የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w91 8/15 ገጽ 13-18
  • የይሖዋ ጥሩነት ብዛት

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • የይሖዋ ጥሩነት ብዛት
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የአምላክ ጥሩነት
  • በፍጥረት ላይ የታየው ጥሩነት
  • የሰው ልጅ መውደቅና መዳን
  • የአምላክ ጥሩነት በዘመናችን
  • ይሖዋ—ከሁሉ የላቀው የጥሩነት ምሳሌ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2002
  • “ጥሩነቱ ምንኛ ታላቅ ነው!”
    ወደ ይሖዋ ቅረብ
  • ጥሩነት—እንዴት ልታዳብረው ትችላለህ?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2019
  • ምንጊዜም ጥሩነት አሳዩ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2002
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
w91 8/15 ገጽ 13-18

የይሖዋ ጥሩነት ብዛት

“ለሚፈሩህም የሰወርሃት፣ ቸርነትህ (ጥሩነትህ (አዓት)) እንደምን በዛች!”​—መዝሙር 31:19

1, 2. (ሀ) ይሖዋ ከረጅም ጊዜ በፊት ምን ታላቅ ሥራ አከናውኖ ነበር? (ለ) ይሖዋ የፍጥረት ሥራዎቹን ውጤት የገለጸው እንዴት ነበር?

አምላክ ‘ሰማይን እንደ ዙፋኑ ምድርን ደግሞ እንደ እግሩ መቀመጫ አድርጎ’ መፍጠር የጀመረበት አንድ ወቅት ነበር። (ኢሳይያስ 66:1) መለኮታዊው መዝገብ ይህ የሆነው መቼ እንደሆነ አይገልጽም። በአጭሩ፦ “በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ” ይላል። (ዘፍጥረት 1:1) ፍጥረት በተፈጠረበት ጊዜ በብዙ ሚልዮኖች የሚቆጠሩ ጋላክሲዎች ወይም የከዋክብት ረጨቶች ተሠርተው ነበር። ብዙዎቹ ጋላክሲዎች በብዙ ሺህ ሚልዮኖች የሚቆጠሩ ከዋክብትን የያዙ ናቸው። ከእነዚህ ጋላክሲዎች በአንዱ የውጨኛ ጫፍ ላይ ከእርስዋ ጋር ሲነፃፀሩ በመጠናቸው አነስተኛ የሆኑ ጥቁር ክብ አካሎች የሚዞሩአት አንድ ደማቅ ኮከብ አለች። ከእነዚህ ክብ አካሎች መካከል አንድዋ ምድር ተብላ ተጠርታለች። ከታላላቆቹ አንፀባራቂ ከዋክብት ጋር ስትነፃፀር ምድር በጣም አነስተኛ ናት። ሆኖም ይሖዋ የእግሩ መረገጫ እንድትሆን ያሰባት ይህችን አካል ነው።

2 ይሖዋ የመፍጠር ችሎታው ምድር ወደተባለችው ፕላኔት እንዲያተኩር አደረገ። በስድስት ረጅም የፍጥረት “ቀናት” ጊዜ ውስጥ ይህች ትንሽ ጨለማ አካል ስትለወጥ “ከፍጥረት ሁሉ በፊት በኩር” የሆነው ጥበበኛ ሠራተኛ ከጎኑ ነበር። በምሳሌያዊ ሁኔታም ለአምላክ እግር ተስማሚ ማረፊያ ቦታ ሆነች። (ቆላስይስ 1:15፤ ዘፀዓት 20:11፤ ምሳሌ 8:30) አምላክ የማሰብ ችሎታ ያለው አዲስ ዓይነት ሕይወት ማለትም የሰውን ዘር ለማስቀመጥ ያቀደው እዚህ ነበር። በምድር ላይ ከሚገኙ ንጥረ ነገሮች የተፈጠሩት የመጀመሪያዎቹ ሰብዓውያን ባልና ሚስት ውብ በሆነ ገነታዊ አካባቢ እንዲኖሩ ተደረጉ። (ዘፍጥረት 1:26, 27፤ 2:7, 8) የዚህ አስደናቂ የፍጥረት ሥራ የመጨረሻ ውጤት በጣም ፍጹምና ውብ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ በስድስተኛው የፍጥረት ቀን የመጨረሻ ክፍል ላይ አምላክ የተሰማውን ስሜት እንዲህ በማለት ይገልጻል፦ “አምላክ የሠራውን ሥራ ሁሉ ተመለከተ፤ እነሆ በጣም ጥሩ ነበር።”​—ዘፍጥረት 1:31 አዓት

