የኢየሱስ መምጣት ወይስ የኢየሱስ መገኘት?
“የመገኘትህና የነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ ምልክት ምን ይሆናል?”—ማቴዎስ 24:3 አዓት
1. በኢየሱስ አገልግሎት ውስጥ ጥያቄዎች ምን ሚና ነበራቸው?
ኢየሱስ ጥያቄዎችን ጥበብ በተሞላበት መንገድ በመጠቀም አድማጮቹ እንዲያስቡና ነገሮችን ከተለያዩ አቅጣጫዎች እንዲመለከቱ ያደርግ ነበር። (ማርቆስ 12:35-37፤ ሉቃስ 6:9፤ 9:20፤ 20:3, 4) ከዚህም በተጨማሪ ለጥያቄዎች መልስ በመስጠቱ አመስጋኞች ልንሆን እንችላለን። እሱ የሰጣቸው መልሶች በሌላ መንገድ ልናውቃቸው ወይም ልንረዳቸው በማንችላቸው እውነቶች ላይ ብርሃን ይፈነጥቃሉ።—ማርቆስ 7:17-23፤ 9:11-13፤ 10:10-12፤ 12:18-27
2. አሁን በየትኛው ጥያቄ ላይ ትኩረት ማድረግ ይኖርብናል?
2 በማቴዎስ 24:3 ላይ ኢየሱስ መልስ ከሰጠባቸው እጅግ አስፈላጊ የሆኑ ጥያቄዎች አንዱን እናገኛለን። ኢየሱስ ምድራዊ ሕይወቱን ሊያጠናቅቅ በተቃረበበት ወቅት የኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ እንደሚጠፋ አስጠንቅቆ ነበር። ይህም የአይሁድ ሥርዓት ፍጻሜን ያመለክት ነበር። የማቴዎስ ዘገባ እንዲህ በማለት ያክላል፦ “እርሱም በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ተቀምጦ ሳለ፣ ደቀ መዛሙርቱ ለብቻቸው ወደ እርሱ ቀርበው፦ ‘ንገረን፣ እነዚህ ነገሮች መቼ ይሆናሉ? የመገኘትህና [“የመምጣትህና፣” የ1954 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ እትም] የነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ ምልክት ምን ይሆናል?’ ብለው ጠየቁት።”—ማቴዎስ 24:3 አዓት
3, 4. በማቴዎስ 24:3 ላይ የሚገኘውን ቁልፍ ቃል በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱሶች የያዟቸው ትርጉሞች ምን መሠረታዊ ልዩነት ይታይባቸዋል?
3 በሚልዮን የሚቆጠሩ የመጽሐፍ ቅዱስ አንባብያን ‘ደቀ መዛሙርቱ ይህን ጥያቄ ያቀረቡት ለምንድን ነው? የኢየሱስ መልስ እኛን ሊነካን የሚገባውስ እንዴት ነው?’ በማለት ራሳቸውን ይጠይቃሉ። ኢየሱስ በሰጠው መልስ ላይ የቅጠሎች መለምለም በጋ “እንደ ቀረበ” እንደሚያሳይ ተናግሯል። (ማቴዎስ 24:32, 33) ስለዚህ ሐዋርያት የጠየቁት የኢየሱስን “መምጣት” የሚጠቁም ምልክት ማለትም ዳግም የሚመጣበት ጊዜ መቃረቡን የሚያረጋግጥ ምልክት ነው በማለት ብዙ አብያተ ክርስቲያናት ያስተምራሉ። ኢየሱስ ‘በሚመጣበት’ ጊዜ ክርስቲያኖችን ወደ ሰማይ በመውሰድ ዓለምን ያጠፋል ብለው ያምናሉ። ይህ ትክክል ነው ብለህ ታምናለህን?
4 የአዲሲቱ ዓለም የቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉምን ጨምሮ አንዳንድ መጽሐፍ ቅዱሶች “መምጣት” ብለው ከመተርጎም ይልቅ “መገኘት” በሚለው ቃል ይጠቀማሉ። ደቀ መዛሙርቱ ያቀረቡት ጥያቄና ኢየሱስ የሰጠው መልስ አብያተ ክርስቲያናት ከሚያስተምሩት ነገር የተለየ ይሆንን? በእርግጥ ጥያቄው ምን ነበር? ኢየሱስ የሰጠውስ መልስ ምን ነበር?
የጠየቁት ምን ነበር?
5, 6. ሐዋርያት በማቴዎስ 24:3 ላይ የምናነበውን ጥያቄ ባቀረቡበት ወቅት ስለ ነበራቸው አስተሳሰብ ምን ብለን ልንደመድም እንችላለን?
