በቤተሰብህ ሕይወት ውስጥ አምላክን በአንደኛ ቦታ አስቀምጠው
ባለፈው ርዕሰ ትምህርት መግቢያ ላይ የተጠቀሱት ባልና ሚስት ቦብና ጂን ወደ ፍቺ አልደረሱም። ከዚህ ይልቅ ችግራቸውን ከአንድ ክርስቲያን አገልጋይ ጋር ተወያዩበት። እርሱም በመሠረቱ ችግራቸው የተነሣው ጉልህ ልዩነት ካለው አስተዳደጋቸው መሆኑን ወዲያውኑ ተገነዘበ።
ለምሳሌም ያህል ቦብ የመጣው ከሠራተኛው መደብ ከሆነ ቤተሰብ ሲሆን ራሱም የጉልበት ሥራ ይሠራ ነበር፤ ስለዚህ ጠዋት ጠዋት ደንበኛ ቁርስ እንዲቀርብለት ይፈልጋል። የቢሮ ሥራ ከሚሠሩ ቤተሰብ የመጣችው ጂን ደግሞ ጠዋት ቡናና ዳቦ ብቻ ታቀርብለታለች። ስለዚህ በቁርስ ጉዳይ ላይ የተነሣው ጭቅጭቅ ተጧጡፎ አጠቃላይ ጦርነት ሆነ።
ቦብና ጂን የንግግር ግንኙነታቸውን ማሻሻል አስፈለጋቸው። ይሁን እንጂ ዋናው የጭንቀታቸው መነሻ ከዚህ በጣም የጠለቀ ነገር ነበር። አገልጋዩ “እርስ በርሳችሁ በ1 ቆሮንቶስ 13:4 ትተያያላችሁን?” ብሎ ጠየቃቸው። ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ እንዲህ ይነበባል፦ “ፍቅር ይታገሣል፣ ቸርነትንም ያደርጋል፤ ፍቅር አይቀናም፤ ፍቅር አይመካም፣ አይታበይም።” የሚቀጥለውም ቁጥር 1ቆሮ 13:5 ፍቅር“የማይገባውን አያደርግም፣ የራሱንም [ጥቅም ብቻ] አይፈልግም፣ አይበሳጭም፣ በደልን አይቆጥርም” ይላል። ጂንና ቦብ ይህንን ቃል እርስ በርስ ባላቸው ግንኙነት ላይ ሊሠሩበት ፈቃደኞች ሆኑ።
የእነዚህ ባልና ሚስት ችግሮች በተለይ መንፈሳዊ መፍትሔ የሚያስፈልጋቸው ነበሩ። ቦብና ጂን ከአምላክ ጋር ጥሩ ዝምድና ይዘው መቀጠል ስለሚፈልጉ ከሁሉም በላይ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በሥራ ላይ ማዋልና “[ይሖዋ (አዓት)] ቤትን ካልሠራ ሠራተኞች በከንቱ ይደክማሉ” የሚለውን ቃል መረዳት ያስፈልጋቸው ነበር። (መዝሙር 127:1) መዝ 127 ከቁጥር 3 እስከ 5 ቤተሰብን ከማነጽ ጋር የተያያዘ ሐሳብ ይዟል። በቤት ውስጥ ደስታን ለማስፈን የሚረዳው ትልቁ ነገር በቤተሰብ ኑሮ ውስጥ አምላክን በአንደኛ ቦታ ማስቀመጥ ነው።—ኤፌሶን 3:14, 15
አምላክን በአንደኛ ቦታ ማስቀመጥ ምን ማለት ነው?
