በደቡብ አፍሪካ ውስጥ ከይሖዋ ድርጅት ጋር ማደግ
ፍራንስ ሙለር እንደተናገረው
ወንድሜ ዴቪድና እኔ እንደ ልማዳችን ከኬፕ ታውን ማዕከላዊ የባቡር ጣቢያ በማታው ባቡር ለመሳፈር በምንሄድበት ጊዜ “ለነጮች ብቻ” የሚል ጽሑፍ ያለበትን ምልክት ስናይ ተገረምን። በ1948 በተደረገው ምርጫ ብሔራዊው ፓርቲ አሸነፈና የአፓርታይድን ፖሊሲ አስጀመረ።
በእርግጥ ቅኝ ገዥዎች በነበሩበት ጊዜ በብዙዎቹ የአፍሪካ አገሮች እንደነበረው ሁሉ በደቡብ አፍሪካም የዘር ልዩነት ለብዙ ዓመታት ሲሠራበት ቆይቶ ነበር። አሁን ግን ይህ ሁኔታ በሕግ የሚሠራበት ነገር ስለሆነ ጥቁር የቆዳ ቀለም ካላቸው ደቡብ አፍሪካውያን ጋር በአንድነት እንድንጓዝ አልተፈቀደልንም። ከአርባ አራት ዓመታት በኋላ ዛሬ አፓርታይድ እየፈራረሰ ነው።
አፓርታይድ ሕጋዊ በነበረባቸው ጊዜያት ሁሉ የሙሉ ጊዜ አገልጋይ የይሖዋ ምስክር ሆኜ አገልግያለሁ። እነዚያ ዓመታት አገልግሎታችንን የምንፈልገውን ያህል ማከናወን ፈታኝ እንዲሆን አድርገውብን ነበር። አሁን በ65 ዓመቴ የይሖዋ ድርጅት በደቡብ አፍሪካ ውስጥ ያደረገውን ግሩም ዕድገት ወደኋላ መለስ ብዬ ለመመልከት ችያለሁ። አብሬው ለማደግ ላገኘሁትም መብት በጣም አመስጋኝ ነኝ።
ክርስቲያናዊ ውርሻ
አባቴ ወጣት በነበረበት ጊዜ ዘወትር ጠዋት ጠዋት ድምፁን ከፍ አድርጎ ለወንድ አያቴ መጽሐፍ ቅዱስ ማንበብ ነበረበት። ከጊዜ በኋላ አባቴ ለአምላክ ቃል ጥልቅ ፍቅር አደረበት። በ1928 ስወለድ አባቴ ፖትጌትርዝረስት በምትባል ከተማ በነበረው የደች የተሐድሶ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያገለግል ነበር። በዚያ ዓመት አጎቴ ዘ ሃርፕ ኦቭ ጐድ የተባለውን መጽሐፍ ቅጂ ሰጠው።
ይሁን እንጂ መጽሐፉ የመናፍቃን መጽሐፍ ነው በማለት አባቴ እንድታቃጥለው ለእናቴ ነገራት። እርሷ ግን ሳታቃጥል አስቀመጠችው። አንድ ቀን አባቴ እንዳጋጣሚ መጽሐፉን አንስቶ ሲገልጠው “አምላክ ሰውን ያሰቃያልን?” የሚለውን ርዕስ አየ። ምንም እንኳን በዚያን ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ተብለው ይጠሩ የነበሩት የይሖዋ ምስክሮች ትክክል እንዳልሆኑ እርግጠኝነት ቢሰማውም ነገሩን ለማወቅ የነበረው ጉጉት ይህንን አሳቡን አሸነፈውና መጽሐፉን ማንበብ ጀመረ። መጽሐፉን ማንበብ ማቆም አልቻለም። ሊነጋጋ ሲል ለመተኛት ወደ አልጋው እየሄደ “ነገሩን ለማመን ባልፈልግም እውነት ያላቸው እነርሱ ናቸው የኔ ፍቅር” አለ።
