የቀድሞዋ ቤተ ክርስቲያን አምላክ ሥላሴ ነው ብላ አስተምራለችን?
ክፍል 3—ክርስትናን ደግፈው የጻፉ ሰዎች (አፖሎጂስቶች) የሥላሴን መሠረተ ትምህርት አስተምረዋልን?
መጠበቂያ ግንብ በህዳር 1, 1991 እና በየካቲት 1, 1992 እትሞቹ ላይ ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱም ሆኑ በመጀመሪያው መቶ ዘመን መጨረሻና በሁለተኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ እዘአ ላይ የኖሩ ሐዋርያዊ አባቶች የሥላሴን መሠረተ ትምህርት እንዳላስተማሩ አሳይቷል። በሁለተኛው መቶ ዘመን የመጨረሻ ክፍሎች ላይ የኖሩ የቤተ ክርስቲያን ሰዎችስ አምላክ ሥላሴ ነው ብለው አስተምረው ነበርን?
ከሁለተኛው መቶ ዘመን አጋማሽ እንደ ዘመናችን አቆጣጠር ጀምሮ እስከዚህ መቶ ዘመን መጨረሻ በነበረው ጊዜ ዛሬ አፖሎጂስት በመባል የሚታወቁ ክርስትናን ደግፈው የጻፉ የቤተ ክርስቲያን ሰዎች ብቅ ብለው ነበር። እነዚህ ፀሐፊዎች ያውቁት የነበረውን ክርስትና በዘመናቸው በነበረው የሮማውያን ዓለም ተስፋፍቶ ከነበረው ፀረ-ክርስቲያናዊ ፍልስፍና ለመከላከል ጽፈው ነበር። የጽሑፍ ሥራዎቻቸው የተገኙት ከሐዋርያዊ አባቶች ጽሑፎች በኋላ ነበር።
በግሪክኛ ከጻፉት አፖሎጂስቶች መሃል ጀስቲን ማርቲር፣ ታቲያን፣ አቴናጐራስ፣ ቴዎፍሎስና የአሌክሳንድሪያው ክሌመንት ይገኙበታል። ተርቱልያን ደግሞ በላቲን ቋንቋ የጻፈ አፖሎጂስት ነበር። ታዲያ እነዚህ አፖሎጂስቶች በአንድ አምላክ ውስጥ እያንዳንዳቸው እውነተኛ አምላክ የሆኑ ሦስት የማይበላለጡ፣ የማይቀዳደሙ አካሎች (አብ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ) አሉ፤ ሆኖም ሦስት አማልክት ሳይሆኑ አንድ አምላክ ናቸው በማለት ዘመናዊውን የሕዝበ ክርስትና ሥላሴ አስተምረው ነበርን?
“ወልድ የበታች ነው”
ዶክተር ኤች አር ቦኤር የቀድሞዋ ቤተ ክርስቲያን አጭር ታሪክ በተሰኘ የእንግሊዝኛ መጽሐፋቸው ላይ የአፖሎጂስቶችን ትምህርት ዋነኛ መንፈስ በተመለከተ የሚከተለውን አስተያየት ሰጥተዋል፦
“ጀስቲን [ማርቲር] ዓለም ከመፈጠሩ በፊት አምላክ ብቻውን ይኖር እንደነበርና ወልድ እንዳልነበረ አስተምሯል። . . . አምላክ ዓለምን ለመፍጠር በፈለገ ጊዜ . . . ዓለምን እንዲፈጥርለት ሌላ መለኮታዊ ፍጡር ወለደ (አስገኘ)። ይህም መለኮታዊ ፍጡር . . . የተወለደ በመሆኑ ምክንያት ወልድ ተብሎ ተጠራ፤ ከአምላክ የማሰብ ኃይል ወይም አእምሮ የተገኘ ስለሆነም ሎጎስ ተብሎ ተጠራ . . .
