ምስሎችን ቅዱስ አድርጐ መመልከት—አወዛጋቢ ጉዳይ ሆኗል
በፖላንድ አገር የሚኖር አንድ ሰው ጉዞውን ለመጀመር ተዘጋጅቷል። ሆኖም ከመሄዱ በፊት አንድ አስፈላጊ የሆነ ጉዳይ ማጠናቀቅ አለበት። በአንድ የኢየሱስ ምስል ፊት ይንበረከክና ስጦታ በማቅረብ በጉዞው እንዲጠብቀው ይጸልያል።
ከፖላንድ በሺህ የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮች ርቆ በሚገኘው ባንግኮክ በተባለ የታይላንድ ከተማ ደግሞ በዓመቱ ውስጥ በፀደይ ወራት ላይ የሚከበረውን የቡድሂስት ዓመታዊ በዓል ልታይ ትችላለህ። በበዓሉ ወቅት የቡድሃ ምስል በጐዳናዎች ተይዞ ይዞራል።
አሁን በተገለጸው ዓይነት ሁኔታ ለምስሎች የቅድስና አክብሮት መስጠት በጣም የተስፋፋ አድራጐት መሆኑን ማወቅ ይኖርብሃል። በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በምስሎች ፊት ይሰግዳሉ። ምስሎች በሺህ ለሚቆጠሩ ዓመታት ወደ አምላክ የሚያቀርቡ አስፈላጊ ነገሮች እንደሆኑ ተደርገው ሲታዩ ቆይተዋል።
አንተስ ምስሎችን ለአምልኮ ስለመጠቀም ምን ይሰማሃል? ለምስሎች የቅድስና አክብሮት መስጠት ትክክል ነው ወይስ ስህተት? አምላክ አምላክስ ምስሎችን ለአምልኮ ስለመጠቀም እንዴት ይሰማዋል? በዚህ መንገድ የሚቀርብለትን አምልኮ እንደሚቀበል የሚያሳይ ማስረጃ አለን? ምናልባት አንተ በግልህ እንደዚህ ስላሉት ጥያቄዎች እምብዛም አስበህ አታውቅ ይሆናል። ሆኖም ከአምላክ ጋር ለሚኖርህ ዝምድና ከፍ ያለ ዋጋ የምትሰጥ ከሆንክ ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ማግኘት ያስፈልግሃል።
እርግጥ ለብዙ ሰዎች ይህ ጉዳይ በቀላሉ እልባት የሚገኝለት አይደለም። በሺህ ለሚቆጠሩ ዓመታት የጦፈና አንዳንዴም ወደ ደም መፋሰስ ያደረሰ ኃይለኛ ክርክር የተደረገበት ርዕሰ ጉዳይ ሆኖ ቆይቷል። ለምሳሌ ያህል በ1513 ከዘአበ የዕብራውያን መሪ የነበረው ሙሴ አንድን የጥጃ ምስል ሰባብሮ ካጠፋ በኋላ ምስሉን ያከብሩ የነበሩ 3,000 የሚያክሉ ሰዎች በሰይፍ እንዲገደሉ አድርጓል።—ዘጸአት ምዕራፍ 32
ኃይማኖታዊ ምስሎችን ለአምልኮ በመጠቀም ረገድ ኃይለኛ ተቃውሞ የተነሣው በአይሁድ ሕዝብ መካከል ብቻ አልነበረም። የጥንት ዓለማዊ ታሪክ ጸሐፊዎች ከሙሴ ዘመን በመቶዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት ይኖር የነበረ ታክህሙሩፕ የሚባል የፐርሺያ መሪ ምስሎች እንዳይመለኩ በመቃወም ሰፊ ጦርነት እንዳካሄደ የሚገልጽ አፈታሪክ አቆይተዋል። በቻይና አገር አንድ ጥንታዊ ንጉሥ በተለያዩ አማልክት ምስሎች ላይ ወታደራዊ ጥቃት ሰንዝሮ እንደነበረ የሚገልጽ አፈታሪክ አለ። ምስሎችን ከደመሰሰ በኋላ ከጭቃ የተሠሩ አማልክትን ቅዱስ አድርጐ ማክበር ሞኝነት ነው በማለት አውግዟል። በኋለኞቹ ዘመናትም ሙሐመድ ገና ሕፃን ሳለ ምስሎችን ለአምልኮ መጠቀምን የሚቃወሙ አረቦች ነበሩ። የእነዚህም ሰዎች ተጽእኖ ሙሐምድ የኋላ ኋላ በጣዖት አምልኮ ላይ የጸና የተቃውሞ አቋም እንዲኖረው ተጨማሪ ምክንያት ሆኗል። ሙሐመድ በቁርአን ውስጥ ጣዖት አምልኮ ምሕረት የማይደረግበት ኃጢአት መሆኑን፣ ለጣዖት አምላኪዎች መጸለይ እንደማይገባና ጣዖት አምላኪ ከሆኑ ሰዎች ጋር ጋብቻ መመሥረት የተከለከለ እንደሆነ አስተምሯል።
