በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የነበረው የትምህርት አሰጣጥ
“ልጆቻችሁንም አስተምሩአቸው።”—ዘዳግም 11:19
1. ይሖዋ አገልጋዮቹ እንዲማሩ እንደሚፈልግ የሚያሳየው ምንድን ነው?
ይሖዋ ታላቅ አስተማሪ ነው። አገልጋዮቹን በድንቁርና እንዲኖሩ ትቷቸው አያውቅም። ለእነሱ እውቀትን ለማካፈል ምንጊዜም ፈቃደኛ ሆኖአል። ፈቃዱንና መንገዶቹን ያስተምራቸዋል። ስፍር ቁጥር ለሌላቸው ብዙ ዘመናት አንድያ ልጁ እንደ አምላክ “ዋና ሠራተኛ” ከጎኑ ሆኖ ያለማቋረጥ ሲማር ነበር። (ምሳሌ 8:30) ኢየሱስ በምድር በነበረበት ጊዜ “አባቴም እንዳስተማረኝ እነዚህን እናገራለሁ” በማለት ገልጿል። (ዮሐንስ 8:28) ኤሊሁ አምላክ ተወዳዳሪ የሌለው አስተማሪ መሆኑን ለማመልከት “እንደሱ ያለ አስተማሪስ ማን ነው?” ሲል ጠይቋል። (ኢዮብ 36:22) ነቢዩ ኢሳይያስ አምላክ የሕዝቦቹ “ታላቅ አስተማሪ” እንደሆነ ተናግሯል። እንዲሁም “ልጆችሽም ሁሉ ከእግዚአብሔር [ከይሖዋ አዓት] የተማሩ ይሆናሉ፣ የልጆችሽም ሰላም ብዙ ይሆናል” ሲል ተንብዮአል። (ኢሳይያስ 30:20፤ 54:13) ይሖዋ የማሰብ ችሎታ ያላቸው ፍጡሮቹ የእውቀት ብርሃን እንዲበራላቸውና በደንብ የተማሩ እንዲሆኑ እንደሚፈልግ አያጠያይቅም።
አባቶች የቤት ራስና ሃይማኖታዊ መሪ በነበሩበት ዘመን የነበረው ትምህርት
2, 3. (ሀ) የቤተሰብ ራስና ሃይማኖታዊ መሪ የነበሩ ታማኝ የጥንት አባቶች ልጆቻቸውን ማስተማርን እንዴት ይመለከቱት ነበር? ይሖዋ ለአብርሃም ምን ትዕዛዝ ሰጠው? (ለ) የአብርሃምን ዝርያዎች እንዲያስተምሩ ከተሰጠው ትዕዛዝ በስተኋላ ያለው ታላቅ ዓላማ ምን ነበር?
2 አባቶች የቤተሰብ ራስና ሃይማኖታዊ መሪ በነበሩበት የቀድሞ ዘመን ይኖሩ የነበሩት የቤተሰብ ራሶች ካሏቸው መሠረታዊ መብቶች አንዱ ልጆቻቸውንና ቤተሰባቸውን ማስተማር ነበር። ለአምላክ አገልጋዮች ልጆቻቸውን ማስተማሩ ሃይማኖታዊ ተግባር ነበር። ይሖዋ ስለ አገልጋዩ ስለ አብርሃም እንዲህ ብሏል፡- “ጽድቅንና ፍርድን በማድረግ የእግዚአብሔርን [የይሖዋን አዓት] መንገድ ይጠብቁ ዘንድ ልጆቹንና ከእርሱ በኋላ ቤቱን እንዲያዝዝ አውቃለሁና [ከእርሱ ጋር ተዋውቄአለሁና አዓት]፤ ይህም እግዚአብሔር [ይሖዋ አዓት] በአብርሃም ላይ የተናገረውን ነገር ሁሉ ያመጣ ዘንድ ነው።”—ዘፍጥረት 18:19
3 ይህ መለኮታዊ አነጋገር ይሖዋ ትምህርትን ትልቅ ቦታ እንዳለው አድርጎ እንደሚመለከተው ያሳያል። አብርሃም፣ ይስሐቅና ያዕቆብ ቤተሰባቸውን በአምላክ የጽድቅ መንገዶችና በፍትሑ እንዲያስተምሩ አምላክ ይፈልግባቸው ነበር። ይህም ቀጣዩ ትውልድ የይሖዋን መንገድ መጠበቅ በሚችልበት ሁኔታ ላይ እንዲቆይ ለማድረግ ይረዳል። በዚህ መንገድ ይሖዋ የአብርሃምን ዘርና “የምድርን አሕዛብ ሁሉ” መባረኩን በሚመለከት የሰጠውን የተስፋ ቃል ለመፈጸም ይችላል።—ዘፍጥረት 18:18፤ 22:17, 18
በእስራኤል የነበረው ሥርዓተ ትምህርት
4, 5. (ሀ) የእስራኤልን ሥርዓተ ትምህርት ከሌሎቹ ብሔራት ሥርዓተ ትምህርት የሚለየው ምንድን ነው? (ለ) በኢንሳይክሎፔዲያ ጁዳይካ ውስጥ ምን ሌላ አስፈላጊ ልዩነት ተዘርዝሯል? ያለ ጥርጥር ለዚህ ልዩነት አስተዋጽዖ ያደረገው ነገር ምንድን ነው?