“እንግዲያውስ ጀስቲንና ሌሎችም አፖሎጂስቶች ወልድ ፍጡር ነው ብለው አስተምረዋል። ከፍ ያለ ፍጡር፣ ዓለምን ለመፍጠር የበቃ ኃያል ፍጡር ነው። ቢሆንም ፍጡር ነው እንጂ ፈጣሪ አይደለም። ይህም በሥነ አምልኮ ትምህርት ሰቦርዲኔሽኒዝም ወይም የበታችነት ተብሎ ይጠራል። ይህም ማለት የአባቱ የበታች፣ ምክትልና ከአባቱ የተገኘና የአባቱ ጥገኛ ነው ማለት ነው። አፖሎጂስቶች ሰቦርዲኔሽንስቶች ወይም በወልድ የበታችነት የሚያምኑ ነበሩ።”1
ዶክተር ማርቲን ቨርነር የክርስትና ቀኖናዊ ሕግ አመሠራረት በተሰኘ የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ላይ የጥንት ክርስቲያኖች ወልድ ከአብ ጋር ስላለው ዝምድና የነበራቸውን ግንዛቤ አስመልክተው የሚከተለውን ብለዋል፦
“ወልድ የአምላክ የበታች እንደነበረ የተረጋገጠ ግንዛቤ ነበር። ክርስቶስ የአምላክ ተገዥ ነበር ማለት ነው። በአዲስ ኪዳን ውስጥ ኢየሱስ ከእግዚአብሔር አብ ጋር ያለው ዝምድና በተወሳበት በማንኛውም ቦታ . . . ወልድ የአብ የበታች መሆኑን በማያሻማ ሁኔታ መገንዘብና መረዳት ይቻላል። በአዲስ ኪዳን የመጀመሪያዎቹ ሦስት ወንጌሎች መግለጫ መሠረት ዋናው የበታችነት እምነት ጠበቃ ኢየሱስ ነው። . . . ይህ ጥንታዊ አቋም ከመጀመሪያው አንስቶ ጽኑና ግልጽ ሆኖ ለረዥም ጊዜ ለመቆየት ችሎ ነበር። ‘ከኒቂያ ጉባኤ በፊት የነበሩት ሃይማኖታዊ ሊቃውንት በሙሉ ሎጎስ የአምላክ የበታች መሆኑን ገልጸዋል።’”2
አር ፒ ሲ ሀንሰን ከዚህ ሐሳብ ጋር በመስማማት ዘ ሰርች ፎር ዘ ክሪስቲያን ዶክትሪን ኦፍ ጎድ በተሰኘ መጽሐፋቸው ላይ እንዲህ ብለዋል፦
“የአርዮስ ክርክር ከመጀመሩ ከአራተኛው መቶ ዘመን በፊት በምሥራቅም ሆነ በምዕራብ አብያተ ክርስቲያናት ወልድ የአብ የበታች መሆኑን የማያምን የሃይማኖት ሊቅ አልነበረም ብለዋል።”3
ዶክተር አልቫን ላምሰንም የመጀመሪያዎቹ ሦስት መቶ ዘመናት ቤተ ክርስቲያን በተሰኘ መጽሐፋቸው ላይ ከኒቂያ ጉባኤ (325 እዘአ) በፊት የነበሩት የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ያስተምሩት ስለነበረው ትምህርት የሚከተለውን ምሥክርነት አክለዋል፦
“ከኒቂያ ጉባኤ በፊት የነበሩት አባቶች በሙሉ ለማለት ባይቻልም በአብዛኛው ወልድ የበታች መሆኑን አረጋግጠዋል። . . . ወልድ የበታች እንደሆነ በግልጽ መናገራቸው ወልድ ከአብ የተለየ መሆኑን እንደሚያምኑ በግልጽ ያሳያል። . . . ከአብ የተለየና የበታች እንደሆነ አድርገው ይመለከቱት ነበር።”4
በተመሳሳይም ሮበርት ኤም ግራንት አምላኮችና አንዱ አምላክ በተሰኘው የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ውስጥ ስለ አፖሎጂስቶች የሚከተለውን ብለዋል፦
“ክርስትናን በመደገፍ የተጻፉት ጽሑፎች ስለ ክርስቶስ የሚሰጡት መግለጫ በአዲስ ኪዳን ውስጥ ከሚገኘው መግለጫ የተለየ አይደለም። የወልድን የበታችነት የሚያረጋግጥ ነው። . . . እንግዲያውስ በእነዚህ የቀድሞ ደራሲዎች ጽሑፍ ውስጥ የሥላሴን መሠረተ ትምህርት አናገኝም። . . . ከኒቂያ ጉባኤ በፊት የነበረው የክርስትና መንፈሳዊ ትምህርት በሙሉ የወልድን የበታችነት የሚያምን ነበር ለማለት ይቻላል።”5
