የመሲሑ መገኘትና አገዛዙ
“ይህ ከእናንተ ወደ ሰማይ የወጣው ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሲሄድ እንዳያችሁት፣ እንዲሁ ይመጣል።”—ሥራ 1:11
1, 2. (ሀ) ኢየሱስ ወደ ሰማይ በወጣ ጊዜ ሁለት መላእክት የኢየሱስን ሐዋርያት ያጽናኗቸው እንዴት ነበር? (ለ) በክርስቶስ መመለስ ተስፋዎች ላይ ምን ጥያቄዎች ይነሳሉ?
አሥራ አንድ ሰዎች ወደ ሰማይ አንጋጠው እየተመለከቱ በምሥራቃዊው የደብረ ዘይት ተራራ ቁልቁለት ላይ ቆመዋል። ኢየሱስ ከመካከላቸው ተነጥሎ ወደ ሰማይ ያረገው ከጥቂት ጊዜ በፊት ነበር። በደመና ከዓይናቸው እስኪሰወር ድረስ ተመለከቱት። እነዚህ ሰዎች ከእርሱ ጋር ባሳለፉአቸው ዓመታት ኢየሱስ መሲሕ መሆኑን የሚያረጋግጡ ብዙ ማስረጃዎችን አይተዋል። በሞቱ እጅግ አዝነው በትንሣኤው ተደስተዋል። አሁን ግን ተለይቶአቸው ሄደ።
2 ሁለት መላእክት በድንገት ታዩና የሚከተሉትን የሚያጽናኑ ቃላት ተናገሩአቸው፦ “የገሊላ ሰዎች ሆይ፣ ወደ ሰማይ እየተመለከታችሁ ስለ ምን ቆማችኋል? ይህ ከእናንተ ወደ ሰማይ የወጣው ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሲሄድ እንዳያችሁት፣ እንዲሁ ይመጣል።” (ሥራ 1:11) የኢየሱስ ወደ ሰማይ መውጣት ስለ ምድርና ስለ ሰው ልጆች ምንም ደንታ የሌለው መሆኑን እንደማያመለክት ማወቃቸው ምንኛ አጽናንቶአቸው ነበር! ኢየሱስ ተመልሶ ይመጣል። እነዚህ ቃላት ሐዋርያቱን በተስፋ እንደሞሉአቸው ምንም ጥርጥር የለውም። በዛሬው ጊዜም በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ክርስቶስ እንደሚመለስ ለሰጠው ተስፋ ከፍተኛ ግምት ይሰጣሉ። አንዳንዶቹ “ዳግም መምጣት” ወይም “ምጽአት” ብለው ይጠሩታል። ብዙዎች ግን የክርስቶስ መመለስ ምን ትርጉም እንዳለው ግራ የገባቸው ይመስላል። ክርስቶስ የሚመለሰው በምን መንገድ ነው? የሚመለሰውስ መቼ ነው? ይህስ በአሁኑ ጊዜ የምንኖረውን ሰዎች ሕይወት የሚነካው እንዴት ነው?
ክርስቶስ የሚመለስበት ሁኔታ
3. ብዙ ሰዎች ስለ ክርስቶስ መመለስ ምን ዓይነት እምነት አላቸው?
3 አን ኢቫንጄሊካል ክርስቶሎጂ የተሰኘው መጽሐፍ እንደሚገልጸው “የክርስቶስ ዳግም ምጽአት ወይም መመለስ (ፓሩሲያ) የአምላክን መንግሥት ለመጨረሻ ጊዜ በግልጽና ለዘላለም ይመሠርታል።” ክርስቶስ ሲመለስ በዓይን እንደሚታይ፣ በግዑዟ ምድር ላይ የሚኖር እያንዳንዱ ሰው እንደሚያየው በሠፊው ይታመናል። ይህንን አስተሳሰብ ለመደገፍ ሲሉም ብዙዎች የሚጠቅሱት “እነሆ፣ ከደመና ጋር ይመጣል፤ ዓይንም ሁሉ የወጉትም ያዩታል” የሚለውን ራእይ 1:7ን ነው። ይሁን እንጂ ይህ ጥቅስ ቃል በቃል የሚወሰድ ነውን?
4, 5. (ሀ) ራእይ 1:7 ቃል በቃል የሚወሰድ አለመሆኑን እንዴት እናውቃለን? (ለ) የራሱ የኢየሱስ ቃላት ይህ ግንዛቤ ትክክል መሆኑን የሚያረጋግጡት እንዴት ነው?
