የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w93 4/1 ገጽ 4-7
  • መጠመቅ ይኖርብሃልን?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • መጠመቅ ይኖርብሃልን?
  • መጠበቂያ ግንብ—1993
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • በምን ዓይነት ሁኔታ?
  • ለምን ዓላማ?
  • ምን ታደርጋለህ?
  • መጠመቅ ለምን አስፈለገ?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2002
  • ጥምቀት ምንድን ነው?
    የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው
  • የጥምቀትህ ትርጉም
    እውነተኛው አንድ አምላክ ያስገኘው የአምልኮ አንድነት
  • ለመጠመቅ የሚያስችለውን ብቃት ማሟላት
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2006
ለተጨማሪ መረጃ
መጠበቂያ ግንብ—1993
w93 4/1 ገጽ 4-7

መጠመቅ ይኖርብሃልን?

ባለፉት ሦስት ዓመታት ውስጥ ወደ አንድ ሚልዮን የሚጠጉ ሰዎች በይሖዋ ምስክሮች ተጠምቀዋል። ይህም በቀን ወደ 824 ሰዎች ወይም በየ7 ደቂቃው 4 ሰዎች ተጠምቀዋል ማለት ነው። ይህ በ15ኛውና በ16ኛ መቶ ዘመናት በሃይማኖታዊ ቅንዓት በመነሳሳት ይደረግ እንደነበረው ያለ ጥምቀት ነውን?

አይደለም፤ እነዚህ ግለሰቦች የተጠመቁት በኃይል ተገደው፣ ሰዎችን በጅምላ ወደ ክርስትና ለመለወጥ የሚደረገው ድርጊት ክፍል በመሆናቸው ወይም በአንዳንድ ሃይማኖታዊ ሰባኪዎች ስሜታዊ ቅስቀሳ ምክንያት አይደለም። እነሱ የተጠመቁት የክርስቲያኖች ጌታና መሪ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲጠመቁ በሰጠው ትእዛዝ መሠረት ነው። ኢየሱስ ያወጣቸውን መመሪያዎችና እርሱ ራሱ መርጦ ያሰለጠናቸው ሐዋርያት የወሰዷቸውን እርምጃዎችና ሂደቶች ተከትለዋል።

ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ ወደ ሰማይ ከማረጉ ቀደም ብሎ ለተከታዮቹ ይህንን የመሰናበቻ ትእዛዝ ሰጣቸው:- “እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፣ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ እነሆም እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ።” (ማቴዎስ 28:​19, 20) ከዚያ ጊዜ ጀምሮ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያለው የውኃ ጥምቀት ይህ ብቻ ነው።

በዚህ መሠረት የመጀመሪያዎቹ የክርስቶስ ተከታዮች “በኢየሩሳሌምም በይሁዳም ሁሉ በሰማርያም እስከ ምድር ዳርም ድረስ [የኢየሱስ] ምስክሮች” እንደሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል። (ሥራ 1:​8) ኢየሱስ አስቀድሞ እንደተናገረው የስብከቱና የማስተማሩ ሥራቸው ያመኑትን ሰዎች ማጥመቅን ያስከትላል። የተጠመቁትም የክርስቶስ ተከታዮች ይሆናሉ።

የዚህ ዓይነቱ ጥምቀት ተመዝግቦ የሚገኝ የመጀመሪያ ምሳሌ በ33 እዘአ በጰንጠቆስጤ ዕለት የተከናወነው ነው። በዚያ ጊዜ ሐዋርያው ጴጥሮስ ‘ከአሥራ አንዱ ጋር ቆሞ’ ለተሰበሰበው ሕዝብ ስለ መሲሑ ስለ ኢየሱስ ተናገረ። ዘገባው እንደሚነግረን በንግግሩ ‘ልባቸው ተነካና’ ምን ማድረግ እንደሚኖርባቸው ጠየቁ። ጴጥሮስም “ንስሐ ግቡ፣ ኃጢአታችሁም ይሰረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ” አላቸው። በውጤቱም “ቃሉንም የተቀበሉ ተጠመቁ፣ በዚያም ቀን ሦስት ሺህ የሚያህል ነፍስ ተጨመሩ።” (ሥራ 2:​14–41) ደቀ መዛሙርቱ ከመጠመቃቸው በፊት የክርስትናን መልእክት ሰምተው በምሥራቹ በማመን ንስሐ እንደገቡ ቀጥሎ ያሉት ዘገባዎች ያረጋግጡልናል። — ሥራ 8:​12, 13, 34–38፤ 10:​34–48፤ 16:​30–34፤ 18:​5, 8፤ 19:​1–5

በምን ዓይነት ሁኔታ?