የሕዝበ ክርስትና የሥላሴ ትምህርት ወልድ ከእግዚአብሔር አብ ጋር በዘላለማዊነት፣ በሥልጣን፣ በደረጃና በጥበብ እኩል ነው ብሎ ያስተምራል። አፖሎጂስቶች ግን ወልድ ከእግዚአብሔር አብ ጋር እኩል እንዳልሆነ ተናግረዋል። ወልድን የበታች እንደሆነ አድርገው ይመለከቱት ነበር። ይህም የሥላሴን ትምህርት የሚፃረር ነው።
የመጀመሪያ መቶ ዘመኑን ትምህርት አንጸባርቀዋል
ስለ አብና ወልድ ዝምድና አፖሎጂስቶችና ሌሎች የቀድሞ ቤተ ክርስቲያን አባቶች በከፍተኛ ደረጃ ያንፀባረቁት የመጀመሪያ መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ያስተማሩትን ነበር። ይህንንም የክርስትና ቀኖናዊ ሕግ አመሠራረት በተሰኘው መጽሐፍ ላይ ተመልከቱ፦
“በጥንቱ የክርስትና ዘመን በኋለኞቹ ዘመናት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ኃይለኛ አለመግባባትና ግጭት የፈጠረውን የመሰለ ምንም ዓይነት በሥላሴ ትምህርት ላይ የተመሠረተ ክርክርና ውዝግብ አልነበረም። ይህም የሆነው የጥንቱ ክርስትና ክርስቶስ . . . በዘመናት ፍጻሜ . . . የእግዚአብሔርን መንግሥት የሚያመጣ በአምላክ የተፈጠረና የተመረጠ የከፍተኛው ሰማያዊ የመላእክት ዓለም ክፍል መሆኑን ያምን ስለነበር መሆኑ አያጠራጥርም።”6
በተጨማሪም የቀድሞዎቹ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ያስተማሩትን በሚመለከት ዘ ኢንተርናሽናል ስታንዳድርድ ባይብል ኢንሳይክሎፒድያ የሚከተለውን የእምነት ቃል ሰጥቷል፦
“በቀድሞው የቤተ ክርስቲያን አስተሳሰብ መሠረት ስለ አምላክ ሲነሳ በመጀመሪያ የሚታወሰው አምላክ የኢየሱስ ክርስቶስ አባት መሆኑ ሳይሆን የሁሉም ፍጡራን ምንጭ መሆኑ ነበር። ስለዚህ እግዚአብሔር አብ ከሁሉ የበለጠ ክብር ሊሰጠው የሚገባ ነው። መጀመሪያ የሌለው፣ የማይሞት፣ የማይለወጥ፣ በቃላት ሊገለጽ የማይችል፣ የማይታይና የማይወለድ የሚሉትን የመሳሰሉ መግለጫዎች የሚሰጡት ለእርሱ ብቻ ነው። ሁሉንም ነገሮችና ፍጥረታትን በሙሉ ካለመኖር ወደ መኖር ያመጣው እርሱ ነው። . . . .
“ይህም ወልድና መንፈስ ቅዱስ አምላኮች ናቸው ከማለት ይልቅ አብ ብቻ አምላክ ነው መባሉ ተገቢ እንደሆነ የሚያመለክት ይመስላል። በቀድሞ ጊዜ ተጽፈው የሚገኙ ብዙ መግለጫዎች ይህን ሐሳብ የሚደግፉ ይመስላሉ።”7
ይህ ኢንሳይክሎፒዲያ ለእነዚህ እውነቶች ዝቅተኛ ግምት በመስጠት የሥላሴ መሠረተ-ትምህርት በቀድሞ ዘመን ተቀባይነት ነበረው ብሎ ቢናገርም መረጃዎቹ ግን አባባሉ እውነት አለመሆኑን ያረጋግጣሉ። ዕውቅ የካቶሊክ ሃይማኖት ሊቅ የሆኑት ጆን ሄነሪ ካርዲናል ኒውማን የተናገሩትን ተመልከቱ፦
“ጌታችንን የሚመለከቱ የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን መሠረተ ትምህርቶች በሙሉ በማያሻማና በማያወላውል መንገድ ተገልጠዋል። . . . የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የምታስተምረው የሥላሴ መሠረተ-ትምህርት ግን በእርግጥ ከዚህ የተለየ ነው። በጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሥላሴን የሚደግፍ አጠቃላይ ስምምነት ነበረ ለማለት እንዴት እንደሚቻል እኔ አይታየኝም። . . .
“የጥንቱ ዘመን እምነቶች በጭራሽ . . . [ሥላሴን] አይጠቅሱም። በእርግጥ ስለ ሦስት አካላት ይናገራሉ፤ ቢሆንም በመሠረተ-ትምህርቱ ውስጥ ምስጢር የሆነ ወይም ሦስቱንም አንድ፣ እኩል፣ ዘላለማዊያን፣ ያልተፈጠሩ፣ ሁሉን ቻዮች፣ ከመረዳት ችሎታ በላይ መሆናቸውን የሚገልጽ ነገር የለም።”8
