የይሖዋ መንገድ ከሁሉ የበለጠ የአኗኗር መንገድ ነው
በኤርኪ ካንካአንፓአ እንደተነገረው
ከሕፃንነቴ ጀምሮ ግቤ በፊንላንድ የይሖዋ ምስክሮች ቅርንጫፍ ወይም ቤቴል ማገልገል ነበር። ስለዚህ በ1941 የበጋ ወራት አንድ ተጓዥ የበላይ ተመልካች “ለወደፊት ምን ዕቅድ አለህ?” ብሎ ሲጠይቀኝ “ሁልጊዜ የምመኘው ቤቴል ለመግባት ነው” ብዬ መለስኩለት።
“ይህን ከንቱ ምኞት እንኳን ብትተወው ይሻልሃል። ፈጽሞ ተቀባይነት አታገኝም” አለኝ። በመጀመሪያ በጣም ቅር ተሰኘሁ፤ ይሁንና ጉዳዩን በይሖዋ እጅ ለመተው ወሰንኩ። ከጥቂት ወራት በኋላ በቤቴል እንዳገለግል ጥሪ ደረሰኝ።
ህዳር 1941 በአንድ ብርዳምና ብሩህ ቀን በሄልስንኪ ያለውን ቅርንጫፍ ቢሮ የበር ደወል ስደውል ዓይን አፋርነት የሚያጠቃኝ የ17 ዓመት ዕድሜ የባላገር ጉብል ነበርኩ። ወዲያውኑም የቅርንጫፍ ቢሮው የበላይ ተመልካች የነበረው ካርሎ ሀርቴቫ አቀባበል አደረገልኝ። በዚያ ጊዜ ቅርንጫፍ ቢሮው በፊንላንድ አገር ያሉ 1,135 ምሥክሮች ላይ ቁጥጥር ነበረው።
ክርስቲያናዊ ቅርስ
በ1914 አባቴ ዘ ዲቫይን ፕላን ኦፍ ዘ ኤጅዝ (መለኮታዊው የዘመናት ዕቅድ) የተሰኘ የመጠበቂያ ግንብ ጽሑፎች ቅጅ የሆኑ መጽሐፍ አግኝቶ ነበር። ይሁን እንጂ ወዲያውኑ አንደኛ የዓለም ጦርነት ስለፈነዳ ለማንበብ ፋታ አልነበረውም።
ፊንላንድ ብሔራዊ ነፃነት ለማግኘት ታደርግ የነበረው ትግል ችግሮችን ፈጥሮ ነበር። ሁለት ኃይለኛ ቡድኖች ማለትም ነጮችና ቀዮች የሚባሉ ቡድኖች ተመሥርተው ነበር። ነጮቹ ካፒታሊስቶችን (ከበርቴዎችን)ና መካከለኛ ገቢ ያላቸውን ሕዝብ ሲወክሉ ቀዮቹ ደግሞ ሠራተኞችን ወክለው ነበር። አባቴ ከሁለቱም ቡድኖች ጨርሶ በመራቅ ገለልተኛ ለመሆን ሞክሮ ነበር። ሆኖም ሁለቱም ቡድኖች በጥርጣሬ መዝገብ አስገቡት።
በኋላ ሊታወቅ እንደተቻለው አባቴ ሁለት ጊዜ የሞት ፍርድ ተበይኖበት ነበር። ሰው ተገድሎ ገዳዩ ተይዞ ሊጠየቅ በማይችልበት ወቅት አባቴን ጨምሮ አሥር ሰዎች ሞት ተፈርዶባቸው ነበር። የፍርድ ሸንጎው አባል የነበረ አንድ የአባቴ መምህር አባቴ ከፍርዱ ነፃ እንዲደረግ ሐሳብ አቅርቦ ሐሳቡም ተቀባይነት አገኘ። ሌሎቹ ዘጠኝ ወጣቶች ግን ተገደሉ።
በሌላ ወቅትም አባቴ ከሞት ፍርድ እንደገና ነጻ እንዲሆን ተፈቅዶለታል። ከዚያ በኋላ ቃል በቃል መሬት ውስጥ ገብቶ ለመደበቅ ወሰነ! እሱና ወንድሙ ዋሻ ቆፍረው ጦርነቱ እስኪያልቅ ኖሩበት። ሕይወታቸውን ለማቆየት ታናሽ ወንድማቸው ምግብና መጠጥ ያደርስላቸው ነበር።