4 ኢንሳይክሎፔዲያ ጁዳይካ “መጽሐፍ ቅዱስ በጥንቷ እስራኤል ስለነበረው የትምህርት ሂደት ለማወቅ የምንችልበት ዋነኛው ምንጭ ነው” በማለት ገልጾአል። ይሖዋ ሙሴን የእስራኤል የመጀመሪያው ሰብዓዊ አስተማሪ አድርጎ ተጠቅሞበታል። (ዘዳግም 1:3, 5፤ 4:5) ሙሴ ከይሖዋ የተቀበላቸውን ቃላት ያስተላልፍ ነበር። (ዘጸአት 24:3) ስለዚህ የእስራኤል ዋና አስተማሪ አምላክ ነበር ማለት ነው። ይህ ራሱ የእስራኤልን ሥርዓተ ትምህርት ከሌሎች ብሔራት የትምህርት አሰጣጥ የተለየ ያደርገዋል።
5 ይኸው የመረጃ ጽሑፍ እንዲህ ብሏል፦ “በሜሶጶጣሚያና በግብጽ የነበረው ከፍተኛ ትምህርት ወይም የመጽሐፍ ትምህርት የመደበኛነት መልክ የያዘና ለተወሰነ የጻፎች ክፍል ብቻ የሚሰጥ ነበር። በእስራኤል ግን ይህ ሁኔታ የነበረ አይመስልም። ልዩነቱ ዕብራውያን ይጠቀሙበት የነበረው በፊደላት የመጻፍ ቀላል ዘዴ ምክንያት ለመሆኑ ጥርጥር የለውም። . . . በትምህርት ታሪክ ውስጥ በፊደላት መጻፍ የተጀመረበት ጊዜ ቸል ተብሎ መታለፍ የለበትም። በግብጽ፣ በሜሶጶጣሚያና በሁለተኛው ሺህ ዘመን በነበሩት ከነዓናውያን ጻፎች ዘንድ የነበረውን ልማድ የሚለውጥ ዘዴ ነበር። ለመረዳት አስቸጋሪ በነበረው የኪዮኒፎርምና የሒሮግሎፊክ ሥዕላዊ የአጻጻፍ ዘዴ የተራቀቁ የነበሩት ጸሐፊዎችና ካህናት ብቻ የተማሩ መሆናቸው ቀረ።”
6. እስራኤላውያን ገና ከታሪካቸው መጀመሪያ ጀምሮ የተማሩ ሰዎች እንደነበሩ የሚያረጋግጥልን ምን የመጽሐፍ ቅዱስ ማስረጃ አለ?
6 መጽሐፍ ቅዱስ እስራኤላውያን ማንበብና መጻፍ የሚችሉ ሕዝቦች እንደነበሩ ማረጋገጫ ይሰጠናል። ወደ ተስፋይቱ ምድር ከመግባታቸው በፊት እንኳን የይሖዋን ሕግጋት በቤታቸው መቃኖችና በደጃፋቸው በሮች ላይ እንዲጽፉ ተነግሯቸው ነበር። (ዘዳግም 6:1, 9፤ 11:20፤ 27:1-3) ይህ ትእዛዝ ምሳሌያዊ አገላለጽ እንደነበር የማያጠራጥር ቢሆንም ተራው የእስራኤል ሕዝብ ማንበብና መጻፍ ባይችል ኖሮ ይህ ትእዛዝ በእርግጥ ምንም ትርጉም አይኖረውም ነበር። ንጉሣዊ አገዛዝ በእስራኤል ከመስፈኑ በፊት እንኳን እንደ ሙሴና ኢያሱ ካሉት መሪዎች ሌላ መጻፍ የሚችሉ ሌሎች ሰዎች እንደነበሩ እንደ ኢያሱ 18:9 እና መሳፍንት 8:14 ያሉት ጥቅሶች ያሳዩናል።—ዘጸአት 34:27፤ ኢያሱ 24:26
የማስተማሪያ ዘዴዎች
7. (ሀ) በቅዱሳን ጽሑፎች መሠረት ለእስራኤላውያን ልጆች መሠረታዊ ትምህርት ይሰጡ የነበሩት እነማን ናቸው? (ለ) በአንድ ፈረንሳዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሑር የተሰጠው መረጃ ምንድን ነው?
