የአንባቢያን ጥያቄዎች
ኢዮብ ይኖር በነበረበት ዘመን ለይሖዋ ታማኝ የነበረው ሰው እሱ ብቻ እንደሆነ አድርገን ከኢዮብ 1:8 መረዳት ይኖርብናልን?
አይኖርብንም። እንደሚከተለው ከሚለው የኢዮብ 1:8 ጥቅስ እንደዚህ ብሎ መደምደም ትክክል አይደለም።
“እግዚአብሔርም [ይሖዋም አዓት] ሰይጣንን፦ በውኑ ባሪያዬን ኢዮብን ተመለከትኸውን? በምድር ላይ እንደ እርሱ ፍጹምና ቅን፣ እግዚአብሔርንም የሚፈራ፣ ከክፋትም የራቀ ሰው የለም አለው።” አምላክ በኢዮብ 2:3 ላይም ሰይጣንን “በውኑ ባሪያዬን ኢዮብን ተመለከትኸውን? በምድር ላይ እንደ እርሱ ፍጹምን ቅን፣ እግዚአብሔርንም የሚፈራ፣ ከክፋትም የራቀ ሰው የለም” ብሎ በመጠየቅ ተመሳሳይ አገላለጽ ተጠቅሟል።
አምላክ ታማኝ አድርጎ የተቀበለው ሰው ኢዮብ ብቻ እንዳልነበረ የኢዮብ መጽሐፍ ራሱ ያመለክታል። ከምዕራፍ 32 ጀምረን ስለ ኤሊሁ እናነባለን። ምንም እንኳን ኤሊሁ ወጣት ቢሆንም የኢዮብን የተሳሳተ አመለካከት በማስተካከል እውነተኛውን አምላክ ከፍ ከፍ አድርጓል።—ኢዮብ 32:6 እስከ 33:6, 31-33፤ ኢዮብ 35:1 እስከ 36:2
እንዲሁም ‘በምድር ላይ እንደ ኢዮብ ያለ ማንም የለም’ የሚለው የአምላክ አነጋገርም ቢሆን ኢዮብ በጻድቅነቱ በተለይ ከሌሎች ጎልቶ የሚታውቅ ነው ማለቱ ነው። ኢዮብ የኖረው ዮሴፍ በግብጽ ውስጥ በሞተበትና ሙሴ የአምላክ ነብይ ሆኖ ማገልገል በጀመረበት ጊዜ መካከል ነው። በዚህ ወቅት ብዙ እስራኤላውያን በግብፅ ይኖሩ ነበር። ሁሉም እስራኤላውያን ታማኝ አልነበሩም፣ በአምላክ ዘንድም ተቀባይነት አልነበራቸውም ብለን ለማሰብ ምንም ምክንያት አይኖረንም። በይሖዋ ላይ ትምክህት የነበራቸው ብዙ እስራኤላውያን ይኖራሉ። (ዘጸአት 2:1-10፤ ዕብራውያን 11:23) ይሁን እንጂ አንዳቸውም ቢሆኑ እንደ ዮሴፍ ወይም የእስራኤልን ሕዝብ ከግብፅ መርቶ እንዳወጣው እንደ ሙሴ በጣም የሚያሳውቃቸው ትልቅ ሚና አልተጫወቱም።
ይሁን እንጂ በሌላ ቦታ የሚኖርና ታማኝነቱን በመጠበቅ ከሌሎች ሁሉ ጎልቶ የታወቀ አንድ ሰው ነበር። “ዖፅ በሚባል አገር ስሙ ኢዮብ የተባለ አንድ ሰው ነበር፤ ያም ሰው ፍጹምና ቅን፣ እግዚአብሔርንም የሚፈራ፣ ከክፋትም የራቀ ነበር።”—ኢዮብ 1:1
ስለዚህ ይሖዋ የኢዮብን እምነትና ለአምላክ የማደርን ዓይነተኛ ወይም የታወቀ ምሳሌውን ጠቅሶ ለመናገር ችሏል። በተመሳሳይም የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ የሆኑት ሕዝቅኤልና ያዕቆብ መለስ ብለው ኢዮብን የጽድቅና የጽናት ምሳሌ አድርገው ከሌሎች ነጥለው ጠቅሰውታል።—ሕዝቅኤል 14:14፤ ያዕቆብ 5:11