የጊልያድ ምሩቃን የተሰጣቸውን የሚሲዮናዊነት አገልግሎት ስጦታ ተቀበሉ
የመጋቢት 1, 1992 የመጠበቂያ ግንብ የጊልያድ ትምህርት ቤት 92ኛ ኮርስ 22 ምሩቃን አንድ ስጦታ ተቀብለዋል። ይህም ስጦታ የሚሲዮናዊነት አገልግሎት ነው። የአስተዳደር አካል አባል የሆነው ሎይድ ባሪ ለተማሪዎቹ ንግግር ሲያደርግ “ይህንን አስደናቂ ስጦታ በታላቅ ደስታ እንድትቀበሉና ለሌሎች ሰዎችም ደስታ ለማስገኘት እንድትጠቀሙበት እንመኛለን” ብሎአል።
ለምረቃው ፕሮግራም በጀርሲ ከተማ ውስጥ በሚገኘው በኒው ጀርሲ መሰብሰቢያ አዳራሽ ውስጥ 4,662 የሚያክሉ የተጋበዙ እንግዶችና የቤቴል ቤተሰብ አባሎች ተገኝተው ነበር። በተጨማሪም በኒውዮርክ ብሩክሊን፣ በዎልኪል እና በፓተርሰን በሚገኙት የመጠበቂያ ግንብ ማህበር መሥሪያ ቤቶች የሚሠሩ 970 ሰዎች በስልክ መስመሮች አማካኝነት በቀጥታ ከአዳራሹ የሚተላለፈውን ፕሮግራም ይከታተሉ ነበር። ተመራቂዎቹ የሚሲዮናዊነት አገልግሎትን ስጦታ አክብረው እንዲይዙና በጥበብ እንዲጠቀሙበት የሚረዱአቸው የመሰነባበቻ ምክሮች ሲሰጡአቸው በፕሮግራሙ ላይ የተገኙ ሁሉ በጥሞና አዳምጠዋል።
ፕሮግራሙ የተከፈተው “እርስ በርሳችሁ ተቀባበሉ” የሚለውን መዝሙር ሞቅ ባለ ስሜት በመዘመር ነበር። ቀጥሎም 98 ዓመት ዕድሜ የሞላው የጊልያድ ትምህርት ቤት ፕሬዚደንት ደብልዩ ፍራንዝ ባቀረበው ልብ የሚመስጥ ጸሎት በፕሮግራሙ ላይ የተገኙት ሁሉ ስሜታቸው ተነክቶአል። ከዚያም የአስተዳደር አካል አባልና የፕሮግራሙ ሊቀ መንበር የሆነው ካሪ ባርበር ለምረቃው ፕሮግራም የመጡትን ሁሉ እንኳን ደህና መጣችሁ ካለ በኋላ “የአሁኑን ያህል የጊልያድ ሚስዮናውያን አስፈላጊ የሆኑበት ጊዜ የለም” ብሎአል። ከራሱ አጭር ንግግር በኋላ ቀጥለው የሚቀርቡትን አጫጭር ምክር አዘል ንግግሮች አስተዋወቀ።
በመጀመሪያ “የአትክልት ሥፍራችሁን ተንከባከቡ” የሚል አጠቃላይ መልዕክት የያዘውን ንግግር ያቀረበው የቤቴል ኮሚቴ አባል የሆነው ከርቲስ ጆንሰን ነበር። ወንድም ጆንሰን እንደገለጸው እነዚህ አዳዲስ ሚስዮናውያን ወደ ምድብ ቦታቸው ሲሄዱ እያንዳንዳቸው የሚንከባከቡት መንፈሳዊ የአትክልት ሥፍራ ይኖራቸዋል። (1 ቆሮንቶስ 3:9) በዓለም ዙሪያ የሚገኙት የይሖዋ ሕዝቦች ጽድቅና ውዳሴ የሚያፈሩ መንፈሳዊ አትክልቶች ናቸው። (ኢሳይያስ 61:11) ‘በሚሲዮናዊ የአገልግሎት ምድባችሁ የምታገኙት ውጤት በአብዛኛው የሚመካው ለመንፈሳዊ አትክልታችሁ በምታደርጉት እንክብካቤ ላይ ነው።’ ግን መንፈሳዊ አትክልታቸውን በሚገባ እንዲንከባከቡ የሚረዳቸው ነገር ምንድን ነው? ‘ትክክለኛ ሥራዎችን ለመኮትኮት ቁርጥ ውሳኔ ካደረጋችሁ፣ በጸሎት አማካኝነት ከይሖዋ ጋር ተቀራርባችሁ ከኖራችሁና ከጸሎታችሁ ጋር የሚስማማ ሥራ ከሠራችሁ ይሖዋ የመንፈሳዊ አትክልታችሁ አጥር ሊሆንላችሁ ይችላል’ አላቸው።
