ጥሩ ምግባር ክፋትን ድል የሚያደርግበት ቀን ይመጣ ይሆን?
ከሁለት ሺህ ዓመት ገደማ በፊት ምንም ጥፋት የሌለበት ኢየሱስ ክርስቶስ የሞት ፍርድ ለመቀበል ፍርድ ቤት ቀርቦ ነበር። እውነትን በመናገሩ ክፉ ሰዎች ሊገድሉት እያሴሩበት ነበር። ሕዝብን ለዓመፅ ያነሳሳል ተብሎ በሐሰት ተከሰሰና ሕዝቡም ይገደል ብሎ ጮኸ። ከአንድ ዝቅተኛ አናፂ ሕይወት ይልቅ ፖለቲካዊ ክብሩን አስበልጦ የተመለከተ አንድ ሮማዊ አገረ ገዥ ኢየሱስን የጭካኔ ሞት እንዲሞት ፈረደበት። ሁኔታው ከውጭ ሲታይ ክፋት ያሸነፈ መሰሎ ነበር።
ይሁን እንጂ ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት በነበረው ምሽት ለደቀ መዛሙርቱ “እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ” በማለት ነግሯቸው ነበር። (ዮሐንስ 16:33) ምን ማለቱ ነበር? በከፊል ሲታይ በዓለም ያለው ክፋት አላስመረረውም ወይም ደግሞ በእርሱ ላይ ለተደረገበት ክፋት ብድር እንዲመልስ አላደረገውም። ዓለም የኢየሱስን አስተሳሰብ በሚፈልገው መንገድ ጨፍልቆ ወደ ክፉ ድርጊት አልመራውም። (በፊሊፕስ ትርጉም ላይ ከሮሜ 12:2 ጋር አወዳድር።) ሲሞትም እንኳን “አባት ሆይ፣ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው” በማለት ስለ ገዳዮቹ ጸልዮአል። — ሉቃስ 23:34
ኢየሱስ እስከ መጨረሻዋ ትንፋሹ ድረስ ክፋት ሊሸነፍ እንደሚችል በተግባር አሳይቷል። ተከታዮቹ በክፋት ላይ የሚያካሄዱትን የራሳቸውን ውጊያ እንዲያጠናክሩ በጥብቅ አሳስቦአቸዋል። ይህን ሊያደርጉ የሚችሉት እንዴት ነው? “ለማንም ስለ ክፉ ፈንታ ክፉን እንዳይመልሱ” የተሰጣቸውን ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር ተግባራዊ በማድረግ እና እንደ ኢየሱስ “ክፉውን በመልካም” በማሸነፍ ነው። (ሮሜ 12:17, 21) ይሁን እንጂ ይህ አካሄድ በእርግጥ ጥሩ ውጤት አለውን?
በዳካው ክፋትን መዋጋት
ኤልሲ በዳካው ታስራ የነበረችና ለአንዲት የ14 ዓመት ሩስያዊት ልጃገረድ ውድ ስጦታ ማለትም የእምነትና የተስፋን ስጦታ የሰጠች አንዲት ጀርመናዊት ሴት ነበረች።
ዳካው በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የረገፉበትና ይህችን ሩስያዊት ወጣት ልጃገረድ ጨምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ላይ አሠቃቂ የሕክምና ሙከራ ይካሄድበት እንደነበር የሚነገርለት ታዋቂ ማጎሪያ ካምፕ ነበረ። ዳካው የክፉ ድርጊት ሠርቶ ማሳያ ቦታ ይመስል ነበር። የሆነ ሆኖ መካን አፈር ይመስል በነበረው እንዲህ ዓይነት ሥፍራም እንኳን ጥሩ ነገር በቅሎበት፣ በብዛትም ተመርቶበታል።