4 የራእይ መጽሐፍ “በምልክቶች” የቀረበ መሆኑን አስታውሱ። (ራእይ 1:1 አዓት) ስለዚህ ይህ ጥቅስ ምሳሌያዊ መሆን አለበት። እንዲህ ባይሆን “ክርስቶስን የወጉት” ሁሉ እንዴት ሊያዩት ይችላሉ? ከሞቱ 20 መቶ ዓመታት ያህል ሆኖአቸዋል። በተጨማሪም መላእክት ክርስቶስ የሚመለሰው በሂደት ዓይነት ሁኔታ “እንዲሁ” እንደሆነ ተናግረዋል። ኢየሱስ የሄደው በምን ዓይነት ሁኔታ ነበር? በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች እያዩት ነበርን? አልነበረም። ሲያርግ ያዩት ጥቂት ታማኝ ሰዎች ብቻ ነበሩ። መላእክቱ ከሐዋርያት ጋር በተነጋገሩበት ጊዜ ሐዋርያቱ ክርስቶስ ሰማይ እስኪደርስ ድረስ አይተውት ነበርን? አላዩም። ደመና ከዓይናቸው ሰውሮታል። ማረግ ከጀመረ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ለሰብአዊ ዓይን የማይታይ መንፈሳዊ አካል በመሆን ወደ መንፈሳዊዎቹ ሰማያት ገብቶአል። (1 ቆሮንቶስ 15:50) ስለዚህ ሐዋርያቱ ያዩት ግፋ ቢል የኢየሱስን ጉዞ መጀመሪያ ብቻ ነው። አባቱ ይሖዋ ወደሚገኝበት የመጨረሻ ቦታ ሲደርስ ሊመለከቱ አይችሉም ነበር። እዚያ መድረሱን ሊያስተውሉ የሚችሉት በእምነት ዓይናቸው ብቻ ነበር።—ዮሐንስ 20:17
5 መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ የሚመለሰው ከሄደበት ሁኔታ ጋር በጣም በሚመሳሰል ሁኔታ እንደሚሆን ያስተምራል። ኢየሱስ ራሱም ከመሞቱ ጥቂት ቀደም ብሎ “ገና ጥቂት ዘመን አለ ከዚህም በኋላ ዓለም አያየኝም” በማለት ተናግሯል። (ዮሐንስ 14:19) በተጨማሪም “የእግዚአብሔር መንግሥት የምትመጣው ሰዎች በሚጠባበቁበት ዓይነት [በጉልህ በመታየት አዓት] አይደለም” ብሏል። (ሉቃስ 17:20) ታዲያ ‘ዓይንም ሁሉ የሚያየው’ በምን መንገድ ነው? ይህን ጥያቄ ለመመለስ በመጀመሪያ ኢየሱስና ተከታዮቹ ስለመመለሱ ለመግለጽ የተጠቀመበትን ቃል በግልጽ መረዳት ያስፈልገናል።
6. (ሀ) “መመለስ”፣ “መድረስ”፣ “ምጽአት” እና “መምጣት” የሚሉት ቃላት ፓሩሲያ ለሚለው የግሪክኛ ቃል በቂ ትርጉሞች ያልሆኑት ለምንድን ነው? (ለ) ፓሩሲያ ወይም “መገኘት” ከአንድ ቅጽበታዊ ሁኔታ የበለጠ ረዥም ጊዜ እንደሚቆይ የሚያሳየው ምንድን ነው?