አምላክን በቤተሰብ ሕይወት ውስጥ በአንደኛ ቦታ ማስቀመጥ “አብሮ የሚጸልይ ቤተሰብ በአንድነት ይቆያል” ከሚለው አባባል የበለጠ ነገር ማድረግን የሚጠይቅ ነው። የቤተሰብ ግንኙነት የተባለው መጽሔት በገለጸው መሠረት ብዙ ሰዎች “ሃይማኖት አዎንታዊና ጤናማ የሆነን የቤተሰብ የእርስ በርስ ግንኙነት ቀላል ያደርገዋል፤ አባሎቹ ከሕይወት የሚያገኙትንም እርካታ ከፍ ያደርገዋል” ብለው ብዙ ሰዎች ያምናሉ። ይሁን እንጂ ሃይማኖትን መከተል ለአምላክ አንደኛውን ቦታ ከመስጠት ጋር አንድ አይደለም። ብዙዎች ከአንድ ሃይማኖት ጋር የሚጣበቁት ልማድ ወይም የቤተሰብ ባሕል ስለሆነ አለዚያም ማኅበራዊ ጥቅም ስለሚያገኙበት ብቻ ነው። አምላክ በዕለት ተዕለት ኑሮአቸው ውስጥ ምንም ቦታ የለውም። ከሁሉም በላይ ግን “በአምላካችን ዓይን ሲታይ ንፁህና ያልረከሰ አምልኮት” የተባለው ሁሉም ሃይማኖት አይደለም።—ያዕቆብ 1:27
በቤተሰብ ሕይወታችን ውስጥ አምላክን በአንደኛ ቦታ ለማስቀመጥ እኛና ቤተሰባችን “በምድር ሁሉ ላይ ልዑል” የሆነውን ይሖዋን እርሱ ያወጣቸውን ብቃቶች በማሟላት ማምለክ ይኖርብናል። (መዝሙር 83:18) የአምላክ ልጅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲህ አለ፦ “ነገር ግን በእውነት የሚሰግዱ ለአብ በመንፈስና በእውነት የሚሰግዱበት ጊዜ ይመጣል አሁንም ሆኖአል፤ አብ ሊሰግዱለት እንደነዚህ ያሉትን ይሻልና፤ እግዚአብሔር መንፈስ ነው፣ የሚሰግዱለትም በመንፈስና በእውነት ሊሰግዱለት ያስፈልጋቸዋል።” (ዮሐንስ 4:23, 24) ይሖዋ አምላክን “በመንፈስ” ለማምለክ ለእርሱ የምናቀርበው ቅዱስ አገልግሎት በፍቅርና በእምነት ከተሞላ ልብ የመነጨ መሆን ይኖርበታል። (ማርቆስ 12:28-31፤ ገላትያ 2:16) ይሖዋን “በእውነት” ማምለክ ሐሰተኛ ትምህርቶችንና እምነቶችን መተውና በመጽሐፍ ቅዱስ ከተገለጸው ፈቃዱ ጋር እንድንስማማ ይጠይቅብናል። ሃይማኖታችን እርሱ ካወጣቸው ብቃቶች ጋር ካልተስማማ ለይሖዋ አምላክ አንደኛውን ቦታ ልንሰጠው አንችልም።a ከእነዚህ ብቃቶች አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው? እነርሱንስ በሥራ መተርጎሙ ቤተሰብህን ሊጠቅም የሚችለው እንዴት ነው?
