‘ሽማግሌዎችን ጥራ’
“ከእናንተ የታመመ ማንም ቢኖር የቤተ ክርስቲያንን ሽማግሌዎች ወደ እርሱ ይጥራ።” — ያዕቆብ 5:14
1, 2. (ሀ) በአሁኑ ጊዜ የይሖዋ አገልጋዮች በምን አደገኛ ሁኔታዎች ውስጥ ይገኛሉ? ምን ሊሰማቸውስ ይችላል? (ለ) አሁን መልስ የሚያስፈልጋቸው ምን ጥያቄዎች ናቸው?
ይመጣል የተባለው ‘አስጨናቂ ዘመን’ መጥቷል። በእነዚህ የመጨረሻ ቀኖች ሰዎች ራስ ወዳዶች፣ ቁሳዊ ሐብት አሳዳጆች፣ ትዕቢተኞች፣ ብዙውን ጊዜ ዓመፅን የሚቀሰቅሱ እየሆኑ ናቸው። (2 ጢሞቴዎስ 3:1–5) በአሁኑ ክፉ የነገሮች ሥርዓት ውስጥ የምንኖር ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን የሚከተሉት ሦስት ትልልቅ ነገሮች ሕይወታችንን አደጋ ላይ ጥለውታል:- ሰይጣን ዲያብሎስ፣ ለአምላክ ደንታ የሌለው የሰው ዘር ዓለምና የወረስነው ኃጢአተኛ ዝንባሌ ናቸው። — ሮሜ 5:12፤ 1 ጴጥሮስ 5:8፤ 1 ዮሐንስ 5:19
2 አንዳንድ ጊዜ በእነዚህ አደጋዎች ምክንያት ሕይወታችን አስጊ ሁኔታ ላይ ይወድቅና በጭንቀት ልንዋጥ እንችላለን። ታዲያ በታማኝነት እንድንጸና የሚረዳንን ድጋፍ ከየት ለማግኘት እንችላለን? ክርስቲያናዊ እንቅስቃሴዎቻችንንና አምልኮታችንን በተመለከተ ውሳኔ ማድረግ ሲያስፈልገን መመሪያ ለማግኘት ወደ ማን ዞር ማለት እንችላለን?
በቅርብ የሚገኝ እርዳታ
3. መጽናናትና የመንፈስ እርጋታ ልናገኝ የምንችለው ከማን ነው? እንዴትስ?
3 የኃይላችን ምንጭ ይሖዋ እንደሆነ ማወቃችን የሚያጽናና የመንፈስ መረጋጋትን የሚሰጥ ነው። (2 ቆሮንቶስ 1:3, 4፤ ፊልጵስዩስ 4:13) መለኮታዊ እርዳታ ማግኘት ምን ማለት እንደሆነ ያየው መዝሙራዊው ዳዊት እንዲህ ሲል ተናግሯል:- “መንገድህን ለእግዚአብሔር [ለይሖዋ አዓት] አደራ ስጥ፣ በእርሱም ታመን፣ እርሱም ያደርግልሃል።” “ትካዜህን [ሸክምህን አዓት] በእግዚአብሔር [በይሖዋ አዓት] ላይ ጣል፣ እርሱም ይደግፍሃል፤ ለጻድቁም ለዘላለም ሁከትን አይሰጠውም።” (መዝሙር 37:5፤ 55:22) እንዲህ ላለው እርዳታ ምንኛ አመስጋኞች ልንሆን ይገባናል!
4. ጴጥሮስም ሆነ ጳውሎስ ማጽናኛ የሰጡት እንዴት ነው?