የጀስቲን ማርቲር ትምህርት
ከቀድሞ አፖሎጂስቶች አንዱ ከ110 እስከ 165 ገደማ የኖረው ጀስቲን ማርቲር ነበር። በዛሬው ጊዜ ከሚገኙት ጽሑፎቹ መሃል በአንድ አምላክ ውስጥ ሦስት እኩል የሆኑ አካሎች መኖራቸውን የሚጠቅስ ነገር የለም።
ለምሳሌ ያህል በካቶሊክ ጀሩሳሌም ባይብል መሠረት ምሳሌ 8:22-30 ኢየሱስ ሰው ሆኖ ከመወለዱ በፊት ስለነበረበት ሁኔታ “ያህዌህ በመጀመሪያ ዓላማውን ሲዘረጋ ከቀድሞ ሥራዎቹ ሁሉ በፊት ፈጠረኝ። . . . እኔ በተወለድኩ ጊዜ ጥልቆች አልነበሩም። . . . ከተራሮች በፊት እኔ ተወለድሁ። . . . እኔ ከጎኑ ሆኘ ዋና ሠራተኛ ነበርኩ” ይላል። ጀስቲን ይህን ጥቅስ ከትሪፎ ጋር ባደረገው ውይይት ላይ እንደሚከተለው በማለት አብራርቶታል።
“ቅዱስ ጽሑፉ ይህ ልጅ ማንኛውም ነገር ከመፈጠሩ በፊት ከአብ እንደተወለደ ተናግሯል። የተወለደም በቁጥርም ሆነ በአካል ከወላጁ የተለየ መሆኑን ማንም ያውቃል።”9
ወልድ ከአብ የተወለደ ስለሆነ ጀስቲን ወልድን “አምላክ” (God) ሲል ጠርቶአል። በመጀመሪያው አፖሎጂው ላይ “የአጽናፈ-ዓለሙ አባት ልጅ አለው። እርሱም የአምላክ የመጀመሪያ ልጅና ቃል በመሆኑ አምላክ (God) ነው”10 ብሏል። መጽሐፍ ቅዱስም የእግዚአብሔርን ልጅ “አምላክ” (God) በሚለው የማዕረግ ስም ይጠራዋል። በኢሳይያስ 9:6 ላይ “ኃያል አምላክ” ተብሎ ተጠርቷል። ይሁንና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መላእክት፣ ሰዎች፣ የሐሰት አማልክትና ሰይጣንም አምላክ (god) ተብለው ተጠርተዋል።” (መላእክት፣ መዝሙር 8:5፤ ከዕብራውያን 2:6, 7 ጋር አወዳድር። ሰዎች፣ መዝሙር 82:6፤ የሐሰት አማልክት ዘጸአት 12:12፤ 1 ቆሮንቶስ 8:5፤ ሰይጣን፦ 2 ቆሮንቶስ 4:4) በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ “አምላክ” ተብሎ የተተረጎመው ኤል የተባለ የዕብራይስጥ ቃል ትርጉሙ “ኃያሉ”፣ “ብርቱው” ማለት ነው። በግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የተጠቀሰው ተመሳሳይ ትርጉም ያለው ቃል ቴኦስ ነው።
ከዚህም በላይ በኢሳይያስ 9:6 ላይ የተጠቀሰው የዕብራይስጥ ቃል በወልድና በአምላክ መሃል ግልጽ ልዩነት እንዳለ ያሳያል። እዚህ ላይ ወልድ “ሁሉን ቻይ” (ኤልሻዳይ) ሳይሆን “ኃያል አምላክ” “ኤል ጊቦር” ተብሎ ተጠርቷል። ‘ኤልሻዳይ’ የሚለው የዕብራይስጥ ቃል ለይሖዋ ብቻ የሚያገለግል ነው።
ይሁን እንጂ ጀስቲን ወልድን “አምላክ” ብሎ ቢጠራውም ወልድ እያንዳንዳቸው አምላክ የሆኑና ሦስቱም አንድ አምላክ ብቻ ከሚሆኑ እኩልነት ያላቸው ሦስት አካላት ውስጥ አንዱ ክፍል ነው እንዳላለ አስተውሉ። ከዚህ ይልቅ ከትሪፎ ጋር ባደረገው ውይይት ላይ እንዲህ ብሏል፦
“ሁሉንም ነገሮች ለሠራው አምላክ [ሁሉን ቻይ ለሆነው አምላክ] ተገዢ የሆነ ሌላ አምላክና ጌታ [ኢየሱስ ሰው ከመሆኑ በፊት] . . . አለ። እርሱም መልአክ ተብሎ ተጠርቶአል። ምክንያቱም ሁሉን የሚችለውና የነገሮች ሁሉ ሠሪ የሆነው አምላክ ለሰዎች ለማስታወቅ የፈለገውን ነገር ሁሉ ለሰዎች የሚያስታውቀው እሱ [ወልድ] ስለሆነ ነው። . . . .
