በጥሩና በክፉ ድርጊት መካከል ለዘመናት የቀጠለ ጦርነት
በቀድሞዎቹ ፊልሞች ላይ “ጥሩው ሰው” ምንጊዜም የክፋትን ኃይሎች እንደሚያሸንፍ ተደርጎ ይታይ ነበር። ይሁን እንጂ ተጨባጩ ሐቅ እንደዚህ ቀላል ሆኖ አያውቅም። በእውኑ ዓለም አብዛኛውን ጊዜ ክፋት የሚያይል ይመስላል።
ስለ ክፉ ድርጊቶች የሚሰራጩት ወሬዎች የየምሽቱ ዜና መደበኛ ገጽታ ናቸው። በዩናይትድ ስቴትስ ሰሜናዊ ክፍል አንድ የሚልዋኪ ሰው 11 ሰዎችን ገድሎ የአካላቸውን ቁርጥራጭ በማቀዝቀዣው ውስጥ አጨቀው። በደቡባዊ የአሜሪካ ክፍል ደግሞ አንድ ያልታወቀ ሰው ወደ አንድ የቴክሳስ ምግብ ቤት ውስጥ መኪናውን ነድቶ በመግባት ለአሥር ደቂቃ ያህል ባገኘው ሰው ሁሉ ላይ በመተኮስ ራሱን ጨምሮ 23 ሰዎችን ገደለ። በኮሪያ አንድ ያኮረፈ ተቃዋሚ በይሖዋ ምስክሮች የመንግሥት አዳራሽ ላይ እሳት ለኮሰበትና 14 አምላኪዎች ሞቱ።
አልፎ አልፎ የሚደርሱ እንዲህ ዓይነቶቹ ክፋቶች ከመኖራቸውም ሌላ ዓለምን በሙሉ የሚነካ ዘግናኝ የሆነ ክፋትም አለ፤ እርሱም አንድን ዘር ለመደምሰስ የሚደረግ ጭፍጨፋ ነው። በዚህ መቶ ዘመን ብቻ በዘርና በፖለቲካዊ ምክንያቶች አንድ ሚልዮን አርመኖች፣ ስድስት ሚልዮን አይሁዶችና ከአንድ ሚልዮን በላይ የሚሆኑ የካምቦድያ ሕዝቦች አልቀዋል። በቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ ጎሣዊ ምንጠራ ተብሎ በሚጠራው ዘመቻ ብዙዎች ተረፍርፈዋል። በምድር ዙሪያ ምን ያህል ንጹሐን ሰዎች በአረመኔያዊ ጭካኔ እንደተሠቃዩ የሚያውቅ ሰው የለም።
እነዚህን የመሳሰሉ አሳዛኝ የሆኑ ድርጊቶችን ሰዎች የሚፈፅሙት ለምንድን ነው? ከሚለው የሚረብሽ ጥያቄ ጋር እንድንፋጠጥ ያስገድዱናል። እነዚህ ጭካኔዎች አእምሮአቸው የተዛባ የጥቂት ሰዎች ውጤት ናቸው በማለት ችላ ብለን ልናልፋቸው አንችልም። ባለንበት መቶ ዘመን የተፈጸመው የክፋት መጠን በዘመናችን ያለው ጭካኔ አእምሮአቸው የተዛባ የጥቂት ሰዎች ውጤት ነው የሚለው አባባል እውነት አለመሆኑን ያሳያል።
ክፉ ድርጊት ከሥነ ምግባር አንፃር ስህተት የሆነ ድርጊት ነው የሚል ፍቺ ተሰጥቶታል። ጥሩ ወይም ክፉ ለማድረግ መምረጥ በሚችል ሰው የሚፈጸም ድርጊት ነው። በአንድ ዓይነት መንገድ የሰውየው ሥነ ምግባራዊ ሚዛን ይዛባና ክፋት ያሸንፋል። ይሁን እንጂ ይህ የሚሆነው ለምንና እንዴት ነው?
