የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w93 9/1 ገጽ 15-20
  • የክርስቲያን ቤተሰብ አብሮ ይሠራል

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • የክርስቲያን ቤተሰብ አብሮ ይሠራል
  • መጠበቂያ ግንብ—1993
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • አንዳንድ ሥራዎችን አብሮ መሥራት አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
  • በቤተሰብ ጥናት አብሮ መሆን
  • በወንጌሉ ሥራ አብሮ መሆን
  • ችግሮችን አብሮ መፍታት
  • አብሮ መዝናናት
  • አብሮ መሆን የሚያስገኘው በረከት
  • ቤተሰብ ለሰው ልጅ የግድ አስፈላጊ ነው!
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1998
  • የቤተሰብ ደስታ የሚገኝበት ቁልፍ ይኖራልን?
    ለቤተሰብ ደስታ ቁልፉ ምንድን ነው?
  • የአምላክን ቃል በቤተሰብ መልክ አዘውትራችሁ አጥኑ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1999
  • ቤተሰቦችን ለመርዳት የተደረገ ዝግጅት
    የመንግሥት አገልግሎታችን—2011
ለተጨማሪ መረጃ
መጠበቂያ ግንብ—1993
w93 9/1 ገጽ 15-20

የክርስቲያን ቤተሰብ አብሮ ይሠራል

“ነገር ግን፣ ወንድሞች ሆይ፣ ሁላችሁ . . . በአንድ ልብና በአንድ አሳብም የተባበራችሁ እንድትሆኑ . . . እለምናችኋለሁ።” — 1 ቆሮንቶስ 1:​10

1. በቤተሰብ አንድነት ረገድ በብዙ ቤተሰብ ውስጥ ያለው ሁኔታ እንዴት ያለ ነው?

ቤተሰብህ አንድነት አለውን? ወይስ እያንዳንዱ በፈለገው መንገድ የሚሄድበት ነው? አንዳንድ ሥራዎችን አንድ ላይ ሆናችሁ ትሠራላችሁን? ወይስ ሁላችሁም በአንድ ጊዜ በአንድ ቦታ የምትገናኙበት ጊዜ በጣም ጥቂት ነው? “ቤተሰብ” የሚለው ቃል ራሱ አንድነት ያለውን ቤት ያመለክታል።a ይሁን እንጂ አንድነት ያላቸው ሁሉም ቤተሰቦች አይደሉም። አንድ እንግሊዛዊ መምህር “ቤተሰብ የጥሩ ኅብረተሰብ መሠረት በመሆን ፋንታ . . . የሐዘናችን ሁሉ ምንጭ ነው” እስከማለት ደርሰዋል። ይህ አባባል ለአንተም ቤተሰብ የሚሠራ ነውን? ከሆነስ የቤተሰብ ሁኔታ የግድ እንዲህ መሆን ይኖርበታልን?

2. ከጥሩ ቤተሰብ የተገኙ መሆናቸውን ያረጋገጡ የመጽሐፍ ቅዱስ ሰዎች እነማን ናቸው?

2 በሁለት ወላጆች የሚተዳደርም ይሁን በአንድ ወላጅ ብዙውን ጊዜ የአንድ ቤተሰብ አንድነት ወይም መከፋፈል ቤተሰቡ በሚያገኘው አመራር ላይ የተመካ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን አንድነት የነበራቸውና ይሖዋን አንድ ሆነው ያመልኩ የነበሩ ቤተሰቦች የይሖዋን በረከት አግኝተዋል። ይህም የዮፍታሄ ሴት ልጅ፣ ሳምሶንና ሳሙኤል ይኖሩ በነበሩበት በጥንቱ የእስራኤል ሕዝብ ታይቷል። እነዚህ ሰዎች እያንዳንዳቸው ከጥሩ ቤተሰብ የተገኙ መሆናቸውን በተለያየ መንገድ አረጋግጠዋል። (መሳፍንት 11:​30–40፤ 13:​2–25፤ 1 ሳሙኤል 1:​21–23፤ 2:​18–21) በጥንቱ የክርስትና ዘመንም በአንዳንዶቹ የጳውሎስ ሚሲዮናዊ ጉዞዎች ታማኝ ባልደረባ ሆኖ ያገለገለው ጢሞቴዎስ በአያቱ በሎይድና በእናቱ በኤውንቄ አማካኝነት የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎችን ተምሮ ያደገ ነበር። ጢሞቴዎስ ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው ደቀ መዝሙርና ሚሲዮናዊ ነበር! — ሥራ 16:​1, 2፤ 2 ጢሞቴዎስ 1:​5፤ 3:​14, 15፤ በተጨማሪም ሥራ 21:​8, 9 ተመልከት።

አንዳንድ ሥራዎችን አብሮ መሥራት አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

3, 4. (ሀ) አንድነት ባለው ቤተሰብ ውስጥ ምን ባሕርያት መታየት ይኖርባቸዋል? (ለ) ቤት ተራ መጠለያ ብቻ እንዳይሆን ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው?