“[ወልድ] ሁሉን ነገር ከሠራው አምላክ የተለየ የሆነው በቁጥር እንጂ በፈቃድ አይደለም።”11
በጀስቲን የመጀመሪያ አፖሎጂ ላይ ክርስቲያኖች አምላክ የለሾች ናቸው እየተባሉ በአረማውያን ይቀርብባቸው የነበሩትን ክሶች ለማስተባበል በጻፈው 6ኛ ምዕራፍ ላይ አንድ ትኩረት የሚስብ ምንባብ ይገኛል። እሱም እንዲህ ይነበባል፦
“እሱን ራሱንም [አምላክንም] ሆነ ወልድን (ከአብ ወጥቶ የመጣውንና ለእኛም እነዚህን ነገሮች ያስተማረንን እንዲሁም እሱን ወይም ወልድን የሚከተሉትንና እሱን መስለው የተሠሩትን ሌሎች ጥሩ መላእክት) እንዲሁም ትንቢታዊውን መንፈስ እናመልካለን፣ እናከብራለንም።”12
ይህን ጽሑፍ የተረጎሙት በርንሃርድ ሎስ የሚከተለውን አስተያየት ሰጥተዋል፦ “ጀስቲን በዚህ ዝርዝር ላይ ክርስቲያኖች ለመላእክትም የሚሰግዱላቸውና ክብር የሚሰጧቸው መሆኑን መጥቀሱ ሳይበቃው መላእክትን ከመንፈስ ቅዱስ በፊት ጠቅሶአል።”13—አን ኢሴይ ኦን ዘ ዲቬሎፕመንት ኦቭ ክርስቲያን ዶክትሪን የተሰኘውን ጽሑፍ ተመልከቱ።14
ስለዚህ ጀስቲን ክርስቲያኖች ሊያመልኩ የሚገባው ማንን ብቻ ስለመሆኑ ከመጽሐፍ ቅዱስ ንጹሕ መሠረተ ትምህርት ፈቀቅ ያለ መሆኑ ግልጽ ቢሆንም መላእክት ከአምላክ ጋር እኩያዎች ሆነው እንደማይታዩ ሁሉ ጀስቲን ወልድ ከአብ ጋር እኩል እንደሆነ አድርጎ አልተመለከተም። ጀስቲንን በሚመለከት በላምሰን ከተጻፈው የመጀመሪያዎቹ ሦስት መቶ ዘመናት ቤተ ክርስቲያን ከተሰኘው መጽሐፍ እንደገና እንጠቅሳለን፦
“ጀስቲን ወልድን ከአብ የተለየና ያነሰ እንደሆነ አድርጎ ቆጥሮታል። የተለየ ነው ሲባልም እንደ ዘመናችን እምነት ከሦስት ሃይፖስታስስ ወይም አካሎች አንዱ መሆኑን ለማስረዳት አይደለም። በባሕርይና በዓይነቱ የተለየ፤ ሥልጣኑንና ማእረጉን ሁሉ ካገኘበት ከአብ የተለየ፣ እውነተኛና ጉልህ የሆነ የራሱ የግል ሕላዌ ያለው፤ ከአብ በታች ሆኖ የሚተዳደርና በሁሉም ነገር ለአብ ፈቃድ የሚገዛ ነው። አብ ከሁሉ በላይ ነው፤ ወልድ ግን የበታች ነው። ማለትም አብ የስልጣን ሁሉ ምንጭ ነው፤ ወልድ ግን የሥልጣን ተቀባይ ነው፤ አብ አመንጪ ወይም ፈጣሪ ነው። ወልድ ደግሞ የአብ አገልጋይ ወይም መሣሪያ በመሆን የአብን ፈቃድ ያስፈጽማል። በቁጥር ሁለት ቢሆኑም እርስ በርስ ይስማማሉ ወይም በፈቃድ አንድ ናቸው። ወልድ ምንጊዜም ለአብ ፈቃድ ይገዛል።”15
በተጨማሪም ጀስቲን መንፈስ ቅዱስ ከአብና ከወልድ ጋር እኩል ነው ብሎ የተናገረበት ቦታ የለም። ስለዚህ ጀስቲን ዘመናዊውን የሕዝበ ክርስትና ሥላሴ አስተምሯል ብሎ በሐቀኝነት ለመከራከር የሚቻልበት ምንም ማስረጃ የለም።
ክሌመንት ምን አስተምሮአል?
ከ150 እስከ 215 እዘአ የኖረው የአሌክሳንድሪያው ክሌመንትም ወልድን “አምላክ” (God) ሲል ጠርቶታል። እንዲያውም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለኢየሱስ ተሰጥቶ የማያውቀውን የማዕረግ ስም በመጠቀም “ፈጣሪ” ሲል ጠርቶታል። ታዲያ ይህን ሲል ወልድ በሁሉም መንገድ ሁሉን ቻይ ከሆነው ፈጣሪ ጋር እኩል ነው ማለቱ ነበርን? አልነበረም። ክሌመንት ስለ ወልድ “ሁሉ በእርሱ ሆነ” የተባለበትን ዮሐንስ 1:3 መጥቀሱ እንደነበር በግልጽ ይታያል። “አምላክ በፍጥረት ሥራዎቹ ወልድን እንደ ወኪሉ አድርጎ ተጠቅሞበታል።”16— ቆላስይስ 1:15-17
ክሌመንት ከሁሉም በላይ የሆነውን አምላክ “የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት”17 በማለት ጠርቶታል። በተጨማሪም “ጌታ [ኢየሱስ] የፈጣሪ ልጅ ነው”18 ብሎአል። ከዚህም በላይ “የሁሉም አምላክ የሆነ አንድ ጥሩና ትክክለኛ ፈጣሪ አለ፣ ወልድም በአብ ውስጥ የሚኖር [ነው]”19 ብሏል። ስለዚህ ወልድ የበላዩ የሆነ አምላክ እንዳለው ጽፏል።