4 በተጨማሪም ፈተናና ችግር የሚደርሰው በእኛ ላይ ብቻ አለመሆኑን ማወቃችን ሊያጽናናን ይችላል። ሐዋርያው ጴጥሮስ እንደሚከተለው በማለት ክርስቲያን ወንድሞቹን አጥብቆ አሳስቧል:- “በዓለም ያሉት ወንድሞቻችሁ ያን መከራ በሙሉ እንዲቀበሉ እያወቃችሁ በእምነት ጸንታችሁ [ሰይጣን ዲያብሎስን] ተቃወሙት።” (1 ጴጥሮስ 5:9) ሁሉም ክርስቲያኖች በእምነት ጸንተው ለመቆም እንደሚፈልጉ የተረጋገጠ ነው። እውነት ነው፣ እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ ሁሉ እኛም ብዙ ጊዜ ‘ከየአቅጣጫው ተጽዕኖ’ ሊደርስብን ይችላል። ቢሆንም ጳውሎስ ከአቅሙ በላይ ‘የሚያስጨንቅ’ ፈተና አልደረሰበትም። ልክ እንደ እሱ እኛም ግራ ልንጋባ እንችል ይሆናል። ነገር ግን ፈጽሞ መውጫውን እስከምናጣ ድረስ አንሆንም። ብንሰደድ እንኳን ‘የተተውን’ አንሆንም፤ ሰዎች መከራ ቢያደርሱብንም “አንጠፋም።” ስለዚህ ‘ተስፋ ቆርጠን እጅ አንሰጥም።’ ‘ዓይናችንን በሚታየው ሳይሆን በማይታየው ነገር ላይ ለማድረግ’ እንጥራለን። (2 ቆሮንቶስ 4:8, 9, 16, 18) ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?
5. ይሖዋ ምን ሦስት እርዳታዎችን አዘጋጅቶልናል?
5 ‘ጸሎት ሰሚ’ የሆነው ይሖዋ በሦስት አቅጣጫ እርዳታ አዘጋጅቶልናል። (መዝሙር 65:2፤ 1 ዮሐንስ 5:14) አንደኛ፣ በመንፈስ አነሳሽነት በተጻፈው ቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት መመሪያ ይሰጠናል። (መዝሙር 119:105፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:16) ሁለተኛ፣ የእሱን ፈቃድ እንድናደርግ ቅዱስ መንፈሱ ኃይል ይሰጠናል። (ከሥራ 4:29–31 ጋር አወዳድር።) እንዲሁም ሦስተኛ፣ የይሖዋ ምድራዊ ድርጅት እኛን ለመርዳት ዝግጁ ነው። እርዳታውን ለማግኘት ምን ማድረግ አለብን?
‘ስጦታ የሆኑ ወንዶች’
6. በተቤራ ይሖዋ ያደረገው እርዳታ ምን ነበር? እንዴትስ?
6 በነቢዩ ሙሴ ዘመን የደረሰ አንድ ሁኔታ ይሖዋ ለአገልጋዮቹ ድጋፍ በመስጠት በኩል ያለውን ፍቅራዊ አሳቢነት እንድንገነዘብ ይረዳናል። ይህም ሁኔታ የተከሰተው በተቤራ ነው። ተቤራ “የሚነድድ፣ የሚንቀለቀል እሳት” ማለት ነው። በሲና ምድረ በዳ በዚህ ቦታ ላይ አምላክ በአጉረምራሚዎቹ እስራኤላውያን ላይ እሳት እንዲነድ አደረገ። ከእስራኤል ሕዝብ ጋር አብረው ከግብፅ የወጡትም ‘ድብልቅ ሕዝቦች’ አምላክ ለሕዝቡ ይሰጠው በነበረው ምግብ እንዳልረኩ በመግለጽ አብረዋቸው አጉረመ ረሙ። ሙሴ የይሖዋን ቁጣ በመመልከት እንዲሁም ለሕዝቡና የሚያስፈልጓቸውን መሠረታዊ ነገሮች ለማሟላት ያለበትን ኃላፊነት በማሰብ ስለተጨነቀ እንዲህ ብሎ ጮኸ:- “እጅግ ከብዶብኛልና ይህን ሁሉ ሕዝብ ልሸከም አልችልም። እንዲህስ ከምታደርግብኝ፣ በፊትህ ሞገስ አግኝቼ እንደ ሆነ፣ በእኔ ላይ የሚሆነውን መከራ እንዳላይ፣ እባክህ፣ ፈጽሞ ግደለኝ።” (ዘኁልቁ 11:1–15) ይሖዋስ ምን አደረገ? ይሖዋም “ከእስራኤል ሽማግሌዎች . . . ሰባ ሰዎችን” ሾመ። በአስተዳደሩ ሥራ ሙሴን በሚገባ ሊያግዙት እንዲችሉ ከመንፈሱ ሰጣቸው። (ዘኁልቁ 11:16, 17, 24, 25) ብቃት ባላቸው በእነዚህ የተሾሙ ወንዶች አማካኝነት ለእስራኤላውያንና አብሯቸው ለወጣው “ብዙ ድብልቅ ሕዝብ” በቀላሉ እርዳታ ማቅረብ ጀመረ። — ዘጸአት 12:38
7, 8. (ሀ) ይሖዋ በጥንት እስራኤል ‘ስጦታ የሆኑ ወንዶች’ ያዘጋጀው እንዴት ነበር? (ለ) ጳውሎስ መዝሙር 68:18ን ለመጀመሪያው መቶ ዘመን ሁኔታ የተጠቀመበት እንዴት ነው?