በማግስቱ አባቴ በአቅራቢያችን ካለ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ ተጨማሪ መጽሐፍቶችን ለማግኘት ሲል 50 ኪሎ ሜትር ያህል በብስክሌቱ ተጓዘ። በየቀኑ ሳያቋርጥ እስከ ሌሊት ድረስ እየቆየ ያነብ ነበር። እንዲያውም ቤተ ክርስቲያኑ ማስተካከያዎችን ያደርግ ይሆናል ብሎ ተስፋ በማድረግ ይማራቸው ስለነበሩት የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች የደች የተሐድሶ ቤተ ክርስቲያንን ቄስ ለማሳመን ይሞክር ነበር። ጥረቱ ሁሉ ከንቱ ስለነበር ከቤተ ክርስቲያኑ ወጣና በቅንዓት መስበክ ጀመረ። የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ዋናው የሕይወቱ ክፍል ሆነ፤ በቤታችንም ውስጥ ከሁሉ የበለጠ ከፍተኛ ጉዳይ ሆነ። ያደግሁት እንዲህ ባለ ሁኔታ ውስጥ ነበር።
በኋላ አባቴ አቅኚ ወይም የሙሉ ጊዜ አገልጋይ ሆነ። ለመስበክ ሲል ሞዴል ቲ በሆነችው አሮጌ ፎርድ መኪናው ረጅም ርቀቶችን ይጓዝ ነበር። እየጨመረ ለመጣው ቤተሰባችን የሚያስፈልጉ ነገሮችን ለማሟላት ሲል ከጥቂት ዓመታት በኋላ አቅኚነትን ለማቆም ተገደደ። ቢሆንም በስብከቱ ሥራ በከፍተኛ ትጋት መካፈሉን ቀጠለ። አልፎ አልፎ እሁድ እሁድ በፒተርዝበርግ ከተማ ሄደን ለመስበክ እስከ 90 ኪሎ ሜትር እንጓዝ ነበር።
የተሳካ የንግድ ሥራ
ቀስ በቀስ አባቴ አንድ አነስተኛ የችርቻሮ ዕቃ መደብር ከፈተ። ወዲያው ሱቁ በእጥፍ ስላደገ ሌላ ሱቅ ተከፈተ። አንዳንድ ሀብታም ገበሬዎች የአባቴ የንግድ ሸሪኮች ሆኑ፤ ከጊዜ በኋላም አንድ የጅምላ ንግድ መደብርና ሌሎች ስድስት የችርቻሮ ንግድ መደብሮች በተለያዩ ቦታዎች በአንድ ላይ ከፈቱ።
አንዳንድ ታላላቅ ወንድሞቼ በንግዱ ሥራ በመግባታቸው ሀብታም የመሆን ተስፋ ነበራቸው። ይሁን እንጂ መንፈሳዊነታችን መዳከም ጀመረ። በዓለማዊ ጓደኞቻችንና ጎረቤቶቻችን ዘንድ ይበልጥ ተቀባይነት እያገኘን መጣን። እነርሱም በፓርቲዎቻቸው ላይ እንድንገኝ ይጋብዙን ጀመር። አባቴ ይህ ሁኔታ ሊያስከትል የሚችለውን አደጋ በመመልከት ቤተሰባችንን አንድ ላይ ሰብስቦ አወያየንና በይሖዋ አገልግሎት ይበልጥ ለመሥራት እንችል ዘንድ ሱቆቹን ሸጦ ወደ ፕሪቶርያ እንድንሄድ ወሰነ። በተቀጠሩ ሠራተኞች የሚካሄድ አንድ ሱቅ ብቻ አስቀረ።
ወንድሞቼ ክዊስና ዴቪድ አቅኚነትን ቀደም ብላ ጀምራ ከነበረችው ከታላቅ እህቴ ከሊና ጋር አቅኚዎች ሆኑ። አሥር አባላት የነበረው ጠቅላላው ቤተሰባችን በ1942 በአንድ ወር ውስጥ በድምሩ 1,000 ሰዓት በስብከቱ ሥራ ላይ አውሏል። በዚያ ዓመት ራሴን ለይሖዋ መወሰኔን በውኃ በመጠመቅ አሳየሁ።
ትምህርቴን ቶሎ ያቆምኩበት ምክንያት
በ1944 ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከፍተኛው ደረጃ ላይ ደርሶ በነበረበት ወቅት የይሖዋ ምስክሮች ተጓዥ የበላይ ተመልካች የነበረው ከርት ኔል አቅኚ ለመሆን ዕቅድ አለህ ወይ በማለት ጠየቀኝ። “አዎን፤ ከሁለት ዓመት በኋላ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ስጨርስ አቅኚ እሆናለሁ” ስል መለስኩለት።