ክሌመንት አምላክ “ብቸኛውና የመጀመሪያው የዘላለም ሕይወት ሰጪ እንደሆነና ይህንንም የዘላለም ሕይወት ወልድ ከእርሱ [ከአምላክ] ተቀብሎ ለእኛ እንደሚሰጥ20 ተናግሮአል።” የመጀመሪያው የዘላለም ሕይወት ሰጭ የዘላለም ሕይወትን ተቀብሎ ከሚያስተላልፈው እንደሚበልጥ ግልጽ ነው። በመሆኑም ክሌመንት “አምላክ የመጀመሪያውና ከሁሉ በላይ የሆነው ልዑል ነው ብሏል።”21 በተጨማሪም ወልድ “ብቻውን ሁሉን ቻይ ለሆነው [አምላክ] በጣም የቀረበ” ነው፣ እንዲሁም “ወልድ ከአብ ፈቃድ ጋር በመስማማት ሁሉንም ነገር ያጠናቅቃል”22 ብሏል። ክሌመንት ሁሉን ቻይ አምላክ በወልድ ላይ ያለውን የበላይነት በተደጋጋሚ ገልጿል።
የመጀመሪያው መቶ ዘመን ቤተ ክርስቲያን የተሰኘው መጽሐፍ ስለ አሌክሳንድሪያው ክሌመንት እንደሚከተለው ይላል፦
“ከክሌመንት ጽሑፎች ላይ የወልድ የበታችነት በግልጽ የተነገረባቸውን ብዙ አንቀጾች መጥቀስ እንችላለን።. . . .
“አንድ ሰው ተራ በሆነ ትኩረት የክሌመንትን ጽሑፍ አንብቦ አንዴም እንኳን ክሌመንት ወልድን ከአብ ጋር አንድ እንደሆነ አድርጎ ተመልክቶታል ብሎ ቢያስብ በጣም ያስገርመናል። ለእኛ እንደሚመስለን የወልድን የጥገኝነትና የበታችነት ባሕርይ ከየትኛውም የጽሑፉ ክፍል መረዳት ይቻላል። ክሌመንት አምላክንና ልጁን የተለያዩ እንደሆኑ ያምን ነበር። በሌላ አነጋገር [አብና ወልድ] አንዱ ከሁሉ በላይ የሆነና ሌላው ደግሞ የበታች የሆነ ሁለት ሕላዌ ያላቸው አካላት እንደሆነ አምኗል።”23
በተጨማሪም እንደሚከተለው ሊባል ይችላል፦ ክሌመንት አንዳንድ ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ኢየሱስ ከሚናገረው አልፎ የሚሄድ ቢመስልም በአንድ አምላክ ውስጥ ሦስት እኩል የሆኑ አካሎች ስላሉበት ሥላሴ የተናገረበት ቦታ የለም። ጀስቲንና ክሌመንት በኖሩበት ዘመን መሃል የነበሩ እንደ ታቲያን፣ ቲዮፊለስና አቴናጎራስ የመሳሰሉት አፖሎጂስቶችም ከጀስቲንና ከክሌመንት ጋር የሚመሳሰል አመለካከት ነበራቸው። ላምሰን “ስለ ሥላሴ ከጀስቲን የተለየ እምነት አልነበራቸውም። ከሥላሴ እምነት ጋር ጨርሶ ሊታረቅ የማይችል እምነት አስተማሩ እንጂ ሊከፈሉ በማይችሉና እኩዮች በሆኑ ሦስት ሦስት አማልክት አያምኑም ነበር።”24
የተርቱሊያን ሃይማኖታዊ ትምህርት
ትሪኒታስ የተሰኘውን የላቲን ቃል ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀመበት ከ160 እስከ 230 የኖረው ተርቱሊያን ነበር። ሄንሪ ቻድዊክ እንደገለጹት ተርቱሊያን አምላክ ‘አንድነት በሦስትነት’25 ያለው ነው የሚል ሐሳብ አቅርቧል። ይሁን እንጂ ተርቱሊያን ይህን ያለው ሦስት እኩል የሆኑና በዘላለማዊነት የማይበላለጡ አካሎችን ለማመልከት ፈልጎ አልነበረም። ሆኖም የእርሱ ትምህርት ከዚያ በኋላ በተነሱ የሥላሴን እምነት የሚደግፉ ጸሐፊዎች ዳብሮ ደርጅቷል።
ተርቱሊያን በወልድ የበታችነት የሚያምን ስለነበር እርሱ ስለ አብ፣ ስለ ወልድና ስለ መንፈስ ቅዱስ የነበረው ግንዛቤ ሕዝበ ክርስትና ከምታምንበት ሥላሴ እጅግ የራቀ ነው። ወልድን የሚመለከተው የአብ የበታች እንደሆነ አድርጎ ነበር። አጌንስት ሄርሞጂንስ በተሰኘ ጽሑፉ ላይ እንደሚከተለው በማለት ጽፏል፦
“ከአምላክ በቀር ያልተወለደና ያልተፈጠረ ሌላ ሕላዌ አለ ብለን ማሰብ አይገባንም . . . አንድያ ልጅና የመጀመሪያ ልጅ ከሆነው ከቃል የሚበልጠውና ከእርሱም በእርግጥ የላቀው አብ ብቻ እንጂ ሌላ ማን ሊሆን ይችላል? . . . ሕልውና የሚሰጥና ለራሱ ሠሪ ያላስፈለገው [አምላክ] ወደ ሕልውና ለመምጣት ምክንያት ወይም ሠሪ ካስፈለገው [ከወልድ] በማዕረግ እጅግ በጣም ከፍ ያለ ነው።”26
በተጨማሪም አጌንስት ፕራክሲያስ በተሰኘው መጽሐፍ ላይ እንደሚከተለው በማለት ወልድ ሁሉን ቻይ ከሆነው አምላክ የተለየና የበታች መሆኑን ገልጿል፦
“አብ ሁሉም ነገር ሲሆን ወልድ ግን እሱ ራሱም ‘ከእኔ አብ ይበልጣል’ በማለት እንዳስታወቀው ከዚያ ምልአት [ከአምላክ] የመነጨና የእሱም ክፋይ ነው። . . . ወላጅ ከተወላጅ ወይም ከልጅ የተለየ የመሆኑን ያህል አብ ከወልድ የበለጠ በመሆኑ ከወልድ የተለየ ነው፤ ላኪ አንድ ሲሆን ተላኪ ደግሞ ሌላ ነው፤ እንደገናም ሠሪ አንድ ሲሆን የተሠራው ነገር ደግሞ ሌላ ነው።”27
