የአምላክ መንግሥት ለአንተ ምን ትርጉም ሊኖራት ይችላል?
ኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮቹ “መንግሥትህ ትምጣ” ብለው እንዲጸልዩ አስተምሯል። (ማቴዎስ 6:10) እነዚህ ቃላት የኢየሱስ ተከታዮች ነን በሚሉ ሰዎች ብዙ ጊዜ ተደጋግመው ወደ አምላክ ቀርበዋል!
ይሁን እንጂ ኢየሱስ ተከታዮቹ መንግሥቲቱ እንድትመጣ እንዲጸልዩ በማስተማር ብቻ አላቆመም። መንግሥቲቱን የስብከት ሥራው ዋና ርዕሰ ጉዳይ አድርጓል። እንዲያውም ኢንሳይክሎፒድያ ብሪታኒካ የእግዚአብሔር መንግሥት “ባጠቃላይ የምትታየው የኢየሱስ ትምህርት ማዕከላዊ መልእክት እንደሆነች ነው” ይላል።
የክርስቶስ ተከታዮች መንግሥቲቱ እንድትመጣ ሲጸልዩ ስለምን ነገር መጸለያቸው ነው? የአምላክ መንግሥት ለእነሱም ሆነ ለአንተ ምን ትርጉም ሊኖራት ይችላል? ኢየሱስስ መንግሥቲቱን እንዴት ይመለከታት ነበር?
ኢየሱስ ለመንግሥቲቱ የነበረው አመለካከት
ኢየሱስ ብዙ ጊዜ ራሱን “የሰው ልጅ” እያለ ይጠራ ነበር። (ማቴዎስ 10:23፤ 11:19፤ 16:28፤ 20:18, 28) ይህም ነቢዩ ዳንኤል “የሰው ልጅ” በማለት የጠቀሰውን ያስታውሰናል። ዳንኤል ወደፊት ስለሚፈጸም ሰማያዊ ሁኔታ እንዲህ ብሎ ነበር፦ “በሌሊት ራዕይ አየሁ እነሆም፣ የሰው ልጅ የሚመስል ከሰማይ ደመናት ጋር መጣ በዘመናት ወደሸመገለውም ደረሰ ወደፊቱም አቀረቡት። ወገኖችና አሕዛብ በልዩ ልዩ ቋንቋም የሚናገሩ ሁሉ ይገዙለት ዘንድ ግዛትና ክብር መንግሥትም ተሰጠው።”—ዳንኤል 7:13, 14
ኢየሱስ ይህን ግዛት ስለሚቀበልበት ጊዜ ሲናገር ለሐዋርያቱ እንዲህ ብሏቸዋል፦ “እናንተ የተከተላችሁኝ በዳግመኛ ልደት የሰው ልጅ በክብሩ ዙፋን በሚቀመጥበት ጊዜ እናንተ ደግሞ በአሥራ ሁለቱ የእሥራኤል ነገድ ስትፈርዱ በአሥራ ሁለት ዙፋን ትቀመጣላችሁ።” ኢየሱስ በተጨማሪም “የሰው ልጅ በክብሩ በሚመጣበት ጊዜ . . . አሕዛብም ሁሉ በፊቱ ይሰበሰባሉ። እረኛም በጎቹን ከፍየሎች እንደሚለይ እርስ በርሳቸው ይለያቸዋል። . . . እነዚያም [አመጸኞች] ወደ ዘላለም ቅጣት ጻድቃን ግን ወደ ዘላለም ሕይወት ይሄዳሉ” ብሏል።—ማቴዎስ 19:28፤ 25:31, 32, 46
ስለ ዙፋኖችና ስለ ልዩ ልዩ አሕዛብ የሚናገሩት እነዚህ መግለጫዎች መንግሥቲቱ ኢየሱስና አንዳንድ ተከታዮቹ በሰው ልጆች ላይ የሚገዙባት መስተዳድር እንደሆነች ያመለክታሉ። ይህች መንግሥት ኃጢአተኞችን በሞት ለመቅጣት የሚያስችል ኃይል ያላት ናት። ይሁን እንጂ የጽድቅ ዝንባሌ ያላቸው ሰዎች በመንግሥቲቱ አስተዳደር ሥር የዘላለም ሕይወትን ስጦታ ይቀበላሉ።