በዚያን ጊዜ የነበሩትን የብዙዎቹን የይሖዋ ምስክሮች አመለካከት በማንጸባረቅ “አንተ ገና እክፍልህ ወንበር ላይ እያለህ አርማጌዶን እንዳይመጣብህ” ሲል አስጠነቀቀኝ። ይህ እንዲደርስብኝ ስላልፈለግሁ ትምህርቴን አቋረጥኩና ጥር 1, 1945 ወደ አቅኚነት አገልግሎት ገባሁ።
አቅኚ ከነበሩት ጓደኞቼ ከፔት ቬንትስልና ከዳኒ ኦቶ ጋር የተመደብኩበት የመጀመሪያው ምድቤ በጆሐንስበርግ አቅራቢያ ያለው ቨሪኒንግ ነበር። ብዙውን ጊዜ በወር ከ200 የሚበልጥ ሰዓት በስብከቱ ሥራ ላይ አውል ነበር። ከጊዜ በኋላ ፔት እንደገና ወደ ፕሪቶርያ ሲመደብ ዳኒ ደግሞ በእርሻ ሥራ ላይ የነበሩትን ሽማግሌ አባቱን ለመርዳት ሲል አቅኚነቱን ማቋረጥ ነበረበት። ይህ ሁኔታ በቨሪኒንግ የነበሩትን 23 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች የምረዳ ብቸኛው ምስክር አደረገኝ።
ከዚያ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ፕሪቶርያ ውስጥ መመደቤን የሚገልጽ ከቅርንጫፍ ቢሮ የተላከ ደብዳቤ ደረሰኝ። ምንም እንኳን አዲስ ምድብ ሊሰጠኝ የቻለበትን ምክንያት በጊዜው ባልረዳውም በኋላ ግን እምብዛም የሕይወት ተሞክሮ የሌለውን የ17 ዓመት ልጅ ብቻውን መተው ጥበብ ላይሆን ይችል እንደነበር ተገነዘብኩ። ገና ብዙ ሥልጠና ስለሚቀረኝ በዚያው ብቀጥል ኖሮ ምናልባት ተስፋ ልቆርጥ እችል ነበር።
ፕሪቶርያ ውስጥ እያገለገልኩ የሚያስፈልገኝን ተሞክሮ ካገኘሁ በኋላ ልዩ አቅኚ እንድሆን ተጋበዝኩ። ከዚያም ፔት ቬንትስልና እኔ አቅኚዎች ሆነው ወደ ፕሪቶርያ ለመጡት ወጣቶች ተግባራዊ የአገልጋዮች ሥልጠና ለመስጠት ዝግጅት አደረግን። በዚያ ጊዜ ፔት በአካባቢው ተጓዥ የበላይ ተመልካች እንዲሆን ተመድቦ ነበር። በኋላም እህቴን ሊናን አገባ። አሁን በደቡብ አፍሪካ ቅርንጫፍ ቢሮ አብረው እያገለገሉ ናቸው።
አቅኚዎች ሆነው ለማገልገል ወደ ፕሪቶርያ ከመጡት መካከል ምስክር በሆነ ቤተሰብ ውስጥ ያደገች ማርቲ ፎስ የተባለች ማራኪ ወጣት ትገኝበታለች። ሁለታችንም ብንዋደድም በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ እንገኝ ስለነበር ትዳር ለመያዝ ገና አልደረስንም። ይሁን እንጂ ወደ ሌሎች ቦታዎች በተመደብን ጊዜ በደብዳቤ መገናኘታችንን ቀጠልን።
የቤቴል አገልግሎትና የጊልያድ ትምህርት ቤት
በ1948 በኬፕ ታውን በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ ቅርንጫፍ ቢሮ እንዳገለግል ተጋበዝኩ። በዚያ ጊዜ ተከራይተናቸው በነበሩት ሦስት ቢሮዎችና በአቅራቢያው በሚገኘው አነስተኛ ፋብሪካ ውስጥ እንሠራ ለነበርነው 17 ሰዎች የሚሆን በአንድ ላይ የምንኖርበት ቤት አልነበረንም። አንዳንዶቻችን ከቤተሰቦቻችን ጋር ስንኖር ሌሎች ደግሞ በአልቤርጎዎች ውስጥ ይኖሩ ነበር።