3 ቤተሰቦች አብረው መሥራታቸው ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው? አንዳቸው የሌላውን ችግር እንዲረዱና እርስ በርሳቸው እንዲከባበሩ ስለሚያደርጋቸው ነው። እርስ በርስ ከመራራቅ ይልቅ በጣም ተቀራርበንና ተደጋግፈን እንድንኖር ያስችለናል። ፋምሊ ሪሌሽንስ በተባለው ጋዜጣ ላይ በቅርቡ የወጣ አንድ ጽሑፍ እንዲህ ሲል ይገልጻል:- “‘የጠንካራ ቤተሰቦችን’ የተለየ ባሕርይ የሚገልጽ በመጠኑም ቢሆን ግልጽ የሆነ መግለጫ ተገኝቷል። ከእነዚህ ባሕርያት መካከል እርስ በርስ መተሳሰብ፣ እርስ በርስ በአድናቆት መተያየት፣ ሞቅ ባለ ስሜት መቀራረብ፣ ጥሩ የሐሳብ ግንኙነት ማድረግ፣ ችግሮችን የመፍታት ችሎታና መንፈሳዊ ጥንካሬ ይገኙባቸዋል።”

4 እነዚህ ባሕሪያት በቤተሰብ ውስጥ ሲኖሩ ቤት ነዳጅ ለመሙላት ቆም እንደሚባልበት የነዳጅ ማደያ ጣቢያ አይሆንም። ተራ የሆነ መኖሪያ ብቻ አይሆንም። የቤተሰቡን አባሎች በሙሉ የሚጋብዝና የሚያስደስት ቦታ ይሆናል። የሞቀ ስሜትና ፍቅር እንዲሁም የመተዛዘን መንፈስ የሰፈነበትና አንዱ የሌላውን ችግር የሚረዳበት የማረፊያ ቦታ ይሆናል። (ምሳሌ 4:​3, 4) የቤተሰብ አንድነት የሚገኝበት ጎጆ እንጂ ግጭትና መከፋፈል ያለበት የጊንጥ ዋሻ አይሆንም። ይሁን እንጂ ይህ ዓይነቱ ቤት ሊገኝ የሚችለው እንዴት ነው?

በቤተሰብ ጥናት አብሮ መሆን

5. እውነተኛውን አምልኮ የምንማረው በምን አማካኝነት ነው?

5 ስለ እውነተኛው የይሖዋ አምልኮ የምንማረው አእምሮአችንን ወይም “የማሰብ ኃይላችንን” በመጠቀም ነው። (ሮሜ 12:​1 አዓት) በሚደረግላቸው ስሜት የሚቀሰቅስ ንግግርና በአፈ ጮሌነት በሚቀርብ የቴሌቪዥን ስብከት አማካኝነት በስሜት እንደሚገነፍሉት ሰዎች ባሕሪያችን በጊዜያዊ ስሜት መመራት የለበትም። ከዚህ ይልቅ የምንገፋፋው መጽሐፍ ቅዱስንና ‘በታማኝና ልባም ባሪያ’ አማካኝነት የሚዘጋጁትን መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የሚረዱ ጽሑፎች ዘወትር በማጥናትና በማሰላሰል በምናገኘው ዕውቀት መሆን ይኖርበታል። (ማቴዎስ 24:​45) ሊያጋጥመን ለሚችለው ማንኛውም ሁኔታና ፈተና የምንወስዳቸው ክርስቲያናዊ እርምጃዎች የክርስቶስን አስተሳሰብ ከማግኘት የሚመነጩ መሆን አለባቸው። በዚህ ረገድ የሚመራን ታላቁ አስተማሪያችን ይሖዋ ነው። — መዝሙር 25:​9፤ ኢሳይያስ 54:​13፤ 1 ቆሮንቶስ 2:​16

6. ለቤተሰብ ጥናት ምሳሌ የሚሆነን ምን በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚደረግ ጥናት አለ?