የአምላክ ጥሩነት

3. በፍጥረት ውስጥ የተገለጠው የትኛው የአምላክ ከፍተኛ ባሕርይ ነው?

3 ከብዙ ሺህ ዓመታት በኋላ የእነዚያ የመጀመሪያዎቹ ሰብዓውያን ባልና ሚስት ዘር የሆነ አንድ ሰው የፍጥረትን ጊዜ በማስታወስ እንዲህ ሲል ጻፈ፦ “[የአምላክ] የማይታየው ባሕርይ እርሱም የዘላለም ኃይሉ ደግሞም አምላክነቱ ከዓለም ፍጥረት ጀምሮ ከተሠሩት ታውቆ ግልጥ ሆኖ ይታያልና።” (ሮሜ 1:20) አዎን እጅግ የላቀው የምድር ውበትና በእርስዋ ላይ የሚኖሩት ፍጥረቶች የአምላክ የማይታዩ ባሕርያት፣ የአምላክ ጥሩነት ጭምር አስደናቂ ነፀብራቅ ናቸው። እንግዲያው አምላክ የፈጠረው ነገር ሁሉ ጥሩ እንደሆነ መናገሩ ምንኛ ተገቢ ነው!​—መዝሙር 31:19

4, 5. ጥሩነት ምንድን ነው?

4 ጥሩነት በገላትያ 5:22 ላይ ሐዋርያው ጳውሎስ እንደገለጸው ስድስተኛው የአምላክ መንፈስ ፍሬ ነው። ቀደም ብለው በወጡት የመጠበቂያ ግንብ መጽሔቶች ላይ የመንፈስ ፍሬዎች የተመዛዘነ ክርስቲያናዊ ባሕርይ በመኮትኮት ረገድ ያላቸውን አስፈላጊነት በመግለጽ የመጀመሪያዎቹ አምስት የመንፈስ ፍሬዎች ተብራርተው ነበር።a ጥሩነትም ሊዘነጋ የማይገባው አስፈላጊ ባሕርይ ነው። አሁን የምናተኩረው በዚህ ባሕርይ ላይ ነው።

5 ጥሩነት ምንድን ነው? ጥሩ የመሆን ባሕርይ ወይም ሁኔታ ነው። የላቀ ወይም ከፍተኛ የሆነ የስነ ምግባር ደረጃ ወይም የሥነምግባር ጥራት ነው። ስለዚህም ለሌሎች ጥሩና ጠቃሚ ሥራዎችን በመሥራት የሚገለጥ ገንቢ ጠባይ ነው። ይህንን ተወዳጅ ጠባይ ልናሳይ የምንችለው እንዴት ነው? በመሠረቱ ይሖዋን በመምሰል ነው። እኛ ግለሰብ ክርስቲያኖች ጥሩነትን እንዴት ልናሳይ እንደምንችል በስፋት ከመመርመራችን በፊት አፍቃሪው አምላካችን ይሖዋ ለሰብዓዊው ቤተሰብ በሰጠውና ከሰብዓዊው ቤተሰብ ጋር ባደረገው ግንኙነት ያሳየውን የጥሩነት ጠባይ እንመርምር።

በፍጥረት ላይ የታየው ጥሩነት

6. ይሖዋ የማሰብ ችሎታ ያላቸውን ሌሎች ፍጥረታት እንዲፈጥር ያነሳሳው ምንድን ነው?