በያንዳንዱ የሥራ ቀን የቤቴል ቤተሰብ አባላት የሆንነው 17 ሰዎች የጠዋት አምልኮአችንን ለማካሄድ በትንሹ ፋብሪካ ልብስ መለወጫ ክፍል ውስጥ እንሰበሰብ ነበር። ብዙዎቻችን የየራሳችንን ምሳ ማዘጋጀት ነበረብን። ከዚያም ቀኑን ሙሉ ስንሠራ ከዋልን በኋላ በተለያዩ የኬፕ ታውን ክልሎች ወደሚገኙት መኖሪያዎቻችን እንጓዛለን። ቀደም ሲል እንደገለጽኩት ወንድሜ ዴቪድና እኔ “ለነጮች ብቻ” የሚል ጽሑፍ ተመለክተን የተገረምነው ወደየቤታችን ከምንጓዝባቸው እንዲህ ካሉት ጉዞዎች በአንዱ ላይ ነበር።
በኬፕ ታውን ውስጥ ወደነበረው ቅርንጫፍ ቢሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ስደርስ ገና ብዙ መማር እንዳለብኝ ተገነዘብኩ። ስለዚህ የቅርንጫፍ ቢሮ የበላይ ተመልካቻችን የነበረውን ወንድም ፊሊፕስን “ሌሎቹ የደረሱበት ደረጃ ላይ ለመድረስ ምን ላድርግ?” ብዬ ጠየቅሁት።
“ፍራንስ” አለኝና “ሌሎች ላይ ካልደረስኩ ብለህ አትጨነቅ፤ ብቻ ወደፊት ግፋ!” ሲል መለሰልኝ። ሁልጊዜ ወንድም ያለኝን ለመፈጸም እጥር ነበር። አንድ ሰው ከይሖዋ ድርጅት የሚመጣውን መንፈሳዊ ምግብ በመመገብና መመሪያን በመከተል ረገድ እኩል የሚራመድ ከሆነ ከድርጅቱ ጋር አብሮ ሊያድግ እንደሚችል ተምሬአለሁ።
በ1950 ሚስዮናዊ ለመሆን እችል ዘንድ ሥልጠና እንዳገኝ በመጠበቂያ ግንብ የጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት ውስጥ 16ኛውን ክፍል እንድካፈል ተጋበዝኩ። በዚያን ጊዜ ትምህርት ቤቱ ከብሩክሊን ኒው ዮርክ 400 ኪሎ ሜትር ርቆ በሚገኘው በሳውዝ ላንሲንግ ኒው ዮርክ ውስጥ ነበር። በብሩክሊን በሚገኘው የጠቅላላውን ዓለም ሥራ በሚያካሂደው የይሖዋ ምስክሮች ዋና መሥሪያ ቤት በጊዜያዊነት በምሠራበት ጊዜ የይሖዋን የሚታይ ድርጅት ማዕከል ተመልክቼዋለሁ። የመሪነቱን ቦታ የያዙት በዚያ የሚገኙ ወንድሞች በሙሉ ነፍሳቸው ለሥራው ፍቅር ያደረባቸው መሆኑን መመልከቴ የይሖዋን ድርጅት በጥልቅ እንዳደንቅ አድርጎኛል።
ቀጣዩ አገልግሎቴ
ወደ ደቡብ አፍሪካ ከተመለስኩ በኋላ ባደግሁባት በሰሜናዊ ትራንስቫል ከተማ ተጓዥ የበላይ ተመልካች ሆኜ እንዳገለግል ተሾምኩ። ለስድስት ዓመታት ደብዳቤ ስንጻጻፍ ከቆየን በኋላ ማርቲና እኔ ታኅሣስ 1952 ተጋባንና በተጓዥነት ሥራ አብራኝ መሥራት ጀመረች። ክርስቲያን ወንድሞቻችን ለጉብኝታችን የነበራቸው አድናቆት ልብን በደስታ የሚያሞቅ ነበር።
ለምሳሌ ያህል አንድ ጊዜ በአንድ የገበሬዎች መንደር ውስጥ የሚገኝ ጉባኤ ስንጎበኝ ያረፍነው ከአንድ ቤተሰብ ጋር ነበር። እነርሱም ሻይ ወይም ቡና ያለወተት ስለሚያቀርቡልን ይቅርታ ጠየቁን። ራቅ ባሉ አካባቢዎች ወደሚገኘው ክልላቸው ሄደን እዚያ ላሉት ገበሬዎች እንድንሰብክላቸው እኛን ለማጓጓዝ የሚያስፈልገውን በቂ ናፍጣ ለመግዛት የሚችሉበትን ገንዘብ ለማግኘት ሲሉ ወተት የምትሰጣቸውን አንዲት ላም እንደሸጧት አወቅን። እንዲህ ያሉትን ወንድሞቻችንን ምን ያህል እንወዳቸዋለን!