6 የቤተሰብ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለእያንዳንዱ ክርስቲያን ቤተሰብ መንፈሳዊነት በጣም አስፈላጊ የሆነ አስተዋጽዖ ያበረክታል። የቤተሰብ ጥናታችሁን የምታደርጉት መቼ መቼ ነው? ሲያመቻችሁ ብቻ የሚደረግ ወይም በየጊዜው በሚደረግ ውሳኔ የሚለዋወጥ ከሆነ የቤተሰብ ጥናታችሁ ቢደረግ እንኳን አልፎ አልፎ ብቻ እንደሚሆን የታወቀ ነው። በቤተሰብ ጥናት አብሮ መሆን ቋሚ ፕሮግራም ማውጣትን ይጠይቃል። እንዲህ ከተደረገ በመንፈሳዊው የቤተሰብ ስብሰባ ለመካፈል በየትኛው ቀንና በስንት ሰዓት መገኘት እንዳለባቸው ሁሉም ያውቃሉ። ከ12,000 በላይ አባላት ያሉት የዓለም አቀፉ የቤቴል ቤተሰብ የቤተሰቡ ጥናት ሰኞ ማታ እንደሚደረግ ያውቃል። እነዚህ ፈቃደኛ የቤቴል ሠራተኞች በፓስፊክ ደሴቶችና በኒው ዚላንድ፣ ከዚያም ደረጃ በደረጃ በአውስትራሊያ፣ በጃፓን፣ በታይዋን፣ በሆንግ ኮንግ፣ ቀጥሎም በእስያ፣ በአፍሪካና በአውሮፓ እንዲሁም በመጨረሻ በአሜሪካ ቀኑ እየመሸ ሲሄድ ሁሉም አንድ ዓይነት ጥናት እንደሚካፈሉ ሲያስቡ ልባቸው በአድናቆት ይሞላል። በብዙ ሺህ በሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮችና ቋንቋዎች የተለያዩ ቢሆኑም ይህ የቤተሰብ ጥናት በቤቴል ቤተሰቦች መካከል የአንድነትና አብሮ የመሆን ስሜት ያሳድርባቸዋል። እናንተም በቤተሰብ ጥናታችሁ አማካኝነት በአነስተኛ መጠን ቢሆንም ተመሳሳይ የሆነ መንፈስ ልትኮተኩቱ ትችላላችሁ። — 1 ጴጥሮስ 2:​17፤ 5:​9

7. ጴጥሮስ በገለጸው መሠረት የእውነትን ቃል እንዴት መመልከት ይኖርብናል?

7 ሐዋርያው ጴጥሮስ “ጌታ ቸር መሆኑን ቀምሳችሁ እንደ ሆነ፣ ለመዳን በእርሱ እንድታድጉ አሁን እንደ ተወለዱ ሕፃናት ተንኮል የሌለበትን የቃልን ወተት ተመኙ” ሲል ይመክረናል። (1 ጴጥሮስ 2:​2, 3) ጴጥሮስ በእነዚህ ቃላት አማካኝነት በጣም ውብ የሆነ መግለጫ ሰጥቶአል። የተጠቀመበት ቃል ኢፒፖተሳት የተባለው የግሪክኛ ግስ ሲሆን ሊንጉስቲክ ኪ ቱ ዘ ግሪክ ኒው ቴስታመንት እንደሚገልጸው ይህ ቃል የመጣው “መናፈቅ፣ መጓጓት፣ መመኘት” የሚል ትርጉም ካለው ቃል ነው። ጠንካራ ምኞትን ወይም ናፍቆትን ያመለክታል። አንድ ጥጃ የእናቱን ጡት እንዴት በጉጉት እንደሚፈልግ እንዲሁም አንድ ሕፃን የእናቱን ጡት ሲጠባ እንዴት እንደሚደሰት ልብ ብላችኋልን? እኛም ለእውነት ቃል ተመሳሳይ ምኞትና ናፍቆት ሊኖረን ይገባል። የግሪክ ምሁር የሆኑት ዊልያም ባርክሌይ እንዲህ ሲሉ ገልጸዋል:- “ለአንድ ቅን ክርስቲያን የአምላክን ቃል ማጥናት የሚያስደስት ነገር እንጂ አድካሚ ሥራ አይደለም። ምክንያቱም ልቡ የሚናፍቀውን ምግብ የሚያገኘው ከዚህ የአምላክ ቃል እንደሆነ ያውቃል።”

8. የቤተሰቡ ራስ የቤተሰብ ጥናት በመምራት ረገድ ምን ትልቅ የሥራ ኃላፊነት አለበት?

