እውነተኛ ነፃነት—ከየት ይገኛል?
“አቤቱ የሰው መንገድ ከራሱ እንዳይደለ አውቃለሁ፤ አካሄዱን ለማቅናት ከሚራመድ ሰው አይደለም። አቤቱ [ይሖዋ አርመኝ (አዓት)]።”—ኤርምያስ 10:23, 24
1, 2. አብዛኞቹ ሰዎች ስለ ነፃነት ያላቸው አመለካከት እንዴት ያለ ነው? ይሁን እንጂ ሊታሰብበት የሚያስፈልገው ሌላው ነገር ምንድን ነው?
እውነተኛውን ነፃነት እንደምታደንቁ አያጠራጥርም። የራሳችሁን አስተያየት የመግለጽ፣ የምትኖሩበትን ቦታና ሁኔታ የመምረጥ ነፃነት እንዲኖራችሁ ትፈልጋላችሁ። የምትሠሩትን የሥራ ዓይነት፣ የምትበሉትን የምግብ አይነት፣ የምትሰሙትን ሙዚቃና የምትፈልጉአቸውን ጓደኞች ራሳችሁ ለመምረጥ ትፈልጋላችሁ። ትላልቅም ሆኑ ጥቃቅን ስለብዙ ጉዳዮች የየራሳችሁ ምርጫ አላችሁ። የተስተካከለ አዕምሮ ያለው ማንም ሰው ምንም አይነት ነፃ ምርጫ ሳይኖረው ለአምባገነን ገዥዎች ባሪያ መሆን አይፈልግም።
2 ይሁን እንጂ ራሳችሁም ሆናችሁ ሌሎች ሰዎች በእውነተኛ ነፃነት ተጠቃሚዎች ለመሆን በምትችሉበት ዓለም ለመኖር አትፈልጉምን? ሁሉም ሰው የሕይወቱ ሙሉ ተጠቃሚ እንዲሆን ነፃነት በሚከበርበት ዓለም ውስጥ ለመኖር አትፈልጉምን? የሚቻል ከሆነ ከፍርሃት፣ ከወንጀል፣ ከድህነት፣ ከአካባቢ መቆሸሽ፣ ከበሽታና ከጦርነት ነፃ በሆነ ዓለም ውስጥ ለመኖር አትፈልጉምን? በእርግጥ እንደነዚህ ዓይነቶቹ ነፃነቶች በጣም የሚፈለጉ ናቸው።
3. ለነፃነት ከፍ ያለ ግምት የምንሰጠው ለምንድን ነው?
3 እኛ የሰው ልጆች ለነፃነት ይህን ያህል ከፍተኛ ግምት የምንሰጠው ለምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ “[የይሖዋ] መንፈስ ባለበት ነፃነት አለ” ይላል። (2 ቆሮንቶስ 3:17) ስለዚህ ይሖዋ የነፃነት አምላክ ነው። እኛንም “በመልኩና በምሳሌው” ስለፈጠረን እውነተኛ ነፃነትን እንድናደንቅና ከእርሱም ተጠቃሚዎች እንድንሆን የሚያስችለንን ነፃ ምርጫ ሰጥቶናል።—ዘፍጥረት 1:26
ነፃነት አግባብ ባልሆነ መንገድ ተሰርቶበታል
4, 5. በታሪክ ዘመናት በሙሉ ነፃነት ያለአግባብ የተሠራበት እንዴት ነው?