እንግዲያውስ በግልጽ እንደምናየው የአምላክ መንግሥት በአምላክ የተቋቋመች ሰማያዊ መንግሥት ናት። መንግሥቲቱ ቤተ ክርስቲያን አይደለችም። ቅዱሳን ጽሑፎችም ከዚህ ዓለም ጋር ምንም ዓይነት ዝምድና እንዳላት አይናገሩም። ከዚህም በላይ ከአምላክ የሚሰጥ መስተዳድር በአንድ ሰው ልብ ውስጥ ብቻ ተወስኖ የሚኖር ነገር ሊሆን አይችልም። የአምላክ መንግሥት መስተዳድር ስለሆነች ክርስትናን በምንቀበልበት ጊዜ በልባችን ውስጥ የምትቀመጥ ነገር ልትሆን አትችልም። ታዲያ አንዳንድ ሰዎች መንግሥቲቱ የልብን ሁኔታ የምታመለክት ናት ብለው የሚያስቡት ለምንድን ነው?
መንግሥቲቱ በውስጣችን የምትገኝ ናትን?
አንዳንድ ሰዎች መንግሥቲቱ በውስጣችን የምትገኝ ነገር እንደሆነች እንዲያስቡ ያደረጋቸው ሉቃስ 17:21 በአንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ላይ የተተረጐመበት ሁኔታ ነው። ዘ ኒው ኢንተርናሽናል ቨርሽን እንደተረጎመው ኢየሱስ “መንግሥቲቱ በውስጣችሁ ናት” ብሏል።
ይህን በሚመለከት ዘ ኢንተርፕሪተርስ ዲክሽነሪ ኦቭ ዘ ባይብል እንዲህ ይላል፦ “ብዙ ጊዜ ኢየሱስ ስለ ‘ምስጢራዊነት’ ወይም ስለ ‘ውስጣዊነት’ እንደተናገረ ተደርጎ ቢጠቀስም ይህ አተረጓጎም ባብዛኛው የተመካው በእንግሊዝኛው ‘within you’ (በአማርኛ ‘በውስጥህ’ ወይም ‘በአንተ ውስጥ’ ማለትም ሊሆን ይችላል) በሚለው የቀድሞ ትርጉም ላይ ነው። . . . ተርጓሚዎቹ ‘you’ የሚለውን የእንግሊዝኛ ቃል በነጠላው (‘አንተ’ እንደሚል አድርገው) መረዳታቸው ተገቢ ያልሆነ ግንዛቤ ነው። (ኢየሱስ በቁጥር 20 ላይ ይናገር የነበረው ለፈሪሳውያን ስለነበረ) እዚህ ላይ ያለው ‘you’ . . . የብዙ ቁጥርን የሚያመለክት ነው። . . . የእግዚአብሔር መንግሥት የአእምሮ ውስጣዊ ሁኔታ፣ ወይም የግል መዳን እንደሆነች የሚናገረው ንድፈ ሐሳብ በዚህ ጥቅስ ዙሪያ ካሉት ሐሳቦች ጋርና መላው አዲስ ኪዳን በዚህ ሐሳብ ላይ ካለው አቀራረብ የሚቃረን ነው።”
ዘ ኒው ኢንተርናሽናል ቨርሽን ስለ ሉቃስ 17:21 በግርጌ ማስታወሻው ላይ የኢየሱስ ቃላት “የእግዚአብሔር መንግሥት በመካከላችሁ ናት” ተብሎ ሊተረጎም እንደሚችል ይገልጻል። ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞችም “የእግዚአብሔር መንግሥት በመካከላችሁ ናት” ወይም “የእግዚአብሔር መንግሥት በእናንተ መሃል ናት” በማለት ይነበባሉ። (ዘ ኒው ኢንግሊሽ ባይብል፣ ዘ ጀሩሳሌም ባይብል፣ ሪቫይዝድ እስታንዳርድ ቨርሽን) በአዲሲቱ ዓለም ትርጉም መሠረት ኢየሱስ “የአምላክ መንግሥት በእናንተ መሃል ናት” ብሏል። ኢየሱስ መንግሥቲቱ ይናገራቸው በነበሩት ኩራተኛ ፈሪሳውያን ውስጥ ነበረች ማለቱ አልነበረም። ኢየሱስ ለረዥም ጊዜ ሲጠበቅ የቆየው መሲሕና የተሰየመ ንጉሥ በመሆን በመካከላቸው መገኘቱን ማመልከቱ ነበር። ይሁን እንጂ የአምላክ መንግሥት የምትመጣው ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ነበር።
መንግሥቲቱ የምትመጣው መቼ ነው?
