ብዙ ሰዎች ለአምላክ መንግሥት የሚሰጡት ትርጉም
ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ አምላክ መንግሥት አዘውትሮ ይናገር ነበር። ይህን በሚመለከት ታሪክ ጸሐፊው ኤች ጂ ዌልስ እንዲህ በማለት ጽፈዋል፦ “ኢየሱስ መንግሥተ ሰማይ ብሎ ለጠራው ትምህርት ከፍተኛ ቦታ መስጠቱና በአንፃሩ ግን በአብዛኞቹ አብያተ ክርስቲያናት ሥርዓትና ትምህርት ውስጥ መንግሥተ ሰማይ ከቁምነገር አለመግባቱ የሚያስደንቅ ነገር ነው። የኢየሱስ ዋነኛ ትምህርት የነበረውና በክርስትና እምነት ውስጥ ግን በጣም አነስተኛ ቦታ ብቻ የተሰጠው የዚህ የመንግሥተ ሰማይ መሠረተ ትምህርት በእርግጥ የሰውን አስተሳሰብ የቀሰቀሰና የለወጠ ከሁሉ የበለጠ ከፍተኛ ለውጥ ያስከተለ መሠረተ ትምህርት ነው።”
አብያተ ክርስቲያናት ስለ አምላክ መንግሥት እምብዛም የማይናገሩት ለምንድነው? አንዱ ምክንያት ምናልባት ስለ መንግሥቲቱ እርግጠኞች ስላልሆኑ ሊሆን ይችላል። ታዲያ ስለመንግሥቲቱ ምን ዓይነት አመለካከቶች አሉ?
መንግሥቲቱ እንዴት ስትታይ እንደቆየች
አንዳንዶች የአምላክን መንግሥት ከካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ጋር አንድ አድርገዋል። በ325 እዘአ በኒቂያ ጉባኤ ጳጳሳት ንጉሠ ነገሥት ቆስጠንጢኖስን የቤተ ክርስቲያን ራስ አድርገው በተቀበሉ ጊዜ ቤተክርስቲያን በፖለቲካ ጉዳዮች ውስጥ መግባት ጀመረች። ለሕዝቡም የአምላክ መንግሥት እንደመጣች ተነገረ። ዘ ኢንሳይክሎፒድያ ብሪታኒካ አውግስቲን (354-430)ባስተማረው መንፈሳዊ ትምህርት መሠረት “የእግዚአብሔር መንግሥት በዚህ ዓለም ላይ መግዛት የጀመረችው ቤተ ክርስቲያን በተቋቋመች ጊዜ ነው።” ቤተ ክርስቲያን በምትሰጠው የቁርባን ሥርዓት ውስጥ ትገኛለች።”
ሌሎች ደግሞ የአምላክ መንግሥት የምትገኘው በሰው ልጆች ጥረት እንደሆነ አድርገው ያስባሉ። ይኸው ኢንሳይክሎፒድያ እንዲህ ይላል፦ “የተሐድሶ አብያተ ክርስቲያናትም . . . ወዲያውኑ የተደራጁና በግዛት የተከፋፈሉ ሆኑ። ይህም [የእግዚአብሔርን መንግሥት መምጣት በሚመለከት የነበረውን]የፍጻሜ ዘመን ተስፋ ቀጨው።” ኤች ጂ ዌልስ እንዲህ በማለት ጽፈዋል፦ “ሰዎች የሕይወታቸውን ተጠያቂነት ለአምላክ መንግሥትና ለሰው ልጅ ወንድማማችነት ከማድረግ ይልቅ ተጨባጭ እውነታዎች መስለው ወደሚታዩት ወደ ፈረንሳይ፣ እንግሊዝ፣ ቅድስቲቱ ሩሲያ፣ እስፓኝ፣ ፕራሺያ፣ . . . አዛወሩ። እነዚህ መንግሥታት የአውሮፓ ተጨባጭና ሕያው አማልክት ነበሩ።”
በዘመናችንም መንግሥቲቱ ዓለማዊ መንግሥት እንደሆነች ተደርጋ ትታያለች። ዘ ኢንሳይክሎፒድያ ብሪታኒካ “ዋናው መሠረታዊ አመለካከት ሰው ራሱ መጪውን ፍጹም ህብረተሰብ መገንባትና በተቀናበረ ሁኔታ ማዘጋጀት አለበት የሚለው ነው። ‘ተስፋ ማድረግና’ ‘መጠባበቁ’ በሰው እየተተካ ነው” በማለት ገልጿል። ይኸው ጽሑፍ “ማህበራዊ ወንጌል” የተባለውን በሚመለከት እንዲህ ይላል፦ “ይህ ንቅናቄ ስለ እግዚአብሔር መንግሥት የሚገልጸውን የክርስቲያን መልእክት ዓለማዊውን ህብረተሰብ ከእግዚአብሔር መንግሥት ሥነ ምግባር አንፃር እንደገና ለማዋቀር እንደሚያስችል ግፊት ብቻ አድርጎ ማየት ጀመረ።”
ብዙ አይሁዳውያንም መንግሥቲቱን የሚመለከቷት የሰው ልጅ ጥረት ውጤት እንደሆነች አድርገው ነው። በ1937 በዩናይትድ ስቴትስ ኮለምበስ ኦሃዮ የተደረገ የአይሁዳውያን የተሐድሶ መምህራን ስብሰባ “ዓለም አቀፍ ወንድማማችነት፣ ፍትሕ፣ እውነትና ሰላም የሚመሠረትበትን የእግዚአብሔር መንግሥት ለማቋቋም ከሰዎች ሁሉ ጋር መተባበር ታሪካዊ ተግባራችን እንደሆነ አድርገን እንቆጥራለን” ብሏል።
ሠፊ ተቀባይነት ያገኘው ሌላው አመለካከት ደግሞ የአምላክ መንግሥት የሰው የልብ ዝንባሌ ናት የሚለው ነው። ለምሳሌ ያህል በዩናይትድ ስቴትስ በ1925 የተደረገው የደቡባዊ ባፕቲስት ስብሰባ “የእግዚአብሔር መንግሥት ማለት በማንኛውም ሰብአዊ ዝምድና፣ በማንኛውም የኑሮ ፈርጅና በማንኛውም የተደራጀ የኅብረተሰብ ተቋም ውስጥ አምላክ በግለሰቡ ልብና ሕይወት ውስጥ የሚኖረው ገዥነት ነው። . . . የእያንዳንዱ ሰው አስተሳሰብና ፈቃድ ለክርስቶስ ፈቃድ ሲገዛ ያኔ የእግዚአብሔር መንግሥት ፍጹም ትሆናለች” ብሏል።
እንግዲያውስ ቤተ ክርስቲያን የእግዚአብሔር መንግሥት ነችን? ይህች መንግሥት የምትመጣው በዓለማዊ መንገድ ነውን? መንግሥቲቱ የልብ ሁኔታ ናትን? የአምላክ መንግሥት ለአንተ ምን ትርጉም አላት?