የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w92 2/15 ገጽ 5-7
  • ምስሎች ወደ አምላክ ሊያቀርቡህ ይችላሉን?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ምስሎች ወደ አምላክ ሊያቀርቡህ ይችላሉን?
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1992
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ዋጋቸው ውድና በጥንቃቄ የተሠሩ ቢሆኑም ጥቅመ ቢስ ናቸው
  • የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን አመለካከት
  • አንድ ጠላት አታሏቸዋል
  • ወደ አምላክ መቅረብ
  • ምስሎች
    ንቁ!—2014
  • ምስሎችን ቅዱስ አድርጐ መመልከት—አወዛጋቢ ጉዳይ ሆኗል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1992
  • አምላክን በምስሎች ተጠቅመን ማምለክ ይኖርብናል?
    ንቁ!—2008
  • ምስሎችን ማምለክ—መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
    ተጨማሪ ርዕሰ ጉዳዮች
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1992
w92 2/15 ገጽ 5-7

ምስሎች ወደ አምላክ ሊያቀርቡህ ይችላሉን?

ዛሬ ብዙ የግብጻውያን፣ የባቢሎናውያንና የግሪክ ምስሎች ቤተ መዘክሮችን ሞልተው ይታያሉ። በአንድ ወቅት በጋለ ስሜት የቅድስና አክብሮት ይሰጣቸው የነበሩ ሐውልቶች ዛሬ ተራ የጥንት ሥነ ጥበብ ሥራዎች ብቻ ሆነው ይታያሉ። የአምላኪዎቻቸው ስሜት ከፈጠረላቸው ኃይል በስተቀር ምንም ዓይነት ኃይል አልነበራቸውም። በቅድስና ይመለከቷቸው የነበሩት ሕዝቦች ሞተው ሲያልቁ እነዚህ ምስሎች አላቸው ይባል የነበረው ኃይል ሁሉ አብሮ ጠፍቷል። ምስሎቹም የማይረቡና ምንም ማድረግ የማይችሉ ሕይወት አልባ የእንጨት፣ የድንጋይ ወይም የብረት ቁሳቁሶች መሆናቸው ተጋለጠ። ቀድሞውንም ምንም ዓይነት ኃይል አልነበራቸውም።

ዛሬ ባሉት ሕዝቦች እየተከበሩና እየተመለኩ ስላሉት ምስሎችስ ምን ሊባል ይቻላል? ከጥንቶቹ የግብጻውያን፣ የባቢሎናውያንና የግሪክ ምስሎች የበለጠ ኃይል አላቸውን? በእርግጥ ሰውን ወደ አምላክ ለማቅረብ መሣሪያ ሆነው አገልግለዋልን?

እያንዳንዱ ትውልድ ባለፈ መጠን የሰው ልጅም ከአምላክ ይበልጥ እየራቀ የሄደ ይመስላል። ታዲያ በዓለም ያሉት ምስሎች ሁሉ የሰውን ልጅ ወደ አምላክ ሊያቀርቡ ይችላሉን? እነዚህ ምስሎች የሰው ክብካቤ ከተለያቸው አቧራ ይከማችባቸውና ይበሰብሳሉ ወይም ይዝጋሉ። ለሰው የሚጠቅም አንዳች ነገር ማድረግ ይቅርና ራሳቸውን መጠበቅ እንኳ አይችሉም። ከሁሉ ይበልጥ ግን መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ ምን ይላል?

ዋጋቸው ውድና በጥንቃቄ የተሠሩ ቢሆኑም ጥቅመ ቢስ ናቸው

መጽሐፍ ቅዱስ ምስሎችን ምንም ዋጋ ወይም ጥቅም እንደሌላቸውና የሚያምኑባቸውን ሰዎችም ወደ አምላክ እንዲቀርቡ ለመርዳት የማይችሉ መሆናቸውን ማጋለጡ ሊያስደንቀን አይገባም። ሃይማኖታዊ ምስሎች አብዛኛውን ጊዜ ዋጋቸው ውድና በጥንቃቄ የተሠሩ ቢሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ “የአሕዛብ ጣዖቶች የወርቅና የብር፣ የሰው እጅ ሥራ ናቸው። አፍ አላቸው አይናገሩም፤ ዓይን አላቸው አያዩም፤ ጆሮ አላቸው አይሰሙም፤ አፍንጫ አላቸው አያሸቱምም፤ እጅ አላቸው አይዳስሱም፤ እግር አላቸው አይሄዱም። በጉሮሮአቸው አይናገሩም። የሚሠሩአቸውም የሚያምኑባቸውም እንደነሱ ይሁኑ” በማለት ምንነታቸውን በትክክል ያሳያል።—መዝሙር 115:4-8

