የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w92 3/15 ገጽ 8-13
  • ከአምላክ የሚሰጠውን ነፃነት ዓላማ አትሳቱ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ከአምላክ የሚሰጠውን ነፃነት ዓላማ አትሳቱ
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1992
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • አምላክ ያለው ነፃነት
  • ለሰው የተሰጠው ነፃነት የተገደበ ነው
  • ነፃነታችን አንፃራዊ የሆነው ለምንድነው?
  • እውነተኛ ነፃነት ሊገኝ ችሏል
  • ከአምላክ የሚሰጠውን ነፃነት ዓላማ አለመሳት
  • ከአምላክ የተቀበላችሁትን ነፃነት በሚገባ ተጠቀሙበት
  • ወደ “ነፃነት አፍቃሪዎች” የወረዳ ስብሰባዎች እንድትመጡ ተጋብዛችኋል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
  • የነፃነት አምላክ የሆነውን ይሖዋን አገልግሉ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2018
  • ነፃ፣ ግን ተጠያቂነት ያለበት ሕዝብ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1992
  • እውነተኛ ነፃነት የሚያስገኘው መንገድ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2018
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1992
w92 3/15 ገጽ 8-13

ከአምላክ የሚሰጠውን ነፃነት ዓላማ አትሳቱ

“የይሖዋ መንፈስ ባለበት፣ በዚያ ነፃነት አለ።”—2 ቆሮንቶስ 3:17

1. ኢሳይያስ 65:13, 14 በይሖዋ ምሥክሮች ላይ የሚሠራው ለምንድን ነው?

ይሖዋ የነፃነት አምላክ ነው። ከአምላክ የሚሰጠው ነፃነት ምንኛ ታላቅ በረከት ነው! የሠራዊት ጌታ የይሖዋ ባሪያዎች እንዲህ ዓይነቱ ነፃነት ስላላቸው “እነሆ ባሪያዎቼ ይበላሉ እናንተ ግን ትራባላችሁ እነሆ፣ ባሪያዎቼ ይጠጣሉ እናንተ ግን ትጠማላችሁ እነሆ፣ ባሪያዎቼ ደስ ይላቸዋል እናንተ ግን ታፍራላችሁ እነሆ፣ ባሪያዎቼ ከልባቸው ደስታ የተነሣ ይዘምራሉ፣ እናንተ ግን ከልባችሁ ኀዘን የተነሣ ትጮሃላችሁ፣ መንፈሳችሁም ስለተሰበረ ወዮ ትላላችሁ” በማለት የተናገራቸው ቃላት በእነርሱ ላይ ተፈጻሚነት አግኝተዋል።—ኢሳይያስ 65:13, 14

2. የይሖዋ ሕዝቦች በመንፈሳዊ የበለጸጉ የሆኑት ለምንድን ነው?

2 የአምላክ ሕዝቦች ይህን መንፈሳዊ ብልጽግና ያገኙት በአምላክ መንፈስ ወይም ፈጣን ኃይል ስለሚመሩ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ “[ይሖዋ (አዓት)] መንፈስ ነው፤ [የይሖዋ (አዓት)] መንፈስ ባለበት በዚያ አርነት አለ” ብሏል። (2 ቆሮንቶስ 3:17) ታዲያ ይህ ከአምላክ የሚሰጠው ነፃነት ዓላማው ምንድን ነው? ከዚህ ነፃነት ሙሉ በሙሉ እንድንጠቀምበትስ ምን ነገር ይፈለግብናል?

አምላክ ያለው ነፃነት

3. አምላክ ምን ዓይነት ነፃነት አለው? ለምንስ?

3 ገደብ የሌለው ፍጹም ነፃነት ያለው ይሖዋ ብቻ ነው። እርሱ ሁሉን ቻይ አምላክና የጽንፈ ዓለሙ የበላይ ገዥ ስለሆነ የእሱን ነፃነት ሊገድብበት የሚችል አንድም ፍጥረት የለም። ታማኙ ሰው ኢዮብ እንደተናገረው “እነሆ፣ ፈጥኖ ቢነጥቅ የሚከለክለው ማን ነው? እርሱንስ ምን ታደርጋለህ የሚለው ማን ነው?” (ኢዮብ 9:12) በተመሳሳይም የባቢሎኑ ንጉሥ ናቡከደነፆር “እጁንም የሚከለክላት ወይም ‘ምን ታደርጋለህ?’ የሚለው የለም” ለማለት ተገዷል።—ዳንኤል 4:35

4. ይሖዋ የራሱን ነፃነት የገደበው እንዴት ነው?