አንዳንድ ጊዜ በተለይም በዕድሜ የገፉ ሰዎች ያለባቸውን ችግሮች ለመፍታት በምሞክርበት ወቅት ለክልል የበላይ ተመልካችነት ሥራ የማልበቃ እንደሆንኩ ይሰማኝ ነበር። አንድ ጊዜ ወኔዬ እንደ ተሟጠጠ ሆኖ ተሰማኝና ብዙ ልምድ የሌለኝ በመሆኔ ተመልሰን ወደ አቅኚነት ሥራ ብንመደብ አዲስ ነገር እንዳይሆንባት ለማርቲ ነገርኳት። እርሷም በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ላይ እንሁን እንጂ በማንኛውም የአገልግሎት ዘርፍ ለማገልገል ደስተኛ እንደምትሆን አረጋገጠችልኝ።
ወደሚቀጥለው ጉባኤ ስንሄድ በወረዳ የበላይ ተመልካችነት ሥራ እንድናገለግል የተመደብን መሆናችንን የሚገልጽ ደብዳቤ ሲደርሰን ምን ያህል እንደተገረምን ልትገምቱት ትችላላችሁ! ወደ ሁለት ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ በደቡብ አፍሪካና በዚያን ጊዜ ደቡብ ምዕራብ አፍሪካ ተብላ ትጠራ በነበረችው በናሚቢያ ተዘዋውረናል። ይሁን እንጂ በአፓርታይድ ሥርዓት የተነሳ ብዙውን ጊዜ ሥራችን አስቸጋሪ ይሆንብን ነበር። ብዙ ጊዜ ወደ ጥቁሮች መንደር ለመግባት እንከለከል ነበር፤ አንዳንድ ጊዜም ትልልቅ ስብሰባዎችን ለማድረግ ፈቃድ አይሰጠንም ነበር።
ለምሳሌ ያህል በ1960 በስዌቶ ከተማ የወረዳ ስብሰባ ለማድረግ ፈቃድ አገኘን። ራቅ ባሉ ጉባኤዎች ውስጥ የሚገኙ ጥቁር ወንድሞች ወደ ስብሰባው ለመምጣት የባቡርና የአውቶቡስ ትኬቶችን ገዝተዋል፤ ሆኖም መንግሥት ስለ ዕቅዳችን ሰማና የተሰጠን ፈቃድ ተሰረዘብን። በጆሐንስበርግ ሌላኛው ክፍል 20 ኪሎ ሜትር ያህል ራቅ ብላ በምትገኝ ከተማ ውስጥ የሚኖር ተግባቢ የሆነ አንድን ባለ ሥልጣን በብልሃት አነጋገርነው። እርሱም የተሻለ ግልጋሎት የሚሰጥ ቦታ በደግነት ፈቀደልን። ግሩም የሆነ ስብሰባ አደረግንና ከ12,000 በላይ የሚሆኑ ሰዎች ተገኝተው ተደስተውበታል።
በቅርብ ዓመታት ያለው ሁኔታ ምን ያህል ተለውጧል! አሁን አፓርታይድ እየፈራረሰ ባለበት ወቅት ጥቁሮች፣ ነጮች፣ ክልሶች ወይም ሕንዶች በሚኖሩበት ቦታ እንደልባችን መሰብሰብ እንችላለን። ምንም ዓይነት ቀለም ይኑረው እያንዳንዱ ሰው አብሮ ለመቀመጥና በወንድማማችነት ለመደሰት ይችላል። አንድ ሰው የት ቦታ ላይ መቀመጥ እንዳለበት እንዲወስን የሚያደርገው የቋንቋው ጉዳይ ብቻ ነው።
ከአሳዛኝ ሁኔታ ትምህርት ማግኘት
