ለይሖዋ በታማኝነት እየቆማችሁ አገልግሉት
“ታማኝ ሆኖ ለሚቆምልህ [ይሖዋ] ታማኝ ሆነህ ትገኛለህ።”—2 ሳሙኤል 22:26 አዓት
1. ይሖዋ ለእርሱ ታማኝ ሆነው ከሚቆሙለት ሰዎች ጋር ያለው አሠራር እንዴት ነው?
ይሖዋ ለሕዝቡ ለሚያደርግላቸው ነገር ሁሉ ወሮታ ሊመለስለት አይችልም። (መዝሙር 116:12) መንፈሳዊና ሥጋዊ ስጦታዎቹና የርህራኄ ምሕረቱ ምንኛ አስደናቂ ናቸው! አምላክ ታማኝ ሆነው ለሚቆሙለት ሰዎች ታማኝ እንደሚሆንላቸው የጥንቱ የእሥራኤል ንጉሥ ዳዊት ያውቅ ነበር። “እግዚአብሔር [ይሖዋ አዓት] ከ[ንጉሥ] ሳኦል እጅና ከጠላቶቹ እጅ ሁሉ ባዳነው ቀን” ዳዊት በጻፈው መዝሙር ላይ ይሖዋ ታማኝ እንደሆነለት ተናግሯል።—2 ሳሙኤል 22:1
2. በ2 ሳሙኤል ምዕራፍ 22 ላይ ተመዝግቦ በሚገኘው የዳዊት መዝሙር ላይ ያሉ አንዳንድ ፍሬ ነገሮች ምንድን ናቸው?
2 ዳዊት (ከመዝሙር 18 ጋር በማመሳሰል) ይሖዋ ለጸሎት መልስ በመስጠት “መሸሸጊያ” መሆኑን በማመስገን መዝሙሩን ይጀምራል። (2 ሳሙኤል 22:2-7) አምላክ ከሰማያዊ ቤተ መቅደሱ ሆኖ ታማኝ አገልጋዮቹን ከኃይለኛ ጠላቶች እጅ ለማዳን እርምጃ ይወስዳል። (ቁጥር 8-19) ስለዚህ ዳዊት የጽድቅ መንገድን በመከተሉና የይሖዋን መንገዶች በመጠበቁ ዋጋውን አግኝቷል። (ቁጥር 20-27) ቀጥሎ የተዘረዘሩት ከአምላክ ባገኘው ብርታት የፈጸማቸው ነገሮች ናቸው። (ቁጥር 28-43) በመጨረሻም ዳዊት በአገሩ ካሉት ስህተት ፈላጊዎችና በውጭ አገር ካሉ ጠላቶች መዳኑን ይጠቅስና “ለንጉሡ ታላቅ የማዳን ሥራ የሚሠራና ለቅቡኡ ፍቅራዊ ደግነትን የሚያሳይ” በመሆኑ ለይሖዋ ምስጋና ያቀርባል። (ቁጥር 44-51 አዓት) የጽድቅን መንገድ ከተከተልንና ብርታት እንዲሰጠን በእርሱ ላይ ከታመንን ይሖዋ እኛንም ሊያድነን ይችላል።
ታማኝ ሆኖ መቆም ምን ማለት ነው?
3. ከቅዱስ ጽሑፉ አንፃር ታማኝ ሆኖ መቆም ማለት ምን ማለት ነው?