4 ይሁን እንጂ ይሖዋ ራሱ ያወጣቸው የጽድቅ ሥርዓቶች ይህ ፍጹም የሆነው ነፃነቱ ከገደብ ውጭ እንዳይሆን አድርገውታል። ይህም አብርሃም ስለ ሰዶም ነዋሪዎች በማሰብ “የምድር ሁሉ ፈራጅ በቅን ፍርድ አይፈርድምን?” በማለት ባቀረበው ጥያቄ ተገልጿል። አምላክ የሰጠው መልስ እርሱ ትክክል የሆነውን ነገር የማድረግ ኃላፊነት ያለበት መሆኑን እንደሚገነዘብ ያመለክታል። በሰዶም ውስጥ ጻድቃን ሰዎች ቢኖሩ ኖሮ ከተማዋን አያጠፋትም ነበር። (ዘፍጥረት 18:22-33) በተጨማሪም የአምላክ ፍቅርና ጥበብ ለቁጣ የዘገየና ራሱን የሚገዛ እንዲሆን ስለሚያደርገው የራሱን ነፃነት ራሱ ገድቦታል።—ኢሳይያስ 42:14

ለሰው የተሰጠው ነፃነት የተገደበ ነው

5. የሰውን ነፃነት ውስን የሚያደርጉ አንዳንድ ምክንያቶች ምንድን ናቸው?

5 ይሖዋ ገደብ የለሽና ፍጹም የሆነ ነፃነት ያለው ቢሆንም ሌሎቹ ፍጥረታት በሙሉ ግን የሚንቀሳቀሱትና የሚሠሩት ተፈጥሮአቸው፣ ችሎታቸው፣ የመኖሪያ አካባቢያቸውና ፍጹም ባልሆኑ የሰው ልጆች ረገድ ደግሞ በጣም ውስን የሆነው የሕይወት ዘመናቸው በሚፈቅድላቸው ክልል ውስጥ ብቻ ነው። አምላክ ሰውን ሲፈጥረው ይሖዋ በወሰነለት ክልል ውስጥ እንዲንቀሳቀስ የሚያስችለውን ፍጹም ነፃነት ሰጥቶት ነበር። የሰው ነፃነት ፍጹምና ገደብ የሌለው እንዳይሆን የሚያደርጉት አያሌ ምክንያቶች አሉ።

6. በአምላክ ተጠያቂዎች መሆናችን የትኞቹ የአምላክ ሕጎች ነፃነታችንን ይገድቡብናል?

6 በመጀመሪያ ደረጃ የሰው ነፃነት የተገደበ የሆነው የሰው ልጅ የተፈጠረው የአምላክን ዓላማ እንዲፈጽም በመሆኑ ነው። ይሖዋ ‘ሁሉን ፈጥሮአልና ስለፈቃዱም ሆነዋልና ተፈጥረውማልና ክብር፣ ውዳሴ፣ ኃይልም ሊቀበል ይገባዋል።’ (ራዕይ 4:11) ስለዚህ ሰው በሠሪውና ሰዎች የሚመሩባቸውን ሕጎች ለማውጣት መብት ባለው ፈጣሪው ዘንድ ተጠያቂ ነው። በሙሴ ሕግ ሥር በነበሩት የጥንት እሥራኤላውያን መሃል የአምላክን ስም የሚሰድብ ወይም የሰንበትን ሕግ የሚጥስ ሰው በሞት እንዲቀጣ አምላክ ደንግጎ ነበር። (ዘጸአት 20:7፤ 31:14, 15፤ ዘሌዋውያን 24:13-16፤ ዘኁልቁ 15:32-36) እኛም ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን በሕጉ ሥር ባንሆንም ፈራጃችን፣ ሕግ ሰጪያችንና ንጉሣችን በሆነው በይሖዋ ተጠያቂዎች ስለሆንን ነፃነታችን የተገደበ ነው።—ኢሳይያስ 33:22፤ ሮሜ 14:12

7, 8. (ሀ) የተፈጥሮ ሕጎች የሰውን ነፃነት የሚገድቡት እንዴት ነው? (ለ) ሰዎች በመሆናችን ነፃነታችንን የሚገድቡት ሌሎች የአምላክ ሕጎች ምን ምን ናቸው?

