ለአምልኮ ቦታህ አክብሮት ታሳያለህን?
“ወንጌል ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ክርስቲያኖች ምንጊዜም ቢሆን ቋሚና የተወሰነ የአምልኮ ቦታ ነበራቸው። ” — “ፕሪሚቲቭ ክርስቲያኒቲ፣ በዊልያም ኬቭ
የአምላክ ሕዝቦች ምንጊዜም ቢሆን ለአምልኮ በአንድነት በመሰብሰብ ይደሰታሉ። ይህ ሁኔታ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ይደረግ እንደነበረው ሁሉ ዛሬም ይደረጋል። እንደ ሉሺያን፣ ክሌመንት፣ ሰማዕቱ ጁስተን እና ተርቱሊያን ያሉ የጥንት ደራሲዎችና ቲኦሎጂያንስ ክርስቲያኖች አዘውትረው ለአምልኮ በአንድነት የሚሰበሰቡባቸው የተወሰኑ ቦታዎች እንደነበሯቸው ገልጸዋል።
መጽሐፍ ቅዱስም ክርስቲያኖች በቡድን ሆነው አዘውትረው ይሰበሰቡ እንደነበረ የሚጠቁሙ ብዙ ሐሳቦችን በመግለጽ ከዚሁ ጋር የሚመሳሰል ነጥብ ይጠቅሳል። እነዚህ ቡድኖች ጉባኤዎች ተብለው ይጠሩ ነበር። ይህ አጠራር ተገቢ ነው፤ ምክንያቱም መጀመሪያ መጽሐፍ ቅዱስ በተጻፈባቸው ቋንቋዎች “ጉባኤ” የሚለው ቃል ለአንድ የተወሰነ ዓላማ ወይም ሥራ የተሰባሰቡ የሰዎችን ቡድን ለማመልከት የቆመ ነው።
ቀደም ሲል የነበሩት የክርስትና አምልኮ ቦታዎች
የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ሲሰበሰቡ ምን ያደርጉ ነበር? መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ዓይነት ብዙ ስብሰባዎች መደረጋቸውን ሲገልጽ የስብሰባዎቹ ዋና ገጽታም ትምህርት መስጠት እንደነበረ ያሳያል። (ሥራ 2:42፤ 11:26፤ 1 ቆሮንቶስ 14:19, 26) የትምህርት ፕሮግራሞቹ ንግግር ማቅረብን፣ የሚያበረታቱ ተሞክሮዎችን መናገርንና በኢየሩሳሌም ከሚገኘው የአስተዳደር አካል ወይም ከአንድ ሐዋርያ የደረሳቸውን ደብዳቤ በጥንቃቄ መመርመርን ይጨምሩ ነበር።
በሥራ 15:22–35 ላይ በአንጾኪያ ለሚገኙ ክርስቲያኖች እንደዚህ ያለው ደብዳቤ ከተነበበላቸው በኋላ ይሁዳና ሲላስ “ወንድሞችን በብዙ ቃል መክረው አጸኑአቸው” የሚል ቃል እናነባለን። ሌላው ዘገባ ደግሞ ጳውሎስና በርናባስ አንጾኪያ በደረሱ ጊዜ “ቤተ ክርስቲያኑን [ጉባኤውን አዓት] ሰብስበው እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር ያደረገውን ሁሉ . . . ተናገሩ” ሲል ይገልጻል። ወደ ይሖዋ መጸለይም የክርስቲያናዊ ስብሰባዎች አንዱና ዋነኛው ገጽታ ነበር። — ሥራ 14:27