ነገር ግን እነዚህ አዳዲስ ደቀ መዛሙርት በውኃ የሚጠመቁት እንዴት ነበር? ውኃ በመርጨት፣ በጭንቅላት ላይ በማፍሰስ ወይስ ሙሉ በሙሉ ውኃ ውስጥ በመጥለቅ ነበር? የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ የሚያሳየው ምንድን ነው? ኢየሱስ ‘ፍለጋውን በጥንቃቄ እንድንከተል’ ምሳሌ ትቶልናል፤ ታዲያ እርሱ የተጠመቀው እንዴት ነበር? — 1 ጴጥሮስ 2:​21

ኢየሱስ ትልቅ ወንዝ በነበረው በዮርዳኖስ እንደተጠመቀ መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል። ከተጠመቀ በኋላ “ከውኃ ወጣ።” (ማርቆስ 1:​10፤ ማቴዎስ 3:​13, 16) ስለዚህ በእርግጥ ኢየሱስ በዮርዳኖስ ወንዝ ውስጥ ሙሉ በሙሉ ጠልቆ ነበር። ኢየሱስ የተጠመቀው በዮሐንስ ነበር። ዮሐንስ ደግሞ ጥምቀት ለማከናወን የሚያመች ቦታ ሲፈልግ “በዚያ ብዙ ውኃ ነበረና” በሳሌም አቅራቢያ በዮርዳኖስ ሸለቆ ያለውን ቦታ መርጦ ነበር። (ዮሐንስ 3:​23) ሙሉ በሙሉ በውኃ ውስጥ ማጥለቅ የኢየሱስ ተከታዮች ጥምቀት የሚያከናውኑበት መደበኛው ሥርዓት እንደነበረ ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ከተናገራቸው ቃላት ለመረዳት ይቻላል። ፊልጶስ ላስተማረው ትምህርት አዎንታዊ ምላሽ በመስጠት “እነሆ ውኃ፤ እንዳልጠመቅ የሚከለክለኝ ምንድር ነው?” ሲል ጠይቋል። ከዚያም “ሁለቱም ወደ ውኃ ወረዱ፣ አጠመቀውም።” በኋላም ‘ከውኃው እንደወጡ’ መመልከት እንችላለን። — ሥራ 8:​36–39

የዓለም ታሪክ በክርስቲያኖች ዘንድ ይደረግ የነበረው ጥምቀት ሙሉ በሙሉ ውኃ ውስጥ በመጥለቅ መሆኑን ያመለክታልን? በእርግጥ ያመለክታል። ሙሉ በሙሉ ውኃ ውስጥ ለማጥለቅ የሚመቹ በርካታ ትልልቅ የማጥመቂያ ገንዳዎች በብዙ አገሮች ውስጥ እስከ ዛሬ ድረስ ይገኛሉ። ሚኒስትሪ የተባለው መጽሔት “ከመጀመሪያዎቹ አሥር እስከ አሥራ አራት መቶ ዘመናት ድረስ ሙሉ በሙሉ ውኃ ውስጥ ማጥለቅ የተለመደ የማጥመቅ ሥርዓት የነበረ መሆኑን በጣም ብዙ የመሬት ቁፋሮ መረጃዎች ይመሰክራሉ” ሲል ይገልጻል። አክሎም እንዲህ አለ:- “ከጥንቶቹ የቤተ ክርስቲያን ፍርስራሾችና አሁንም ግልጋሎት እየሰጡ ካሉት ጥንታዊ ቤተ ክርስቲያኖች ለክርስቲያኖች ጥምቀት ታሪካዊ ማስረጃ ሊሆኑ የሚችሉ አንዳንድ ምልክቶችን ማግኘት ይቻላል። በካታኮምብ ዋሻዎችና በቤተ ክርስቲያኖች የሚገኙት ሥዕሎች፤ ሞዛይክ በተለጠፈባቸው ወለሎች፣ ግድግዳዎችና ጣሪያዎች እንዲሁም በጥንታዊ የአዲስ ኪዳን የብራና ጽሑፎች ላይ ያሉት ሥዕሎች ለክርስቲያናዊው ጥምቀት ታሪክ ተጨማሪ ዝርዝር ማስረጃዎችን ይሰጣሉ። . . . ይህም የጥንቶቹ የቤተ ክርስቲያን አባቶች በጻፏቸው ጽሑፎች ውስጥ ሁሉ ከሚገኘው የጥንቱ ቤተ ክርስቲያን የተለመደ የማጥመቂያ ዘዴ ሙሉ በሙሉ ውኃ ውስጥ መንከር እንደሆነ ከሚገልጸው ማስረጃ በተጨማሪ ነው።”

