የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w92 4/1 ገጽ 6-8
  • ሰው ሠራሽ “አዲስ ዓለም” ቀርቧልን?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ሰው ሠራሽ “አዲስ ዓለም” ቀርቧልን?
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1992
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የኃጢአትና የሞት ባሪያ መሆን
  • በነፃ ምርጫ ያለአግባብ መጠቀም
  • ‘ሰው አካሄዱን ሊያቀና አይችልም’
  • ከሁሉ የተሻለውን የሚያውቀው ማን ነው?
  • ነፃ፣ ግን ተጠያቂነት ያለበት ሕዝብ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1992
  • ከአምላክ የሚሰጠውን ነፃነት ዓላማ አትሳቱ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1992
  • እውነተኛ ነፃነት የሚያስገኘው መንገድ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2018
  • ይሖዋን የሚያመልኩ ሁሉ ያገኙት ነፃነት
    እውነተኛውን አንድ አምላክ አምልክ
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1992
w92 4/1 ገጽ 6-8

ሰው ሠራሽ “አዲስ ዓለም” ቀርቧልን?

1. በቅርብ ዓመት ሕዝቦች ለበለጠ ፖለቲካዊ ነፃነት ያላቸው ምኞት የተገለጸው እንዴት ነው?

በአሁኑ ጊዜ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የሐሰት ሃይማኖት ባሪያዎች ሆነዋል። አብዛኞቹም ከዚህ ባርነት ለመውጣት አይፈልጉም። ይሁን እንጂ የፖለቲካ ነጻነት ለማግኘት የሚጠይቁ ሰዎች ቁጥር በጣም እየበዛ ሄዷል። ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ በምሥራቅ አውሮፓና በሌሎች አገሮች በተፈጸሙት አስደናቂ ሁኔታዎች እንደታየው ሰዎች የበለጠ ነፃነት የሚሰጡ የመስተዳድር ዓይነቶችን ይፈልጋሉ። በዚህም ምክንያት ብዙ ሰዎች አዲስ የነፃነት ዘመን ቀርቧል እያሉ ነው። ይህን ለውጥ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንት “አዲስ የዓለም ሥርዓት” ሲሉ ጠርተውታል። በእርግጥም በየትኛውም አገር ያሉ የዓለም መሪዎች ቀዝቃዛው ጦርነትና የጦር መሳሪያ እሽቅድምድም እንዳበቃና ለሰው ልጅ አዲስ የሰላም ዘመን እንደባተለት እየተናገሩ ነው።—ከ1 ተሰሎንቄ 5:3 ጋር አወዳድር

2, 3. እውነተኛ ነፃነት እንዳይኖር እንቅፋት የሚሆኑት ምን ሁኔታዎች ናቸው?

2 ሆኖም የሰው ልጆች ጥረት የጦር መሣሪያዎችን ብዛት ሊቀንስና የበለጠ ነጻነት የሚሰጡት አገዛዞችን ሊያስገኝ ቢችልም እንኳን እውነተኛ ነፃነት ሊገኝ ይችላልን? በፍጹም አይችልም። ምክንያቱም ዲሞክራቲክ ናቸው የሚባሉትን አገሮች ጨምሮ በሁሉም አገሮች የድሆች ቁጥር እየጨመረ ሄዷል። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ደግሞ ኤኮኖሚያዊ ፍላጎታቸውን ለማሟላትና ኑሮአቸውን ለማሸነፍ ይፍጨረጨራሉ። በሳይንስና በሕክምና ብዙ መሻሻል ቢደረግም በየቀኑ በዓለም ዙሪያ በተመጣጠነ ምግብ ጉድለት ወይም ሊወገዱ በሚችሉ በሽታዎች ሳቢያ በአማካይ 40,000 ሕፃናት እንደሚሞቱ አንድ የተባበሩት መንግሥት ድርጅት አረጋግጦአል። በዚህ መስክ ብዙ ጥናት ያደረጉ አንድ ሰው “ድህነት የሰውን ዘር የወደፊት ሕልውና አደጋ ላይ የሚጥል ቋሚ መልክ እየያዘ ነው” ብለዋል።

