የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w92 7/1 ገጽ 14-19
  • ሽማግሌዎች፣ በጽድቅ ፍረዱ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ሽማግሌዎች፣ በጽድቅ ፍረዱ
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1992
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ክርስቶስ—ጥሩ ምሳሌ የሚሆን ፈራጅ
  • ምድራዊ ፈራጆች
  • ‘በፍርሃት የሚመላለሱ’ ፈራጆች
  • የሙሉ ጊዜ እረኞች
  • መሐሪ እረኞችና ፈራጆች ሆኖ ማገልገል
  • የፍርድ ጉዳዮችን በሚያዳምጡበት ጊዜ ሊኖራቸው የሚገባው ተገቢ አመለካከት
  • የፍርድ ጉዳዮችን የሚያዳምጡበት ዓላማ
  • ይሖዋ፣ የማያዳላው “የምድር ሁሉ ፈራጅ”
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1992
  • የጉባኤውን ሰላምና ንጽሕና መጠበቅ
    የይሖዋን ፈቃድ ለማድረግ የተደራጀ ሕዝብ
  • ለኃጢአተኞች ፍቅርና ምሕረት ማሳየት
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2024
  • “በአደራ የተሰጣችሁን የአምላክ መንጋ ጠብቁ”
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2011
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1992
w92 7/1 ገጽ 14-19

ሽማግሌዎች፣ በጽድቅ ፍረዱ

“የወንድሞቻችሁን ነገር ስትሰሙ . . . በጽድቅ ፍረዱ።”—ዘዳግም 1:16

1. በፍርድ ጉዳይ ምን የውክልና ሥልጣን ተሰጥቶአል? ይህስ ፈራጆች ሆነው ለሚያገለግሉ ሰዎች ምን ትርጉም ይኖረዋል?

ይሖዋ የመጨረሻው ከፍተኛ ፈራጅ እንደመሆኑ መጠን ለልጁ የፈራጅነት ሥልጣን ሰጥቶታል። (ዮሐንስ 5:27) ክርስቶስም በተራው የክርስቲያን ጉባኤ ራስ እንደመሆኑ መጠን የታማኝና ልባም ባሪያን ክፍልና የአስተዳደር አካሉን በመጠቀም አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ በፈራጅነት የሚያገለግሉ ሽማግሌዎችን በጉባኤዎች ውስጥ ይሾማል። (ማቴዎስ 24:45-47፤ 1 ቆሮንቶስ 5:12, 13፤ ቲቶ 1:5, 9) እነዚህ ሽማግሌዎች በምትክነት የሚያገለግሉ ፈራጆች እንደመሆናቸው መጠን ሰማያዊ ዳኞች የሆኑትን የይሖዋንና የክርስቶስ ኢየሱስን ምሳሌ አጥብቀው የመከተል ግዴታ አለባቸው።

ክርስቶስ—ጥሩ ምሳሌ የሚሆን ፈራጅ

2, 3. (ሀ) ክርስቶስ ፈራጅ ለመሆን የሚያስችሉ ብቃቶች እንዳሉት የትኛው መሲሐዊ ትንቢት ያሳያል? (ለ) በተለይ ልብ ሊባሉ የሚገቡት የትኞቹ ነጥቦች ናቸው?

2 ክርስቶስ ፈራጅ እንደሚሆን “የ[ይሖዋ (አዓት)] መንፈስ፣ የጥበብና የማስተዋል መንፈስ፣ የምክርና የኃይል መንፈስ፣ የእውቀትና [ይሖዋን አዓት] የመፍራት መንፈስ ያርፍበታል። [ይሖዋን አዓት] በመፍራት ደስታውን ያያል። ዓይኑም እንደምታይ አይፈርድም፣ ጆሮውም እንደምትሰማ አይበይንም፤ ነገር ግን ለድሆች በጽድቅ ይፈርዳል፣ ለምድርም የዋሆች በቅንነት ይበይናል” የሚል ትንቢት ተጽፎአል።—ኢሳይያስ 11:2-4

3 በዚህ ትንቢት ውስጥ የተጠቀሱትን ክርስቶስ በምድር ‘በሚኖሩት ሕዝቦች ላይ በጽድቅ እንዲፈርድ’ የሚያስችሉ ብቃቶች ልብ ብላችሁ አስተውሉ። (ሥራ 17:31) ኢየሱስ የሚፈርደው በይሖዋ መንፈስ፣ በመለኮታዊ ጥበብ፣ በማስተዋል፣ በምክርና በእውቀት ነው። በተጨማሪም ይሖዋን በመፍራት የሚፈርድ መሆኑን አስተውሉ። ስለዚህ የክርስቶስ የፍርድ ወንበር የአምላክን የፍርድ ወንበር ይወክላል ማለት ነው። (2 ቆሮንቶስ 5:10፤ ሮሜ 14:10) ስለ ነገሮች የሚሰጠው ፍርድ ከአምላክ ፍርድ ጋር የሚስማማ እንዲሆን በጥንቃቄ ይፈርዳል። (ዮሐንስ 8:16) ውጪያዊውን ሁኔታ ብቻ ተመልክቶ ወይም የአሉባልታ ወሬ ብቻ አዳምጦ አይፈርድም። ከዚህ ይልቅ ለድሆችና ለየዋሆች በቅንነት ይፈርዳል። እንዴት ያለ አስደናቂ ፈራጅ ነው! በዛሬው ጊዜ በፈራጅነት እንዲያገለግሉ ለሚጠየቁ ፍጹማን ያልሆኑ ሰዎች እርሱ በጣም ጥሩ አርዓያ ይሆናል።