8 የቤተሰብ ጥናት በቤተሰቡ ራስ ላይ ትልቅ ኃላፊነት ይጭንበታል። የቤተሰቡ ጥናት ሁሉንም የሚያስደስትና ሁሉም ሊሳተፉበት የሚችሉ መሆኑን ማረጋገጥ አለበት። ልጆች ጥናቱ ለትልልቆች ብቻ እንደተዘጋጀ ሊሰማቸው አይገባም። አስፈላጊው ነገር በጥናቱ የሚሸፈነው ትምህርት ብዛት ሳይሆን የጥናቱ ጥራት ነው። በጥናቱ ላይ መጽሐፍ ቅዱስ ሕያው ሆኖ እንዲታያቸው አድርግ። አስፈላጊ በሚሆንበት ቦታ ላይ የምትወያዩባቸው ሁኔታዎች የተፈጸሙባቸውን የፓለስቲና ምድር አካባቢዎችና ገጽታዎች ልጆችህ በዓይነ ኅሊናቸው እንዲመለከቱ እርዳቸው። ሁሉም በየግላቸው ምርምር አድርገው እንዲመጡና የምርምራቸውን ውጤት ለቤተሰቡ እንዲያካፍሉ መበረታታት ይኖርባቸዋል። በዚህ መንገድ ልጆችም ‘በይሖዋ ፊት ሊያድጉ’ ይችላሉ። — 1 ሳሙኤል 2:​20, 21

በወንጌሉ ሥራ አብሮ መሆን

9. የስብከቱን ሥራ ለመላው ቤተሰብ የሚያስደስት አጋጣሚ ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው?

9 ኢየሱስ “አስቀድሞም ወንጌል ለአሕዛብ ሁሉ ይሰበክ ዘንድ ይገባል” ብሏል። (ማርቆስ 13:​10) እነዚህ ቃላት እያንዳንዱ ትጉህ ክርስቲያን የሥራ ምድብ እንዳለው ይገልፃሉ። ይህም ሥራ ወንጌልን የመስበክና ስለ እግዚአብሔር መንግሥት አገዛዝ የሚገልጸውን ምሥራች ለሌሎች ማካፈል ነው። መላው ቤተሰብ አንድ ላይ ሆኖ ይህን ሥራ መሥራቱ የሚያበረታታና የሚያስደስት ተሞክሮ ሊሆን ይችላል። እናትና አባት በልጆቻቸው የምስራች አቀራረብ በጣም ይደሰታሉ። በ15 እና በ21 ዓመት ዕድሜ መካከል ያሉ ሦስት ወንድ ልጆች ያሏቸው አንድ ባልና ሚስት ሁል ጊዜ እሮብ እሮብ ከትምህርት ቤት በኋላና ቅዳሜ ጠዋት ለሕዝብ በሚደረገው የስብከት ሥራ ከልጆቻቸው ጋር አብረዋቸው የመካፈል ልማድ እንዳላቸው ይናገራሉ። አባትዬው እንዲህ ይላል:- “በየጊዜው አንድ ነገር እናስተምራቸዋለን። በአገልግሎት የምናሳልፈው ጊዜ አስደሳችና የሚያበረታታ ተሞክሮ እንዲሆን እንጥራለን።”

10. ወላጆች በአገልግሎት ረገድ ልጆቻቸውን ሊጠቅሙ የሚችሉት እንዴት ነው?

10 መላው ቤተሰብ በስብከትና በማስተማሩ ሥራ አብሮ መካፈሉ ጥሩ ውጤት ሊያስገኝ ይችላል። ሰዎች ሕፃናት የሚናገሩትን ቀላልና ልባዊ የሆነ መልእክት ይበልጥ የሚያዳምጡበት ጊዜ አለ። አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜም አባታቸውና እናታቸው አጠገባቸው ስለሚኖሩ ሊረዱአቸው ይችላሉ። ወላጆች ልጆቻቸው ደረጃ በደረጃ ስልጠና እያገኙ እንዳሉና በዚህ መንገድ ‘የእውነትን ቃል በትክክል የሚናገሩና የማያሳፍሩ’ አገልጋዮች መሆናቸውን ማረጋገጥ አለባቸው። ቤተሰቦች በዚህ መንገድ አብረው ሲሰብኩ ወላጆች ልጆቻቸው በአገልግሎቱ ያላቸውን ዝንባሌ፣ ፍሬያማነትና ጥሩ ጠባይ ለማየት ይችላሉ። ቋሚ የሆነ እቅድ በማውጣት የልጁን እድገት ይከታተላሉ እንዲሁም እምነቱን ለማጠንከር ዘላቂ የሆነ ስልጠናና ማበረታቻ ይሰጣሉ። በዚሁ ጊዜም ልጆቹ ወላጆቻቸው በአገልግሎት ረገድ የሚያሳዩአቸውን ጥሩ ምሳሌነት ለመመልከት ይችላሉ። ቤተሰቦች እርስ በርሳቸው እየተሳሰቡ አብረው መሥራታቸው በዚህ ጭንቀትና ዓመፅ በበዛበት ዘመን ወንጀል በሚበዛባቸው አካባቢዎች ከአደጋ ሊጠብቃቸው ይችላል። — 2 ጢሞቴዎስ 2:​15፤ ፊልጵስዩስ 3:⁠16