6 ሐቁ ክርስቶስ የሚፈጽመው ድርጊት በ“መመለስ” ብቻ የተወሰነ አለመሆኑ ነው። “መምጣት”፣ “መድረስ” ወይም “ምጽአት” የሚለው ቃል ለአጭር ጊዜ ብቅ የማለትን ሁኔታ ያመለክታል። ኢየሱስና ተከታዮቹ የተጠቀሙበት የግሪክኛ ቃል ግን ከዚህ የበለጠ ትርጉም ያለው ነው። ፓሩሲያ የተሰኘው ቃል ትርጉሙ ቃል በቃል “ከጎን መሆን” ወይም “መገኘት” ማለት ነው። አብዛኞቹ ምሁራን ይህ ቃል መምጣትን ብቻ ሳይሆን አንድ ንጉሣዊ ሥልጣን ያለው ሰው ከሚያደርገው ጉብኝት ጋር ተመሳሳይነት ያለውን መገኘት የሚያመለክት እንደሆነ ይስማማሉ። ይህ መገኘት በአንድ ቅጽበታዊ ጊዜ የሚፈጸም ድርጊት አይደለም። ተለይቶ የሚታወቅ ዘመን፣ የተወሰነ ርዝማኔ ያለው ጊዜ ነው። በማቴዎስ 24:37-39 ላይ ኢየሱስ “የሰው ልጅ መምጣት [ፓሩሲያ]” በውኃ ጥፋት እንዳከተመው እንደ “ኖኅ ዘመን” እንደሚሆን ተናግሯል። የውኃ ጥፋቱ ከመምጣቱና ያንን ብልሹ የዓለም ሥርዓት ጠራርጎ ከማጥፋቱ አስቀድሞ ኖኅ ለብዙ አሥር ዓመታት መርከብ ይሠራና ክፉዎችን ያስጠነቅቅ ነበር። በተመሳሳይ የክርስቶስ የማይታይ መገኘትም በታላቅ ጥፋት ከመደምደሙ በፊት ለጥቂት አሥር ዓመታት ይቆያል።
7. (ሀ) ፓሩሲያው ለሰው ዓይን የማይታይ መሆኑን የሚያረጋግጠው ምንድን ነው? (ለ) የክርስቶስ መመለስ ‘በዓይን ሁሉ’ እንደሚታይ የሚገልጹ ጥቅሶች የሚፈጸሙት መቼና እንዴት ነው?
7 ፓሩሲያ ቃል በቃል ለሰው ዓይን የሚታይ እንዳልሆነ ጥርጥር የለውም። ቃል በቃል ለሰው ዓይን የሚታይ ቢሆን ኖሮ ኢየሱስ ወደፊት እንደምንመለከተው መገኘቱን ለማስተዋል እንዲረዳቸው ብሎ ለደቀ መዛሙርቱ ምልክት በመስጠት ብዙ ጊዜ ማጥፋት ለምን አስፈለገው?a ይሁን እንጂ ክርስቶስ የሰይጣንን ዓለም ሥርዓት ለማጥፋት በሚመጣበት ጊዜ የመገኘቱን ሐቅ ለሁሉም በግድ ግልጽ ይሆናል። ‘ዓይንም ሁሉ የሚያየውም’ ያን ጊዜ ነው። የኢየሱስ ጠላቶችም እንኳን እጅግ የሚያፀፅታቸው ቢሆንም የክርስቶስ ግዛት እውን መሆኑን ለማስተዋል ይችላሉ።—ማቴዎስ 24:30፤ 2 ተሰሎንቄ 2:8፤ ራእይ 1:5, 6
መገኘቱ የሚጀምረው መቼ ነው?
8. የክርስቶስን መገኘት መጀመሪያ ለይቶ የሚያሳውቀው ምን ሁኔታ ነው? ይህስ የሆነው የት ነው?
8 የመሲሑ መገኘት የሚጀምረው ተደጋግሞ የተገለጸው የመሲሐዊ ትንቢቶች ዋና ምልክት ሲፈጸም ነው። በሰማይ ንጉሥ ሆኖ ዘውድ ይጭናል። (2 ሳሙኤል 7:12-16፤ ኢሳይያስ 9:6, 7፤ ሕዝቅኤል 21:26, 27) ኢየሱስ ራሱም መገኘቱ ከንግሥናው ጋር የተያያዘ እንደሚሆን ገልጿል። በአያሌ ምሳሌዎቹ ላይ ቤተሰቡንና ባሪያዎቹን ትቶ ረዘም ላለ ጊዜ “ንግሥናውን” ወይም “ንጉሣዊ ሥልጣኑን” ወደሚቀበልበት “ሩቅ አገር” እንደሄደ ባለቤት አድርጎ ራሱን ገልጿል። ይህን ምሳሌ የሰጠው ፓሩሲያው መቼ እንደሚጀምር ሐዋርያቱ ላቀረቡለት ጥያቄ በሰጠው መልስ ላይ ነበር። ሌላውን ምሳሌ የሰጠው ደግሞ “የእግዚአብሔር መንግሥት ፈጥኖ ሊገለጥ እንዳለው ስለመሰላቸው” ነበር። (ሉቃስ 19:11, 12, 15፤ ማቴዎስ 24:3፤ 25:14, 19) ስለዚህ በምድር ላይ ሰው ሆኖ በነበረበት ጊዜ ዘውድ የሚጭንበት ጊዜ ገና ሩቅ ዘመን የሚቆይና “ሩቅ አገር” በሆነው በሰማይ የሚፈጸም ነገር ነበር። ንግሥናውን የሚቀበለው መቼ ነበር?