ሂትለርን የሚጠብቁት ቅልብ ወታደሮች እናቷን በጭካኔ በፆታ ሲያስነውሯት ለመመልከት ትገደድ ለነበረችው ለዚህች በአሥራዎቹ የዕድሜ ክልል የምትገኝ ወጣት ኤልሲ በጣም አዘነችላት። ኤልሲ በሕይወቷ ቆርጣ ለልጅቱ ስለ ጥሩነት፣ ስለ ክፋትና ስለ ቅዱስ ጽሑፋዊው የትንሳኤ ተስፋ ልትነግራት የምትችልበትን አጋጣሚ ትፈልግ ነበር። ይህች ወጣት ጓደኛዋ ሰዎችን መጥላት ትታ ሰውን መውደድን አስተማረቻት። ሩስያዊቱ ልጃገረድም በኤልሲ እርዳታ ከዳካው ሰቆቃ ሁኔታ በሕይወት ተረፈች።
ኤልሲ ያደረገችውን ያን ነገር ልታደርግ የቻለችው የክርስቶስን ከራስ ወዳድነት የራቀ ምሳሌ ለመከተል ስለፈለገች ነው። ከይሖዋ ምስክሮች አንዷ ስለነበረች ክፋትን በክፋት እንዳትመልስ ተምራለች፤ ስለዚህ እምነቷ ሌሎችንም እንዲሁ እንዲያደርጉ ለመርዳት አንቀሳቀሳት። በዳካው ሥቃይ የደረሰባት ብትሆንም በክፉው መንግሥት ላይ የሞራል ድል ተቀዳጅታለች። እንዲህ ያለውን ድል ያገኘችው እርሷ ብቻ አልነበረችም።
ፖል ጆንሰን የክርስትና ታሪክ በተሰኘ መጽሐፋቸው ላይ “[የይሖዋ ምስክሮች] ሙሉ በሙሉ ክፉ እንደሆነ ካወገዙት የናዚ መንግሥት ጋር ምንም ዓይነት ትብብር ለማድረግ እምቢተኞች ሆነዋል። . . . ዘጠና ሰባት በመቶ የሚያክሉት ምሥክሮች በተለያየ መንገድ ስደት ደርሶባቸዋል” በማለት ገልጸዋል። ታዲያ ዋጋ ቢስ የሆነ ትግል ነበርን? አና ፓቬልሺንስካ የተባሉ የፖላንድ ተወላጅ የሆኑት ሴት ሶሺዮሎጂስት አቋምና በደል በኦሽዊትዝ በተሰኘ መጽሐፋቸው ላይ ስለ ምስክሮቹ “ይህ አነስተኛ የእስረኞች ቡድን ጠንካራ የሆነ ርዕዮተ ዓለም ያለው ኃይል ስለነበረ በናሲዝም ላይ ባደረገው ውጊያ አሸንፏል” ብለዋል።
ይሁንና ለብዙዎቻችን ዋናው ውጊያችን ከውጭ ካለ ክፋት ማለትም ከውጫዊው የክፋት ተጽእኖዎች ጋር መሆኑ ቀርቶ ከውስጣችን ካለ ክፋት ማለትም ከራሳችን ዝንባሌ ጋር የሚደረግ ነው። ውጊያው ከራሳችን ጋር የሚደረግ ትግል ነው።
በውስጣችን ያለውን ክፋት ማሸነፍ
ሐዋርያው ጳውሎስ ይህን ውጊያ በሚከተለው መንገድ ገልጾታል:- “የማልወደውን ክፉን ነገር አደርጋለሁና ዳሩ ግን የምወደውን በጎውን ነገር አላደርገውም።” (ሮሜ 7:19) ጳውሎስ አሳምሮ እንደሚያውቀው በጎውን ነገር ማድረግ ሁልጊዜ በተፈጥሮ የሚገኝ ቀላል ነገር አይደለም።
ዩጂንዮa በጣም ረዥም ለሆኑበት ሁለት ዓመታት በራሱ የክፋት ዝንባሌ ላይ ውጊያ ያካሄደ የስፓኝ ተወላጅ የሆነ አንድ ወጣት ነበረ። “በራሴ ላይ መጨከን ነበረብኝ” ይላል ሁኔታውን ሲገልጽ። “ከልጅነቴ ጀምሮ የፆታ ብልግና የመፈጸም ዝንባሌ ነበረኝ። በአሥራዎቹ የዕድሜ ክልል እንዳለሁ ግብረ ሰዶም በሚፈጸምባቸው የፈንጠዝያ ቦታዎች ላይ በፈቃዴ ተሳትፌአለሁ፣ እውነቱን ለመናገር እንደዚያ ዓይነቱ አኗኗር ደስ ይለኝ ነበር” ብሏል። ታዲያ የኋላ ኋላ እንዲለወጥ ያደረገው ምንድን ነው?