3 በተጨማሪም ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ብዙ ሰዎች ይበልጥ እየጨመረና እየከፋ በሄደው ወንጀል ተጠቅተዋል። የዘር፣ የፖለቲካና የሃይማኖት ጥላቻ የተለያዩ አገሮችን እየከፋፈለ ነው። በአንዳንድ አካባቢዎች የሚታየው ሁኔታ በዘካርያስ 14:13 ላይ ከተገለጸው ወደፊት የሚመጣ ሁኔታ እምብዛም የራቀ አይደለም። ይህ ጥቅስ በቱዴይስ ኢንግሊሽ ቨርሽን መሠረት “ሰዎች በጣም ግራ ከመጋባታቸውና ከመፍራታቸው የተነሳ እያንዳንዱ ሰው አጠገቡ ባለው ሰው ላይ ጥቃት ይፈጽማል” ይላል። አደንዛዥ ዕጾችን አለአግባብ መጠቀምና የአባለዘር በሽታዎች በዓለም በሙሉ የተስፋፉ ወረርሽኞች ሆነዋል። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በኤድስ ተለክፈዋል፤ በዩናይትድ ስቴትስ ብቻ ከ120,000 በላይ ሰዎች ሞተዋል።

የኃጢአትና የሞት ባሪያ መሆን

4, 5. በዛሬው ጊዜ ምንም ያህል ነፃነት ቢኖር ሰዎችን ሁሉ አንቆ የያዘው ምን ዓይነት ባርነት ነው?

4 ይሁን እንጂ እነዚህ ሁሉ መጥፎ ሁኔታዎች ባይኖሩ እንኳን ሰዎች እውነተኛ ነፃነት ሊኖራቸው አይችልም። ሰዎች ሁሉ ከባርነት ሊወጡ አይችሉም። እንዲህ የሆነው ለምንድን ነው? ነገሩን በምሳሌ እንመልከት። አንድ አምባገነን ገዥ ተነስቶ በምድር ላይ የሚኖሩትን ሰዎች በሙሉ ባሪያ አድርጎ ቢገዛና ሁሉንም አንድ በአንድ ገድሎ ቢጨርስስ? የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን በአምላክ ላይ ካመጹና በዲያብሎስ ጨቋኝ አገዛዝ ሥር በባርነት መኖር ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ መላው የሰው ልጅ የሚኖርበት ሁኔታ ከዚህ የተለየ አይደለም።—2 ቆሮንቶስ 4:4

5 በዘፍጥረት ምዕራፍ 1 እና 2 እንደተገለጸው አምላክ የሰው ልጆችን በፈጠረ ጊዜ ዓላማው ፍጹም ሆነው በገነት ውስጥ ለዘላለም እንዲኖሩ ነበር። ይሁን እንጂ ቅድመ-አያታችን የሆነው አዳም በአምላክ ላይ በማመጹ ምክንያት ሁላችንም ገና ከመፀነሳችን ጀምሮ ሞት የተፈረደብን ሆነናል። “ኃጢአት በአንድ ሰው [የሰው ዘር ቤተሰብ ራስ በሆነው በአዳም] ወደ ዓለም ገባ፣ በኃጢአትም ሞት። እንደዚሁም ሁሉ ኃጢአትን ስላደረጉ ሞት ለሰው ሁሉ ደረሰ።” መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለውም “ሞት ነገሰ”። (ሮሜ 5:12, 14) ስለዚህ በግላችን ምንም ያህል ነጻነት ቢኖረን ሁላችንም የኃጢአትና የሞት ባሪያዎች ነን።

6. መዝሙር 90:10 ከተጻፈ ወዲህ በዕድሜ እርዝማኔ ላይ ምንም ያህል መሻሻል ያልታየው ለምንድን ነው?

