“እንደምን አደሩ! የአምላክ ስም ማን እንደሆነ ያውቃሉ?”
በብራዚል ላለው የይሖዋ ምስክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ በፎርታሊዛ ከተማ ከሚኖሩ የ12 ዓመት ዕድሜ ባላቸው መንትያ እህትማማቾች የተጻፈ የሚቀጥለው ደብዳቤ ደርሶት ነበር:-
“በ1990 ገና የአምስተኛ ክፍል ተማሪዎች ሳለን ትምህርት ቤታችን የሳይንስ፣ የሥነ ጥበብና ባሕላዊ ትርዕይት አዘጋጅቶ ነበር። እኛም ሌሎቹ ተማሪዎች ለማዘጋጀት ካቀዱት የተለየ ነገር ለማቅረብ እንደምንፈልግ ለአስተማሪያችን ገለጽን። መምህራችንም ስለ ይሖዋና ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ስንናገር ሰምታን ስለነበረ ‘እንግዲያስ ስለ አምላካችሁ ልትጽፉ ትችላላችሁ’ በማለት ሐሳብ አቀረበችልን።
“እኛም ሁኔታውን ምስክርነት ለመስጠት እንደሚያስችል አጋጣሚ ተመለከትነውና በይሖዋ ስም ላይ ያተኮሩ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች ለማቅረብ ወሰንን። በትላልቅ ፊደላት የተጻፉ የመዝሙር 83:18ን ቃላት አዘጋጀንና በተከፈተ የመጽሐፍ ቅዱስ ሥዕል ላይ አጣበቅነው። እንዲሁም የይሖዋን ስም የያዙ የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞችን በጠረጴዛ ላይ አስቀመጥን። በዚያው ጠረጴዛ ላይ ልዩ ልዩ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን አስቀመጥን። ለጎብኝዎች በይሖዋ ስም የሚጠቀም አንድ በጣም ታዋቂ ፊልም ለማሳየት የቪድዮ ካሴት ቅጂዎችንና ቴሌቪዢን በጠረጴዛው ጫፍ ላይ አስቀመጥን።
“ትርእይቱ በሚካሄድበት ወቅት ወደ ጠረጴዛችን ሰው ሲመጣ ‘እንደምን አደሩ! የአምላክ ስም ማን እንደሆነ ያውቃሉ?’ እንል ነበር። ጎብኝው መልስ እንዲሰጥ አጋጣሚ ከሰጠነው በኋላ እንደ ጆዋ ፌሬይራ ዴ አልሜይዳ፣ ዘ ጀሩሳሌም ባይብል እና የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም ከመሳሰሉት የተለያዩ መጽሐፍ ቅዱሶች ውስጥ ስሙን አውጥተን በማሳየት ‘ተመልከቱ! አያሌ መጽሐፍ ቅዱሶች የአምላክ ስም ይሖዋ መሆኑን ይገልጻሉ’ በማለት ገለጻችንን እንቀጥል ነበር። ከዚያም ቴሌቪዥኑን ከፍተን በማጫወት የፊልሙ ዋና ገጸ ባሕርይ ይሖዋ የአምላክ ስም እንደሆነ ጎላ አድርጎ የሚጠቀምበትን ትርእይት እናሳይ ነበር። ሰዎቹ ፍላጎት ሲያሳዩ ተጨማሪ እውቀት የሚሰጣቸው መጽሔት ወይም ትራክት እንሰጣቸው ነበር።
“ወደ ጠረጴዛችን ከመጡት ወጣቶች አንዱ የወጣቶች ጥያቄዎችና ሊሠሩ የሚችሉ መልሶቻቸው የተሰኘውን መጽሐፍ እንድንሰጠው ጠየቀን። መምህራችን የቤተሰብህን ሕይወት አስደሳች አድርገው የተሰኘውን መጽሐፍ መረመረችና ‘አቤት አቤት! ምንኛ የሚያስደስት መጽሐፍ ነው!’ በማለት በአድናቆት ተናገረች። እስከ ትርእይቱ መጨረሻ ድረስ 7 መጻሕፍትን፣ 18 ትራክቶችንና 67 መጽሔቶችን አበረከትን። በትርእይቱም የሦስተኛነትን ማዕረግ አግኝተን ተሸለምን። ከሁሉ በላይ ግን መለኮታዊውን ስም ይሖዋን ለማሳወቅ መብት በማግኘታችን በጣም ተደስተናል።”