አዲስ ዓለም በቅርቡ ይመጣል!
የፖለቲካ ሰዎች በእነርሱ ጥረት ስለሚመጣ አዲስ የዓለም ሥርዓት ብዙ ተናግረዋል። ዓለምን ከፍርሐት ስለ ማላቀቅና በሕዝቦችና በመንግሥታት መካከል ትብብር እንዳይኖር እንቅፋት የሚሆኑትን ነገሮች ስለማስወገድ ይናገራሉ። ይሁን እንጂ አዲስ ዓለም የመምጣቱና ያለመምጣቱ ጉዳይ በሰዎች ላይ የተመካ ነውን?
ሰዎች ሰላምና አስተማማኝ ሕይወት የሰፈነበት ዓለም ለመመሥረት በብዙ መቶ ለሚቆጠሩ ዓመታት ደክመዋል። እንዲህ ዓይነቶቹን ሙከራዎች ያደረጉት ብዙዎችም በሙሉ የልብ ቅንነት ተነሣስተው እንደነበረ አያጠራጥርም። እንዲህ ዓይነት ግቦቻቸውን ለመፈጸም ሰዎች ምንም ዓይነት የአስተዳደር መዋቅሮችን ቢያመነጩም “ለሚራመደው ሰው አካሄዱን ማቅናት አልተሰጠውም” የሚሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት እውነት መሆናቸው ተረጋግጦአል።—ኤርምያስ 10:23
አዲስ ዓለም እንደሚመጣ አምላክ ቃል ገብቷል
ሆኖም ይኸው በመንፈስ ቅዱስ መሪነት የተጻፈ የአምላክ ቃል አዲስ ዓለም እንደሚመጣ ዋስትና ይሰጣል። አሮጌው የነገሮች ሥርዓት ፍጻሜ እንደሚኖረው ከተነበየ በኋላ ክርስቲያኑ ሐዋርያው ጴጥሮስ “ጽድቅ የሚኖርባቸውን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እንደ ተስፋ ቃሉ እንጠብቃለን” በማለት ተናግሯል።—2 ጴጥሮስ 3:10-13
ይህስ የማን ተስፋ ቃል ነው? ‘በምድር ሁሉ ላይ ልዑል የሆነው’ ይሖዋ አምላክ እንጂ ሌላ ማንም የሰጠን ተስፋ አይደለም። (መዝሙር 83:18) ይሖዋ ሰዎች ያቃታቸውን ነገር ያከናውናል። አዎን፤ ይሖዋ አምላክ አዲስ ዓለም ያመጣል። ግን መቼ?
አዲስ ዓለም በጣም ቀርቧል!
የአምላክ የአዲስ ዓለም ተስፋ ሙሉ በሙሉ እውን ከመሆኑ በፊት ያሁኑ “ዓለም” ወይም “የነገሮች ሥርዓት” ወደ ፍጻሜው መምጣት አለበት። ይህን በሚመለከት የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀመዛሙርት “ንገረን ይህ መቼ ይሆናል? የመምጣትህና የዓለም ፍጻሜ ምልክቱ ምንድነው” በማለት ጠይቀውታል። (ማቴዎስ 24:3) ይበልጥ ትክክል የሆነው የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም እንዳስቀመጠው የኢየሱስ ተከታዮች “ንገረን፣ ይህ መቼ ይሆናል? የመገኘትህና የነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ ምልክቱ ምንድነው?” ብለው ጠየቁት።
መልስ ሲሰጥም ኢየሱስ በሰማያዊ መንግሥት ሥልጣኑ በመንፈሳዊ አካል በማይታይ ሁኔታ የመገኘቱን ምልክት ብዙ ገጽታዎች ተነበየ። (1 ጴጥሮስ 3:18) ለምሳሌ ያህል እንዲህ አለ፦ “ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣል። የምግብ እጥረትና የምድር መናወጥ በየሥፍራው ይሆናል።” “የምጥ ጣር” መጀመሪያ ከነበረው ከ1914 ጀምሮ ኢየሱስ ለይቶ ያመለከተውን “ይህ ትውልድ” የማይታየው የኢየሱስ መገኘት ምልክት ክፍል በመሆን ተከታታይ ጦርነት፣ የምግብ እጥረትና የምድር መናወጥ አጋጥሞታል።—ማቴዎስ 24:7, 8, 34