“አምላክን ለማስደሰት ፈለግሁ፣ ስለዚህ እከተለው የነበረውን አኗኗር እሱ እንደማይደግፈው ከመጽሐፍ ቅዱስ ተማርኩ” አለ ዩጂንዮ። “ስለዚህ የተለየ ዓይነት ሰው ለመሆን፣ በአምላክ መመሪያዎች ለመኖር ወሰንኩ። በየቀኑ ገና ወደ አእምሮዬ ይጎርፍ ከነበረው አፍራሽና የብልግና አስተሳሰብ ጋር መዋጋት ነበረብኝ። በዚህ ውጊያ ለማሸነፍ ቁርጥ ውሳኔ አድርጌ ነበርና የአምላክን እርዳታ ለማግኘት ያለማቋረጥ እጸልይ ነበር። ምንም እንኳን አሁንም በራሴ ላይ ጥብቅ ብሆንም የከፋው መጥፎ ውጊያ ከሁለት ዓመት በኋላ አለፈ። ይሁን እንጂ ትግሉ ዋጋ ያለው ነበር። አሁን ራሴ ለራሴ አክብሮት አለኝ፣ ጥሩ ጋብቻና ከሁሉም ይበልጥ ደግሞ ከአምላክ ጋር ጥሩ ዝምድና አለኝ። በእርግጥ ጥረት ካደረጋችሁ ክፉ አስተሳሰቦች ፍሬ ከማፍራታቸው በፊት ሊወገዱ እንደሚችሉ ከራሴ ተሞክሮ አውቄአለሁ።”
አንድን ክፉ አስተሳሰብ ባስወገድን ቁጥር፣ ክፉን በክፉ ለመመለስ እምቢ ባልን ቁጥር በጎነት ክፋትን ያሸንፋል። ሆኖም እንዲህ ዓይነት ድሎች ምንም ያህል አስፈላጊ ቢሆኑም ሁለቱን ዋነኛ የክፋት ምንጮች ሊያስወግዱአቸው አይችሉም። የቱንም ያህል ብንጣጣር የተወረሰውን ድካማችንን ሙሉ በሙሉ ልናሸንፍ አንችልም፣ ሰይጣንም እስካሁን ድረስ በሰው ልጆች ላይ ክፉ ተጽእኖ ያደርጋል። ታዲያ ይህ ሁኔታ አንድ ቀን ይለወጥ ይሆን?
ዲያብሎስን እንዳልነበር ማድረግ
ኢየሱስ እስከ ሞት ድረስ ታማኝ መሆኑ ለዲያብሎስ ታላቅ ሽንፈት ነበር። ዲያብሎስ የኢየሱስን ፍጹም አቋም ጠባቂነት ለማበላሸት ያደረገው ሙከራ ውድቅ ሆኗል። ይህ ውድቀትም የሰይጣን ፍጻሜ የመጀመሪያው ምልክት ሆኗል። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚገልጸው ኢየሱስ “በሞቱ አማካኝነት . . . ዲያብሎስን ለመሻር” ሞትን ቀምሷል። (ዕብራውያን 2:14) ኢየሱስ ከትንሣኤው በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ “ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጠኝ” ብሎ ነግሯቸዋል። (ማቴዎስ 28:18) ይህንንም ሥልጣን የሰይጣንን ሥራ ለመሻር ይጠቀምበታል።
የራእይ መጽሐፍ ኢየሱስ ሰይጣንን ከሰማይ አውጥቶ ስለወረወረበት ቀን ይገልጻል። ቀንደኛው ክፉ አድራጊ ከአጋንንቱ ጋር እንቅስቃሴው በምድር አቅራቢያ ብቻ መወሰን ነበረበት። በውጤቱም መጽሐፍ ቅዱስ “ለምድርና ለባሕር ወዮላቸው፣ ዲያብሎስ ጥቂት ዘመን እንዳለው አውቆ በታላቅ ቁጣ ወደ እናንተ ወርዶአልና” በማለት ክፋት እንደሚበዛ ያስጠነቅቃል። — ራእይ 12:7–9, 12
ይህ ታሪካዊ ክስተት ቀደም ሲል ማለትም በመጀመሪያው የዓለም ጦርነት አካባቢ እንደተፈጸመ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ያመለክታል።b ይህም በዘመናችን የምንመለከተው ጉልህ የክፋት መብዛት መንስዔው ምን እንደሆነ ማብራሪያ ይሰጣል። ይሁን እንጂ ሰይጣን ዳግመኛ በማንም ላይ ተጽእኖ ለማድረግ እንዳይችል በቅርቡ ሙሉ በሙሉ ይገታል። — ራእይ 20:1–3ን ተመልከት።
ይህስ ሁሉ ለሰው ልጆች ምን ትርጉም ይኖረዋል?