7 በእስራኤል ውስጥ ልጆች ገና ከትንሽነታቸው ጀምሮ አባትና እናታቸው ያስተምሯቸው ነበር። (ዘዳግም 11:18, 19፤ ምሳሌ 1:8፤ 31:26) የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት በተባለ የፈረንሳይኛ መዝገበ ቃላት ላይ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሑር የሆኑት ኢ መንዡኖ እንዲህ ብለዋል፦ “አንድ ልጅ መናገር እንደቻለ ወዲያው ከሕጉ ጥቂት ክፍሎችን ይማራል። እናቱ አንድ ጥቅስ እየደጋገመች ትነግረዋለች። ያንን ሲያውቀው ደግሞ ሌላ ትነግረዋለች። በኋላም ልጁ የሚያስታውሳቸው ጥቅሶች ተጽፈው በእጁ ላይ ይደረጋሉ። በዚህ መንገድ ማንበብ ይለማመዳሉ። እያደጉ ሲሄዱም ሃይማኖታዊ ትምህርቶችን ማንበብና በጌታ ሕግ ላይ ማሰላሰል ይቀጥላሉ።”
8. (ሀ) በእስራኤል ውስጥ ምን መሠረታዊ ማስተማሪያ ዘዴ ነበር? የዚህስ ዘዴ ጉልህ ባሕርያት ምን ምን ነበሩ? (ለ) ለማስታወስ የሚረዷቸውን ምን ነገሮች ይጠቀሙ ነበር?
8 ይህም መሠረታዊው የማስተማሪያ ዘዴ ነገሮችን በቃል መያዝ እንደነበር ይጠቁማል። የይሖዋ ሕግጋትና ይሖዋ ከሕዝቦቹ ጋር ያደረገውን ግንኙነት በተመለከተ የተማሯቸው ነገሮች በልብ ውስጥ ዘልቀው መግባት ነበረባቸው። (ዘዳግም 6:6, 7) ሊያሰላስሏቸው የሚገቡ ነገሮች ነበሩ። (መዝሙር 77:11, 12) ወጣቶችም ሆኑ ትልልቆች እነዚህን በቃላቸው ለመያዝ የሚያስችሏቸውን የተለያዩ የማስታወሻ ዘዴዎችን ይጠቀሙ ነበር። እነዚህም ዘዴዎች በየመስመሩ መጀመሪያ ወይም መጨረሻ ያሉት ፊደላት ወደታች ሲነበቡ ትርጉም የሚሰጡ ቃላት ወይም የፊደላት ቅደም ተከተል እንዲሆኑ ማድረግን፤ አንቀጾችን ቅደም ተከተል በያዙ ፊደላት መከፋፈልን፣ ተከታታይ የመዝሙር ጥቅሶች በተለያዩ ፊደላት እንዲጀምሩ ማድረግን፤ በፊደላት ቅደም ተከተል ማስቀመጥን (እንደ ምሳሌ 31:10-31 ያሉ)፤ (በአንድ ዓይነት ፊደላት ወይም ተመሳሳይ ድምፅ ባላቸው ፊደላት የሚጀምሩ ቃላት) መጠቀምንና ከምሳሌ 30 አጋማሽ ጀምሮ እንደሚታየው ጥቅሶችን በቁጥር መከፋፈልን ይጨምሩ ነበር። ለጥንቱ የዕብራይስጥ አጻጻፍ ምሳሌ ከሆኑት ጥንታውያን ጽሑፎች አንዱ ጌዝር የተባለው የቀን መቁጠሪያ ተማሪዎች ለማስታወስ ይጠቀሙበት የነበረ ጽሑፍ እንደሆነ አንዳንድ ምሑራን ይገምታሉ።
ሥርዓተ ትምህርት
9. (ሀ) ከእስራኤላውያን ልጆች የትምህርት ፕሮግራም አንዱ ትልቅ ክፍል የነበረው ምንድን ነው? (ለ) አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ኢንሳይክሎፔዲያ ከዓመታዊ ክብረ በዓሎች ጋር ተያይዞ ይሰጥ ስለነበረው ትምህርት ምን ገለጸ?