በሕዝበ ክርስትና ውስጥም እንደ ኢራኒየስ፣ ኦሪገን፣ የቂሳሪያው ዩሲቢየስ፣ ኤፒፋኒየስና አውግስቲን የመሳሰሉት የሁለተኛው፣ የሦስተኛው፣ የአራተኛውና የአምስተኛው መቶ ዘመን እዘአ እውቅ የሃይማኖት ሰዎች ምስሎችን ለአምልኮ መጠቀምን ተቃውመዋል። በአራተኛው መቶ ዘመን እዘአ መጀመሪያ ላይ በእስፓኝ ኤልቪራ የተሰበሰበ የጳጳሶች ቡድን ምስሎችን ቅዱስ አድርጐ ማክበርን የሚቃወሙ ታላላቅ ውሳኔዎችን አስተላልፎ ነበር። ይህ ከፍተኛ ዝና ያተረፈው የኤልቪራ ምክር ቤት በቤተ ክርስቲያኖች ውስጥ ምስሎችን መጠቀምን የሚከለክልና በምስል አምላኪዎች ላይ ከባድ ቅጣት እንዲፈጸም የሚያደርግ ድንጋጌ አውጥቶ ነበር።
አይኰኖክላስቶስ የተባሉ ምስል ሰባሪዎች
ከላይ የተጠቀሱት ሁኔታዎች በታሪክ ውስጥ ታላላቅ ተብለው ከሚቆጠሩት ግጭቶች አንዱ ለሆነው የስምንተኛውና የዘጠነኛው መቶ ዘመን የአይኰኖክላስቶስ ወይም የምስል ሰባሪዎች ግጭት መድረኩን አመቻችተዋል። አንድ ታሪክ ጸሐፊ “ይህ መራራ ግጭት ለአንድ ተኩል መቶ ዓመት የቆየ እንደነበረና በሰዎች ላይ ተነግሮ የማያልቅ ሥቃይ ያደረሰ እንደነበረ” እንዲሁም “በምሥራቅና በምዕራብ ግዛቶች መሃል የተፈጠረውን መከፋፈል ካስከተሉት መንስኤዎች አንዱ” እንደነበረ ያትታል።
“አይኰኖክላስት” የተባለው የእንግሊዝኛ ቃል “ምስል” የሚል ትርጉም ካለው “አይኰን” እና “ሰባሪ” የሚል ትርጉም ካለው “ክላስቴስ” ከሚባሉ የግሪክኛ ቃሎች የመጣ ነው። ስሙ ራሱ እንደሚያመለክተው ምስሎችን የሚቃወመው ይህ ንቅናቄ ከአውሮፓ በሙሉ ምስሎችን ማስወገድንና ማጥፋትን ዋነኛ ዓላማው አድርጐ ነበር። ምስሎችን ለአምልኮ መጠቀም እንዲቀር ለማድረግ አያሌ ጸረ ምስል ሕጎች በሥራ ላይ ውለው ነበር። ለምስሎች የቅድስና አክብሮት መስጠት ነገሥታትንና ሊቃነ ጳጳሳትን፣ ጄኔራሎችንና አቡኖችን ወደ ሃይማኖታዊ ውጊያ ጐትቶ ያስገባ አወዛጋቢ የፖለቲካ ጉዳይ ሆኖ ነበር።
ይህ ግጭት በቃላት ጦርነት ብቻ ተወስኖ የቀረ አልነበረም። በማክሊንቶክና እስትሮንግ የተዘጋጀው የመጽሐፍ ቅዱስ፣ የመንፈሳዊ ትምህርትና የቤተ ክርስቲያን ስነ ጽሑፍ ሳይክሎፔድያ ንጉሥ ሊዮ ሦስተኛ በቤተ ክርስቲያኖች ውስጥ ምስሎችን መጠቀምን የሚከለክል አዋጅ ካወጣ በኋላ ሕዝቡ “አዋጁን በመቃወም በኅብረት እንደተነሡና በተለይ ደግሞ በኮንስታንቲኖፕል ዓመፅ የሞላባቸው ረብሻዎች” በየቀኑ ይደረጉ እንደነበረ አትቷል። በንጉሠ ነገሥቱ ጦር ኃይሎችና በሕዝቡ መካከል የተፈጠሩት ግጭቶች ብዙ ግድያና እልቂት አስከትለዋል። መነኩሴዎች በጭካኔ ተሰደዋል። በመቶዎች የሚቆጠሩ ዓመታት ካለፉ በኋላ በ16ኛው መቶ ዘመን በስዊዘርላንድ፣ ዙሪክ ውስጥ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ምስሎችን ስለመጠቀም በርካታ የሆኑ ሕዝባዊ ክርክሮች ተደርገዋል። ከክርክሮቹም በኋላ ምስሎች ከቤተ ክርስቲያኖች እንዲወገዱ የሚጠይቅ ድንጋጌ ተላልፎ ነበር። አንዳንድ የተሐድሶ መሪዎች የምስሎችን አምልኮ በጋለ ስሜትና በኃይል በማውገዛቸው ትልቅ ዝና አትርፈዋል።
ዛሬም እንኳ ቢሆን ምስሎችን ለአምልኮ በመጠቀም ረገድ በዘመናዊ ሃይማኖት ሊቃውንት መሃል ሰፊ መከፋፈል አለ። የሚቀጥለው ርዕሰ ትምህርት ምስሎች በእርግጥ ሰውን ወደ አምላክ እንዲቀርብ ይረዱት እንደሆነና እንዳልሆነ እንድትገመግም ይረዳሃል።