ምድራዊ ፈራጆች

4. (ሀ) በሺህ ዓመቱ የክርስቶስ ግዛት ዘመን 144,000ዎቹ ከሚኖሩአቸው ሥራዎች መካከል አንዱ ምን ይሆናል? (ለ) አንዳንድ የተቀቡ ክርስቲያኖች ገና በምድር ላይ እያሉም ፈራጆች ሆነው እንደሚሾሙ የትኛው ትንቢት ያሳያል?

4 ከ12ቱ ሐዋርያት በመጀመር የተመረጡ አነስተኛ ቁጥር ያላቸው የተቀቡ ክርስቲያኖች በሺህ ዓመቱ ግዛት ውስጥ ከክርስቶስ ጋር ተባባሪ ፈራጆች እንደሚሆኑ ቅዱሳን ጽሑፎች ያሳያሉ። (ሉቃስ 22:28-30፤ 1 ቆሮንቶስ 6:2፤ ራእይ 20:4) ከ1918-19 ባሉት ጊዜያት የተቀቡት የመንፈሳዊ እስራኤል ቀሪ አባሎች ራሳቸው ፍርድ ከተሰጣቸው በኋላ እንደገና ተቋቁመዋል። (ሚልክያስ 3:2-4) ይህን የመንፈሳዊ እስራኤላውያን መልሶ መቋቋም በሚመለከት የሚከተለው ትንቢት ተነግሮ ነበር፦ “ፈራጆችሽንም እንደ ቀድሞ አማካሪዎችሽንም እንደ መጀመሪያው ጊዜ መልሼ አስነሣለሁ።” (ኢሳይያስ 1:26) ስለዚህ ይሖዋ የሥጋዊ እስራኤላውያን ብሔር በተቋቋመበት ጊዜ እንዳደረገው ሁሉ ለቅቡዓን ቀሪዎችም ጻድቅ ፈራጆች እና አማካሪዎች ሰጥቶአቸው ነበር።

5. (ሀ) መንፈሳዊ እስራኤላውያን እንደገና ከተቋቋሙ በኋላ “ፈራጆች” እንዲሆኑ የተሾሙት እነማን ናቸው? እነርሱንስ የራእይ መጽሐፍ እንዴት ይገልጻቸዋል? (ለ) በዛሬው ጊዜ ቅቡዓን የበላይ ተመልካቾች በፍርድ ሥራዎች ረገድ በእነማን ይታገዛሉ? እነርሱስ ጥሩ ፈራጆች እንዲሆኑ እንዴት ባለ መንገድ በመሰልጠን ላይ ናቸው?

5 በመጀመሪያ ደረጃ “ፈራጆች” እንዲሆኑ የተሾሙት በሙሉ የተቀቡና ሽማግሌ የሆኑ ‘አስተዋይ ወንዶች’ ነበሩ። (1 ቆሮንቶስ 6:4, 5) ታማኝ የሆኑና የጉባኤውን ከበሬታ ያተረፉ ቅቡዓን የበላይ ተመልካቾች በኢየሱስ ቀን እጅ ውስጥ ማለትም በእርሱ ቁጥጥርና መሪነት ሥር ያሉ መሆናቸው በራእይ መጽሐፍ ውስጥ ተገልጾአል። (ራእይ 1:16, 20፤ 2:1) ቅቡዓኑ ከ1935 ጀምሮ ቁጥራቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የሚሄደውንና “ታላቁን መከራ” አልፈው በገነቲቱ ምድር ለዘላለም ለመኖር ተስፋ የሚያደርጉትን የ“እጅግ ብዙ ሰዎች”ን ድጋፍ በማግኘት ላይ ናቸው። (ራእይ 7:9, 10, 14-17) “የበጉ ሰርግ” እየቀረበ በመጣ መጠን በምድር ዙሪያ በሚገኙት ከ66,000 በላይ በሚሆኑት የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች ውስጥ ሽማግሌዎችና ፈራጆች ሆነው እንዲያገለግሉ በቅቡዓኑ የአስተዳደር አካል የሚሾሙት የእጅግ ብዙ ሰዎች አባላት ቁጥር እየጨመረ ሄዶአል።a (ራእይ 19:7-9) እነዚህ ሰዎች በልዩ ትምህርት ቤቶች አማካኝነት “በአዲሱ ምድር” ኅብረተሰብ ውስጥ ኃላፊነት ለመያዝ የሚያስችላቸውን ሥልጠና በማግኘት ላይ ናቸው። (2 ጴጥሮስ 3:13) በ1991 ማለቂያ ላይ በብዙ አገሮች ተደርጎ የነበረው የመንግሥት አገልግሎት ትምህርት ቤት ትልቅ ትኩረት የሰጠው የፍርድ ጉዳዮችን በተገቢ ሁኔታ በመያዝ ጉዳይ ላይ ነበር። በፈራጅነት የሚያገለግሉ ሽማግሌዎች እውነተኛና ጻድቅ ፈራጅ የሆኑትን ይሖዋንና ኢየሱስ ክርስቶስን የመምሰል ግዴታ አለባቸው።—ዮሐንስ 5:30፤ 8:16፤ ራእይ 19:1, 2

‘በፍርሃት የሚመላለሱ’ ፈራጆች

6. በፍርድ ኮሚቴዎች ውስጥ የሚያገለግሉ ሽማግሌዎች ‘በፍርሃት መመላለስ’ የሚኖርባቸው ለምንድን ነው?