7 እስራኤላውያን ለብዙ ዓመታት በተስፋይቱ ምድር ከተቀመጡ በኋላ ይሖዋ በምሳሌያዊ ሁኔታ ወደ ጽዮን ተራራ ወጣ። ዳዊትን ወደፊት ለሚመጣው የአምላክ መንግሥት አምሳያ ለሆነው መንግሥት ንጉሥ አድርጎ ሾመው። ኢየሩሳሌምን ዋና ከተማ አደረገ። ዳዊት ሁሉን ቻይ የሆነውን አምላክ ለማወደስ እንዲህ ሲል ዘምሯል:- “ወደ ላይ ዓረግህ፣ ምርኮኞችንም ወሰድህ፣ ሰዎችንም እንደ ስጦታ አድርገህ ተቀብለሃል።” (መዝሙር 68:14, 18 አዓት) በእርግጥም ተስፋይቱ ምድር ድል በተደረገችበት ጊዜ ተማርከው የተወሰዱ ወንዶች ሌዋውያንን በሥራ ረድተዋቸዋል። — ዕዝራ 8:20
8 በመጀመሪያ መቶ ዘመን እዘአ ክርስቲያኑ ሐዋርያ ጳውሎስ የመዝሙራዊው ቃላት ትንቢታዊ ፍጻሜ እንዳላቸው አመልክቷል። ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጻፈ:- “ነገር ግን እንደ ክርስቶስ ስጦታ መጠን ለእያንዳንዳችን ይገባናል የማንለው ደግነት ተሰጠን። ስለዚህ:- ‘ወደ ላይ በወጣ ጊዜ ምርኮን ማረከ፤ ወንዶችንም ስጦታ አድርጎ ሰጠ’ ይላል። ወደ ምድር ታችኛ ክፍል ደግሞ ወረደ ማለት ካልሆነ፣ ይህ ወጣ ማለትስ ምን ማለት ነው? ይህ የወረደው ሁሉን ይሞላ ዘንድ ከሰማያት ሁሉ በላይ የወጣው ደግሞ ያው ነው።” (ኤፌሶን 4:7–10 አዓት) “ይህ የወረደው” የተባለው ማን ነው? የይሖዋ ወኪል ከሆነውና ከመሲሐዊው ንጉሥ ከታላቁ ዳዊት ከኢየሱስ ክርስቶስ ሌላ ማንም ሊሆን አይችልም። አምላክ ከሞት ያስነሳውና ‘ከፍ ከፍ በማድረግ’ የላቀ ቦታ የሠጠው እሱ ነው። — ፊልጵስዩስ 2:5–11
9. (ሀ) በመጀመሪያው መቶ ዘመን ስጦታ የሆኑ ወንዶች እነማን ነበሩ? (ለ) በዘመናችን ስጦታ የሆኑ ወንዶች እነማን ናቸው?