7 ሁለተኛ፣ የሰው ልጅ ነፃነት በአምላክ የተፈጥሮ ሕጎች የተገደበ ነው። ለምሳሌ ያህል በስበት ሕግ ምክንያት አንድ ሰው ከሰማይ ጠቀስ ሕንፃ ላይ ዘልሎ ምንም ጉዳት አያገኘኝም ወይም አልሞትም ሊል አይችልም። የአምላክ የተፈጥሮ ሕጎች ሰው አንዳንድ ነገሮችን የማድረግ ነፃነቱን እንደሚገድቡበት አያጠራጥርም።

8 ሦስተኛ፣ የሰው ልጅ ነፃነት በአምላክ የሥነ ምግባር ሕጎች ምክንያት የተገደበ ነው። ጳውሎስ በገላትያ 6:7, 8 ላይ “አትሳቱ እግዚአብሔር አይዘበትበትም፤ ሰው የሚዘራውን ሁሉ ያንኑ ደግሞ ያጭዳልና። በገዛ ሥጋው የሚዘራ ከሥጋ መበስበስን ያጭዳልና፣ በመንፈስ ግን የሚዘራ ከመንፈስ የዘላለምን ሕይወት ያጭዳል” በማለት የተናገረው ቃል እውነት መሆኑን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ሳታዩ አትቀሩም። ይሖዋ አምላክ ያወጣቸው የሥነ ምግባር ሕግጋትም ነፃነታችንን እንደሚገድቡ ሊታበል አይችልም። ቢሆንም ሕይወት ለማግኘት ከፈለግን እነዚህን ሕጎች መታዘዝ ይፈለግብናል።

9. የሰብአዊው ማኅበረሰብ አባሎች መሆናችን ነፃነታችንን የሚገድበው እንዴት ነው?

9 አራተኛ፣ የሰው ልጅ በምድር ላይ የሚኖረው ብቻውን ስላልሆነና የሰው ልጅ ማኅበረሰብ ክፍል ስለሆነ ነፃነቱ የተገደበ ነው። ነፃነት ሊኖረው የሚችለው የሌሎችን ነፃነት እስካልተጋፋ ድረስ ብቻ ነው። መንግሥታዊ “የበላይ ባለሥልጣኖች” የአምላክን ሕግ እንድንጥስ እስካልጠየቁን ድረስ ልንታዘዛቸውና ልንገዛላቸው ይገባል። (ሮሜ 13:1፤ ሥራ 5:29) ለምሳሌ ያህል ግብር መክፈልንና የመኪና አነዳድ ፍጥነትን የሚመለከቱ ሕጎችንና የመሳሰሉትን መታዘዝ ይኖርብናል። እንደነዚህ ለመሳሰሉት “የቄሣር” ሕጎች የመታዘዝ ግዴት ያለብን መሆኑ አምላክ የሰጠን ነፃነት ፍጹምና ገደብ የለሽ አለመሆኑን ያሳያል።—ማርቆስ 12:17፤ ሮሜ 13:7

ነፃነታችን አንፃራዊ የሆነው ለምንድነው?

10, 11. ይሖዋ ለሰዎች አንፃራዊ ወይም የተገደበ ነፃነት የሰጠበት ምክንያት ምንድን ነው?

10 አምላክ ለሰዎች የተወሰነና አንፃራዊ ነፃነት የሰጠው ለምንድን ነው? አንዱ ምክንያት ፈጣሪ በሚናገሯቸው መልካም ቃላትና በጠባያቸው ክብርና ውዳሴ የሚያመጡ አስተዋይ ፍጡሮች በምድር ላይ እንዲኖሩት ስለፈለገ ነው። ይህን ማድረግ የሚችሉት ሰዎች ብቻ ናቸው። እንስሳት ግን አይችሉም። እንስሳት የሚመሩት በደመነፍስ ወይም በተፈጥሮ ባሕርያቸው በመሆኑ ስለ ጥሩ ስነ ምግባር የሚያውቁት ነገር የለም። አንድን ውሻ አንድ ነገር እንዳይወስድ ማሠልጠን ይቻላል። ሥርቆት መጥፎ የሆነበትን ምክንያት ግን ማስተማር አይቻልም። ሰው ፈጣሪውን በፍቅርና በአድናቆት ተነሣሥቶ ለማገልገል ነፃ ምርጫ ሊያደርግ ሲችል ማንኛውም እንስሳ የሚያደርገው ነገር ሁሉ በተፈጥሮ ባሕርዩ ውስጥ የተቀረጸ ስለሆነ ለአምላክ ውዳሴና ክብር የሚያመጣ ውሳኔ ሊያደርግ አይችልም።