3 የዳዊት የመዳን መዝሙር “ታማኝ ሆኖ ለሚቆምልህ [ይሖዋ] ታማኝ ሆነህ ትገኛለህ” በማለት የሚያጽናና ዋስትና ይሰጠናል። (2 ሳሙኤል 22:26 አዓት) “ታማኝ የሆነን ሰው” ወይም “ፍቅራዊ ደግነት ያለውን ሰው” የሚገልጸው ቻሲድ የሚለው የዕብራይስጥ ቃል ነው። (መዝሙር 18:25 የግርጌ ማስታወሻ) ቼሴድ የሚለው ስም የሚያስተላልፈው ሐሳብ ከዓላማው ጋር የተያያዙት ነገሮች ከፍጻሜ እስኪደርሱ ድረስ ከአንድ ነገር ጋር ራሱን በፍቅር የሚያጣብቅ ደግነትን ነው። ይሖዋ ለአገልጋዮቹ ይህን ዓይነት ደግነት ያሳያል፤ እነርሱም ይህን ዓይነት ደግነት ለእርሱ ያሳዩታል። ይህ ጻድቅና ቅዱስ የሆነ ታማኝነት “ፍቅራዊ ደግነት” እና “ታማኝ ፍቅር” ተብሎ ተተርጉሞአል። (ዘፍጥረት 20:13፤ 21:23) በግሪክኛው ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ “ታማኝ ሆኖ መቆም” ሆሲዮቴስ በሚለው ስምና ሆሲዮስ በሚለው ቃል የሚገለጸውን የቅድስናንና የአምልኮታዊ ፍርሃትን ሐሳብ ያስተላልፋል። እንዲህ ዓይነቱ ታማኝነት ታማኝ ሆኖ ከጎን መቆምንና ለአምላክ ያደሩ መሆንን የሚጨምር ሲሆን ትርጉሙ ለአምላክ ያደሩ መሆንና ለአምላክ የሚገባውን ግዳጅ በሙሉ በጥንቃቄ መፈጸም ማለት ነው። ለይሖዋ ታማኝ ሆኖ ከጎኑ መቆም ማለት ልክ እንደ ኃይለኛ ማጣበቂያ ሙጫ በሚያጣብቅ ለአምላክ የማደር ኃይለኛ ስሜት ከእርሱ ከአምላክ ጋር መጣበቅ ማለት ነው።
4. ይሖዋ ታማኝ ሆኖ እንደሚቆም የታየው እንዴት ነው?
4 የይሖዋ የራሱ ታማኝነት በብዙ መንገዶች ተገልጾአል። ለምሳሌ ያህል በክፉዎች ላይ የፍርድ እርምጃ የሚወስደው ለሕዝቡ ባለው ታማኝ ፍቅርና ለፍትሕና ለጽድቅ ባለው ታማኝነት ምክንያት ነው። (ራእይ 15:3, 4፤ 16:5) ከአብርሃም ጋር ለገባው ቃል ኪዳን የነበረው ታማኝነት ለእሥራኤላውያን ታጋሽ እንዲሆንላቸው ገፋፍቶታል። (2 ነገሥት 13:23) ለይሖዋ ታማኝ ሆነው ከጎኑ የሚቆሙ ሁሉ የታማኝነት የሕይወት ጉዟቸውን እስኪፈጽሙ ድረስ የይሖዋን እርዳታ እንደሚያገኙና በኋላም እንደሚያስታውሳቸው እርግጠኞች ሊሆኑ ይችላሉ። (መዝሙር 37:27, 28፤ 97:10) ኢየሱስ ዋናው የአምላክ “ቅዱስ” [“ታማኝ” አዓት] በመሆን ነፍሱ በሲኦል እንደማትቀር በማወቁ ብርታት አግኝቷል።—መዝሙር 16:10፤ ሥራ 2:25, 27
5. ይሖዋ ታማኝ ሆኖ ከጎናችን የሚቆም በመሆኑ ከአገልጋዮቹ ምን ይፈልጋል? ማብራሪያ ማግኘት የሚገባውስ ምን ጥያቄ ነው?
5 ይሖዋ አምላክ ታማኝ ስለሆነ ከአገልጋዮቹ ታማኝነትን ይሻል። (ኤፌሶን 4:24) ለምሳሌ ያህል ወንዶች ለጉባኤ ሽማግሌነት ሹመት እንዲበቁ በታማኝነት የሚቆሙ መሆን አለባቸው። (ቲቶ 1:8) የይሖዋ ሕዝቦች ይሖዋን በታማኝነት ከጎኑ እየቆሙ እንዲያገለግሉት ሊገፋፏቸው የሚገቡት ምን ምክንያቶች ናቸው?
ለተማርናቸው ነገሮች አድናቆት ይኑረን
6. ስለተማርናቸው ቅዱስ ጽሑፋዊ ነገሮች እንዴት ሊሰማን ይገባል? ስለ እንዲህ ዓይነቶቹ እውቀቶችስ ምን ማስታወስ ይገባናል?
6 ለተማርናቸው ቅዱስ ጽሑፋዊ ነገሮች አመስጋኝ መሆን ይሖዋን በታማኝነት እንድንቆምለትና እንድናገለግለው ሊገፋፋን ይገባል። ሐዋርያው ጳውሎስ ጢሞቴዎስን እንደሚከተለው በማለት አጥብቆ አሳስቦታል፦ “አንተ ግን በተማርህበትና በተረዳህበት ነገር ጸንተህ ኑር፣ ከማን እንደተማርኸው ታውቃለህና፤ ከሕፃንነትህም ጀምረህ ክርስቶስ ኢየሱስን በማመን፣ መዳን የሚገኝበትን ጥበብ ሊሰጡህ የሚችሉትን ቅዱሳን መጻሕፍትን አውቀሃል።” (2 ጢሞቴዎስ 3:14, 15) እንዲህ ዓይነቱ ዕውቀት “በታማኝና ልባም ባሪያ” በኩል ከአምላክ የመጣ መሆኑን አስታውስ።—ማቴዎስ 24:45-47
7. ሽማግሌዎች አምላክ በታማኙ ባሪያው በኩል ስለሚያቀርበው መንፈሳዊ ምግብ እንዴት ሊሰማቸው ይገባል?