የመጀመሪያው መቶ ዘመን ጉባኤዎች ለአምልኮ ይሰበሰቡባቸው የነበሩት ቦታዎች ዛሬ እንዳሉት የሕዝበ ክርስትና ቤተ ክርስቲያኖች በተራቀቀ መንገድ የተሠሩ ሕንፃዎች አልነበሩም። በአብዛኛው የጥንት ክርስቲያኖች በግል ቤቶች ውስጥ ይሰበሰቡ ነበር። (ሮሜ 16:5፤ 1 ቆሮንቶስ 16:19፤ ቆላስይስ 4:15፤ ፊልሞና 2) ብዙ ጊዜ በሰገነት ላይ ወይም በደርብ ላይ ይሰበሰቡ ነበር። የጌታ ራት የተከበረው በደርብ ላይ ነበር። እንዲሁም በጰንጠቆስጤ ዕለት 120 የሚያክሉት ደቀ መዛሙርት በመንፈስ ቅዱስ የተቀቡት በሰገነት ላይ ተሰብስበው እያሉ ነበር። — ሉቃስ 22:11, 12, 19, 20፤ ሥራ 1:13, 14፤ 2:1–4፤ 20:7, 9
ዛሬ የይሖዋ ምስክሮች ሐዋርያት የተዉልንን ምሳሌ ይከተላሉ። የመንግሥት አዳራሾች ተብለው በሚጠሩ የመሰብሰቢያ ቦታዎች ይጠቀማሉ። በእነዚህም ቦታዎች የአምላክ መንግሥት ምሥራች ሰባኪዎች ለመሆን ይሠለጥናሉ። (ማቴዎስ 24:14) በመንግሥት አዳራሹ ውስጥ ቅዱሳን ጽሑፎችን ያጠናሉ፣ ይጸልያሉ እንዲሁም እርስ በርሳቸው ይተናነጻሉ። ይህንንም የሚያደርጉት መጽሐፍ ቅዱስ በዕብራውያን 10:24, 25 ላይ እንዲህ በማለት በሰጠው ምክር መሠረት ነው:- “ለፍቅርና ለመልካምም ሥራ እንድንነቃቃ እርስ በርሳችን እንተያይ፤ በአንዳንዶችም ዘንድ ልማድ እንደ ሆነው፣ መሰብሰባችንን አንተው እርስ በርሳችን እንመካከር እንጂ፤ ይልቁንም ቀኑ ሲቀርብ እያያችሁ አብልጣችሁ ይህን አድርጉ።”
በአምልኮ ቦታችን በአግባቡ መጠቀም
“እግዚአብሔርስ የሰላም አምላክ ነው እንጂ የሁከት አምላክ አይደለም።” እንዲሁም “ሁሉ በአገባብና በሥርዓት ይሁን” በማለት ሐዋርያው ጳውሎስ የተናገራቸውን ቃላት ታስታውሳለህን? በጥቅሱ ዙሪያ ያሉትን ሐሳቦች ብትመረምር ጳውሎስ የክርስቲያን ስብሰባዎች እንዴት መመራት እንደሚገባቸው እየተናገረ እንደ ነበር ትገነዘባለህ። ዛሬም ያሉት ክርስቲያኖች በሐዋርያት ዘመን ይደረግ እንደነበረው ስብሰባዎቻቸው በሥርዓትና በሚገባ ተደራጅተው መካሄዳቸውን ይከታተላሉ። — 1 ቆሮንቶስ 14:26–40
የጥቅምት 15, 1969 መጠበቂያ ግንብ እትም እንዲህ ብሎ ነበር:- “በመንግሥት አዳራሹ የሚገኘው ለእውነተኛ አምልኮና ለመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ካለን እውነተኛ ፍቅር የሚመነጨው መንፈሳዊ አየር ጤናማ ነው። በአዳራሹ የሚታየው ቀለል ያለ ሁኔታ በዚያ የሚገኙትን ሁሉ በወዳጅነት ስሜት ተነሳስተው እንዲጨዋወቱ ያደርጋቸዋል እንጂ መደረግ ያለበት አንድ ዓይነት ምስጢራዊ ሥርዓት ብቻ መስሎ እንዲታያቸው አያደርግም።” እርግጥ ነው በመንግሥት አዳራሹ ስንጠቀም የተከበረ ቦታ መሆኑን የሚያንጸባርቁ ነገሮችን ለማሳየት አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ አለብን።
በዚህ ረገድ ሕዝበ ክርስትና አክብሮት እንደጎደላት አሳይታለች። አንዳንድ ሃይማኖታዊ ድርጅቶች የአምልኮ ቦታዎቻቸውን የሕዝብ መዝናኛ ማዕከሎች አድርገዋቸዋል። ሃይማኖታዊ የሮክ ሙዚቃ ዝግጅት፣ የከባድ ሚዛን ማንሻ ስፖርት ክፍሎች፣ የከረምቦላ መጫወቻ፣ መዋዕለ ሕፃናትና የቤት ውስጥ ሲኒማ አላቸው። አንድ ቤተ ክርስቲያን በፕሮግራሙ ውስጥ የነፃ ትግል ውድድር አዘጋጅቷል። ይህ ሁሉ ሐዋርያት ከተዉልን ምሳሌ ጋር በፍጹም አይስማማም።
በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበረ አንድ ጉባኤ አላግባብ ቢመላለስ እርማት ይሰጠው ነበር። ለምሳሌ በቆሮንቶስ በነበረው የክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ይገኙ የነበሩ አንዳንድ ሰዎች የጌታ ራትን በዓል ለመብላትና ለመጠጣት የሚያስችል ጥሩ አጋጣሚ አድርገው ቆጥረውት ነበር። ከስብሰባው በፊት ወይም ስብሰባው በሚካሄድበት ወቅት ለመብላት ሲሉ ራታቸውን ይዘው ይመጡ ነበር፤ እንዲያውም አንዳንዶቹ ከልክ በላይ ይበሉና ይጠጡ ነበር። በእውነትም ይህ የማይገባ ድርጊት ነበር። ሐዋርያው ጳውሎስ “የምትበሉባቸውና የምትጠጡባቸው ቤቶች የላችሁምን?” በማለት ጻፈላቸው። — 1 ቆሮንቶስ 11:20–29
ከጳውሎስ ምክር ጋር በመስማማት የይሖዋ ምስክሮች የግል ጉዳዮቻቸውን በቤታቸው ወይም ከመንግሥት አዳራሹ ውጭ ሌላ ቦታ ለማድረግ ጥረት ያደርጋሉ። እርግጥ ነው አዘውትረን መሰብሰባችን ከብዙ ወዳጆቻችን ጋር በአንድ ጊዜ ለመገናኘት አመቺ ሁኔታ ይፈጥርልናል። ይሁን እንጂ የመንግሥት አዳራሹ የተወሰነው ለይሖዋ ስለሆነ ለእሱ አምልኮ ብቻ ልንጠቀምበት ይገባል። ስብሰባችንን የግል ሥራ መሥሪያ ወይም መገበያያ ልናደርገው አይገባንም።
ከዚህም በላይ ጉባኤዎች የመንግሥት አዳራሾቹን የመዝናኛ ፕሮግራሞችና የገንዘብ ትርፍ የሚያስገኙ እንቅስቃሴዎች ሊያካሂዱባቸው ወይም የሕፃናት መዋያ የመሳሰሉ ማኅበራዊ አገልግሎቶችን ሊያከናውኑባቸው አይገባም። አንድ ሰው እንደነዚህ የመሳሰሉትን የግል ጉዳዮቹንም ሆነ ንግዱን የሚያከናውንባቸው ሌሎች ቦታዎች አሉ።
በአንድ የመንግሥት አዳራሽ ውስጥ ሽማግሌዎች የጉባኤው አባላት ዕቃ የመዋዋስ ልማድ እያዳበሩ መሄዳቸውን ተመልክተዋል። እንዲሁም የቪዲዮ ካሴት ፊልሞችን በመንግሥት አዳራሹ ውስጥ የመለዋወጥ ልማድ እንዳለ ተመልክተዋል። ምንም እንኳ ይህ አድራጐት ንግድ ነክ ባይሆንም ሽማግሌዎቹ እንደነዚህ ያሉትን ጉዳዮች በተቻለ መጠን እቤታቸው ማድረጉ ጥበብ እንደሆነ በማሳየት ረድተዋቸዋል።
ተመልካችን ቅር የሚያሰኙ ነገሮችን ለማስወገድና በመንግሥት አዳራሹ በተገቢው መንገድ እየተጠቀምን መሆኑን ለማወቅ እያንዳንዳችን ራሳችንን እንዲህ እያልን መጠየቅ ይኖርብናል:- ‘በቤቴ ላደርገው የሚገባኝን የግል ጉዳይ በመንግሥት አዳራሹ ውስጥ አደርጋለሁን?’ ለምሳሌ ሽርሽር ለመሄድ ወይም አንድ ላይ ለመጫወት ካሰብን ስለዝግጅቱ በቤታችን ብንወያይ አይሻልምን? የምንፈልጋቸውን ሰዎች በስልክ ልናነጋግራቸው ወይም ቤታቸው ድረስ ልንሄድ አንችልምን? የጳውሎስን አባባል በመዋስ እንዲህ ልንል እንችላለን:- ‘እንደነዚህ ያሉትን ጉዳዮች የምናከናውንባቸው ቤቶች የሉንምን?’
