በዓለም ላይ ከፍተኛ ለውጥ ያስከተለው ሳምንት
“[በይሖዋ (አዓት)] ስም የሚመጣ የተባረከ ነው።”—ማቴዎስ 21:9
1. ባለፈው ነሐሴ በደረሱት ሁኔታዎች የተነኩት ምን ሁለት የተለያዩ ቡድኖች ነበሩ?
“ዓለምን ያናወጡ ሦስት አስጨናቂ ቀኖች።” በነሐሴ ወር 1991 ይወጡ የነበሩ እነዚህን የመሰሉ የዜና አምዶች ዓለም በጥቂት ቀናት ውስጥ ልትገለበጥ እንደምትችል አጥብቀው ተናግረው ነበር። በእርግጥም የነሐሴ ወር የመጨረሻ ቀኖች ለዓለም ብቻ ሳይሆን ኢየሱስ “ከዓለም አይደሉም” ብሎ ለተናገረላቸው ሰዎችም ታላላቅ ነገሮች የተፈጸሙባቸው ቀኖች ነበሩ። እነዚህ ሰዎች በአሁኑ ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች ተብለው ይታወቃሉ።—ዮሐንስ 17:14
2, 3. (ሀ) የጦርነት ደመና ቢያንዣብብም በዛግሬብ ጎልቶ የተገለጸው ምን አይነት ነፃነት ነበር? (ለ) ጠንካራ እምነት በኦዴሳ ዋጋ ያስገኘው እንዴት ነበር?
2 በዩጎዝላቪያ ለመደረግ የመጀመሪያ የሆነው የይሖዋ ምሥክሮች ዓለም አቀፍ ስብሰባ ሊደረግ የታቀደው ከነሐሴ 16 እስከ 18 ነበር። በኋላ እንደታየውም ይህ ስብሰባ የእርስ በርስ ጦርነት ሊፈነዳ በተቃረበበት አገር የተደረገ የመጀመሪያው ትልቅ የይሖዋ ሕዝቦች ስብሰባ ሆኖአል። የአካባቢው ምሥክሮች ከአጎራባች አገር ከመጡ የበጎ ፈቃድ ሠራተኞች ጋር ሆነው በዛግሬብ የሚገኘውን የሀስክ ግራንዳስኪ የእግር ኳስ ስታዲየም ሙሉ በሙሉ ለማደስ ሁለት ወር ያህል ደክመዋል። ከብዙ ድካም በኋላ ለ“አምላካዊ ነፃነት አፍቃሪዎች” ስብሰባ ተስማሚ የሆነ በጣም ፅዱ ሥፍራ ሆነ። ከዩናይትድ ስቴትስ የሚመጡ 600 ልዑካንን ጨምሮ በሺህ የሚቆጠሩ ዓለም አቀፍ ልኡካን እንዲገኙ ታቅዶ ነበር። የእርስ በርስ ጦርነት ደመና ማንዣበብ ሲጀምር “አሜሪካውያኑ ሊመጡ አይችሉም” የሚል ወሬ መናፈስ ጀምሮ ነበር። ይሁን እንጂ እነሱም ሆኑ ከሌሎች አገሮች የመጡ ልዑካን በስብሰባው ላይ ተገኝተዋል። 10,000 የሚያህሉ ተሰብሳቢዎች እንደሚገኙ ተጠብቆ ነበር። በስብሰባው የመጨረሻ ቀን በእስታዲየሙ የተገኙት ተሰብሳቢዎች ቁጥር ግን 14,684 ነበር! ሁሉም ‘መሰብሰባቸውን ባለመተዋቸው’ ተባርከዋል።—ዕብራውያን 10:25
3 በዛግሬብ ተደርጎ ከነበረው ስብሰባ በኋላ በነበሩት ሦስት ቀናት በሶቪየት ህብረት ያልተሳካ የመንግሥት ግልበጣ ሙከራ ተደርጎ ነበር። በዚያ ወቅት ነፃነት አፍቃሪዎች በዩክሬይን ኦዴሳ ሊያደርጉ ለነበረው ስብሰባ የመጨረሻ ዝግጅት በማድረግ ላይ ነበሩ። ስብሰባው ሊደረግ ይችል ይሆን? ወንድሞች በጠንካራ እምነት የስታዲየሙን ሙሉ እድሳት አጠናቀቁ፣ ልዑካንም መምጣታቸውን