መጽሐፍ ቅዱስ ጣዖታት ዋጋቢስ መሆናቸውን ከማጋለጥ በተጨማሪ ምስሎችንና አምላኪዎቻቸውን እንደሚከተለው በማለት ያወግዛል፦ “እንደተቀረጸ ዐምድ [ወፎች እህል እንዳይበሉ ለማስፈራራት በእርሻ መካከል እንደተተከለ ምስል (አዓት)] ናቸው። እነሱም አይናገሩም፤ መራመድም አይችሉምና ይሸከሙአቸዋል። ክፉ መሥራትም አይቻላቸውምና፣ ደግሞም መልካም ይሠሩ ዘንድ አይችሉም አትፍሩአቸው። ሰው ሁሉ እውቀት አጥቶ ሰንፏል፣ አንጥረኛውም ሁሉ ከቀረጸው ምስል የተነሣ አፍሯል፤ ቀልጦ የተሠራ ምስሉ ውሸት ነውና እስትንፋስም የላቸውምና። እነሱ ምናምንቴ [ከንቱና] የቀልድ ሥራ ናቸው፤ በተጐበኙ ጊዜ ይጠፋሉ።”—ኤርምያስ 10:5, 14, 15

የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን አመለካከት

እውነት ነው፤ ለሃይማኖታዊ ምስሎች የሚጸልዩ፣ ሻማ የሚያበሩና የሚሳለሙ ብዙ ሰዎች ራሳቸውን ጣዖት አምላኪዎች ወይም ምስል አምላኪዎች እንደሆኑ አድርገው አይቆጥሩም። ለምሳሌ ያህል ካቶሊኮች የክርስቶስንና የማርያምን ምስሎች ቅዱስ አድርገው የሚያከብሩት ምስሎቹ በራሳቸው ምንም ዓይነት መለኮትነት ስላላቸው ሳይሆን ክርስቶስንና ማርያምን የሚወክሉ በመሆናቸው ነው ይላሉ። ዘ ወርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፔድያ “በሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ምስሎች በምስሎቹ የተወከሉት ሰዎች ምሳሌዎች እንደሆኑ ተደርገው ይከበራሉ” በማለት አትቷል። የካቶሊክ ቀሳውስት ለአንድ ምስል የሚሰጠው አክብሮት ለአምላክ ለራሱ ከሚሰጠው አክብሮት በባሕሪው አነስተኛ እስከሆነ ድረስ ምስልን ማክበር ተገቢ ነው ብለው ሰብከዋል።

ሐቁ ግን እነዚህ ምስሎች እንደ ቅዱስ ነገር ተቆጥረው እየተከበሩ ያሉ መሆናቸው ነው። ዘ ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፔድያ እንኳ ሳይቀር እንዲህ ዓይነቱ አክብሮት “የአምልኮ ድርጊት” መሆኑን አምኗል። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ክርስቶስ “በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም” ብሎ በተናገረ ጊዜ ወደ አምላክ ለመቅረብ ያግዛሉ ብሎ በማሰብ በምስሎች መጠቀም ተገቢ አለመሆኑን አመልክቷል። (ዮሐንስ 14:6) እንግዲያውስ የመጀመሪያ መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ምስሎችን ለአምልኮ ከመጠቀም መራቃቸው ሊያስደንቀን አይገባም።

ይሁን እንጂ በዛሬው ጊዜ ያሉት የሕዝበ ክርስትና ሃይማኖቶች በምስሎቻቸው ብዛት ከሌሎች ሃይማኖቶች ሁሉ በልጠዋል። አዎን ለምስል የቅድስና አክብሮት መስጠት ስሕተት መሆኑን የሚያጋልጡ ብዙ ታሪካዊና ቅዱስ ጽሑፋዊ ማስረጃዎች ቢኖሩም በዓለም ዙሪያ ክርስቲያኖች ነን የሚሉ ሰዎች አምላክን ለመፈለግ በሚያደርጉት ልባዊ ጥረት በምስሎች ፊት ወድቀው መስገዳቸውንና መጸለያቸውን ቀጥለዋል። ይህ የሆነው ለምንድነው?