ባል ለአምላክ አንደኛውን ቦታ ሲሰጥ
በ1 ቆሮንቶስ 11:3 ላይ መጽሐፍ ቅዱስ “ነገር ግን የወንድ ሁሉ ራስ ክርስቶስ፣ የሴትም ራስ ወንድ፣ የክርስቶስም ራስ እግዚአብሔር” ነው ይላል። ባል ከሆንክ በቤተሰብህ ውስጥ ዋነኛ ውሳኔ የማድረግ ኃላፊነት በአምላክ ተሰጥቶሃል። ሆኖም ይህ ለየትኛውም ባል ጨቋኝና አምባ ገነን እንዲሆን ፈቃድ አይሰጠውም።
መጽሐፍ ቅዱስ ባሎች ሚስቶቻቸውን የሚነካ ውሳኔ ሲያደርጉ ስሜታቸውን እንዲያውቁና ግምት ውስጥ እንዲያስገቡ ያበረታታቸዋል። (ከዘፍጥረት 21:9-14 ጋር አወዳድር) ቅዱሳን ጽሑፎች ‘እያንዳንዱ ለራሱ የሚጠቅመውን አይመልከት ለባልንጀራው ደግሞ እንጂ’ የሚል ማስጠንቀቂያ ለሁላችንም ይሰጡናል። (ፊልጵስዩስ 2:2-4) መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረታዊ ሥርዓት የሚያስጥስ እስካልሆነ ድረስ አንድ ክርስትያን ባል በአብዛኛው የሚስቱን ምርጫ ያስቀድማል። ለግል ሁኔታዋ አሳቢነት ስላለውም ከአቅሟ በላይ ብዙ ሃላፊነቶች ያልተጫኑባት መሆኑን ያረጋግጣል። ለምሳሌም ያህል በተለይ የመሥሪያ ቤት ሥራ ካላት በቤት ውስጥ ሥራዎች ይረዳታል።
ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፎአል፦ “ባሎች ደግሞ እንደ ገዛ ሥጋቸው አድርገው የገዛ ሚስቶቻቸውን ሊወዱአቸው ይገባቸዋል። የገዛ ሚስቱን የሚወድ ራሱን ይወዳል፤ ማንም የገዛ ሥጋውን የሚጠላ ከቶ የለምና፣ ነገር ግን . . . ክርስቶስ ደግሞ ለቤተ ክርስቲያን እንዳደረገላት ይመግበዋል ይከባከበውማል።” (ኤፌሶን 5:28, 29) ኢየሱስ ክርስቶስ የጉባኤውን አባሎች የሚይዘው በፍቅራዊ መንገድ ነው።
ሐዋርያው ጴጥሮስ ቀጥሎ የሰጠውም ምክር ሊታሰብበት የሚገባው ነው፦ “እናንተ ባሎች ሆይ፣ [ደካማ ዕቃን እንደምትይዙ አድርጋችሁ] ከሚስቶቻችሁ ጋር በማስተዋል አብራችሁ ኑሩ፤ ጸሎታችሁ እንዳይከለከል፣ አብረው ደግሞ የሕይወትን ጸጋ እንደሚወርሱ አድርጋችሁ አክብሩአቸው።” (1 ጴጥሮስ 3:7) አንድ ባል ሚስቱን ፍቅር በጎደለው መንገድ መያዙ ጸሎቱ እንዲከለከል ምክንያት መሆኑን ማወቁ ነገሩን በክብደት እንድንይዘው ሊገፋፋን አዎን፣ አንድ ሰው አምላክ ጸሎቱን እንዲሰማለትና እንዲመልስለት ከፈለገ ሚስቱን በፍቅር መያዝ ያስፈልገዋል።
አምላክን በአንደኛ ቦታ ማስቀመጥ አንድ አባት ከልጆቹ ጋር ያለውንም ግንኙነት ይነካል። መንፈሳዊ ደኅንነታቸው በጥልቅ ሊያሳስበው ይገባል። በአንድ በአሜሪካ ውስጥ በተደረገ ከፍተኛ ጥናት ላይ ግማሽ የሚሆኑት ወንድሞች ብቻ “በቅዱሳን ጽሑፎች ጥናት ወይም የውይይት ቡድኖች ተሳትፎ ማድረጉ” ‘ለቤተሰባቸው መንፈሳዊ እድገት በጣም ጠቃሚ ሆኖ’ እንዳገኙት ተናግረዋል። የቀሩት ግን “ሃይማኖታዊ ስብከቶችን በተመለከተ በሬድዮና በቴሌቪዥን የሚተላለፉትን ፕሮግራሞች እንደሚመለከቱና እንደሚያዳምጡ” ወይም ‘የሕይወትን ትርጉም ለማወቅ እንደሚያሰላስሉ’ ጠቅሰዋል።
ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ ለአባቶች “ልጆቻችሁን [በይሖዋ (አዓት)] ምክርና በተግሣጽ አሳድጓቸው እንጂ አታስቆጡአቸው” ይላል። (ኤፌሶን 6:4) በይሖዋ ምስክሮች መካከል አባቶች በቤተሰብ አምልኮ ረገድ ቤተሰባቸውን እንዲመሩ ይጠበቅባቸዋል። ዘወትር የቤተሰብ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን በመምራት፣ በክርስቲያን ስብሰባዎች ላይ በመገኘትና ከሌሎች ቅዱስ ጽሑፋዊ ብቃቶች ጋር በመስማማት እነዚህ ሰዎች በቤተሰባቸው ሕይወት ውስጥ ለአምላክ አንደኛውን ቦታ ይሰጡታል።
ሚስት ለአምላክ አንደኛ ቦታ ስትሰጥ
ሚስት ከሆንሽ ባልሽ የቤተሰብ ራስ በመሆን ተግባሩን ለማከናወን ሲጥር ድጋፍሽን በመስጠት አምላክን በአንደኛ ቦታ ልታስቀምጪ ትችያለሽ። መጽሐፍ ቅዱስ “ሚስቶች ሆይ፣ በጌታ እንደሚገባ ለባሎቻችሁ ተገዙ” ይላል። (ቆላስይስ 3:18) አንድ ወንድ ሐሳብ የማይሰጥና የማይቀበል ወይም ቤተሰቡን በአምልኮ ለመምራት ግድየለሽ ከሆነ ይህ አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል። ያም ሆነ ይህ ዘወትር ጉድለቱን ማጉላት ወይም ይባስ ብሎ እርሱን መዳፈርና ማንቋሸሽ የቤተሰቡን ችግር ያባብሰዋል።
ምሳሌ 14:1 እንዲህ ይላል፦ “ብልሃተኛ ሴት ቤትዋን ትሠራለች፤ ሰነፍ ሴት ግን በእጅዋ ታፈርሰዋለች።” በእውነት ጥበበኛ የሆነች ያገባች ሴት ለአምላክ አንደኛ ቦታ ለመስጠትና ‘ቤትዋን ለመስራት’ የምትችልበት አንዱ መንገድ ለባልዋ በመገዛት ነው። (1 ቆሮንቶስ 11:3) ‘በምላስዋ የርህራሄ ሕግ’ ስላለ ባልዋን ያለ አግባብ ከመንቀፍ ትቆጠባለች። (ምሳሌ 31:26) በተጨማሪም ውሳኔዎቹ እንዲሳኩ ጠንክራ ትሠራለች።
ያገባች ሴት ለአምላክ አንደኛ ቦታ ለመስጠት የሚያስችላት ሌላው መንገድ ታታሪ መሆን ነው። እርግጥ በመሥሪያ ቤት ተቀጥራ የምትሠራ ከሆነ ቤትዋን እንደምትፈልገው ለመንከባከብ የሚያስፈልገው ጊዜ ወይም ኃይል ላይኖራት ይችላል። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ “የቤትዋን ሰዎች አካሄድ በደህና ትመለከታለች፣ የሀኬትንም እንጀራ አትበላም” በማለት እንደሚናገርላት “ልባም ሚስት” ለመሆን ጥረት ልታደርግ ትችላለች።—ምሳሌ 31:10, 27