አንዳንድ የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮች በሰማያዊቱ መሲሐዊት መንግሥት አብረዉት እንዲገዙ ተመርጠዋል። እነሱም እንደ ኢየሱስ ለአምላክ ታማኝ ሆነው ከሞቱ በኋላ መንፈሳዊ ሕይወት ይዘው በሰማይ እንዲኖሩ ትንሣኤ ያገኛሉ። (1 ጴጥሮስ 3:18) ቁጥራቸው ከሌሎች የዘላለም ሕይወት ወራሾች ጋር ሲወዳደር ጥቂት ሲሆን ከሰው ዘር መሃል የተዋጁ 144,000 ነገሥታትና ካህናት ይሆናሉ። (ራዕይ 14:1-4፤ 20:6) ከኢየሱስ ተባባሪ ገዢዎች መካከል ታማኝ ሐዋርያቱም ይኖራሉ።—ሉቃስ 12:32
ባንድ ወቅት ኢየሱስ ለተከታዮቹ ሲናገር “የሰው ልጅ በመንግሥቱ ሲመጣ እስኪያዩ ድረስ እዚህ ከሚቆሙት ሞትን የማይቀምሱ አንዳንድ አሉ” በማለት ቃል ገብቶ ነበር። (ማቴዎስ 16:28) ቀጥሎ ያለው ቁጥር ከጥቂት ቀናት በኋላ ይህ የኢየሱስ ተስፋ እንደተፈጸመ ይገልጻል። በዚያን ጊዜ ሦስት ደቀ መዛሙርቱን ወደ ተራራ ይዞአቸው ወጥቶ በፊታቸው ሲለወጥ በመንግሥቱ በሚመጣበት ጊዜ የሚኖረውን ክብር በራዕይ ተመለከቱ። (ማቴዎስ 17:1-9) ይሁንና መንግሥቲቱ በዚያን ጊዜ ገና አልተቋቋመችም ነበር። ታዲያ የምትቋቋመው መቼ ነበር?
ከኢየሱስ ምሳሌዎች አንዱ ኢየሱስ ወዲያውኑ መሲሐዊ ንጉሥ ሆኖ እንደማይሾም ያመለክታል። በሉቃስ 19:11-15 ላይ እንዲህ እናነባለን፦ “ወደ ኢየሩሳሌም መቅረቡ ስለሆነ የእግዚአብሔርም መንግሥት ፈጥኖ ሊገለጥ እንዳለው ስለመሰላቸው ምሳሌ ጭምር ተናገረ። ስለዚህም እንዲህ አላቸው፦ አንድ መኮንን ለራሱ መንግሥትን ይዞ ሊመለስ ወደሩቅ አገር ሄደ። አሥር ባሪያዎችንም ጠርቶ አሥር ምናን ሰጣቸውና፦ እስክመጣ ድረስ ነግዱ አላቸው። . . . መንግሥትንም ይዞ በተመለሰ ጊዜ ገንዘብ የሰጣቸውን እነዚያን ባሪያዎች ነግደው ምን ያህል እንዳተረፉ ያውቅ ዘንድ እንዲጠሩለት አዘዘ።”
በዚያ ዘመን አንድ ሰው ከእሥራኤል ወደ ሮም ተጉዞ፣ ሥልጣን እስኪሰጠው ቆይቶ ንጉሥ ሆኖ ወደ ትውልድ ቦታው ለመመለስ ብዙ ጊዜ ይፈጅ ነበር። ‘መኮንኑ’ ኢየሱስ ነው። የንጉሥነት ሥልጣኑን የሚቀበለው በሰማይ ካለው አባቱ ነው። ይሁንና ወዲያውኑ መሲሐዊ ንጉሥ ሆኖ አይሾምም። ንጉሥ ሆኖ እስኪመለስ ድረስ በሚኖረው የተወሰነ ጊዜ ተከታዮቹ የመንግሥቲቱን የምሥራች የማወጅ ሥራቸውን በማካሄድ ሲነግዱ ይጠብቁታል።
መንግሥቲቱ የምትመጣው እንዴት ነው?