7 በተለይም የተሾሙ ሽማግሌዎች አምላክ በታማኙ ባሪያ በኩል የሚያቀርበውን የሚያፋፋ መንፈሳዊ ምግብ ማድነቅ ይኖርባቸዋል። ከአያሌ ዓመታት በፊት ጥቂት ሽማግሌዎች እንዲህ ዓይነቱን አድናቆት አጥተው ነበር። እነዚህ ሰዎች “በመጠበቂያ ግንብ ላይ የሚወጡት ትምህርቶች . . . አምላክ እውነትን የሚያስተላልፍባቸው መንገዶች መሆናቸውን ለመቀበል ባለመፈለግ የሚተቹና ሁልጊዜም ሌሎች የእነርሱን አስተሳሰብ እንዲቀበሉ ለመገፋፋት የሚጥሩ” እንደነበሩ አንድ ታዛቢ ገልጿል። ታማኝ ሆነው የሚቆሙ ሽማግሌዎች ግን አምላክ በታማኙ ባሪያ በኩል ከሚያቀርበው መንፈሳዊ ምግብ ማናቸውንም እንዳይቀበሉ ሌሎችን ለመገፋፋት ፈጽሞ አይሞክሩም ነበር።
8. በታማኝና ልባም ባሪያ በኩል የሚቀርቡ አንዳንድ ቅዱስ ጽሑፋዊ ሐሳቦችን ሙሉ በሙሉ መረዳት ባንችል ምን ማድረግ አለብን?
8 ሁላችንም የይሖዋ ውስን ምስክሮች በመሆናችን ለእርሱና ለድርጅቱ ታማኝ በመሆን ከጎናቸው መቆም አለብን። አሁን ወደ መንፈሳዊ ሞት፣ የኋላ ኋላ ደግሞ ወደ ጥፋት ሊመራ የሚችለውን የክህደት መንገድ በመከተል ከአምላክ አስደናቂ ብርሃን ዘወር ማለትን ፈጽሞ ልናስበውም እንኳን አይገባንም። (ኤርምያስ 17:13) ነገር ግን በታማኙ ባሪያ አማካኝነት የሚቀርቡትን አንዳንድ ቅዱስ ጽሑፋዊ ፍሬ ሐሳቦች ሙሉ በሙሉ ለመቀበል ወይም ለመረዳት ከባድ ቢሆንብንስ? እንዲህ ከሆነ እውነትን የተማርነው ከየት መሆኑን በትሕትና አምነን እንድንቀበልና ጉዳዩን የሚያብራራ አንድ ዓይነት ጽሑፍ ተዘጋጅቶ ፈተናችን ወደ ፍጻሜው እስኪመጣ ድረስ ፈተናውን ለመቋቋም ጥበብ እንዲሰጠን እንጸልይ።—ያዕቆብ 1:5-8
ክርስቲያናዊ ወንድማማችነትን አድንቅ
9. 1 ዮሐንስ 1:3-6 ክርስቲያኖች የጓደኝነት ወይም የማኅበርተኝነት መንፈስ ሊኖራቸው እንደሚገባ የሚያሳየው እንዴት ነው?
9 በክርስቲያናዊ ወንድማማችነታችን ውስጥ ላለው የኅብረት መንፈስ ልባዊ አድናቆት ማሳየት ይሖዋን በታማኝነት ከጎኑ ቆመን እንድናገለግለው የሚገፋፋን ሌላ ኃይል ይሰጠናል። እንዲያውም ይህ መንፈስ ከሌለን ከአምላክና ከክርስቶስ ጋር ያለን ዝምድና ጠንካራ ሊሆን አይችልም። ሐዋርያው ዮሐንስ ለቅቡዓን ክርስቲያኖች “እናንተ ደግሞ ከእኛ ጋር ኅብረት እንዲኖራችሁ ያየነውንና የሰማነውን ለእናንተ ደግሞ እናወራላችኋለን። ኅብረታችንም ከአባት ጋር ከልጁም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ነው። . . . ከእርሱ ጋር ኅብረት አለን ብንል በጨለማም ብንመላለስ እንዋሻለን እውነትንም አናደርግም” በማለት ነግሯቸዋል። (1 ዮሐንስ 1:3-6) ይህ መሠረታዊ ሥርዓት ተስፋቸው ሰማያዊም ሆነ ምድራዊ፣ በሁሉም ክርስቲያኖች ላይ ይሠራል።
10. ኤዎድያንና ሲንጤኪን የግል ችግራቸውን ለመፍታት ችግር እንደነበረባቸው በግልጽ ቢታይም ጳውሎስ እነዚህን ሴቶች እንዴት ተመለከታቸው?