9, 10. ክርስቶስ አሁን በሰማይ በመግዛት ላይ እንደሆነ ምን ማስረጃ አለ? ኢየሱስ ግዛቱን የጀመረውስ መቼ ነው?
9 የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት “የመገኘትህና የነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ ምልክቱ ምን ይሆናል?” ብለው በጠየቁት ጊዜ ኢየሱስ መልስ የሰጠው የዚህን የወደፊት ጊዜ ዝርዝር መግለጫ በመስጠት ነበር። (ማቴዎስ ምዕራፍ 24፤ ማርቆስ ምዕራፍ 13፤ ሉቃስ ምዕራፍ 21፤ በተጨማሪም 2 ጢሞቴዎስ 3:1-5ንና ራእይ ምዕራፍ 6ን ተመልከቱ።) ይህ ምልክት በችግር የተሞላ ዘመንን በዝርዝር እንደሚገልጽ ሥዕላዊ መግለጫ የሚቆጠር ነው። በአንድ የተወሰነ አካባቢ ብቻ ሳይሆን በመላው ምድር ዙሪያ በሚፈጸሙ ዓለም አቀፍ ጦርነቶች፣ እየጨመረ በሚሄድ ወንጀል፣ በቤተሰብ ኑሮ መበላሸት፣ ወረርሽኝ በሆኑ በሽታዎች፣ በረሀብና በምድር መንቀጥቀጦች ተለይቶ የሚታወቅ ጊዜ ነው። ታዲያ እንዲህ ያለ ሁኔታ ተፈጽሞአልን? እያንዳንዱ ቀን ባለፈ ቁጥር የ20ኛው መቶ ዘመን ኢየሱስ ከሰጠው መግለጫ ጋር ፍጹም በሆነ ሁኔታ እንደሚስማማ ይረጋግጣል።
10 የታሪክ ጸሐፊዎች 1914 የሰው ልጅ ታሪክ አዲስ ምዕራፍ የተከፈተበት፣ ከእነዚህ ችግሮች ውስጥ ብዙዎቹ ከቁጥጥር ውጭ መውጣትና በምድር አቀፍ ደረጃ መባባስ የጀመሩበት፣ የዓለም አቅጣጫ የተለወጠበት ዓመት እንደሆነ ይስማማሉ። አዎ፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ፍጻሜ በመሆን የተከሰቱት ገሐድ የዓለም ሁኔታዎች በሙሉ የሚያመለክቱት 1914 ኢየሱስ በሰማይ ንጉሥ ሆኖ መግዛት የጀመረበት ዓመት መሆኑን ነው። በተጨማሪም በዳንኤል ምዕራፍ 4 ላይ ያለ አንድ ትንቢት ይኸው 1914 በይሖዋ የተሾመው ንጉሥ መግዛት የሚጀምርበት ዓመት መሆኑን እንድንገነዘብ የሚያስችለን በዘመን አቆጣጠር ላይ የተመሠረተ ማስረጃ ይሰጠናል።b
የመከራ ዘመን የሆነው ለምንድን ነው?
11, 12. (ሀ) አንዳንድ ሰዎች ክርስቶስ አሁን በሰማይ በመግዛት ላይ እንዳለ ለማመን የሚያዳግታቸው ለምንድን ነው? (ለ) ኢየሱስ ንጉሥ ሆኖ ዘውድ ከጫነ ወዲህ የሆነውን እንዴት ልንገልጽ እንችላለን?