በ1947 አባቴ አንድ ትልቅ ስህተት ሠራ። እሱና እናቴ ከሚኖሩበት ቦታ 200 ኪሎ ሜትር ርቆ የሚገኘው ሱቁ በአጭበርባሪ ሠራተኞች ምክንያት ስለከሰረ ሱቁን ራሱ ለመቆጣጠር እንዲችል ብቻውን ወደ ቦታው ሄደ። ከእናቴ ጋር ለረጅም ጊዜ ተራርቀው በመቆየታቸው ምክንያት ፈተና ላይ ወደቀ። ከዚህ የተነሳ ተወገደ።
የአባቴ መወገድ ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ቀናተኛ መሆን ብቻ በቂ እንዳልሆነ ሐዘን ባለበት መንገድ በአእምሮዬ ውስጥ እንዲቀረጽ አድርጓል። ሁሉም ሰው የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በጥብቅ መከተል ይገባዋል። (1 ቆሮንቶስ 7:5) ከብዙ ዓመታት በኋላ አባቴ ወደ ክርስቲያን ጉባኤ ተመለሰ፤ እስከሞተበት እስከ 1970 ድረስም በታማኝነት አገልግሏል። ውዷ እናቴም በ1991 እስከሞተችበት ጊዜ ድረስ ታማኝ ሆና ቆይታለች።
ተጨማሪ በረከቶች
ማርቲና እኔ የይሖዋ ምስክሮች እስካሁን ካደረጓቸው ስብሰባዎች ሁሉ ትልቁ በሆነው በ1958 በኒው ዮርክ ከተማ ያንኪ ስታዲየምና በፖሎ ግራውንድስ በተደረገው ስብሰባ ላይ ተገኝተናል። የይሖዋ አስደናቂ ድርጅት አካል በመሆናችን ደስታችን የተትረፈረፈ ነበር። እሁድ ከሰዓት በኋላ ተሰብስቦ ከነበረው ከ253,000 በላይ ከሚሆን ሕዝብ ጋር አብሮ መሆን በጭራሽ የማይረሳን ትዝታ ነው። እዚያ መገኘታችን ለእኛ ‘ከሁሉም ሕዝቦች የተውጣጡ እጅግ ብዙ ሰዎች’ አንድ ላይ በሰላም ተሰብስበው በእውናችን እንደምናይ ያህል ነበር። (ራእይ 7:9, 10) ማርቲ ጊልያድ ትምህርት ቤት ለመካፈል እዚያው ኒው ዮርክ ቆየች። እኔም ተመልሼ በደቡብ አፍሪካ የወረዳ የበላይ ተመልካችነት ሥራዬን ቀጠልኩ።
በ1959 ማርቲ ከ32ኛው የጊልያድ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ክፍል ጋር ትምህርቷን ተከታትላ ከተመለሰች በኋላ ከጆሐንስበርግ በስተ ምሥራቅ በኤላንስፎንቴይን አቅራቢያ ይገኝ በነበረው በደቡብ አፍሪካ ቅርንጫፍ ቢሮ እንድናገለግል ተጋበዝን። በነዚህ ዓመታት ሁሉ የድርጅቱን ዕድገት በተለይም በፍቅርና ነገሮችን በሌሎች ቦታ ሆኖ በመመልከት በኩል ያደረገውን ዕድገት በብዙ መንገዶች ተመልክቻለሁ። ይሖዋ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ድርጅቱን እንደሚመራና ራሳቸውን የሚያቀርቡትን ሰዎች እንደሚጠቀምባቸው ለማወቅ ችያለሁ።