ተርቱሊያን አጌንስት ሄርሞጂንስ ላይ ወልድ ሕላዌ አግኝቶ ያልኖረበት ጊዜ እንደነበረና በዚህም ምክንያት ወልድ እንደ አምላክ ዘላለማዊነት አለው ብሎ እንደማያምን ተናግሯል።28 ካርዲናል ኒውማን “ተርቱሊያን የጌታችንን ዘላለማዊነት በሚመለከት ሄትሮዶክሳዊ [አጠቃላይ ስምምነትና ተቀባይነት ያላገኙ መሠረተ-ትምህርቶችን የሚያምን] እንደነበረ ተደርጎ መታየት አለበት”29 ብለዋል። ተርቱሊያንን በሚመለከት ላምሶን እንደሚከተለው ተናግረዋል፦
“ይህ ግሪካውያን ሎጎስ ብለው የሚጠሩት የመገኘት ምክንያት ተርቱሊያን እንደሚያምነው በኋላ ቃል ወይም ወልድ ሆኖ እውነተኛ ሕልውና አገኘ። ከዚያ በፊት ግን የአብ ባሕርይ ክፍል ሆኖ ከዘላለም እስከ ዘላለም ይኖር ነበር። ይሁን እንጂ ተርቱሊያን ለወልድ የሰጠው ደረጃ ከአብ ያነሰ ነበር . . .
“የተርቱሊያን እምነት በዛሬው ጊዜ ለሥላሴ እምነት በሚሰጠው ትርጉም መሠረት ቢመዘን ተርቱሊያንን በመናፍቅነት ከማውገዝ ለማዳን የሚደረገው ማንኛውም ሙከራ ከንቱ ይሆናል። የሚቀርብበትን ክስ ለአንድ አፍታ እንኳን ለመቋቋም ባልቻለ ነበር።”30
የሥላሴን እምነት አላስተማሩም
የአፖሎጂስቶችን ጽሑፎች በሙሉ ብታነቧቸው በአንዳንድ ረገድ ከመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች የራቁ ሆነው ልታገኟቸው ብትችሉም አንዳቸውም አብ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ በዘላለማዊነት፣ በሥልጣን፣ በደረጃና በጥበብ እኩል ናቸው ብለው እንዳላስተማሩ ትገነዘባላችሁ።
በሁለተኛውና በሦስተኛው መቶ ዘመን የኖሩ እንደ ኢራኒየስ፣ ሂፖሊተስ፣ ኦሪገን፣ ሲፕሪያንና ኖቫሺያን የመሳሰሉት ጸሐፊዎችም ከአፖሎጂስቶች የተለዩ አልነበሩም። አንዳንዶቹ አብንና ወልድን በአንዳንድ መንገዶች እኩል አድርገው ቢመለከቷቸውም በሌሎች መንገዶች ግን ወልድ ከአብ የበታች እንደሆነ አድርገው ይመለከቱት ነበር። ከእነሱ መሃል መንፈስ ቅዱስ ከአብና ከወልድ ጋር እኩል እንደሆነ ያሰበ አንድም አልነበረም። ለምሳሌ ያህል ኦሪገን ቅዱሳን ጽሑፎች (185-254 እዘአ) የእግዚአብሔር ልጅ “ከፍጥረት ሁሉ በኩር” እንደሆነና “ከፍጥረት ሥራዎች ሁሉ እጅግ በጣም ጥንታዊ መሆኑን ያወሳሉ”31 በማለት ተናግሯል።
የእነዚህን የቀድሞ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ጽሑፎች ባልተዛባ አስተሳሰብ ማንበብ የሕዝበ ክርስትና የሥላሴ እምነት በእነሱ ዘመን ፈጽሞ እንዳልነበረ ያሳያል። የመጀመሪያዎቹ ሦስት መቶ ዘመናት ቤተ ክርስቲያን እንደሚከተለው ይላል፦
“በዘመናችን በጣም ተስፋፍቶ የሚገኘው የሥላሴ እምነት . . . ከጀስቲን አነጋገር ምንም ድጋፍ አያገኝም። ከኒቂያ ጉባኤ በፊት የተነሱ አባቶች፣ ማለትም ከክርስቶስ ልደት በኋላ በነበሩት ሦስት መቶ ዘመናት የተነሱት ፀሐፊዎች በሙሉ ከዚህ የተለዩ አይደሉም። እውነት ነው፣ ስለ አብ፣ ስለ ወልድ እና ስለ ትንቢታዊው መንፈስ ወይም ስለ መንፈስ ቅዱስ ተናግረዋል። ይሁንና ዛሬ በሥላሴ አማኞች እንደሚታመነው እኩያሞች እንደሆኑ ወይም ፍጹም አንድ እንደሆኑ ወይም አንድነት በሶስትነት እንዳላቸው በምንም መንገድ አልተናገሩም። እነርሱ የተናገሩት የዚህን ተቃራኒ ነው። እነዚህ አባቶች የገለጹት የሥላሴ ትምህርት በዘመናችን ከሚገኘው መሠረተ ትምህርት ፈጽሞ የተለየ ነው። ይህን የምንናገረው በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ እንደሚገኝ እንደማንኛውም ሐቅ በበቂ ማስረጃ ላይ የተመሠረተ ስለሆነ ነው።”32