በ1918 ጦርነቱ ካበቃ በኋላ አባቴ አግብቶ በዋሻው አጠገብ ቤት ሠራ። ዋሻው በኋላ ለኔ መጫወቻ ስለሆነልኝ በደንብ ላውቀው ችያለሁ። አባቴ እዚያ ከመሬት በታች ተደብቆ ሳለ ብዙ ይጸልይ እንደነበር አጫውቶኛል። አምላክን እንዴት እንደሚያገለግለው ካወቀ እንደሚያገለግለው ቃል ገብቶ ነበር።
አባቴ ወዲያው እንዳገባ ለንግድ ሥራ በሚጓዝበት ግዜ የሚያነበው ነገር ይዞ ለመሄድ ወሰነ። ከጣራው ሥር ባለ ቆጥ መሳይ ቦታ ከዓመታት በፊት የገዛውን ዘ ዲቫይን ፕላን ኦፍ ዘ ኤጅዝ መጽሐፍ አገኘው። “የይሖዋ ቀን” የሚለውን ምዕራፍ ከፍቶ ማንበብ ጀመረ። ሲያነብም ለራሱ “ይህ እውነት ነው፣ ይህ እውነት ነው” ይል ነበር። ከጣሪያው ሥር ካለው ቦታ ወርዶ ሲመጣም ለእናቴ “እውነተኛውን ሃይማኖት አገኘሁ” ብሎ ነገራት።
አባቴ ወዲያውኑ ስለተማራቸው ነገሮች ከወዳጆቹና ከጎረቤቶቹ በመጀመር ለሌሎች መስበክ ጀመረ። ከዚያም በኋላ የሕዝብ ንግግር መስጠት ጀመረ። ወዲያውኑም በአካባቢው የነበሩ ሌሎች ሰዎች ተባበሩት። ከዚያም አባቴ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በመባል ይጠሩ የነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች ጋር ሲገናኝ በ1923 ተጠመቀ። እኛ ልጆችም ስንወለድ አባባ እኛን ማስተማሩን ችላ አላለም። እንዲያውም ጉባኤ ከተቋቋመ በኋላ በእያንዳንዱ ስብሰባ እንድንገኝ ይጠበቅብን ነበር።
የልጅነት ትውስታዎች
በልጅነቴ የአምስት ዓመት ዕድሜ ሳለሁ በ1929 በአካባቢያችን ትልቅ ስብሰባ እንደተደረገ አስታውሳለሁ። ከአቅራቢያው ጉባኤዎች ብዙ ሰዎች ተሰብስበውና ከቅርንጫፍ ቢሮው የመጣ አንድ ተወካይም ተገኝቶ ነበር። በዚያ ዘመን በፊንላንድ በትልቅ ስብሰባዎች ላይ ልጆችን የመመረቅ ልማድ ነበር። ስለዚህ ኢየሱስ በምድራዊ አገልግሎቱ ጊዜ እንዳደረገው ከቤቴል የመጣው ወንድም ልጆችን ባረከ። ያንን ሁኔታ ፈጽሞ አልረሳውም።—ማርቆስ 10:16
ሌላው የልጅነት ትውስታዬ በ1931 የይሖዋ ምሥክሮች የሚለውን መጠሪያ ስንቀበል የሆነው ነበር። አባቴ የወቅቱን ጉዳይ ትርጉም አዘልነት በመገንዘብ ስለ አዲሱ ስማችን የሚገልጸውን ማስታወቂያ ክብደት በመስጠት ለጉባኤያችን አነበበ።
ማስታወስ ከምችልበት ጊዜ አንስቶ አባቴ ወደ ስብከቱ ሥራ አብሬው እሄድ ነበር። መጀመሪያ ላይ አባቴ ሲናገር አዳምጥ ነበር፤ በመጨረሻው ግን ስብከቱን ብቻዬን እሰራ ነበር። በ1935 አንድ ተጓዥ የበላይ ተመልካች ሲጎበኘን ወደ ጎረቤቶቻችን ሁሉ ዘንድ ሄጄ በስብሰባው እንዲገኙ ጋበዝኳቸው። ትናንሽ መጻሕፍት ተቀበሉኝ።
ትምህርት ቤትና ትልቅ ውሳኔ