10 የኅብረትን መንፈስ ጠብቆ ለማቆየት ጥረት ያስፈልጋል። ለምሳሌ ያህል ኤዎድያንና ሲንጤኪን የተባሉት ክርስቲያን ሴቶች በመካከላቸው የነበረውን ችግር ለመፍታት አስቸጋሪ ሆኖ ያገኙት ይመስላል። በመሆኑም ጳውሎስ “በአንድ አሳብ በጌታ እንዲስማሙ” በጥብቅ አሳስቦአቸዋል። ጨምሮም “አንተም ደግሞ በሥራዬ አብረህ የተጠመድህ እውነተኛ [እውነተኛ የቀንበር ጓደኛዬ አዓት] ሆይ፣ እንድታግዛቸው እለምንሃለሁ፤ ስሞቻቸው በሕይወት መጽሐፍ ከተጻፉት ከቀሌምንጦስና ደግሞ ከእኔ ጋር አብረው ከሠሩት ከሌሎቹ ጋር በወንጌል ከእኔ ጋር አብረው ተጋድለዋልና” ብሏል። (ፊልጵስዩስ 4:2, 3) እነዚያ አምላካዊ የሆኑ ሴቶች ከጳውሎስና ከሌሎች ጋር “በወንጌል” አብረው ተጋድለው ነበር፣ ጳውሎስም “ስሞቻቸው በሕይወት መጽሐፍ ከተጻፉት” መካከል እንደነበሩም እርግጠኛ ነበር።
11. አንድ ታማኝ ክርስቲያን መንፈሳዊ ችግር ቢያጋጥመው ምን ማስታወስ ተገቢ ይሆናል?
11 ክርስቲያኖች በይሖዋ ድርጅት ውስጥ ባገኙት መብት ምን ነገር እንደሠሩና ከይሖዋ ጎን በታማኝነት ቆመው ምን ያህል እንዳገለገሉት የሚያሳይ አርማ አያደርጉም። መንፈሳዊ እክል ሲያጋጥማቸው ለዓመታት ከይሖዋ ጎን ቆመው በታማኝነት የፈጸሙትን አገልግሎት ከግምት አለማስገባት ምንኛ ፍቅር የጎደለው ነው! ‘እውነተኛ የቀንበር ጓደኛ’ ተብሎ የተጠራው ሌሎችን ለመርዳት ዝግጁ የነበረ ታማኝ ወንድም ሳይሆን አይቀርም። አንተም ሽማግሌ ከሆንክ ለመሰል ሽማግሌዎች ርህራኄ በተሞላበት መንገድ እርዳታ ለመስጠት ዝግጁ የሆንክ “እውነተኛ የቀንበር ጓደኛ” ነህን? ሁላችንም ልክ አምላክ እንደሚያደርገው መሰል አማኞች የሠሩትን መልካም ሥራ ከግምት የምናስገባና ቀንበራቸውን በትዕግሥት እንዲሸከሙ በፍቅር የምንረዳቸው እንሁን።—ገላትያ 6:2፤ ዕብራውያን 6:10
የምንሄድበት ሌላ ቦታ የለም
12. የኢየሱስ አነጋገር ‘ከደቀ መዛሙርቱ ብዙዎቹን ወደ ኋላ እንዲመለሱ’ ቢያደርጋቸውም ጴጥሮስ ምን አቋም ወስዶ ነበር?