11 በተጨማሪም አምላክ ይህን የመሰለ መጠነኛ ነፃነት ለሰው ልጅ የሰጠው ለሰው ጥቅምና ደስታ ስለሚያስብ ነው። ሰዎች መጠነኛ ነፃነታቸውን አዳዲስ ነገሮችን ለመፍጠርና ለመፈልሰፍ እንዲሁም ለጋስና ተባባሪ ለመሆን ሊጠቀሙበት ይችላሉ። ሰዎች የሚሠሩትን ሥራ፣ የሚኖሩበትን ቦታና የመሳሰሉትን ነገሮች የመምረጥ ነፃነት አላቸው። በዛሬው ጊዜ በኢኮኖሚያዊና በፖለቲካዊ ሁኔታዎች ምክንያት የሰው ልጅ በዚህ ረገድ ያለው የመምረጥ ነፃነት በጣም ውስን ሆኗል። ይሁን እንጂ ይህ የሆነው በሰው ልጅ ስግብግብነት ምክንያት ነው እንጂ በአምላክ የመጀመሪያ አፈጣጠር ምክንያት አይደለም።

12. አብዛኞቹ የሰው ልጆች በባርነት ስር የወደቁት ለምንድን ነው?

12 ይሖዋ ለሰዎች ትልቅ ነፃነት ቢሰጥም በዛሬው ጊዜ አብዛኛው የሰው ልጅ በአስጨናቂ ቀንበር ውስጥ ይኖራል። ይህ የሆነው ለምንድን ነው? የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት አዳምና ሔዋን አምላክ የሰጣቸውን ነፃነት ዓላማ ስለሳቱ ነው። አምላክ የወሰነላቸውን የነፃነት ገደብ ጥሰው በመሄድ የሠራዊት ጌታ ይሖዋ በእነሱ ላይ ያለውን የመግዛት መብት ተገዳደሩ። (ዘፍጥረት 3:1-7፤ ኤርምያስ 10:10፤ 50:31) ነፃነታቸውን ለአምላክ ክብር በሚያመጣ መንገድ እየተጠቀሙ ረክተው ከመኖር ይልቅ ትክክልና ስሕተት ስለሆኑት ነገሮች በራሳቸው ሥልጣን ለመወሰን በመምረጥ ነፃነታቸውን ለስስት ዓላማ ተጠቀሙበት። ይህንን በማድረጋቸው በይሖዋ ላይ ካመጸው ከሰይጣን ዲያብሎስ ጋር ተባበሩ። ይሁን እንጂ ኃጢአተኞቹ አዳምና ሔዋን የበለጠ ነፃነት በማግኘት ፈንታ በራሳቸው ላይ ተጨማሪ ገደብና ባርነት በመጨረሻም ሞትን አመጡ። ዘሮቻቸውም ይህንኑ የነፃነት እጦት ወረሱ። “ሁሉም ኃጢአትን ሠርተዋልና፤ የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሏቸዋል።” “የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነው።”—ሮሜ 3:23፤ 5:12፤ 6:23

13. ሰይጣን ሰዎችን ባሪያ ሊያደርግ የቻለው ለምን ነበር?

13 በተጨማሪም በኤደን በተነሣው አመጽ ምክንያት አዳምና ዝርያዎቹ የሰይጣን ዲያብሎስ ባሪያዎች ሆኑ። እንዲያውም ‘መላው ዓለም በክፉው ኃይል ተይዟል’! (1 ዮሐንስ 5:19) ሰይጣን ከሰው የበለጠ ኃይልና ችሎታ ስላለው ከአምላክ የራቀውን የሰው ልጅ በሙሉ አታልሎ ባሪያው ለማድረግ ችሎአል። ከዚህም በላይ ራስ ወዳድ የሆኑ ሰዎች በስስት ተነሣስተው ሰዎችን በመግዛት ብዙ ጉዳት አድርሰውባቸዋል። (መክብብ 8:9) ስለዚህ ዛሬ የሰው ልጅ ባጠቃላይ የኃጢአትና የሞት፣ የሰይጣንና የአጋንንቱ፣ እንዲሁም የዓለም ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች ባሪያ ነው።

እውነተኛ ነፃነት ሊገኝ ችሏል

14. የሰው ልጅ እውነተኛ ነፃነት ለማግኘት ያለው ተስፋ ከምን ጋር የተሳሰረ ነው?