በትምህርት ቤት የይሖዋ ምሥክር ወላጆች ያሉን እኛ አራታችን ብቻ ነበርንና ከሌሎች ወጣቶች ጋር ክርስቲያናዊ ባልሆኑ ጠባዮች ባለመተባበራችን ብዙውን ጊዜ ይሾፍብን ነበር። የትምህርት ቤት ጓደኞቼ ሲጋራ እንዳጨስ ቢያባብሉኝም ፈጽሞ አላደረግሁትም። በሹፈት ራስላውያን ወይም ሀርቴቫውያን በመባል እንጠራም ነበር። (ራስል የመጀመሪያው የመጠበቂያ ግንብ ማህበር ፕሬዚደንት ሲሆን ሀርቴቫ ደግሞ የፊንላንድ ቅርንጫፍ ቢሮ የበላይ ተመልካች ነበር።) ባንድ ወቅት ያሾፉብን የነበሩ አንዳንድ ወጣቶች የኋላ ኋላ ምሥክሮች እንደሆኑ ስነግራችሁ ደስ ይለኛል።
አስተማሪዬ ትምህርቴን እንድቀጥል ያበረታታኝ ነበርና አንድ ጊዜ መሐንዲስ ስለመሆን አስቤ ነበር። ከዚያ በኋላ ግን 1939 በፀደይ ወራት በፖሪ የተደረገው የይሖዋ ምሥክሮች ትልቅ ስብሰባ ሕይወቴን ለወጠው ታናሽ ወንድሜ ቱሞና እኔም ራሴ ሕይወታችንን ለይሖዋ ወሰንንና ውሳኔያችንንም በዚያ ስብሰባ ላይ ግንቦት 28/1939 በውሃ ጥምቀት አሳየን። ከዚያም መስከረም ላይ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ፈነዳ።
በአውሮፓ ሁኔታዎቹ በአስደናቂ ሁኔታ ተለወጡ። በፊንላንድና በሶቪየት ህብረት መሃል የነበረው ሁኔታ በጣም አስጊ ሆነ። አባቴ አርማጌዶን እንደቀረበ አጥብቆ በማመን አቅኚዎች እንድንሆን አበረታታን። ስለዚህ ታህሣሥ 1940 ወንድሜና እኔ በሰሜናዊ ፊንላንድ በአቅኚነት ማገልገል ጀመርን።
አቅኚነትና የቤቴል አገልግሎት
በአቅኚነት ስናገለግል አብዛኛውን ጊዜ የምንቀመጠው ከይርጆ ካሊዮ ጋር ነበር። ይርጆ ካሊዮ ከ30 ዓመታት በፊት በዩናይትድ እስቴትስ ፔንሲልቫኒያ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ የሆነ ወንድም ነበር። ይርጆ ከመጠን በላይ ሰው ወዳድ ስለነበር ለኛ ምቹ መስተንግዶ ለማቅረብ የተቻለውን ሁሉ ያደርግ ነበር። የሥጋ ወንድሙ የነበረው ኪዮስቲ ካሊዮ ከ1937 እስከ 1940 የፊንላንድ ፕሬዚደንት ሆኖ አገልግሎአል። ይርጆ ዘላቂና አለም አቀፍ ሰላም እንደምታመጣ ተስፋ ሊደረግባት የምትችል ብቸኛዋ ጥሩ መንግሥት የአምላክ መንግሥት እንደሆነች በማስረዳት ለወንድሙ በቂ ምሥክርነት እንደሰጠው ነግሮን ነበር።
ጊዜው እያለፈ ሲሄድ የቤቴል ቤተሰብ አባል ለመሆን የነበረኝ ምኞት እየጨመረ ሄደ። ደስ የሚለው ነገር ምንም እንኳን ተጓዥ የበላይ ተመልካቹ ምኞቴ ይፈጸምልኛል ብዬ እንዳላስብ ቢያስጠነቅቀኝም በቤቴል ለማገልገል ያቀረብኩት ማመልከቻ ተቀባይነት አገኘ። በቤቴል የተሰጠኝ የመጀመሪያ ሥራ ተላላኪነት ነበር። ይሁን እንጂ ወዲያውኑ በፋብሪካው የመሥራት መብት አገኘሁ። በፋብሪካውም የሕትመት ክፍሉንና የጭነት ክፍሉን ጨምሮ በብዙ ክፍሎች ሠርቻለሁ።