ይህን ትውልድ ከ1914 ጀምሮ ተወዳዳሪ በሌለው መንገድ ጦርነት አዋክቦታል። አንደኛው የዓለም ጦርነት ወደ 14 ሚልዮን የሚገመቱ ሰዎችን ሕይወት አጥፍቷል። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት 55 ሚልዮን ወታደሮችና ሲቪሎች ተገድለዋል። እንዲያውም ከ1914 ወዲህ ከ100 ሚልዮን በላይ ሰዎች በጦርነት ጠፍተዋል። በእርግጥም ይህ የኢየሱስን መገኘት የሚያሳየው ምልክት ክፍል ነው።
በኢየሱስ የተተነበዩት የምግብ እጥረቶችም ሁለቱንም የዓለም ጦርነቶች በየተራ በመከተል ብዙ አገሮችን አጥቅተዋል። ሳይንሳዊ መሻሻል ቢኖርም በአሁኑ ጊዜ የምድር አራተኛ እጅ እየተራበ ነው። በየዓመቱ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሕፃናትና ሌሎችም በምግብ ጉድለት ይሞታሉ። ዘ ወርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፔዲያ እንዲህ ይላል፦ “አብዛኞቹ የአፍሪካ፣ የእስያና የላቲን አሜሪካ ታዳጊ አገሮች ለሕዝቦቻቸው በቂ ምግብ የላቸውም። በእነዚህ አገሮች የሚኖሩ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ይራባሉ። በአንድ የሆነ ምክንያት የእህል ምርት ወይም ከውጭ ሀገር የሚገባ ምግብ ሲቀንስ ረሀብ ሊነሳና በሺዎች ወይም በሚልዮኖች የሚቆጠሩ ሕዝቦች ሊሞቱ ይችላሉ።”
“የፍጻሜው ዘመን” በጀመረበት በዚህ ትውልድ ልዩ ልዩ የምድር መናወጥ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕይወት አጥፍቶአል። (ዳንኤል 12:4) በምድር መናወጥ ምን ያህል ሰዎች እንደሞቱ የሚሰጠው ግምት ይለያያል። ይሁን እንጂ ከ1914 ጀምሮ በምድር መናወጥ መሞት በምድር ዙሪያ ተባብሷል። እነዚህም በብዙ መቶ ሺዎች የሚቆጠር ሕይወት አጥፍተዋል። ከእነዚህ በሁለቱ ብቻ ላይ ሐሳብ ሲሰጥ የጥቅምት 19, 1989 ዮርክሻየር ፖስት ጋዜጣ እንዲህ ብሏል፦ “በ1920 በቻይና በጂያንግሱ ክፍለ ሀገር የደረሰው የምድር መናወጥ 180,000 ሰዎችን ገድሏል። በሐምሌ 28, 1976ም ቻይና በዘመናዊ ታሪኳ ተወዳዳሪ የሌለው መናወጥ ደርሶባታል። ታንግሻን የምትባለው በሰሜናዊ ምሥራቅ የምትገኘው ከተማ በሪቸር መለኪያ መጠኑ 7.8 በሆነ የምድር መናወጥ በወደመች ጊዜ ቢያንስ 240,000 ሰዎች ሞተዋል።” ጋዜጣው በሃያኛው ምዕተ ዓመት የደረሱ ሌሎች 30 ታላላቅ የምድር መናወጦችን ዘርዝሯል።
የመንግሥት ስብከት ሥራም ከኢየሱስ የማይታይ መገኘት ምልክት ገጽታዎች እንደ አንዱ ሆኖ ተተንብዮአል። ጥያቄ ላቀረቡለት ደቀመዛሙርቱ “ለአሕዛብም ሁሉ ምሥክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል በዚያን ጊዜም መጨረሻው ይመጣል” በማለት ነገራቸው። (ማቴዎስ 24:14) ኢየሱስ እንደተነበየው ይህ የስብከት ሥራ በምድር ዙሪያ በ212 አገሮች ከ4,000,000 በላይ በሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች እየተካሄደ ነው።
እነዚህና ሌሎችም ትንቢቶች በዚህ ዘመን መፈጸማቸው በእርግጥም መጨረሻዎቹ ቀኖች እየኖርን እንዳለን ያረጋግጣል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5) ከፊታችን ቀርቦ ያለው ኢየሱስ ክርስቶስ የተነበየው “ታላቅ መከራ” ነው። ይህ ታላቅ መከራ ሁሉን በሚገዛው በአምላክ ታላቅ ቀን ላይ በሚሆነው የ“አርማጌዶን” ጦርነት ላይ ሲያከትም ለአሁኑ ክፉ የነገሮች ሥርዓት ፍጻሜውን ያመጣል። (ማቴዎስ 24:21፤ ራእይ 16:14-16) ከዚያም አምላክ የገባልን የአዲስ ዓለም ተስፋ እውን ይሆናል።a