9 ታዲያ እነዚህ ‘ስጦታ የሆኑ ወንዶች’ እነማን ናቸው? የአምላክ ዋና ወኪል የሆነው የሰጠውን ስጦታ ሲያብራራ ጳውሎስ እንዲህ አለ:- “አንዳንዶቹ ሐዋርያት፣ ሌሎቹም ነቢያት፣ ሌሎቹም ወንጌልን ሰባኪዎች፣ ሌሎቹም እረኞችና አስተማሪዎች እንዲሆኑ ሰጠ፤ . . . ቅዱሳን አገልግሎትን ለመሥራትና ለክርስቶስ አካል ሕንጻ ፍጹማን ይሆኑ ዘንድ።” (ኤፌሶን 4:11–13) እንደ ሐዋርያት፣ ነቢያት፣ ወንጌልን ሰባኪዎች፣ እረኞችና አስተማሪዎች ሆነው ያገለገሉት የክርስቶስ ተከታዮች በሙሉ ይህንን ተግባራቸውን ያከናወኑት በቲኦክራቲካዊ አመራር ሥር በመሆን ነው። (ሉቃስ 6:12–16፤ ሥራ 8:12፤ 11:27, 28፤ 15:22፤ 1 ጴጥሮስ 5:1–3) በዘመናችን በመንፈስ ቅዱስ የተሾሙ መንፈሳዊ ብቃት ያላቸው ሽማግሌዎች በዓለም ዙሪያ በሚገኙት 70,000 በሚሆኑት የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች ውስጥ የበላይ ተመልካቾች በመሆን ያገለግላሉ። ለእኛ “ስጦታ የሆኑት ወንዶች” እነርሱ ናቸው። (ሥራ 20:28) በዓለም ዙሪያ የመንግሥቱ ስብከት ሥራ በፍጥነት መስፋፋቱን ስለቀጠለ ብዙ ተጨማሪ ወንድሞች ተጣጥረው ብቃቱን በማሟላት ወደ ‘በላይ ተመልካችነት’ ቦታ እየደረሱ ሲሆን ከዚህ ጋር የተያያዙትን ኃላፊነቶችም እያከናወኑ ነው። (1 ጢሞቴዎስ 3:1) እነሱም ለዚህ ቦታ ሲሾሙ ስጦታ የሆኑ ወንዶች ከተባሉት መካከል ይሆናሉ።
10. ኢሳይያስ ስለ “መሳፍንት” የሠጠው መግለጫ ዛሬ ላሉት ክርስቲያን ሽማግሌዎች የሚስማማው እንዴት ነው?
10 ነቢዩ ኢሳይያስ “መሳፍንት” ወይም በመንግሥቱ ግዛት ውስጥ የሚነሱት አስተዳዳሪዎች ስለሚያከናውኑት ሥራ በትንቢት የሰጠው መግለጫ ለእነዚህ ክርስቲያን ሽማግሌዎች ወይም ስጦታ ለሆኑት ወንዶች ይስማማል። እያንዳንዱ ክርስቲያን ሽማግሌ “ከነፋስ እንደ መሸሸጊያ፣ ከዐውሎ ነፋስም እንደ መጠጊያ፣ በጥም ቦታም እንደ ወንዝ ፈሳሽ፣ በበረሀም አገር እንደ ትልቅ ድንጋይ ጥላ” መሆን አለበት። (ኢሳይያስ 32:1, 2) ይህም የእነዚህ የተሾሙ ወንዶች ፍቅራዊ የበላይ ጥበቃ ለአምላክ ሕዝብ ምን ያህል ድጋፍ የሚሰጥ መሆን እንዳለበት ይገልጻል። ከዚህ የበላይ ጥበቃ ሙሉ በሙሉ ለመጠቀም የምትችለው እንዴት ነው?
ራስህ ተነሳስተህ እርዳታ ጠይቅ
11. መንፈሳዊነታችን ዝቅ በሚልበት ጊዜ እርዳታ ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?