5 ኢየሱስ ስለ ቤተ መቅደሱ ከተናገረው አንፃር ሲታይ ደቀ መዛሙርቱ ‘የመገኘቱን [ወይም ‘የመምጣቱን’]ና የነገሮች ሥርዓት መደምደሚያን [ቃል በቃል “ዘመን”] ምልክት’ ሲጠይቁ በአእምሯቸው ይዘውት የነበረው የአይሁድ ሥርዓትን ሳይሆን አይቀርም።—በ1 ቆሮንቶስ 10:11 ኪንግ ጄምስ ቨርሽን እና በገላትያ 1:4 ላይ ከሚገኘው “ዓለም” ከሚለው ቃል ጋር አወዳድር።
6 በዚህ ጊዜ ሐዋርያት ስለ ኢየሱስ ትምህርቶች የነበራቸው ማስተዋል አነስተኛ ነበር። ቀደም ሲል ‘የእግዚአብሔር መንግሥት ፈጥኖ የሚገለጥ’ መስሏቸው ነበር። (ሉቃስ 19:11፤ ማቴዎስ 16:21-23፤ ማርቆስ 10:35-40) በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ይህን ውይይት ካደረጉ በኋላም እንኳን ኢየሱስ በዚያ ወቅት የእስራኤልን መንግሥት ይመልስ እንደሆነ ጠይቀውታል። ይህን ጥያቄ ያቀረቡት በመንፈስ ቅዱስ ከመቀባታቸው በፊት ነበር።—ሥራ 1:6
7. ሐዋርያት ኢየሱስን ወደፊት ስለሚኖረው ሚና የጠየቁት ለምን ነበር?
7 ሆኖም ይህን ጥያቄ ከማቅረባቸው ከጥቂት ጊዜ በፊት “ገና ጥቂት ጊዜ ብርሃን ከእናንተ ጋር ነው። . . . ብርሃን ሳለላችሁ ተመላለሱ” ስላላቸው ከእነሱ እንደሚለይ ያውቁ ነበር። (ዮሐንስ 12:35፤ ሉቃስ 19:12-27) ስለዚህ ‘ኢየሱስ ከእኛ ተለይቶ የሚሄድ ከሆነ ሲመለስ ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው?’ የሚል ጥያቄ ተፈጥሮባቸው መሆን አለበት። ኢየሱስ መሲሕ ሆኖ በመጣበት ወቅት ብዙዎች አላወቁትም ነበር። አንድ ዓመት ካለፈ በኋላም ቢሆን መሲሕ የሚያደርገውን ሁሉ ይፈጽማል ወይስ አይፈጽምም በሚለው ጉዳይ ላይ አንዳንድ ጥያቄዎች ተነሥተው ነበር። (ማቴዎስ 11:2, 3) ስለዚህ ሐዋርያት ስለ ወደፊቱ ጊዜ የሚጠይቁበት ምክንያት ነበራቸው። ይሁን እንጂ አሁንም ቢሆን የጠየቁት ፈጥኖ የሚመጣበትን ጊዜ ምልክት ነበር ወይስ ሌላ ነገር?
8. ሐዋርያት ከኢየሱስ ጋር የተነጋገሩት በየትኛው ቋንቋ ሳይሆን አይቀርም?
8 ራስህን በደብረ ዘይት ተራራ ላይ የተደረገውን ውይይት በማዳመጥ ላይ እንደነበረ ወፍ አድርገህ አስብ። (ከመክብብ 10:20 ጋር አወዳድር።) ምናልባት ኢየሱስና ሐዋርያቱ በዕብራይስጥ ቋንቋ ሲነጋገሩ ሰምተህ ሊሆን ይችላል። (ማርቆስ 14:70፤ ዮሐንስ 5:2፤ 19:17, 20፤ ሥራ 21:40) ሆኖም ግሪክኛም ሳያውቁ አይቀርም።
ማቴዎስ በግሪክኛ የጻፈው ነገር
9. አብዛኞቹ ዘመናዊ የማቴዎስ ወንጌል ትርጉሞች የተመሠረቱት በምን ላይ ነው?
9 በሁለተኛው መቶ ዘመን እዘአ የተጻፉ የታሪክ መዛግብት ማቴዎስ ወንጌሉን በመጀመሪያ የጻፈው በዕብራይስጥ ቋንቋ እንደሆነ ያመለክታሉ። ከሁኔታው ለመረዳት እንደሚቻለው ቆየት ብሎ በግሪክኛ ሳይጽፈው አልቀረም። በዘመናችን ብዙ ጥንታዊ ግሪክኛ የእጅ ጽሑፎች የሚገኙ ሲሆን የማቴዎስ ወንጌልን በጊዜያችን ወዳሉ ቋንቋዎች ለመተርጎም መሠረት ሆነው አገልግለዋል። ማቴዎስ በደብረ ዘይት ተራራ የተደረገውን ውይይት አስመልክቶ የጻፈው ነገር ምንድን ነው? ደቀ መዛሙርቱ የጠየቁትንና ኢየሱስ ሐሳብ የሰጠበትን “መምጣት” ወይም “መገኘት” በተመለከተ የጻፈው ነገር ምንድን ነው?
10. (ሀ) ማቴዎስ “መምጣት” ለሚለው ቃል ብዙውን ጊዜ ይጠቀምበት የነበረው የግሪክኛ ቃል የትኛው ነው? ይህ ቃል ምን ትርጉሞች አሉት? (ለ) ትኩረታችንን የሚስበው ሌላ የግሪክኛ ቃል የትኛው ነው?
