዘህ በእግረኛ መንገዱ ጠርዙን ይዘህ አትሂድ። ከብዙ ሰዎች ጋር በቂ ብርሃን ባለበት መሄድ ለአደጋ ከመጋለጥ ይጠብቅሃል። ተሳፋሪ በሌላቸው ታክሲዎች አትሂድ። ሌቦች ሰው እንዲያያቸውና ማንነታቸውን ለይቶ እንዲያውቅ አይፈልጉም።
ሰዎች ስለ ወንጀል ይበልጥ ጠንቃቆች ቢሆኑ ብዙውን ጊዜ ሊወገድ የሚችለው ሌላ የተስፋፋ ወንጀል ደግሞ ቤት ሰብሮ መግባት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “እንደ ሌባ በመስኰት ይገባሉ” የሚለውን ማነጻጸሪያ መጠቀሙ ትክክል ነው። (ኢዩኤል 2:9) ተግባራዊ ጥበብ አንድ ሰው በሩን ወይም መስኰቱን ሳይቀረቅር እንዳይተው ያስገድደዋል። ችግር ከተፈጠረ በኋላ መፍትሔ ከመፈለግ ችግሩን መከላከሉ ይሻላል የሚለው አባባል ምን ጊዜም እውነት ነው። ተጨማሪ ገንዘብ አውጥተህ ቤትህን ማጠናከርህ ስርቆትንና አካላዊ ጉዳትን ለመከላከል ዋስትና ነው።
ብትዘረፍስ?
አዎን፣ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ሁሉ ብታደርግም በአንድ ዘራፊ ቁም ብትባልስ? ላለመሸበር ወይም የችኰላ እንቅስቃሴ ላለማድረግ ሞክር። ሌባው ራሱም ሊደነግጥና አንተ የምታደርገውን እንቅስቃሴ በተሳሳተ ሁኔታ ሊተረጉመው እንደሚችል አስታውስ። ሰውዬው ወይም ሴትየዋ የሚፈቅዱልህ ከሆነ ለመናገርና ለማግባባት ሞክር። (አዎን አጥቂህ ሴትም ልትሆን ትችላለች።) አንዳንድ ጊዜ ዘራፊዎቹ እያጠቁ ያሉት ምንም ክፋት የሌለበትን አንድን እውነተኛ ክርስቲያን መሆኑን ሲያውቁ ለዝበዋል። ምላሹ ምንም ይሁን የሚፈልጉት ገንዘብህን ወይም ንብረትህን ብቻ ከሆነ ለመከላከል አትሞክር። የሚጠየቀውን ሁሉ ስጥ። መጽሐፍ ቅዱስ የሰውየው ሕይወት ከማንኛውም ንብረቱ እንደሚበልጥ ያስተምራል።—ከማርቆስ 8:36 ጋር አወዳድር።
በጣም ተጠግተህ በጥንቃቄ የምትመረምር ሳትመስል ዘራፊው ባለባበስ ይሁን ወይም በአካላዊ መልኩ ያለውን ልዩ መለያ ባሕርይ ለማስተዋል ሞክር። አነጋገሩ ምን ዓይነት ነው? አብዛኞቹ ወንጀለኞች የግል የወንጀል አፈጻጸም ዘዴያቸው አንድ ዓይነት በመሆኑ በቀላሉ ሊታወቁ ስለሚችሉ ከላይ የተጠቀሱት ሁሉ ዝርዝሮች ለፖሊስ በምትነግርበት ጊዜ ጠቃሚ ሊሆኑ ይችላሉ።
ለራስህ መከላከያ መሣሪያ መያዝስ? ያለ አንዳች ጥርጥር መሣሪያ መያዝ ለክርስቲያን ጥበብ አይደለም። ዘራፊው መሣሪያህን እያወጣህ እንዳለህ ከመሰለው አንተን ከመጉዳት ወይም ከመግደል አያመነታም። ከዚህም በላይ ለአመጽ መልሶ ማጥቃት ከታጠቅህ “ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ሥርዓት እንዴት ልትከተል ትችላለህ?—ሮሜ 12:18
