ያለብኝን ኩራት በማስወገዴ ደስታ አገኘሁ
በ1970 እድሜዬ 23 ዓመት ነበር። ከፍተኛ ደረጃ ላይ ለመድረስ ትልቅ ጉጉት ነበረኝ። በአይቨሪያ ጣሊያን አገር በሚገኘው ተቀጥሬ በምሠራበት አንድ የመኪና ክበብ ውስጥ ዋና ጸሐፊ ሆኜ ነበር። ትልቅ ሰው ለመሆን ቁርጥ ውሳኔ ነበረኝ። ሆኖም በጣም አዝንና ይከፋኝ ነበር። ለምን?
ባለቤቴ አብዛኛውን ጊዜውን የሚያሳልፈው በየቡና ቤቱ ከጓደኞቹ ጋር ካርታ በመጫወት ነበር። አብዛኛውን የቤተሰብ ኃላፊነት በእኔ ትከሻ ላይ ጥሎታል። ግንኙነታችንም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ ሄደ። በትናንሽ ነገሮችም እንጣላ ጀመር። ከዚህም የተነሳ አዕምሮዬ አፍራሽ በሆኑ አስተሳሰቦች ተሞላ።
‘አንቺን እኮ ማንም የሚወድሽ ሰው የለም። በስልጣንሽ ለመጠቀም ብቻ ነው የሚፈልጉሽ’ ማለት ጀመርኩ። ‘አምላክ ሊኖር አይችልም ቢኖር ኖሮ ይህን ሁሉ ሥቃይና ክፋት እንዲኖር አይፈቅድም ነበር። ሕይወት ማለት እኮ ለሞት የሚደረግ ሩጫ ነው።’ እያልኩ ከራሴ ጋር እነጋገራለሁ። ይህ ሁሉ ለምን እንደዚህ እንደሆነ ለመረዳት አልቻልኩም ነበር።
ለውጥ ማድረግ ጀመርኩ
በ1977 አንድ ቀን ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች በራችንን አንኳኩ። ባለቤቴ ጆንካርሎ ወደ ውስጥ እንዲገቡ ጋበዛቸውና ሊያነጋግሩት ወደ ሳሎን ገቡ። የጆንካርሎ እቅድ እነርሱም እንደ እርሱ የዝግመተ ለውጥ አማኞች እንዲሆኑ ለማድረግ ነበር። ይሁን እንጂ የእሱን አስተሳሰብ ሊለውጡ የቻሉት እነርሱ ሆነው ተገኙ!
ጆንካርሎ ወዲያውኑ በሕይወቱ ላይ ለውጥ ማድረግ ጀመረ። በጣም ትዕግስተኛ ሆነ፣ አብዛኛውን ጊዜውንና ትኩረቱን ለእኔና ለሴቷ ልጃችን ይሰጥ ጀመር። እየተማራቸው ስላሉት ነገሮች ሊነግረኝ ይሞክራል፤ ይሁን እንጂ ሁልጊዜ መራራ የሆነ ንግግር እናገረውና ውይይቱን እዘጋበታለሁ።
ከዚያም አንድ ቀን ምሥክሮቹ ሊያነጋግሩት ሲመጡ ቁጭ ብዬ በሚገባ አዳመጥሁ። እነርሱም ስለዚህ የነገሮች ሥርዓት ፍጻሜና ስለ አምላክ መንግሥት፣ ስለ ገነቲቱ ምድር እንዲሁም ስለ ሙታን ትንሳኤ ተናገሩ። በጣም ደነገጥሁ! ከዚያ በኋላ ባሉት ሦስት ሌሊቶች እንቅልፍ አልወሰደኝም! የበለጠ ለማወቅ ፈልጌ ነበር። ይሁን እንጂ የነበረኝ ኩራት ባለቤቴን ጥያቄዎች እንዳልጠይቀው ከለከለኝ። ከዚያም አንድ ቀን ኮስተር ብሎ፦ “ዛሬ አንቺ ታዳምጪኛለሽ። እኔ ለጥያቄዎችሽ ሁሉ መልስ አለኝ” ብሎ ተናገረኝ። ከዚያም የመጽሐፍ ቅዱስን እውነቶች አዘነበብኝ።
ይሖዋ የፈጣሪ ስም እንደሆነ፣ የፈጣሪ ዋና ባሕርይ ፍቅር እንደ ሆነና በዚህ ፍቅሩ ተገፋፍቶ የዘላለም ሕይወት ለማግኘት እንድንችል ሲል ልጁን ቤዛ እንዲሆን እንደላከውና ክፉዎች በአርማጌዶን ከጠፉ በኋላ ክርስቶስ በሺው ዓመት ግዛቱ ወቅት የሞቱትን እንደሚያስነሳ ጆንካርሎ ነገረኝ። ከሞት የሚነሱትም ወደ አዕምሮአዊና አካላዊ ፍጽምና እንደሚደርሱና ገነት በሆነችው ምድር ላይ ለዘላለም የመኖር አጋጣሚ እንደሚኖራቸውም ነገረኝ።
በሚቀጥለው ቀን ለመጀመሪያ ጊዜ ከባለቤቴ ጋር ወደ መንግሥት አዳራሽ ሄድኩ። ከዚያም በኋላ፦ “እነዚህ ሰዎች እርስ በርሳቸው ይዋደዳሉ። ወደዚህ መምጣቴን መቀጠል እፈልጋለሁ፤ ምክንያቱም እነዚህ ሰዎች ደስተኞች ናቸው” አልኩት። ስብሰባዎችን አዘውትሬ መከታተል ጀመርኩ። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትም ተመራልኝ። የተማርኩትን ነገር ብዙ አሰላሰልኩበትና እውነተኞቹን የአምላክ ሕዝቦች እንዳገኘሁ አመንኩ። በ1979 ባለቤቴና እኔ ራሳችንን ለይሖዋ መወሰናችንን በመጠመቅ አሳየን።