ዘ ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፔድያ “በጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ጥምቀት ይከናወን የነበረው ሙሉ በሙሉ በውኃ ውስጥ በማጥለቅ እንደነበር ከማስረጃዎቹ ለማየት ይቻላል” ሲል አምኗል። እንግዲያው በጋዜጦች ርዕሰ አንቀጽ ላይ እንደሚከተሉት ያሉ ርዕሶችን ማግኘት አያስደንቅም:- “ካቶሊኮች ሙሉ በሙሉ ውኃ ውስጥ በማጥለቅ የሚደረገውን የጥምቀት ሥርዓት መልሰው አመጡ” (The Edmonton Journal, ካናዳ፣ መስከረም 24, 1983)፣ “እዚህ ባሉት ካቶሊኮች ዘንድ ሙሉ በሙሉ ውኃ ውስጥ አጥልቆ ማጥመቅ የተለመደ ሆኗል” (St. Louis Post-Dispatch, ሚያዝያ 7, 1987)፣ “ብዙ ካቶሊኮች ሙሉ በሙሉ ውኃ ውስጥ በማጥለቅ ማጥመቅን መርጠዋል” (The New York Times, መጋቢት 25, 1989) እንዲሁም “ሙሉ በሙሉ በውኃ ውስጥ አጥልቆ ማጥመቅ እያንሰራራ ነው” (The Houston Chronicle, ነሐሴ 24, 1991)።

ለምን ዓላማ?

ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ እንዲጠመቁ የደነገገው ለምን ነበር? ጥምቀት በሙሉ ልባቸው ራሳቸውን ለአምላክ መወሰናቸውን የሚያሳይ ተስማሚ ምልክት ስለሆነ ነው። ‘ምሥራቹ’ በዓለም በሙሉ መሰበክ ይገባዋል፤ ‘ከሁሉም ሕዝቦች የተውጣጡ ሰዎች’ ደቀ መዛሙርት መሆን ይኖርባቸዋል። (ማቴዎስ 24:​14፤ 28:​19) ይህም ማለት አምላክ ከተወለዱበት ጊዜ ጀምረው ለእርሱ የተወሰነ ከሆነው ከአይሁድ ሕዝብ ጋር ብቻ ግንኙነት ማድረጉን ያቆማል ማለት ነው። ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚናገረውን እውነት ተቀብለው የተጠመቁ የመጀመሪያዎቹ አሕዛብ ወይም አይሁዳውያን ያልሆኑ ሰዎች ቆርኔሌዎስና ቤተሰቡ ሆኑ።

ውኃ ውስጥ መጥለቅ ተጠማቂዎቹ በራስ ላይ ለሚያተኩር የሕይወት ጉዞ የሞቱ መሆናቸውን ያሳያል። ከውኃው ውስጥ መውጣታቸው ደግሞ አሁን የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ ሕያዋን መሆናቸውንና ኢየሱስ እንዳደረገው በሕይወታቸው ውስጥ ለአምላክ ፈቃድ ቀዳሚውን ቦታ እንደሰጡት የሚያሳይ ምልክት ነው። (ማቴዎስ 16:​24) “በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም” መጠመቅ ስለ እያንዳንዳቸው የሚናገረውን እውነት ተምረው እንደተቀበሉ እንዲሁም ማንነታቸውን እንደተገነዘቡ ያመለክታል። (ማቴዎስ 28:​19፤ ከሥራ 13:​48 ጋር አወዳድር።) ጥምቀት አምላክን ለመታዘዝና ለፈቃዱ ለመገዛት የሚወሰድ የመጀመሪያ እርምጃ ብቻ ነው።