ቀጥሎም ሎይድ ባሪ “ሁልጊዜ በጌታ ደስ ይበላችሁ” የሚል አጠቃላይ መልዕክት የያዘ ንግግር አቀረበ። (ፊልጵስዩስ 4:4) በጃፓን አገር ከ25 ዓመታት ለሚበልጥ ጊዜ ሚሲዮናዊ ሆኖ በማገልገል ያገኘውን ተሞክሮ መሠረት በማድረግ ተመራቂዎቹ በተሰጣቸው ሚሲዮናዊ አገልግሎት እንዲደሰቱ ስለሚረዱአቸው አንዳንድ ተግባራዊ ሐሳቦች ተናግሮአል። “ከአምላክ አገልግሎት የምታገኙት ደስታ ብዙ ጭንቀቶችንና ምናልባትም የሚያጋጥማችሁን አካላዊ ሕመም እንኳን እንድትወጡ ይረዳችኋል” ብሎአል። (ምሳሌ 17:22) እስከ ዛሬ ድረስ ከገጠሟቸው የተለዩ ሁኔታዎችና ችግሮች ሊያጋጥሟቸው እንደሚችሉ ተመራቂዎቹን አሳሰባቸው። አዲስ ቋንቋ መማር ሊኖርባቸው ይችላል። “ቋንቋውን ለማጥናት ጠንክራችሁ መሥራት ይኖርባችኋል። ይሁን እንጂ ከሰዎች ጋር በራሳቸው ቋንቋ እንደልብ ለመነጋገር መቻላችሁ ደስታችሁን ይጨምርላችኋል።”
ቀጥሎ “ሽልማቱን ትኩር ብላችሁ ተመልከቱ” በሚል አጠቃላይ መልዕክት ንግግር ያደረገው የፋብሪካ ኮሚቴ አባል የሆነው ኤልዶር ቲም ነው። ሽልማቱ ምንድን ነው? የዘላለም ሕይወት ነው! ይህን ለማግኘት ትኩረታችንን በሽልማቱ ላይ ማድረግ አለብን። ተናጋሪው በመጀመሪያው መቶ ዘመን በሚደረጉት የሩጫ ውድድሮችና ክርስቲያኖች በሚያደርጉት የሕይወት ሩጫ መካከል ያለውን ተመሣሣይነትና ልዩነት ገለጸ። ክርስቲያኖች ልክ እንደ ሯጮቹ ራሳቸውን በሚገባ ማሠልጠን፣ ሕግጋትን መጠበቅ እና የማይመቹ ሸክሞችን አውልቀው መጣል አለባቸው። ይሁን እንጂ ክርስቲያኖች የሚሮጡት ዕድሜ ልካቸውን በመሆኑና የሚያገኙትም ሽልማት የዘላለም ሕይወት በመሆኑ ከስፖርተኞች ይለያሉ። አሸናፊ ሆኖ ሽልማቱን የሚያገኘው አንድ ሰው ብቻ ሳይሆን የሕይወትን ሩጫ እስከ መጨረሻው የሮጡ ሁሉ ናቸው። “የሕይወት ሽልማት ለማግኘት ሽልማቱን ከሚሰጠው ከይሖዋ ጋር ተስማምተን መኖር ይኖርብናል። ከይሖዋ ጋር ተስማምተን ለመኖር ደግሞ ከወንድሞቻችን ጋር ተስማምተን መኖር ይገባናል” በማለት ወንድም ቲም ንግግሩን ደመደመ።