11 ውኃ ውስጥ እየሰመጠ ያለ አንድ ሰው በደመ ነፍስ ለእርዳታ መጮሁ አይቀርም። ለመጮኽም ምንም ጊዜ አያባክንም። አንድ ሰው ሕይወቱ አደጋ ላይ በሚወድቅበት ጊዜ እርዳታ እንዲጠይቅ ሌላ ሰው እንዲገፋፋው አያስፈልግም። ንጉሥ ዳዊት ደጋግሞ ከይሖዋ እርዳታ አልጠየቀምን? (መዝሙር 3:4፤ 4:1፤ 5:1–3፤ 17:1, 6፤ 34:6, 17–19፤ 39:12) እኛም መንፈሳዊነታችን ዝቅ ካለ ምናልባትም የተስፋ መቁረጥ ባሕር ቢውጠን በተመሳሳይ በጸሎት ወደ ይሖዋ ዘወር በማለት በመንፈስ ቅዱሱ አማካኝነት እንዲመራን እንለምነዋለን። (መዝሙር 55:22፤ ፊልጵስዩስ 4:6, 7) ከቅዱሳን ጽሑፎችም ማጽናኛ ለማግኘት እንጥራለን። (ሮሜ 15:4) በእኛ ሁኔታ ሊሠራ የሚችል ምክር ለማግኘት የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የሚያወጣቸውን ክርስቲያናዊ ጽሑፎች እንመረምራለን። ይህም ብዙ ጊዜ የራሳችንን ችግር እንድንፈታ ያስችለናል። ነገር ግን የደረሰብን ችግር በጣም ከበረታብን የተሾሙ የጉባኤ ሽማግሌዎችን ምክር ልንጠይቅ እንችላለን። እንዲያውም “ሽማግሌዎችን” የግድ መጥራት የሚያስፈልጉን ጊዜያት ይኖራሉ። ክርስቲያን ሽማግሌዎችን የምንጠራው ለምንድን ነው? እነርሱስ መንፈሳዊ እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ሰዎች ሊረዱ የሚችሉት እንዴት ነው?
12-14. (ሀ) አንድ ሰው በሚታመምበት ጊዜ ሊከተለው የሚገባው የጥበብ መንገድ ምንድን ነው? (ለ) በያዕቆብ 5:14 መሠረት “የታመሙ” ክርስቲያኖች ምን እንዲያደርጉ ተመክረዋል? (ሐ) ያዕቆብ 5:14 የሚናገረው ስለ ምን ዓይነት ሕመም ነው? እንደዚህ ብለህ የመለስከውስ ለምንድን ነው?
12 በምንታመምበት ጊዜ የሰውነታችን የጥገና ክፍሎች ሥራቸውን እንዲያከናውኑ እድል ለመስጠት ስንል እናርፋለን። ነገር ግን በሽታችን እየጠና የሚሄድ ከሆነ ጥሩ የሕክምና እርዳታ ለማግኘት መፈለጋችን ጥበብ ይሆናል። በመንፈሳዊ ብንደክም ተመሳሳይ ነገር ማድረግ አይኖርብንምን?
13 በዚህ ረገድ ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ የመከረንን ልብ በል። እንዲህ ይላል:- “ከእናንተ የታመመ ማንም ቢኖር የቤተ ክርስቲያንን ሽማግሌዎች ወደ እርሱ ይጥራ፤ በጌታም [በይሖዋም አዓት] ስም እርሱን ዘይት ቀብተው ይጸልዩለት።” (ያዕቆብ 5:14) እዚህ ላይ ያዕቆብ የጠቀሰው ምን ዓይነት በሽታ ነው? በዚያ ዘመን ዘይት መቀባት የተለመደ ሕክምና ስለነበረ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተንታኞች ያዕቆብ የጠቀሰው ስለ አካላዊ ሕመም ነው ብለው ደምድመዋል። (ሉቃስ 10:34) በተጨማሪም ያዕቆብ በመፈወስ ስጦታ አማካኝነት የሚደረገውን ተአምራታዊ ፈውስ በአእምሮው ይዞ ነበር ብለው ያምናሉ። ሆኖም በጥቅሱ ዙሪያ ያለው ሐሳብ ምን ያመለክታል?