ገለልተኝነትን መጠበቅ
በ1942 በ18 ዓመት ዕድሜዬ ለወታደራዊ አገልግሎት ተጠራሁ። ምልመላውን ባለመቀበሌ ረዥም ጊዜ የወሰደ ተደጋጋሚ ምርመራ እንዲደረግብኝ ተደረገ፤ ከእነዚህ ምርመራዎችም መሃል ሁለቱን ጊዜ የተመረመርኩት የጠመንጃ አፈሙዝ ተደግኖብኝ ነበር። በሌሎች ጊዜዎች በምመረመርበት ጊዜ እስከ አጥንት ድረስ ጠስቆ የሚሰማ ቅዝቃዜ ባለበት የእሥር ቤት ክፍል ታሥሬያለሁ።
በመጨረሻም ጥር 1943 እኔና ሌሎችም ምሥክሮች ፍርድ የምንቀበልበት ጊዜ መጣ። የመረመረን የሠራዊት መኮንን የእሥራት አመታችን ከአሥር ዓመት እንዳያንስ ጠይቆ ነበር። የሠራዊቱ ቄስ ደግሞ ከዚህ የባሰ ፍርድ እንድንቀበል በመፈለግ “ለእነዚህ ከሐዲዎች የሚገባው ቅጣት የሞት ፍርድ ወይም ደግሞ በጃንጥላ የሚቃኙ ቡድኖች አድርጎ ወደ ሩሲያ መላክ ነው። [ይህም ሞታችንን አይቀሬ የሚያደርግ ነበር።]” ብሎ በደብዳቤ ጠይቆ ነበር።
የእምነታችንን ጽናት ለመፈተን የውሸት ፍርድ እንዲበየንብን ዝግጅት ተደርጎ ነበር። እኔ በፍርድ ቤቱ ፊት ቀርቤ የሞት ፍርድ ተቀበልኩ። ይሁን እንጂ ያንኑ ዕለት እንደገና ወደ ፍርድ ቤቱ ተጠርቼ ሦስት ዓመት ተኩል እንድታሠር ስለተፈረደብኝ የፊተኛው ፍርድ ለማስፈራራት ታስቦ የተደረገ ሌላ ሙከራ እንደነበረ አወቅን። እኔም ይግባኝ ጠይቄ ፍርዱ ወደ ሁለት ዓመት እሥራት ተቀነሰልኝ።
በእሥር ቤቱ የምግብ እጥረት ነበር፤ ከሌሎች እሥረኞችም ጥላቻ ያዘለ ማስፈራራት ወይም ዛቻ ይደርስብን ነበር። ሁለት ጊዜያት በግብረ-ሰዶማውያን ጥቃት ሊደርስብኝ ነበር። ደግነቱ ለማምለጥ ችያለሁ። አንደኛው ግብረ-ሰዶም ፈጻሚ የሚፈልገውን ነገር ካልፈጸምኩለት እንደሚገድለኝ ዝቶብኝ ነበር። ይሁንና ለምርመራ በቀረብኩበት ጊዜ ሁሉ እንዳደረግሁት ይሖዋን ጠርቼ እሱም ረድቶኛል። እንደ እውነቱ ከሆነ ይህ እሥረኛ ከዚያ በፊት ሰው ገድሎ ስለነበር የእሱ ማስፈራራትም ቢሆን አነስተኛ ጉዳይ አልነበረም። ሰውየው ከተለቀቀ በኋላም ሌላ የነፍስ ግድያ ወንጀል ፈጽሞ ወደ እስር ቤት ተመልሷል።
ወዲያውኑ የባለ አደራነት ሥራ ልቀበል የቻልኩት የይሖዋ ምሥክሮች በታማኝነት የታወቁ ስለሆኑ አያጠራጥርም። ሥራዬም ለእሥረኞች የምግብ ራሽን ማከፋፈል ነበር፤ ስለዚህ በእሥር ቤቱ ግቢ እንደልቤ እንድዘዋወር ተፈቅዶልኝ ነበር። ስለዚህ ለራሴ በቂ ምግብ ማግኘት ብቻ ሳይሆን ክርስቲያን ወንድሞቼም ጥሩ እንክብካቤ እንዲያገኙ ማድረግ ችያለሁ። እንዲያውም አንድ ወንድም እሥር ቤት ሳለ ክብደት ጨምሮ ነበር፤ ከምግብ እጥረት አንፃር ሲታይ ይህ ብርቅ ነበር!