ቀጥሎ አጠቃላይ መልዕክቱ “ቅዱሳን ጽሑፎች በሚሰጡት መጽናናት ተስፋ አለን” የሚል ንግግር ያደረገው የአስተዳደር አካል አባል የሆነው ሚልተን ሔንሸል ነው። (ሮሜ 15:4) ተናጋሪው ንግግሩን ሲጀምር ‘ባለፉት አምስት ወራት መጽሐፍ ቅዱስን በትጋት ስታጠኑ ቆይታችኋል። ከይሖዋ ጋር ትልቅ የመቀራረብ ሁኔታ ገንብታችኋል። ጠንካራ ተስፋ አላችሁ። ወደ ምድብ ቦታችሁ በምትሄዱበት ጊዜ ተስፋችሁ ይህን ያህል ጠንካራ የሆነበትን ምክንያት አስታውሱ። ጠንካራ ተስፋ የኖራችሁ ከቅዱሳን ጽሑፎች ጋር ተቀራርባችሁ ስለምትኖሩ ነው።’ ተናጋሪው መጽሐፍ ቅዱስ የሚሠጠውን ተስፋ በምሳሌ ለማሣየት በመሳፍንት ምዕራፍ 6 እስከ 8 ድረስ የሚገኘውንና የጌድዮን እስራኤላውያንን ከምድያማውያን ጭቆና ለማውጣት እንደተሾመ የሚናገረውን ታሪክ ገለጸ። ታሪኩንና ታሪኩ በጊዜያችን ያለውን ትርጉም ከገለጸ በኋላ እንዲህ አለ፦ “ከቅዱሳን ጽሑፎች ጋር ተቀራርባችሁ ለመኖርና እንደነዚህ ስለመሳሰሉት ነገሮች ለማሰብ የሚያስችላችሁን አጋጣሚ ስታገኙ ሰውነታችሁ ይታደሳል። ድፍረትም ታገኛላችሁ።”
ሁለቱ የትምህርት ቤቱ ዋነኛ አስተማሪዎች ምን ዓይነት የመሠነባበቻ ምክር እንደሚሰጡ ሁሉም በጉጉት ይጠባበቁ ነበር። በመጀመሪያ ጃክ ሬድፎርድ “ትክክለኛውን ነገር ሥሩ” የሚል አጠቃላይ መልዕክት የያዘ ንግግር አቀረበ። ተመራቂዎቹንም ሲያሳስባቸው “በጊልያድ በቅዱሳን ጽሑፎች መሠረት ትክክለኛ ስለሆኑ ነገሮች የጠለቀ ሥልጠና አግኝታችኋል። አሁን ደግሞ ከፍተኛ ትዕግስት ወደሚጠይቀው የሚሲዮናዊነት ምድባችሁ ትሄዳላችሁ። አልፎ አልፎ በሥራችሁ ላይ ችግር ሊያጋጥማችሁ እንደሚችል እናውቃለን። ሆኖም የተለያዩ ችግሮችና የስሜት መለዋወጥ ቢያጋጥማችሁም ትክክለኛውን ነገር እንደምታደርጉ እናውቃለን።” በዚህ ረገድ ምን ነገሮች ሊረዱአቸው ይችላሉ? በመጀመሪያ ደረጃ ለሌሎች ሰዎች ትክክለኛ አመለካከት ሊኖራቸው ያስፈልጋል። ቀጥሎም ተናጋሪው ‘ከአለፍጽምና ፍጽምናን አትጠብቁ’ አላቸው። በተጨማሪም ፈታኝ ለሆኑ ሁኔታዎች ጥሩ አመለካከት መያዝ ይጠቅማል። ‘ሁላችንም ብንሆን በሕይወታችን ውስጥ የምንደሰትበትና የምንከፋበት ጊዜ አለ። ደስ የምትሰኙባቸው ጊዜያት ችግር አይፈጥሩባችሁም። በሚሲዮናዊ አገልግሎታችሁ ጸንታችሁ ለመቆየት መቻላችሁ የሚወሰነው አሳዛኝ ሁኔታዎችን ለመቋቋም በሚኖራችሁ ችሎታ ላይ ነው።’—ያዕቆብ 1:2-4