10 በመጀመሪያዎቹ የማቴዎስ ወንጌል 23 ምዕራፎች ውስጥ “መምጣት” የሚል ትርጉም ያለውን ኤርኮማይ የተባለ የተለመደ የግሪክኛ ግሥ ከ80 ጊዜ በላይ ተጠቅሶ እናገኘዋለን። በዮሐንስ 1:48 ላይ እንደተገለጸው ቃሉ ብዙውን ጊዜ መቅረብን የሚያመለክት ሐሳብ ያስተላልፋል። ጥቅሱ ‘ኢየሱስ ናትናኤል ወደ እርሱ ሲመጣ አይቶ’ ሲል ይገልጻል። ኤርኮማይ የተባለው ግሥ እንደ አገባቡ “መምጣት፣” “መሄድ፣” “መድረስ” ወይም “በመንገድ ላይ መሆን” የሚል ትርጉም ሊኖረው ይችላል። (ማቴዎስ 2:8, 11፤ 8:28፤ ዮሐንስ 4:25, 27, 45፤ 20:4, 8፤ ሥራ 8:40፤ 13:51) ሆኖም በማቴዎስ 24:3, 27, 37, 39 ላይ ማቴዎስ በወንጌሎች ላይ በሌላ በማንኛውም ቦታ የማይገኘውን ፓሩስያ የተባለ ለየት ያለ ቃል ተጠቅሟል። መጽሐፍ ቅዱስን በመንፈሱ አነሳሽነት ያስጻፈው አምላክ እንደመሆኑ መጠን ማቴዎስ ወንጌሉን በግሪክኛ በሚጽፍበት ወቅት በእነዚህ ጥቅሶች ላይ ይህን የግሪክኛ ቃል እንዲመርጥ የገፋፋው ለምን ነበር? ይህ ቃል ምን ማለት ነው? ይህን ማወቅ የሚኖርብን ለምንድን ነው?
11. (ሀ) የፓሩስያ ትርጉም ምንድን ነው? (ለ) ጆሴፈስ በጽሑፎቹ ውስጥ ፓሩስያን እንዴት እንደተጠቀመበት የሚጠቁሙት ምሳሌዎች ስለ ፓሩስያ ያለን ግንዛቤ ትክክለኛ መሆኑን የሚያረጋግጡት እንዴት ነው? (የግርጌ ማስታወሻውን ተመልከት።)
11 ነጥቡን ግልጽ በሆነ መንገድ ለማስቀመጥ ፓሩስያ ማለት “መገኘት” ማለት ነው። የቫይን ኤክስፖዚተሪ ዲክሽነሪ ኦቭ ኒው ቴስታመንት ዎርድስ እንዲህ ይላል፦ “ፓሩስያ . . . ቃል በቃል ሲተረጎም መገኘት ማለት ነው፤ ፓራ ማለት ጋር ማለት ሲሆን ኦስያ ማለት መሆን (ሆነ የሚል ትርጉም ካለው ኤይሚ ከተባለው ቃል የመጣ ነው) ማለት ነው፤ ቃሉ መምጣትንም ሆነ ከመጡ በኋላ አብሮ መሆንን ያመለክታል። ለምሳሌ ያህል በአንድ የፓፒረስ ደብዳቤ ላይ አንዲት ወይዘሮ ከንብረቷ ጋር የሚዛመዱ አንዳንድ ጉዳዮችን ለመከታተል የግድ በዚያ ቦታ ፓሩስያ [መገኘት] እንደሚኖርባት ተናግራለች።” ሌሎች መዝገበ ቃላቶች ፓሩስያ ‘የአንድ ገዢ ጉብኝትን’ እንደሚያመለክት ይገልጻሉ። ስለዚህ መምጣትን ብቻ ሳይሆን ከመጡ በኋላ ያለውን የቆይታ ጊዜ ጭምር የሚያመለክት ነው። በሐዋርያት ዘመን ይኖር የነበረው አይሁዳዊው ታሪክ ጸሐፊ ጆሴፈስ ፓሩስያን በዚህ መንገድ መጠቀሙ ትኩረት የሚስብ ነው።a
12. መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ የፓሩስያን ትርጉም ትክክለኛነት ለማረጋገጥ የሚረዳን እንዴት ነው?