9 በእስራኤል የነበረው ትምህርት ማንበብና መጻፍን በማስተማር ብቻ የተወሰነ አልነበረም። ይማሯቸው ከነበሩት ታላላቅ የትምህርት ዓይነቶች አንዱ ታሪክ ነበር። ይሖዋ ለሕዝቦቹ ያደረጋቸውን አስደናቂ ሥራዎቹን መማር የሥርዓተ ትምህርቱ አንዱ መሠረታዊ ክፍል ነበር። ይህም ከትውልድ ወደ ትውልድ ሊያስተምሩት የሚገባ ነበር። (ዘዳግም 4:9, 10፤ መዝሙር 78:1-7) ዓመታዊ በዓሎች የሚከበሩበት ወቅት የቤተሰቡ ራስ ልጆቹን እንዲያስተምር ጥሩ አጋጣሚ ይሰጠው ነበር። (ዘጸአት 13:14፤ ዘሌዋውያን 23:37-43) ከዚህ ጋር በሚዛመድ ሁኔታ ዓለም አቀፋዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ኢንሳይክሎፔድያ እንዲህ ይላል፦ “አባት እቤት ውስጥ በሚሰጠው ትምህርትና ስለ በዓላቱ ትርጉም በሚሰጠው ማብራሪያ አማካኝነት የዕብራውያን ልጆች ባለፈው ዘመን አምላክ ራሱን እንዴት እንደገለጸላቸው፣ በአሁኑ ጊዜ እንዴት መኖር እንደሚገባቸው እንዲሁም የሕዝቡን የወደፊት ሁኔታ በተመለከተ አምላክ ምን ቃል ኪዳን እንደገባላቸው ይማሩ ነበር።”
10. ለልጃገረዶች ይሰጥ የነበረው ተግባራዊ ሥልጠና ምን ነበር? ለወንዶች ልጆችስ?
10 በወላጆች የሚሰጠው ትምህርት ተግባራዊ ሥልጠናንም ይጨምር ነበር። ልጃገረዶች የቤት ውስጥ ሞያን ይማሩ ነበር። የመጽሐፈ ምሳሌ የመዝጊያ ምዕራፍ እነዚህ ትምህርቶች ብዙና የተለያዩ እንደነበሩ ያሳያል፤ መፍተልን፣ ልብስ መሥራትን፣ ምግብ ማብሰልን፣ መነገድንና ጠቅላላ የቤት ውስጥ አስተዳደርን ያጠቃልሉ ነበር። ወንዶች ልጆች ብዙውን ጊዜ የአባታቸውን ሥራ ወይም ሙያ እርሻም ሆነ ወይም አንዳንድ ንግዶች ወይም የእጅ ሥራዎች መሥራትን ይማሩ ነበር። በኋለኞቹ ዓመታት የአይሁድ መምህራን “ልጁን አንድ ጠቃሚ ሞያ የማያስተምር ሰው ሌባ እንዲሆን ያዘጋጀዋል” የሚል አነጋገር ነበራቸው።
11. በእስራኤል ውስጥ ይሰጥ የነበረውን ትምህርት መሠረታዊ ዓላማ የሚያሳየው ምንድን ነው? ይህስ በዛሬው ጊዜ ላሉ ወጣቶች ምን ትምህርት ይዟል?
11 በእስራኤል ውስጥ የነበረው የማስተማሪያ ዘዴ የቱን ያህል መንፈሳዊ ጥልቀት እንደነበረው በምሳሌ መጽሐፍ ውስጥ በግልጽ ተቀምጧል። የዚህም ትምህርት ዓላማ እንደ ጥበብ፣ ተግሣጽ፣ መረዳት፣ ማስተዋል፣ ፍትሕ፣ ብልሃት፣ እውቀትና የማሰብ ችሎታ ስላሉት ከፍ ያሉ ነገሮች “ተሞክሮ የጎደላቸውን ሰዎች” ለማስተማር ነበር። እሥራኤላውያን እነዚህን ሁሉ ‘ይሖዋን ከመፍራት’ ጋር መማር ነበረባቸው። (ምሳሌ 1:1-7፤ 2:1-14) ይህም አንድ የአምላክ አገልጋይ በዛሬው ጊዜ ትምህርቱን ውይም ትምህርቷን እንዲያሻሽሉ ሊያነሳሷቸው የሚገባቸውን ምክንያቶች አጥብቆ ይገልጻል።
ካህናት፣ ሌዋውያንና ነቢያት
12. ከወላጆች ሌላ የእስራኤልን ሕዝብ የማስተማር ድርሻ የነበራቸው እነማን ናቸው? “ሕግ” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል መሠረታዊ ትርጉሙ ምንድን ነው?