ከእሥር ቤት መስከረም 1944 ተለቀቅን። ወንድም ሀርቴቫም የተለቀቀው በዚያው ቀን ነበር። እኔም ስፈታ ወደ ቤቴል አገልግሎት ተመለስኩ። ለራሴም “ከእሥር ቤት ሕይወት ጋር ሲወዳደር በቤቴል በየቀኑ 16 ሰዓት መሥራት እጅግ በጣም ይመረጣል” ብዬ አሰብኩ። ከዚያ ወዲህ ለሥራ ለግሜ አላውቅም።
ልዩ ልዩ የአገልግሎት መብቶች
በ1944 ቆየት ብሎ ማርጊት ከምትባል አንዲት ውብ አቅኚ ጋር ተገናኘሁና እርሷም እሷን ለማግባት ላለኝ ፍላጎት ምላሽ ስለሰጠች የካቲት 9, 1946 ተጋባን። በተጋባንበት የመጀመሪያ ዓመት እኔ በቤቴል ሳገለግል ማርጊት በአቅኚነት ሄልስንኪ ታገለግል ነበር። ከዚያ ጥር 1947 ለክልል የበላይ ተመልካችነት ሥራ ተመደብን።
በተጓዥነት ሥራችን ላይ አብዛኛውን ጊዜ የምናድረው የሚኖርበት ቤት አንዲት ክፍል ብቻ ከሆነ ቤተሰቦች ጋር ነበር። ሊሰጡን ከሚችሉት ነገር ከሁሉ የበለጠውን እንዳቀረቡልን እናውቅ ስለነበር አማርረን አናውቅም። በዚያ ዘመን ክልሎቹ በጣም ትናንሾች ነበር፤ አንዳንድ ጉባኤዎችማ ጭራሹኑ የተጠመቁ ምስክሮችም አልነበሯቸውም!