12 “መገኘት” የሚለው ትርጉም በጥንታዊ ሥነ ጽሑፎች በግልጽ የሰፈረ ቢሆንም ክርስቲያኖች በተለይ ለማወቅ የሚፈልጉት የአምላክ ቃል ፓሩስያን እንዴት እንደሚጠቀምበት ነው። እንደ ጥንታዊ ሥነ ጽሑፎች ሁሉ የአምላክ ቃልም ፓሩስያን መገኘት ብሎ ተርጉሞታል። ይህን ከጳውሎስ መልእክቶች ለመረዳት እንችላለን። ለምሳሌ ያህል “ሁልጊዜ እንደ ታዘዛችሁ፣ በእናንተ ዘንድ በመኖሬ [“ስገኝ፣” አዓት] ብቻ ሳይሆን ይልቁን አሁን ስርቅ፣ በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ የራሳችሁን መዳን ፈጽሙ” በማለት ለፊልጵስዩስ ክርስቲያኖች ጽፎላቸዋል። በተጨማሪም “[በእነሱ] ዘንድ እንደ ገና በመገኘቱ [ፓሩስያ]” ሊደሰቱ እንደሚችሉ ተናግሯል። (ፊልጵስዩስ 1:25, 26 አዓት፤ 2:12 ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን) ሌሎች ትርጉሞች “እንደገና ከእናንተ ጋር በመሆኔ” (ዌይማውዝ፤ ኒው ኢንተርናሽናል ቨርዥን)፤ “እንደገና ከእናንተ ጋር ስሆን” (ጀሩሳሌም ባይብል፤ ኒው ኢንግሊሽ ባይብል)፤ እና “እንደገና በመካከላችሁ ስሆን” ይላሉ። (ትዌንቲዝ ሴንቸሪ ኒው ቴስታመንት) በ2 ቆሮንቶስ 10:10, 11 [አዓት] ላይ ጳውሎስ በቦታው ‘በአካል ሲገኝ’ ያለውን ሁኔታ ‘ርቆ ሳለ’ ከሚኖረው ሁኔታ ጋር አነጻጽሮታል። ጳውሎስ በእነዚህ ምሳሌዎች ላይ የተናገረው መድረሱን ወይም መምጣቱን አስመልክቶ እንዳልሆነ ግልጽ ነው፤ ፓሩስያ የተባለውን ቃል የተጠቀመበት መገኘት የሚለውን ትርጉም በሚያስተላልፍ መንፈስ ነው።b (ከ1 ቆሮንቶስ 16:17 [አዓት] ጋር አወዳድር።) ታዲያ ስለ ኢየሱስ ፓሩስያ የሚናገሩትን ጥቅሶች በተመለከተ ምን ለማለት ይቻላል? እነዚህ ጥቅሶች “መምጣት” የሚል ትርጉም አላቸው ወይስ ለረጅም ጊዜ መገኘትን ያመለክታሉ?
13, 14. (ሀ) ፓሩስያ ለረጅም ጊዜ የሚቆይ ነገርን ያመለክታል የሚል ድምዳሜ ላይ መድረስ የሚኖርብን ለምንድን ነው? (ለ) የኢየሱስ ፓሩስያ ርዝመት ምን ያህል ነው ሊባል ይችላል?
13 በጳውሎስ ዘመን የነበሩት በመንፈስ የተቀቡ ክርስቲያኖች ስለ ኢየሱስ ፓሩስያ ለማወቅ ይፈልጉ ነበር። ይሁን እንጂ ጳውሎስ ‘ከአሳባቸው ቶሎ እንዳይናወጡ’ አስጠንቅቋቸው ነበር። የሕዝበ ክርስትናን የቀሳውስት ቡድን የሚያመለክተው “የዓመፅ ሰው” በመጀመሪያ መገለጥ ነበረበት። ጳውሎስ የዓመፅ ሰው “መምጣት [“መገኘት፣” አዓት] በተአምራት ሁሉና በምልክቶች . . . እንደ ሰይጣን አሠራር ነው” ሲል ጽፏል። (2 ተሰሎንቄ 2:2, 3, 9) በግልጽ ለመረዳት እንደሚቻለው “የዓመፅ ሰው” ፓሩስያ ወይም መገኘት ለጥቂት ጊዜያት ብቻ የሚቆይ አልነበረም፤ የማታለያ ምልክቶቹ የሚታዩበትን ረጅም ጊዜ የሚሸፍን ይሆናል። ይህ ከፍተኛ ትርጉም የሚኖረው ለምንድን ነው?
14 ከዚያ በፊት የሚገኘውን የሚከተለውን ጥቅስ ተመልከት፦ “በዚያም ጊዜ ጌታ ኢየሱስ በአፉ መንፈስ የሚያጠፋው፣ ሲመጣም [“በሚገኝበት ወቅት፣” አዓት] በመገለጡ የሚሽረው ዓመፀኛ ይገለጣል።” “የዓመፅ ሰው” መገኘት ለተወሰነ ዘመን እንደሚቆይ ሁሉ የኢየሱስ መገኘትም ለተወሰነ ጊዜ ከቆየ በኋላ “የጥፋት ልጅ” የሆነው የዓመፅ ሰው በሚጠፋበት ወቅት ወደ ፍጻሜው ላይ ይደርሳል።—2 ተሰሎንቄ 2:8
የዕብራይስጥ ቋንቋ አማራጮች
15, 16. (ሀ) ማቴዎስ ወደ ዕብራይስጥ ቋንቋ በተተረጎመባቸው ብዙ ትርጉሞች ውስጥ የተሠራበት ቃል የትኛው ነው? (ለ) ቦህ በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የተሠራበት እንዴት ነው?
