የይሖዋ ምስክሮች—ከስሙ በስተጀርባ ያለው ድርጅት
ጥቅምት 6, 1990 ለመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስና ትናንሽ ጽሑፎች ማኅበር ዓመታዊ ስብሰባ በዩናይትድ እስቴትስ ኒው ጄርሲ፣ በኒው ጄርሲ ከተማ በሚገኘው የይሖዋ ምስክሮች የትልቅ ስብሰባ አዳራሽ ተሰብስበው የነበሩት 5,000 የሚያህሉ ሰዎች ያላሰቡት አስደሳች ዜና እየጠበቃቸው ነበር። ሊቀ መንበሩ ጆን ኢ ባር የይሖዋ ምስክሮች—ከስሙ በስተጀርባ ያለው ድርጅት የሚል ርዕስ ያለው የ55 ደቂቃ ቪዲዮ መውጣቱን ለተሰብሳቢዎቹ ነገራቸው። ይህ ቪድዮ በማህበሩ ተዘጋጅቶ ለመቅረብ የመጀመሪያው ሲሆን ይሖዋ ከፈቀደ ግን የመጨረሻው አይሆንም።
ቪድዮው የይሖዋ ሕዝቦች ለመለኮታዊው ስም ለመመስከርና “የመንግሥቱን ወንጌል” ለማሠራጨት እንዴት እንደተደራጁ የሚገልጽ ነው። (ማቴዎስ 24:14) በብሩክሊን ኒውዮርክ ያለው ዋና መሥሪያ ቤትና በመጠበቂያ ግንብ ማህበር እርሻዎች ያሉት ድርጅቶች ጎላ ተደርገው ተገልጸዋል። ቪድዮው በእንግሊዝኛ ከ500,000 በላይ በሚሆኑ ቅጂዎች የተዘጋጀ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ (ወይም በቅርቡ) ደግሞ በ26 ሌሎች ቋንቋዎች ማግኘት ይቻላል።a
ምን ዓይነት ተቀባይነት አገኘ?
የይሖዋ ምስክሮች ያልሆኑ ሰዎች እንዴት ተቀበሉት? አንድ ነጋዴ እንደሚከተለው ሲል ጽፎአል፦
“ቴፑን እጅግ በጣም ጥሩ የሆነ ጥራት ያለው ሆኖ አግኝቼዋለሁ። በተለይ በጣም የተደነቅኩት በቪድዮው ላይ በተቀረጹት ሥዕሎች ብሩሕነትና ጥሩ የባለሞያ ሕትመት በመሆናቸው ነው። ቴፕ መሆኑን እረሳና ይበልጡን የማስበው ፊልም እንደሆነ አድርጌ ነው። ይህ ቴፕ ስለ ኒውዮርኩ ዋና መሥሪያ ቤታችሁ ለማስረዳት ከሌላው ነገር ሁሉ ይበልጥ ጠቃሚ መሆን ይኖርበታል። ይህን ግሩም ነገር በማዘጋጀታችሁ እንኳን ደስ አላችሁ እላለሁ።”—ጄ. ጄ.