6 በተጨማሪም አሁን ያለን ሕይወት በጣም አጭር ነው። የታደሉት እንኳን የሚኖሩት ለጥቂት አሥርተ ዓመታት ብቻ ነው፤ ያልታደሉት ደግሞ በጥቂት ጊዜ ይቀጫሉ። አንድ አዲስ ጥናት “ሳይንስና የህክምና ጥበብ የሰውን ልጅ ዕድሜ እስከ መጨረሻው የተፈጥሮ ጣሪያ አድርሰውታል” ብሏል። ይህም የሆነው በአዳም ኃጢአት ምክንያት አለፍጽምናና ሞት በዘር ባገኘነው የተፈጥሮ ባሕሪ ውስጥ ተቀርጾ የሚገኝ በመሆኑ ነው። ሰባና ሰማኒያ ዓመት ዕድሜ ላይ ደርሰን የተሻለ ዕውቀትና ጥበብ አግኝተን ይበልጥ በሕይወታችን ልንደሰት በምንችልበት ጊዜ አካላችን ተጎሳቁሎ ወደ አፈር መመለሳችን ምንኛ የሚያሳዝን ነገር ነው!—መዝሙር 90:10

7. የምንፈልገውንና በግድ የሚያስፈልገንን እውነተኛ ነፃነት ሰዎች ሊያስገኙልን የማይችሉት ለምንድን ነው?

7 ታዲያ ከዚህ ሁኔታ ነፃ ሊያወጣን የሚችለው የትኛው ዓይነት የሰው አገዛዝ ነው? የትኛውም ዓይነት የሰው አገዛዝ አይችልም። ከበሽታ፣ ከእርጅናና ከሞት እርግማን ነፃ ሊያወጣን የሚችል የመንግሥት ባለ ሥልጣን ወይም የሳይንስ ሊቅ ወይም ሐኪም የለም። ማንኛውም ዓይነት ሰብአዊ አገዛዝ አለመረጋጋትን፣ የፍትሕ መጓደልን፣ ወንጀልን፣ ረሐብንና ድህነትን ሊያጠፋ አይችልም። (መዝሙር 89:48) ሰዎች የቱንም ያህል ጥሩ ዓላማ ይዘው ቢነሱ፣ የምንናፍቀውንና የግዴታ የሚያስፈልገንን እውነተኛ ነጻነት ሊያስገኙልን አይችሉም።—መዝሙር 146:3

በነፃ ምርጫ ያለአግባብ መጠቀም

8, 9. የሰውን ዘር አሁን ባለበት አሳዛኝ ሁኔታ ላይ የጣለው ምንድነው?

8 የሰው ልጅ እንዲህ ባለው አሳዛኝ ሁኔታ ውስጥ የወደቀው የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን በነጻ ምርጫ መብታቸው አለአግባብ ስለተጠቀሙ ነው። አንደኛ ጴጥሮስ 2:16 በዘ ጀሩሳሌም ባይብል መሠረት “እንደ ነፃ ሰዎች ኑሩ እንጂ ነፃነታችሁን የክፋት ሰበብ አድርጋችሁ አትጠቀሙበት” ይላል። ስለዚህ የሰው ልጅ ገደብ የሌለበት ነፃነት እንዲኖረው የአምላክ አላማ አልነበረም። ለሰው ልጅ የተሰጠው ነፃነት ጻድቅ በሆኑና ለሰው ልጆች ሁሉ ዘላቂ ጥቅም ሊያስገኙ በሚችሉ የአምላክ ሕግጋት አጥርና ገደብ ውስጥ ሊሠራበት ይገባ ነበር። ይህም አጥር ወይም ገደብ ሠፊ የሆነ የግል ምርጫና ነጻነት የሚሰጥ ስለሆነ የአምላክ አገዛዝ ጭቆና ያለበት አይሆንም ነበር።—ዘዳግም 32:4

