የኤልያስን የመሰለ እምነት አለህን?
በዛሬው ጊዜ ያለው ሰብአዊ ህብረተሰብ ቀስ በቀስ እምነት የሚያሳጣ ነው። ምሁራን አምላክ አለ በሚለው እምነት ላይ ያሾፋሉ። ሃይማኖታዊ ግብዞችም አምላክን መሳለቂያ አድርገውታል። ዓለማዊነት የተጠናወተው ይህ ዓለም አምላክ ኖረ አልኖረ ምንም ልዩነት እንደማያመጣ ያስባል። እነዚህ ሁኔታዎች አንድን ሰው በማስፈራራትም ሆነ ወይም ተስፋ በማስቆረጥ ወይም በግዴለሽነት ስሜት እንዲለከፍ በማድረግ እምነቱ እንዲሸረሸር ያደርጋሉ። ሐዋርያው ጳውሎስ እምነት ማጣትን “ቶሎ የሚከበን ኃጢአት” ብሎ መጥራቱ አያስደንቅም!—ዕብራውያን 12:1
ምናልባትም ጳውሎስ ትኩረታችንን ጠንካራ እምነት ባሳዩ ወንዶችና ሴቶች አኗኗር ላይ እንድናደርግ ያሳሰበው በዚህ ምክንያት ሊሆን ይችላል። (ዕብራውያን ምዕራፍ 11) እንደነዚህ ያሉት ምሳሌዎች መንፈሳችንን በማነሳሳት እምነታችንን ያጠነክሩታል። ለምሳሌ ያህል ነቢዩ ኤልያስን እንውሰድና ከረዥሙና በተሟላ ሁኔታ ከተፈጸመው የነቢይነት ሥራው ውስጥ በመጀመሪያው ክፍል ላይ ብቻ እናተኩር። ነቢዩ ኤልያስ የኖረው እንደዛሬው ጊዜ በእውነተኛው አምላክ ላይ ማመን ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ደርሶ በነበረበት ዘመን ይኖሩ በነበሩት በንጉሥ አክአብና በአረማዊት ሚስቱ በኤልዛቤል ዘመን ነበር።
ምግባረ ብልሹ የነበረው የአሥሩ ነገድ መንግሥት
አክአብና ሚስቱ አንድ አይነት ሰዎች ነበሩ። አክአብ ከአሥሩ ነገድ የእሥራኤል መንግሥት ነገሥታት ሰባተኛው ንጉሥ ነበር። ከእሱ አስቀድሞ የነበሩት ነገሥታት ክፉዎች ቢሆኑም እሱ ግን ከሁሉም የባሰ ክፉ ሰው ነበር። የአገሩን ምግባረ ብልሹ የጥጃ አምልኮ ጠብቆ ማቆየቱ ሳይበቃ የውጭ አገር ዜጋ የሆነችውን ልዕልት ኤልዛቤልን በማግባቱ በእሥራኤል ምድር ታይቶ በማይታወቅ በአል የተባለውን አምላክ አምልኮ አስፋፋ።—1 ነገሥት 16:30-33
ኤልዛቤል ከሕፃንነቷ ጀምሮ በበኣል አምልኮ የተዘፈቀች ሴት ነበረች። የበአል ሚስት ተብላ የምትታመነው አስታሮት የተባለች እንስት አምላክ ካህን የነበረው ኢት በአል የሚባለው አባቷ ከእሥራኤል በስተሰሜን የሚገኘውን የሲዶን መንግሥት ንግሥና የወሰደው ከእርሱ በፊት የነበረውን ንጉሥ በመግደል ነበር። ኤልዛቤል ደካማ ሥነምግባር በነበረው ባልዋ ላይ ተጽዕኖ በማሳደር በእስራኤል ምድር የበአል አምልኮ እንዲስፋፋ አደረገች። ብዙም ሳይቆይ በምድሪቱ የነበሩት የበኣል 450 ነቢያትና እንስት አምላክ የነበረችው የአሸራ 400 ነቢያት ከንጉሡ ማዕድ ይበላሉ ነበር። የእነዚህ የሐሰት አማልክት የአምልኮ ሥርዓት በእውነተኛው አምላክ በይሖዋ ዓይን በጣም አስፀያፊ ነበር! የወንድ ብልት ምስሎች፣ የመዋለድ ሃይማኖታዊ ሥነ-ሥርዓቶች፣ የቤተ-መቅደስ አመንዝሮች (ወንዶችም ሴቶችም)፣ አልፎ ተርፎም ሕፃናትን መሥዋዕት ማድረግና የመሳሰሉት የዚህ ውዳቂ መጥፎ ሃይማኖት ክፍሎች ነበሩ። ይህ ውዳቂና መጥፎ ሃይማኖት በአክዓብ ቡራኬና ድጋፍ በመንግሥቱ በሙሉ ያላንዳች እንቅፋት ተስፋፋ።
በሚልዮን የሚቆጠሩ እሥራኤላውያን ምድርንና የውሃ ዑደቷን የፈጠረውን ይሖዋን ረሱ። በእነሱ አስተሳሰብ በደረቁ ወቅት ፍጻሜ ላይ ምድሪቱን በዝናብ የሚባርካት በአል ነበር። በየዓመቱም ደረቁን ወራት አሳልፎ ዝናብ እንዲሰጣቸው የመዋለድና የዝናባማው ወቅት አምላክ ነው ተብሎ ይጠራ የነበረውን ‘የደመናት ነጂ’ በአልን በተስፋ ይጠባበቁ ነበረ። ዓመት አልፎ ዓመት ሲተካም ዝናብ ይመጣ ነበር። ለዚህም ምስጋና ይቀበል የነበረው በአል ነበር።
ኤልያስ ድርቅ አወጀ
ኤልያስ ብቅ ያለው ከረዥም ዝናብ አልባ የበጋ ወራት በኋላ ሕዝቡ በኣል ሕይወት አድን ዝናብ እንዲያመጣላቸው በተስፋ መጠባበቅ በጀመሩበት ጊዜ ሳይሆን አይቀርም።a ኤልያስ በመጽሐፍ ቅዱስ የታሪክ መዝገብ ውስጥ ብቅ ያለው እንደ መብረቅ ብልጭታ በድንገት ነው። ስለ አስተዳደጉም ሆነ ስለ ትውልዱ ምንም የተነገረን ነገር የለም። ኤልያስ ግን እንደ ነጎድጓድ ድምጽ ዝናብ መምጣቱን የሚያበስር ሰው አልነበረም። ለአክአብ “በፊቱ የቆምሁት የእሥራኤል አምላክ ሕያው [ይሖዋን (አዓት)]! ከአፌ ቃል በቀር [በቃሌ ትዕዛዝ ካልሆነ በቀር] በእነዚህ ዓመታት ጠልና ዝናብ አይሆንም” አለው።—1 ነገሥት 17:1
የባላገር ደበሎ የለበሰውን ይህን ሰው በዓይነ-ሕሊናችሁ ተመልከቱ። ኤልያስ ወጣ ገባ የሆነው የገለአድ ኮረብታማ አገር ተወላጅ ሲሆን ዝቅተኛ ኑሮ ይኖሩ በነበሩት የመንጋ እረኞች መሃል ያደገ ሰው ሳይሆን አይቀርም። በኃያሉ ንጉሥ በአክአብ ፊት የቆመው ምናልባት በዝሆን ጥርስ ባጌጠውና ዕፁብ ድንቅ ጌጣጌጦችና ግርማ ያላቸው ጣኦቶች ባሉበት በታላቁ ቤተመንግሥት ሊሆን ይችላል። የይሖዋ አምልኮ ፈጽሞ ወደተረሳባትና ግርግር ወደበዛባት ወደተመሸገችው የሰማሪያ ከተማ ሄዶ ለአክአብ ይህ በአል የሚባለው አምላኩ ምንም ማድረግ የማይችልና እዚህ ግባ የማይባል የማይረባ አምላክ መሆኑን ነገረው። በዚህም ሆነ በሚቀጥሉት ዓመታት ዝናብና ጠል እንደማይኖር ተናገረ!