12 የዘላለም ሕይወት ለማግኘት የምንሄድበት ሌላ ቦታ እንደሌለ ሁልጊዜ ካስታወስን ይሖዋን ከድርጅቱ ጋር ሆነን በታማኝነት እንድንቆምለትና እንድናገለግለው እንነሳሳለን። የኢየሱስ አነጋገር ‘ከደቀ መዛሙርቱ ብዙዎችን ወደ ኋላ እንዲመለሱ’ ባደረጋቸው ጊዜ ሐዋርያቱን “እናንተ ደግሞ ልትሄዱ ትወዳላችሁን?” ሲል ጠየቃቸው። ጴጥሮስ “ጌታ ሆይ፣ ወደ ማን እንሄዳለን? አንተ የዘላለም ሕይወት ቃል አለህ፤ እኛስ አንተ ክርስቶስ የሕያው የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆንህ አምነናል አውቀናልም” በማለት መለሰ።—ዮሐንስ 6:66-69
13, 14. (ሀ) የመጀመሪያው መቶ ዘመን የአይሁዳውያን ሃይማኖት የአምላክን ሞገስ ያጣው ለምን ነበር? (ለ) ለረዥም ጊዜ የይሖዋ ምስክር የሆነ ወንድም ስለሚታየው የአምላክ ድርጅት ምን አለ?
13 በመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ በነበረው የይሁዲነት ሃይማኖት ዘንድ “የዘላለም ሕይወት ቃል” አይገኝም ነበር። የአይሁድ ሃይማኖት ዋና ኃጢአቱ ኢየሱስ መሲሕ መሆኑን አለመቀበሉ ነበር። አይሁዳዊነት በምንም መልኩ ሙሉ በሙሉ በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ላይ የተመሠረተ አልነበረም። ሰዱቃውያን የመላእክትን ሕልውና የሚክዱና በትንሣኤ የማያምኑ ነበሩ። ፈሪሳውያን በዚህ ረገድ ከሰዱቃውያን ጋር ባይስማሙም ቅዱስ ጽሑፋዊ ባልሆኑ ወጎቻቸው ምክንያት የአምላክን ቃል በመሻር በደለኞች ሆነው ነበር። (ማቴዎስ 15:1-11፤ ሥራ 23:6-9) እነዚህ ወጎች አይሁድን በባርነት በመያዝ ብዙዎቹ ኢየሱስን መቀበል አስቸጋሪ እንዲሆንባቸው አድርገው ነበር። (ቆላስይስ 2:8) ሳውል (ጳውሎስ) ‘ለአባቶቹ ወግ የነበረው ቅንዓት’ በድንቁርና የክርስቶስ ተከታዮች ጨካኝ አሳዳጅ እንዲሆን አድርጎት ነበር።—ገላትያ 1:13, 14, 23
14 የአይሁዳውያን ሃይማኖት የአምላክን ሞገስ አጣ፤ ይሖዋ በልጁ ተከታዮች የተገነባውን ‘ለመልካም ሥራ የሚቀና ሕዝብ’ የያዘውን ድርጅት ባርኮት ነበር። (ቲቶ 2:14) ያ ድርጅት ዛሬም አለ፣ አንድ ለረዥም ጊዜ የይሖዋ ምስክር የነበረ ሰው ስለ እርሱ ሲናገር “ለእኔ ከሁሉ የበለጠ ትልቅ ነገር ቢኖር ከሚታየው የይሖዋ ድርጅት ጋር ተጣብቆ የመኖር ጉዳይ ነው። በሰው አስተሳሰብ ላይ ተደግፎ መቆም ምን ያህል የማያስተማምን እንደሆነ የቀድሞ ተሞክሮዬ አስተምሮኛል። አእምሮዬ በዚያ ነጥብ ላይ አንዴ ከቆረጠ በኋላ ከታማኙ ድርጅት ጋር ጎን ለጎን ለመኖር ቁርጥ ውሳኔ አደረግሁ። አለበለዚያ አንድ ሰው የይሖዋን ሞገስና በረከት እንዴት ሊያገኝ ይችላል?” ብሏል። የአምላክን ሞገስና የዘላለም ሕይወት ለማግኘት ልንሄድበት የምንችል ሌላ ቦታ የለም።
15. ከሚታየው የይሖዋ ድርጅትና በውስጡ ኃላፊነት ካላቸው ጋር መተባበር የሚገባን ለምንድን ነው?