ቀጠሉ። የመንግሥት ግልበጣው እንደ ተአምር ሊቆጠር በሚችል ሁኔታ በድንገት ቆመ። ነሐሴ 24 እና 25 12,115 ተሰብሳቢዎች የተገኙበትና የተሰብሳቢዎቹ 16 በመቶ የሚሆኑት ማለትም 1,943 ሰዎች የተጠመቁበት አስደሳች ስብሰባ ተደረገ! እነዚህ አዳዲስ ምሥክሮችም ሆኑ ለረዥም ዘመናት ፍጹም አቋማቸውን ጠብቀው የኖሩት ክርስቲያኖች በይሖዋ ሙሉ በሙሉ በመተማመን ወደዚህ ስብሰባ በመምጣታቸው ተደስተዋል።—ምሳሌ 3:5, 6
4. የምሥራቅ አውሮፓ ምስክሮች የተከተሉት የትኛውን ኢየሱስ የተወው ምሳሌ ነው?
4 እነዚህ ታማኝ ምሥክሮች አርአያችን የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ የተወውን ምሳሌ ተከትለዋል። ኢየሱስ አይሁዳውያን ሊገድሉት ይፈልጉ በነበሩበት ጊዜም እንኳን ሳይቀር ይሖዋ እንዲከበሩ ባዘዛቸው በዓላት ላይ ከመገኘት ችላ ብሎ አያውቅም። የመጨረሻውን የማለፍ በዓል ለማክበር ወደ ኢየሩሳሌም በመጓዝ ላይ ሳለ ሊገድሉት ይፈልጉ የነበሩ አይሁድ በቤተ መቅደሱ ዙሪያ ቆመው “ምን ይመስላችኋል? ወደ በዓሉ አይመጣም ይሆንን?” ይባባሉ ነበር። (ዮሐንስ 11:56) እሱ ግን መጣ! መምጣቱም የሰውን ልጅ የታሪክ አቅጣጫ ሙሉ በሙሉ በመለወጥ ለተደመደመው ሳምንት መድረኩን አመቻቸ። እንደ አይሁድ የቀን አቆጣጠር ከኒሳን 8 እስከ 14 በዋለው በዚህ ሳምንት የተፈጸሙትን ዋና ዋና ጉዳዮች ብንከልሳቸውስ?
ኒሣን 8
5. ኒሳን 8, 33 እዘአ ኢየሱስ ወደ ቢታኒያ ሲጓዝ ሳለ ምን ተገንዝቦ ነበር?
5 በዚህ ቀን ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ቢታኒያ ደረሱ። በቢታኒያም ኢየሱስ በቅርቡ ከሞት ባስነሣው ወዳጁ በአልዓዛር ቤት ስድስት ቀን ያድራል። ቢታኒያ ለኢየሩሳሌም ቅርብ ናት። ቀደም ሲል ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ለብቻቸው አድርጎ “እነሆ ወደ ኢየሩሳሌም እንወጣለን፣ የሰው ልጅም ለካህናት አለቆችና ለጻፎች ይሰጣል፤ የሞት ፍርድም ይፈርዱበታል፣ ሊዘባበቱበትም ሊገርፉትም ሊሰቅሉትም ለአሕዛብ አሳልፈው ይሰጡታል፣ በሦስተኛውም ቀን ይነሣል” ብሎአቸው ነበር። (ማቴዎስ 20:18, 19) ኢየሱስ አሰቃቂ ስቃይ እንደሚደርስበት በሚገባ ያውቅ ነበር። ይሁን እንጂ ይህ ከፍተኛ የፈተና ሰዓት እየቀረበ በሄደበት ጊዜ እንኳን ወንድሞቹን በፍቅር ከማገልገል አልተቆጠበም። እኛም ሁልጊዜ “በኢየሱስ ክርስቶስ የነበረ ይህ ሐሳብ” ይኑረን።—ፊልጵስዩስ 2:1-5፤ 1 ዮሐንስ 3:16
ኒሣን 9
6. ኒሳን 9 ምሽት ላይ ማርያም ምን አደረገች? ኢየሱስስ ለይሁዳ ምን አለው?