14 ከኃጢአትና ከሞት እንዲሁም ከሰይጣንና ከሰይጣን ዓለም ነፃነት ማግኘት በአምላክ ሉዓላዊነት ትክክለኛነት ላይ የተነሳው ግድድር እልባት ከማግኘቱ ጋር የተሳሰረ ነው። ይህን ግድድር ያስነሳው ሰይጣን በመሆኑ ፈርኦን ለተወሰነ ጊዜ እንዲኖር ይሖዋ እንደፈቀደ ሁሉ ሰይጣንም ለተወሰነ ጊዜ እንዲኖር ፈቅዶለታል። ይህም የሆነው ይሖዋ ኃይሉን እንዲገልጥና ስሙም በምድር ሁሉ እንዲነገር ለማድረግ ነው። (ዘጸአት 9:15, 16) ይሖዋ በቅርቡ የአጽናፈ ዓለሙ ልዑል ገዥ መሆኑን ያረጋግጣል። በሰይጣን፣ በአዳምና በሔዋን ዓመጽ ምክንያት የመጣውን ስድብ በማስወገድ ስሙን ይቀድሳል። ስለዚህ ይሖዋን የሚፈሩ ሁሉ ከኃጢአትና ከሞት ባርነት ነፃ ወጥተው ከአምላክ የተሰጠ ነፃነት ወደሚሰፍንባት አዲስ ዓለም ይገባሉ።—ሮሜ 8:19-23

15. ኢየሱስ የሰውን ዘር ወደ ነፃነት ለመመለስ ምን ድርሻ አበርክቷል?

15 አምላክ የሰውን ልጅ ወደ ነፃነት ለመመለስ ሲል ልጁ ሰው ሆኖ ወደ ምድር እንዲመጣ አድርጓል። የአምላክ ልጅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስም ፍጹም ሰብአዊ ሕይወቱን በፈቃደኝነት አሳልፎ በመስጠት ለሰው ልጅ ነፃ መውጣት ምክንያት የሆነውን የቤዛ መሥዋዕት አቅርቧል። (ማቴዎስ 20:28) በተጨማሪም የነፃነት መልእክት አውጆአል። በአገልግሎቱ መጀመሪያ ላይ የሚከተሉት የኢሳይያስ ቃላት በራሱ ላይ እንደሚፈጸሙ አመልክቷል፦ “የጌታ [የይሖዋ (አዓት)] መንፈስ በእኔ ላይ ነው፣ ለድሆች የምሥራችን እሰብክ ዘንድ [ይሖዋ (አዓት)] ቀብቶኛልና፤ ልባቸው የተሰበረውን እጠግን ዘንድ፣ ለተማረኩትም ነፃነትን፣ ለታሰሩትም መፈታትን እናገር ዘንድ ልኮኛል።”—ኢሳይያስ 61:1፤ ሉቃስ 4:16-21

16. የመጀመሪያው መቶ ዘመን አይሁድ እውነተኛ ነፃነት ለማግኘት ምን እርምጃ መውሰድ ነበረባቸው?