ከይሖዋ ምስክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን የሚያጠኑ ሰዎች ቪድዮውን በመመልከት ተጠቅመዋል። የሚከተለው ደብዳቤ ምክንያቱን ያስረዳል፦
“ዕድሜው 20 ዓመት ከሆነና በአካባቢው ዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን ከሚከታተል ወጣት ጋር መጽሐፍ ቅዱስ አጠናለሁ። እየከፋ ያለው የዓለም ሁኔታ ያሳስበዋል። ቴፑንና በሕይወታቸው እውነተኛ ዓላማ ያላቸውን እነዚያን ሁሉ የሚያማምሩ የቤቴል ወጣቶች ከተመለከተ በኋላ ግን ጠቅላላ አመለካከቱ ተለወጠ። በልዩ ስብሰባችን ቀን ተገኘና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቱን በሳምንት ሁለት ጊዜ እንድናደርገው ጠየቀኝ። አንዲት ሌላ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህር የሆነች የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ ለዘመዶቿ ለማሳየት ቴፑን ተውሳ ወሰደች። ዘመዶቿ የይሖዋ ምስክሮች ምንም ታዋቂ ያልሆነ ደካማና አነስተኛ ድርጅት ብቻ ያላቸው ይመስላቸው ነበር። በሥራችን ዓለም አቀፋዊነትና በምናገኘው ስኬት በጣም ተደነቁ። ለዚህም ይሖዋ የተመሰገነ ይሁን።”—ጄ ቢ
“መጽሐፍ ቅዱስ የማስጠናት ሴት ይህን ቪድዮ ከተመለከተች በኋላ የደስታና የአድናቆት እንባዋን ስታጎርፈው የተሰማኝን ደስታ ቃላት ሊገልጹት አይችሉም። ዓይኖቿ በእንባ ተሞልተው ‘ይህ የእውነተኛው አምላክ የይሖዋ ድርጅት መሆኑን ሰው ሊገነዘብ የማይችለው እንዴት ነው? እንዲህ ዓይነት ሰዎች መኖራቸውን በፍጹም አላውቅም ነበር’ አለች። ከዚያም ‘መጠመቅ እፈልጋለሁ’ አለች።”—ሲ ዲ
“ከመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቻችን ጋር በቪድዮው በመጠቀም ብዙ ስኬት አግኝተናል። ትናንት ማታ ከሚስቴ ጥናቶች የአንዷ ባል መጥቶ ነበር። በጣም ተቃዋሚ ነበር። ቪድዮውን ተመለከተ። ከዚያ በኋላ ጥያቄዎች ሲጠይቅ ቆየና መጽሐፍ ቅዱስና መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የምንገለገልበትን በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ የተባለውን መጽሐፍ ይዞ ሄደ። ከዚህ ቀደም የሚስቱን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች በሙሉ አቃጥሎ ነበር!”—ዲ ኤች
የሚከተለው አስተያየት እንደሚገልጸው ወጣቶችም ቪድዮውን በጣም የሚመስጥ ሆኖ አግኝተውታል፦
“ዕድሜዬ ስድስት ዓመት ተኩል ነው። ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የሚገልጸውንና ካርቶኖቹ በፍጥነት ሲሄዱ የሚያሳየውን ክፍል ወድጄዋለሁ።”—ኬ ደብልዩ
“ትንንሽ ልጆቻችን ቪድዮው በቴሌቪዥን ላይ ከተመለከቱት ከማንኛውም ፕሮግራም የበለጠ እንደሆነ ተናግረዋል።”—አር ሲ