ሰዎች ሊያመጡአቸው የማይችሉ በረከቶች
የፖለቲካ ሰዎች አዲስ የዓለም ሥርዓት እናመጣለን እያሉ ይኩራራሉ። ይሁን እንጂ የሰማይና የምድር አምላክ የሆነው ይሖዋ ያሁኑን ሥርዓት በአዲስ ዓለም እንዲተኩ ሰዎችን አልጠየቀም። ይህንንም ራሱ ብቻ በሚያውቀው ቀንና ሰዓት ላይ ያደርገዋል። (ማቴዎስ 24:34, 36) ሽማግሌው ሐዋርያው ዮሐንስ ሰው ሳይሆን አምላክ ሊያደርገው ያለውን ነገር አስቀድሞ አይቷል፦
“አዲስ ሰማይንና አዲስ ምድርንም አየሁ፤ ፊተኛው ሰማይና ፊተኛይቱ ምድር አልፈዋልና ባሕርም ወደፊት የለም። ቅድስቲቱም ከተማ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም ለባሏ እንደተሸለመች ሙሽራ ተዘጋጅታ ከሰማይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ስትወርድ አየሁ። ታላቅም ድምፅ ከሰማይ፦ እነሆ፣ የእግዚአብሔር ድንኳን በሰዎች መካከል ነው። ከእነርሱም ጋር ያድራል። እነርሱም ሕዝቡ ይሆናሉ። እግዚአብሔርም እርሱ ራሱ ከእነርሱ ጋር ሆኖ አምላካቸው ይሆናል። እንባዎችንም ከዓይኖቻቸው ያብሳል። ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም። ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም። የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና ብሎ ሲናገር ሰማሁ። በዙፋንም የተቀመጠው እነሆ፣ ሁሉን አዲስ አደርጋለሁ አለ። ለእኔም፦ እነዚህ ቃሎች የታመኑና እውነተኛዎች ናቸውና ጻፍ አለኝ።”—ራእይ 21:1-5
“አዲሱ ሰማይ” የኢየሱስ ክርስቶስ ሰማያዊ መንግሥት ነው። “አዲሲቱ ምድር” ሌላ ምድራዊ ሉል ሳትሆን የዘር፣ የብሔር ወይም የቋንቋ መከፋፈል የሌለበት ሁሉም የክርስቶስ መንግሥት ታዛዥ ተገዢዎች የሆኑ አዲስ የሰዎች ማኅበረሰብ ነው። (ከመዝሙር 96:1 ጋር አወዳድር) ያሁኑ ምሳሌያዊ ሰማይና ምድር ማለትም የዲያብሎስ የነገሮች ሥርዓት በዲያብሎስና በአጋንንቱ ቁጥጥር ስር ካሉት የአስተዳደር መዋቅሩ ጋር ይጠፋል። (1 ዮሐንስ 5:19) ቃል በቃል ባሕር ቢኖርም ዕረፍት የለሹን ክፉ የሰው ዘር ዓለም የሚያመለክተው ምሳሌያዊ ባሕር ያልፋል። የኢየሱስ ተባባሪ ሰማያዊ ገዥዎች አዲሲቱ ኢየሩሳሌም ይሆናሉ፤ ከኢየሱስ ጋር በመተባበር ጻድቁን ሰብአዊ ኅብረተሰብ የምትገዛውን እንደ ርዕሰ ከተማ ያለች ድርጅት ያቋቁማሉ። ታዛዦቹ የሰው ዘሮች በሺው ዓመት የፍርድ ቀን ወቅት በክርስቶስ አማካኝነት ከአምላክ ጋር ሙሉ በሙሉ እየታረቁ በሚሄዱበት ጊዜ አምላክ በወኪሉ አማካኝነት ከእነሱ ጋር ይሆናል።—ራእይ 14:1-4፤ 20:6
በመንግሥቱ አገዛዝ ስር ለመደሰት የሚያበቁ ብዙ ምክንያቶች ይኖራሉ። ከበሽታ፣ ከኀዘንና ከመሳሰሉት የሚመጣው ኀዘን፣ ጩኸትና ሥቃይ የቀድሞ ተሞክሮዎች ብቻ ይሆናሉ። ከመጀመሪያው ወላጃችን ከኃጢአተኛው አዳም ወደ ሰው ዘር ሁሉ የተዛመተው ሞትም እንኳ አይኖርም። (ሮሜ 5:12) ዓለም አቀፍ የፍርሃት መንሥኤ የሆነው ይህ ሞት ለዘላለም ሲቀር ምን ዓይነት ደስታ ይሰፍናል!