15 ከዚህ በፊት እንደተገለጸው ማቴዎስ ወንጌሉን በመጀመሪያ የጻፈው በዕብራይስጥ ሳይሆን አይቀርም። ስለዚህ በማቴዎስ 24:3, 27, 37, 39 ላይ የተጠቀመው የዕብራይስጥ ቃል የትኛው ነው? ማቴዎስ በዘመናዊ የዕብራይስጥ ቋንቋ የተተረጎመባቸው ትርጉሞች በሐዋርያት ጥያቄም ሆነ በኢየሱስ መልስ ላይ ቦህ በተባለው ግሥ ይጠቀማሉ። ይህም እንደሚከተሉት ያሉ ንባቦች እንዲፈጠሩ ሊያደርግ ይችላል፦ “[የቦህ]ና የነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ ምልክት ምን ይሆናል?” “የኖኅ ዘመን እንደ ነበረ የሰው ልጅ [ቦህ]ም እንዲሁ ይሆናል።” ቦህ ማለት ምን ማለት ነው?
16 ምንም እንኳ የተለያዩ ትርጉሞች ቢኖሩትም ቦህ የተባለው የዕብራይስጥ ግሥ መሠረታዊ ትርጉሙ “መምጣት” የሚል ነው። ቲኦሎጂካል ዲክሽነሪ ኦቭ ዘ ኦልድ ቴስታመንት ‘በዕብራይስጥ ጽሑፎች ውስጥ በብዛት ከሚገኙት ግሦች አንዱ የሆነውና በእነዚህ ጽሑፎች ውስጥ 2,532 ጊዜ ሠፍሮ የሚገኘው ቦህ የተባለው ቃል እንቅስቃሴን ለመግለጽ የሚያገለግል ዋነኛ ግሥ ነው’ ይላል። (ዘፍጥረት 7:1, 13፤ ዘጸአት 12:25፤ 28:35፤ 2 ሳሙኤል 19:30፤ 2 ነገሥት 10:21፤ መዝሙር 65:2፤ ኢሳይያስ 1:23፤ ሕዝቅኤል 11:16፤ ዳንኤል 9:13፤ አሞጽ 8:11) ኢየሱስና ሐዋርያቱ በእንዲህ ዓይነቱ የተለያዩ ትርጉሞች ባሉት ቃል ተጠቅመው ከነበሩ ትርጉሙ አከራካሪ ሊሆን ይችላል። ሆኖም ቦህ በሚለው ቃል ተጠቅመው ነበርን?
17. (ሀ) ዘመናዊ የማቴዎስ የዕብራይስጥ ትርጉሞች ኢየሱስና ሐዋርያቱ የተናገሩትን ቃል በትክክል ላያመለክቱ የሚችሉት ለምንድን ነው? (ለ) ኢየሱስና ሐዋርያቱ በየትኛው ቃል ተጠቅመው ሊሆን እንደሚችል የሚያሳይ ፍንጭ የምናገኘው ከየትኛው ሌላ ምንጭ ነው? ይህ ምንጭ ትኩረታችንን የሚስበው በየትኛው ሌላ ምክንያት ነው? (የግርጌ ማስታወሻውን ተመልከት።)
17 ዘመናዊ የዕብራይስጥ ትርጉሞች ማቴዎስ በዕብራይስጥ የጻፈውን ነገር በትክክል ላያስተላልፉ እንደሚችሉ አስታውስ። ኢየሱስ ከፓሩስያ ትርጉም ጋር የሚስማማ ከቦህ የተለየ ቃል ተጠቅሞ ሊሆን እንደሚችል የተረጋገጠ ነው። ይህን ፕሮፌሰር ጆርጅ ሀዋርድ በ1995 ከጻፉት ሂብሪው ጎስፔል ኦቭ ማቲው ከተባለው መጽሐፍ መረዳት እንችላለን። መጽሐፉ ሼምቶብ ቤን አይሳክ ኢበን ሻፕረት የተባለ በ14ኛው መቶ ዘመን ይኖር የነበረ አይሁዳዊ ሐኪም ክርስትናን በመቃወም በጻፈው ጽሑፍ ላይ የሚያተኩር ነበር። ይህ ጽሑፍ የማቴዎስ ወንጌልን የዕብራይስጥ ጽሑፍ ይዟል። ይህ የማቴዎስ ጽሑፍ በሼምቶብ ዘመን ከላቲን ወይም ከግሪክኛ ቋንቋ የተተረጎመ ሳይሆን በጣም የቆየና በመጀመሪያ በዕብራይስጥ ቋንቋ የተዘጋጀ እንደ ነበር የሚያሳይ ማስረጃ አለ።c በመሆኑም በደብረ ዘይት ተራራ ከተባለው ነገር ጋር በይበልጥ የተቀራረበ ሐሳብ እንድናገኝ ሊረዳን ይችላል።
18. ሼምቶብ የተጠቀመበት ትኩረት የሚስብ የዕብራይስጥ ቃል የትኛው ነው? እሱስ ምን ትርጉም አለው?