ከሁሉም በላይ አንዲት ሚስት በሕይወትዋ ውስጥ የአምላክን አምልኮ በአንደኛ ቦታ ማስቀመጥ ያስፈልጋታል። ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ይሖዋ ምስክሮች የመንግሥት አዳራሽ የሚመጡ ብዙ ሰዎች ልጆች ስላላቸው ንጽሕና አስተያየታቸውን ይሰጣሉ። በዚህ ረገድ አንዲት ሚስት የሚኖራት ድርሻ በጣም ከፍተኛ ነው። ሆኖም መንፈሳዊነቷን ለመጠበቅ በጸሎት፣ በጥናትና ለአምላክ በምታቀርበው አገልግሎት መትጋት ይኖርባታል።
ወጣቶች ለአምላክ አንደኛ ቦታ ሲሰጡ
አዶለሰንት ካውንስለር በተባለ ጽሑፍ ውስጥ የወጣ አንድ ርዕሰ አንቀጽ እንዲህ ይላል፦ “ልጆች ወላጆቻቸውን በቁጥጥራቸው ሥር ለማድረግ የሚያስችሏቸውን ዝንባሌዎችና ፍልስፍናዎች ወደ መፍጠር አዘንብለዋል። . . . በፍጥነት የሚገኝን ክብርና ሥጋዊ ሀብት በሚያበረታታና በሚያከብር ኅብረተሰብ የተከበቡ በመሆናቸው ወጣቶች ‘ሁሉንም ነገር አሁንኑ’ የሚል ዝንባሌ ይዘዋል።” ወጣት ከሆንክ የአንተም ዝንባሌ እንደዚህ ነውን?
ቆላስይስ 3:20 “ልጆች ሆይ፣ ይህ ለጌታ ደስ የሚያሰኝ ነውና በሁሉ ለወላጆቻችሁ ታዘዙ” ይላል። ይህንን ታዛዥነት እንደ መለኮታዊ ግዴታ አድርጎ የሚመለከት ወጣት ከወላጆቹ ጋር ይተባበራል። ለምሳሌ ያህል እነርሱ ከማይፈልጓቸው የትምህርት ቤት ጓደኞቹ ጋር በምሥጢር በመገናኘት ትእዛዛቸውን አያፈርስም፤ ወይም የፈለገውን አንድ ነገር ለማሳካት ሲል በተንኮል ከወላጆቹ አንዱን አግባብቶ እንዲደግፈው አያደርግም። (ምሳሌ 3:32) ከዚህ ይልቅ በሕይወቱ ውስጥ ለአምላክ አንደኛውን ቦታ የሚሰጥ ማንኛውም ወጣት ለፍቅራዊ የወላጅ አመራር የሚገዛ ይሆናል።
ምንጊዜም አምላክን በአንደኛ ቦታ አስቀምጡ
በቤተሰብ ክልል ውስጥ ያለን ቦታ ምንም ይሁን ምን በሕይወታችን ውስጥ አምላክን ልናስቀድምና ከእርሱ ጋር የተቀራረበ ግንኙነት ልንፈጥር እንችላለን። አንተና ቤተሰብህ ይህንን እያደረጋችሁ ነውን?
በእነዚህ “የመጨረሻ ቀኖች” ሁላችንም “አስጨናቂ ጊዜያት” መጥተውብናል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5) ሆኖም በመንፈሳዊ እየዳበሩ ለመሄድና ከዚህ የነገሮች ሥርዓት ፍጻሜ ለመትረፍ ይቻላል። (ማቴዎስ 24:3-14) ከትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ጋር የሚስማማ ነገር በማድረግ አንተና ቤተሰብህ ገነት በምትሆነዋ ምድር ላይ የዘላለም ሕይወት የማግኘት ተስፋ ሊኖራችሁ ይችላል። (ሉቃስ 23:43፤ ዮሐንስ 17:3፤ ራእይ 21:3, 4) ይህ ሊሆን የሚችለው ግን በቤተሰብህ ሕይወት ውስጥ ለአምላክ አንደኛውን ቦታ ከሰጠኸው ነው።
[የግርጌ ማስታወሻ]
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ልባም ሴት በባልዋ ትደነቃለች
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ባሎች በቤተሰቡ አምልኮ ቀዳሚ ሆነው እንዲመሩ መጽሐፍ ቅዱስ ያበረታታቸዋል