እነዚህን በረከቶች በሚመለከት ዋስትና የሰጠው ማንም ሟች የሆነ ሰው ሳይሆን አምላክ ራሱ ነው። “እነሆ ሁሉን አዲስ አደርጋለሁ” ያለው እርሱ ነው። አዎን፣ ይሖዋ አምላክ ሐዋርያው ዮሐንስን “እነዚህ ቃሎች የታመኑና እውነተኛዎች ናቸውና ጻፍ” ብሎ ነግሮታል።
የሚያስፈልጉንን መሠረታዊ ነገሮች በሙሉ እናገኛለን
አምላክ በሚያመጣው አዲስ ዓለም ውስጥ ምድር ውላ አድራ ገነት ትሆናለች። ኢየሱስ በጐኑ ለተሰቀለውና ልቡ ለተሰበረው ክፉ አድራጊ “ዛሬ እውነት እልሃለሁ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ” ብሎ ቃል ስለገባለት ይህ እርግጠኛ ነገር ነው። (ሉቃስ 23:43 አዓት) በገነታዊ ሁኔታዎች መሃል ምግብና መጠለያ የመሳሰሉት ሰብአዊ ፍላጐቶች ሙሉ በሙሉ ይሟላሉ።
የምግብ እጥረት ባሁኑ ጊዜ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት እያጠፉ ነው። የተራቡትን ለመመገብ የሚደረጉት ጥረቶች ምንም ያህል የሚያስመሰግኑና የላቁ ቢሆኑም ሰዎች እንዲህ ዓይነቶቹን ችግሮች እንዳያቃልሉ ስስትና ሌሎች ምክንያቶችም ያግዷቸዋል። ለምሳሌ ያህል የደቡብ አፍሪካ የጆሃንስበርግ ጋዜጣ ሳተርዴይ ስታር እንዲህ በማለት ዘግቧል፦ “ፖለቲካዊ ውዝግቦች፣ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪዎችና ፈጽሞ የማያልቁ ከሚመስሉት የአፍሪካ ውጊያዎች የተነሣ የሚመጣ መሰላቸት ተደማምረው እርዳታውን እያዘገዩት ነው። . . . በራብ በከፍተኛ ሁኔታ ከተመቱት አገሮች አንዷ በሆነችው በሱዳን ከ5 እስከ 6 ሚልዮን የሚደርሱ ሕዝቦች በ1991 ረሃብ ያጋጥማቸዋል።” በአምላክ አዲስ ዓለም ግን ረሃብ የተረሳ ጉዳይ ይሆናል። በመንግሥቱ አገዛዝ ስር “በምድር ላይ ብዙ እህል፣ በተራሮችም ላይ መትረፍረፍ ይሆናል።”—መዝሙር 72:16
መጠለያ በዘመናችን ለብዙዎች በበቂ ሁኔታ ሊሟላ ያልቻለ ሌላው ለሰው አስፈላጊ የሆነ ነገር ነው። በሚልዮን የሚቆጠሩ የሚኖሩት በደሳሳ ጐጆዎች ነው። ወይም ጭራሹን ቤት የላቸውም በኒው ዮርክ ታይምስ መሠረት በአንድ ምሥራቃዊ አገር “በአንድ የኤሌክትሮኒክ ኩባንያ የ20 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ሠራተኞች ቤት ለማግኘት 73 ዓመት የሚያስጠብቅ ምዝገባ ያጋጥማቸዋል። የመንግሥት ዘገባው አንዳንድ ሰዎች በመጋዘኖች፣ በቢሮዎች ወይም በመጸዳጃ ቤቶች መኖር ያለባቸው መሆኑን ያመለክታል።” በአዲሲቱ ዓለም ግን ሁኔታው እንዴት የተለየ ይሆናል! በመጪው ገነት “ቤቶችን ይሠራሉ፣ ይቀመጡባቸውማል፤ ወይንንም ይተክላሉ፣ ፍሬውንም ይበላሉ። ሌላ እንዲኖርበት አይሠሩም። ሌላም እንዲበላው አይተክሉም። የሕዝቤ ዕድሜ እንደ ዛፍ ይሆናልና እኔም የመረጥኋቸው በእጃቸው ሥራ ረጅም ዘመን ደስ ይላቸዋልና።”—ኢሳይያስ 65:21, 22