15 በአምላክ መንፈስ የሚመራውና ስሙንና ዓላማዎቹን በማሳወቅ ላይ ያለው የይሖዋ ድርጅት ብቻ እንደሆነ ስለምናውቅ ልባችን ከድርጅቱ ጋር እንድንተባበር ሊያነሳሳን ይገባል። እርግጥ በድርጅቱ ውስጥ የኃላፊነት ቦታ የያዙት ሰዎች ፍጽምና የሌላቸው ናቸው። (ሮሜ 5:12) ይሁን እንጂ አሮንና ማርያም በሙሴ ላይ ስህተት ፈላጊዎች በመሆን ከአምላክ የተሰጠ ኃላፊነት አደራ የተሰጠው ለእነርሱ ሳይሆን ለእርሱ መሆኑን በዘነጉ ጊዜ “ይሖዋ ተቆጥቶባቸው” ነበር። (ዘኁልቁ 12:7-9) ዛሬም ታማኝ ክርስቲያኖች “ከዋኖቻቸው” ጋር እንዲተባበሩ ይሖዋ ስለሚፈልግ እነርሱም እንዲሁ ያደርጋሉ። (ዕብራውያን 13:7, 17) በታማኝነት ከጎናቸው እንደቆምን የምናሳየው በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች አዘውትረን በመገኘትና ሌሎችን ‘ለፍቅርና ለመልካም ሥራ የሚያነሳሳ’ ሐሳብ በመስጠት ጭምር ነው።—ዕብራውያን 10:24, 25
የምታንጽ ሁን
16. ይሖዋን በታማኝነት ከጎኑ እንድንቆምለትና እንድናገለግለው ሊያነሳሳን የሚገባው ለሌሎች ምን የማድረግ ፍላጎት ነው?
16 ለሌሎች የምናንጽ ለመሆን ያለን ፍላጎትም ይሖዋን በታማኝነት ከጐኑ ቆመን እንድናገለግለው ሊቀሰቅሰን ይገባል። ጳውሎስ “እውቀት ያስታብያል፣ ፍቅር ግን ያንጻል” በማለት ጽፎአል። (1 ቆሮንቶስ 8:1) አንድ ዓይነት እውቀት ባለ እውቀቶቹን አስታብዮአቸው ስለነበር ጳውሎስ ፍቅርን የሚያሳዩ ሁሉ ፍቅር እነርሱን ያንጻቸዋል ማለቱ መሆን አለበት። ዌይስና ኢንግሊሽ በሚባሉ ፕሮፌሰሮች የተጻፈ መጽሐፍ እንደሚከተለው ይላል፦ “ለመውደድ ችሎታ ያለው ሰው ብዙውን ጊዜ መልሶ ይወደዳል። በማንኛውም የኑሮ ዘርፍ በጎ ምኞትንና አሳቢነትን ለመሰንዘር መቻል . . . እንዲህ ዓይነቶቹን ስሜቶች በሚሰነዝረውና በሚቀበለው ሰው ላይ ጉልህ የሆነ ገንቢ ውጤት ስላለው ለሁለቱም ደስታ ያመጣል።” ‘ከመቀበል ይልቅ መስጠት የበለጠ ደስታ አለው’ የሚሉት የኢየሱስ ቃላት እንደሚያመለክቱት ፍቅር በማሳየት ሌሎችንና ራሳችንን እናንፃለን።—ሥራ 20:35
17. ፍቅር የሚያንጸው እንዴት ነው? ምን ከማድረግስ ይጠብቀናል?
17 በ1 ቆሮንቶስ 8:1 ላይ ጳውሎስ ሥርዓታዊ ፍቅርን የሚያመለክተውን አጋፔ የተሰኘውን የግሪክኛ ቃል ተጠቅሟል። አጋፔ ያንፃል፤ ምክንያቱም ታጋሽና ደግ ነው፣ በሁሉ ነገር ይታገሣል፣ ይጸናል፣ አጋፔ አይወድቅም። ይህ ፍቅር እንደ ኩራትና ቅናት የመሳሰሉትን ጎጂ ስሜቶች ያስወግዳል። (1 ቆሮንቶስ 13:4-8) እንዲህ ዓይነቱ ፍቅር እንደ እኛው ፍጽምና በሌላቸው ወንድሞቻችን ላይ ከማጉረምረም ይጠብቀናል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን በነበሩት እውነተኛ ክርስቲያኖች መካከል “ሾልከው እንደገቡት” ለአምላክ አክብሮት የጎደላቸው ሰዎች ከመሆን ይጠብቀናል። እነዚያ ሰዎች “ጌትነትን የሚጥሉና ሥልጣን [ክብር አዓት] ያላቸውን የሚሳደቡ” ነበሩ፣ በግልጽ እንደሚታየውም አንድ ዓይነት ክብር እንደተሰጣቸው ቅቡዓን ክርስቲያን የበላይ ተመልካቾች ያሉ ግለሰቦችን የሚተናኮሉ ነበሩ። (ይሁዳ 3, 4, 8) እኛ ለይሖዋ ታማኝ ሆነን ከጎኑ በመቆም ከዚህ ጋር ተመሳሳይ የሆነ ነገር እንድናደርግ ለሚገፋፋን ፈተና ፈጽሞ አንሸነፍ።
ዲያብሎስን ተቃወሙ
18. ሰይጣን የይሖዋን ሕዝቦች ምን ሊያደርጋቸው ይፈልጋል? ነገር ግን ይህን ማድረግ የማይችለው ለምንድን ነው?