ምንም ዓይነት ጥንቃቄ ብታደርግም አንድ ቀን ተጠቂ እንደማትሆን ዋስትና የለም። ወንጀል በበዛባቸው ከተሞች ባልሆነ ሰዓትና ባልሆነ ቦታ መገኘትህ ለጥቃቱ በቂ ነው። ከቅርብ ጊዜ በፊት በኒውዮርክ ውስጥ አንድ የሕግ ጠበቃ አንድ ስኒ ቡና ለመግዛት ከቢሮው ወጣ። ወደ መደብሩ ሲገባ የሆኑ ወጣቶች መጡና በዙሪያው መተኰስ ጀመሩ። የሕግ ጠበቃው ራሱ ላይ በጥይት ተመትቶ ሞተ። “በጊዜና በአጋጣሚ” ምክንያት ሕይወቱን አጣ። እንዴት የሚያሳዝን ነገር ነው! በአሁኑ ጊዜ ዓለምን እያጥለቀለቀ ላለው የወንጀል ጐርፍ ዘላቂ መፍትሔ ይመጣል የሚል ተስፋ አለን?—መክብብ 9:11
ወንጀል የሚያቆምበት ጊዜ
ከሁለት ሺህ ዓመታት በፊት ኢየሱስ ከቀደሙት ትውልዶች ይልቅ አስፈሪ የሆኑ ሁኔታዎችን የሚያይ ትውልድ እንደሚመጣ ትንቢት ተናግሮ ነበር። በሺህ ሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በቴሌቪዥንና በፈጣን መገናኛዎች አማካኝነት በአካባቢያቸው የዜና ማስተላለፊያዎች ላይ ግፍና ጭካኔዎች በእውን ሲፈጸሙ ይመለከታሉ። ዓለም እንደ አንድ መንደር ሆናለች። ስለዚህ የዓለም ዜና ወዲያው የአካባቢ ዜና ይሆናል። በዚህም ምክንያት እውነታው በየዕለቱ በቤት ላይ ያቃጭላል። ኢየሱስ እንደተነበየውም ብዙ ሰዎች “ከፍርሃትና በዓለም የሚመጣበትን ከመጠበቅ የተነሣ ይደክማሉ።”—ሉቃስ 21:26
ኢየሱስ ከ1914 ጀምሮ የተፈጸሙትንና “የዚህ ሥርዓት መደምደሚያ” ዋዜማ የሆኑትን ድርጊቶች ከሩቅ አይቷል። (ማቴዎስ 24:3-14) ይሁን እንጂ እንዲህም ብሏል፦ “ይህ ሁሉ መሆኑን ስታዩ የእግዚአብሔር መንግሥት እንደቀረበች እወቁ።” (ሉቃስ 21:31) ያም ማለት የአምላክ የጽድቅ አገዛዝ በቅርቡ ምድርን አስደናቂ በሆነ መንገድ ይነካል ማለት ነው።—ማቴዎስ 6:9, 10፤ ራእይ 21:1-4
በዚያ አገዛዝ ሥር የምድርን ገነታዊ ሁኔታዎች የሚካፈሉት ገሮች፣ ሰላማውያንና ለአምላክ ታዛዦች የሆኑ ብቻ ናቸው። ወንጀለኞችና ክፉ አድራጊዎችስ ምን ይሆናሉ? “እንደ ሣር ፈጥነው ይደርቃሉና እንደለመለመ ቅጠልም ይረግፋሉ። ክፉ አድራጊዎች ይጠፋሉና [ይሖዋን (አዓት)] ተስፋ የሚያደርጉ ግን እነርሱ ምድርን ይወርሳሉ።” በዚያ የጽድቅ ሰማያዊ መንግሥት ሥር ሽብርም ሆነ ወንጀል አይኖርም።—መዝሙር 37:2, 9
ስለዚህ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ የሠላምና ዘለቄታዊ የዓለም መንግሥት ተስፋ ይበልጥ ለማወቅ ከፈለግህ የይሖዋ ምሥክሮችን በአቅራቢያህ ወይም በመንግሥት አዳራሻቸው አግኝተህ ጠይቃቸው። ያለምንም ክፍያ መጽሐፍ ቅዱስን እንድትማር በደስታ ይረዱሃል።
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
“ክፉ አድራጊዎች ይጠፋሉና [ይሖዋን (አዓት)] ተስፋ የሚያደርጉ ግን እነርሱ ምድርን ይወርሳሉ።”
[በገጽ 7 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ቻርልስ ዲክንስ የደረሰው ጥበበኛው ኪስ አውላቂ ከዘመናዊ ማጅራት መቺዎች ጋር ሲወዳደር ገና ያልሰለጠነ ነው
[ምንጮች]
Graphic Works of GEORGE CRUIKSHANK, by Richard A. Vogler, Dover Publications, Inc.