የአምላክ ወዳጆች መንግሥቱ እንድትመጣ በሚጸልዩበት ጊዜ ምን መለመናቸው ነው? ሰማያዊቱ መንግሥት እውነተኛ ሰላምና ብልጽግና እናመጣለን ብለው የገቡትን ተስፋ ሳይፈጽሙ የቀሩትን ሰው ሠራሽ መንግሥታዊ ሥርዓቶች በማጥፋት ወሳኝ እርምጃ እንድትወስድ መጠየቃቸው ነው። ነቢዩ ዳንኤል ይህን ሁኔታ በማስመልከት “በእነዚያም ነገሥታት ዘመን የሰማይ አምላክ ለዘላለም የማይፈርስ መንግሥት ያስነሣል፤ ለሌላ ሕዝብም የማይሰጥ መንግሥት ይሆናል፤ እነዚያንም መንግሥታት ሁሉ ትፈጫቸዋለች ታጠፋቸውማለች፣ ለዘላለምም [ጸንታ] ትቆማለች” በማለት ጽፏል። (ዳንኤል 2:44) ታዲያ ይህ የሚሆነው መቼ ነው?
ኢየሱስ ይህ የሚፈጸመው በሰው ታሪክ ውስጥ ተወዳዳሪ የማይገኝለት ብጥብጥ ሲደርስ በሚያዩ ሕዝቦች ትውልድ ውስጥ እንደሚሆን ተንብዮአል። ኢየሱስ “መገኘቱን” በሚመለከት ከዚያ በፊት ታይቶ የማይታወቅ ጦርነት፣ የምድር መናወጥ፣ ረሀብ፣ ቸነፈር እንደሚሆንና የአምላክ መንግሥት ምሥራች በዓለም አቀፍ ደረጃ እንደሚሰበክ በመግለጽ የተጠቃለለ “ምልክት” ሰጥቷል።—ማቴዎስ ምዕራፍ 24, 25፤ ማርቆስ ምዕራፍ 13፤ ሉቃስ ምዕራፍ 21
የኢየሱስ ትንቢት አሁን በዚህ በ20ኛው መቶ ዘመን እየተፈጸሙ ያሉትን ሁኔታዎች የሚመለከት ነው። ስለዚህ የአምላክ መንግሥት ለሰው ዘር ታላቅ በረከቶችን የምታመጣበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም። የመንግሥቲቱ አገዛዝ የሚያመጣቸውን ጥቅሞች ከሚያገኙት ሰዎች መሃል ልትሆን ትችላለህ። ይሁንና የአምላክ መንግሥት ለአንተና ለምታፈቅራቸው ሰዎች ምን ትርጉም ሊኖራት ይችላል?