16 ታዲያ ሰዎች ይህን ነፃነት የሚያገኙት እንዴት ነው? ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “እናንተ በቃሌ ብትኖሩ በእውነት ደቀመዛሙርቴ ናችሁ፤ እውነትንም ታውቃላችሁ፣ እውነትም አርነት ያወጣችኋል” አላቸው። ስለዚህ የኢየሱስ ተከታዮች መንፈሳዊ ነፃነት አግኝተዋል ማለት ነው። (ዮሐንስ 8:31, 32, 36) በተጨማሪም ኢየሱስ ለሮማዊው ገዢ ለጴንጤናዊው ጲላጦስ “እኔ ለእውነት ልመሰክር ስለዚህ ተወልጃለሁ ስለዚህም ወደ ዓለም መጥቻለሁ፤ ከእውነት የሆነ ሁሉ ድምፄን ይሰማል” ብሏል። (ዮሐንስ 18:37) ኢየሱስ ክርስቶስ የሰበከውንና በተግባር ያሳየውን እውነት የተቀበሉ አይሁዶች ከኃጢአታቸው ንስሐ ገብተውና ከስህተት አካሄዳቸው ተመልሰው የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ ሕይወታቸውን ለይሖዋ በመወሰን እንደ ኢየሱስ በውሃ ተጠምቀዋል። (ማቴዎስ 3:13-17፤ ሥራ 3:19) ይህን በማድረጋቸውም ከአምላክ የሚሰጠውን ገደብ ያለው ወይም አንፃራዊ ነፃነት አግኝተዋል።

17. ይሖዋ ለአገልጋዮቹ ነፃነት የሚሰጠው ለምንድን ነው?

17 ይሖዋ ለታማኝ አገልጋዮቹ ነፃነት የሰጠው በመሠረቱ የራሱን ልዕልና ለማረጋገጥ ቢሆንም ደስታና ጥቅም እንዲያገኙ ሲልም ይህን ነፃነት ሰጥቷቸዋል። እሥራኤላውያንን ከግብፅ ባርነት ነፃ ያወጣቸው የንጉሥ ካህናትና ምሥክሮቹ በመሆን እንዲያከብሩት ብሎ ነበር። (ዘጸአት 19:5, 6፤ ኢሳይያስ 43:10-12) በተመሳሳይም ይሖዋ ሕዝቡን ከባቢሎን ምርኮ ነፃ ያወጣበት ዋና ዓላማ የራሱን ቤተ መቅደስ መልሰው እንዲሠሩና እውነተኛ አምልኮቱን መልሰው እንዲያቋቁሙ ነበር። (ዕዝራ 1:2-4) ምርኮኞቹ ስለ ሥጋዊ ምቾታቸው ብቻ ማሰብ በጀመሩ ጊዜ ይሖዋ ነቢያቱን ሐጌንና ዘካርያስን ልኮ ሕዝቡ በአምላክ ፊት ስላለባቸው ግዴታ እንዲያስገነዝቧቸው አደረገ። አምላክ የሰጣቸውን ነፃነት በትክክለኛ አመለካከት ማየት በመጀመራቸው ቤተ መቅደሱን ሠርተው ጨረሱ። ይህም ለአምላክ ክብር ለራሳቸው ደግሞ ምቾትና ደኅንነት አምጥቶላቸዋል።

ከአምላክ የሚሰጠውን ነፃነት ዓላማ አለመሳት

18. የይሖዋ ዘመናዊ አገልጋዮች አምላክ የሰጣቸውን ነፃነት ዓላማ አልሳቱም ሊባል የሚችለው ለምንድን ነው?

18 ስለ አምላክ ዘመናዊ አገልጋዮችስ ምን ሊባል ይቻላል? በድርጅት ደረጃ አምላክ የሰጣቸውን ነፃነት ዓላማ አልሳቱም። በ1870ዎቹ ዓመታት ከባቢሎናዊ ስህተቶች ነፃ መውጣትና እየጨመረ የሚሄድ ክርስቲያናዊ ነፃነት ማግኘት ጀመሩ። ይህም በምሳሌ 4:18 ላይ “የጻድቃን መንገድ እንደ ንጋት ብርሃን ነው፣ ሙሉ ቀን እስኪሆንም ድረስ እየተጨመረ ይበራል” ከሚለው ቃል ጋር የሚስማማ ነበር። ሆኖም የአምላክ ጥንታዊ ሕዝቦች ለጊዜው ወደ ባቢሎናዊ ምርኮ ተወስደው እንደነበረ ሁሉ የይሖዋ አገልጋዮችም በ1918 በታላቂቱ ባቢሎን እስራት ስር ወድቀው ነበር። (ራዕይ 17:1, 2, 5) ምሳሌያዊዎቹ “ሁለት ምሥክሮች” በመንፈሳዊ ሁኔታ በድን ሆነው አስከሬናቸው በአደባባይ ላይ በወደቀ ጊዜ የዚህች የዓለም የሐሰት ሃይማኖት ግዛት አባሎች ተደስተው ነበር። ይሁንና የአምላክ ቅቡዓን አገልጋዮች በ1919 ይገባናል በማንለው የአምላክ ቸርነት መንፈሳዊ ነፃነት አግኝተው እንደገና ሕያው ሆኑ። (ራዕይ 11:3, 7-11) አምላክ የሰጣቸውን ነፃነት ሥራ ላይ በማዋል የልዑሉ አምላክ ቀናተኛ ምሥክሮች ሆኑ። ስለዚህ በ1931 የይሖዋ ምሥክሮች የሚለውን መጠሪያ መቀበላቸው ምንኛ የተገባ ነበር! (ኢሳይያስ 43:10-12) በተለይ ከ1935 ጀምሮ በምድር ላይ ዘላለማዊ ሕይወት ለማግኘት ተስፋ የሚያደርጉ “እጅግ ብዙ ሰዎች” ከእነዚህ ቅቡዓን ምሥክሮች ጋር ተባብረዋል። እነዚህ እጅግ ብዙ ሰዎችም ቢሆኑ ከአምላክ የተሰጣቸውን ነፃነት ዓላማ አልሳቱም።—ራዕይ 7:9-17