6 ክርስቶስ እንኳን በይሖዋ ፍርሃትና በይሖዋ መንፈስ እርዳታ የሚፈርድ ከሆነ፣ ፍጹማን ያልሆኑ ሽማግሌዎች እንዴት አብልጠው በይሖዋ ፍርሃትና በይሖዋ መንፈስ መፍረድ ይገባቸው! በፍርድ ኮሚቴ እንዲያገለግሉ በሚመደቡበት ጊዜ በጽድቅ ለመፍረድ እንዲችሉ ይረዳቸው ዘንድ ‘ሳያደላ የሚፈርደውን አባት’ በመጥራት ‘ፍርሃት ማሳየት’ ይኖርባቸዋል። (1 ጴጥሮስ 1:17) ሽማግሌዎች የሚሰጡት ውሳኔ የሰዎችን ሕይወት የሚመለከት እንደሆነና ስለ እነዚህም ሰዎች ‘ነፍስ ስሌትን እንደሚሰጡ’ ማስታወስ ይኖርባቸዋል። (ዕብራውያን 13:17) በዚህም ምክንያት ሊወገዱ የሚችሉ የፍርድ ስህተቶችን ቢፈጽሙ በይሖዋ ዘንድ ይጠየቁበታል። ጄ. ኤች. ኤ ኢብራርድ በዕብራውያን 13:17 ላይ በሰጡት ሐሳብ እንዲህ ብለዋል፦ “እረኛው በሥሩ ያሉትን ነፍሳት በሙሉ የመጠበቅ እና የመንከባከብ ኃላፊነት አለበት። . . . በተጨማሪም ስለ ሁሉም በጎች በራሱ ጥፋት ስለጠፉትም ጭምር ስሌት ያቀርባል። ይህ ከባድ ቃል ነው። እያንዳንዱ የቃሉ አገልጋይ ይህን ከባድ የኃላፊነት ሥልጣን በፈቃደኝነት እንደተቀበለ መገንዘብ ይኖርበታል።”—ከዮሐንስ 17:12 እና ከያዕቆብ 3:1 ጋር አወዳድር።

7. (ሀ) የዘመናችን ፈራጆች ምን ነገር ማስታወስ ይኖርባቸዋል? ዓላማቸውስ ምን መሆን ይኖርበታል? (ለ) ሽማግሌዎች በማቴዎስ 18:18-20 ላይ ካለው ሐሳብ ምን ትምህርት ማግኘት ይኖርባቸዋል?

7 በፈራጅነት ቦታ የሚሠሩ ሽማግሌዎች በማንኛውም ጉዳይ ላይ ፍርድ የሚሰጡት ይሖዋና ኢየሱስ ክርስቶስ መሆናቸውን ማስታወስ ይኖርባቸዋል። ለእስራኤል ፈራጆች ተነግሮአቸው የነበረውን ቃል አስታውሱ፦ “[ለይሖዋ አዓት] እንጂ ለሰው አትፈርዱምና፣ እርሱም በፍርድ ነገር ከእናንተ ጋር ነውና የምታደርጉትን ተመልከቱ። አሁንም [ይሖዋን አዓት] መፍራት በእናንተ ላይ ይሁን። . . . እንዲህም ብታደርጉ በደለኞች አትሆኑም።” (2 ዜና 19:6-10) ሽማግሌዎች በአንድ ጉዳይ ላይ ፍርድ በሚሰጡበት ጊዜ ይሖዋ ‘ከሚሰጡት ፍርድ ጋር አብሮአቸው መሆኑን’ ለማረጋገጥ ተገቢውን ፍርሃት በማሳየት የተቻላቸውን ሁሉ ማድረግ ይኖርባቸዋል። የሚያስተላልፉት ውሳኔ ይሖዋና ክርስቶስ ስለ ጉዳዩ ያላቸውን አመለካከት የሚያንጸባርቅ መሆን ይገባዋል። በምድር ላይ በምሳሌያዊ ሁኔታ ‘ያሠሩት’ (ጥፋተኛ ሆኖ ያገኙት) ወይም ‘የፈቱት’ (ንጹሕ ሆኖ ያገኙት) በመንፈስ መሪነት በተጻፈው የአምላክ ቃል ውስጥ በተገለጸው መሠረት በሰማይ ከእነርሱ ርምጃ ቀድሞ የታሠረ ወይም የተፈታ መሆን ይኖርበታል። በኢየሱስ ስም ወደ ይሖዋ ቢጸልዩ ኢየሱስ በመካከላቸው ሆኖ ይረዳቸዋል። (ማቴዎስ 18:18-20፤ በአዓት የግርጌ ማስታወሻና በእንግሊዝኛ መጠበቂያ ግንብ የካቲት 15, 1988፤ ገጽ 9 ላይ ያለውን ሐሳብ ተመልከት።) ሽማግሌዎች የፍርድ ጉዳዮችን በሚያዳምጡበት ጊዜ የሚኖረው መንፈስ ክርስቶስ በእርግጥ በመካከላቸው መኖሩን የሚያሳይ መሆን ይኖርበታል።