ኤልያስ ይህን የመሰለ እምነት ያገኘው ከየት ነው? በዚህ ዕብሪተኛና ከሐዲ ንጉሥ ፊት ሲቆም ፍርሃት አልተሰማውም? ምናልባት ተሰምቶት ይሆናል። ከሺህ የሚበልጡ ዓመታት ካለፉ በኋላ የኢየሱስ ግማሽ ወንድም የነበረው ያዕቆብ ኤልያስ “እንደኛ የሆነ (የኛ ዓይነት ስሜት ያለው) ሰው ነበር” በማለት ያረጋግጥልናል። (ያዕቆብ 5:17) ይሁንና “በፊቱ የቆምሁት የእሥራኤል አምላክ ሕያው [ይሖዋን (አዓት)]” የሚሉትን የኤልያስ ቃላት አስተውሉ። ኤልያስ የይሖዋ አገልጋይ እንደመሆኑ መጠን ከንጉሥ አክአብ ዙፋን እጅግ በሚበልጠው በጽንፈ ዓለሙ ልዑል ዙፋን ፊት እንደቆመ አስታውሷል! የዚህ የይሖዋ ዙፋን ወኪልና መልእክተኛ ነበር። ይህን ሲያስብ አክዓብን የመሰለ የይሖዋን በረከት ያጣ አንድ ኢምንት ሰብአዊ ንጉሥ የሚፈራበት ምን ምክንያት ይኖረዋል?
ይሖዋ ለኤልያስ ይህን ያህል እውን ሆኖ ሊታየው የቻለው እንዲሁ በአጋጣሚ አልነበረም። ነቢዩ አምላክ ለሕዝቦቹ ስላደረጋቸው ነገሮች የሚገልጸውን የታሪክ መዝገብ አጥንቶ እንደነበረ ጥርጥር የለውም። አይሁዳውያን የሐሰት አማልክትን ወደማምለክ ዞር ካሉ በድርቅና በረሀብ እንደሚቀጣቸው ይሖዋ አስጠንቅቆአቸው ነበር። (ዘዳግም 11:16, 17) ኤልያስ ይሖዋ ምንጊዜም ቃሉን እንደሚፈጽም እርግጠኛ በመሆን “ዝናብ እንዳይዘንብ ጸለየ።”—ያዕቆብ 5:17
አመራር በመከተል የተገለጸ እምነት
ይሁን እንጂ ለጊዜው ኤልያስ በተናገረው የድርቅ መልእክት ምክንያት ሕይወቱ አደጋ ላይ ወድቆ ነበር። ሌላው የእምነቱ ገጽታ የሚታይበት ጊዜ መጥቶ ነበር። በሕይወት ለመቆየት “ከዚህ ተነሥተህ ወደ ምሥራቅ ሂድ፣ በዮርዳኖስም ትይዩ ባለው በኮራት ፈፋ ውስጥ ተሸሸግ፣ ከወንዙም ትጠጣለህ፣ ቁራዎችም በዚያ ይመግቡህ ዘንድ አዝዣለሁ” ብሎ የነገረውን የይሖዋን መመሪያ በመከተል ታማኝነቱን ማረጋገጥ ነበረበት።—1 ነገሥት 17:3, 4
ኤልያስ ወዲያውኑ የተሰጠውን ትዕዛዝ ፈጸመ። በምድሩ ላይ ከመጣው ድርቅና ረሀብ ለመትረፍ ከፈለገ ይሖዋ በሚያደርግለት በማንኛውም ዝግጅት ላይ መመካት ነበረበት። ይህ ፈጽሞ ቀላል አልነበረም። ለረዥም ወራት ከሰው ርቆና ተደብቆ መኖር ነበረበት። በሙሴ ሕግ እርኩስ እንደሆኑ በተነገረላቸውና ጥንብ በሊታ በሆኑት ቁራዎች የተወሰደለትን ሥጋና እንጀራ መብላትና ይህም ሥጋ የበከተ ጥንብ ሳይሆን