9 ይሁን እንጂ የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን ትክክለኛና ስህተት የሆኑትን ነገሮች ራሳቸው ለመወሰን መረጡ። ሆን ብለው ከአምላክ አገዛዝ ስለወጡ ጥበብ የተሞላበትን እርዳታውንና ድጋፉን ነፈጋቸው። (ዘፍጥረት 3:17-19) በዚህም ምክንያት ፍጽምናቸውን አጥተው በራሳቸው ላይ ሞትና ኃጢአት አስከተሉ። የሰው ልጆችም ነፃነት በማግኘት ፈንታ በኃጢአትና በሞት ባርነት ሥር ወደቁ፣ በተጨማሪም ፍጹም ላልሆኑትና አብዛኛውን ጊዜ ጨካኝ ለሆኑ ገዢዎች ፈቃድ የሚገዙ ሆኑ።—ዘዳግም 32:5

10. ይሖዋ ነገሮችን በፍቅራዊ መንገድ የያዛቸው እንዴት ነው?

10 አምላክ የሰው ልጆች ሙሉ ነፃነት አግኝተው እንዲሞክሩ የፈቀደው ለተወሰነ ጊዜ ብቻ ነው። ከአምላክ የሆነ የሰው አገዛዝ የማይሳካ መሆኑን ውጤቶቹ ያለምንም ጥርጥር ቁልጭ አድርገው እንደሚያሳዩ አምላክ አውቆ ነበር። ነፃ ምርጫ በትክክል ከተሰራበት በጣም ውድ ሀብት ስለሆነ አምላክ የሰውን የነፃ ምርጫ ነፃነት በመንጠቅ ፈንታ በፍቅር ተገፋፍቶ ለተወሰነ ጊዜ የደረሰው ነገር ሁሉ እንዲደርስ ፈቅዷል።

‘ሰው አካሄዱን ሊያቀና አይችልም’

11. ታሪክ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነተኛነት የደገፈው እንዴት ነው?

11 “የሰው መንገድ ከራሱ እንዳይደለ አውቃለሁ፣ አካሄዱንም ለማቅናት ከሚራመድ ሰው አይደለም። አቤቱ [ይሖዋ አርመኝ (አዓት)]” የሚለው በኤርምያስ ምዕራፍ 10 ቁጥር 23 እና 24 ላይ የተመዘገበው ቃል እውነት መሆኑን የታሪክ መዝገብ አረጋግጧል። በተጨማሪም “ሰው ሰውን የገዛው ለጉዳቱ ነው” የሚለው የመክብብ 8:9 ቃል ትክክል መሆኑን ታሪክ አረጋግጧል። ይህ ቃል ምንኛ እውነት ነው! የሰው ልጅ ቤተሰብ የተለያዩ መከራዎች ሲፈራረቁበት ከኖረ በኋላ በመጨረሻ ግብዓተ መሬቱ ይፈጸማል። ሐዋርያው ጳውሎስ በሮሜ 8:22 ላይ “ፍጥረት ሁሉ እስከ አሁን አብሮ በመቃተትና በምጥ መኖሩን እናውቃለን” በማለት የሰው ፍጥረት የሚገኝበትን ሁኔታ በትክክል ገልጾአል። አዎ፣ የሰው ልጅ ከአምላክ ሕግጋት ነፃ ለመሆን ያደረገው ሙከራ ከፍተኛ ውድቀት አድርሶበታል።

12. ሙሉ በሙሉ ነፃ ስለመሆን አንዳንድ የታሪክ ምንጮች ምን ይላሉ?

12 ኢንኩዚሽን ኤንድ ሊበርቲ የተሰኘ መጽሐፍ ደራሲ በራስ ሐሳብ ስለ መመራትና ስለ ነፃነት የሚከተለውን አስተያየት ሰጥተዋል፦ “በራስ ሐሳብ ለመመራት መቻል ራሱ ብቻውን የግድ ተፈላጊ ነገር ነው ሊባል አይቻልም። ተጨማሪ ማስተካከያና ገደብ ካልተደረገበት የሚኮራበት ነገር አይደለም። እንዲያውም የራስ ወዳድነት ባሕርይ አንዱ ገጽታ ሊሆን ይችላል። . . . ሰው ሙሉ በሙሉ ራሴን ችዬ በራሴ የምመራ ፍጡር ልሁን ብሎ ቢያስብ ትልቅ ጅልነት ነው። ሊሆንም አይችልም።” አንድ ጊዜ የእንግሊዙ መስፍን ልዑል ፊሊፕ እንዲህ ብለዋል፦ “የተፈለገውን ነገር ሁሉ ለማድረግ ነፃ መሆን ጥሩ ነገር መስሎ ሊታይ ይችላል። ይሁን እንጅ የኑሮ ገጠመኝ ደጋግሞ የሚያስተምረው ራስን መግዛት የሌለበት ነፃነት . . . ለሌሎች አሳቢነት የሌለው ባሕርይ ምንም ያህል ውድ ሀብት ይምሰል እንጂ የማህበረሰብን የኑሮ ጣዕም እንደሚያበላሽ እርግጠኛ ነገር መሆኑን ነው።”