የትምህርት ቤቱ ሬጂስትራር የሆነው ዩሊሰስ ግላስ የሰጠው ንግግር አጠቃላይ መልእክት “መጪው ጊዜ ምን ተስፋ ይዞአል?” የሚል ነበር። በአባታዊ አነጋገሩ ተመራቂዎቹ ተስፋቸው ብሩሕ እንደሆነ እንዲኖር አበረታታቸው። (ምሳሌ 13:12) ‘ተስፋ ማጣት ሲጀምር እምብዛም አይታወቅም’ በማለት ከገለጸ በኋላ ‘ከአምላክ ጋር ያለንን ዝምድና ከሚመለከቱ ጉዳዮች ይልቅ በራሳችን ጉዳዮች እንዳንጣበብ የሚያደርጉ ሁኔታዎች ሊፈጠሩ ይችላሉ። ልንታመም እንችላለን። ወይም ሌሎች የበደሉን ሆኖ ይሰማን ይሆናል። አንዳንዶች እኛ ካለን የበለጠ ቁሳዊ ነገር ይኖራቸውና ወይም በአገልግሎት ከእኛ የበለጠ ውጤት ያገኙና ልንቀናባቸው እንችላለን። እንደነዚህ ያሉት ስሜቶች እንዲያሸንፉን ከፈቀድን ሳናውቀው የመንግስቱ ተስፋ ከልባችንና ከአዕምሮአችን ይደበዝዝና ለሕይወት በምናደርገው ሩጫ ላይ የሚገጥሙንን ችግሮች መወጣት እናቆም ይሆናል።’ በዚህ ጊዜ ምን ሊደረግ ይችላል? ‘ተስፋችን እንደገና እንዲያንሰራራ ከፈለግን አዎንታዊ የሆኑ እርምጃዎችን መውሰድ አለብን። አዕምሮአችንና ልባችንን በአምላክ እርግጠኛ ተስፋዎች በመሙላት አስተሳሰባችንን በጠቅላላ ወደ አምላክ መንግሥት ማዞር ይኖርብናል። ከይሖዋ ጋር የነበረንን የንግግር ግንኙነት ማደስ ይኖርብናል። ይህም ደስታ እንደሚያስገኝልን የተረጋገጠ ነው።’
የምረቃውን ንግግር ያደረገው የአስተዳደር አካል አባል የሆነው ካርል ክላይን ነበር። ያቀረበው ንግግር አጠቃላይ መልዕክት “ትሁት ልንሆን የሚገባን ለምንድን ነው?” የሚል ነበር። ለዚህ ጥያቄ መልሱ ምንድን ነው? በንግግሩ መክፈቻ ላይ በተናገራቸው ቃላት ‘ትሁት መሆን ትክክለኛ፣ ቅን፣ ጥበብና ፍቅር የሞላበት ማለት ነው ብሎ ከገለጸ በኋላ ልንመስላቸው የሚገቡንን አራት የትህትና ምሳሌዎች ሲዘረዝር አድማጮቹ በጉጉት ያዳምጡ ነበር። (1)ይሖዋ አምላክ ከአብርሃምና ከሙሴ ባደረገው ግንኙነት ያሳየው ትህትና (ዘፍጥረት 18:22-33፤ ዘኁልቁ 14:11-21፤ ኤፌሶን 5:1)፤ (2) ኢየሱስ ክርስቶስ እስከ ሞት ድረስ “ራሱን አዋረደ” (ፊልጵስዩስ 2:5-8፤ 1 ጴጥሮስ 2:21)፤ (3) ሐዋርያው ጳውሎስ ለጌታ በትልቅ ትህትና ይገዛ ነበር። (ሥራ 20:18, 19፤ 1 ቆሮንቶስ 11:1)፤ (4) ‘በመካከላችን ዋነኞች ከሆኑት’ መካከል አንዱ የነበረው የመጀመሪያው የማህበሩ ፕሬዚዳንት ወንድም ራስል አንድ ጊዜ ሲጽፍ እንዲህ ብሎ ነበር፦ “ጌታ ፈቃዱ ሆኖ በጣም ዝቅተኛ በሆነው ችሎታችን እንድንሠራ የሰጠን ሥራ መልሶ ግንባታ፣ ማስተካከልና ማስማማት የሚጠይቅ እንጂ ከራሳችን አመንጭተን የምንሠራው አይደለም” ብሎአል። (ዕብራውያን 13:7) ወንድም ክላይን በመቀጠል ትሁት የምንሆንባቸውን ሌሎች ምክንያቶች ዘርዝሮአል። በእርግጥ ተመራቂዎቹ ትሁቶች እንዲሆኑ የተሰጣቸውን ምክር ቢከተሉ በሚሲዮናዊነት አገልግሎት ስጦታቸው በጥበብ ለመጠቀም ይችላሉ።