4 በታሪክ ዘመናት በሙሉ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በነፃ ምርጫ ነፃነታቸው አላግባብ በተጠቀሙ ሰዎች ምክንያት በባርነት ቀንበር ሥር ወድቀዋል፣ ተደብድበዋል፣ ተገድለዋል። መጽሐፍ ቅዱስ ከ3,500 ዓመታት በፊት “ግብፃውያን የእሥራኤልን ልጆች በመከራ ገዙአቸው። በጽኑ ሥራ . . . በመከራም በሚያሠሩአቸው ሥራ ሁሉ ሕይወታቸውን ያስመርሯቸው ነበር” ይላል። (ዘጸአት 1:13, 14) ዘ ኢንሳይክሎፒድያ አሜሪካና በአራተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ በአቴናና በሌሎች ሁለት የግሪክ ከተሞች የባሮቹ ቁጥር ነፃ ከሆኑት ሰዎች በአራት እጥፍ በልጦ እንደነበር ይናገራል። ይኸው ኢንሳይክሎፒድያ “በመጀመሪያ ላይ የሮማ ባሮች ምንም ዓይነት መብት አልነበራቸውም። በጣም ቀላል ለሆነ ጥፋት እስከሞት በሚያደርስ ቅጣት ይቀጡ ነበር” ብሏል። ኮምተንስ ኢንሳይክሎፒዲያ “የሮማ መንግሥት የተመሠረተው በባሮች ጉልበት ላይ ነበር። . . . ባሮች በእርሻ ቦታዎች ላይ በሰንሰለት ታሥረው ይሠሩ ነበር። ማታ ማታ ደግሞ በአንድ ላይ ይታሠሩና ግማሽ ቁመቱ መሬት ውስጥ በተቀበረ ትልቅ እሥር ቤት ውስጥ ይታጎሩ ነበር” ያላል። ብዙዎቹ ባሮች ነፃ የነበሩበት ጊዜ እንደነበር ስንገነዘብ እነዚህ ሰዎች እንዴት ያለ መራራ ሕይወት አሳልፈው እንደነበር ለመገመት እንችላለን።
5 የሕዝበ ክርስትና አገሮች ለብዙ መቶ ዘመናት የባሪያ ንግድ ሲያካሂዱ ቆይተዋል። ዘ ወርልድ ኢንሳይክሎፒድያ “ከ1,500 እስከ 1,800 በነበሩት ዓመታት አውሮፓውያን አሥር ሚልዮን የሚያክሉ ጥቁር ባሪያዎችን ከአፍሪካ ወደ ምዕራባዊው ንፍቀ ክበብ አጓጉዘዋል” ይላል። በዚህ በሃያኛው መቶ ዘመንም ቢሆን በሚልዮን የሚቆጠሩ ምርኮኞች በናዚ የማጎሪያ ካምፖች ውስጥ ታሥረው በሥራ ብዛት ሞተዋል ወይም የመንግሥት ፖሊሲ ለማስፈጸም ሲባል ብቻ ተገድለዋል። ከእነዚህ ሰዎች መካከል ነፍሰ ገዳይ የነበረውን የናዚ መንግሥት ለመደገፍ እምቢተኞች በመሆናቸው ብቻ ወደ ማጎሪያ ካምፖች የተጣሉ የይሖዋ ምሥክሮች ይገኛሉ።
የሐሰት ሃይማኖት ባሪያ መሆን
6. በጥንቷ ከነዓን የሐሰት ሃይማኖት ሰዎችን ባሪያ ያደረገው እንዴት ነው?
6 የሐሰት ሃይማኖት ደጋፊ ከመሆን የሚመጣ ባርነትም አለ። ለምሳሌ ያህል በጥንትዋ ከነዓን ሞሎክ ለተባለ ጣዖት ሕፃናት መሥዋዕት ይደረጉ ነበር። ከዚህ የሐሰት አምላክ ግዙፍ ምስል ውስጥ የእሳት እቶን ይንቀለቀል እንደነበር ይነገራል። ገና በሕይወት ያሉ ሕፃናት እጁን ዘርግቶ በተቀመጠው የሞሎክ ምስል ላይ ይቀመጡና ከሥሩ ወዳለው የእሳት ነበልባል ይጣሉ ነበር። አንዳንድ እስራኤላውያን እንኳን ሳይቀሩ ይህን የሐሰት አምልኮ ፈጽመው ነበር። አምላክ ‘እሱ ያላዘዘውንና በልቡም ያላሰበውን ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን ለሞሎክ በእሳት የማቃጠል ድርጊት ፈጸሙ።’ (ኤርምያስ 32:35) ሞሎክ ለአምላኪዎቹ ምን ጥቅም አምጥቶላቸዋል? እነዚያ ከነዓናውያንና የሞሎክ አምልኮ ዛሬ የት አሉ? ሁሉም ጠፍተዋል። ያ አምልኮ በእውነት ላይ ሳይሆን በሐሰት ላይ የተመሠረተ የሐሰት አምልኮ ነበር።—ኢሳይያስ 60:12
7. የአዝቴክ ሃይማኖት ክፍል የነበረ ምን አስከፊ ልማድ ነበር?