12 ምንም እንኳን መሠረታዊ ትምህርቶች በወላጆች የሚሰጡ ቢሆንም ይሖዋ በካህናት፣ በክህነት በማያገለግሉ ሌዋውያንና በነቢያት አማካኝነት ለሕዝቡ ተጨማሪ ትምህርት ይሰጣቸው ነበር። ሙሴ የሌዊን ነገድ ሲባርክ ባሰማው የመጨረሻው ቃል ላይ “ፍርድህን ለያዕቆብ፣ ሕግህንም ለእስራኤል ያስተምራሉ” ሲል ገልጿል። (ዘዳግም 33:8, 10) “ሕግ” የሚለው የዕብራይስጥ ቃል (ቶራህ) ግሡ “ማሳየት፣” “ማስተማር፣” “መምራት” የሚል ትርጉም ካለው ምንጭ የመጣ ነው። ኢንሳይክሎፔዲያ ጁዳይካ እንደሚገልጸው “እንግዲያው የቃሉ [የቶራህ] ትርጉም ‘ማስተማር፣’ ‘የሃይማኖታዊ መሠረተ ትምህርት’ ወይም ‘መመሪያ መስጠት’ ነው።”
13. የእስራኤል ሕግ ከሌሎች ብሔራት የሕግ ሥርዓት የሚለየው ለምን ነበር?
13 ይህም እስራኤላውያንን ከሌሎች ብሔራትና ከዘመናዊዎቹ ብሔራትም እንኳን የተለዩ ያደርጋቸዋል። በዛሬው ጊዜ ፖለቲካዊ ብሔራት ሕግጋት ቢኖራቸውም አጠቃላዩ ሕዝብ ስለ ሕጉ የሚያውቀው በጣም ትንሹን ነው። ሰዎች ሕጉን ሲጥሱ እንዲከራከሩላቸው ለሚቀጥሯቸው ጠበቆች ከፍተኛ ገንዘብ ይከፍላሉ። የሕግ ትምህርት ቤት ገብተው የሚማሩት ባለሞያዎች ብቻ ናቸው። በእስራኤላውያን ዘንድ ግን ሕጉ አምላክ ሕዝቦቹ እንዴት ሊያመልኩት እንደሚፈልግና ከፈቃዱ ጋር እንዴት ተስማምተው ሊኖሩ እንደሚችሉ ለመግለጽ ያገለግል ነበር። ከሌሎች አገሮች ሕግጋት የተለየ በመሆን ሕጉ ለአምላክና ለጎረቤት ፍቅር ማሳየትን ይጨምራል። (ዘሌዋውያን 19:18፤ ዘዳግም 6:5) ሕጉ ለሰብአዊ ሁኔታዎች ግምት የማይሰጥ የሕግ መጽሐፍ ከመሆን በጣም የራቀ ነበር። ሕጉ ሊማሩት በሚገባ የሕይወት መንገድ ውስጥ የሚያስፈልጉትን የሃይማኖት መሠረተ ትምህርቶች፣ ሌሎች ትምህርቶችንና መመሪያዎችን የሚሰጥ ነበር።
14. ይሖዋ የሌዋውያንን ክህነት የተወበት አንዱ ምክንያት ምን ነበር? (ሚልክያስ 2:7, 8)
14 ካህናቱና ሌዋውያኑ ታማኞች በነበሩበት ጊዜ ሕዝቡን የማስተማር ኃላፊነታቸውን ተወጥተዋል። ብዙውን ጊዜ ግን ካህናቱ ሕዝቡን የማስተማር ሥራቸውን ቸል ይሉት ነበር። ስለ አምላክ ሕግ ትምህርት አለመሰጠቱ የኋላ ኋላ ለካህናቱም ሆነ ለሕዝቡ አደገኛ ውጤት አስከትሎባቸው ነበር። በስምንተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ይሖዋ እንዲህ ሲል ትንቢት ተናግሮ ነበር፦ “ሕዝቤ እውቀት ከማጣቱ የተነሣ ጠፍቷል፤ አንተም እውቀትን ጠልተሃልና እኔ ካህን እንዳትሆነኝ እጠላሃለሁ፤ የአምላክህንም ሕግ ረስተሃልና እኔ ደግሞ ልጆችህን እረሳለሁ።”—ሆሴዕ 4:6
15. (ሀ) ይሖዋ ከካህናት ሌላ እስራኤልን እንዲያስተምሩ ያስነሳቸው እነማንን ነበር? እነርሱስ አስተማሪ በመሆን ስላላቸው ሚና አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሑር ምን ብለው ጻፉ? (ለ) እስራኤልና ይሁዳ የይሖዋንና የመንገዶቹን እውቀት በመተዋቸው በመጨረሻው ምን ደረሰባቸው?