ከእነዚህ ንግግሮች በኋላ ሊቀመንበሩ ከተለያዩ አገሮች የተላኩትን የተለያዩ የሰላምታ ደብዳቤዎች አነበበ። አሁን ተመራቂዎቹ ዲፕሎማቸውን የሚቀበሉበት ሰዓት ደረሰ። ተመራቂዎቹ ከሰባት የተለያዩ አገሮች የመጡ ሲሆን እነዚህም አገሮች ካናዳ፣ ፊንላንድ፣ ፈረንሳይ፣ ሞሪታኒያ፣ ኔዘርላንድ፣ ስዊድንና ዩናይትድ ስቴትስ ናቸው። የተመደቡባቸው አገሮች ግን 11 ናቸው። እነርሱም ቦሊቪያ፣ ኢስቶኒያ፣ ግሬናዳ፣ ጓቲማላ፣ ሆንዱራስ፣ ሀንጋሪያ፣ ሞሪታኒያ፣ ፔሩ፣ ቶጎ፣ ቱርክ እና ቬንዙዌላ ናቸው።
የጥቂት ጊዜ እረፍት ከተደረገ በኋላ የከሰዓት በኋላው ፕሮግራም የአገልግሎት ክፍል ኮሚቴ አባል በሆነው በጆኤል አዳምስ አጠር ያለ የመጠበቂያ ግንብ ጥናት ተመራ። ቀጥሎም ተመራቂዎቹ በትምህርት ቤቱ በቆዩባቸው ጊዜያት በመስክ አገልግሎት ያጋጠሙአቸውን አንዳንድ ተሞክሮዎች ተናገሩ። በመጨረሻም መላውን ተሰብሳቢና ተመራቂዎቹንም ጭምር የሚያነቃቃ “ቲኦክራቲካዊ ሥርዓት የምናከብረው ለምንድን ነው?” የሚል ድራማ ቀረበ።
በእርግጥም እነዚህ ተመራቂዎች ወደ ተመደቡባቸው አገሮች ከመሄዳቸው በፊት የሚሲዮናዊነት አገልግሎት ስጦታቸውን ለራሳቸው ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም ጭምር ደስታ በሚያመጣ መንገድ እንዲጠቀሙ የሚረዳቸውን ምክርና ማበረታቻ አግኝተዋል።
[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሠንጠረዥ]
የክፍሉ ስታትስቲክስ
የተወከሉት አገሮች ቁጥር፦ 7
የተመደቡባቸው አገሮች ቁጥር፦ 11
ጠቅላላ የተማሪዎች ቁጥር፦ 22
አማካይ ዕድሜ፦ 33.4
በእውነት ውስጥ የቆዩባቸው አማካይ ዓመታት፦ 16.7
በሙሉ ጊዜ አገልግሎት የቆዩባቸው አማካይ ዓመታት፦ 11.8
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስ የጊልያድ ትምህርት ቤት ተመራቂዎች 98ኛ ክፍል
ከዚህ በታች ባለው ዝርዝር ተርታዎች ቁጥር የተሰጣቸው ከፊት ወደ ኋላ ሲሆን የስም ዝርዝሮቹ ደግሞ በእያንዳንዱ ተርታ ከግራ ወደ ቀኝ በዝርዝር ተጽፈዋል።
(1) ቻን ቺን ዋህ ኤም፤ ባውንቼክስ ኤን፤ ቻፕማን ቢ፤ ኦስትበርግ ኤ፤ ኮል ኤል፤ ጃክሰን ኬ፤ ሚርዊክ ኤ። (2) ስሚዝ ጄ፤ ዎሊን ኬ፤ ቻፕማን አር፤ ጋቦር ኤን፤ ቻን ቺን ዋህ ጄ፤ ስሚዝ ሲ፤ ኤድቪክ ኤል፤ (3) ባውንቼክስ ኢ፤ ኦስትበርግ ኤስ፤ ኮል ኬ፤ ጃክሰን አር፤ ጋቦር ኤስ፤ ኤድቪክ ቪ፤ ሚርዊክ አር፤ ዎሊን ጂ።