6 በመጀመሪያ ደረጃ ሰማያዊ አባታችን የማሰብ ችሎታ ያላቸው ሕያዋን ፍጥረታት ልክ እንደርሱ በሕይወት እንዲደሰቱ ለማድረግ ያነሳሳው ነገር ምንድንነው? ሐዋርያው ዮሐንስ “እግዚአብሔር ፍቅር ነው” በማለት የዚህን ጥያቄ መልስ ይሰጠናል። (1 ዮሐንስ 4:8) አዎን፣ የሕይወት ምንጭ የሆነው ታላቅ አምላክ ምድራዊና ሰማያዊ መኖሪያ የተሰጣቸውን ሕያዋን ፍጥረታት እንዲፈጥር ያነሳሳው ራስ ወዳድነት የሌለበት ፍቅሩ ነው። እርግጥ ሰማይም ሆነ ሰማያዊ ፍጥረታት ምን እንደሚመስሉ የምናውቀው ነገር የለም። እነርሱ ለሰው ዓይን የማይታዩ መናፍስት ናቸው፤ መኖሪያቸውም በመንፈሳዊው ዓለም ውስጥ ነው። ሆኖም ይሖዋ ለሰብዓውያን ልጆቹ የሰጠውን በዙሪያህ ያለችውን ምድራዊ መኖሪያ ተመልከት። እስቲ ስለ ራሱ ስለ ሰውም አስብ። የአምላክን ጥሩነት የሚያሳዩ በርካታ ማስረጃዎችን በገዛ ዐይንህ መመልከት ትጀምራለህ።

7-9. የአምላክ ጥሩነት አምላክ ምድርንና በእርስዋ ላይ የሚኖረውን ሰው በፈጠረበት ሁኔታ የታየው እንዴት ነው?

7 ይሖዋ ለመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን ሕይወትን ሰጣቸው። ከዚህም በላይ ሕይወት በጣም አስደሳችና ተወዳጅ እንዲሆን አድርጓል። በመጀመሪያ ደረጃ መኖሪያቸው የሆነችውን ምድርን የመሽከርከር ችሎታ ያላት እንድትሆን፣ የተስተካከለ የአየር ጠባይ መጠንና ተስማሚ የሆነ ከባቢ አየር እንዲኖራት አድርጎ ፈጥሮአታል። ፍጹም በሆነ መንገድ እየሠሩ ለሰው ልጆች ትልቅ ጥቅምና ምቾት የሚያስገኙትን የውሃ፣ የናይትሮጂንና የኦክሲጅንን ዑደቶች አዘጋጅቷል። የምድርንም ገጽ ለሰው ምግብነት በሚያገለግሉና ለማየት ደስ በሚያሰኙ በብዙ ሺህ ዓይነት ዕፅዋት አልብሶታል። ሰማይንም በቀለማቸውና በዝማሬያቸው ከፍተኛ ደስታን በሚሰጡ ወፎች ሞልቶታል። ባሕርን በውስጡ በሚርመሰመሱ ዓሦች፣ ምድርንም በተለያዩ የዱርና ለማዳ ሊሆኑ በሚችሉ የእንስሳት ዓይነቶች ሞልቷቸዋል። እንዴት ያለ አስደናቂ ቸርነት ነው! አምላክ ጥሩ ልብ እንዳለው የሚያረጋግጡ ሕያው ማስረጃዎች ናቸው።​—መዝሙር 104:24