“የአምስት ዓመት ወንድ ልጃችን ቪዲዮውን ተጀምሮ እስኪያልቅ ድረስ በትኩረት ለሁለተኛ ጊዜ ከተመለከተ በኋላ ‘ይህን ቪድዮ በየቀኑ ልናየው እንችላለን?’ ብሎ ጠየቀ። የሦስት ዓመት ሴት ልጃችን ደግሞ ከእርሱ ጋር አብራ ‘እኔም ቤቴል መሄድና መጻሕፍት ማዘጋጀት እፈልጋለሁ!’ አለች።”—ኤም ኢ
“ዕድሜያቸው 12 እና 9 የሆኑት ሮቢንና ሻናን የሚባሉ ወንድና ሴት ልጆቼ ቴፑን በተደጋጋሚ እየተመለከቱት ነው። ትንሿ ልጄ ቴፑን ካየች በኋላ ‘ወደ መስክ አገልግሎት መሄድ እወዳለሁ። በጣም የሚያስደስት ነው’ አለች። ይህ ቪድዮ በቤተሰብ ሕይወታችን ላይ ቀጥተኛ ውጤት እንዳለው ይሰማናል። በቴሌቪዥን ላይ መመልከቱ ምንም ጉዳት እንደማያስከትል የምታምኑበትን ፕሮግራም ከፍቶ ማየት እንዴት የሚያስደስት ነው!”—ኤን ቢ
“ዕድሜዬ 131/2 ነው። አዲሱ ቪዲዮ አስደናቂዎቹን የይሖዋ ዝግጅቶች ምን ያህል እንደ ቀላል ነገር እመለከታቸው እንደነበረ አስገንዝቦኛል። ከአምላክ ሕዝቦች መካከል አንዱ መሆን መብት ነው።”—ኬ ደብልዩ
“ዕድሜዬ 16 ዓመት ነው። ይህ ቪድዮ በዓለም አቀፍ ደረጃ በመካሄድ ላይ ያለው ሥራ መሆኑን በጥብቅ እንድገነዘብ ረድቶኛል።”—ኤ ኤም
“ልጆቻችን እውነተኛ መለኮታዊ መዝናኛ ምን ሊመስል እንደሚችል በመገንዘባቸው ምክንያት ሁል ጊዜ የሚመለከቱት የቴሌቪዥን ፕሮግራም ምንም የማይማርክ ሆኖ እንዳገኙት ተናግረዋል። ቪድዮው ወደ ሙሉ ጊዜ አገልግሎት የመግባት ፍላጎታቸውንም አጠናክሮታል።”—ኤል ኤም
ለብዙ ዓመታት የይሖዋ ምስክሮች የነበሩትም እንኳን በቪድዮው ላይ በተመለከቱት ነገር ስሜታቸው ተነክቷል።
“ቪድዮው በእኛ በይሖዋ ሕዝቦች ላይ እንኳን ይህን ያህል ኃይል ካለው ሌሎችን ምን ያህል ይነካቸው? ይህ ሥርዓት ለመኖር በጣም አስቸጋሪ እየሆነ በመጣ ቁጥር ከጊዜዬ ውስጥ አንድ ሰዓት እየወሰድሁ በመኖሪያ ቤቴ ቁጭ ብዬ ቤቴልን እጎበኛለሁ።”—ኬ ቢ
“በእያንዳንዱ ጥቃቅን ሥራ ላይ የሚውለውን ጥንቃቄና ትክክለኛነት ከተመለከትኩ በኋላ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎቼ ወዳሉበት ክፍል ሄጄ እቅፍ እንዳደርጋቸው የሚጎተጉት ስሜት ተሰማኝ።”—ኤል ፒ
የይሖዋ ምስክሮች—ከስሙ በስተጀርባ ያለው ድርጅት የተሰኘውን ቪድዮ ጊዜ መድባችሁ እንድትመለከቱት እናበረታታችኋለን። በሕይወት ላይ የተለየ አስተያየት የሚሰጣችሁ ከመሆኑም በላይ ለወደፊቱ አስተማማኝ ጊዜ እንደሚመጣ እርግጠኞች እንድትሆኑ ይረዳችኋል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a የአሜሪካ የምልክት ቋንቋ፣ አረብኛ፣ ባስክኛ፣ ካንቶኔስ፣ ካታላን፣ ክራኦሺያን፣ ዜክ (ቦሂሚያን)፣ ዳኒሽ፣ ዳች፣ ፊኒሽ፣ ፈረንሳይኛ፣ ጀርመንኛ፣ ግሪክኛ፣ ሀንጋሪያን፣ ጣሊያንኛ፣ ጃፓንኛ፣ ኮርያንኛ፣ ማንዳሪን፣ ኖርዌጂያን፣ ፖሊሽ፣ ፖርቱጊዝ (ብራዚል)፣ ፖርቱጊዝ (አውሮፓ)፣ ሮማኒያን፣ ስሎቫክ፣ ስፓኒሽ፣ ስዊድሽ።