11. አንድ ልጅ ለእውነት ያለው ቅንዓት በቀላሉ እንዲቀንስ ሊያደርግ የሚችለው ምንድን ነው?

11 ልጆች የትልልቆችን ግብዝነት በቀላሉ መመልከት ይችላሉ። ወላጆች ለእውነትና ከቤት ወደ ቤት ለሚደረገው አገልግሎት እውነተኛ ፍቅር ከሌላቸው ልጆቹ ቀናተኞች ይሆናሉ ብሎ መጠበቅ አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል። እንግዲያው የጤና እክል የሌለበት ወላጅ የመስክ አገልግሎቱ ከልጆቹ ጋር የሚያደርገው ሳምንታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ብቻ ከሆነ እነዚህ ልጆች ትልቅ ሲሆኑ ከባድ ችግር ሊገጥማቸው ይችላል። — ምሳሌ 22:​6፤ ኤፌሶን 6:​4

12. አንዳንድ ቤተሰቦች ከይሖዋ ልዩ የሆነ በረከት ሊያገኙ የሚችሉት እንዴት ነው?

12 ‘በአንድ ሐሳብ የመስማማት’ አንዱ ጥቅም ቢያንስ አንዱ የቤተሰቡ አባል በጉባኤው ውስጥ የሙሉ ጊዜ አቅኚ አገልጋይ እንዲሆን ለመርዳት ጥረታቸውን እንዲያስተባብሩ መርዳቱ ነው። በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ብዙ ቤተሰቦች እንዲህ ያደርጋሉ። ይህን በማድረጋቸውም አቅኚ የሆነው የቤተሰባቸው አባል ከሚያገኘው ተሞክሮና እየጨመረ ከሚሄደው ፍሬያማነት ሁሉም በረከት አግኝተዋል። — 2 ቆሮንቶስ 13:​11፤ ፊልጵስዩስ 2:​1–4

ችግሮችን አብሮ መፍታት

13, 14. (ሀ) የአንድን ቤተሰብ አንድነት ሊነኩ የሚችሉ ሁኔታዎች ምንድን ናቸው? (ለ) ብዙዎቹን የቤተሰብ ችግሮች መከላከል የሚቻለው እንዴት ነው?

13 በዚህ “ውጥረት” እና “አደጋ” በተስፋፋበት አስቸጋሪ ዘመን ሁላችንም ተጽዕኖ ይደርስብናል። (2 ጢሞቴዎስ 3:​1 ሪቫይዝድ ስታንዳርድ ቨርዥን፤ ፊሊፕስ) በሥራ ቦታ፣ በትምህርት ቤት፣ ከቤት ውጭ በየትም ቦታ እንዲሁም በቤትም እንኳን ሳይቀር ችግሮች አሉ። አንዳንዶች በሕመም ወይም ሥር በሰደዱ የስሜት መቃወስ ችግሮች ይሰቃያሉ። ይህም በቤተሰቡ ውስጥ ውጥረትና አለመግባባት ሊያስከትል ይችላል። እንደዚህ ዓይነቶቹን ሁኔታዎች እንዴት መቆጣጠር ይቻላል? እርስ በርስ በመኮራረፍና ዝም በማለት ነውን? በአንድ ቤት ውስጥ እየኖሩ ራስን በማግለል ነውን? አይደለም። ከዚህ ይልቅ ጭንቀቶቻችንን ሁሉ መናገርና እርዳታ መጠየቅ ያስፈልገናል። ይህንን ለማድረግ ደግሞ ከአፍቃሪ የቤተሰብ ክልል የተሻለ ምን ቦታ ይኖራል? — 1 ቆሮንቶስ 16:​14፤ 1 ጴጥሮስ 4:⁠8