የሙሉ ጊዜ እረኞች

8. በይሖዋ እና በኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌነት እንደታየው ሽማግሌዎች በአንደኛ ደረጃ ሊያተኩሩ የሚገባቸው በምን ሥራ ላይ ነው? (ኢሳይያስ 40:10, 11፤ ዮሐንስ 10:11, 27-29)

8 ሽማግሌዎች የሙሉ ጊዜ እረኞች ናቸው እንጂ የሙሉ ጊዜ ፈራጆች አይደሉም። ፈዋሾች ናቸው እንጂ ቀጭዎች አይደሉም። (ያዕቆብ 5:13-16) የበላይ ተመልካቾች (ኤጲስቆጶስ) ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል የሚያስተላልፈው መሠረታዊ ሐሳብ እንክብካቤና ጥበቃ ማድረግን ነው። የአዲስ ኪዳን መንፈሣዊ መዝገበ ቃላት የቃሉን ትርጉም በሚመለከት እንዲህ ይላል፦ “ቃሉ [ኤጲስቆጶስ] [በ1 ጴጥሮስ 2:25] ላይ ለተጠቀሰው እረኛ የሚል ቃል ማዳበሪያ ሆኖ የመጠበቅንና የመከላከልን የእረኝነት ሥራ ያመለክታል።” አዎ፣ እረኞች በአንደኛ ደረጃ ያላቸው ኃላፊነት በጎቹን መጠበቅና ከመንጋው መካከል እንዳይወጡ መከላከል ነው እንጂ ከመንጋው መካከል ማስወጣት አይደለም።

9, 10. (ሀ) ጳውሎስ ዋናውን የሽማግሌዎች የሥራ ግዴታ ያጎላው እንዴት ነው? ስለዚህ ምን ዓይነት ጥያቄ ሊነሳ ይችላል? (ለ) በሥራ 20:29 ላይ ያሉት የጳውሎስ ቃላት ምን ያመለክታሉ? ስለዚህ ሽማግሌዎች የፍርድ ጉዳዮችን ለመቀነስ ምን ጥረት ሊያደርጉ ይችላሉ?

9 ሐዋርያው ጳውሎስ በኤፌሶን ጉባኤ ለሚገኙት ሽማግሌዎች እንደሚከተለው በማለት ስለ ጉዳዩ ጠበቅ አድርጎ ገልጾአል። “በገዛ ልጁ ደም የዋጃትን የእግዚአብሔርን ጉባኤ ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን የበላይ ተመልካቾች አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ።” (ሥራ 20:28) ጳውሎስ ያጎላው መቅጣትን ሳይሆን እረኝነትን ነው። አንዳንድ ሽማግሌዎች፦ ‘ለእረኝነት ሥራ የበለጠ ጊዜ ብንመድብ የፍርድ ጉዳዮችን ለመመርመርና ለመመልከት የምናጠፋውን ጊዜ ለማዳን አንችልምን?’ ብለው ራሳቸውን ቢጠይቁ ጥሩ ነው።

10 እውነት ነው፣ ጳውሎስ “ከጨካኞች ተኩላዎች” እንዲጠበቁ አስጠንቅቋል። ይሁን እንጂ ጳውሎስ እነዚህ ሰዎች ‘መንጋውን በርኅራኄ ባለመያዛቸው’ ወቅሶአቸው የለምን? (ሥራ 20:29) ታማኞቹ የበላይ ተመልካቾች እንዲህ ያሉትን “ተኩላዎች” ከጉባኤ ማስወጣት እንደሚኖርባቸው ቢያመለክትም፣ የሐዋርያው ቃላት ሽማግሌዎች የመንጋውን ሌሎች ክፍሎች ‘በርኅራኄ’ መያዝ እንደሚኖርባቸው ያመለክቱ የለምን? አንድ በግ በመንፈሳዊ ደክሞ ከመንገድ ዳር ቢወድቅ ለእርሱ የሚያስፈልገው ምንድን ነው? መምታት ነው ወይስ ማከም? መቅጣት ነው ወይስ የእረኝነት እንክብካቤና ጥበቃ ማድረግ? (ያዕቆብ 5:14, 15) ስለዚህ ሽማግሌዎች ለእረኝነቱ ሥራ ቋሚ ጊዜ መመደብ ይኖርባቸዋል። ተገቢ የሆነ የእረኝነት ሥራ ቢሠራ ኖሮ በኃጢአት የተጠመዱ ክርስቲያኖችን የፍርድ ጉዳይ ለመመልከት የሚባክነውን ብዙ ጊዜ ማዳን ይቻል ነበር። ሽማግሌዎች በመጀመሪያ ደረጃ ሊያስቡ የሚገባቸው ለመንጋው እረፍትና እፎይታ በማስገኘት በይሖዋ ሕዝቦች መካከል ሰላምና እርጋታ እንዲሰፍን ማድረግ ነው።—ኢሳይያስ 32:1, 2

መሐሪ እረኞችና ፈራጆች ሆኖ ማገልገል

11. በፍርድ ኮሚቴዎች የሚያገለግሉ ሽማግሌዎች ያለ አድልዎ መፍረድ የሚኖርባቸውና “ላይኛይቱ ጥበብ” የምታስፈልጋቸው ለምንድን ነው?