6 ፀሐይ ጠልቃ ኒሳን 9 ሲጀምር ኢየሱስ ቀድሞ ለምጻም በነበረው በስምኦን ቤት በተደረገለት የእራት ግብዣ ላይ ተገኝቶ ነበር። የአልዓዛር እህት ማርያም ዋጋው ውድ የሆነ ሽቶ በኢየሱስ ራስና እግር ላይ ያፈሰሰችውና ራስዋንም ዝቅ በማድረግ እግሩን በፀጉሯ ያበሰችው እዚህ ነበር። ያደረገችውን ድርጊት ይሁዳ በተቃወመ ጊዜ ኢየሱስ “ለምቀበርበት ቀን እንድትጠብቀው ተውአት” አለ። የካህናት አለቆች ከአይሁድ ብዙዎች ወደ ቢታንያ እንደሚሄዱና በኢየሱስ እንደሚያምኑ በሰሙ ጊዜ እሱንና አልዓዛርን ሊገድሏቸው ተማከሩ።—ዮሐንስ 12:1-7
7. ኒሳን 9 ጧት የይሖዋ ስም የተከበረው እንዴት ነው? ኢየሱስስ ምን ትንቢት ተናገረ?
7 ኢየሱስ ጧት በማለዳ ወደ ኢየሩሳሌም መጓዝ ጀመረ። ብዙ ሰዎችም የዘንባባ ዝንጣፊዎችን በእጆቻቸው ይዘው ሊቀበሉት ወጡና “ሆሣዕና፤ በጌታ ስም የሚመጣ የእሥራኤል ንጉሥ የተባረከ ነው” እያሉ ጮኹ። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ በአህያ ላይ ተቀምጦ ወደ ከተማይቱ በመሄድ የዘካርያስ 9:9ን ትንቢት ፈጸመ። ወደ ኢየሩሳሌም ሲቀርብም ሮማውያን ቀስታቸውን ገትረው እንደሚከቧትና እንደሚያጠፏት ትንቢት በመናገር አለቀሰላት። ይህም ትንቢት 37 ዓመታት ቆይቶ በአስደናቂ ሁኔታ ተፈጽሞአል። (ይህም የጥንቷን ኢየሩሳሌም አካሄድ በመከተል ከሐዲ የሆነችው ሕዝበ ክርስትና ተመሳሳይ ዕጣ እንደሚደርስባት ያመለክታል።) የአይሁድ መሪዎች ኢየሱስ ንጉሣቸው እንዲሆን አልፈለጉም። ከዚህ ይልቅ በቁጣ “እነሆ፣ ዓለሙ በኋላው ተከትሎት ሄዷል ተባባሉ።”—ዮሐንስ 12:13, 19
ኒሳን 10
8. ኒሳን 10 ዕለት ኢየሱስ ለይሖዋ የጸሎት ቤት ጥልቅ አክብሮት ያሳየው እንዴት ነበር? ምን ሁኔታስ ተከተለ?