18 ሼምቶብ ያዘጋጀው የማቴዎስ ጽሑፍ በማቴዎስ 24:3, 27, 39 ላይ ቦህ የተባለውን ግሥ አይጠቀምም። ከዚህ ይልቅ ከዚህ ጋር ተዛማጅ የሆነውን ቢያህ የተባለ ስም ይጠቀማል። ይህ ስም በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ በሕዝቅኤል 8:5 ላይ ብቻ የሚገኝ ሲሆን እዚህ ቦታ ላይ ‘መግቢያ’ የሚል ትርጉም ተሰጥቶታል። እዚህ ላይ ቢያህ የመምጣትን ድርጊት ከመግለጽ ይልቅ የአንድን ሕንፃ በር ያመለክታል፤ በራፉን ወይም በሩን አልፈህ ስትገባ በሕንፃው ውስጥ ትሆናለህ። በተጨማሪም በሙት ባሕር ውስጥ የተገኙ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆኑ ሃይማኖታዊ ጽሑፎች የክህነታዊ አገልግሎቶች መድረስን ወይም መጀመርን ለማመልከት ብዙውን ጊዜ ቢያህ በሚለው ቃል ይጠቀማሉ። (1 ዜና መዋዕል 24:3-19፤ ሉቃስ 1:5, 8, 23 ተመልከት።) በተጨማሪም በጥንቱ የሶርያ ቋንቋ (ወይም አረማይክ) የተዘጋጀው ፔሺታ በ1986 ወደ ዕብራይስጥ ሲተረጎም በማቴዎስ 24:3, 27, 37, 39 ላይ ቢያህ በሚለው ቃል ተጠቅመዋል። ስለዚህ በጥንት ጊዜያት ቢያህ የተባለው ስም በመጽሐፍ ቅዱስ ከተሠራበት ቦህ ከተባለው ግሥ ትንሽ ለየት ያለ ትርጉም እንደነበረው የሚያሳይ ማስረጃ አለ። ይህ ትኩረታችንን የሚስበው ለምንድን ነው?
19. ኢየሱስና ሐዋርያቱ ቢያህ በሚለው ቃል ተጠቅመው ከነበረ ምን መደምደሚያ ላይ መድረስ እንችላለን?
19 ሐዋርያት ጥያቄ ባቀረቡበት ጊዜም ሆነ ኢየሱስ መልስ በሰጠበት ወቅት ቢያህ በሚለው ስም ተጠቅመው ሊሆን ይችላል። ሌላው ቀርቶ ሐዋርያት በአእምሯቸው ይዘውት የነበረው የኢየሱስን ተመልሶ መምጣት ብቻ ቢሆን እንኳ ክርስቶስ እነሱ ያስቡት ከነበረው የበለጠ ነገር ጨምሮ ለመናገር ቢያህ በሚለው ቃል ተጠቅሞ ሊሆን ይችላል። ኢየሱስ አዲስ ሥራ ለመጀመር የሚመጣ መሆኑን መግለጹ ሊሆን ይችላል፤ ሲመጣ አዲሱን ሥራውን ማከናወን ይጀምራል። ይህ ማቴዎስ ከጊዜ በኋላ ከተጠቀመበት ፓሩስያ ከሚለው ትርጉም ጋር ይመሳሰላል። እንዲህ ዓይነቱ የቢያህ አጠቃቀም ኢየሱስ የሰጠው ጥምር “ምልክት” የእሱን መገኘት ያመለክታል በማለት የይሖዋ ምሥክሮች ከረጅም ጊዜ በፊት ሲያስተምሩት የቆዩትን ትምህርት እንደሚደግፍ ግልጽ ነው።
የመገኘቱን መደምደሚያ መጠበቅ
20, 21. ኢየሱስ የኖኅ ዘመንን በተመለከተ ካቀረበው ሐሳብ ምን ልንማር እንችላለን?
20 የኢየሱስን መገኘት በተመለከተ ያደረግነው ጥናት በኑሯችንና በተስፋችን ላይ ቀጥተኛ ተጽዕኖ ማሳደር ይኖርበታል። ኢየሱስ ተከታዮቹን ነቅተው እንዲጠብቁ አጥብቆ መክሯቸዋል። ምንም እንኳ ብዙ ሰዎች ባያስተውሉትም መገኘቱ ተለይቶ ሊታወቅ የሚችልበትን የሚከተለውን ምልክት ሰጥቷል፦ “የኖኅ ዘመን እንደ ነበረ የሰው ልጅ መምጣት [“መገኘት፣” አዓት] እንዲሁ ይሆናልና። በዚያች ወራት ከጥፋት ውኃ በፊት፣ ኖኅ ወደ መርከብ እስከገባበት ቀን ድረስ፣ ሲበሉና ሲጠጡ ሲያገቡና ሲጋቡም እንደ ነበሩ፣ የጥፋት ውኃም መጥቶ ሁሉን እስከ ወሰደ ድረስ እንዳላወቁ፣ የሰው ልጅ መምጣት [“መገኘት፣” አዓት] ደግሞ እንዲሁ ይሆናል።”—ማቴዎስ 24:37-39
21 በኖኅ ዘመን በነበረው ትውልድ የኖሩት አብዛኞቹ ሰዎች የተለመደውን ኑሯቸውን ብቻ ያሳድዱ ነበር። ኢየሱስ ‘በሰው ልጅ መገኘት’ ጊዜ ተመሳሳይ ነገር እንደሚፈጸም አስቀድሞ ተናግሯል። በኖኅ ዘመን የነበሩት ሰዎች ምንም ነገር እንደማይደርስ ሆኖ ተሰምቷቸው ሊሆን ይችላል። አንተ ግን ምን እንደተፈጸመ በትክክል ታውቃለህ። ረዘም ላሉ ጊዜያት የቆየው ያ ዘመን ተፈጸመ፤ ‘የጥፋት ውኃ መጥቶ ሁሉንም አጠፋ።’ ሉቃስ ኢየሱስ ‘የኖኅን ዘመን’ ‘ከሰው ልጅ ዘመን’ ጋር ያወዳደረበትን ተመሳሳይ ታሪክ ዘግቧል። ኢየሱስ “የሰው ልጅ በሚገለጥበት ቀን እንዲሁ ይሆናል” በማለት አጥብቆ መክሯል።—ሉቃስ 17:26-30
22. በማቴዎስ ምዕራፍ 24 ላይ በሚገኘው የኢየሱስ ትንቢት ላይ ለየት ያለ ትኩረት ማድረግ የሚኖርብን ለምንድን ነው?