11 አንድ ክርስቲያን የተሳሳተ ነገር ከመፈጸሙ በፊት ጠንከር ያለ የእረኝነት ክትትል ቢደረግ በይሖዋ ሕዝቦች መካከል የሚነሱትን የፍርድ ጉዳዮች ብዛት መቀነስ ይቻላል። (ከገላትያ 6:1 ጋር አወዳድር።) ይሁን እንጂ፣ በሰው አለፍጽምናና ኃጢአተኝነት ምክንያት ክርስቲያን የበላይ ተመልካቾች ከበድ ያሉ ኃጢአቶች የተፈጸሙባቸውን ጉዳዮች ለመመልከት መገደዳቸው አይቀርም። በነዚህ ጊዜያት እንዴት ባሉ መሠረታዊ ሥርዓቶች መመራት ይኖርባቸዋል? እነዚህ መሠረታዊ ሥርዓቶች ከሙሴ ዘመን ጀምሮ በመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች ዘመንም ሆነ በእኛ ዘመን አልተለወጡም። ሙሴ ለእስራኤል ፈራጆች የተናገራቸው የሚከተሉት ቃላት አሁንም ይሠራሉ፦ “በሰውና በወንድሙ ከእርሱም ጋር ባለው መጻተኛ መካከል በጽድቅ ፍረዱ። በፍርድ አድልዎ አታድርጉ። . . .” (ዘዳግም 1:16, 17) በፍርድ አድልዎ አለማድረግ “የላይኛይቱ ጥበብ” ባሕርይ ነው። ይህ ዓይነቱ ጥበብ ደግሞ በፍርድ ኮሚቴዎች ውስጥ ለሚያገለግሉ ሽማግሌዎች በጣም ያስፈልጋቸዋል። (ያዕቆብ 3:17፤ ምሳሌ 24:23) እንዲህ ያለው ጥበብ በድካምና በክፋት መካከል ያለውን ልዩነት ለይተው እንዲያስተውሉ ይረዳቸዋል።

12. ፈራጆች ጻድቅ ብቻ ሳይሆኑ ጥሩ ሰዎችም መሆን የሚያስፈልጋቸው በምን መንገድ ነው?

12 ሽማግሌዎች ይሖዋ ስለ መጥፎና ጥሩ ነገሮች ያወጣውን የአቋም ደረጃ መሠረት በማድረግ “በጽድቅ መፍረድ” አለባቸው። (መዝሙር 19:9) ጻድቅ ለመሆን ጥረት ቢያደርጉም ጥሩ ሰዎች ለመሆንም መጣር ይኖርባቸዋል። ጳውሎስ በሮሜ 5:7, 8 ላይ በገለጸው መሠረት በጻድቅና በጥሩ ሰው መካከል ያለውን ልዩነት ተገንዝበው ከዚህ ጋር የሚስማማ ባሕርይ ማሳየት ይኖርባቸዋል። ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል የተባለው መጽሐፍ “ጽድቅ” በሚለው ርዕስ ሥር ስለ ሮሜ 5:7, 8 የሰጠው ሐሳብ እንዲህ ይላል፦ “የግሪክኛው ቃል አጠቃቀም የሚያሳየው በጥሩነቱ የሚታወቅ ሰው ለሌሎች ጥሩ ነገር የሚያስገኝ ወይም ጥቅም የሚያመጣ ነገር ለማድረግ የሚያስብና ይህን አሳቢነቱን በተግባር የሚገልጽ መሆኑን ነው። ፍትሕ የሚፈልግበትን ነገር ብቻ ሳይሆን ከዚያ አልፎ በመሄድ ለሌሎች ተገቢውን አሳቢነት የሚያሳይና እነርሱን ለመርዳትና ለመጥቀም ፍላጎት ያለውን ሰው ያመለክታል።” (ጥራዝ 2፣ ገጽ 809) ጻድቅ ብቻ ሳይሆኑ ጥሩም የሆኑ ሽማግሌዎች ኃጢአት የሠራውን ሰው ወደ ንስሐ ለመመለስ ሲሉ በአሳቢነትና ሞቅ ባለ ስሜት ይይዟቸዋል። (ሮሜ 2:4) የሚቻል ሆኖ በሚገኝበት ቦታ ሁሉ ምሕረትና ርኅራኄ ለማሳየት መፈለግ ይኖርባቸዋል። በደለኛው ሰው በመጀመሪያ ላይ ጥረታቸውን የማይቀበል መስሎ ቢታይም ንስሐ መግባት የሚያስፈልገው መሆኑን እንዲገነዘብ ለመርዳት የሚቻላቸውን ሁሉ ማድረግ ይኖርባቸዋል።—ኤፌሶን 4:32-5:1፤ ያዕቆብ 2:13፤ ይሁዳ 22, 23

የፍርድ ጉዳዮችን በሚያዳምጡበት ጊዜ ሊኖራቸው የሚገባው ተገቢ አመለካከት

13. (ሀ) አንድ ሽማግሌ እንደ ፈራጅ ሆኖ በሚሠራበት ጊዜም ቢሆን ምን መሆኑ አይቀርም? (ለ) የፍርድ ጉዳዮች በሚሰሙበት ጊዜም ቢሆን ተፈጻሚነት የሚኖረው የትኛው የጳውሎስ ምክር ነው?