7 ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት በማዕከላዊ አሜሪካ ይኖሩ የነበሩት የአዝቴክ ጎሣዎች በሐሰት አምልኮ የባርነት ቀንበር ውስጥ ይኖሩ ነበር። ሰዎች የግል አማልክት ነበሩአቸው። የተፈጥሮ ኃይሎችም አንደ አማልክት ተደርገው ይመለኩ ነበር። የየዕለቱ ተግባራት የየራሳቸው አማልክት ነበሩዋቸው። ተክሎችም የየራሳቸው አማልክት ነበሯቸው። ራስን መግደል እንኳን የራሱ አምላክ ነበረው። የጥንቶቹ አሜሪካኖች የፀሐይ መንግሥታት የተሰኘው መጽሐፍ የሚከተለውን ተርኳል፦ “የሜክሲኮው የአዝቴክ መንግሥት ከላይ እስከታች ድረስ የማይታዩትን የተፈጥሮ ኃይሎች በተቻለ መጠን በጣም ብዙ የሰው ልብ በመስጠት ለማስደሰትና ጠብቆ ለማቆየት ይደረግ በነበረው ጥረት መሠረት የተደራጀ ነበር። የአማልክቱ መጠጥ ደም ነበር። ለአማልክቱ መሥዋዕት የሚሆኑትን እሥረኞች ለማግኘት ሁልጊዜ ያለማቋረጥ ጦርነቶች ይደረጉ ነበር።” ታላቅ የፒራሚድ ቤተመቅደስ በ1486 በተመረቀ ጊዜ በሺህ የሚቆጠሩ እሥረኞች “በመደዳ ተሰልፈው በየተራ በመሥዋዕቱ ድንጋይ ላይ ታርደዋል። ልባቸው ተቆርጦ ከወጣ በኋላ የፀሐይን አምላክ ለመለመን ለአጭር ጊዜ በእጅ ወደላይ ይዘው ለፀሐይ ያሳዩ ነበር።” ዘ ወርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፒዲያ ደግሞ “አንዳንድ ጊዜ አምላኪዎቹ የታረደውን ሰው ሥጋ ይበሉ ነበር” ይላል። ሆኖም ይህ ጎሣ ለዚህ ደም የተጠማ ሃይማኖት ባሪያ መሆኑ የአዝቴክን ግዛት ከመውደቅ አላዳነውም።
8. አንድ አስጎብኚ በአዝቴክ ሕዝቦች መሃል ከደረሰው እልቂት ስለሚበልጥ ዘመናዊ እልቂት ምን አለ?