22 የምንኖረው ኢየሱስ አስቀድሞ የተናገራቸው ሁኔታዎች ማለትም ጦርነቶች፣ የመሬት መንቀጥቀጥ፣ መቅሠፍትና የምግብ እጥረቶች እየተከሰቱ ባሉበትና በደቀ መዛሙርቱ ላይ ስደት እየደረሰ ባለበት ወቅት ላይ ስለሆነ ይህ ሁሉ ለእኛ ልዩ ትርጉም ይኖረዋል። (ማቴዎስ 24:7-9፤ ሉቃስ 21:10-12) ምንም እንኳ አብዛኞቹ ሰዎች እንደማንኛውም የታሪክ ክፍል አድርገው ቢመለከቷቸውም እነዚህ ሁኔታዎች ታሪክን ከለወጠውና የመጀመሪያው የዓለም ጦርነት የሚል ስያሜ ከተሰጠው ግጭት ጀምሮ ሲታዩ ኖረዋል። ሆኖም ንቁ የሆኑ ሰዎች በለስ ስታቆጠቁጥ በማየት በጋ እንደቀረበ እንደሚያስተውሉ ሁሉ እውነተኛ ክርስቲያኖችም የእነዚህን ዐበይት ክስተቶች ትርጉም ያስተውላሉ። ኢየሱስ “እንዲሁ ደግሞ እናንተ ይህ ሁሉ መሆኑን ስታዩ የእግዚአብሔር መንግሥት እንደ ቀረበች እወቁ” የሚል ምክር ሰጥቷል።—ሉቃስ 21:31
23. በማቴዎስ ምዕራፍ 24 ላይ የሚገኙት የኢየሱስ ቃላት ልዩ ትርጉም ያላቸው ለእነማን ነው? ለምንስ?
23 ኢየሱስ በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ሆኖ የሰጠው መልስ በአብዛኛው ያተኮረው በተከታዮቹ ላይ ነው። መጨረሻው ከመምጣቱ በፊት በመላው ምድር ላይ በሚካሄደው ምሥራቹን የመስበክ ሕይወት አድን በሆነው ሥራ የሚካፈሉት እነሱ ናቸው። ‘የጥፋት ርኲሰት በተቀደሰችው ስፍራ ሲቆም’ ማስተዋል የሚችሉት እነሱ ናቸው። ከታላቁ መከራ ‘በመሸሽ’ አዎንታዊ ምላሽ የሚሰጡት እነሱ ናቸው። በተጨማሪም “እነዚያ ቀኖችስ ባያጥሩ ሥጋ የለበሰ ሁሉ ባልዳነም ነበር፤ ነገር ግን እነዚያ ቀኖች ስለ ተመረጡት ሰዎች ያጥራሉ” የሚሉት ቃላት በቀጥታ የሚመለከታቸው እነሱ ናቸው። (ማቴዎስ 24:9, 14-22) ይሁን እንጂ እነዚህ አሳሳቢ ቃላት ምን ትርጉም አላቸው? በፊቱ የላቀ ደስታ፣ ልበ ሙሉነትና ቅንዓት እንዲኖረን ምክንያት ይሆኑናል ሊባል የሚችለውስ ለምንድን ነው? በማቴዎስ 24:22 ላይ የምናደርገው የሚቀጥለው ጥናት መልሱን ይሰጠናል።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ጆሴፈስ ፓሩስያን እንዴት እንደተጠቀመበት የሚጠቁሙ ምሳሌዎች፦ በሲና ተራራ ላይ የወረደው ነጎድጓድና መብረቅ “አምላክ እዚያ መገኘቱን [ፓሩስያን] ያሳያል።” በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ይታይ የነበረው ተአምራዊ ምልክት “የአምላክን መገኘት [ፓሩስያን] ያመለክታል።” አምላክ በዙሪያው የሚገኙትን የእሳት ሰረገሎች ለኤልሳዕ አገልጋይ በማሳየት “ለአገልጋዩ ኃይሉንና በቦታው የተገኘ መሆኑን [ፓሩስያን] እንዲገነዘብ አድርጎታል።” ፔትሮኒየስ የተባለው ሮማዊ ባለ ሥልጣን ከአይሁዳውያን ጋር ሰላም ለመፍጠር ጥረት ባደረገበት ወቅት አምላክ ዝናብ በማዝነብ ‘ለፔትሮኒየስ መገኘቱን [ፓሩስያን] አሳይቷል’ በማለት ጆሴፈስ ተናግሯል። ጆሴፈስ ፓሩስያን መቅረብን ወይም ለአጭር ጊዜ ወደ አንድ ቦታ መምጣትን