የሙሉ ጊዜ አገልግሎት
በሚቀጥለው ዓመት በተደረገው የክልል ስብሰባ ላይ ለሙሉ ጊዜ የስብከት ሥራ የሚያበረታታ ንግግር ተሰጠ። ይህን አገልግሎት ለመጀመር እንደተንቀሳቀስሁ ሆኖ ተሰማኝ። ነገሩን ለይሖዋ በጸሎት ነገርኩት። ይሁን እንጂ አረገዝኩና እቅዴ ተቋረጠ። ቀጥለው በነበሩት አራት ዓመታት ውስጥ ሦስት ልጆችን ወለድን። ሁለቱ ልጆቻችን በተለያየ ጊዜ ለሕይወታቸው የሚያሰጋ አካላዊ ሕመም ታመሙብን። ለይሖዋ ምስጋና ይግባውና ሁለቱም ሙሉ በሙሉ ዳኑ።
የሙሉ ጊዜ አገልጋይ ለመሆን ያለኝን እቅዴን ከእንግዲህ በኋላ ላዘገየው እንደማልችል ተሰማኝ። በሚስትነትና በእናትነት ኃላፊነቶቼ ላይ የበለጠ ለማተኮር እንድችል ስል ሥጋዊ ሥራዬን ተውኩ። ባለቤቴና እኔ አስፈላጊ ያልሆኑ ነገሮች ትተን በአንድ አቅጣጫ ብቻ በሚገኝ ገቢ ለመኖር እቅድ አወጣን። ይሁን እንጂ ይሖዋ አብዝቶ ባረከን እንጂ ለድህነት ወይም ለችግር አሳልፎ አልሰጠንም።
በ1984 በዚያን ጊዜ 15 ዓመት የሆናትና በቅርቡ የተጠመቀችው ሴት ልጄ አቅኚ ሆና የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ጀመረች። በዚያው ጊዜ ባለቤቴም ሽማግሌ ሆኖ ተሾመ። ታዲያ እኔስ? አቅኚ ሆኜ ማገልገል እንደማልችል ቢሰማኝም በስብከቱ ሥራ በወር 30 ሰዓት ለማሳለፍ ግብ አወጣሁ። ያወጣሁት ግብ ላይ ስለደረስኩ ‘ግሩም ሠርተሻል! በጣም ብዙ እየሠራሽ ነው’ አልኩ ለራሴ።
ይሁን እንጂ አሁንም ኩራት እያስቸገረኝ መጣ። (ምሳሌ 16:18) በጣም ጥሩ እየሠራሁ እንዳለሁና ከዚህ የበለጠ መንፈሳዊ እድገት ማድረግ እንደማያስፈልገኝ አሰብኩ። መንፈሳዊነቴ መዳከም ጀመረ። እንዲያውም ያገኘኋቸውን መልካም ባህርያት እያጣሁ መጣሁ። ከዚያም የሚያስፈልገኝን ተግሳጽ ተቀበልሁ።
በ1985 ሁለት ተጓዥ የበላይ ተመልካቾችና ሚስቶቻቸው በጉባኤያችን ውስጥ አጭር ጉብኝት በሚያደርጉበት ጊዜ እኛ ቤት አርፈው ነበር። እነዚህን ትሁት ራሳቸውን መስዋዕት የሚያደርጉ ክርስቲያኖች ስመለከት ነገሮችን እንዳሰላስልባቸው አደረገኝ። በመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ጽሑፎች በመጠቀምም ትህትናን በተመለከተ ምርመራ አደረግሁ። ይሖዋ ከእኛ ኃጢአተኛ ከሆንን ሰዎች ጋር በሚያደርጋቸው ግንኙነቶች ስላሳየው ትልቅ ትህትና አሰብኩ። (መዝሙር 18:35) አስተሳሰቤን መለወጥ እንዳለብኝ ተረዳሁ።
ትህትናን እንድኮተኩት፣ በሚፈልገው መንገድ እሱን እንዳገለግለውና ያለኝን ስጦታ ለእሱ ክብር እንድጠቀምበት እንዲረዳኝ ይሖዋን ለመንኩት። የአቅኚነት አገልግሎት ማመልከቻ ቅጽ ሞላሁ። በመጋቢት 1989 በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ማገልገል ጀመርኩ።
አሁን በእውነት ደስተኛ ነኝ ብዬ ለመናገር እችላለሁ። ለደስታዬ አስተዋጽኦ ያደረገልኝ ያለብኝን ኩራት ማስወገዴ ነው። በሕይወት ለመኖርና ለተቸገሩ ሰዎች እውነተኛው አምላክ ይሖዋ ለሚፈልጉት ሩቅ እንዳልሆነ እንዲያውቁ ለመርዳት ጥሩ ምክንያት አለኝ።—ቬራ ብራንዶሊኒ እንደተናገረችው።