“ክፋት አይሠሩም”
ኢየሱስ የአምላክ መንግሥት ንጉሥ በመሆን ‘በምድር ላይ የተሰጠውን ሥልጣን’ የመንፈሳዊ ማሠልጠኛ ፕሮግራም ለማደራጀት ይጠቀምበታል። “በዓለም [በፍሬያማዋ ምድር አዓት] የሚኖሩ ጽድቅን ይማራሉ።” (ኢሳይያስ 26:9) የዚህ መንፈሳዊ ፕሮግራም ጥቅም ለሁሉም ግልጽ ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስ “አይጎዱም [ክፋት አይሠሩም እንደ ግሪንስ ኢንተርሊኒየር ሂብሪው/ግሪክ ኢንግሊሽ ባይብል] አያጠፉምም፤ ውኃ ባሕርን እንደሚከድን ምድር እግዚአብሔርን በማወቅ ትሞላለችና” በማለት ያረጋግጥልናል። — ኢሳይያስ 11:9
አሁንም እንኳን ብዙዎቹ የክፋት ዝንባሌዎቻችን ሊሸነፉ ይችላሉ። አጋንንታዊ ተጽእኖ ጨርሶ ሲቀር “ከክፉ ፈቀቅ ለማለትና መልካሙን ለማድረግ” እጅግ በጣም ቀላል እንደሚሆን ጥርጥር የለውም። — 1 ጴጥሮስ 3:11
አምላክ ጥሩ በመሆኑ ጥሩነት ክፋትን እንደሚያሸንፍና ጥሩ ነገር ለማድረግ የሚመኙ ሰዎችም ኢየሱስ በራሱ ምሳሌነት እንዳረጋገጠው በአምላክ እርዳታ ክፋትን ለማሸነፍ እንደሚችሉ እርግጠኞች ለመሆን በቂ ምክንያት አለን። (መዝሙር 119:68) አሁን ክፋትን ለመዋጋት ፈቃደኞች የሆኑ ሰዎች ክፋትን እስከነጭራሹ በምታጠፋው በአምላክ መንግሥት በምትተዳደረው የጸዳች ምድር ላይ ለመኖር ተስፋ ሊያደርጉ ይችላሉ። መዝሙራዊው ውጤቱን እንደሚከተለው በማለት ይገልጸዋል:- “ፍቅራዊ ደግነትና እውነት ተገናኙ፤ ጽድቅና ሰላም ተሳሳሙ። እውነት ራሷ ከምድር ትበቅላለች፣ ጽድቅም ከሰማይ በመሆን ቁልቁል ትመለከታለች።” — መዝሙር 85:10, 11 አዓት
[የግርጌ ማስታወሻ]
a እውነተኛ ስሙ አይደለም።
b ተጨማሪ ዝርዝር ለማግኘት በመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የተዘጋጀውን በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ የተሰኘውን መጽሐፍ ገጽ 20–22 ተመልከቱ።