8 ኢየሱስ እንደገና ቤተ መቅደሱን ጎበኘ። ለሁለተኛ ጊዜም ስግብግቦቹን ነጋዴዎችና የገንዘብ ለዋጮችን አባረረ። ንግድ ወይም “የገንዘብ ፍቅር” በአምላክ የጸሎት ቤት ውስጥ መንገስ አይገባውም! (1 ጢሞቴዎስ 6:9, 10) ኢየሱስ የሚሞትበት ጊዜ ቀርቦአል። ይህንንም ሲገልጽ ስለአንዲት ቅንጣት ዘር መዘራት ምሳሌ ተናገረ። ይህች ዘር ስትሞት ብዙ ፍሬ የሚያፈራ ዛላ ታወጣለች። በተመሳሳይም የኢየሱስ መሞት በእርሱ ለሚያምኑ ለብዙዎች የዘላለም ሕይወት ያስገኛል። ኢየሱስ መሞቻው የቀረበ መሆኑን እያሰበ በጣም ስለተረበሸ አሟሟቱ የአባቱ ስም የሚከበርበት እንዲሆን ጸለየ። በምላሹም የአምላክ ድምፅ ከሰማይ እንደ ነጎድጓድ “አከበርሁት ደግሞም አከብረዋለሁ” ሲል ተሰማ።—ዮሐንስ 12:27, 28
ኒሳን 11—ብዙ ሥራ የተከናወነበት ቀን
9. (ሀ) ኒሳን 11 ማለዳ ኢየሱስ ከሐዲዎቹን አይሁድ ለማውገዝ በምሳሌዎች እንዴት ተጠቀመ? (ለ) በኢየሱስ ምሳሌ መሠረት ታላቅ አጋጣሚ ያመለጣቸው እነማን ነበሩ?
9 ኢየሱስና ደቀመዛሙርቱ ቀኑን ሙሉ ሲሠሩ ለመዋል ከቢታኒያ ተነሱ። ኢየሱስ ወደ ክህደት ያዘነበለው የአይሁዳውያን ሃይማኖት ሊወገዝ የሚገባው መሆኑን ለማሳየት በሦስት ምሳሌዎች ተጠቀመ። በመንገድ ላይ ሲሄድ ሳለ አንዲት ፍሬ የሌላት የበለስ ዛፍ አግኝቶ ረገመ። የጠወለገችው ዛፍ እምነተ-ቢሶችና ፍሬ ቢሶች ለሆኑት የአይሁድ ሕዝቦች ምሳሌ ሆነች። ወደ ቤተ መቅደሱ ገብቶም አይሁድ ኢየሱስን በመግደላቸው ከይሖዋ የተቀበሉትን አደራ መብላታቸውን በከፍተኛ ደረጃ እንደሚያሳዩ ለመግለጽ የጌታቸውን የወይን አትክልት የሚጠብቁ ምስጋና ቢስ ገበሬዎች የአትክልቱን ባለቤት ልጅ እንዴት እንደገደሉት ነገራቸው። በአንድ ንጉሥ ማለትም በይሖዋ ስለተዘጋጀ የሠርግ ድግስና እድምተኞቹ (አይሁድ) በድግሡ ላይ ላለመገኘት የራስ ወዳድነት ሰበብ እንደፈጠሩ ገለጸላቸው። ስለዚህ ግብዣው ለውጭ ሰዎች ማለትም ለአሕዛብ ቀረበና ከመካከላቸው አንዳንዶቹ ምላሽ ሰጡ። የሠርግ ልብስ ሳይለብስ የመጣ አንድ ሰው ግን ወደ ውጭ ተጣለ። ይህ ሰው የሚያመለክተው አስመሳዮቹን የሕዝበ ክርስትና ክርስቲያኖች ነው። በኢየሱስ ዘመን የነበሩ ብዙ አይሁድ ተጠርተው ነበር። ሰማያዊውን መንግሥት ከሚወርሱት 144,000 የታተሙ መሃል ሊሆኑ “የተመረጡት ግን ጥቂቶች” ነበሩ።—ማቴዎስ 22:14፤ ራዕይ 7:4
10-12. (ሀ) ኢየሱስ አይሁዳውያን ካህናትን ክፉኛ የነቀፋቸው ለምን ነበር? በእነዚያ ግብዞች ላይ ምን ኃይለኛ ውግዘት ጫነባቸው? (ለ) በከሃዲው የአይሁድ ሕዝብ ላይ የመጨረሻ ፍርድ የተፈጸመው እንዴት ነበር?