14 ማንኛውም ሐኪም እንደሚያውቀው በሽታን ከማዳን አስቀድሞ መከላከል የተሻለ ነው። የቤተሰብ ችግርም ቢሆን ከዚህ የተለየ አይደለም። ክፍትና ግልጽ ውይይት ማድረግ ብዙ ጊዜ ችግሮቹ ከባድ እንዳይሆኑ አስቀድሞ ለመከላከል ያስችላል። ከባድ ችግሮች ቢነሱም እንኳን ቤተሰቡ አንድ ላይ ሆኖ ጉዳዩን የሚመለከቱትን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ከመረመረ ችግሮቹን ለመቆጣጠርና እንዲያውም መፍትሄ እንኳን ለማግኘት ይቻላል። በቆላስይስ 3:​12–14 ላይ ያሉትን የሚከተሉትን የጳውሎስን ቃላት በሥራ ላይ በማዋል ሸካራ የነበረው ግንኙነት ወደ ለስላሳነት ሊለወጥ ይችላል:- “ምሕረትን፣ ርኅራኄን፣ ቸርነትን፣ ትሕትናን፣ የዋህነትን፣ ትዕግሥትን ልበሱ፤ እርስ በርሳችሁ ትዕግሥትን አድርጉ፣ ማንም በባልንጀራው ላይ የሚነቅፈው ነገር ካለው፣ ይቅር ተባባሉ፤ . . . በእነዚህም ሁሉ ላይ የፍጻሜ ማሰሪያ የሆነውን ፍቅርን ልበሱ።”

አብሮ መዝናናት

15, 16. (ሀ) የክርስቲያን ቤተሰብ በምን ባሕርያት ተለይቶ መታወቅ ይኖርበታል? (ለ) አንዳንድ ሃይማኖቶች ምን ዓይነት ሰዎችን ያፈራሉ? ለምንስ?

15 ይሖዋ ደስተኛ አምላክ ነው። እውነትም ለሰው ዘሮች ተስፋ የያዘ አስደሳች መልእክት ነው። ከዚህም በላይ ከመንፈስ ፍሬዎች አንዱ ደስታ ነው። ይህ ደስታ አንድ ስፖርተኛ በአንዳንድ ውድድሮች አሸንፎ ከሚያገኘው ጊዜያዊ ደስታ በጣም የተለየ ነው። ይህ ደስታ ከይሖዋ ጋር የቅርብ ዝምድና ከመኮትኮት የሚገኝ ከልብ ገንፍሎ የሚወጣ የማያቋርጥ የእርካታ ስሜት ነው። በመንፈሳዊ ነገሮችና ገንቢ በሆኑ ግንኙነቶች ላይ የተመሠረተ ደስታ ነው። — ገላትያ 5:​22፤ 1 ጢሞቴዎስ 1:​11

16 ስለዚህ ክርስቲያን የይሖዋ ምስክሮች እንደመሆናችን መጠን የተከፋን ወይም የማንስቅና የማንጫወት የምንሆንበት ምንም ምክንያት የለም። አንዳንድ ሃይማኖቶች አፍራሽ በሆኑ ነገሮች ላይ እምነት ስለሚያደርጉ ደስታ የሌላቸውን ሰዎች አፍርተዋል። የሚያስተምሩት ትምህርት መጽሐፍ ቅዱሳዊም ሚዛናዊም ያልሆነ ድፍንፍን ያለና ደስታ የማይገኝበት አምልኮ አስገኝቷል። በአምላክ አገልግሎት ደስተኛ የሆኑ ቤተሰቦችን አያፈሩም። ኢየሱስ የመዝናናትንና የማረፍን አስፈላጊነት ተገንዝቦ ነበር። ለምሳሌ ያህል በአንድ ወቅት ደቀ መዛሙርቱን “ብቻችሁን ወደ አንድ ገለልተኛ ስፍራ ሂዱና ጥቂት ዕረፉ” ሲል ጋብዟቸዋል። — ማርቆስ 6:​30–32 1980 ትርጉም ፤ መዝሙር 126:​1–3፤ ኤርምያስ 30:​18, 19

17, 18. ክርስቲያን ቤተሰቦች እንዴት ባሉ ተገቢ መንገዶች መዝናናት ይችላሉ?