14 በጥቅሱ ላይ “ደስታ” “ከመከራ” ጋር ተነጻጽሮ ተገልጿል። ይህም ያዕቆብ ስለ መንፈሳዊ ሕመም እየተናገረ እንደነበረ ያመለክታል። (ያዕቆብ 5:13) ለእርዳታ ይጠሩ የተባሉት ‘የጉባኤ ሽማግሌዎች’ እንጂ ሐኪሞች ወይም ተአምራታዊ የመፈወስ ስጦታ የነበራቸው ሰዎች አልነበሩም። ታዲያ እነሱስ መጥተው ምን እንደሚያደርጉ ነው የተገለጸው? ያዕቆብ እንዲህ አለ:- “ይጸልዩለት። የእምነትም ጸሎት ድውዩን ያድናል።” (ያዕቆብ 5:14, 15፤ ከመዝሙር 119:9–16 ጋር አወዳድር።) ያዕቆብ ስለ መንፈሳዊ ሕመም እየጠቀሰ እንዳለ ያለጥርጥር የሚያረጋግጠው ሐቅ ለመዳን የሚፈልጉ ኃጢአታቸውን እንዲናዘዙ ማበረታታቱ ነው። ያዕቆብ “እርስ በርሳችሁ በኃጢአታችሁ ተናዘዙ” ሲል ጽፏል። በመንፈሳዊ የታመመው ከባድ ኃጢአት በመሥራቱ ምክንያት ከሆነ የታመመው ሰው ከመንፈሳዊ ሕመሙ ሊያገግም የሚችለው በአምላክ ቃል ላይ ለተመሠረቱት ምክሮች አዎንታዊ ምላሽ የሰጠ እንደሆነ፣ ንስሐ የገባና ከኃጢአተኛ መንገዱ የተመለሰ እንደሆነ ብቻ ነው። — ያዕቆብ 5:16፤ ሥራ 3:19
15. በያዕቆብ 5:13, 14 ላይ የተመከርነው ምን ዓይነት እርምጃ እንድንወስድ ነው?
15 ያዕቆብ ከሰጠው ምክር ልብ የምንለው አንድ ሌላ ነገርም አለ። አንድ ክርስቲያን መከራ ሲደርስበት ‘መጸለይ’፣ ደስ ካለው ደግሞ ‘መዘመር’ ይኖርበታል። በሁለቱም ሁኔታዎች ማለት አንድ ሰው መከራ ሲደርስበትም ሆነ ሲደሰት እርምጃ መውሰድን ይጠይቅበታል። በአንድ በኩል መጸለይ፤ በሌላ በኩል ደግሞ በደስታ መዘመር ይኖርበታል። እንግዲያው ያዕቆብ “ከእናንተ የታመመ ማንም ቢኖር” ሲል ምን መጠበቅ ይኖርብናል? አዎ፣ ራሳችን ተነሳስተን ቁርጥ ያለ እርምጃ እንድንወስድ በድጋሚ ያሳስበናል። ‘የጉባኤ ሽማግሌዎችን ወደ እርሱ ይጥራ።’ — መዝሙር 50:15፤ ኤፌሶን 5:19፤ ቆላስይስ 3:16
“ሽማግሌዎች” እንዴት ይረዱናል?
16, 17. ሽማግሌዎች የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በሥራ ላይ እንድናውል የሚረዱን እንዴት ነው?