10 ግብዞቹ የአይሁድ ካህናት ኢየሱስን የሚይዙበትን አጋጣሚ ይፈልጉ ነበር። ኢየሱስ ግን እርሱም ለማጥመድ ሲሉ ያቀረቡአቸውን በርካታ ጥያቄዎች በመመለስ በሕዝቡ ፊት አፋቸውን አስያዛቸው። እነዚህ ከሐዲ ሃይማኖታዊ አይሁዶች ምንኛ ክፉ ናቸው! ኢየሱስም ክፉኛ ነቀፋቸው። በዘመናችን እንዳሉት ቀሳውስት ለራሳቸው የተመረጠ የከበሬታ ቦታ፣ ልዩ አድርጎ የሚያሳያቸው ልብስና “ረቢ” (መምህር) “አባት”ና በመሳሰሉት የከፍተኛ ማዕረግ ስሞች ለመጠራት ይፈልጉ ነበር። ኢየሱስ “ራሱን ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ይዋረዳል፣ ራሱንም የሚያዋርድ ሁሉ ከፍ ይላል” የሚለውን ደንብ ነገራቸው።—ማቴዎስ 23:12
11 ኢየሱስ እነዚህን ሃይማኖታዊ መሪዎች በኃይል አወገዛቸው። ዕውሮች መሪዎችና ግብዞች ብሎ በመጥራት ሰባት ጊዜ “ወዮላችሁ” ብሏቸዋል። “ወዮላችሁ” ባለበት በእያንዳንዱ ጊዜም ወዮ የተባለላቸው ለምን እንደሆነ ገልጾአል። ወደ መንግሥተ ሰማያት የሚያስገባውን በር ይዘጋሉ። አንድን ሰው አጥምደው ተከታያቸው በሚያደርጉበት ጊዜ በፊተኛው ከባድ ኃጢአቱ ምክንያትም ይሁን ተከታያቸው ከሆነ በኋላ በሚኖረው ሃይማኖታዊ አክራሪነት ምክንያት ለጥፋት የተዘጋጀ እጥፍ የገሃነም ልጅ ያደርጉታል። ፈሪሳውያን በቤተ መቅደሱ የሚከናወነው አምልኮ ንጽሕና እንዲጠበቅ ከማድረግ ፈንታ በቤተ መቅደሱ ወርቅ ላይ ያተኩሩ ስለነበር ኢየሱስ “እናንተ ደንቆሮዎችና ዕውሮች” ብሏቸዋል። ከአዝሙድና ከእንስላል ከከሙንም አሥራት ሲያወጡ ፍርድንና ምሕረትን፣ ታማኝነትንም፣ በሕግ ያለውንም ዋና ነገር ችላ ይሉ ነበር። በሃይማኖታዊ ሥርዓታቸው መሠረት የሚደረገው መታጠብ ውስጣዊ ርኩስነታቸውን ሊያነፃ አይችልም። ውስጣዊ ርኩስነታቸውን ሊያነፃ የሚችለው የሚሠዋበት ጊዜ ደርሶ በነበረው በኢየሱስ መሥዋዕት በማመን የሚገኘው ንፁሕ ልብ ብቻ ነው። ውስጣዊ ግብዝነታቸውና ዓመጸኝነታቸው “በኖራ እንደተለሰነ መቃብር” ንጹሕና ቅዱስ መስለው ለመታየት የሚያደርጉት ማንኛውም ሙከራ እውነት አለመሆኑን ያጋልጥ ነበር።—ማቴዎስ 23:13-29
12 አዎን በእርግጥም ከጥንት ጀምሮ “የነቢያት ገዳዮች ልጆች” ለሆኑት ለእነዚህ ፈሪሳውያን ወዮ ሊባልላቸው ይገባ ነበር! ኢየሱስን ብቻ ሳይሆን እሱ የላካቸውንም ጭምር ስለሚገድሉ ለገሃነም የተመደቡ እባቦችና የእፉኝት ልጆች ናቸው። ይህም “በዚህ ትውልድ ላይ” የሚፈጸም ፍርድ ነው። ኢየሩሳሌም ከ37 ዓመታት በኋላ ፈጽማ ስለጠፋች ይህ ትንቢት በትክክል ተፈጽሞአል።—ማቴዎስ 23:30-36
13. ኢየሱስ ለቤተ መቅደሱ ስለሚደረግ መዋጮ የሰጠው አስተያየት ዛሬ በምን ሁኔታዎች ላይ ይንፀባረቃል?