በ1948 ወደ ቤቴል አገልግሎት እንድንመለስ ተጋበዝን። ሁለት ዓመት ቆይቶም ዋላስ ኤንድሬስ ከዩናይትድ እስቴትስ ወደ ፊንላንድ መጥቶ ብዙም ሳይቆይ የቅርንጫፍ የበላይ ተመልካች ሆኖ ተሾመ። እንግሊዝኛ መማራችንን እንድንቀጥል ከልብ አበረታታንና እኛም እንዲሁ አደረግን። በመሆኑም የካቲት 1952 በደቡብ ላንሲንግ ኒው ዮርክ በተጀመረው በጊልያድ የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት 19ኛውን ክፍል የሚስዮናውያን ትምህርት እንድንከታተል ተጋበዝን።
ከተመረቅን በኋላ ተመልሰን ፊንላንድ ተመደብን። ይሁን እንጅ ዩናይትድ እስቴትስን ለቀን ከመሄዳችን በፊት በብሩክሊን ኒው ዮርክ በይሖዋ ምሥክሮች ዓለም አቀፍ ዋና መሥሪያ ቤት በማተሚያ መሣሪያ የመሥራት ሥልጠና ተሰጠኝ።
ወደ ፊንላንድ ስንመለስ በተጓዥነቱ ሥራ ተመደብን፣ ይሁንና በ1955 እንደገና ወደ ፊንላንድ ቅርንጫፍ እንድንመለስ ተጋበዝን። በዚያ ዓመት የፋብሪካው የበላይ ተመልካች ሆኜ ተሾምኩ፣ ሁለት ዓመት ቆይቶ በ1957 ደግሞ የቅርጫፍ የበላይ ተመልካች ሆኜ ተሾምኩ። ከ1976 ወዲህ የፊንላንድ ቅርንጫፍ ኮሚቴ አስተባባሪ በመሆን አገልግያለሁ።
ደስ የሚለው ነገር አባቴና እናቴ እስከ ዕለተ-ሞታቸው ድረስ ለይሖዋ ታማኞች ሆነው መኖራቸው ነው። ከጊዜ በኋላ ቁጥራቸው ከመቶ በላይ የሆኑ የአባቴ ዘመዶች ምሥክሮች ሆነዋል። እስከዚህ ዕለትም ወንድሜና እህቶቼ ከነቤተሰቦቻቸው ይሖዋን በማገልገል ላይ ሲሆኑ አንዷ እህቴ አቅኚ ናት።
የበለጸገና አርኪ ሕይወት
ዓመታቱ ሥራ በሥራ ላይ የሚደራረብባቸው ነበሩ፤ ይሁንና ሥራው የአምላክ ሥራ ስለሆነ በእርግጥም የበለጸገና እርካታ የሚያስገኝ ነበር። (1 ቆሮንቶስ 3:6-9) ሕይወቴ ሙሉ በሙሉ የረጋና አስደሳች አልነበረም። ችግሮችና መከራዎችም ነበሩበት። በአፍላ ሕይወቴ ራስ መቅጣትን መማር እንዳለብኝ ተገነዘብኩ። ሁልጊዜ የፈለግሁትን ነገር እኔ እንደምፈልገው ብቻ መሥራት እንደማልችል ተረዳሁ። ብዙ ጊዜ እርማት ይሰጠኝ ስለነበር ቀስ በቀስ ትክክለኛውን አኗኗር ተማርኩ።
ለምሳሌ ያህል በጦርነቱ ዘመን ያጋጠሙኝ ፈተናዎችና እጦቶች ያለቅንጦት እንዴት እንደምኖር አስተምረውኛል። አንድ ነገር በእርግጥ አስፈላጊ መሆን አለመሆኑን ለይቼ ማስተዋልን ተማርኩ። እስከ አሁንም እንኳን ይህ ወይም ያ ያስፈልገኝ እንደሆነ ራሴን የመጠየቅ ልማድ አለኝ። ከዚያም በጣም የሚያስፈልገኝ አለመሆኑን ከተገነዘብኩ አልገዛውም።
ይሖዋ በድርጅቱ አማካኝነት የሚሰጠው አመራር በጣም ግልጽ ሆኖልኛል። በፊንላንድ ቅርንጫፍ ባገለገልኩባቸው ዓመታት ውስጥ የይሖዋ ምሥክሮች ቁጥር ከ1,135 ተነስቶ ከ18,000 በላይ ወደመሆን ሲያድግ በማየት ደስታ አግኝቻለሁ! በእርግጥም ሥራዬ እንደተባረከ ለማየት ብችልም ሥራው የተባረከው የእኛ ሥራ ሳይሆን የይሖዋ ሥራ መሆኑንም አውቃለሁ። (1 ቆሮንቶስ 3:6, 7) በአፍላ ሕይወቴ የይሖዋን መንገድ የመረጥኩ ሲሆን መንገዱም በእርግጥ ከሁሉ የበለጠ የሕይወት መንገድ ሆኖልኛል።
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኤርኪ ካንካአንፓአ ባሁኑ ጊዜ ከሚስቱ ከማርጊት ጋር