ክፋት ለምን እንደሚፈጸም ሃይማኖቶች የሚሰጧቸው ማብራሪያዎች ብዙውን ጊዜ አጥጋቢ አይደሉም። ካቶሊካዊ ፈላስፋ ቶማስ አኪናስ “አምላክ ክፋት እንዲኖር ባይፈቅድ ኖሮ ብዙ ጥሩ ነገሮች ይቀሩብን ነበር” ብሏል። ብዙ ፕሮቴስታንት ፈላስፋዎችም ተመሳሳይ አመለካከት አላቸው። ለምሳሌ ያህል ጎትፍሪድ ሊፕኒትስ የተባለው ፈላስፋ በኢንሳይክሎፒድያ ብሪታኒካ ላይ ክፋት “በዓለም ላይ ላለው ደግነት መነሻ ብቻ እንደሆነና ይህ አንፃራዊ ሁኔታ በመኖሩ ጥሩ ነገር በድምቀቱ እየጨመረ የሚሄድ” እንደሆነ አድርጎ ተመልክቶታል። በሌላ አነጋገርም ጥሩ ነገርን ለማድነቅ ክፋት ያስፈልገናል ማለቱ ነው። ሆኖም እንዲህ ዓይነቱ አስተሳሰብ ለአንድ የካንሰር በሽተኛ የእርሱ መታመም ሌላው ሰው በእርግጥ በሕይወት እንዳለና ጤነኛ እንደሆነ እንዲሰማው ለማድረግ የሚያስፈልግ ብቻ ነው ብሎ እንደመናገር ያህል ነው።
ክፉ አሳቦች ምንጭ አላቸው። በተዘዋዋሪ ተወቃሹ አምላክ ይሆን? መጽሐፍ ቅዱስ “ማንም ሲፈተን በእግዚአብሔር እፈተናለሁ አይበል፤ እግዚአብሔር በክፉ አይፈተንምና፤ እርሱ ራሱስ ማንንም አይፈትንም” በማለት መልስ ይሰጣል። ለክፋት ተጠያቂው አምላክ ካልሆነ ታዲያ ማን ነው? የሚቀጥሉት ጥቅሶች መልሱን ይሰጣሉ:- “እያንዳንዱ በራሱ ምኞት ሲሳብና ሲታለል ይፈተናል። ከዚህ በኋላ ምኞት ፀንሳ ኃጢአትን ትወልዳለች፤ ኃጢአትም ካደገች በኋላ ሞትን ትወልዳለች።” (ያዕቆብ 1:13–15) በመሆኑም አንድ ክፉ ድርጊት የሚወለደው አንድ ሰው ክፉውን ምኞት በማስወገድ ፈንታ ተቀብሎ ሲያስተናግደው ነው። ይሁን እንጂ ነገሩ በዚህ ብቻ አያበቃም።
ክፉ ምኞቶች የሚነሱት የሰው ልጅ መሠረታዊ የሆነ ጉድለት ይኸውም የተወረሰ አለፍጽምና ስላለበት መሆኑን ቅዱሳን ጽሑፎች ያስረዳሉ። ሐዋርያው ጳውሎስ “ኃጢአት በአንድ ሰው ወደ ዓለም ገባ በኃጢአትም ሞት፣ እንደዚሁም ሁሉ ኃጢአትን ስላደረጉ ሞት ለሰው ሁሉ ደረሰ” በማለት ጽፏል። (ሮሜ 5:12) በተወረሰው ኃጢአት ምክንያትም ራስ ወዳድነት በሐሳባችን ውስጥ ያለውን ደግነት ሊያይልበትና ርኅራኄአችንን ጭካኔ ሊያሸንፈው ይችላል።
እርግጥ ነው አንድ ዓይነት ጠባይ ስህተት መሆኑን አብዛኞቹ ሰዎች በደመ ነፍስ ያውቃሉ። ሕሊናቸው ወይም ጳውሎስ እንዳለው ‘በልባቸው የተጻፈው ሕግ’ አንድን ክፉ ድርጊት እንዳይፈጽሙ ይከለክላቸዋል። (ሮሜ 2:15) ያም ሆኖ ጭካኔ የተሞላበት አካባቢ እንዲህ ዓይነቶቹን ስሜቶች ሊጫናቸው፣ ኅሊናም በተደጋጋሚ ችላ ከተባለ ሊደነዝዝ ይችላል።a — ከ1 ጢሞቴዎስ 4:2 ጋር አወዳድር።