16 አንዳንድ ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ከግል ሕይወታችን ጋር እንዴት እንደምናያይዛቸው ማወቅ አዳጋች ይሆንብናል። በዚህ ጊዜ ሽማግሌዎች ከምንገምተው በላይ የእርዳታ ምንጭ ሊሆኑልን ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል በመንፈሳዊ የታመመውን ሰው ሕመምን የሚያስታግሰውን ከአምላክ ቃል የሚገኝ ትምህርት በጥሩ ችሎታ ‘እንደ ዘይት በይሖዋ ስም በመቀባት’ ይጸልዩለታል። በዚህ መንገድ ሽማግሌዎች በመንፈሳዊ እንድናገግም ብዙ አስተዋጽዖ ሊያበረክቱ ይችላሉ። (መዝሙር 141:5) ብዙ ጊዜ እኛን ለማጽናናት የሚያስፈልገው ነገር አስተሳሰባችን ትክክል መሆኑን የሚያረጋግጥ ቃል መስማት ብቻ ይሆናል። ብዙ ልምድ ካለው ክርስቲያን ሽማግሌ ጋር ጉዳዩን መወያየቱ ትክክለኛ የሆነውን ነገር ለመፈጸም ያደረግነውን ቁርጥ ውሳኔ ያጠነክርልናል። — ምሳሌ 27:17
17 ክርስቲያን ሽማግሌዎች በመንፈሳዊ የታመመውን ሰው እንዲጠይቁት በሚጠሩበት ጊዜ ‘ለተጨነቁት ነፍሳት በሚያጽናና ቃል መናገር’ አለባቸው። በተጨማሪም ‘ደካማውን ይደግፋሉ፤ ለሰውም ሁሉ ትዕግሥት’ ያሳያሉ። (1 ተሰሎንቄ 5:14) ‘ሽማግሌዎች’ እና ‘በመንፈሳዊ የደከሙት’ ተገናኝተው ልብ ለልብ መነጋገራቸውና መግባባታቸው በመንፈሳዊ የታመመው ሰው መንፈሳዊ ጤንነቱ ሙሉ በሙሉ እንዲመለስለት ያደርገዋል።
የግል ኃላፊነትና ጸሎት
18, 19. ከገላትያ 6:2, 5 ጋር በተያያዘ ሁኔታ ክርስቲያን ሽማግሌዎች ምን ሚና ይጫወታሉ?
18 ክርስቲያን ሽማግሌዎች የአምላክን መንጋ በተመለከተ ያለባቸውን ኃላፊነት መወጣት አለባቸው። ሽማግሌዎች ድጋፍ ሰጪዎች መሆን አለባቸው። ለምሳሌ ያህል ጳውሎስ እንዲህ ብሏል:- “ወንድሞች ሆይ፣ ሰው በማናቸውም በደል ስንኳ ቢገኝ፣ መንፈሳውያን የሆናችሁ እናንተ እንደዚህ ያለውን ሰው በየውሃት መንፈስ አቅኑት፤ አንተ ደግሞ እንዳትፈተን ራስህን ጠብቅ። ከእናንተ እያንዳንዱ የአንዱን ሸክም ይሸከም እንዲሁም የክርስቶስን ሕግ ፈጽሙ።” በተጨማሪም ሐዋርያው ጳውሎስ “እያንዳንዱ የገዛ ራሱን ሸክም ሊሸከም ነውና” ሲል ጽፏል። — ገላትያ 6:1, 2, 5
19 የራሳችንን ሸክም እየተሸከምን የሌላውንም ጭምር መሸከም የምንችለው እንዴት ነው? በእንግሊዝኛ “በርደን” (ጭነት) እና “ሎድ” (ሸክም) ተብለው በተተረጎሙት የግሪክኛ ቃላት መካከል ያለው የትርጉም ልዩነት መልሱን ይሰጠናል። አንድ ክርስቲያን መንፈሳዊ ችግር ውስጥ ቢገባና ይህ ችግር ለእሱ ከባድ ጭነት ቢሆንበት ሽማግሌዎችና ሌሎች መሰል አማኞች ይረዱታል። በዚህ መንገድ “ሸክሙን” (በእንግሊዝኛው “በርደን”) በመሸከም ያግዙታል። ነገር ግን ግለሰቡ ለአምላክ ያለበትን የኃላፊነት “ሸክም” (በእንግሊዝኛው “ሎድ”) ራሱ መሸከም አለበት።a ሽማግሌዎች ማበረታቻና ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር በመስጠት እንዲሁም በጸሎት የወንድሞቻቸውን “ጭነት” በደስታ ይሸከማሉ። ይሁን እንጂ ሽማግሌዎች የግላችንን መንፈሳዊ የኃላፊነት “ሸክም” ሊያወርዱልን አይችሉም። — ሮሜ 15:1
20. ጸሎት ቸል መባል የማይኖርበት ለምንድን ነው?