በሕጉ መሠረት በተገቢው ሁኔታ ደሙ የፈሰሰ እንደሚሆን በይሖዋ መተማመን ነበረበት። ይህ ለረዥም ጊዜ የቀጠለ ተአምር ለአንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተቺዎች በጭራሽ መስሎ ሊታያቸው ባለመቻሉ “ቁራዎች” በሚለው ቃል ቦታ የገባው የመጀመሪያው የዕብራይስጥ ቃል “አረቦች” የሚል መሆን አለበት ብለው ሐሳብ ይሰጣሉ። ይሁንና ቁራዎች መመረጣቸው ተስማሚ ነው። አክአብና ኤልዛቤል በአካባቢው መንግሥታት ሁሉ ዘንድ ይፈልጉት የነበረውን ኤልያስን እነዚህ ቁራሽ ምግብ ይዘው ወደ ምድረበዳ የሚበሩት ንጹሐን ያልሆኑና ዝቅተኛ ግምት የሚሰጣቸው ወፎች ይመግቡት ይሆናል ብሎ ሊጠረጥር የሚችል ሰው አይኖርም።—1 ነገሥት 18:3, 4, 10
ድርቁ ውሎ ሲያድር ኤልያስ በኮራት ፈፋ የነበረው ውኃ እየቀነሰ መሄዱ ሊያሳስበው ጀምሮ ይሆናል። አብዛኞቹ የእሥራኤል ሸለቆ ፏፏቴዎች በድርቅ ጊዜ ስለሚደርቁ ይኸኛውም ፏፏቴ “ከብዙ ቀን በኋላ” ደረቀ። የወንዙ ውኃ ቀስበቀስ ጭልጭል ወደማለት እየቀነሰ ሲሄድና በጎድጓዳ ሥፍራ የነበሩት የተጠራቀሙት የውሃ ኩሬዎችም በየቀኑ እየጎደሉ ሲሄዱ ኤልያስ ምን እንደተሰማው ልትገምቱ ትችላላችሁን? ውኃው ጨርሶ ሲደርቅ ምን እንደሚደርስበት ሳያሳስበው እንዳልቀረ ጥርጥር የለውም። የሆነ ሆኖ ኤልያስ በታማኝነት ተቀመጠ። ወንዙ ከደረቀ በኋላ ይሖዋ የሚቀጥለውን መመሪያ ሰጠው። ነቢዩ ወደ ሰራፕታ እንዲሄድ ተነገረው። እዚያም በአንዲት መበለት ቤት ቀለብ እንደሚያገኝ ተነገረው።—1 ነገሥት 17:7-9
ሰራፕታ! ይህች ከተማ ኤልዛቤል ያደገችባትና የገዛ አባቷ ንጉሥ ሆኖ የገዛበት የሲዶን ግዛት ነበረች! ኤልያስ እዚያ መሄዱ ለሕይወቱ አያሰጋውምን? ኤልያስ ገርሞት ሊሆን ይችላል። ይሁንና “ተነሥቶ ሄደ።”—1 ነገሥት 17:10
ይሖዋ ቀለብና ሕይወት ይሰጣል
የኤልያስ ታዛዥነት ወዲያውኑ ዋጋ አገኘ። አስቀድሞ እንደተነገረው አንዲት መበለት አገኘ። ይህች መበለት በአገሩ ሰዎች መሃል እንኳን የማይገኝ ዓይነት እምነት እንዳላት ተገነዘበ። ይህች ድሃ መበለት የነበራት ለራሷና ለትንሽ ወንድ ልጅዋ አንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ጋግራ የሚበሉት ዱቄትና ዘይት ብቻ ነበር። ሆኖም በዚያ ከፍተኛ ችግር በነበረበት ጊዜም ቢሆን