13 የበላይ ተመልካቾች አንድን የፍርድ ጉዳይ ለመስማት በሚቀመጡበት ጊዜም “በመልካሙ እረኛ” ሥር ያሉትን የይሖዋ በጎች በመጠበቅ ሥራ ላይ መሆናቸውን መዘንጋት አይኖርባቸውም። (ዮሐንስ 10:11) ጳውሎስ በችግር ላይ ለወደቁ በጎች ስለሚሰጠው የዘወትር እርዳታ የሰጠው ምክር የፍርድ ጉዳዮችን በሚሰሙበት ጊዜም ተፈጻሚነት አለው። ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፎአል፦ “ወንድሞች ሆይ፣ ሰው በማናቸውም በደል ስንኳ ቢገኝ፣ መንፈሳውያን የሆናችሁ እናንተ እንደዚህ ያለውን ሰው በየውሃት መንፈስ አቅኑት፤ አንተ ደግሞ እንዳትፈተን ራስህን ጠብቅ። ከእናንተ እያንዳንዱ የአንዱን ሸክም ይሸከም እንዲሁም የክርስቶስን ሕግ ፈጽሙ።”—ገላትያ 6:1, 2b

14. የበላይ ተመልካቾች የፍርድ ጉዳዮችን ስለ መስማት ምን አመለካከት ሊኖራቸው ይገባል? በደል ስለፈጸመውስ ሰው ምን ዓይነት ዝንባሌ ሊኖራቸው ይገባል?

14 በአንድ የፍርድ ኮሚቴ ውስጥ የሚያገለግሉ ሽማግሌዎች አንድን ጉዳይ ለመስማት ሲሰበሰቡ ስብሰባቸው ሌላው የእረኝነት ሥራቸው ክፍል እንደሆነ አድርገው መመልከት አለባቸው እንጂ ራሳቸውን ቅጣት ለማስፈጸም እንደተሰበሰቡ የበላይ ዳኞች አድርገው መመልከት የለባቸውም። አንድ የይሖዋ በግ ችግር ውስጥ ወድቋል። ሽማግሌዎች እርሱን ለማዳን ምን ሊያደርጉ ይችላሉ? ከመንጋው መካከል ባዝኖ የተነጠለ ከሆነ ይህ ሁኔታ የደረሰበት ሽማግሌዎቹ የእረኝነት ሥራቸውን ችላ ስላሉ ነውን? ከባድ ኃጢአት ተሠርቶ ከሆነ የይሖዋን የጽድቅ ሕግጋት ማላላት አለባቸው ማለት አይደለም። ይሁን እንጂ የሚወሰድበትን እርምጃ የሚያቃልልለት ሁኔታ መኖሩን በትኩረት መከታተላቸው የሚቻል ሲሆን ምህረት እንዲያደርጉለት ይረዳቸዋል። (መዝሙር 103:8-10፤ 130:3) አንዳንድ በደለኞች ግን ባላቸው መጥፎ ዝንባሌ ስለሚጸኑ ሽማግሌዎቹ ጠንከር ማለት ሊኖርባቸው ይችላል። ሆኖም ግን የጭካኔ ባሕርይ ሊያሳዩት ፈጽሞ አይገባም።—1 ቆሮንቶስ 5:13

የፍርድ ጉዳዮችን የሚያዳምጡበት ዓላማ

15. በግለሰቦች መካከል ከባድ ችግር በሚፈጠርበት ጊዜ በመጀመሪያ መጣራት የሚኖርበት ነገር ምንድን ነው?

15 በግለሰቦች መካከል ከባድ ችግር በሚፈጠርበት ጊዜ አስተዋይ ሽማግሌዎች ግለሰቦቹ በማቴዎስ 5:23, 24 ወይም በማቴዎስ 18:15 መሠረት ለጉዳዩ መፍትሔ ለማስገኘት ሞክረው እንደሆነ ያጣራሉ። ይህ ሙከራቸው አልተሳካ ከሆነ ግን ከአንድ ወይም ከሁለት ሽማግሌዎች የሚሰጥ ምክር በቂ ሊሆን ይችላል። የፍርድ እርምጃ መውሰድ የሚያስፈልገው ወደ ውገዳ የሚያደርስ ከባድ ኃጢአት ሲፈጸም ብቻ ነው። (ማቴዎስ 18:17፤ 1 ቆሮንቶስ 5:11) አንድን የፍርድ ኮሚቴ ለማቋቋም በቂ የሆነ ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክንያት መኖር አለበት። (የእንግሊዝኛ መጠበቂያ ግንብ መስከረም 15, 1989፣ ገጽ 18 ተመልከት።) አንድን ልዩ ጉዳይ ለመመልከት አንድ የፍርድ ኮሚቴ በሚቋቋምበት ጊዜ ጥሩ ችሎታ ያላቸው ሽማግሌዎች መመረጥ ይኖርባቸዋል።

16. ሽማግሌዎች አንድን የፍርድ ጉዳይ በሚሰሙበት ጊዜ ለማግኘት የሚሞክሩት ውጤት ምንድን ነው?