20 ጸሎት በጣም አስፈላጊ በመሆኑ ቸል ሊባል አይገባውም። ይሁን እንጂ በመንፈሳዊ የታመሙ ብዙ ክርስቲያኖች መጸለይ አዳጋች ይሆንባቸዋል። ሽማግሌዎች በመንፈሳዊ ለታመመ ሰው የእምነት ጸሎት የሚያቀርቡበት ዓላማ ምንድን ነው? ከወደቀበት ከባድ የተስፋ መቁረጥ ሁኔታ “ጌታም [ይሖዋም አዓት] ያስነሣዋል፤” የእውነትንና የጽድቅን መንገድ እንዲከተልም ያጠነክረዋል። በመንፈሳዊ የታመመ አንድ ክርስቲያን መጥፎ አስተሳሰብ አድሮበት ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን በጣም ከባድ ኃጢአት አልፈጸመ ይሆናል። ያዕቆብ “ኃጢአትንም ሠርቶ እንደ ሆነ ይሰረይለታል” ይላል። ሽማግሌዎች ስለእሱ አጥብቀው በመጸለይ የሚሰጡት ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር በመንፈሳዊ የደከመው ሰው የፈጸማቸው ከባድ ኃጢአቶች ካሉ እንዲናዘዝና የንስሐ መንፈስ እንዲያሳይ ሊያነሳሳው ይችላል። ይህም በአምላክ በኩል ይቅርታ ያስገኛል። — ያዕቆብ 5:15, 16
21. (ሀ) አንዳንድ ክርስቲያኖች ሽማግሌዎችን ለመጥራት ወደኋላ የሚሉት ለምንድን ነው? (ለ) በሚቀጥለው ርዕሰ ትምህርት ላይ የምንመረምረው ምንድን ነው?
21 ትጉህ ሽማግሌዎች ወደ ክርስቲያን ጉባኤ እየጎረፉ ያሉትን አዲሶች መንከባከቡ ሥራ ስለሚያበዛባቸው የበላይ ጥበቃ ማድረጉ አድካሚ ይሆንባቸዋል። በእርግጥም፣ እነዚህ ስጦታ የሆኑ ወንዶች በእነዚህ አስጨናቂ ቀናት ጸንተን እንድንቆም የሚረዱን የይሖዋ ግሩም ዝግጅቶች ናቸው። ይሁን እንጂ አንዳንድ ክርስቲያኖች እነዚህ ወንድሞች ምንም ጊዜ እንደሌላቸው ወይም ብዙ ችግሮች እንዳሉባቸው በማሰብ የእነሱን እርዳታ ከመጠየቅ ወደኋላ ይላሉ። የሚቀጥለው ርዕሰ ትምህርት እነዚህ ወንድሞች በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የበታች እረኞች ሆነው በፈቃደኝነት ስለሚያገለግሉ እኛን ለመርዳት ደስተኞች መሆናቸውን እንድንገነዘብ ይረዳናል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በፍሪትስ ረንከር የተዘጋጀው ኤ ሊንጉስቲክ ኪ ቱ ዘ ግሪክ ኒው ቴስታመንት የተባለው መጽሐፍ ፎርቲዎን ለተባለው ቃል ፍቺ ሲሰጥ “አንድ ሰው መሸከም ያለበት ሸክም” ይላል። አክሎም:- “ቃሉ የአንድን ሰው ጓዝ ወይም የአንድን ወታደር ትጥቅና ስንቅ ለመግለጽ የሚያገለግል ወታደራዊ ቃል ነው” ይላል።
እንዴት ብለህ ትመልሳለህ?
◻ እርዳታ በሚያስፈልገን ጊዜ ይሖዋ ምን ሦስት ዓይነት እርዳታዎችን አዘጋጅቶልናል?
◻ በዘመናችን ስጦታ የሆኑ ወንዶች እነማን ናቸው?
◻ ሽማግሌዎችን መጥራት የሚኖርብን መቼ ነው?
◻ ከክርስቲያን ሽማግሌዎች ምን እርዳታ እናገኛለን ብለን ልንጠብቅ እንችላለን?
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጸሎት፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትና ከሽማግሌዎች የሚገኘው እርዳታ የሚሰጡትን መንፈሳዊ ጥቅም ታገኛለህን?