19, 20. (ሀ) የይሖዋ ሕዝቦች አምላክ የሰጣቸውን ነፃነት የተጠቀሙበት አንደኛው ታላቅ መንገድ ምንድን ነው? (ለ) የይሖዋ ምሥክሮች አምላክ የሰጣቸውን ነፃነት በጥሩ ሁኔታ የተጠቀሙበት ሌላው ትልቅ መንገድ ምንድን ነው?

19 የይሖዋ ሕዝቦች ከአምላክ የተሰጣቸውን ነፃነት በሁለት ታላላቅ መንገዶች ተጠቅመውበታል። በመጀመሪያ ደረጃ ነፃነታቸውን ትክክለኛ የሆነ አካሄድ ለመከተል ይጠቀሙበታል። (1 ጴጥሮስ 2:16) በዚህም ጥሩ ስምና ዝና አትርፈዋል። ለምሳሌ ያህል አንድ ጊዜ አንድ ሰው በስዊዘርላንድ አገር በዙሪክ ከተማ ወደሚገኝ አንድ የመንግሥት አዳራሽ ሄደና የይሖዋ ምሥክር ለመሆን እፈልጋለሁ አለ። ለምን እንደፈለገ ሲጠየቅ እህቱ የይሖዋ ምሥክር እንደነበረችና በመጥፎ ሥነምግባር መመላለስ ስለጀመረች እንደተወገደች ተናገረ። ቀጥሎም ‘መጥፎ ሥነምግባር የማይፈቅድ የዚህ ድርጅት አባል መሆን እፈልጋለሁ’ አለ። ዘ ካቶሊክ ኢንሳይክሎፒድያ የይሖዋ ምሥክሮች “በዓለም ውስጥ ካሉት በጣም ጥሩ ጠባይ ያላቸው ሕዝቦች አንዱ እንደሆኑ በሚገባ ታውቋል” ያለው አለምክንያት አልነበረም።

20 የይሖዋ ምሥክሮች ከአምላክ የተሰጣቸውን ነፃነት ኢየሱስ እንዳደረገው የመንግሥቱን ምሥራች የመስበክ ተልእኮአቸውን በመፈጸምም ይጠቀሙበታል። (ማቴዎስ 4:17) በአንደበትም ሆነ በታተሙ ጽሑፎች አማካኝነት መደበኛም ሆነ መደበኛ ባልሆኑ ዘዴዎች የይሖዋን መንግሥት እያወጁ ነው። እንዲህ ማድረጋቸውም እምነታቸውን ስለሚያጠነክርላቸውና ተስፋቸውን ብሩሕ ስለሚያደርግላቸው ለራሳቸው ከፍተኛ ጥቅም አስገኝቶላቸዋል። ከዚህም በላይ ይህ ሥራ ለራሳቸውም ሆነ ለሚሰሟቸው ሰዎች ደኅንነት ያስገኛል። (1 ጢሞቴዎስ 4:16) ዳይናሚክ ሪሊጂየስ ሙቭመንትስ የተሰኘ መጽሐፍ ስለዚህ ሥራ ሲያትት “የይሖዋ ምሥክሮችን ያህል ለሃይማኖታቸው ተግተው የሚሠሩ አባሎች ያሉት ሃይማኖታዊ ድርጅት ማግኘት ያስቸግራል” ብሏል።

21. ይሖዋ የሕዝቡን አገልግሎት እየባረከ ለመሆኑ ምን ማስረጃ አለ?

