የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w92 3/1 ገጽ 24-25
  • ምድሪቱን ጎብኙ፤ በጎቹን ጎብኙ!

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ምድሪቱን ጎብኙ፤ በጎቹን ጎብኙ!
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1992
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ኢየሱስ ለበጎቹ ያስባል
    ክርስቲያናዊ ሕይወታችንና አገልግሎታችን​—የስብሰባው አስተዋጽኦ—2018
  • መጽናኛ ማግኘት የሚቻለው ከየት ነው?
    ከታላቁ አስተማሪ ተማር
  • “የጠፋውን እፈልጋለሁ”
    ወደ ይሖዋ ተመለስ
  • ጥሩው እረኛ እና የበጎች ጉረኖዎች
    ኢየሱስ—መንገድ፣ እውነት፣ ሕይወት
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1992
w92 3/1 ገጽ 24-25

የተስፋይቱ ምድር ገጽታዎች

ምድሪቱን ጎብኙ፤ በጎቹን ጎብኙ!

በሺህ የሚቆጠሩ ክርስቲያኖች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ ሁኔታዎች የተፈጸሙባቸውን ቦታዎች ማየት መጽሐፍ ቅዱስን እንዲረዱ እንደሚረዳቸውና ይበልጥም ትርጉም ያለው እንደሚያደርግላቸው በማሰብ የተስፋይቱን ምድር ጎብኝተዋል። በእርግጥም መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያስተውሉ ረድቷቸዋል። የመጽሐፍ ቅዱስ ንባባቸውንም ትርጉም ያለው አድርጎላቸዋል።

ምድሪቱን በአካል እዚያው ሄደህ የጎበኘህም ሆንክ በመጻሕፍትና በጽሑፎች ላይ የሠፈሩትን በማጥናት ምድሪቱን በሐሳብህ የዳሰስካት ብትሆን በጎቹን ስለመጎብኘት አስበህ ታውቃለህን? በጎችን ከተስፋይቱ ምድር ጋር ምን አገናኛቸው? ብለህ ታስብ ይሆናል። እንደእውነቱ ከሆነ በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን በጎች የተስፋይቱ ምድር ኑሮ ዋና ክፍል ስለነበሩ የተስፋይቱ ምድር ጉብኝት በጎችን ካልጨመረ የተሟላ ነው ሊባል አይችልም።

ዛሬ በዚህ አካባቢ የሚታዩት በጎች በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ከነበሩት ጋር በጣም ስለሚመሳሰሉ እዚህ ላይ የምታየው ፎቶግራፍ የጉብኝትህ ክፍል ሊሆን ይችላል።a ረዣዥም ላታቸው በስብ የተሞላ ነው። (ዘሌዋውያን 7:3፤ 9:19) ወፍራሙ ጠጉራቸው አብዛኛውን ጊዜ ነጭ ነው። የያዕቆብ በጎች ግን “ዝንጉርጉርና ነቁጣ ያለበት ጥቁር” ነበሩ።—ዘፍጥረት 30:32

ይኸው ታሪክ ብዙ መንጋ ያለው ሰው ባለጠጋ ተደርጎ ይቆጠር እንደነበር ያሳያል። (ዘፍጥረት 30:43) ስለ ኢዮብ እንዲህ እናነባለን፦ “ሀብቱም ሰባት ሺህ በጎች፣ ሦስት ሺህም ግመሎች፣ አምስት መቶም ጥማድ በሬ፣ አምስት መቶም እንስት አህዮች ነበረ። . . . ያም ሰው በምሥራቅ ካሉ ሰዎች ሁሉ ይልቅ ታላቅ ነበረ።” (ኢዮብ 1:3፤ 42:12) ናባልም 3,000 በጎችና 1,000 ፍየሎች እንደነበሩት አስታውሱ። ናባል በዳዊት ዘመን ምን አይነት ማዕረግና ሥልጣን የነበረው ይመስላችኋል? (1 ሳሙኤል 25:2) ይሁን እንጂ ብዙ መንጋ እንደትልቅ ብልጥግና ይቆጠር የነበረው ለምን ነበር?

ይህ የሆነበት ምክንያት በጎች ለእረኛው ወይም ለባለቤታቸው ጠቃሚ ምርቶችን ያስገኙ ስለነበረ ነው። ሱፋቸው ወይም ጠጉራቸው ራሱ ሁሌ የሚታደስ ንብረት ነበረ። ምሳሌ 31:13, 21, 22 ይህን ሱፍ አንዲት ልባምና ታታሪ ሴት ለቤተሰቧ ልብስ ለመሥራት ወይም የሚሸጡ ልብሶች ለመሥራት እንዴት ልትጠቀምበት እንደምትችል ለመረዳት እንድንችል ይረዳናል። (ኢዮብ 31:20) ሱፍ ጠቃሚ የሆነ የንግድ ሸቀጥ ነበረ። ይህም የሞአብ ንጉሥ “ባለበጎች ነበረ። ለእሥራኤልም ንጉሥ የመቶ ሺህ ጠቦትና የመቶ ሺህ ያልተሸለቱ አውራ በጎች ይገብርለት ነበር” በሚለው መግለጫ ላይ ተመልክቷል። (2 ነገሥት 3:4) አዎን “ያልተሸለቱ” በጎች መሆናቸው ዋጋቸውን ከፍ አድርጎት ነበር።