15 እንደ ካህናቱ ሁሉ ይሖዋ ነቢያትን አስተማሪዎች አድርጎ አስነስቶ ነበር። እንዲህ እናነባለን፦ “እግዚአብሔርም [ይሖዋም አዓት] ከክፉ መንገዳችሁ ተመለሱ፤ ለአባቶቻችሁም እንዳዘዝሁት፣ በባሪያዎቼ በነቢያት የላክሁላችሁን ትዕዛዜንና ሥርዓቴን ሕጌንም ሁሉ ጠብቁ ብሎ በነቢዩ ሁሉና በባለ ራእዩ አፍ ሁሉ በእስራኤልና በይሁዳ መሰከረ።” (2 ነገሥት 17:13) የነቢያትን የአስተማሪነት ሚና በተመለከተ ፈረንሳዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሑር ሮላንድ ድ ቮ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፦ “ነቢያትም ሕዝቡን የማስተማር ተልዕኮ ነበራቸው። ይህም የወደፊቱን ሁኔታ ከመተንበይ ሥራቸው ጋር የሚሄድ ተግባር ነበር። በመንፈስ ተነሳስተው ትንቢት መናገራቸውም ስብከታቸው የአምላክ ቃል መሆኑን በማረጋገጥ ኃይል ይጨምርለት ነበር። በንጉሣዊ አገዛዝ ዘመን ነቢያት የሕዝቡ የሃይማኖትና የሥነ ምግባር አስተማሪዎች እንደነበሩ የተረጋገጠ ነው። ሁልጊዜ ከማንም የበለጠ ተሰሚነት ነበራቸው ባንልም ከአስተማሪዎቻቸው ሁሉ የተሻሉ ናቸው ብለን ልንጨምር እንችላለን።” ካህናቱና ሌዋውያኑ ትክክለኛ ትምህርት ካለማስተማራቸው የተነሳ እንዲሁም ሕዝቡ የይሖዋን ነቢያት ባለመስማታቸው ጭምር እስራኤላውያን የይሖዋን መንገዶች ተው፤ ስለዚህም ሰማርያ በ740 ከዘአበ በአሦራውያን ስትደመሰስ ኢየሩሳሌምና ቤተ መቅደሷ ደግሞ በ607 ከዘአበ በባቢሎናውያን ጠፉ።
በግዞት በነበሩበት ጊዜና ከዚያ በኋላ የነበረው የትምህርት አሰጣጥ
16, 17. (ሀ) ዳንኤልና ሦስት ጓደኞቹ ምን የትምህርት ፕሮግራም እንዲከታተሉ ተገደው ነበር? (ለ) ይህን የባቢሎን ትምህርት እንዲማሩ ቢደረጉም ለይሖዋ ታማኝ ሆነው እንዲቆዩ የረዳቸው ነገር ምንድን ነው?
16 ኢየሩሳሌም ከመጥፋቷ ከአንድ አሥር ዓመት ቀደም ብሎ ንጉሥ ኢዮአኪን እንዲሁም ልዑላንና መኳንንት በንጉሥ ናቡከደነፆር አማካኝነት ወደ ባቢሎን ተወስደው ነበር። (2 ነገሥት 24:15) ከነሱም ውስጥ ዳንኤልና ሌሎች ሦስት ወጣት መኮንኖች ይገኙባቸዋል። (ዳንኤል 1:3, 6) ናቡከደነፆር አራቱንም “የከለዳውያንን ትምህርትና ቋንቋ ያስተምሯቸው ዘንድ” የሦስት ዓመት ልዩ ሥልጠና እንዲወስዱ አዘዘ። ከዚህም በላይ “ከንጉሡ መብል ከሚጠጣውም ጠጅ በየዕለቱ ድርጎአቸው” ይሰጣቸው ነበር። (ዳንኤል 1:4, 5) ይህ ከብዙ ምክንያቶች አንፃር አደጋ ነበረው። የትምህርት ፕሮግራሙ የሦስት ዓመት የቋንቋ ትምህርት ብቻ የነበረ አይመስልም። በአንቀጹ ውስጥ ያለው “ከለዳውያን” የሚለው ቃል አንዳንዶች እንደሚያስቡት የሚወክለው “የባቢሎንን ሕዝብ ሳይሆን የተማረውን ክፍል” ነበር። (ዘ ሶንሲኖ ቡክስ ኦቭ ዘ ባይብል) ኬ ኤፍ ኪል በዳንኤል መጽሐፍ ላይ በሰጡት አስተያየት “ዳንኤልና ጓደኞቹ የከለዳውያን ካህናትንና በባቢሎን ትምህርት ቤቶች የተማሩትን ሰዎች ጥበብ እንዲማሩ ታቅዶ ነበር።” የንጉሡ የምግብ ዳረጎትም የተከለከሉ ምግቦችን በሚመለከት በሙሴ ሕግ ውስጥ የነበሩትን ድንጋጌዎች እንዲጥሱ የሚያጋልጣቸው ነበር። ይህንን እንዴት ይወጡት ይሆን?