የመንግሥቲቱ አገዛዝ የምታመጣቸው በረከቶች
በምድር ዙሪያ ደስታ ይሠፍናል። “በአዲስ ሰማያት” ማለት በሰማያዊው መንግሥት ሥር “አዲስ ምድር” ማለትም የመንግሥቲቱ ታዛዥ ዓለም አቀፍ ተገዢዎች ይኖራሉ። ሐዋርያው ዮሐንስ “እግዚአብሔርም እርሱ ራሱ ከእነርሱ ጋር ሆኖ አምላካቸው ይሆናል” ብሏል። “እንባዎችንም ከዓይኖቻቸው ያብሳል።” በዚያን ጊዜ ከደስታ በቀር ምንም ዓይነት የሚያሳዝን ነገር አይኖርም። ምክንያቱም “ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም።”—ራዕይ 21:1-4
ከእንግዲህ ወዲህ ሞት አይኖርም። ይህ መራራ ኀዘን የሚያመጣብን ሞት ወዳጆቻችንንና የምናፈቅራቸውን ሰዎች አይነጥቀንም። ‘ሞት የኋለኛው ጠላት በመሆን ይሻራል።’ (1 ቆሮንቶስ 15:26) የቀብር ሥነ ሥርዓቶች በአምላክ መታሰቢያ ውስጥ በሚገኙ ሰዎች ትንሣኤ ሲተኩ ምን ዓይነት ታላቅ ደስታ ይኖር ይሆን!—ዮሐንስ 5:28, 29
ሕመምና አካላዊ ድካም በጥሩ ጤንነት ይተካል። ከዚያ በኋላ የሆስፒታል አልጋዎች በአካላዊና በአእምሮ ሕመም በታወኩ ሰዎች አይጨናነቁም። የሕክምና ሊቅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ “ለአሕዛብ መፈወሻ” እንዲሆን የቤዛውን ዋጋ ሥራ ላይ ያውላል። (ራዕይ 22:1, 2፤ ማቴዎስ 20:28፤ 1 ዮሐንስ 2:1, 2) በምድር ላይ ሳለ ያከናወናቸው ፈውሶች በመንግሥቱ አማካኝነት ለሚያደርጋቸው ነገሮች ናሙና የሚሆኑ ነበሩ።—ከኢሳይያስ 33:24፤ ማቴዎስ 14:14 ጋር አወዳድሩ።
የምግብ አቅርቦት የተትረፈረፈ ይሆናል። መዝሙራዊው እንደተናገረው “በምድር ላይ በቂ እህል ይኖራል። ተራራዎችም በሰብል ይሸፈናሉ።” (መዝሙር 72:16) በዚህም ላይ የኢሳይያስ ትንቢት እንዲህ በማለት ይጨምርበታል፦ “የሠራዊት ጌታ [ይሖዋ(አዓት)] በዚህች በጽዮን ተራራ ለዓለም መንግሥታት ሁሉ ታላቅ ግብዣ ያዘጋጃል፤ የመልካም ምግብና የጥሩ ወይን ጠጅ ግብዣ ይሆናል።” (ኢሳይያስ 25:6 እንደ 1980 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ እትም) በእርግጥ በመንግሥቲቱ ግዛት ሥር ረሀብ የምድርን ነዋሪዎች አያሳድድም።
መላዋ ምድር ገነት ትሆናለች። ስለዚህ ኢየሱስ ለተጸጸተው ክፉ አድራጊ “ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ” በማለት የገባለት የተስፋ ቃል ይፈጸማል። (ሉቃስ 23:43) አንተም ከክፋት ጸድታ አስደሳች የመናፈሻ ቦታ ወደ መምሰል በምትለወጠው ምድር ላይ የዘላለም ሕይወት ልታገኝ ትችላለህ።—ዮሐንስ 17:3
እነዚህ አስደናቂ ተስፋዎች በታዛዥ ሰዎች ሁሉ ፊት ተዘርግተዋል። በይሖዋ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፈው ቃሉ መጽሐፍ ቅዱስ እነዚህን የተባረኩ ዋስትናዎች ይሰጣል። የአምላክ መንግሥት ለአንተ የሚኖራት ትርጉም እነዚህን ሁሉ የሚያጠቃልል ሊሆን ይችላል።
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ ስለ አምላክ መንግሥት የተናገረውን ታምናለህ?