ይሖዋን ለማምለክ የተወሰነ ጊዜና ቦታ
መጽሐፍ ቅዱስ በመክብብ 3:1 ላይ “ለሁሉ ዘመን አለው፣ ከሰማይ በታችም ለሆነ ነገር ሁሉ ጊዜ አለው” ይላል። በመንግሥት አዳራሹ በሚደረጉት ስብሰባዎች ላይ ስንገኝ ከክርስቲያን አገልግሎት ጋር በተያያዙ ተግባሮች ሙሉ በሙሉ ራሳችንን ማስጠመድ እንችላለን። ይህ ጊዜ ይሖዋን ለማምለክ የተወሰነ ጊዜ ነው።
የኢየሱስ ግማሽ ወንድም የነበረው ያዕቆብ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ አድልዎ እንዳናሳይ መክሮናል። (ያዕቆብ 2:1–9) ይህንን ምክር በመንግሥት አዳራሾቻችን ውስጥ እንዴት ልንሠራበት እንችላለን? የአድልዎ ሁኔታ ሊታይ የሚችለው ለአንዳንድ ማኅበራዊ ጉዳዮች የጥሪ ወረቀት በመንግሥት አዳራሹ ውስጥ በግልጽ በሚታደልበት ጊዜ ሊሆን ይችላል። በአንድ ጉባኤ እንደነዚህ ዓይነት የጥሪ ወረቀቶችን በሚጋብዟቸው ሰዎች መጽሐፍ መያዣ ቦርሳ ውስጥ ወይም በመጽሐፍ ቅዱሳቸው ውስጥ የማስቀመጥ ልማድ ነበር። ይህ አድራጐት የጥሪውን ወረቀት በፖስታ ቤት ከመላክ ወይም በየቤታቸው ከማድረስ እንደሚያድን የታወቀ ነው። ይሁን እንጂ የጥሪው ወረቀት ያልተሰጣቸው ሰዎች እንደዚህ ያለው ጥሪ ለሌሎች ግለሰቦች ሲታደል ሲያዩ ምን ይሰማቸዋል? ይህ አድልዎ እንዳለ አያሳይምን?
በመንግሥት አዳራሹ ውስጥ አንድ ሰው ለሌላው የግል መልእክት ሊያደርስ ወይም ደግሞ የታሸገ ነገር ሊሰጠው አይችልም የሚል ጥብቅ ሕግ መኖር አለበት ማለት አይደለም፤ ወይም ስለ ዕለት ተዕለት ጉዳዮቻችን ወይም ስላጋጠሙን ነገሮች በመንግሥት አዳራሹ ውስጥ ማውራት ወይም አንድን ሰው እቤታችን እንዲመጣ መጋበዙ ወይም ወደ አንድ ዓይነት መዝናኛ አብሮን እንዲሄድ መፈለጋችንን መንገሩ ስህተት ነው ማለት አይደለም። ነገር ግን እንደነዚህ ያሉ ነገሮች ግድ ሆኖብን በአጋጣሚ የሚደረጉና ሌሎችን ሳንነካ ወይም ተጠንቅቀን የምናደርጋቸው ነገሮች መሆን ይኖርባቸዋል። ወደ መንግሥት አዳራሹ የመጣንበት ዋነኛ ዓላማ በመንፈሳዊ ለመታነጽ ስለሆነ የግል ዝግጅቶቻችን ልባችንን እንዲከፍሉብን ልንፈቅድላቸው አይገባም። — ማቴዎስ 6:33፤ ፊልጵስዩስ 1:10
ምሳሌ የሚሆኑ ወንዶች
ለመንግሥት አዳራሹ አክብሮት በማሳየት ረገድ ሽማግሌዎችና ዲያቆናት ቅንዓት የተሞላበት ምሳሌ ያሳያሉ። ብዙውን ጊዜ ከመንግሥት አዳራሹ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን እንዲከታተሉና እንዲያስተባብሩ የተመደቡ አንድ ወይም ሁለት ሽማግሌዎችና ዲያቆናት ይኖራሉ። ከአንድ በላይ ጉባኤዎች የሚጠቀሙበት አዳራሽ ሲሆን የሽማግሌዎች ኮሚቴ እነዚህን ጉዳዮች ይከታተላል።
