ሕዝበ ክርስትና በአፍሪካ የዘራችው ምንድን ነው?
በ1867 ቻርልስ ላቪዥሪ የሚባሉ ፈረንሳዊ ካቶሊክ የአልጀርስ ከተማ ሊቀ ጳጳስ እንዲሆኑ ተሹመው ወደ አፍሪካ መጡ። እሳቸውም “ፈረንሳይ አልጀሪያን ታላቅና የክርስትና ምንጭ የሆነች አገር እንድታደርጋት አምላክ መርጦአታል” ብለው ነበር።
የላቬዥሪ ምኞት ግን በአልጀሪያ ብቻ አልተወሰነም። እንዲያውም “ማዕከላዊውንና ሰሜናዊውን አፍሪካ በሕዝበ ክርስትና የጋራ ሕይወት አንድ ለማድረግ” በማሰብ ሚስዮናውያንን በበረሃማው አካባቢ በሙሉ ላኩ።
በዚሁ ጊዜ በምዕራባዊው፣ በደቡባዊውና በምሥራቃዊው የአህጉሪቱ ክፍሎች የፕሮቴስታንት ሚስዮናውያን እንቅስቃሴያቸውን ጀምረው ነበር። እነርሱም የማንቀጥቀጥ፣ የማላብና የማቃዠት ሕመም የሚያመጣውን ተደጋጋሚ የወባ ጥቃትና የመሳሰሉትን ብዙ ችግሮች በድፍረት ተጋፍጠዋል። ብዙዎቹ በበረሃው በሽታዎች ስለተዳከሙ ብዙ ሳይቆዩ ሞተዋል። ይሁን እንጂ ሌሎች ሚስዮናውያን መምጣታቸውን አላቆሙም። አድላ ስቴቨንሰን “በአፍሪካ ውስጥ የሚጓዝ ማንኛውም ሰው የሚስዮናውያንን ጀግንነት ለማስታወስ ይገደዳል። . . . ከቢጫ ወባ፣ ከተቅማጥና ከሆድ ትላትሎች ጋር ተጋድለዋል። . . . በአፍሪካ አገሮች በሙሉ . . . መቃብሮቻቸውን አይቼአለሁ” በማለት ተናግረዋል።
የሚስዮናዊነት ፍሬ
ሚስዮናውያን ወደ አፍሪካ ዘልቀው ሲገቡ አብዛኞቹ ጎሣዎች መሐይማን መሆናቸውን ተገነዘቡ። ራምዴሲ ክርስትና በአፍሪካ በአፍሪካውያን አስተያየት በተሰኘው መጽሐፋቸው ላይ “በግምት ስምንት መቶ ከሚሆኑት [የአፍሪካ] ቋንቋዎች ውስጥ ሚስዮናውያን ከመምጣታቸው በፊት ጽሑፍ የነበራቸው አራቱ ብቻ ነበሩ” ብለዋል። ስለዚህ ሚስዮናውያን እነዚህን ጽሑፍ ያልነበራቸውን ቋንቋዎች በጽሑፍ ሊያሰፍሩ የሚችሉበትን መንገድ መፈልሰፍ ነበረባቸው። ከዚያም የመማሪያ መጻሕፍትን አዘጋጁና ሕዝቡን ንባብ ለማስተማር ቆርጠው ተነሱ። ለዚህ ዓላማቸው ሲሉ በአፍሪካ በሙሉ ትምህርት ቤቶችን ሠሩ።
ሚስዮናውያኑ ሆስፒታሎችንም ሠርተዋል። ራም ዴሳይ “እነርሱ የሠሩትን የሚያክል የሰብአዊነት ሥራ የሠራ ሌላ ድርጅት የለም” ብለዋል። አፍሪካውያኑ ከአውሮፓ የሚፈልጉት የሕክምና እንክብካቤ ብቻ ሳይሆን ሌሎች የሸቀጥ ዕቃዎችንም ጭምር ነበር። አንዳንድ ሚስዮናውያን ሰዎችን ወደ ሃይማኖታችን ይስብልናል ብለው ስላሰቡ የንግድ መደብሮችን ከፈቱ። ለምሳሌ ያህል ከስዊዘርላንድ የመጣው የባሰል ሚሽን ጋና ውስጥ የንግድ ኩባንያ መሠረተ። ሚስዮናውያኑ የካካዋ ዛፍ ጋና ውስጥ በጥሩ ሁኔታ እንደሚበቅል ተገነዘቡ። በዛሬው ጊዜ ጋና በካካዎ ምርት ከዓለም የሦስተኛነትን ደረጃ ይዛለች።
ከሕዝበ ክርስትና ሚስዮናውያን የላቀ የሥራ ክንውን በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሰው መጽሐፍ ቅዱስን መተርጎማቸው ነበር። ይሁን እንጂ የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ማሠራጨት ሌላ ከባድ ኃላፊነት የሚያስከትል ነው። ክርስቲያኑ ሐዋርያው ጳውሎስ ይህን ኃላፊነት ሲገልጽ “እንግዲህ አንተ ሌላውን የምታስተምር ራስህን አታስተምርምን? አትስረቅ ብለህ የምትሰብክ ትሰርቃለህን? አታመንዝር የምትል ታመነዝራለህን?” በማለት ጠይቆአል። መጽሐፍ ቅዱስ ክርስትናን የሚያስተምሩ ሰዎች ራሳቸው በአምላክ ቃል ውስጥ ባሉት መልካም መሠረታዊ ሥርዓቶች መገዛት እንደሚገባቸው ያስጠነቅቃል።—ሮሜ 2:21, 24
ታዲያ የሕዝበ ክርስትና ሚስዮናውያን በአፍሪካ ውስጥ ስለነበራቸው ሁኔታ ምን ሊባል ይቻላል? የመጽሐፍ ቅዱስን አምላክ አስከብረዋል ወይስ የክርስትናን ትምህርቶች በተሳሳተ መንገድ ወክለዋል?