8 እስቲ አሁን ደግሞ አምላክ ሰውን የፈጠረበትን ሁኔታ እንመልከት። ክንዶቹ፣ እግሮቹና እጆቹ ሚዛኑን ጠብቆና ቀጥ ብሎ እንዲጓዝ ያስችሉታል። በዚህም ምድር ላይ ከሚያገኛቸው ነገሮች ምግቡንና የሚያስፈልጉትን ነገሮች ሊያዘጋጅ ይችላል። ይሖዋ የማጣጣም ችሎታንም ስለሰጠው መብላትና መጠጣት በኤሌክትሪክ የሚሠራ ዕቃ ለሥራው የሚያስፈልገውን ኃይል እንዲያገኝ የኤሌክትሪክ ኃይል ከሚያገኝበት መስመር ጋር እንደማገናኘት ያህል ኃይል ለማግኘት ብቻ የሚደረግ መካኒካዊ ሥራ እንዳይሆንበት አስችሎታል። መብላትና መጠጣት ሆድን ከመሙላቱም በላይ የጣዕም ስሜቶችን ስለሚያረካ ከፍተኛ ደስታ የሚገኝበት ተግባር ሆኖአል። ይሖዋ ለሰው ልጆች ጆሮ ከመስጠቱም በላይ ጆሮዎቹን የሚያስደስቱለት ድምጾች በዙሪያው እንዲኖሩ አድርጎአል። ቀስ ብሎ የሚወርደውን የጅረት ድምጽ፣ የወፎችን ዝማሬ፣ የሚፍለቀለቀውን የሕፃን ልጅ ሳቅ ማዳመጥ ምንኛ የሚያስደስት ነገር ነው! አዎን ከፍጥረት ጊዜ ወዲህ ብዙ መጥፎ ነገሮች ቢኖሩም አሁንም በሕይወት መኖር በጣም የሚያስደስት ነገር ነው። ይህም ሊሆን የቻለው አምላክ ጥሩ ስለሆነ ነው።

9 ሌሎቹን የስሜት ሕዋሳቶቻችንንም እንመልከት። ዓይናችንን የሚያስደስቱ የተለያዩና ማራኪ የሆኑ ብዙ ዓይነት ቀለሞች አሉ! አስደሳች የሆነውን የአበቦች መዓዛ ማሽተት በጣም ያረካል። መዝሙራዊው እንደሚከተለው በማለት ስለ ይሖዋ መናገሩ የሚያስገርም አይሆንም፦ “ግሩምና ድንቅ ሆኜ ተፈጥሬአለሁና አመሰግንሃለሁ፤ ሥራህ ድንቅ ነው!”​—መዝሙር 139:14

የሰው ልጅ መውደቅና መዳን

10. አብዛኞቹ ሰዎች ለአምላክ ጥሩነት ምላሽ የሰጡት እንዴት ነው? ሆኖም ከአምላክ የጥሩነት ባሕርይ መጠቀማቸውን የቀጠሉት እንዴት ነው?

10 የሚያሳዝነው ግን ውሎ አድሮ የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን አምላክ ላሳያቸው ጥሩነት ሁሉ አድናቆት የጎደላቸው ሆነው ተገኙ። ይህም የታየው የይሖዋን ትዕዛዛት ባፈረሱበትና እርሱ ያስቀመጠውን አንድ ብቸኛ ዕገዳ በተላለፉበት ጊዜ ነው። በዚህም ምክንያት እነርሱና ዝርያዎቻቸው ሐዘንን፣ ሥቃይንና ሞትን አወቁ። (ዘፍጥረት 2:16, 17፤ 3:16-19፤ ሮሜ 5:12) የትዕዛዝ አፍራሽነት ድርጊት ከተፈጸመበት ጊዜ ወዲህ ባለፉት ሺህ ዓመታት ውስጥ አብዛኛው የሰው ልጅ ለአምላክ የጥሩነት ባሕርይ ግድየለሽ ወይም የአድናቆት ባሕርይ የጎደለው ሆኖአል። ይህም ሆኖ እያለ እነዚህ አመስጋኞችና አድናቂዎች ያልሆኑ ሰዎች አሁንም ከአምላክ ጥሩነት መጠቀማቸው አልቀረም። የተጠቀሙት በምን መንገድ ነው? ሐዋርያው ጳውሎስ በመካከለኛው ምሥራቅ ለምትገኘው ለልስጥራ ነዋሪዎች እንዲህ በማለት ገልጾላቸዋል፦ “ከዚህም ሁሉ ጋር [አምላክ] መልካም (ጥሩ) ሥራ እየሠራ፣ ከሰማይ ዝናብን ፍሬ የሚሆንበትንም ወራት ሲሰጠን፣ ልባችንንም በመብልና በደስታ ሲሞላው ራሱን ያለ ምስክር አልተወም።”​—ሥራ 14:17

11. የአምላክ ጥሩነት ለሰው ዘር አስደሳች የሆነ መኖሪያ ሥፍራ ከማቅረብም በላይ ርቆ የሚሄደው በምን መንገድ ነው?