ጥምቀት ለሚጠመቀው ሰው ጸጋን፣ ቅድስናን ወይም መንፈሳዊ ጥቅምን የሚያላብስ ቅዱስ ሃይማኖታዊ ምሥጢር ነው የሚለውን በሰፊው የሚታመንበትን ሃይማኖታዊ አመለካከት ቅዱሳን ጽሑፎች አይደግፉትም። ለምሳሌ ያህል ባለፈው ርዕሰ ትምህርት የተጠቀሰው የጳጳስ ዮጂንየስ አራተኛ ድንጋጌ ጥምቀትን በተመለከተ እንዲህ በማለት ይቀጥላል:- “የዚህ ቅዱስ ምሥጢር ውጤት በውርሻ የመጣውንም ሆነ የተሠራውን ኃጢአት መደምሰስ፤ እንዲሁም በኃጢአት ምክንያት የሚመጣውን ቅጣት ሁሉ ማስቀረት ነው። በዚህም ምክንያት ተጠማቂዎቹ ባለፉት ጊዜያት የሠሯቸው ኃጢአቶች አይቆጠሩባቸውም፤ ከጥምቀታቸው በኋላ ምንም ኃጢአት ሳይሠሩ ከሞቱ ደግሞ ወዲያውኑ መንግሥተ ሰማያት በመግባት አምላክን ለማየት ይችላሉ።”

ይሁን እንጂ ኢየሱስ ‘ኃጢአትን ያላደረገ’ ቢሆንም እንኳን ተጠምቋል። (1 ጴጥሮስ 2:​22) ከዚህም በላይ በቅዱሳን ጽሑፎች መሠረት የኃጢአት ይቅርታ ሊገኝ የሚችለው በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት ብቻ ነው። ሐናንያ የጠርሴሱን ሳውል:- “ተነሣና [የኢየሱስን ስም ] እየጠራህ ተጠመቅ ከኃጢአትህም ታጠብ ” ሲል አሳስቦታል። (ሥራ 22:​12–16) አዎን፤ መዳን የሚቻለው በፈሰሰው በኢየሱስ ደም አማካኝነትና በእምነት ‘ስሙን በመጥራት’ ብቻ ነው። — ዕብራውያን 9:​22፤ 1 ዮሐንስ 1:​7

በ1 ጴጥሮስ 3:​21 ላይ ስላሉት የጴጥሮስ ቃላትስ ምን ሊባል ይቻላል? እዚያ ላይ ጴጥሮስ እንዲህ አለ:- “ይህም ውኃ ደግሞ ማለት ጥምቀት ምሳሌው ሆኖ አሁን ያድነናል፣ (የሰውነትን እድፍ ማስወገድ አይደለም፣ ለእግዚአብሔር የበጎ ሕሊና ልመና ነው እንጂ፣) ይህም በኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ነው።” ጴጥሮስ ጥምቀትን ኖህ በጥፋት ውኃ ውስጥ ሲያልፍ ካጋጠመው ሁኔታ ጋር እያወዳደረው ነበር። (ቁጥር 20) ኖህ በአምላክ ላይ ሙሉ እምነት ስለነበረው ቤተሰቡን ለማዳን መርከብ ሠራ። (ዕብራውያን 11:​7) በተመሳሳይም በዛሬው ጊዜ ሰዎች በይሖዋ አምላክና እርሱ በክርስቶስ ኢየሱስ በኩል በከፈተው የመዳን ዝግጅት ላይ እምነት በማድረግ ከዚህ ክፉ ዓለም ሊድኑ ይችላሉ። ይህንን እምነታቸውንም በሥራ ማሳየት አለባቸው። ከኃጢአት ንስሐ በመግባት፣ ከተሳሳተ መንገድ በመመለስና በጸሎት አማካኝነት ራሳቸውን ለይሖዋ አምላክ ያለ ገደብ በመወሰን ጥሩ ሕሊና ለማግኘት አምላክን ለመጠየቅ ይችላሉ። ነገር ግን ለኃጢአት ይቅርታ የሚገኘውና መዳን የሚቻለው የኢየሱስን መሥዋዕትና እርሱ የመሥዋዕቱን ዋጋ ለአምላክ በሰማይ ለማቅረብ ያስቻለውን ትንሣኤን መሠረት በማድረግ ነው። — 1 ጴጥሮስ 3:​22

ምን ታደርጋለህ?

