ወደ “ብርሃን አብሪዎች” የወረዳ ስብሰባ እንድትመጡ ተጋብዛችኋል
“እነሆ ጨለማ ምድርን ድቅድቅ ጨለማም አሕዛብን ይሸፍናል።” (ኢሳይያስ 60:2) እነዚህ ቃሎች በዛሬ ጊዜ ምንኛ እውነትን ያዘሉ ናቸው! ሰዎች አምላክ የሚደሰትበትን አምልኮ እንዳያውቁ ሐሰተኛ ሃይማኖት በጨለማ ሸብቦ እንደያዛቸው የማያጠያይቅ ጉዳይ ነው። ለምን እንደዚያ እንላለን? ምክንያቱም የዚህ ዓለም አምላክ የሆነው ሰይጣን “የማያምኑትን ሐሳብ አሳውሯልና።”—2 ቆሮንቶስ 4:4
በተቃራኒው ደግሞ በሰይጣን ያልታወሩት የይሖዋ ምስክሮች ናቸው። “በአንቺ ላይ እግዚአብሔር ይወጣል ክብሩም በአንቺ ላይ ይታያል” የሚለው የነቢዩ የኢሳይያስ ቃል በእነርሱ ላይ ሊሠራ ይችላል። (ኢሳይያስ 60:2) ከጨለማ ወጥተው ወደሚደነቀው የአምላክ ብርሃን በመምጣታቸው ምንኛ አመስጋኞች ናቸው! ይህ ብርሃን በአካል እንኳ የታወሩት ማየት ይችሉ ዘንድ አእምሮአቸውን የሚያበራላቸው መንፈሳዊ ብርሃን የሆነው በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘው እውነት ነው።
እርግጥ ነው ለዚህ እርዳታ ያስፈልጋል፤ አንድ ሰው አምላክ እኛን ለመርዳት ባዘጋጀልን አጋዥ ዝግጅት ሳይጠቀም መጽሐፍ ቅዱስን እንዲሁ በማንበብ ብቻ ብርሃኑ ምን እንደሆነ ሊያስተውል አይችልም። በማቴዎስ 24:45-47 ላይ አስቀድሞ ይመጣል ተብሎ የተነገረለትን “ታማኝና ልባም ባሪያ” ይሖዋ አምላክ የሰጠን በዚህ ምክንያት ነው። በአሁኑ ጊዜ ‘ይህ ልባም ባሪያ’ በይሖዋ ምሥክሮች የአስተዳደር አካል የተወከለ ሲሆን “ብርሃን አብሪዎች” የተባለው የወረዳ ስብሰባ የተዘጋጀው በዚህ አካል መመሪያ መሠረት ነው።
የዚህ ስብሰባ ዋና ዓላማ ጳውሎስ በፊልጵስዩስ 2:15 ላይ እንደገለጸው የይሖዋ ሕዝቦች በበለጠ ሁኔታ ብርሃን አብሪዎች እንዲሆኑ ለመርዳት ታስቦ ነው። በዚህ ጥቅስ ላይ ክርስቲያኖች “በዓለም ላይ ብርሃን አብሪዎች” እንዲሆኑ ተመክረዋል።—ማቴዎስ 5:14, 16
በዩናይትድ ስቴትስ ይህ የብርሃን አብሪዎች የወረዳ ስብሰባ የሚጀምረው ዓርብ ሰኔ 5 ቀን ልክ ከጠዋቱ 4:20 ላይ ነው። የመግቢያው ሙዚቃ በዕለቱ የሚደረጉትን መንፈሳዊ ዝግጅቶች ሁሉም በአንድ ልብና ሐሳብ እንዲከታተሉ ይረዳቸዋል። እያንዳንዱ ቀን ለራሱ የተመደበለት አጠቃላይ መልዕክት ሲኖረው ዓርብ ዕለት ለሚቀርቡት ንግግሮች አጠቃላይ መልእክቱ “ብርሃንህንና እውነትህን ላክ” የሚል ይሆናል።—መዝሙር 43:3
የዓርብ ጠዋት ፕሮግራም ቁልፍ ንግግር በሆነው “ብርሃን አብሪዎች—ለምን ዓላማ?” በሚለው ይጀምራል። እርግጥ ነው የክርስቲያኖች ብርሃን አብሪነት በግል ጥቅም ፍለጋ ወይም በራስ ወዳድነት ላይ የተመሠረተ አይደለም። ይልቁንም ዋነኛ ብርሃን አብሪ የነበረው ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ምድር የመጣው እውነትን ለመመስከርና የፈጣሪን ስም ከፍ ከፍ ለማድረግ እንደሆነ ሁሉ ክርስቲያኖችም የእርሱን አርአያ ይከተላሉ።