አንድ ጠላት አታሏቸዋል

ነቢዩ ኢሳይያስ በዘመኑ የነበሩ ምስል አምላኪዎች “እንዳያዩ ዓይኖቻቸውን፣ እንዳያስተውሉም ልቦቻቸውን ስለጨፈኑ” የድርጊታቸውን ከንቱነት ለማየት እንዳልቻሉ ተናግሯል። (ኢሳይያስ 44:18) በሰው ልጆች ላይ ይህን የመሰለ ግፊት የሚያሳድረው ማን ሊሆን ይችላል? በ754 እዘአ የተደረገው የአይኰኖክላስቶስ ጉባኤ የሰው ልጅ ከእውነተኛው አምላክ እንዲርቅ በማድረግ ምስሎችን ቅዱስ አድርጎ እንዲመለከትና እንዲያከብር ያደረገው ሰይጣን ነው ብሎ ነበር። ይህ አባባል ትክክል ነበርን?

አዎን ትክክል ነበር። ምክንያቱም ይህ ጉባኤ ከመደረጉ በመቶዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት የአምላክ ቀንደኛ ባላንጣ የሆነው ሰይጣን ዲያብሎስ እውነት “እንዳያበራላቸው” “የሕዝቦችን ሐሳብ እንዳሳወረ” ከሚናገረው በመንፈስ መሪነት ከተጻፈው ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ስለሚስማማ ነው። (2 ቆሮንቶስ 4:4) ስለዚህ አንድ ሰው አንድን ምስል ቅዱስ አድርጐ በመመልከት በሚያከብርበት ጊዜ ወደ አምላክ በመቅረብ ፋንታ የአጋንንትን ፍላጐት ይፈጽማል።—1 ቆሮንቶስ 10:19, 20

ወደ አምላክ መቅረብ

ምስሎች ወደ አምላክ እንድንቀርብ ሊረዱን አይችሉም። ታላቁ ፈጣሪ ይሖዋ አምላክ ለምስሎች የቅድስና አክብሮት እንዲሰጥ አይፈልግም። (ዘዳግም 7:25) “ይሖዋ ቀናተኛ አምላክ (ለእሱ ብቻ የተወሰነ አምልኮ የሚፈልግ) ነው።” (ናሆም 1:2 (አዓት)) “እኔ [ይሖዋ (አዓት)] ነኝ፤ ስሜ ይህ ነው፤ ክብሬን ለሌላ፣ ምስጋናዬንም ለተቀረጹ ምስሎች አልሰጥም” ብሏል። (ኢሳይያስ 42:8) በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ ምስሎችን ቅዱስ አድርገው በመቁጠር የሚያከብሩ ሰዎች “የእግዚአብሔርን መንግሥት እንደማይወርሱ” ያስጠነቅቃል።—ገላትያ 5:19-21

ሆኖም ይሖዋ መሐሪና ይቅር ባይ አምላክ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ከጣዖቶቻቸው ወደ አምላክ ስለተመለሱ ሰዎችና ጣዖታዊ ተግባሮቻቸውን ካቆሙ በኋላ ጻድቃን ስለተባሉ ሰዎች ይናገራል። (1 ቆሮንቶስ 6:9-11፤ 1 ተሰሎንቄ 1:9) እነዚህ ሰዎች ኢየሱስ “እግዚአብሔር መንፈስ ነው፤ የሚሰግዱለትም በመንፈስና በእውነት ሊሰግዱለት ያስፈልጋቸዋል” በማለት የተናገረውን ፈጽመዋል።—ዮሐንስ 4:24