ለተወሰነ ጊዜ ከይሖዋ ምስክሮች ጋር የቅርብ ግንኙነት ስታደርግ የቆየህ ነህን? ምናልባትም በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች መሠረት በሕይወትህ ውስጥ አስፈላጊ ለውጦችን አድርገህ ይሆናል፤ ነገር ግን ራስህን ለመወሰንና ለመጠመቅ ገና እርምጃ አልወሰድክ ይሆናል። የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ ብትፈልግም ጥምቀት ግዴታ ውስጥ ያስገባኛል ብለህ ትፈራ ይሆናል። በዚህ ምክንያት ለተወሰነ ጊዜ እንዲህ ዓይነቱን ኃላፊነት ወይም ተጠያቂነት ላለመቀበል ትመርጥ ይሆናል። ባለፈው ዓመት ወደ 11.5 ሚልዮን የሚጠጉ ሰዎች በጌታ ራት በዓል ላይ ተገኝተው ነበር። ይሁን እንጂ ዓመቱን ሙሉ የምሥራቹን በመስበኩ ሥራ ይካፈሉ የነበሩት ሰዎች ከፍተኛ ቁጥር ከ4.5 ሚልዮን የሚያንስ ነበር። ይህ ማለት ሰባት ሚልዮን የሚያህሉ ሰዎች ለአምላክ እውነት የተወሰነ አድናቆት እያሳዩ ቢሆንም የተጠመቁ የይሖዋ ምስክሮች አይደሉም። በእርግጥ ከእነዚህ አንዳንዶቹ ትንንሽ ልጆችና ፍላጎት ያሳዩ አዳዲስ ሰዎች ናቸው። በስብከቱ ሥራ ከሚካፈሉት ውስጥም ቢሆን አንዳንዶቹ ገና ያልተጠመቁ ናቸው። ስለዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ትክክለኛ እውቀት ቢያገኙም ባለመጠመቃቸው በአምላክ የመዳን ዝግጅት ሙሉ በሙሉ ያልተጠቀሙ ብዙ ሰዎች አሉ።

ልታስታውሰው የሚገባህ በጣም አስፈላጊ ነጥብ ኃላፊነት የሚያስከትልብህ አምላክ ከአንተ የሚፈልግብህን ነገር ማወቅህ መሆኑን ነው። ያዕቆብ 4:​17 “እንግዲህ መልካም ነገር ማድረግን እያወቀ የማያደርግ ሰው፣ አለማድረጉ ኃጢአት ይሆንበታል” ይላል። (የ1980 ትርጉም ) ሕዝቅኤል 33:​7–9 የአምላክ ትዕዛዛትና መመሪያዎች የተነገሩት ሰው እነዚህን ነገሮች በሥራ ላይ የማዋል ኃላፊነት እንዳለበት ያሳያል። ስለዚህ ዋናው ጥያቄ ሰውየው ለአምላክ ልባዊ የሆነ ፍቅርና እርሱን ለማስደሰት እውነተኛ ፍላጎት አለው ወይስ የለውም የሚል ነው። በእርግጥ እንዲህ ዓይነቱ ፍቅር ያለውና ከይሖዋ አምላክ ጋር ልዩ ዝምድና እንዲኖረው የሚፈልግ ሰው ሕይወቱን ለአምላክ ያለገደብ ከመወሰን ወደኋላ አይልም። ጥምቀት ራስን የመወሰን ውጪያዊ ምልክት ነው። ለመዳን የሚደረግ አስፈላጊ እርምጃ ነው። እውነተኛ አማኞች ይጠመቃሉ። — ሥራ 8:​12

ራሳቸውን ለወሰኑ ታማኝ ግለሰቦች በምትመጣዋ አዲስ ዓለም ውስጥ አምላክ ከሚያደርግላቸው ታላላቅ ነገሮች አንጻር ሲታይ ይህ አሮጌና ክፉ የነገሮች ሥርዓት የሚሰጣቸው ከሚመስሉት ጊዜያዊ ጥቅሞች በከፍተኛ ሁኔታ የሚያመዝኑ ናቸው። የአምላክን ኃያል ክንድ ስናስብ እንደ እኛው ላሉ ሰዎች የሚኖረን ፍርሃት ይጠፋል። (1 ቆሮንቶስ 10:​22፤ 1 ጴጥሮስ 5:​6, 7) በእውነትም ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ፊልጶስን “እንዳልጠመቅ የሚከለክለኝ ምንድር ነው?” ሲል እንደጠየቀው ራስህን የምትጠይቅበት ጊዜው አሁን ነው።

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ልክ እንደ ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ “ እንዳልጠመቅ የሚከለክለኝ ምንድር ነው?” ብለህ ራስህን ትጠይቃለህን?

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