ለቤተሰብ ጭንቀት መንስዔው ምንድን ነው?
‘እርስዋ ሰነፍ ናት!’ በማለት ቦብ በንዴት ተናገረ። ‘የቤት ሥራ ጨርሶ አትችልም’ አለ።
‘ፈጽሞ እውነት አይደለም!’ በማለት ጂን መልስ ሰጠች። ‘ምንም ዓይነት ሙከራ ባደርግ በፍጹም አያደንቅም። እንደሱ ያለ ሰውን መንቀፍ የሚወድ ሰው አይቼ አላውቅም።’
በቦብና በጂን ሕይወት ውስጥ የጎደለው ነገር ምንድን ነው?a ያልጠናው ትዳራቸው ገና አራት ወሩ ቢሆንም ሊፈርስ ተቃርቦ ነበር። ሆኖም የእነርሱ ሁኔታ ልዩ አይደለም ምክንያቱም በትዳር ውስጥ ስምምነት እንደጠፋ ከልዩ ልዩ ቦታዎች የተገኙ ጥናቶች ያሳያሉ። በአሁኑ ጊዜ ባለሞያዎች በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ከሚደረጉት አዲስ ጋብቻዎች ግማሽ የሚሆኑት በፍቺ እንደሚያበቁ ይናገራሉ። በተመሳሳይም ከሌሎች ብዙ አገሮች የማያስደስቱ ዘገባዎች ይመጣሉ። ሆኖም ፍቺ የችግሩ አንድ ገጽታ ብቻ ነው። ብዛት ያላቸው ቤተሰቦች በተለያዩ ምክንያቶች ጭንቀት አለባቸው።
ቤተሰብ የሚጨነቅባቸው አንዳንድ ምክንያቶች
በቤተሰብ ውስጥ አስጨናቂ ሁኔታዎች ሲፈጠሩ ልጆች በከፍተኛ ደረጃ ይነካሉ። የኒውስ ዊክ መጽሔት እንዲህ ሲል ዘግቦአል፦ “ባለፈው አሥርተ ዓመት ውስጥ [በዩናይትድ ስቴትስ] ከተወለዱት ልጆች አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት 18 ዓመት ከመድረሳቸው በፊት እንጀራ እናት ወይም እንጀራ አባት ማየታቸው አይቀርም። በአሁኑ ጊዜ ከሚገኙት ልጆች ውስጥ ከአራቱ አንዱ በአንድ ወላጅ ብቻ ያደገ ነው። በዛሬው ጊዜ ከሚኖሩት ልጆች 22 በመቶ የሚሆኑት ከጋብቻ ውጭ የተወለዱ ናቸው። ከእነዚህም ውስጥ አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት ገና በአሥራዎቹ ዕድሜ ከሚገኙ እናቶች የተወለዱ ናቸው።”
ለቤተሰብ ጭንቀት መነሻ ምክንያት የሆነውን ከዚህ ጋር የተዛመደ ሌላ ነገር በመጥቀስ የልጆች አያያዝ ኤክስፐርት የሆኑት ጄ ፓትሪክ ጋነን እንዲህ ይላሉ፦ “በቅርብ ጊዜ የተደረጉ ጥናቶች በአሥር ሚልዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች በትክክል ጥሩ ሁኔታ ባልሰፈነባቸው ቤተሰቦች ውስጥ ያደጉ ናቸው፤ ይኸውም አመጽ፣ ከቅርብ ዘመድ ጋር የሚደረግ የጾታ ግንኙነት፣ ወይም በአልኮል ምክንያት የሚፈጠር ጩኸት በየዕለቱ በሚታይባቸው ቤተሰቦች ውስጥ ያደጉ መሆናቸውን አሳይቷል።” እንደነዚህ ያሉ ነገሮችን እያዩ ያደጉ ብዙ ልጆች ጎልማሳ በሚሆኑበት ጊዜ የቤተሰብ ጭንቀቶችን እንዴት እንደሚያስወግዱ ባያውቁ ምንም የሚያስደንቅ አይሆንም።
ሁኔታዎችን የሚያጠኑ አንዳንድ ሰዎች ለቤተሰብ ችግር መነሻው በኢንዱስትሪ በበለጸጉት አገሮች የተስፋፉት የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊና የስነ ምግባር ለውጦች እንደሆኑ ይናገራሉ። ለምሳሌ ያህል ብዛት ያላቸው ሴቶች ወደ ሥራው ዓለም መግባታቸው የቤት ውስጥ ተግባሮችን ማንና እንዴት መሥራት እንዳለበት መላ የሌለው ዝግጅት ማድረግን አስከትሏል። እናቶች በተረበሸ መንፈስ አስቸጋሪ የሆኑ የሥራ ዓይነቶችን እያጉረመረሙ ይሠራሉ፤ አባቶችም ያለ ፈቃዳቸው ከቤት ውስጥ ሥራ ጋር ይታገላሉ፤ ልጆችም በሕፃናት መዋያ ማዕከሎች ካለው ሕይወት ጋር በሐዘኔታ ራሳቸውን ያስተካክላሉ።
ብዙ ቤተሰቦች በዓለም ዙሪያ በሚገኙ አገሮች ውስጥ በከባድ ተጽዕኖ ሥር ይገኛሉ። አንድ በሥራ ላይ ያለ ወላጅ ይህንን “በማያቋርጥ የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ውስጥ ከመኖር” ጋር አወዳድሮታል። በቅርብ ጊዜ በተደረገ የሕዝብ አስተያየት መገምገሚያ ላይ ሐሳባቸውን ከሰጡት ውስጥ ግማሽ ያህል የሚሆኑት ‘የአሜሪካውያን ቤተሰብ ከ10 ዓመታት በፊት ከነበረው ይልቅ ዛሬ ብሶበታል’ ብለው መናገራቸው ምንም የሚያስደንቅ አይሆንም። ሁኔታው እየተሻሻለ ይሄዳል ብለው የሚያምኑ እምብዛም የሉም።
በዚህም ምክንያት የቤተሰብ ጭንቀት በቴሌቪዥንና በራዲዮ የዘወትር የመወያያ ርዕስ ሆኗል። ሕዝቡም ቤተሰብን በተመለከተ የተዘጋጁ ራስን በራስ ለመርዳት የሚረዱ መጽሐፎችን ያነባል። ከእነዚህ መጻሕፍት አንዳንዶቹ በመጠኑ ጥልቅና ተግባራዊ የሆነ ምክር ይሰጣሉ። ‘ይበልጥ በግልጽ መወያየት’ ወይም ‘ስሜትን መገላለጥ’ ጠቃሚ ስለመሆኑ ምክር ቢሰጥም ዋናውን የቤት ውስጥ ጭንቀት መነሻ የሚገልጽ አይደለም። የሚቀጥለው ርዕሰ ትምህርት ይህንና የቤተሰብ ችግርን እንዴት ማሸነፍ እንደሚቻል ያሳያል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ምሥጢር ለመጠበቅ ሲባል ስማቸው ተቀይሯል