በዘመናችን የሚፈጸመው የተባባሰ ክፋት በሰብአዊ አለፍጽምና ላይ ብቻ ሊሳበብ ይችላልን? ታሪክ ጸሐፊው ጄፍሪ በርተን ራስል እንደሚከተለው ብለዋል:- “በእያንዳንዳችን ውስጥ ክፋት ያለ መሆኑ እውነት ነው፣ ይሁን እንጂ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ተናጠል ክፋቶች አንድ ላይ ቢደመሩም እንኳን በፖላንድ ባለው የኦሽዊትዝ ማጎሪያ ካምፕ የተፈጸመውን አያክሉም። . . . በዚህን ያህል መጠን የተፈጸመ ክፋት በዓይነቱም ሆነ በመጠኑ የተለየ ይመስላል።” የዚህን በዓይነቱ የተለየ ክፋት ምንጭ ለይቶ ያመለከተ ከኢየሱስ ክርስቶስ ሌላ ምንም የለም።
ኢየሱስ ከመሞቱ ከጥቂት ጊዜ አስቀድሞ እርሱን ለመግደል ያቀዱት ሰዎች ድርጊቱን የሚፈጽሙት ሙሉ በሙሉ በራሳቸው ፈቃድ ብቻ እንዳልሆነ ገልጾ ነበር። አንድ የማይታይ ኃይል እየመራቸው ነበር። ኢየሱስ “እናንተ ከአባታችሁ ከዲያብሎስ ናችሁ፣ የአባታችሁንም ምኞት ልታደርጉ ትወዳላችሁ። እርሱ ከመጀመሪያው ነፍሰ ገዳይ ነበረ፤ እውነትም በእርሱ ስለ ሌለ በእውነት አልቆመም” ብሎአል። (ዮሐንስ 8:44) ኢየሱስ “የዚህ ዓለም ገዢ” ብሎ የጠራው ዲያብሎስ ክፋትን በማነሣሣት ረገድ የጎላ ሚና እንዳለው ግልጽ ነው። — ዮሐንስ 16:11፤ 1 ዮሐንስ 5:19
ሰብአዊ አለፍጽምናና ሰይጣናዊ ተጽእኖ ተዳምረው ለብዙ ሺህ ዓመታት ከፍተኛ ስቃይ አድርሰዋል። በሰው ልጅ ላይ ያደረጉትን አፈና እንዳላሉ የሚያሳይ ምንም ፍንጭ የለም። ታዲያ ክፋት እንዲሁ ይቀጥላልን? ወይስ የጥሩ ምግባር ኃይሎች በመጨረሻው ክፋትን ይደመስሱት ይሆንን?
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በቅርቡ ጥናት የሚያካሂዱ ሰዎች በቴሌቪዥን ላይ በግልጽ በሚታይ ወንጀልና በወጣቶች በሚፈጸሙ የዓመፅ ድርጊቶች መካከል ግንኙነት እንዳለ ተገንዝበዋል። ከፍተኛ ወንጀል የተስፋፋባቸው አካባቢዎችና የተበታተኑ ቤተሰቦችም ለጸረ ማኅበራዊ ጠባዮች መንስኤዎች ናቸው። በናዚ ጀርመን የማያቋርጥ የዘረኝነት ፕሮፓጋንዳ አንዳንድ ሰዎች በአይሁድና በባሪያዎች ላይ የተፈጸመው ጭካኔ ተገቢ እንደሆነ እንዲሰማቸው፣ አልፎ ተርፎም እንዲኩራሩበት አድርጓቸዋል።
[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
U.S. Army photo
[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
U.S. Army photo