17 ዳንኤል ለአራቱ ወጣት አይሁዳውያን መኮንኖች ቃል አቀባይ በመሆን ሕሊናቸውን የሚያስጥስ ምግብ ወይም መጠጥ እንደማይበሉ ወይም እንደማይጠጡ ገና ከመጀመሪያው በግልጽ አስረዳ። (ዳንኤል 1:8, 11-13) ይሖዋም ይህንን ቆራጥ አቋማቸውን በመባረክ በኃላፊነት ቦታ ላይ የነበረውን ባቢሎናዊ ባለ ሥልጣን ልብ አራራላቸው። (ዳንኤል 1:9, 14-16) አራቱም ወጣት ዕብራውያን በኋላ በሕይወታቸው የታዩት ነገሮች በባቢሎናውያን ልማድ የተሰጣቸው የሦስት ዓመት የትምህርት ፕሮግራም ከይሖዋና ከንጹህ አምልኮቱ ጋር ከነበራቸው ጥልቅ ግንኙነት እንዳላራቃቸው ያለምንም ጥርጣሬ ያረጋግጣሉ። (ዳንኤል ምዕራፍ 3 እና 6) በባቢሎናውያን የሦስት ዓመት ከፍተኛ ትምህርት ውስጥ በግዳጅ ቢነከሩም ይሖዋ ያለምንም ጉዳት ከዚያ እንዲወጡ አስቻላቸው። “ለእነዚህም ለአራቱ ብላቴኖች እግዚአብሔር በትምህርትና በጥበብ ሁሉ እውቀትንና ማስተዋልን ሰጣቸው፤ ዳንኤልም በራእይና በሕልም ሁሉ አስተዋይ ነበር። ንጉሡም በጠየቃቸው በጥበብና በማስተዋል ነገር ሁሉ በግዛቱ ሁሉ ከሚኖሩ የሕልም ተርጓሚዎችና አስማተኞች ሁሉ እነርሱ አሥር እጅ የበለጡ ሆነው አገኘባቸው።”—ዳንኤል 1:17, 20
18. ከባቢሎን ግዞት በኋላ በይሁዳ ምን የትምህርት ፕሮግራም ተካሂዶ ነበር?
18 ከባቢሎን ግዞት በኋላ “የእግዚአብሔርን [የይሖዋን አዓት] ሕግ ይፈልግና ያደርግ ዘንድ፣ ለእስራኤልም ሥርዓትንና ፍርድን ያስተምር ዘንድ ልቡን አዘጋጅቶ” በነበረው በዕዝራ አማካኝነት ታላቅ የማስተማር ሥራ ይካሄድ ጀመር። (ዕዝራ 7:10) በዚህ በኩል ‘ሕጉን . . . ለሕዝቡ ያስተምሩ በነበሩት’ ታማኝ የሆኑ ሌዋውያን እርዳታ ያገኝ ነበር። (ነህምያ 8:7) ዕዝራ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሑርና “ፈጣን ጸሐፊ” ወይም ገልባጭ ነበር። (ዕዝራ 7:6) ጻፎች እንደ አንድ ቡድን ሆነው መታወቅ የጀመሩት በሱ ዘመን ነበር።
የአይሁድ መምህራን ትምህርት ቤቶች
19. ኢየሱስ ወደ ምድር በመጣበት ጊዜ በእስራኤል ውስጥ ምን የአስተማሪዎች ቡድን ተፈጥሮ ነበር? እሱና ደቀ መዛሙርቱ የአይሁዳውያንን ከፍተኛ ትምህርት ያልተማሩትስ በምን ዋና ዋና ምክንያቶች ነበር?