16 ሽማግሌዎች አንድን የፍርድ ጉዳይ በሚያዳምጡበት ጊዜ ለማግኘት የሚፈልጉት ውጤት ምንድን ነው? በመጀመሪያ ደረጃ፣ እውነቱ ካልታወቀ በጽድቅ መፍረድ አይቻልም። በእስራኤል ሕዝብ መካከል ከባድ ኃጢአት እንደተፈጸመ በሚሰማበት ጊዜ እንደሚደረገው ጉዳዩ በጥብቅ ‘መመርመር’ ይኖርበታል። (ዘዳግም 13:14፤ 17:4) ስለዚህ ሽማግሌዎች አንድን የፍርድ ጉዳይ ለመስማት ከሚሰበሰቡባቸው ዓላማዎች አንዱ ስለጉዳዩ እውነተኛውን ነገር ፈልጎ ማግኘት ነው። ይሁን እንጂ ይህን በፍቅር ማድረግ ይቻላል፣ መደረግም ይኖርበታል። (1 ቆሮንቶስ 13:4, 6, 7) ሐቁ ከታወቀ በኋላ ሽማግሌዎች ጉባኤውን ለመጠበቅ የሚያስችላቸውን፣ የይሖዋ ከፍተኛ የጽድቅ ደረጃዎች የሚጠበቁበትንና መንፈሱ መፍሰሱን እንዲቀጥል የሚያደርገውን ማንኛውንም አስፈላጊ እርምጃ ይወስዳሉ። (1 ቆሮንቶስ 5:7, 8) ይሁን እንጂ፣ ሽማግሌዎች የፍርድ ጉዳዮችን ከሚሰሙባቸው ዓላማዎች አንዱ የሚቻል ከሆነ አደጋ ላይ የወደቀውን ኃጢአተኛ ማዳን ነው።—ከሉቃስ 15:8-10 ጋር አወዳድር።

17. (ሀ) የአንድ የተከሰሰ ሰው ጉዳይ በሚሰማበት ጊዜ ለሰውየው ምን ዓይነት አያያዝ ሊደረግለት ይገባል? ዓላማውስ ምን መሆን ይኖርበታል? (ለ) የፍርድ ኮሚቴው አባሎች ይህን ለማድረግ እንዲችሉ ምን ይፈለግባቸዋል?

17 ተከስሶ በፍርድ ኮሚቴ ፊት የቀረበ አንድ ሰው እንደ አምላክ በግ እንጂ በሌላ መልክ ሊታይ አይገባም። በርኅራኄ መያዝ ይኖርበታል። አንድ ሰው ኃጢአት (ኃጢአቶች) ቢፈጽም በጽድቅ የሚፈርዱ ፈራጆች ዓላማ ኃጢአተኛው ራሱን እንዲያስተካክል፣ የተሳሳተ መንገድ መያዙን እንዲገነዘብ፣ ንስሐ እንዲገባና ከተያዘበት ‘የዲያብሎስ ወጥመድ’ እንዲወጣ መርዳት ነው። ይህን ዓላማ ለመፈጸም ከአንድ ጊዜ የበለጠ ስብሰባ ማድረግ አስፈላጊ ሊሆን ይችላል። ‘ጥሩ የማስተማር ችሎታ’ እና ‘በየዋህነት መንፈስ ማስተማር’ ያስፈልጋል። (2 ጢሞቴዎስ 2:24-26፤ 4:2) ኃጢአተኛው ኃጢአት መሥራቱን ተገንዝቦ በእውነት ከልቡ ቢነካና ይሖዋን ይቅርታ ቢጠይቅስ? (ከሥራ 2:37 ጋር አወዳድር።) ከልቡ እርዳታ ለማግኘት የሚፈልግ ከሆነ ለምን ይወገዳል?—የእንግሊዝኛ መጠበቂያ ግንብ ጥር 1, 1983፣ ገጽ 31፣ አንቀጽ 1 ተመልከት።

18. (ሀ) አንድ የፍርድ ኮሚቴ ጽኑ አቋም በመውሰድ አንድን ኃጢአተኛ ማስወገድ የሚኖርበት መቼ ነው? (ለ) ሽማግሌዎች ስለ ባዘኑ በጎች መድከምና ጠንክረው መሥራት የሚኖርባቸው እንዴት ያለ የሚያሳዝን ሁኔታ በመኖሩ ነው?