እነዚህን ጉዳዮች የሚከታተሉ የተወሰኑ ወንዶች የሚመደቡ ቢሆንም ሁሉም ዲያቆናትና ሽማግሌዎች ለአዳራሹ እንክብካቤ በማድረግ በኩል ልባዊ ትኩረት ሊሰጡ ይገባል። የመንግሥት አዳራሹ ለይሖዋ የተወሰነና ለእርሱ አምልኮ የምንጠቀምበት እንደሆነ ያምኑበታል።
እድሳት ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ሽማግሌዎች ነገ ዛሬ እያሉ ማዘግየት የለባቸውም። (2 ዜና መዋዕል 24:5, 13፤ 29:3፤ 34:8፤ ነህምያ 10:39፤ 13:11) በአንዳንድ ጉባኤዎች አስፈላጊው ጥገና ወዲያውኑ መከናወን እንዲችል የመንግሥት አዳራሹን ሁኔታ አዘውትረው ይከታተላሉ። የሚያስፈልጉት ዕቃዎች በእጅ መኖራቸውንና ሊሠራባቸው የሚችሉ መሆናቸውን ለማረጋገጥ በየጊዜው ዕቃዎቹን ቆጥረው ይመዘግባሉ። ልዩ ልዩ ዕቃዎች፣ የተለያዩ መሣሪያዎችና የጽዳት መገልገያዎች የሚቀመጡበት ቦታ ካለ አለመዝረክረካቸውንና በንጽሕና መያዛቸውን ሁሉም ሽማግሌዎችና ዲያቆናት ተግተው መከታተል ይኖርባቸዋል። የመጽሔትና የመጻሕፍት አገልጋዮችም ቢሆኑ ባዶ ካርቶኖች አዳራሹን እንዳያጣብቡት ወዲያው በማስወገድ ለአዳራሹ ንጽሕና ያላቸውን አሳቢነት ማሳየት ይኖርባቸዋል።
ሽማግሌዎችና ዲያቆናት ጥሩ ምሳሌ በመሆን ጉባኤው ለመንግሥት አዳራሹ ቅንዓት የተሞላበት እንክብካቤ እንዲያደርግ ሊረዱት ይችላሉ። (ዕብራውያን 13:7) የጉባኤው አባሎች በጠቅላላ አዳራሹን በማጽዳቱ ሥራ በመካፈልና አጠቃላይ መልኩ ያማረ እንዲሆን ልባዊ ፍላጐት በማሳየት አክብሮታቸውን መግለጽ ይችላሉ።
ኢየሱስ በማቴዎስ 18:20 ላይ እንደዚህ አለ:- “ሁለት ወይም ሦስት በስሜ በሚሰበሰቡበት በዚያ በመካከላቸው እሆናለሁና።” አዎን፣ ኢየሱስ ይሖዋን ለማምለክ ስንሰበሰብ የምናደርገውን ነገር ይከታተላል። ይህም በግል ቤቶችም ይሁን እንደ ክልልና ወረዳ ባሉ ትልልቅ ስብሰባዎች ላይ የምናደርገውን ማንኛውንም ስብሰባ ይጨምራል።
በሚልዮን ለሚቆጠሩት የይሖዋ ምስክሮች አዘውትረው ይሖዋን ከሚያመልኩበት የመንግሥት አዳራሽ የሚበልጥባቸው ሌላ ቦታ የለም። ለዚህ ቦታ ተገቢውን አክብሮት ያሳያሉ። አዳራሹን ለመንከባከብ በትጋት ይሠራሉ፤ በተቻላቸው መጠን በተገቢው መንገድ ሊጠቀሙበትም ይሞክራሉ። ይሖዋ ራሱ የሰጠውን የሚከተለውን ማስጠንቀቂያ የምትሠሩበት ሁኑ:- “ወደ እግዚአብሔር ቤት በገባህ ጊዜ እግርህን ጠብቅ።” — መክብብ 5:1