11 ሆኖም የአምላክ ጥሩነት አስደሳች የሆኑትን ለሕይወት አስፈላጊ የሆኑ በምድር ላይ በብዛት የሚገኙ ዝግጅቶችን በማቅረብ ብቻ የተወሰነ አይደለም። ከዚህም የበለጠ ነገር አድርጓል። ይሖዋ የአዳምን ዝርያዎች ኃጢአት ይቅር ለማለትና ከሰው ልጆች መካከል ታማኞች ከሆኑት ጋር ያለውን ዝምድና ለማሳደግ ዝግጁ መሆኑን አሳይቷል። ይህ የአምላክ ጥሩነት አንድ ገጽታ ይሖዋ ለሙሴ ‘መልካምነቱን በፊቱ ለማሳለፍ’ ቃል በገባበት ጊዜ ለማስተዋል ተችሎአል። ሙሴ የሚከተለውን እወጃ ሰምቶ ነበር፦ “[ይሖዋ፣ ይሖዋ (አዓት)] መሐሪ፣ ሞገስ ያለው፣ ታጋሽም፣ ባለ ብዙ ቸርነትና እውነት፣ እስከ ሺህ ትውልድም ቸርነትን የሚጠብቅ፣ አበሳንና መተላለፍን ኃጢአትንም ይቅር የሚል።”​—ዘፀዓት 33:19፤ 34:6, 7

12. የይሖዋን ጥሩነት የሚያሳዩት የትኞቹ የሙሴ ሕግ ዝግጅቶች ናቸው?

12 በሙሴ ዘመን ይሖዋ ለአዲሱ የእስራኤል ብሔር ያልታሰበ ኃጢአት የሠሩ ሰዎች ጊዜያዊ የኃጢአት ይቅርታ ሊያገኙ የሚችሉበትን አንድ ሕጋዊ ሥርዓት አቋቁሞላቸው ነበር። እስራኤላውያን ሙሴ መካከለኛ በሆነበት የሕጉ ቃል ኪዳን አማካኝነት የአምላክ ልዩ ሕዝብ በመሆን ኃጢአታቸውንና ርኩስ የሆነ ሥራቸውን ሊሸፍኑ የሚችሉ የተለያዩ የእንስሳት መስዋዕቶችን እንዲያቀርቡ ተምረው ነበር። በዚህም መንገድ ንስሐ የሚገቡ እስራኤላውያን ፍጽምና የጎደለው ባሕርይ ቢኖራቸውም እንኳ ወደ ይሖዋ ቀርበው ተቀባይነት ሊያገኙና አምልኮታቸውም እርሱን እንደሚያስደስተው ሊያውቁ ይችሉ ነበር። በሕጉ ሥር ይተዳደር የነበረው የዚህ ብሄር አባል የሆነው ንጉሥ ዳዊት በዚህ ረገድ የተገለጸውን የአምላክን ጥሩነት መረዳቱን እንደሚከተለው በማለት ገልጿል፦ “የልጅነቴን ኃጢአትና መተላለፍ አታስብብኝ፤ አቤቱ [ይሖዋ (አዓት)]ስለ ቸርነትህ (ጥሩነትህ) ብዛት እንደ ምህረትህ አስበኝ።”​—መዝሙር 25:7

13. ይሖዋ ለኃጢአት ይቅርታ ከእንስሳት መስዋዕት ይበልጥ ውጤት የሚያስገኘውን መንገድ ያዘጋጀው እንዴት ነው?