18 ሰይጣን የአምላክ ሕዝቦች በመሆን ያለንን አንድነት ሊያጠፋ እንደሚፈልግ ማወቃችን ይሖዋን በታማኝነት ከጎኑ ቆመን ለማገልገል ያለንን ቆራጥነት ሊጨምርልን ይገባል። ሰይጣን ሁሉንም የአምላክ ሕዝቦች ለማጥፋትም እንኳን ሳይቀር ይፈልጋል። የዲያብሎስ ምድራዊ አገልጋዮችም አንዳንድ ጊዜ እውነተኛ አምላኪዎችን ይገድላሉ። ነገር ግን ሰይጣን ሁሉንም እንዲያጠፋ አምላክ አይፈቅድለትም። ኢየሱስ ‘በሞት ላይ ሥልጣን ያለውን፣ ይኸውም ዲያብሎስን በሞት ይሽረዋል።’ (ዕብራውያን 2:14) በተለይ በ1914 ክርስቶስ ንጉሥ ከሆነ በኋላ ሰይጣን ከሰማይ ከተባረረ ወዲህ የሚንቀሳቀስበት የግዛት ክልል ውስን ሆኖበታል። ይሖዋ በወሰነው ጊዜ ደግሞ ኢየሱስ ሰይጣንንና ድርጅቱን ይደመስሳቸዋል።
19. (ሀ) ይህ መጽሔት አያሌ ዓመታት ቀደም ብሎ ስለ ሰይጣን ጥረቶች ምን ማስጠንቀቂያ ሰጥቶ ነበር? (ለ) የሰይጣንን ወጥመዶች ለማስወገድ ከመሰል አማኞች ጋር ባለን ግንኙነት ምን ጥንቃቄ ማድረግ አለብን?
19 ይህ መጽሔት አንድ ጊዜ እንደሚከተለው በማለት አስጠንቅቆ ነበር፦ “ሰይጣን ዲያብሎስ በአምላክ ሕዝቦች መካከል ትርምስ ለማምጣት፣ እንዲጣሉና እንዲደባደቡ ለማድረግ፣ ወይም ደግሞ ለወንድሞች የሚኖራቸውን ፍቅር ወደማጥፋት የሚያደርስ የራስ ወዳድነት ጠባይ እንዲያሳዩና እንዲያሳድጉ ለማድረግ ከቻለ እነርሱን ለመዋጥ የሚያደርገው ጥረት ይሳካለታል።” (መጠበቂያ ግንብ፣ ግንቦት 1921፣ ገጽ 134) እርስ በርሳችን ስም እንድንጠፋፋ፣ ወይም እንድንጣላ በማድረግ ዲያብሎስ አንድነታችንን እንዲያናጋ አንፍቀድለት። (ዘሌዋውያን 19:16) እኛ በግላችን ይሖዋን በታማኝነት ከጎኑ ቆመው እያገለገሉ ያሉትን በመጉዳት ወይም ሕይወትን አስቸጋሪ እንድናደርግባቸው በማነሳሳት ሰይጣን ፈጽሞ አያሸንፈን። (ከ2 ቆሮንቶስ 2:10, 11 ጋር አወዳድር።) ከዚህ ይልቅ “በመጠን ኑሩ ንቁም። ባላጋራችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሣ አንበሳ ይዞራልና፤ በዓለም ያሉት ወንድሞቻችሁ ያን መከራ በሙሉ እንዲቀበሉ እያወቃችሁ በእምነት ጸንታችሁ ተቃወሙት” በማለት የተናገራቸውን የጴጥሮስን ቃላት በሥራ ላይ እናውል። (1 ጴጥሮስ 5:8, 9) በሰይጣን ላይ ጽኑ አቋም በመውሰድ የይሖዋ ሕዝቦች በመሆን የተባረከ አንድነታችንን ልንጠብቅ እንችላለን። መዝሙር 133:1-3
በጸሎት አማካኝነት በአምላክ ላይ ተደግፋችሁ ቁሙ
20, 21. በጸሎት አማካኝነት በይሖዋ ላይ ተደግፎ መቆም እርሱን በታማኝነት ከማገልገል ጋር የሚዛመደው እንዴት ነው?