17 ቤተሰቦችም በተመሳሳይ የሚዝናኑበት ጊዜ ያስፈልጋቸዋል። አንድ ወላጅ ስለ ልጆቹ እንዲህ ብሏል:- “አብረን ለመዝናናት የምናደርጋቸው ብዙ ነገሮች አሉ። ወደ ሐይቆች እንሄዳለን፣ በመናፈሻ ቦታዎች ኳስ እንጫወታለን፣ ወደተራራዎች ሄደን ለመንሸራሸር ዝግጅት እናደርጋለን። አልፎ አልፎ ደግሞ አብረን ሙሉ ቀን የምናገለግልበት ‘የአቅኚዎች ቀን’ አለን። በዚህ ቀን ለየት ያለ ምግብ አዘጋጅተን እንመገባለን፤ ሥጦታ የምንሰጣጥበትም ጊዜ አለ።”

18 ወላጆች ሊያዘጋጁ ከሚችሉአቸው መዝናኛዎች መካከል አራዊት ወደሚታዩበት ቦታ ሄዶ መንሸራሸር፣ የተለያዩ መጫዎቻዎች ወዳሉባቸው ቦታዎች መሄድ፣ ቤተ መዘክሮችንና ሌሎች አስደናቂ ቦታዎችን መጎብኘት ይገኛሉ። በጫካ ውስጥ በእግር መንሸራሸር፣ ወፎችን መመልከትና አትክልት መትከል አብረን ልንደሰት የምንችልባቸው እንቅስቃሴዎች ሊሆኑ ይችላሉ። በተጨማሪም ወላጆች ልጆቻቸው የሙዚቃ መሣሪያዎችን መጫወት እንዲለማመዱ ወይም በትርፍ ጊዜ ለመዝናናት የሚሠራ ሥራ ወይም ሆቢ እንዲኖራቸው ሊያበረታቷቸው ይችላሉ። ሚዛናዊ የሆኑ ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር ለመጫወት ጊዜ እንደሚያመቻቹ የተረጋገጠ ነው። ቤተሰብ አብሮ የሚጫወት ከሆነ አብሮ ይቆያል።

19. ቤተሰብን ሊጎዳ የሚችለው ዘመናዊ ዝንባሌ ምንድን ነው?

19 በአሁኑ ጊዜ ወጣቶች ከቤተሰባቸው ተነጥለው ለራሳቸው የሚያዝናናቸውን ነገር ማድረጋቸው በጣም የተስፋፋ ነገር ሆኖአል። አንድ ወጣት በትርፍ ጊዜው ለመዝናናት የሚሠራው ሥራ ወይም የራሱ የሆነ በጣም የሚወደው የጊዜ ማሳለፊያ ቢኖረው ምንም ጉዳት ባይኖረውም እንዲህ ዓይነቱ ፍላጎት ዘወትር ከቤተሰብ መለየትን እንዲፈጥር መፍቀድ ጥበብ አይሆንም። ከዚህ ይልቅ “እያንዳንዱ ለራሱ የሚጠቅመውን አይመልከት፣ ለባልንጀራው ደግሞ እንጂ” በማለት ጳውሎስ የሰጠውን ምክር በሥራ ላይ ለማዋል እንፈልጋለን። — ፊልጵስዩስ 2:​4

20. ትልልቅ ስብሰባዎች ብዙ ደስታ የሚገኝባቸው አጋጣሚዎች ሊሆኑ የሚችሉት እንዴት ነው?

20 በትልልቅ ስብሰባዎች ላይ ቤተሰቦች አንድ ላይ ተቀምጠው ማየት በጣም ያስደስታል! ቤተሰቦች አብረው ሲቀመጡ ትልልቆቹ ልጆች ትንንሾቹን ሊረዷቸው ይችላሉ። እንዲህ ዓይነቱ ዝግጅት አንዳንድ ወጣቶች በቡድን ሆነው ከኋላ በመቀመጥ ለስብሰባው ፕሮግራም ምንም ትኩረት እንዳይሰጡ ከሚያደርጋቸው ዝንባሌ ይከላከላል። ቤተሰቡ በየትኛው መንገድ እንደሚጓዝ፣ እገረመንገዳቸውን ምን ቦታዎችን እንደሚያዩና የት እንደሚያርፉ ከተመካከሩ ወደ ስብሰባዎችና ከስብሰባዎች ወደ ቤት የሚደረገው ጉዞም አስደሳች ሊሆን ይችላል። በኢየሱስ ዘመን ቤተሰቦች አንድ ላይ ሆነው ወደ ኢየሩሳሌም ሲጓዙ እንዴት ያለ የሚያስደስት ጊዜ ያሳልፉ እንደነበረ ገምት! — ሉቃስ 2:​41, 42

አብሮ መሆን የሚያስገኘው በረከት

21. (ሀ) ከጋብቻ የተሳካ ውጤት ለማግኘት ጥረት ልናደርግ የምንችለው እንዴት ነው? (ለ) ዘላቂ ለሆነ ትዳር የተሰጡት አራቱ ጥሩ ምክሮች ምንድን ናቸው?