18 በሌላ በኩል ደግሞ የአንድ የፍርድ ኮሚቴ አባሎች ያጋጠማቸው ጉዳይ ግልጽ የሆነ ጸጸት የሌለበት ክህደት፣ በይሖዋ ሕጎች ላይ ሆን ተብሎ የተደረገ ዓመፅ ወይም ፍጹም ክፋት ቢሆን ንስሐ የማይገባውን አመፀኛ በማስወገድ የጉባኤውን አባሎች የመጠበቅ ኃላፊነት አለባቸው። የፍርድ ኮሚቴው ከጥፋተኛው ጋር በተደጋጋሚ ጊዜ እየተሰበሰበ አምላካዊ ኀዘን ለማሳየት ፈቃደኛ ያልሆነን ኃጢአተኛ በግድ ንስሐ እንዲገባ ለማድረግ የመሞከር ወይም የመለመን ግዴታ የለበትም።c በቅርብ ዓመታት ውስጥ በዓለም ዙርያ ካሉት አስፋፊዎች አንድ በመቶ የሚሆኑት ተወግደዋል። ይህም ማለት በበረቱ ውስጥ ከሚኖሩት መቶ በጎች መካከል አንዱ ቢያንስ ለተወሰነ ጊዜ ያህል ይጠፋል ማለት ነው። አንድን ሰው ወደ በጎች በረት ለማምጣት የሚወስደው ጊዜና ጥረት ሲታሰብ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች በየዓመቱ ‘ለሰይጣን መሰጠታቸው’ ከልብ የሚያሳዝን አይደለምን?—1 ቆሮንቶስ 5:5

19. በፍርድ ኮሚቴ የሚያገለግሉ ሽማግሌዎች ፈጽሞ መርሳት የማይኖርባቸው ነገር ምንድን ነው? ስለዚህ ዓላማቸው ምን ይሆናል?

19 አንድን የፍርድ ጉዳይ መመልከት የጀመሩ ሽማግሌዎች በጉባኤው ውስጥ ከሚሠሩት ኃጢአቶች መካከል አብዛኞቹ በድካም እንጂ በክፋት ምክንያት የማይሠሩ መሆናቸውን ማስታወስ ይገባቸዋል። ኢየሱስ ስለ ጠፋው በግ የተናገረውን ምሳሌ ሲደመድም የተናገረውን መርሳት የለባቸውም፦ “እላችኋለሁ፣ እንዲሁ ንስሐ ከማያስፈልጋቸው ከዘጠና ዘጠኝ ጻድቃን ይልቅ ንስሐ በሚገባ በአንድ ኃጢአተኛ ምክንያት በሰማይ ደስታ ይሆናል።” (ሉቃስ 15:7) በእርግጥም “ይሖዋ ሁሉ ወደ ንስሐ እንዲደርሱ እንጂ ማንም እንዲጠፋ” አይፈልግም። (2 ጴጥሮስ 3:9) በዓለም በሙሉ የሚገኙ የፍርድ ኮሚቴዎች በይሖዋ እርዳታ ኃጢአተኞችን ወደ ንስሐ በመመለስና ወደ ዘላለም ሕይወት በሚያስገባው ጠባብ መንገድ ላይ በሁለት እግራቸው ጸንተው እንዲቆሙ በመርዳት በሰማይ ደስታ እንዲኖር የተቻላቸውን ሁሉ ያድርጉ።—ማቴዎስ 7:13, 14

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a ከሌሎች በጎች የተውጣጡት ሽማግሌዎች በክርስቶስ ቀኝ እጅ በመሆናቸው ረገድ ስለሚኖራቸው አቋም በመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስ እና ትራክት ማኅበር በታተመው ራእይ፣ ታላቁ መደምደሚያው ቀርቦአል! በተባለው መጽሐፍ በገጽ 136 ላይ የሚገኘውን የግርጌ ማስታወሻ ተመልከት።

b የእንግሊዝኛ መጠበቂያ ግንብ፣ መስከረም 15, 1989፣ ገጽ 19 ተመልከት።

c የእንግሊዝኛ መጠበቂያ ግንብ መስከረም 1, 1981 ገጽ 26 አንቀጽ 24 ተመልከት።

የክለሳ ጥያቄዎች

◻ ሽማግሌዎች የታላቁን እረኛና የመልካሙን እረኛ ምሳሌ በመከተል ዋነኛ ፍላጎታቸው ሊያደርጉ የሚገባው ምንን ነው?

◻ ሽማግሌዎች የፍርድ ጉዳዮችን ብዛት ለመቀነስ በምን በኩል ጥረት ሊያደርጉ ይችላሉ?

◻ ፈራጆች ጻድቅ ብቻ ሳይሆኑ ጥሩም መሆን የሚኖርባቸው በምን መንገድ ነው?

◻ የአንድ ጥፋተኛ የፍርድ ጉዳይ በሚሰማበት ጊዜ ለበደለኛው እንዴት ያለ አያያዝ ማድረግ ይገባል? ምንስ ዓላማ ሊኖራቸው ይገባል?

◻ ማስወገድ ሌላው አማራጭ በሙሉ ከተሞከረ በኋላ የሚወሰድ የመጨረሻ እርምጃ የሆነው ለምንድን ነው?

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጥሩ የእረኝነት ሥራ በመሥራት ብዙ የፍርድ ጉዳዮችን ማስቀረት ይቻላል

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የፍርድ ጉዳይ በሚሰማበት ጊዜም ቢሆን ሽማግሌዎቹ በደል የሠራውን ሰው በየዋህነት መንፈስ ለማስተካከል መሞከር ይኖርባቸዋል

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