21 ከአምላክ የተቀበልነውን ነፃነት ዓላማ ለማከናወን በምናደርገው ጥረት ይሖዋ አብዝቶ እየባረከን ነው። ይህንንም ካለፈው ዓመት የመስክ አገልግሎት ሪፖርት መረዳት ይቻላል። የአስፋፊዎች ከፍተኛ ቁጥር ከአራት ሚሊዮን በላይ ሲሆን በመታሰቢያው በዓል ላይ ከአሥር ሚሊዮን በላይ ሰዎች ተገኝተዋል። አየርላንድ በሃያ ዘጠኝ ተከታታይ ወራት ውስጥ 29 ከፍተኛ የአስፋፊዎች ቁጥር፣ ሜክሲኮ በ80 ወራት ውስጥ 78 ከፍተኛ የአስፋፊዎች ቁጥር፣ ጃፓን ደግሞ በተከታታይ 153 ከፍተኛ የአስፋፊዎች ቁጥር አግኝተዋል።

ከአምላክ የተቀበላችሁትን ነፃነት በሚገባ ተጠቀሙበት

22. ራሳችንን የትኞቹን አሳሳቢ ጥያቄዎች መጠየቅ ይገባናል?

22 አንተም ከይሖዋ ውስን ምሥክሮች አንዱ ከሆንክ አምላክ የሰጠህን ነፃነት በሚገባ እየተጠቀምክበት ነውን? እያንዳንዳችን ራሳችንን እንዲህ እያልን ብንጠይቅ ጥሩ ነው፦ “አምላክ በሰጠኝ ነፃነት የምጠቀመው ማንንም ሰው በመጥፎ አድራጎት እንዳላደናቅፍ እየተጠነቀቅኩ ነውን? የአምላክን ሕግ የማስቀድም ብሆንም የቄሣርን ሕጎች በጥንቃቄ አከብራለሁን? ከጉባኤ ሽማግሌዎች ጋር ሙሉ በሙሉ እተባበራለሁን? አምላክ የሰጠኝን ነፃነት በስብከቱ ሥራ ሙሉ በሙሉ እየተጠቀምኩበት ነውን? ሁልጊዜ “የጌታ ሥራ የሚበዛልኝ ነኝን? አምላክ የሰጠኝን ነፃነት አገልግሎቴን ለማስፋት በጉባኤ ውስጥ የበለጠ ሐላፊነት ለመቀበል ወይም ወደ ሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመድረስ ልጠቀምበት ስችል በዓለማዊ ሥራ ዕድገት ለማግኘት እየተጠቀምኩበት ነውን?”—1 ቆሮንቶስ 15:58

23. አምላክ የሰጠንን ነፃነት ዓላማ እንዳንስት ምን ማድረግ ይኖርብናል?

23 ሁላችንም ‘ይሖዋ ቸር እንደሆነ እንቅመስና እንይ።’ (መዝሙር 34:8) በእርሱ እንታመን፣ ከሕጎቹ ጋር እንስማማ፣ መንግሥቱን በቅንዓት በማስታወቅም ቅዱስ ስሙን እናክብር። “በበረከት የሚዘሩ በበረከት ደግሞ እንደሚያጭዱ” አስታውሱ። (2 ቆሮንቶስ 9:6) ስለዚህ ለይሖዋ የሙሉ ልብ አገልግሎት በማቅረብ አምላክ የሰጠንን ነፃነት ዓላማ እንዳልሳትን እናሳይ።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

◻ አምላክ ያለው ነፃነት ምን ዓይነት ነው?

◻ የሰው ነፃነት ምን ዓይነት ገደቦች አሉት?

◻ እውነተኛ ነፃነት ማግኘት የተቻለው እንዴት ነው?

◻ አምላክ የሰጠንን ነፃነት ዓላማ እንዳንስት ምን ማድረግ አለብን?

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሰብአዊ ነፃነት የስበትን ሕግ በመሳሰሉት ነገሮች የተገደበ ነው

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