ወደ አምላክ መቅረብ አዳጋች ነገር አለመሆኑን መጽሐፍ ቅዱስን በቅንነት በማጥናት መገንዘብ ይቻላል። (ሥራ 17:26-28) አምላክ ሞቅ ያለ የፍቅር ባሕርይ ያለውና ሰዎች እንዲቀርቡት የሚፈልግ ነው። ከእሱም ጋር የቅርብ ወዳጅነት እንድንመሠርት ይጋብዘናል ይጠብቅብናልም።—ኢሳይያስ 1:18

የይሖዋ ምስክሮች የሰማያዊ አባታችንን ማንነት እንድታውቅና ይሖዋ ስለተባለው ስሙና ስለ ባሕርያቱ እንዲሁም ለሰው ልጆች ስላደረጋቸው ነገሮች እንድትማር ይጋብዙሃል። ወደ አምላክ ለመቅረብ ያግዛሉ የሚባሉ እንደ ሐውልት ወይም ምስልና ሥዕሎች የመሳሰሉ የሚታዩ ነገሮች አስፈላጊ አለመሆናቸውን ቃሉ በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ ገጾች አማካኝነት ትረዳለህ። አዎን፣ “ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ ወደ እናንተም ይቀርባል።”—ያዕቆብ 4:8

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ታሪክ ጸሐፊዎች . . .ብለዋል

◻ “በ6ኛው መቶ ዘመን ከዘአበ የተመሠረተው የቡዲሂዝም መሪ የነበረው የቡድሀ የመጀመሪያ ምስል እስከ መጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ ድረስ አልተሠራም ነበር።”

“የሂንዱ የአምልኮ ባሕል ለብዙ መቶ ዓመታት ምንም ዓይነት የአምልኮ ምስሎች አልነበሩትም።”

“ሂንዱይዝምና ቡድሂዝም በተጀመሩበት ጊዜ ምንም ዓይነት የአምልኮ ምስል ያልነበራቸው ሲሆኑ ምስሎችን ያስገቡት ቀስ በቀስ ነበር። የክርስትና እምነትም እንዲሁ አድርጓል።”—ዘ ኢንሳይክሎፔድያ ኦቭ ሪሊጅን በሚርስያ ኤሊያድ

◻ “እውነተኛው የአምላክ አምልኮ አለምንም ምስል ይከናወን እንደነበረ ከተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች በግልጽ መረዳት ይቻላል። . . . በአዲስ ኪዳን ውስጥም የእንግዳ አማልክትና የጣዖቶች አምልኮ ተከልክሏል።”—ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፔድያ

◻ “በጥንት ክርስቲያኖች አምልኮ ምስሎች አይታወቁም ነበር።”—የመጽሐፍ ቅዱስ፣ የመንፈሳዊ ትምህርትና የቤተ ክርስቲያን ስነ ጽሑፍ ሳይክሎፔድያ በማክሊንቶክና እስትሮንግ የተዘጋጀ

◻ “በአዲስ ኪዳን ውስጥም ሆነ በማንኛውም የክርስትና እምነት በተመሠረተባቸው የመጀመሪያ ዘመናት በተጻፉ እውነተኛ ጽሑፎች ክርስቲያኖች በአደባባይም ሆነ በግላቸው ምስሎችን ይጠቀሙ እንደነበረ የሚያሳይ ምንም ፍንጭ አልተገኘም።”—አጠር ያለ የሃይማኖታዊ እውቀት ሳይክሎፔድያ በኤልያስ ቤንጃሚን ሳንፎርድ የተዘጋጀ

◻ “የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች ምስሎችን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የማስቀመጥ ሐሳብ ቢቀርብላቸው በጣም ይዘገንናቸው ነበር። በምስሎች ፊት መንበርከክን ወይም መጸለይን ከጣዖት አምልኮ ለይተው አይመለከቱም ነበር።”—የቤተ ክርስቲያን ታሪክ በጆን ፍሌቸር ኸርስት የተዘጋጀ

◻ “በቀድሞዋ ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስንም ሆነ የቅዱሳንን ሥዕል መሥራትና ማክበር በጥብቅ የተከለከለ ነበር።”—አዲሱ ኢንሳይክሎፔድያ ብሪታኒካ

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

አምላክ “ለአብ በመንፈስና በእውነት የሚሰግዱለትን” እንደሚፈልግ ኢየሱስ አጥብቆ ገልጿል

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