13 ከጊዜ በኋላ ደግሞ የይሖዋ ጥሩነት ኃጢአትን ይቅር ለማለት የሚያስችል ይበልጥ ውጤታማና ዘላቂ የሆነ መንገድ እንዲያዘጋጅ አነሳሳው። ይህም የሆነው የንጉሥ ዳዊት ዝርያ በሆነው በኢየሱስ መስዋዕት አማካኝነት ነበር። (ማቴዎስ 1:6-16፤ ሉቃስ 3:23-31) ኢየሱስ ምንም አይነት ኃጢአት አላደረገም። ስለዚህ እርሱ ሲሞት የተሰዋው ሕይወቱ ትልቅ ዋጋ ይኖረዋል። አምላክም የአዳም ኃጢአተኛ ዘሮች በሙሉ የሠሩትን ኃጢአት ሊሸፍን እንደሚችል መስዋዕት አድርጎ ተቀብሎታል። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጻፈ፦ “ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሎአቸዋል፤ በኢየሱስ ክርስቶስም በሆነው ቤዛነት በኩል እንዲያው በጸጋው ይጸድቃሉ። እርሱንም እግዚአብሔር በእምነት የሚገኝ በደሙም የሆነ ማስተሰሪያ አድርጎ አቆመው።”​—ሮሜ 3:23-26

14. በቤዛዊው መስዋዕት አማካኝነት ሰዎች ምን አስደናቂ ተስፋዎችን ለማግኘት ችለዋል?

14 ክርስቲያኖች በኢየሱስ ቤዛዊ መስዋዕት ማመናቸው እሥራኤላውያን በሙሴ ሕግ መሠረት ያቀርቡአቸው ከነበሩት የእንስሳት መስዋዕት በጣም የበለጠ ጥቅም አስገኝቶላቸዋል። የተወሰነ ቁጥር ያላቸው ክርስቲያኖች ጻድቃን ሆነው እንዲቆጠሩና በአምላክ መንፈስ የአምላክን ልጅነት እንዲያገኙ አስችሎአል። በዚህም መንገድ የክርስቶስ ወንድሞች ይሆናሉ። ከኢየሱስ ጋር በሰማያዊ መንግሥቱ ተካፋዮች እንዲሆኑም መንፈሳዊ ፍጡራን ሆነው ከሙታን ይነሳሉ። (ሉቃስ 22:29, 30፤ ሮሜ 8:14-17) አምላክ እንደነዚህ ያሉትን ተስፋዎች በዚህች ትንሽ በሆነችው በምድር ፕላኔት ላይ ለሚኖሩ ፍጡሮች መክፈቱ ምን ያህል ከፍተኛ መብት እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል። ይህንን ተስፋ የሚጠባበቁ ጥቂት ሰዎች አሁንም አሉ። ይሁን እንጂ በብዙ ሚልዮን ለሚቆጠሩ ሌሎች ክርስቲያኖች ቤዛውን ማመናቸው አዳምና ሔዋን ያጡትን ውብ በሆነችው የአትክልት ቦታ፣ በገነቲቱ ምድር ላይ የዘላለም ሕይወት የማግኘትን መንገድ ይከፍትላቸዋል። የሕጉ ቃል ኪዳን ብቻውን ለተገዢዎቹ ሰማያዊም ሆነ ምድራዊ ተስፋ ሊሰጥ አልቻለም ነበር።

15. ምሥራቹ ምንን ይጨምራል?