ለማመልከት አልተጠቀመበትም። ፓሩስያ ማለት ቀጣይ በሆነ መልኩ በማይታይ ሁኔታም እንኳ ቢሆን መገኘት ማለት ነው። (ዘጸአት 20:18-21፤ 25:22፤ ዘሌዋውያን 16:2፤ 2 ነገሥት 6:15-17)—አንቲኩዊቲስ ኦቭ ዘ ጁዊሽ 3ኛ መጽሐፍ ምዕራፍ 5 አንቀጽ 2 [80]፤ ምዕራፍ 8፣ አንቀጽ 5 [202]፤ 9ኛ መጽሐፍ ምዕራፍ 4 አንቀጽ 3 [55]፤ 18ኛ መጽሐፍ፣ ምዕራፍ 8 አንቀጽ 6 [284] ጋር አወዳድር።
b ኢ ደብልዩ ቡሊንገር ኤ ክሪቲካል ሌክሲኮን ኤንድ ኮንኮርዳንስ ቱ ዘ ኢንግሊሽ ኤንድ ግሪክ ኒው ቴስታመንት በተባለው መጽሐፋቸው ላይ ፓሩስያ ‘አብሮ መሆንን ወይም መገኘትን የሚያመለክት ሲሆን መገኘትና መምጣት ማለት ነው፤ መምጣት ሲባል ከመጡ በኋላ ለዘለቄታው መኖር የሚል ሐሳብ ያዘለ ነው’ ሲሉ ገልጸዋል።
c አንዱ ማስረጃ 19 ጊዜ በቀጥታ ተጽፎ ወይም በምሕጻረ ቃላት ተቀምጦ የሚገኘውን “ስሙ” የሚለውን የዕብራይስጥ አገላለጽ የያዘ መሆኑ ነው። ፕሮፌሰር ሀዋርድ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፦ “አንድ አይሁዳዊ ተከራካሪ በክርስቲያን ጽሑፍ ውስጥ መለኮታዊውን ስም መጥቀሱ የሚያስደንቅ ነገር ነው። ይህ ከግሪክ ወይም ከላቲን የተተረጎመ የዕብራይስጥ ትርጉም ቢሆን ኖሮ ማንም በጽሑፉ ውስጥ አዶናይ [ጌታ] የሚለውን እንጂ በቃላት ሊነገር የማይችለውን መለኮታዊ ስም የሚያመለክቱትን የሐወሐ የተባሉ ፊደላት አገኛለሁ ብሎ ሊጠብቅ አይችልም ነበር። . . . በቃላት ሊገለጽ የማይችለውን ይህን ስም የጨመረው እሱ ነው ብሎ ማሰብ ፈጽሞ የማይቻል ነገር ነው። ሼምቶብ የነበረው የማቴዎስ መጽሐፍ ቅጂ መለኮታዊውን ስም የያዘ እንደነበረና ስሙን ከመጽሐፉ ውስጥ በማውጣት ተጠያቂ ከመሆን ይልቅ እንዳለ ማስቀመጡን መርጦ ሊሆን እንደሚችል ማስረጃዎቹ በግልጽ ያሳያሉ።” ባለ ማጣቀሻው የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም መለኮታዊውን ስም በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የሚጠቀምበትን ምክንያት ሲያስረዳ ሼምቶብ ያዘጋጀውን የማቴዎስ ጽሑፍ (J2) ማስረጃ አድርጎ ይጠቅሳል።
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
◻ መጽሐፍ ቅዱሶች ማቴዎስ 24:3ን የተረጎሙባቸውን የተለያዩ መንገዶች መረዳት በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
◻ የፓሩስያ ትርጉም ምንድን ነው? ይህስ ትኩረታችንን የሚስበው ለምንድን ነው?
◻ በማቴዎስ 24:3 ረገድ የግሪክኛውና የዕብራይስጡ አገላለጽ ምን ተመሳሳይነት ሊኖራቸው ይችላል?
◻ ማቴዎስ 24ን ለመረዳት ጊዜን በተመለከተ ማስተዋል የሚያስፈልገን ቁልፍ ነገር ምንድን ነው?
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የኢየሩሳሌምን ከተማ ቁልቁል ማየት የሚቻልበት የደብረ ዘይት ተራራ