13 ኢየሱስ ቤተ መቅደሱን ለቆ ከመውጣቱ በፊት በገንዘብ መሰብሰቢያ ሣጥን ውስጥ ሁለት ሳንቲም የጣለችን አንዲት ድሃ መበለት “ከጉድለትዋ የነበራትን ትዳርዋን ሁሉ ጣለች” በማለት አመስግኖ ተናገረ። በእርግጥም የእሷ ስጦታ ለይስሙላ ብቻ ከሚጥሉ ስግብግብ ሀብታሞች የተለየ ነበር! የይሖዋ ምሥክሮችም እንደዚያች ድሃ መበለት በዛሬው ጊዜ ዓለም አቀፉን የመንግሥት ሥራ ለመደገፍና ለማስፋፋት ጊዜያቸውን፣ ጉልበታቸውንና ገንዘባቸውን በፈቃደኛነት ይሠዋሉ። ይህም አድራጎታቸው የመንጎቻቸውን ጠጉር እየሸለቱ ለራሳቸው ከፍ ያለ የግል ሀብት ከሚያከማቹት የቴሌቪዢን ወንጌላውያን ፈጽሞ የተለየ ነው!—ሉቃስ 20:45–21:4
ኒሣን 11 ሊያበቃ በተቃረበበት ጊዜ
14. ኢየሱስ ምን አሳዛኝ ሁኔታ ገለጸ? የደቀ መዛሙርቱን ተጨማሪ ጥያቄ የመለሰው እንዴት ነው?
14 ኢየሱስ ለኢየሩሳሌምና ለሕዝቧ እያለቀሰ “በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው እስክትሉ ድረስ ከእንግዲህ ወዲህ አታዩኝም!” አለ። (ማቴዎስ 23:37-39) በኋላም በደብረ ዘይት ተቀምጠው ሳሉ የኢየሱስ የቅርብ ደቀ መዛሙርት ስለዚህ ጉዳይ ጠየቁትና መልስ ሲሰጣቸው በመንግሥቱ ሥልጣን መገኘቱንና የሰይጣን ክፉ ሥርዓት መደምደሚያ መቅረቡን የሚያመለክተውን ምልክት ገለጸላቸው።—ማቴዎስ 24:1–25:46፤ ማርቆስ 13:1-37፤ ሉቃስ 21:5-36
15. ኢየሱስ ለፍርድ ስለሚገኝበት ጊዜ ምን ምልክት ሰጠ? ይህስ የተፈጸመው ከመቼ ጀምሮ ነው?
15 ኢየሱስ በቤተ መቅደሱ ላይ ስለሚፈጸመው የይሖዋ የጥፋት ፍርድ ከተናገረ በኋላ ይህ ጥፋት ወደፊት በጠቅላላው ሥርዓት መደምደሚያ ላይ ለሚፈጸመው መቅሠፍታዊ ሁኔታ ጥላ እንደሚሆን አመልክቷል። የሚገኝበትም ጊዜ ከዚያ በፊት ታይቶ የማይታወቅ መጠን በሚኖረው ጦርነት፣ በፍቅር መጥፋትና ከአመጸኝነት ጋር አብሮ በሚመጣ ረሀብ፣ የምድር መናወጥና ቸነፈር ተለይቶ እንደሚታወቅ ተናግሯል። ይህም ከ1914 ወዲህ ባለው የ20ኛው መቶ ዘመን ክፍል በትክክል ተፈጽሞአል።
16, 17. ኢየሱስ በትንቢት የገለጸው የትኞቹን የዓለም ሁኔታዎች ነው? ክርስቲያኖችስ ለትንቢቱ ምላሽ መስጠት ያለባቸው እንዴት መሆን ይኖርበታል??