ከሁሉ የተሻለውን የሚያውቀው ማን ነው?

13, 14. ለሰብዓዊው ቤተሰብ እውነተኛ ነፃነት ሊያስገኝ የሚችለው ማን ብቻ ነው?

13 አንድ ቤት እንዴት መደራጀት እንዳለበት የሚያውቁት ተሞክሮና በቂ ችሎታ ያላቸው አፍቃሪ ወላጆች ናቸው ወይስ ወጣት ልጆች? መልሱ ግልጽ ነው። በተመሳሳይም ለሰው ልጆች የሚበጃቸውን የሚያውቀው የሰው ልጆች ፈጣሪ የሆነው ሰማያዊ አባታችን ነው። የሰው ልጆች ማህበረሰብ እንዴት መደራጀትና መተዳደር እንደሚገባው ያውቃል። ነፃ ምርጫ የማድረግ መብት ለሰው ሁሉ እውነተኛ ነፃነት እንዲያስገኝ ከተፈለገ በምን ዓይነት ሁኔታ መገደብና መመራት እንደሚኖርበት እርሱ ያውቃል። የሰውን ልጅ ከወደቀበት ባርነት እንዴት እንደሚያወጣውና ለሰው ሁሉ እውነተኛ ነፃነት እንዴት እንደሚያስገኝ የሚያውቀው የጽንፈ-ዓለሙ ሁሉን ቻይ አምላክ ይሖዋ ብቻ ነው።—ኢሳይያስ 48:17-19

14 ይሖዋ በቃሉ ውስጥ በሮሜ 8:21 ላይ መንፈሳችንን የሚያነሳሳ ተስፋ ሰጥቶአል፦ “ፍጥረት ራሱ ደግሞ ከጥፋት ባርነት ነፃነት ወጥቶ ለእግዚአብሔር ልጆች ወደሚሆን ክቡር ነፃነት እንዲደርስ ነው።” አዎ፣ አምላክ የሰውን ዘር አሁን ከወደቀበት አሳዛኝ ሁኔታ ሙሉ በሙሉ ነፃ ለማውጣት ቃል ገብቶአናል። የሚቀጥለው ርዕሰ ትምህርት አምላክ ይህን የሚፈጽመው እንዴት እንደሆነ ይገልጻል።

ምን ብለህ ትመልሳለህ

(ከገጽ 3 እስከ 8 የተገለጸውን የሚከልሱ ጥያቄዎች)

◻ ሰዎች ለነፃነት ጠንካራ ስሜት ያላቸው ለምንድነው?

◻ ሰዎች በታሪክ ዘመናት ሁሉ ባሪያዎች ሆነው የተገዙት በምን መንገዶች ነው?

◻ ይሖዋ በነፃ ምርጫ ያለአግባብ መጠቀምን ይህን ለሚያክል ረዥም ጊዜ የፈቀደው ለምንድን ነው?

◻ ለሰው ልጆች እውነተኛ ነፃነት ማምጣት የሚችለው ማን ብቻ ነው? ለምንስ?

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የሰው ዕድሜ ከ3,500 ዓመት በፊት በመዝሙር 90:10 ላይ ከተገለጸው ሁኔታ ጋር በጣም ይመሳሰላል

[ምንጭ]

Courtesy of The British Museum

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