20 በጸሎት አማካኝነት በአምላክ ላይ ተደግፈን መቆማችን ይሖዋን በታማኝነት ከጎኑ ቆመን በማገልገል እንድንቀጥል ይረዳናል። ጸሎታችንን እየመለሰልን እንዳለ ስናይ ይበልጥ ወደ እርሱ እንቀርባለን። ሐዋርያው ጳውሎስ “ወንዶች በስፍራ ሁሉ አለ ቁጣና አለ ክፉ አሳብ የተቀደሱትን እጆች እያነሱ እንዲጸልዩ እፈቅዳለሁ” ብሎ በጻፈ ጊዜ በጸሎት አማካኝነት በይሖዋ አምላክ ላይ ተደግፎ መቆም እንደሚገባ በጥብቅ አሳስቦአል። (1 ጢሞቴዎስ 2:8) ለምሳሌ ያህል ሽማግሌዎች በጸሎት አማካኝነት በአምላክ ላይ መደገፋቸው ምንኛ አስፈላጊ ነው! የጉባኤ ጉዳዮችን ለመወያየት በሚሰበሰቡበት ጊዜ እንዲህ ዓይነቱ ታማኝነት ካላቸው ማቆሚያ ከሌለው ክርክርና በዚህም ሳቢያ ሊከተል ከሚችል የቁጣ ግንፋሎት ይጠብቃቸዋል።
21 በጸሎት አማካኝነት በይሖዋ አምላክ ላይ ተደግፈን መቆማችን በአገልግሎቱ ላለን መብት እንድንጠነቀቅ ይረዳናል። ለብዙ ዓመታት ከይሖዋ ጎን በታማኝነት ቆሞ ያገለገለ አንድ ሰው “በዓለም አቀፉ የአምላክ ድርጅት ውስጥ የሚሰጠንን ማንኛውንም የሥራ ምድብ በፈቃደኝነት መቀበላችንና በምድብ ሥራችን ላይ ሳንነቃነቅ መቆየታችን በልባዊ ጥረታችን ላይ የአምላክን የድጋፍ ፈገግታ ያመጣልናል። የተመደብንበት ሥራ ዝቅተኛ ቢመስልም እንኳን ብዙውን ጊዜ ያ ሥራ በታማኝነት ካልተፈጸመ ሌሎች ብዙ አስፈላጊ አገልግሎቶች ሊጉላሉ እንደሚችሉ ይታወቃል። ስለዚህ ትሑታን ከሆንንና የራሳችንን ስም ሳይሆን በቀጥታ የይሖዋን ስም ለማክበር የምንፈልግ ከሆነ ምንጊዜም ‘ፍንክች የማንል፣ የማንነቃነቅ፣ የይሖዋ ሥራ የሚበዛልን’ እንደሆንን እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን’” ብሏል።—1 ቆሮንቶስ 15:58
22. የይሖዋ ብዙ በረከቶች በታማኝነት ከጎኑ ቆመን ማገልገላችንን እንዴት ሊነኩት ይገባል?
22 እርግጥ በይሖዋ አገልግሎት የምንሠራው ምንም ይሁን ምን፣ ለሚያደርግልን ሁሉ ውለታውን ልንከፍለው አንችልም። በይሖዋ ድርጅት ውስጥ የይሖዋ ወዳጆች በሆኑ ሰዎች ተከበን ስንኖር ምንኛ ተረጋግተን እንኖራለን! (ያዕቆብ 2:23) ሰይጣን ራሱ ሊነቅለው በማይችል ሥር የሰደደ የወንድማማች ፍቅር በሚመነጭ አንድነት ይሖዋ ባርኮናል። እንግዲያው ምንጊዜም በታማኝነት ከጎናችን ከሚቆመው ሰማያዊ አባታችን ጋር እንጣበቅና ሕዝቦቹ በመሆን በአንድነት እንሥራ። አሁንና ለዘላለሙ ከይሖዋ ጎን በታማኝነት ቆመን እናገልግል።
ምን ብላችሁ ትመልሳላችሁ?
◻ ታማኝ ሆኖ መቆም ሲባል ምን ማለት ነው?
◻ ይሖዋን በታማኝነት ከጎኑ እንድንቆምለትና እንድናገለግለው ሊያደርጉን የሚገባቸው አንዳንድ ምክንያቶች ምንድን ናቸው?
◻ ዲያብሎስን መቃወም ያለብን ለምንድን ነው?
◻ ጸሎት ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች እንድንሆን ሊረዳን የሚችለው እንዴት ነው?
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ለይሖዋ ታማኝ ሆነው ከጎኑ የሚቆሙት አገልጋዮቹ አንበሳ መሰል የሆነው ጠላታቸው ዲያብሎስ አንድነታቸውን እንዲያናጋ አይፈቅዱለትም