11 ይሁን እንጂ አንዳንድ ሰዎች ‘መሲሕ በሰማይ ላይ ሆኖ መግዛት ከጀመረ ዓለም በጣም በመከራ የተሞላው ለምንድን ነው? አገዛዙ ውጤት አልባ ነው ማለት ነውን?’ ብለው ይጠይቁ ይሆናል። አንድ ምሳሌ ሊረዳን ይችላል። አንዲት አገር በአንድ ክፉ ፕሬዚዳንት ትተዳደራለች እንበል። በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች የጭቆና ሰንሰለቱን በመዘርጋት ብልሹ ሥርዓቱን መሥርቷል። ምርጫ ተካሄደና አንድ ጥሩ ሰው ያሸንፋል። ከዚያ በኋላ ምን ይሆናል? በአንዳንድ ዲሞክራሲያዊ አገሮች እንደደረሰው አዲሱ ፕሬዚዳንት የቃል ኪዳን ሥነ ሥርዓቱን ከመፈጸሙ በፊት ጥቂት የሽግግር ወራት ያልፋሉ። አሁን በዚህ ወቅት እነዚህ ሁለት ሰዎች የሚሠሩት እንዴት ነው? ጥሩው ሰው ወዲያውኑ ከእርሱ በፊት በቦታው የነበረው ፕሬዚዳንት በአገሪቱ በሙሉ የሠራውን ክፋት መንቀፍና ማፈራረስ ይጀምራልን? ከዚህ ይልቅ አዲስ ካቢኔ በማቋቋምና የቀድሞው ፕሬዚዳንት አጭበርባሪ የቅርብ ወዳጆችና የጥቅም ተካፋዮች ከሆኑ ሰዎች ጋር የነበረውን ግንኙነት በማቋረጥ በመጀመሪያ በዋና ከተማዋ ላይ አያተኩርምን? በዚህ መንገድ ወደ ሙሉ ሥልጣኑ በሚወጣበት ጊዜ ንጹሕ በሆነና ብቃት ባለው የሥልጣን መንበር ላይ ሆኖ ሊሠራ ይችላል። መጥፎው ፕሬዚዳንት ግን ከሥልጣን ከመባረሩ በፊት በቀረው አጭር ጊዜ የተቻለውን ያህል ሀብት አግባብ በሌለው መንገድ ከአገሪቱ ለማስወጣት አይጠቀምበትምን?
12 የክርስቶስ ፓሩሲያም ከዚህ ጋር ተመሳሳይ ነው ሊባል ይችላል። ራእይ 12:7-12 እንደሚገልጸው ክርስቶስ በሰማይ ንጉሥ ሆኖ በተሾመበት ጊዜ የወሰደው የመጀመሪያ እርምጃ ሰይጣንንና አጋንንቱን ከሰማይ መወርወርና የጽንፈ ዓለማዊውን መስተዳድር መንበር ማጽዳት ነበር። ሰይጣን ይህ ለረዥም ጊዜ ሲጠበቅ የቆየ ሽንፈት ሲደርስበት ክርስቶስ በዚህች ምድር ላይ ሙሉ ሥልጣን ከመያዙ በፊት በቀረው አጭር ጊዜ ምን ያደርጋል? ምግባረ ብልሹ እንደሆነው ፕሬዚዳንት ከዚህ አሮጌ ዓለም የተቻለውን ያህል ብዙ ነገር ለማግኘት ይጥራል። የሚፈልገው ገንዘብ አይደለም። የሚፈልገው የሚከተሉትን ሰዎች ሕይወት ነው። የተቻለውን ያህል ብዙ ሰዎችን ከይሖዋና በመግዛት ላይ ካለው ንጉሥ ለማራቅ ይፈልጋል።
13. ቅዱሳን ጽሑፎች የክርስቶስ አገዛዝ ሲጀምር በዚህ ምድር ላይ ችግር እንደሚኖር የሚያሳዩት እንዴት ነው?
13 እንግዲያውስ የመሢሑ አገዛዝ የሚጀምርበት ጊዜ “ለምድር ወዮ” የሚሆንበት ጊዜ መሆኑ ምንም አያስደንቅም። (ራእይ 12:12) በተመሳሳይም መዝሙር 110:1, 2, 6 መሢሑ መግዛት የሚጀምረው ‘በጠላቶቹ መካከል’ እንደሆነ ይገልጻል። ‘አሕዛብን’ ከማንኛውም የሰይጣን ዓለም ብልሹ ሥርዓት ገጽታዎች ጋር ሙሉ በሙሉ ደቁሶ የሚያጠፋው ከዚህ በኋላ ነው።
መሢሑ ምድርን በሚገዛበት ጊዜ
14. መሢሑ የሰይጣንን ክፉ የነገሮች ሥርዓት ካጠፋ በኋላ ምን ሊያደርግ ይችላል?
14 መሢሐዊው ንጉሥ ኢየሱስ ክርስቶስ የሰይጣንን ዓለምና ደጋፊዎቹን በሙሉ ካጠፋ በኋላ የሺህ ዓመት ግዛቱ መለያ ባሕርያት የሚሆኑትን አስደናቂ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችን ለመፈጸም በሚያስችለው ሁኔታ ላይ ይሆናል። ኢሳይያስ 11:1-10 መሢሑ ምን ዓይነት ገዢ እንደሚሆን እንድንገነዘብ ይረዳናል። ቁጥር 2 “የእግዚአብሔር [የይሖዋ አዓት] መንፈስ፣ . . . የጥበብና የማስተዋል መንፈስ፣ የምክርና የኃይል መንፈስ” እንደሚኖረው ይነግረናል።
15. በመሢሐዊው ግዛት ‘የኃይል መንፈስ’ ምን ትርጉም ይኖረዋል?