በምድር ላይ ያሉ ሕይወት ያላቸው ነገሮች እርስ በርሳቸውና ከአካባቢያቸው ጋር ያለውን ዝምድና በሚመለከት የተፈጠሩት ችግሮችም ቢሆኑ አምላክ ቃል በገባው አዲስ ዓለም አይኖሩም። ለሕይወት አስጊ የሆነና ሰብል አጥፊ የሆነው የአየር መበከል አይኖርም። ባሁኑ ጊዜ የበርካታ ዕፅዋትንና እንስሳትን ሕይወት አደጋ ላይ የጣለው የአካባቢ መበከልና የመኖሪያ ቤቶቻቸው መደምሰስ ያን ጊዜ ምንም አስጊ አይሆንም። እንደ ኦዞን ንብርብር መሳሳት የመሳሰሉት ነገሮች ያኔ በምድር ላይ ያለን ሕይወት አደጋ ላይ አይጥሉም። ይሖዋ አምላክ እነዚህን ችግሮች እንደሚፈታቸው እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን ምክንያቱም ቃሉ በቅርብ ጊዜ ውስጥ “ምድርን የሚያጠፉትን እንደሚያጠፋ” ስለሚያረጋግጥልን ነው።—ራእይ 11:18
በአዲሲቱ ዓለም ውስጥ ጦርነት ጊዜ ያለፈበት ነገር ይሆናል። ይህ የሚሆነው ግን የፖለቲካ ሰዎች መንግሥታትን ትጥቅ ማስፈታት ስለሚሳካላቸው አይደለም። ከዚህ ይልቅ አምላክ የፖለቲካ መሪዎች ማድረግ የሚሳናቸውን ስለሚያደርግ ነው። ከእነዚህ የመዝሙራዊው ቃላት ጋር በመስማማት ለታዛዦቹ የሰው ዘሮች ሰላምን ያመጣላቸዋል፦ “[የይሖዋን (አዓት)] ሥራ በምድር ያደረገውንም ተአምራት እንድታዩ ኑ። እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ጦርነትን ይሽራል። ቀስትን ይሰብራል ጦርንም ይቆርጣል። በእሳትም ጋሻን ያቃጥላል።” (መዝሙር 46:8, 9) አምላክ አመጣዋለሁ ብሎ ቃል በገባለት አዲስ ዓለም ውስጥ ሕዝቦች እውነተኛ ሰላም ያገኛሉ፤ ደኅንነታቸውም አስተማማኝ ይሆናል እንጂ አይዋጉም።—ሚክያስ 4:2-4
እዚያ ትኖር ይሆን?
ይሖዋ አምላክ ቃል የገባው አዲስ ዓለም እንደሚመጣ ትምክህት ሊያድርብህ ይችላል። እርሱ አይዋሽም። (ዕብራውያን 6:17, 18) ቃሉ መጽሐፍ ቅዱስ እውነት ነው። ተስፋ የሰጣቸው ነገሮችም ይፈጸማሉ።—ዮሐንስ 17:17
ለታዛዥ የሰው ዘሮች የሚሆን አስደናቂ በረከቶች የምሥራች ነው የይሖዋ ምስክሮች ቅን ልብ ካላቸው ሰዎች ጋር ለመካፈል የሚጥሩት። እናንተም አሁኑኑ ስለ መለኮታዊ ዓላማዎች እውቀት ለማግኘት ጥረት ማድረግና በቅዱስ ጽሑፎቹ ውስጥ በሚገኙት አስደናቂ ተስፋዎች ላይም እርምጃ መውሰድ አለባችሁ። ይህ አካሄድ ፍጻሜ ወደሌለው ሕይወት ሊመራ ይችላል ምክንያቱም ኢየሱስ “እውነተኛ አምላክ ብቻ የሆንህ አንተን የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት” ብሏል። (ዮሐንስ 17:3) እንግዲያው ወደፊት በሚመጡት የደስታ ጊዜዎች የመካፈል መብት ሊኖርህ ይችላል፤ የአምላክ አዲስ ዓለም ቀርቧልና!
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ በተባለው በመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስና የትንንሽ ጽሑፎች ማህበር የታተመውን መጽሐፍ ምዕራፍ 17 እና 18ን ተመልከቱ።