በ1962 ለቅርንጫፍ ቢሮ ሥራ የሚሰጠውን የአሥር ወር የሥልጠና ኮርስ ለመካፈል ወደ ብሩክሊን ኒው ዮርክ ተመለስኩ። በ1967 የደቡብ አፍሪካ ቅርንጫፍ ቢሮ የበላይ ተመልካች ሆኜ በተሾምኩ ጊዜ ይህን ኮርስ ጠቃሚ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። በ1976 የቅርንጫፍ ቢሮ ኮሚቴዎች ተሾሙ። ስለዚህ አሁን ትልልቅ ውሳኔዎችን ማድረጉ በደቡብ አፍሪካ ተሞክሮ ያላቸው የአምስት ክርስቲያን ሽማግሌዎች ኃላፊነት ነው።
በአፓርታይድ ሥርዓት ሥር ያሳለፍነው ሕይወት
የአፓርታይድ ሕጎች የቅርንጫፍ ቢሯችንን አሠራር ነክቶተውታል። በ1952 የኤላንስፎንቴይን የቤቴል መኖሪያ ቤት ሲሠራ ሕጉ ለጥቁሮችና ለክልሶች መኖሪያ የሚሆን ተጨማሪ ሕንፃ እንዲሠራ የሚጠይቅ ነበር። እንዲሁም ሕጉ ጥቁሮች ከነጮች ተለይተው የአፍሪካውያን መኖሪያ በመባል ይጠራ በነበረ ቦታ እንዲበሉ ይጠይቅ ነበር። በኋላም በቤቴል ወጥ ቤት ውስጥ እንዲበሉ የመመገቢያ ቦታ ተዘጋጀላቸው። በ1959 ቤቴል ስንገባ የነበረው የአመጋገብ ዝግጅት ይህ ነበር። ዘርን መሠረት በማድረግ የሚፈጸመውን ይህንን ሁሉ ልዩነት ለመቀበል ተቸግሬ ነበር።
ከጊዜ በኋላ መንግሥት ጥቁሮች ወንድሞቻችን ከዋናው የቤቴል መኖሪያ በስተጀርባ በነበረው ሕንፃ ውስጥ እንዳይኖሩ ከለከለ። እነዚህ ወንድሞች 20 ኪሎ ሜትር ርቆ በሚገኘው የጥቁሮች መንደር ውስጥ መኖር ነበረባቸው። አንዳንዶቹ በኪራይ ቤት ውስጥ ሲኖሩ ሌሎች ደግሞ በወንደ ላጤዎች ሆስቴል ውስጥ ይኖሩ ነበር። ይህ ደስ የማይል ሁኔታ ለብዙ ዓመታት ቀጥሎ ነበር።
ቤቴልን ማስፋፋት
ይህ በእንዲህ እንዳለ በኤላንስፎንቴይን ይገኝ የነበረው ቤቴል መስፋፋት አስፈለገው። ሦስት ጊዜ ያህል እንዲሰፋ ከተደረገ በኋላ የነበረን ቦታ ከዚህ በላይ ለማስፋት የማያስችለን ሆነ። የአስተዳደር አካሉ ጥቁር ወንድሞቻችንም አብረውን ሊኖሩ በሚችሉበት ቦታ ላይ የቤቴል ሕንፃ እንድንሠራ መንግሥት ሊፈቅድልን ይችላል ብለን ተስፋ በምናደርግበት አካባቢ መሬት እንድንፈልግ መመሪያ ሰጠን። በየዕለቱ ጠዋት ጠዋት የቤቴል ቤተሰብ በሙሉ ይሖዋ ይህ የሚሳካበትን መንገድ እንዲከፍትልን እንጸልይ ነበር።
በመጨረሻ ከጆሐንስበርግ በስተ ምዕራብ በክሩገርስድሮፕ አካባቢ ተስማሚ የሆነ መሬት ያገኘንበት ቀን እንዴት የሚያስደስት ነበር! ይሁን እንጂ እንደገና ለጥቁር ወንድሞቻችን ሌላ ሕንጻ እንድንሠራ ተጠየቅን። በነገሩ ብንስማማም ከ20 በላይ ጥቁሮች እዚያ እንዲኖሩ ፈቃድ ለማግኘት ሳንችል ቀረን። በ1980ዎቹ አጋማሽ ላይ ሁኔታዎች እየተለወጡ መሄድ ጀመሩ። ለዚህም አመስጋኞች ነን። መንግሥት ጥብቅ የሆኑትን የአፓርታይድ ሕጎች ማላላት በመጀመሩ ጥቁሮች፣ ክልሶችና ሕንዶች የሆኑ ተጨማሪ ወንድሞቻችን ከእኛ ጋር በቤቴል ለማገልገል ተጠሩ።