ኤልያስ ዝናብ እስኪዘንብ ድረስ የማድጋው ዱቄትና የማሰሮው ዘይት እንዳያልቅ ይሖዋ እንደሚጠብቅላት የነገራትን ተስፋ በመተማመን አስቀድማ ለኤልያስ እንጎቻ ለማዘጋጀት ፈቃደኛ ሆነች። ኢየሱስ ክርስቶስ በዘመኑ የነበሩትን እምነተ ቢስ አይሁዳውያን ሲያወግዝ የዚያችን መበለት የታማኝነት ምሳሌ ማስታወሱ አያስደንቅም!—1 ነገሥት 17:13-16፤ ሉቃስ 4:25, 26
ይህ ተአምር ቢደረግላቸውም የመበለቲቱና የኤልያስ እምነት ከባድ ፈተና ገጠመው። የመበለቲቱ ልጅ በድንገት ሞተ። መበለቲቱም በሐዘን ቅስሟ ስለተሰበረ ይህ አሳዛኝ ሁኔታ የደረሰባት “የእግዚአብሔር [የእውነተኛው አምላክ (አዓት)] ሰው” በሆነው በኤልያስ ምክንያት እንደሆነ ተሰማት። ምናልባት ላለፈ ኃጢአትዋ ቅጣት እየተቀበለች እንዳይሆን አሰበች። ይሁንና ኤልያስ የልጅዋን ሬሳ ወስዶ ወደ ሰገነቱ ላይ ወጣ። ይሖዋ ለመኖር ከሚያስችል ቀለብ የበለጠ ነገር መስጠት እንደሚችል ያውቅ ነበር። ይሖዋ የሕይወትም ምንጭ ነው! ስለዚህ ኤልያስ የልጁ ሕይወት እንዲመለስለት አምርሮ በመደጋገም ጸለየ።
ኤልያስ በትንሣኤ ለማመን የመጀመሪያ ሰው ባይሆንም የሞተ ሰው እንዳስነሳ በመጽሐፍ ቅዱስ የተመዘገበው የመጀመሪያ ሰው እርሱ ነው። ብላቴናው “ዳነ”! ኤልያስ ልጅዋን ወደ እርሷ አምጥቶ “እነሆ ልጅሽ በሕይወት ይኖራል” ብሎ ሲሰጣት የእናቱን ደስታ ማየት ለዓይን የሚደንቅ ትርኢት እንደነበር እርግጠኛ ነገር ነው። “የእግዚአብሔር (የእውነተኛው አምላክ) ሰው እንደሆንህ የይሖዋም ቃል በአፍህ እውነት እንደሆነ አሁን አወቅሁ” ያለችው ከደስታ እንባ ጋር እንደሚሆን አያጠራጥርም።—1 ነገሥት 17:17-24
“አምላኬ ይሖዋ ነው”
የኤልያስ ስም ትርጉሙ “አምላኬ ይሖዋ ነው!” ማለት መሆኑ ልብ የሚነካና ተገቢ ነው! በድርቅና በረሀብ ዘመን ይሖዋ ምግብና መጠጥ ሰጥቶታል፣ ሥነ-ምግባራዊ ውጥንቅጥ በተስፋፋበት ዘመን ይሖዋ አስተማማኝ መመሪያ ሰጥቶታል፣ ሰው በሞተበት ጊዜ ሕይወቱን እንዲመለስለት ይሖዋ ተጠቅሞበታል። ኤልያስ በአምላኩ ላይ የነበረውን እምነት በሥራ እንዲገልጽ በተጠየቀበት ጊዜ ሁሉ ማለትም ይሖዋ የሚያስፈልገውን ነገር ሁሉ እንደሚሰጠው እንደሚያምን፣ አመራሩን እንደሚከተል፣ ስሙን የሚቀድስ አምላክ መሆኑን እንደሚያምን በማረጋገጡ እምነቱን በይሖዋ ላይ እንዲያደርግ የሚያስችሉ ተጨማሪ ምክንያቶች በመስጠት ይሖዋ ባርኮታል። ከአምላኩ ከይሖዋ አስቸጋሪና እንዲያውም የሚያስፈሩ የሥራ ምድቦችን መቀበሉን በቀጠለ መጠን ይህንኑ እምነቱን የሚጨምርለትን የይሖዋ እርዳታ አለማቋረጥ አግኝቶአል። እንዲያውም ወደፊት የሚያደርጋቸው በጣም አስደናቂ የሆኑ ተአምራቶቹ ነበሩ።