15 አምላክ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ተግባራዊ ስላደረጋቸው አዳዲስ ዝግጅቶች የሚገልጸውን መልዕክት የአምላክን ጥሩነት ስለሚያንጸባርቅ “ምሥራች” ተብሎ መጠራቱ ተገቢ ነው።(2 ጢሞቴዎስ 1:9, 10) አንዳንድ ጊዜ ምሥራቹ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “የመንግሥቱ ምሥራች” ተብሎ ይጠራል። በዛሬው ጊዜም ይህ ምሥራች መንግሥቲቱ ከሞት በተነሣው በኢየሱስ ገዥነት የተቋቋመች መሆኗን በመግለጽ ላይ ያተኩራል። (ማቴዎስ 24:14፤ ራእይ 11:15፤ 14:6, 7) ይሁን እንጂ ምሥራቹ ሌሎች ነገሮችንም የሚጨምር ነው። ከላይ የተጠቀሱት ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ የጻፋቸው ቃላት እንደሚያመለክቱት ኢየሱስ ስለ እኛ ሲል ራሱን ቤዛ አድርጎ መሰዋቱን ማወቅንም ይጨምራል። ያለዚህ መስዋዕት የኢየሱስ መንግሥት መቋቋሙና ከምድር ላይ የተመረጡት 144,000 ካህናትና ነገሥታት ወደ ሰማይ መወሰዳቸው ይቅርና ከአምላክ ጋር እንኳን ጥሩ ዝምድና ለማግኘትና ለመዳን አንችልም ነበር። ቤዛው ለአምላክ ጥሩነት አስደናቂ የሆነ መግለጫ ነው።

የአምላክ ጥሩነት በዘመናችን

16, 17. ሆሴዕ 3:5 (ሀ) በ537 ከዘአበ (ለ) በ1919 እዘአ ተፈጻሚነቱን ያገኘው እንዴት ነው?

16 ሐዋርያው ጳውሎስ ‘የመጨረሻዎቹን ቀኖች’ አስቀድሞ በመመልከት ‘ሰዎች መልካም (ጥሩ) የሆነውን የማይወዱ ይሆናሉ’ በማለት አስጠንቅቋል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-3) እንደ ቸርነትና እንደጉርብትና ወዳጅነት ያሉት የተለመዱ የጥሩነት ባሕርይ መገለጫዎች ተፈላጊነት አይኖራቸውም። እንግዲያው በሆሴዕ 3:5 ላይ የሚገኘው አስደሳች ትንቢት በጣም ያጽናናል። “ከዚያም በኋላ የእስራኤል ልጆች ተመልሰው አምላካቸውን [ይሖዋንና (አዓት)] ንጉሣቸውን ዳዊትን ይፈልጋሉ፤ በኋለኛውም ዘመን ፈርተው ወደ [ይሖዋንና (አዓት)]ወደ በረከቱ ይመጣሉ።”

17 ይህ ትንቢት የመጀመሪያ ተፈጻሚነቱን ያገኘው አይሁዳውያን ከባቢሎን ምርኮ ወደ ተስፋይቱ ምድር በተመለሱበት በ537 ከዘአበ ነበር። በዘመናችንም የመንፈሳዊ እስራኤል ቀሪዎች ከሰይጣን ድርጅት ወጥተው ይሖዋንና ጥሩነቱን ተግተው መፈለግ ከጀመሩበት ዓመት ከ1919 ጀምሮ ሲፈጸም ቆይቶአል። ሰማያዊ ስልጣን የያዘውን ኢየሱስ ክርስቶስን የሚወክለው “ንጉሣቸው ዳዊት” ከ1914 ጀምሮ በመግዛት ላይ ነው። እርሱ ከሰማይ ሆኖ እየመራቸው ምሥራቹን ለአሕዛብ የማሳወቁን ሥራ በቅንዓት ተያይዘዋል። በዚህም መንገድ “ለአሕዛብ ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ [የተቋቋመችውን] የመንግሥት ወንጌል [ምሥራች (አዓት)] በዓለም ሁሉ ይሰበካል፣ በዚያን ጊዜም መጨረሻው ይመጣል” የሚለውንና በማቴዎስ 24:14 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘውን ሥራ መፈጸም ጀምረዋል።

18. የምሥራቹን በመስበክ ከመንፈሳዊ እስራኤል ቀሪዎች ጋር የተባበሩት እነማን ናቸው?