16 ይህ ሁሉ ሁኔታ ከፍተኛ መደምደሚያ ላይ የሚደርሰው “ከዓለምም መጀመሪያ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ያልሆነ እንግዲህም ከቶ የማይሆን ታላቅ መከራ” በሚሆንበት ጊዜ ነው። ይህ ታላቅ መከራም ልክ በኖኅ ዘመን እንደነበረው የውሃ መጥለቅለቅ ከፍተኛ ጥፋት የሚያስከትል ስለሚሆን ዓለማዊ ነገሮችን በማሳደድ እንዳንዋጥ ኢየሱስ አስጠንቅቋል። “ጌታችሁ በምን ሰዓት እንደሚመጣ አታውቁምና እንግዲህ ንቁ።” ስለዚህ የጌታ መገኘት ዘመን ማስጠንቀቂያ እንዲያሰማና የተትረፈረፈ ምግብ እንዲያቀርብ ጌታችን ቅቡዓን “ታማኝና ልባም ባሪያ” በመሾሙ ምንኛ ደስ ሊለን ይገባል!—ማቴዎስ 24:21, 42, 45-47
17 በዚህ በሃያኛው መቶ ዘመናችን ‘አሕዛብ መውጫውን በማጣት በፍርሃት ሲጨነቁና . . . በዓለም ላይ የሚመጣውን በመጠባበቅ በፍርሃት ሲሸበሩ’ ተመልክተናል። ኢየሱስ ግን “ይህ ሁሉ መሆን በሚጀምርበት ጊዜ ደህንነታችሁ ቀርቦአልና ቀና ብላችሁ ወደ ላይ ተመልከቱ” ብሏል። (የ1980 ትርጉም) “ነገር ግን ልባችሁ በመጠጥ ብዛትና በስካር ስለትዳርም በማሰብ እንዳይከብድ፣ ያ ቀንም በድንገት እንዳይመጣባችሁ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ” በማለትም አስጠንቅቆናል። “በሰው ልጅ” ማለትም በኢየሱስ መገኘት ጊዜ በፊቱ ሞገስ አግኝተን ልንቆም የምንችለው ነቅተን ከኖርን ብቻ ነው።—ሉቃስ 21:25-28, 34-36
18. ከኢየሱስ የ10ሩ ደናግልና የመክሊቶቹ ምሳሌ ምን ማበረታቻ ልናገኝ እንችላለን?
18 ኢየሱስ በዘመናችን ስለሚፈጸሙት ሁኔታዎች የተናገረውን አስደናቂ መግለጫ ሲያጠቃልል ሦስት ምሳሌዎችን ተናግሮአል። መጀመሪያ በአሥሩ ደናግል ምሳሌ ላይ “ነቅቶ የመጠበቅን” አስፈላጊነት በድጋሚ አጥብቆ ገልጿል። ከዚያም በባሪያዎቹና በመክሊቶቹ ምሳሌ ላይ ታታሪነት ‘ወደ ጌታው ደስታ ለመግባት’ እንደሚያስችልና ብዙ በረከት እንደሚያስገኝ አሳይቷል። በእነዚህ ምሳሌዎች ጥላነት የተገለጹት ቅቡዓን ክርስቲያኖችና ሌሎች በጎችም ከእነዚህ መግለጫዎች ብዙ ማበረታቻ ሊያገኙ ይችላሉ።—ማቴዎስ 25:1-30
19, 20. በኢየሱስ የበጎችና የፍየሎች ምሳሌ ላይ ምን ዘመናዊ ዝምድና ተለይቶ ተገልጾአል?