—1 ነገሥት ምዕራፍ 18ን ተመልከቱ
በዛሬው ጊዜ ያሉት የይሖዋ አገልጋዮችም የሚገኙበት ሁኔታ ለኤልያስ ከተደረገለት ጋር በጣም ተመሳሳይ ነው። በተአምራዊ ሁኔታ ምግብ አይቀርብልን ወይም የትንሣኤ ተአምር እንድንሠራ አምላክ አይጠቀምብን ይሆናል። ምክንያቱም ያለንበት ጊዜ እንዲህ ዓይነት ተአምራት የሚደረጉበት ዘመን አይደለም። ይሖዋ ግን በኤልያስ ዘመን ከነበረው ቅንጣት ያህል አልተለወጠም።—1 ቆሮንቶስ 13:8፤ ያዕቆብ 1:17
እኛም ከአምላክ የተሰጠንን መልእክት ይዘን ወደ አንዳንድ አስቸጋሪና አስፈሪ ቀበሌዎች የሚያስኬዱ ተስፋ የሚያስቆርጡና ተፈታታኝ የሆኑ የሥራ ምድቦችን እንቀበል ይሆናል። ስደትም ያጋጥመን ይሆናል። ልንራብም እንችላለን። ይሁንና ይሖዋ ለታማኝ ግለሰቦችና ለጠቅላላው ድርጅቱ አገልጋዮቹን እንደሚመራና እንደሚጠብቅ በተደጋጋሚ አረጋግጧል። አገልጋዮቹ እንዲሠሩ የመደበላቸውን ማንኛውም ዓይነት ሥራ ለመፈጸም እንዲችሉ ዛሬም ኃይል ይሰጣቸዋል። በዚህ በረብሻ የተሞላ ዓለም ውስጥ የሚመጣባቸውን ማንኛውም ዓይነት ችግር እንዲቋቋሙ አሁንም ይረዳቸዋል።—መዝሙር 55:22
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ኢየሱስና ያዕቆብ ሁለቱም በምድር ላይ ለ“ሦስት ዓመት ተኩል” ዝናብ እንዳልዘነበ ተናግረዋል። ሆኖም ኤልያስ ድርቁ ማክተሙን ለመንገር ወደ አክአብ ፊት የቀረበው “በሦስተኛው ዓመት” እንደሆነ የተነገረው ኤልያስ ድርቅ እንደሚሆን ካስታወቀበት ጊዜ ጀምሮ ሲቆጠር እንደሆነ አያጠራጥርም። በመሆኑም ኤልያስ መጀመሪያ በአክአብ ፊት የቀረበው ከረዥም ዝናብ አልባ ደረቅ ወቅት በኋላ መሆን አለበት።—ሉቃስ 4:25፤ ያዕቆብ 5:17፤ 1 ነገሥት 18:1
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አንተም እንደ ኤልያስ ይሖዋ ለአገልጋዮቹ የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ እንደሚያሟላላቸው ታምናለህን?