15 በኢየሱስ ግዛት ‘የኃይል መንፈስ’ ምን ሊያከናውን እንደሚችል አስቡት። በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ተአምራት ለማድረግ የሚያስችል ከይሖዋ የተቀበለው አስደናቂ ኃይል ነበረው። በተአምር በሚፈውስበት ጊዜ “እወዳለሁ!” በማለት ሰዎችን ለመርዳት ያለውን ልባዊ ፍላጎት አሳይቷል። (ማቴዎስ 8:3) ነገር ግን በዚያን ጊዜ የፈጸማቸው ተአምራት በሰማይ በሚገዛበት ጊዜ ከሚያደርጋቸው ነገሮች ጋር ሲወዳደሩ በጣም አነስተኞች ናቸው። ኢየሱስ በመላው ምድር ላይ ተአምራት ይሠራል! ሕመምተኞች፣ ዕውሮች፣ ደንቆሮዎች፣ ሽባዎችና አንካሶች ዘላቂ ፈውስ ያገኛሉ። (ኢሳይያስ 35:5, 6) ለሁሉ ሰው በእኩልነት የሚዳረስ የተትረፈረፈ ምግብ ስለሚኖር ረሀብ ለዘላለም ይጠፋል። (መዝሙር 72:16) አምላክ ሊያስታውሳቸው የሚፈልጋቸው በመቃብር ውስጥ የሚገኙ ቁጥር ሥፍር የሌላቸው ሰዎችስ? የኢየሱስ ‘ኃያልነት’ እነሱን የማስነሳት ኃይሉንና ለእያንዳንዳቸውም በገነት ላይ ለዘላለም የመኖር አጋጣሚ መስጠትን ይጨምራል! (ዮሐንስ 5:28, 29) ሆኖም መሢሐዊው ንጉሥ ይህ ሁሉ ኃይል እያለውም እንኳን ምንጊዜም ፍጹም ትሑት ነው። “ይሖዋን በመፍራት ደስታ” የሚያገኝ ነው።—ኢሳይያስ 11:3
16. መሢሐዊው ንጉሥ ምን ዓይነት ዳኛ ይሆናል? ይህስ ከሰብአዊ ዳኞች ጋር የሚነፃፀረው እንዴት ነው?
16 በተጨማሪም ይህ ንጉሥ ፍጹም ዳኛ ይሆናል። “ዓይኑ እንደምታይ አይፈርድም፣ ጆሮውም እንደምትሰማ አይበይንም።” ባለፉት ዘመናትም ይሁን በአሁኑ ጊዜ እንዲህ ተብሎ ሊነገርለት የሚችል ሰብአዊ ዳኛ ማን ነው? በጣም አመዛዛኝ ነው የሚባለው ሰው እንኳን ቢሆን የሚፈርደው ባለው ጥበብ ወይም ማስተዋል በመጠቀም በሚያየውና በሚሰማው መሠረት ነው። በመሆኑም የዚህ አሮጌ ዓለም ዳኞችና ከተራው ሕዝብ መካከል የሚመረጡ የፍርድ ኮሚቴዎች በአፈ ጮሌነትና በሚቀርቡ የሐሰት ምክንያት አሰጣጦች፣ በሸንጎ ተዋናዮች ወይም እርስ በርስ በሚጋጩ ማስረጃዎች ስሜታቸው ሊሳብ ወይም ሊደለሉ ይችላሉ። ብዙውን ጊዜ ውጤታማ መከላከያ ማቅረብ የሚችሉት ሀብታሞችና ሥልጣን ያላቸው ሰዎች ስለሆኑ በሐቅ ሲታይ ፍትሕን በሀብታቸው ወይም በሥልጣናቸው ይገዛሉ። በመሢሐዊው ንጉሥ ግዛት ግን እንዲህ አይደለም! እርሱ ልብን ያነባል። እሱ ሳያውቀው የሚቀር ነገር የለም። ፍቅርና ምሕረትን አጣምሮ የሚይዝ ፍትሕ በገንዘብ የሚገዛ ነገር አይሆንም። ምንጊዜም የሚሠፍን ፍትሕ ይኖራል።—ኢሳይያስ 11:3-5
አገዛዙ አንተን የሚነካህ እንዴት ነው?