19 ሦስተኛው ምሳሌ ኢየሱስ በክብራማ ሰማያዊ ዙፋኑ ላይ ተቀምጦ በመንግሥታዊ ሥልጣኑ በሚገኝበት ጊዜ የሚሆነውን ነገር ያመለክታል። ይህ ጊዜም አሕዛብ የሚፈረዱበትና የምድር ሕዝቦች በሙሉ፤ ትሑት በግ መሰል ሰዎች በአንድ ወገን፣ እልከኞች የሆኑት ፍየል መሰል ሰዎች ደግሞ በሌላ ወገን በመሆን በሁለት ቡድን የሚለዩበት ጊዜ ነው። በጎቹ የንጉሡን ወንድሞች ማለትም በዓለም ፍጻሜ ዘመን በምድር ላይ የቀሩትን ቅቡዓን እንደሚደግፉ ለማሳየት ብዙ ችግር ይቀበላሉ። እነዚህ በጎች የሕይወት ሽልማት ሲቀበሉ አድናቆት የሌላቸው ፍየሎች ደግሞ ወደዘላለም ጥፋት ይሄዳሉ።—ማቴዎስ 25:31-46
20 በዚህ የሥርዓቱ መደምደሚያ ዘመን በሌሎች በጎችና በንጉሡ ወንድሞች መሃል እጅግ ታላቅ የሆነ ዝምድና እንመለከታለን። ንጉሡ በተገኘበት ዘመን መጀመሪያ ላይ ሥራው በአብዛኛው የተጫነው በቅቡዓን ቀሪዎች ላይ ቢሆንም ዛሬ ግን በምድር ላይ ከሚገኙት የአምላክ አገልጋዮች 99.8 በመቶ የሚሆኑት በሚሊዮን የሚቆጠሩት ቀናተኛ ሌሎች በጎች ናቸው። (ዮሐንስ 10:16) ፍጹም አቋም ጠባቂዎች እንደሆኑት ቅቡዓን ቀሪ ባልንጀሮቻቸው ‘ረሀብን፣ ጥማትን፣ እርዛትን፣ ሕመምንና እሥራትን’ በትዕግሥት ለመቀበል ፈቃደኞች መሆናቸውን አሳይተዋል።a
ኒሳን 12
21. ኒሳን 12 ላይ የተቀላጠፈው ምንድነው? እንዴትስ?
21 ኢየሱስን ለመግደል ይደረግ የነበረው ሴራ መቀላጠፍ ጀመረ። ይሁዳ ወደ ቤተመቅደሱ ሄዶ ሊቀ ካህናቱን አነጋገረና ኢየሱስን በ30 ብር አሳልፎ ለመስጠት ተስማማ። ይህም እንኳን ሳይቀር በትንቢት ተነግሮ ነበር።—ዘካርያስ 11:12
ኒሳን 13
22. በኒሳን 13 ምን ዝግጅት ተደረገ?
22 ኢየሱስ ለጸሎትና ለማሰላሰል እንዲመቸው ብሎ ሳይሆን አይቀርም በቢታኒያ ቀርቶ ደቀመዛሙርቱ “እገሌ የሚባል አንድ ሰው” እንዲፈልጉ ወደ ኢየሩሳሌም ላካቸው። በዚህ ሰው ቤት ትልቅ የእልፍኝ አዳራሽ ውስጥ ፋሲካን አሰናዱለት። (ማቴዎስ 26:17-19) ኒሳን 13 ፀሐይ ስትጠልቅ በታሪክ ዘመን ሁሉ እጅግ ታላቅ ነገር የተፈጸመበትን በዓል ከደቀመዛሙርቱ ጋር ለማክበር ወደ ኢየሩሳሌም ሄደ። ኒሳን 14 ምን ይዞ ይመጣ ይሆን? የሚቀጥለው ርዕሰ ትምህርታችን ይነግረናል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a የሚቀጥለው ርዕሰ ትምህርት በቅቡዓን ታናሽ መንጋና በሌሎች በጎች መሃል ያለውን የተቀራረበ ዝምድና ይበልጥ እንድንገዘነብ ሊረዳን ይገባል።
እንዴት ብለህ ታጠቃልላለህ?
◻ አንዳንዶች ለኢየሱስ ከኒሳን 8 እስከ 10 ባሉት ቀናት ምን ዓይነት መስተንግዶና አቀባበል አድርገው ነበር?
◻ ኢየሱስ ኒሳን 11 ቀን ግብዞቹን የሃይማኖት መሪዎች ያወገዘው እንዴት ነው?
◻ ኢየሱስ የትኛውን ታላቅ ትንቢት ተናገረ? ይህስ ትንቢት በዘመናችን በመፈጸም ላይ የሚገኘው እንዴት ነው?
◻ ኒሳን 12 እና 13 ቀን የመጨረሻዎቹ ክንውኖች መጣደፍ የጀመሩት እንዴት ነበር?
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ ሁለት ዲናሮች ማለትም የነበራትን ትዳርዋን ሁሉ የጣለችውን ድሃ መበለት አመሰገነ