አሁን ምንም ዓይነት ቀለም ቢኖራቸው በመረጡት ሕንፃ ላይ ለመኖር የሚችሉ ግለሰቦች ያሉበት የተባበረ የቤቴል ቤተሰብ ስላለን ደስተኞች ነን። በተጨማሪም ለብዙ ዓመታት ከታገልን በኋላ በመጨረሻ እንደ አንድ ሃይማኖት ተደርገን ሕጋዊ እውቅና ለማግኘት ችለናል። በአገሪቱ ውስጥ “በደቡብ አፍሪካ የይሖዋ ምስክሮች” የሚባል በሕግ የተመዘገበ ማኅበር ተቋቁሟል። አሁን ጋብቻን ለማስፈጸም ሕጋዊ ሥልጣን ያላቸው ወንድሞች አሉን፤ እንዲሁም በጥቁሮች መኖሪያዎች ውስጥ የመንግሥት አዳራሾች እንደ አሸን በመፍላት ላይ ናቸው።
በኬፕ ታውን ቅርንጫፍ ቢሮ እሠራ ከነበረበት ጊዜ አንስቶ የይሖዋ ድርጅት ምን ያህል አድጓል! የቤቴል መኖሪያ የሌላቸው 17 አባላት ካሉት ትንሽ ቤተሰብ ተነስተን አሁን የተራቀቁ ኮምፒዩተሮች፣ የሮታሪ ማተሚያዎችና ቆንጆ መኖሪያ ያለበት ዘመናዊ የቤቴል ሕንፃ ያለው ከ400 በላይ የሚሆኑ አባላት ያሉት የቤቴል ቤተሰብ ወደ መሆን አድገናል! አዎን፤ በደቡብ አፍሪካ ውስጥ ከሚገኘው የይሖዋ ድርጅት ጋር የማደግ መብት አግኝቻለሁ። ከ50 ዓመታት በፊት አገልግሎቴን ስጀምር ከነበርነው ከ400 የመንግሥቱ አስፋፊዎች ተነስተን አሁን ወደ 55,000 የምንጠጋ ሆነናል!
ላለፉት 40 ዓመታት ከጎኔ ሆና የምትደግፈኝ ሚስት በማግኘቴ ይሖዋን አመሰግነዋለሁ። “ጽዋዬም የተረፈ ነው።” (መዝሙር 23:5) ማርቲና እኔ በመንፈስ የሚመራው የይሖዋ ድርጅት አካል በመሆናችን አመስጋኞች ነን። የይሖዋ ቤት በሆነው በቤቴል ውስጥ እርሱን በማገልገል ለመቀጠል እንዲሁም ወደፊት እየገፋ ካለው ድርጅቱ ጋር እኩል ለመራመድ ቁርጥ ውሳኔ አድርገናል።
[ምንጭ]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
ዛየር
አንጎላ
ዛምቢያ
ናሚቢያ
ቦትስዋና
ዚምባዌ
ስዊዚላንድ
ሌሶቶ
ደቡብ አፍሪካ
ፕሪቶርያ
ጆሐንስበርግ
ኬፕ ታውን
ፖርት ኤልዛቤት
ደቡባዊ አትላንቲክ ውቅያኖስ
ሕንድ ውቅያኖስ
የሞዛምቢክ የባሕር ወሽመጥ
[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ፔት ቬንትስልና ፍራንስ ሙለር (በስተግራ ) በ1945 በአቅኚነት ሥራ ላይ እያሉ
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ፍራንስና ማርቲ ሙለር