17, 18. (ሀ) በኢሳይያስ 11:6-9 ላይ ስለ ሰው ልጅ መጪ ጊዜ ምን ብሩሕ መግለጫ ተስሏል? (ለ) ይህ ትንቢት በመጀመሪያ ደረጃ የሚሠራው ለእነማን ነው? ለምንስ? (ሐ) ይህ ትንቢት ቃል በቃል ፍጻሜም የሚኖረው እንዴት ነው?
17 የመሢሑ አገዛዝ በተገዢዎቹ ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ እንዳለው መረዳት ይቻላል። ሰዎችን የሚለውጥ አገዛዝ ነው። ኢሳይያስ 11:6-9 ይህ ዓይነቱ ለውጥ የቱን ያህል ሠፊ እንደሆነ ይገልጻል። ይህ ትንቢት እንደ ድብ፣ ተኩላ፣ ነብር፣ አንበሳ፣ እፉኝት የመሳሰሉት ሌሎች እንስሳትን በማደን የሚኖሩ አደገኛ እንስሳት ከማይጎዱት የቤት እንስሳት ጋር፣ እንዲያውም ከልጆች ጋርም ሳይቀር አብረው ሲሆኑ የሚያሳይ ልብን የሚነካ ሥዕል ያሳያል። ሌሎች እንስሳትን በማደን የሚኖሩት እንስሳት ምንም ዓይነት ጉዳት የማያስከትሉ ይሆናሉ። ለምን? ቁጥር 9 “በተቀደሰው ተራራዬ ሁሉ ላይ አይጎዱም አያጠፉምም፤ ውኃ ባሕርን እንደሚከድን ምድር እግዚአብሔርን [ይሖዋን አዓት] በማወቅ ትሞላለችና” በማለት መልሱን ይሰጠናል።
18 በእርግጥ “ይሖዋን ማወቅ” ቃል በቃል በእንስሳት ላይ ምንም ውጤት ሊኖረው አይችልም። ስለዚህ እነዚህ ጥቅሶች በመጀመሪያ ደረጃ በሰዎች ላይ የሚፈጸሙ መሆን አለባቸው። የመሢሑ አገዛዝ ሰዎችን ስለ ይሖዋና ስለ መንገዶቹ የሚያስተምር፣ ባልንጀሮቻቸው የሆኑትን ሰዎች በሙሉ በፍቅር፣ በአክብሮትና በክብር እንዲይዙ የሚያስተምር ምድር አቀፍ የትምህርት ፕሮግራም ያካሂዳል። በመጪዋ ገነት መሢሑ የሰው ልጆችን ተአምራዊ በሆነ መንገድ በአካልም ሆነ በሥነ ምግባር ወደ ፍጽምና ደረጃ ከፍ ያደርጋቸዋል። ሰብአዊውን ባሕርይ የሚያበላሹና ጎጂ የሆኑ አውሬ መሰል ጠባዮች ይወገዳሉ። በመጨረሻም የሰው ልጅ ቃል በቃል ከአውሬዎች ጋር በሰላም ይኖራል!—ከዘፍጥረት 1:28 ጋር አወዳድሩት።
19. የመሢሑ አገዛዝ በእነዚህ የመጨረሻ ቀኖች የሰዎችን ሕይወት የሚነካው እንዴት ነው?
19 ይሁንና መሢሑ አሁንም በመግዛት ላይ መሆኑን አስታውሱ። አሁንም እንኳን የመንግሥቱ ተገዢዎች ኢሳይያስ 11:6-9ን በመፈጸም በሰላም አብረው መኖርን እየተማሩ ነው። ከዚህም በላይ ወደ 80 ለሚጠጉ ዓመታት ኢየሱስ “በዚያ ቀን እንዲህ ይሆናል፤ ለአሕዛብ ምልክት ሊሆን የቆመውን የእሴይን ሥር አሕዛብ ይፈልጉታል፤ ማረፊያውም የተከበረ ይሆናል” የሚለውን የኢሳይያስ 11:10ን ትንቢት ሲፈጽም ቆይቷል። ከሁሉም ብሔራት የተውጣጡ ሰዎች ወደ መሲሑ ዘወር እያሉ ነው። ለምን? ምክንያቱም መግዛት ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ “ምልክት ሊሆን ስለቆመ” ነው። ከላይ በተገለጸው ሠፊ የማስተማር ፕሮግራሙ አማካኝነት በዓለም ዙሪያ መገኘቱን ሲያሳውቅ ቆይቷል። እንዲያውም የዚህ አሮጌ ሥርዓት ፍጻሜ ከመምጣቱ በፊት የሚከናወነው ዓለም አቀፍ የስብከት ሥራ የመገኘቱ ጉልህ ምልክት እንደሚሆን ተንብዮአል።—ማቴዎስ 24:14
20. የመሢሑ አገዛዝ ተገዢዎች ማስወገድ ያለባቸው ምን ዓይነት አመለካከት ነው? ለምንስ?