አውራ በጎች በስተቀኝ በኩል በፎቶግራፍ ላይ እንደሚታየው በግ ያሉ አስደናቂ ቀንዶች ሊኖራቸው ይችላል። ይህስ ኢዮቤልዩን ለማወጅ ያገለግል የነበረው መለከት የበግ ቀንድ እንደነበረ ያስታውሳችኋልን? (ዘሌዋውያን 25:8-10) ቀዳዳ ያላቸው ተመሳሳይ መለከቶች የማስጠንቀቂያ ድምጽ ለማሰማት ወይም የጦር እንቅስቃሴዎችን ለመምራት ያገለግሉ ነበር።—መሳፍንት 6:34፤ 7:18, 19፤ ኢዮኤል 2:1

መገንዘብ እንደሚቻለው የበጎች መንጋ ካላችሁ ቀለብም አይቸግራችሁም ማለት ነው። ምክንያቱም በጎች እሥራኤላውያን ሊበሉ ከሚችሉአቸው ንጹሕ እንስሳት መሃል ስለሆኑ ነው። (ዘዳግም 14:4) ሥጋው ተቀቅሎ ወይም ተጠብሶ ሊበላ ይችል ነበር። የተጠበሰ የበግ ሥጋ በየዓመቱ በሚከበረው የማለፍ በዓል የሚቀርብ ዋነኛ ምግብ ነበር። (ዘጸአት 12:3-9) በጎች ለመጠጥም ሆነ አይብ ለመሥራት የሚያገለግል ወተት ይሰጣሉ።—1 ሳሙኤል 17:17, 18፤ ኢዮብ 10:10፤ ኢሳይያስ 7:21, 22

በበጎች መንጋና በእረኛቸው መሃል ያለውን ጥብቅ መተሳሰር ማስተዋልም በጎችን ከመጎብኘት የሚገኝ ትልቅ ትምህርት ነው። ታማኝ የበግ እረኛ በጎቹን ይንከባከባል። በጎቹ ኢየሱስ እንደጠቀሰው የእረኛቸውን ድምፅ ለይተው ስለሚያውቁ በስም በሚጠራቸው ጊዜ ምላሽ ይሰጣሉ። (ዮሐንስ 10:3, 4) ትጉህ የበግ እረኛ አንድ በግ እንኳን ቢጠፋበት ይፈልገዋል። የጠፋበትን በግ ሲያገኘው በትከሻው ላይ ተሸክሞ ወደ መንጎቹ ያመጣዋል።—ሉቃስ 15:4, 5

ዳዊት ራሱን ይሖዋ እረኛው ከሆነለት በግ ጋር ሲያመሳስል እሱ ራሱ ከመንጎቹ ጋር የነበረውን የግል ተሞክሮ አስታውሷል። በጎች በእረኛቸው አማካኝነት ጥበቃ ያገኙ እንደነበረ ሁሉ ዳዊትም የይሖዋን ጥበቃ አግኝቷል። በጎቹ የሚንከባከባቸውን እረኛ አመራር ይከተላሉ። ጉዳት ቢደርስባቸውም ፈዋሽ ዘይት ቀብቶ ቁስላቸውን ያስርላቸው ነበር። ይህስ በሕዝቅኤል 34:3-8 ላይ ከተገለጹት የእሥራኤል መሪዎች የራስ ወዳድነት ተግባር ምንኛ የተለየ ነው!

መጽሐፍ ቅዱስ በርካታ ስለ በጎች የሚገልጹ ትንቢታዊና ምሳሌያዊ መግለጫዎችን ይዟል። ስለዚህ የተስፋይቱን ምድር በጎች መጎብኘትህና ከእነሱም ጋር መተዋወቅህ እንደ “ታናሹ መንጋ”፣ “የእግዚአብሔር በግ” እና “ሌሎች በጎች” የመሰሉትን አነጋገሮች በጥልቅ እንድትረዳ ያስችልሃል።—ሉቃስ 12:32፤ ዮሐንስ 1:36፤ 10:16

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ከላይ የሚታየውን የይሁዳ ምድረ በዳና የበጎች ፎቶግራፍ በ1992 የይሖዋ ምሥክሮች የቀን መቁጠሪያ ላይ ማየት ይቻላል።

[በገጽ 24 ላይ የሚገኘው ሥዕል ምንጭ]

Pictorial Archive (Near Eastern History) Est.

[በገጽ 25 ላይ የሚገኘው ሥዕል ምንጭ]

Garo Nalbandian

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