21 የተሳኩ ጋብቻዎችንና አንድነት ያላቸውን ቤተሰቦች ማግኘት በፍጹም ቀላል ሆኖ አያውቅም። በአጋጣሚ የሚገኙ ነገሮችም አይደሉም። አንዳንዶች ማንኛውንም ጥረት አቁመው ጋብቻው በፍቺ እንዲያበቃ ማድረግና ሌላ አዲስ ጅምር መሞከር የሚቀል መስሎ ታይቷቸዋል። ይሁን እንጂ ብዙውን ጊዜ በሁለተኛውም ሆነ በሦስተኛው ጋብቻቸው ያው የቀድሞ ችግር ያጋጥማቸዋል። ክርስቲያናዊው መፍትሔ ከሁሉ ይሻላል። የፍቅርና የአክብሮት መጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን በሥራ ላይ በማዋል ጋብቻችሁን የተሳካ ለማድረግ ጣሩ። አንድነት ያለው ቤተሰብ ከራስ ወዳድነት በራቀ መንፈስ በመስጠትና በመቀበል ላይ የተመካ ነው። አንድ የጋብቻ አማካሪ ትዳር እንዲዘልቅ የሚያስችል አንድ ቀላል መመሪያ አስቀምጠዋል። እንዲህ ብለው ጽፈዋል:- “በጥሩ ጋብቻዎች ውስጥ የሚገኙ እጅግ አስፈላጊ የሆኑ አራት ባሕርያት ለመስማት ፈቃደኛ መሆን፣ ይቅርታ የመጠየቅ ችሎታ፣ ሳያቋርጡ የስሜት ድጋፍ የመስጠት ችሎታና በፍቅር የመደባበስ ፍላጎት ናቸው።” እነዚህ ባሕርያት በእርግጥም ጋብቻ እንዲዘልቅ ለማድረግ ያስችላሉ። ምክንያቱም ጥልቅ በሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ላይ የተመሠረቱ ባሕርያት ናቸው። — 1 ቆሮንቶስ 13:​1–8፤ ኤፌሶን 5:​33፤ ያዕቆብ 1:​19

22. አንድነት ያለው ቤተሰብ ሲኖረን ከምናገኛቸው ጥቅሞች አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው?

22 የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር የምንከተል ከሆነ አንድነት ላለው ቤተሰብ ጽኑ መሠረት ይኖረናል። አንድነት ያላቸው ቤተሰቦች ደግሞ አንድነት ላለውና በመንፈሳዊ ጠንካራ ለሆነ ጉባኤ መሠረት ናቸው። በዚህ መንገድ አንድ ሆነን ለይሖዋ እየጨመረ የሚሄድ ምስጋና ስናቀርብ ብዙ በረከቶችን ከእሱ እናገኛ⁠ለን።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a  “ቤተሰብ ተብሎ የተተረጎመው ፋምሊ የሚለው የእንግሊዘኛ ቃል የመጣው ፋምሊያ ከሚለው የላቲን ቃል ሲሆን ቃሉም በመጀመሪያ በአንድ ትልቅ ቤት ውስጥ ያሉትን አገልጋዮችና ባሪያዎች ከዚያም የቤቱን ባለቤት፣ የቤት እመቤቷን፣ ልጆቹንና ጠቅላላ የቤተሰቡን አባሎች የሚጨምረውን ቤተሰብ ለማመልከት ያገለግላል። — በኤሪክ ፓርትሪጅ የተዘጋጀው ኦሪጂንስ — ኤ ሾርት ኤቲሞሎጂካል ዲክሽነሪ ኦቭ ሞደርን ኢንግሊሽ።

ታስታውሳለህን?

◻ ቤተሰብ በመተባበር መሥራቱ ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው?

◻ ቋሚ የቤተሰብ ጥናት በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

◻ ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር በመስክ አገልግሎት መሠማራታቸው ጥሩ የሆነው ለምንድን ነው?

◻ ችግሮችን በቤተሰብ ክልል ውስጥ መወያየት የሚረዳው ለምንድን ነው?

◻ ክርስቲያን ቤተሰብ የተከዘና ሐዘንተኛ መሆን የማይኖርበት ለምንድን ነው?

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ቤተሰብህ ቢያንስ በቀን አንድ ጊዜ አንድ ላይ ምግብ ይበላልን?

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የቤተሰብ ሽርሽር የሚያዝናና የሚያስደስት መሆን ይኖርበታል

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