18 ዛሬ ከቅቡዓን ቀሪዎች ጋር በተመሳሳይ መንገድ የይሖዋን ጥሩነት የሚያወድሱ “እጅግ ብዙ ሰዎች” አሉ።(ራእይ 7:9) በአሁኑ ጊዜ ከአራት ሚልዮን የሚበልጡ ሰዎች ለአሕዛብ ሁሉ ምሥራቹን በሚያውጁበት ጊዜ ሐዋርያው ዮሐንስ በራእይ የተመለከተው መልአክ ያሰማውን የሚከተለውን ድምጽ ያስተጋባሉ፦ “የፍርዱ ሰዓት ደርሶአልና እግዚአብሔርን ፍሩ ክብርንም ስጡት፤ ሰማይንና ምድርንም ባሕርንም የውኃንም ምንጮች ለሠራው ስገዱለት።”​—ራእይ 14:7

19. ለአምላክ ጥሩነት ማስረጃዎች ከሆኑት ነገሮች መካከል ትልቁን ጥቀስ።

19 ለአምላክ ጥሩነት ማረጋገጫ ከሚሆኑን ነገሮች ሁሉ የሚበልጠው ከፍተኛ ደረጃ ባለው በዚህ ሥራ ከእርሱ ጋር አብረን እንድንሠራ መፍቀዱ ነው። ‘የደስተኛው አምላክ ክብራማ የምሥራች’ ለእኛ በአደራ መሰጠቱ እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው! (1 ጢሞቴዎስ 1:11 አዓት) ይህንን ምሥራች ለሌሎች ሰዎች በመስበክና በማስተማር በጣም አስፈላጊ የአምላክ የመንፈስ ፍሬ የሆነውን ጥሩነትን እናሳያለን። በዚህም ምክንያት “የቸርነትህንም [የጥሩነትህንም (አዓት)] ብዛት መታሰብ ያወጣሉ፣ በጽድቅህም ሐሴትን ያደርጋሉ” ብሎ የተናገረው የጥንቱ አገልጋይ ዳዊት የነበረው ዓይነት ዝንባሌ ይኖረናል።​—መዝሙር 145:7

20. በሚቀጥለው ርዕሰ ትምህርት ላይ ስለ ጥሩነት ምን ተጨማሪ ማብራሪያ ይሰጣል?

20 ይሁን እንጂ ምሥራቹን በመስበክ ሥራ መካፈል በሕይወታችን ውስጥ መልካምነትን ወይም ጥሩነትን ለማሳየት የምንችልበት ብቸኛ መንገድ ነውን? በፍጹም አይደለም። ‘እንደ ተወደዱ ልጆች አምላክን የምንመስል እንድንሆን’ ተበረታተናል።(ኤፌሶን 5:1) የአምላክ የጥሩነት ባሕርይ በተለያዩ መንገዶች ታይቷል። እንግዲያው የእኛም የጥሩነት ባሕርይ የሕይወታችንን ብዙ ገጽታዎች መንካት ይኖርበታል። ከእነዚህም ውስጥ አንዳንዶቹ በሚቀጥለው ርዕሰ ትምህርት ውስጥ ይብራራሉ።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a የመንፈስ ፍሬዎች ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ደግነት፣ ጥሩነት፣ እምነት፣ የዋህነትና ራስን መግዛት ናቸው።

ልትመልሳቸው ትችላለህ?

◻ ፍጥረት የአምላክን የጥሩነት ባሕርይ የሚያንፀባርቀው በምን መንገድ ነው?

◻ ይሖዋ ንስሐ የሚገቡ ሰዎችን ኃጢአት ይቅር ለማለት ምን ዝግጅቶችን አድርጓል?

◻ በሆሴዕ 3:5 ፍጻሜ መሠረት ቅቡዓን ቀሪዎች ወደ ይሖዋና ወደ ጥሩነቱ የመጡት መቼ ነበር? ይህስ ወደ ምን የሚመራ ሆነ?

◻ በዛሬው ጊዜ ከአምላክ ጥሩነት ማስረጃዎች ውስጥ ትልቁ ምንድን ነው?

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ፍጥረት ለአምላክ የጥሩነት ብዛት ማረጋገጫ ይሰጣል

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በስብከቱ ሥራ ተካፋይ እንድንሆን መፍቀዱ ከፍተኛ የሆነ የአምላክ የጥሩነት ባሕርይ ማረጋገጫ ነው

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