8 በአንድ ወቅት ጎብኚዎች በአንድ ሙዚየም ውስጥ የአዝቴክ ቀሳውስት የአንድ ወጣት ሰው ልብ አርደው ሲያወጡ የሚያሳይ ሥዕል ተመልክተው ነበር። አስጎብኚው ስለ ሥዕሉ በሚገልጽበት ጊዜ ከጎብኚዎቹ መሃል አንዳንዶቹ በመሰቀቅ ጮኹ። አስጎብኚውም “የአዝቴክ ጎሳዎች ለአረመኔ አማልክት ወጣት ሰዎችን ሲሠዉ የሚያሳየውን ሥዕል በማየታችሁ በጣም ተሰቅቃችኋል። ግን በዚህ በሃያኛው መቶ ዘመን በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የጦርነት አምላክ ለሆነው ለማርስ ተሰውተዋል። ታዲያ ከዚህኛው የሚሻልበት መንገድ አለ?” ብሏቸዋል። አብዛኛውን ጊዜ በጦር ሜዳ ላይ በተቃራኒ ወገኖች ተሰልፈው እርስ በርሳቸው የሚዋጉት ሰዎች አንድ ዓይነት ሃይማኖት ያላቸው ቢሆኑም በጦርነቱ ጊዜ በየአገሩ የሚኖሩ የሃይማኖት መሪዎች ሠራዊታቸው ድል እንዲያገኝ መጸለያቸውና ሠራዊታቸውን ባርከው መላካቸው የታወቀ ጉዳይ ነው።—1 ዮሐንስ 3:10-12፤ 4:8, 20, 21፤ 5:3
9. በሰው ታሪክ ከደረሱት እልቂቶች ይበልጥ የብዙ ትናንሽ ልጆችን ሕይወት እያጠፋ ያለው የትኛው ልማድ ነው?
9 በአሁኑ ጊዜ በየዓመቱ በመላው ዓለም ከ40 እስከ 50 ሚልዮን በሚያክሉ ገና ያልተወለዱ ሕፃናት ላይ በውርጃ አማካኝነት የሚፈጸመው ግድያ ለሞሎክ፣ ለአዝቴክ ወይም ለጦርነት ከተሠውት ወጣቶች ቁጥር እጅግ ይበልጣል። ባለፉት ሦስት ዓመታት ብቻ በውርጃ ምክንያት የሞቱት ሕፃናት ብዛት በዚህ በሃያኛው መቶ ዘመን በተደረጉት ጦርነቶች ምክንያት ከሞቱት ሰዎች ቁጥር ይበልጣል። በአሁኑ ጊዜ በ12ቱ የናዚ ግዛት ዓመታት ከሞቱት ሰዎች በብዙ እጥፍ የሚበልጡ ሕፃናት በውርጃ ምክንያት በየዓመቱ ይሞታሉ። በቅርብ አሥርተ ዓመታት ብቻ ለሞሎክ ወይም ለአዝቴክ ከተሠዉት ጠቅላላ ሰዎች ብዙ ሺህ ጊዜ የሚበልጡ ሕፃናት በውርጃ ምክንያት ተገድለዋል። ሆኖም ሁሉም ባይሆኑም አብዛኞቹ አስወራጆችም ሆኑ ውርጃውን የሚፈጽሙት ሰዎች ሃይማኖት እንዳላቸው ይናገራሉ።
10. ሰዎች ለሐሰት ሃይማኖት ባሪያ የሆኑበት ሌላው መንገድ ምንድነው?
10 የሐሰት ሃይማኖት ሰዎችን ባሪያ የሚያደርግባቸው ሌሎች መንገዶችም አሉ። ለምሳሌ ያህል ብዙ ሰዎች ሙታን በመንፈሳዊው ዓለም ውስጥ ሕያዋን ሆነው እንደሚኖሩ ያምናሉ። ይህ እምነት ካስከተላቸው ውጤቶች አንዱ አስቀድሞ ከሞቱ ወላጆችና አያቶች ጥቅም ለማግኘት ታስቦ የሚሰጣቸው ፍርሃትና አምልኮት ነው። ይህም ፍርሃት በሕይወት የሚኖሩት ሰዎች ሙታንን ለመለማመን ይረዳሉ ተብለው ለሚታመንባቸው ጠንቋዮች፣ መናፍስት ጠሪዎችና ቀሳውስት ባሪያዎች እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። ታዲያ ከዚህ ባርነት መውጫ መንገድ ይኖራልን? የሚል ጥያቄ ሊቀርብ ይችላል።—ዘዳግም 18:10-12፤ መክብብ 9:5, 10
[በገጽ 4, 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በታሪክ ዘመናት በሙሉ አንዳንድ ሰዎች ሌሎችን በባርነት ለመግዛት በነፃ ምርጫቸው አለአግባብ ተጠቅመዋል።