እንደ እውነቱ ከሆነ ከተርቱሊያን በፊት ሥላሴ የሚባል ቃል ተጠቅሶ አያውቅም። የተርቱሊያን “ሄትሮዶክሳዊ” ሥላሴም በዛሬው ጊዜ ከሚታመንበት ሥላሴ በጣም የተለየ ነው። ታዲያ በዛሬው ጊዜ የሚታመነው የሥላሴ እምነት ከየት መጣ? በ325 እዘአ በኒቂያ ከተደረገው ጉባኤ ነውን? እነዚህን ጥያቄዎች ወደፊት በሚወጣ የመጠበቂያ ግንብ እትም ላይ በክፍል 4 በሚቀርበው ርዕሰ ትምህርት እንመረምራለን።
References:
1. A Short History of the Early Church, by Harry R. Boer, 1976, page 110.
2. The Formation of Christian Dogma, by Martin Werner, 1957, page 125.
3. The Search for the Christian Doctrine of God, by R. P. C. Hanson, 1988, page 64.
4. The Church of the First Three Centuries, by Alvan Lamson, 1869, pages 70-1.
5. Gods and the One God, by Robert M. Grant, 1986, pages 109, 156, 160.
6. The Formation of Christian Dogma, pages 122, 125.
7. The International Standard Bible Encyclopedia, 1982, Volume 2, page 513.
8. An Essay on the Development of Christian Doctrine, by John Henry Cardinal Newman, Sixth Edition, 1989, pages 14-18.
9. The Ante-Nicene Fathers, edited by Alexander Roberts and James Donaldson, American Reprint of the Edinburgh Edition, 1885, Volume I, page 264.
10. Ibid., page 184.
11. The Ante-Nicene Fathers, Volume 1, page 223.
12. Ibid., page 164.
13. A Short History of Christian Doctrine, by Bernhard Lohse, translated from the German by F. Ernest Stoeffler, 1963, second paperback printing, 1980, page 43.
14. An Essay on the Development of Christian Doctrine, page 20.
15. The Church of the First Three Centuries, pages 73-4, 76.
16. The Ante-Nicene Fathers, Volume II, page 234.
17. Ibid., page 227.
18. Ibid., page 228.
19. Ibid.
20. Ibid., page 593.
21. Ibid.
22. Ibid., page 524.
23. The Church of the First Three Centuries, pages 124-5.
24. Ibid., page 95.
25. The Early Church, by Henry Chadwick, 1980 printing, page 89.
26. The Ante-Nicene Fathers, Volume III, page 487.
27. Ibid., pages 603-4.
28. Ibid., page 478.
29. An Essay on the Development of Christian Doctrine, pages 19, 20.
30. The Church of the First Three Centuries, pages 108-9.
31. The Ante-Nicene Fathers, Volume IV, page 560.
32. The Church of the First Three Centuries, pages 75-6.
[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ክሌመንት
[ምንጭ]
Historical Pictures Service
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ተርቱሊያ
[ምንጭ]
Historical Pictures Service