20 ስለዚህ ክርስቶስ በንጉሣዊ ሥልጣን መገኘቱ በሃይማኖታዊ ሊቃውንት መካከል ምሁራዊ ክርክር የሚደረግበት የተራቀቀ ባሕረ ሐሳብ አይደለም። ኢሳይያስ እንደተነበየው አገዛዙ እዚችው ምድር ላይ ያሉ ሰዎችን ሕይወት የሚነካና የሚለውጥ ነው። ኢየሱስ የመንግሥቱ ተገዢዎች የሚሆኑ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ከዚህ ብልሹ የዓለም ሥርዓት መርቶ አውጥቷል። አንተስ እንዲህ ዓይነቱ ተገዢ ነህን? ከሆንክ ለገዢያችን የሚገባውን ትጋትና ደስታ በማሳየት አገልግል! እርግጥ ነው፣ ለመድከምና “የመምጣቱ የተስፋ ቃል ወዴት ነው?” ከሚለው የዓለም የጥርጣሬ ጩኸት ጋር ለመተባበር በጣም ቀላል ነው። (2 ጴጥሮስ 3:4) ነገር ግን ኢየሱስ ራሱ እንደተናገረው “እስከ መጨረሻው የሚጸና ግን እርሱ ይድናል።”—ማቴዎስ 24:13
21. ሁላችንም ለመሢሐዊው ተስፋ ያለንን አድናቆት ከፍ ልናደርግ የምንችለው እንዴት ነው?
21 እያንዳንዱ ቀን ባለፈ ቁጥር መገኘቱን ለመላው ዓለም እንዲያሳይ ይሖዋ ልጁን ወደሚያዝበት ታላቅ ቀን እየቀረብን እንሄዳለን። በዚያ ቀን ላይ ያለህ ተስፋ እንዲመነምን ፈጽሞ አትፍቀድ። የኢየሱስን መሲሕነትና በመግዛት ላይ ያለ ንጉሥ በመሆን ያሉትን ብቃቶች አሰላስል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለሠፈረው ታላቅ መሢሐዊ ተስፋ አመንጪና ወጣኝ ስለሆነው ስለ ይሖዋ አምላክም በጥልቅ አስብ። እንዲህ ስታደርግም ሐዋርያው ጳውሎስ “የእግዚአብሔር ባለጠግነትና ጥበብ እውቀቱም እንዴት ጥልቅ ነው!” ብሎ በጻፈ ጊዜ እንደተሰማው ዓይነት ስሜት እንደሚሰማህ አያጠራጥርም።—ሮሜ 11:33
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በ1864 የሃይማኖት ምሁር የሆኑት አር ጎቬት ጉዳዩን እንደሚከተለው በማለት ገልጸው ነበር፦ “ይህ ለእኔ በጣም ግልጽ ይመስለኛል። የመገኘቱ ምልክት መሰጠቱ ምሥጢር መሆኑን ያሳያል። የምናየው ነገር መገኘቱን እንድናውቅ ምልክት አያስፈልገንም።”
b ለዝርዝሩ “መንግሥትህ ትምጣ” የሚለውን መጽሐፍ ገጽ 133-9 ተመልከቱ።
እንዴት ብላችሁ ትመልሳላችሁ?
◻ ክርስቶስ የሚመለሰው በምን ሁኔታ ነው?
◻ የክርስቶስ ፓሩሲያ የማይታይና ለተወሰነ ጊዜ የሚቆይ መሆኑን እንዴት እናውቃለን?
◻ የክርስቶስ መገኘት የጀመረው መቼ ነው? ይህንንስ እንዴት እናውቃለን?
◻ መሢሑ ምን ዓይነት ሰማያዊ ገዢ ነው?
◻ የክርስቶስ አገዛዝ የተገዢዎቹን ሕይወት የሚነካው በምን መንገዶች ነው?
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ እንደሚመለስ የሚገልጸው ተስፋ ለታማኝ ሐዋርያቱ ትልቅ ትርጉም ነበረው
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ ከሰማይ ላይ ሆኖ ሲገዛ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተአምር ያደርጋል
[ምንጭ]
Earth: Based on NASA photo