19 ኢየሱስ በምድር ላይ በመጣበት ጊዜ ጻፎች ከእውነተኛው የአምላክ ቃል ትምህርቶች ይልቅ ከወጎች ጋር ይበልጥ የተያያዙ የተከበሩ የአስተማሪዎች ቡድን ሆነው ነበር። “ራቢ” በሚባል የክብር ስም መጠራትን ይወድዱ ነበር። ትርጉሙም ታላቁ “መምህር ሆይ” ማለት ነው። (ማቴዎስ 23:6, 7 የአዓት የግርጌ ማስታወሻ) በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ብዙውን ጊዜ ጻፎች ከፈሪሳውያን ጋር ተያይዘው ይጠቀሳሉ። ከፈሪሳውያን አንዳንዶቹ ራሳቸው የሕግ አስተማሪዎች ነበሩ። (ሥራ 5:34) ኢየሱስ በወጋቸውና “የሰውም ሥርዓት የሆነ ትምህርት” በማስተማራቸው የተነሳ የአምላክን ቃል ውድቅ በማድረጋቸው ምክንያት ሁለቱንም ቡድኖች ወቅሷቸዋል። (ማቴዎስ 15:1, 6, 9) ኢየሱስም ሆነ አብዛኞቹ ደቀ መዛሙርቱ በአይሁድ መምህራን ትምህርት ቤቶች ውስጥ ገብተው የተማሩ አለመሆናቸው የሚያስደንቅ አይደለም።—ዮሐንስ 7:14, 15፤ ሥራ 4:13፤ 22:3
20. በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ስለነበረው የትምህርት አሰጣጥ ያደረግነው ይህ አጠር ያለ አጠቃላይ ጥናት ምን ያሳየናል? የይሖዋ አገልጋዮች ትምህርት እንደሚያስፈልጋቸው የሚያመለክተውስ ምንድን ነው?
20 በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ስለነበረው ትምህርት ያደረግነው ይህ አጠር ያለ አጠቃላይ ጥናት ይሖዋ የሕዝቦቹ ታላቅ አስተማሪ እንደሆነ አሳይቷል። አምላክ በሙሴ በኩል በእስራኤል ውጤታማ የሆነ ሥርዓተ ትምህርት አደራጅቶ ነበር። ይሁን እንጂ ከረጅም ጊዜ በኋላ የአይሁዳውያን ከፍተኛ የትምህርት ሥርዓት መጣና ከአምላክ ቃል ጋር የሚቃረኑ ነገሮችን ማስተማር ጀመረ። ኢየሱስ እንዲህ ባሉት የአይሁድ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ገብቶ ባይማርም ተወዳዳሪ የሌለው መምህር ነበር። (ማቴዎስ 7:28, 29፤ 23:8፤ ዮሐንስ 13:13) ደቀ መዛሙርቱንም የማስተማር ተልዕኮ ሰጥቶአቸዋል። እንዲያውም እስከዚህ ክፉ የነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ ድረስ እንዲያስተምሩ ነግሯቸዋል። (ማቴዎስ 28:19, 20) ይህንንም ለማድረግ ጥሩ አስተማሪዎች መሆንና መማርም ነበረባቸው። ስለዚህ በዛሬው ጊዜ ያሉ እውነተኛ ክርስቲያኖች ትምህርትን እንዴት አድርገው ሊመለከቱት ይገባል? ይህን ጥያቄ በሚቀጥለው ርዕሰ ትምህርት እንመረምረዋለን።
የማስታወስ ችሎታን መፈተኛ
◻ ይሖዋ አገልጋዮቹ እንዲማሩ እንደሚፈልግ እርግጠኞች ለመሆን የምንችለው ለምንድን ነው?
◻ የእስራኤል ሥርዓተ ትምህርት ከሌሎች ብሔራት ሥርዓተ ትምህርት የሚለየው በምን በምን መንገዶች ነው?
◻ እስራኤላውያን ልጆች ምን ዓይነት ትምህርት ይሰጣቸው ነበር?
◻ በእስራኤል ውስጥ ምን ዓይነት የማስተማሪያ ዘዴዎች ይሠራባቸው ነበር?
◻ ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ በአይሁዳውያን ከፍተኛ ትምህርት ቤቶች ገብተው ያልተማሩት ለምን ነበር?
[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ዳንኤልና ጓደኞቹ የባቢሎንን ትምህርት እንዲከታተሉ ቢገደዱም ከይሖዋ ዘወር እንዲሉ አላደረጋቸውም