ኢየሱስ “በዓለም ሳለሁ የዓለም ብርሃን ነኝ” በማለት በትክክል ተናግሯል። (ዮሐንስ 9:5) እዚህ ላይ ልንረዳ እንደምንችለው ኢየሱስ የእርሱን ፈለግ እንድንከተል ምሳሌውን ትቶልናል። (1 ጴጥሮስ 2:21) በመጀመሪያው ቀን ከሰዓት በኋላ በሚከናወነው ፕሮግራም ላይ የወጣቶችን ትኩረት የሚስብ የንጉሥ ኢዮስያስን ታሪክ አስመልክቶ የሚቀርብ የመጽሐፍ ቅዱስ ድራማና ንግግር ይኖራል።
የቅዳሜ ቀን አጠቃላይ መልእክት “የዓለም ብርሃን ናችሁ . . . ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ” የሚል ይሆናል። (ማቴዎስ 5:14, 16) በጠዋቱ ፕሮግራም ላይ “ብርሃናችሁ በሰው ፊት ይብራ” በሚል ርዕስ በተከታታይ ተናጋሪዎች የሚሸፈን ንግግር ይቀርባል። ራሳቸውን ለይሖዋ የወሰኑ ውሳኔያቸውን በውኃ ጥምቀት እንዲያሳዩም አጋጣሚ ያገኛሉ። ከሰዓት በኋላ ያለው በተከታታይ ተናጋሪዎች የሚሸፈን ንግግር ስሜትን የሚያነቃቃ ሲሆን ርዕሱም “በኢየሱስ ክርስቶስ መገኘትና መገለጥ ላይ የሚያብራራ የዕውቀት ብርሃን ማብራት” የሚል ይሆናል።
ለወረዳው ስብሰባ ሦስተኛ እና የመጨረሻ ቀን በሆነው እሁድ ዕለት የተመረጠው አጠቃላይ መልዕክት “እንደ ብርሃን ልጆች ተመላለሱ” የሚል ነው። (ኤፌሶን 5:8) የጠዋቱ ፕሮግራም “በክርስቲያን ቤተሰብ ውስጥ እርስ በርስ መረዳዳት” በሚል ርዕስ በተከታታይ ተናጋሪዎች የሚሸፈን ስለ ቤተሰብ ግዴታዎች የሚያወሳ ንግግር ይቀርባል። እንዲሁም ለአምላክና ለኢየሱስ መገዛት ምን ማለት እንደሆነ የሚገልጽ ንግግር ይኖራል።
የወረዳው ስብሰባ እሁድ ዕለት ከሰዓት በኋላ “የዓለም ብርሃን የሆነውን ተከተሉት” የሚል ርዕስ በሚኖረው በሕዝብ ንግግር ወደ ድምዳሜው ይደርሳል። ይህ ንግግር የዮሐንስ 1:1-16ን መልዕክት የሚያብራራ ሲሆን የመጽሐፍ ቅዱስ ዕውቀት ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ በማስረዳት ኢየሱስ ክርስቶስ የዓለም ብርሃን መሆኑን የሚያጎላ ይሆናል። የወረዳው ስብሰባ “በብርሃን ውስጥ የምትጓዙ ሁኑ” ብሎ አጥብቆ በሚመክር ንግግር ይዘጋል።
ይሖዋ በሚታየው ድርጅቱ አማካኝነት ላዘጋጀው ለዚህ መንፈሳዊ ድግስ አድናቆታችሁን አሳዩ። ፕሮግራሙ ዐርብ ጠዋት በመዝሙር ከሚከፈትበት ቀን ጀምሮ እስከ እሁድ ማታ በጸሎት እስከሚደመደምበት ቀን ድረስ ተገኙ። ከመድረኩ ላይ የሚሰጡትን ትምህርቶች ሁሉ ልብ ብላችሁ ተከታተሉ። በሚቀርቡት ትምህርቶች ላይ ትኩረት እንድትሰጡ እና ለወደፊቱ ጊዜ ለማስታወስ እንዲረዳችሁ ማስታወሻዎችን ያዙ። በመጨረሻም በፈቃደኝነት አገልግሎት ለማበርከት ዕቅድ አውጡ። በዚህም መንገድ መቀበል የሚያመጣውን ደስታ ብቻ ሳይሆን በመስጠት የሚገኘውን የበለጠውን ደስታ ታገኛላችሁ።—ሥራ 20:35