ጎረቤትህን መውደድ ያለብህ ለምንድን ነው?
የዘላለም ሕይወት ማግኘታችን ለአምላክና ለጎረቤቶቻችን ባለን ፍቅር ላይ የተመካ ነው። ይህ ነጥብ ከ2,000 ዓመታት በፊት በተካሄደ ውይይት ላይ ግልጽ ተደርጓል።
የሙሴን ሕግ ጠንቅቆ የተማረ አንድ አይሁዳዊ ኢየሱስን “የዘላለምን ሕይወት እንድወርስ ምን ላድርግ?” ሲል ጠየቀው። ኢየሱስም መልሶ “በሕግ የተጻፈው ምንድር ነው? እንዴትስ ታነባለህ?” አለው። ሰውየውም ከሕጉ በመጥቀስ እንዲህ አለ:- “ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህም በፍጹም ኃይልህም በፍጹም ሐሳብህም ውደድ፤ ባልንጀራህን [ጎረቤትህን አዓት] እንደ ራስህ ውደድ።” ኢየሱስም “እውነት መለስህ፤ ይህን አድርግ በሕይወትም ትኖራለህ” አለው። — ሉቃስ 10:25–28
ከዚያም ጠያቂው ኢየሱስን “ባልንጀራዬስ [ጎረቤቴስ አዓት] ማን ነው?” ሲል ጠየቀው። ኢየሱስ በቀጥታ ከመመለስ ይልቅ በወንበዴዎች ስለ ተዘረፈ፣ ስለ ተደበደበና በሕይወትና በሞት መካከል ትተውት ስለሄዱ ስለ አንድ አይሁዳዊ ምሳሌያዊ ታሪክ ነገረው። በዚያው መንገድ ላይ ሁለት አይሁዳውያን አለፉ፤ የመጀመሪያው ካህን ሌላው ደግሞ ሌዋዊ ነበር። ሁለቱም እንደ እነርሱ አይሁዳዊ የነበረው ሰው የደረሰበትን ሁኔታ አስተውለዋል። ነገር ግን እርሱን ለመርዳት ምንም አላደረጉም። ቀጥሎ አንድ ሳምራዊ መጣ። እርሱም አዘነለትና የተጎዳውን አይሁዳዊ ቁሰሎች በጨርቅ አሠራቸው፤ ከዚያም ወደ እንግዶች ማረፊያ ወሰደውና ለሚደረግለት ተጨማሪ እንክብካቤ የሚያስፈልገውን ወጪ ከፍሎለት ሄደ።
ኢየሱስ ጠያቂውን “እንግዲህ ከነዚህ ከሦስቱ በወንበዴዎች እጅ ለወደቀው ባልንጀራ [ጐረቤት አዓት] የሆነው ማንኛው ይመስልሃል?” አለው። ርኅሩኁ ሳምራዊ እንደነበረ ግልጽ ነው። እውነተኛ የጎረቤት ፍቅር የጎሳ ልዩነት የማያግደው መሆኑን ኢየሱስ በዚህ መንገድ አሳይቷል። — ሉቃስ 10:29–37
የጎረቤት ፍቅር እጦት
ዛሬ በተለያዩ ጎሳዎች መካከል እያደገ የመጣ የከረረ ጥላቻ አለ። ለምሳሌ በቅርቡ በጀርመን ውስጥ የአዲሶቹ ናዚዎች አባላት አንድን ሰው መሬት ላይ ጥለው በትላልቅ ጫማዎቻቸው ሁሉም የጎን አጥንቶቹ እስኪሰባበሩ ድረስ ረጋገጡት። ከዚያም ከፍተኛ የአልኮል መጠን ያለው መጠጥ አፈሰሱበትና በእሳት ለኮሱት። ይህ ሰው እንዲሞት ይህ ሁሉ ጥቃት የደረሰበት አይሁዳዊ ይሆናል በሚል ነው። ከዚህ ጋር ግንኙነት የሌለው ሌላ ነገርም ደርሷል። በሐምበርግ አጠገብ አንድ ቤት በቦምብ በመፈንዳቱ ተቀጣጠለና ትውልዳቸው ቱርካውያን የሆኑ ሦስት ሰዎች ተቃጥለው ሞተዋል። ከእነዚህም መካከል አንዲት የአሥር ዓመት ልጃገረድ ትገኛለች።
በቦልካንና ከዚያ በስተምሥራቅ ራቅ ብለው ባሉ አገሮችም የጎሳ ጦርነቶች በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት እየቀጠፉ ነው። በባንግላዴሽ፣ በሕንድ፣ በፓኪስታን በሃይማኖትና በባሕል በማይጣጣሙ ሕዝቦች መካከል በተደረጉ ግጭቶች ሌሎች ሰዎች ሞተዋል። በአፍሪካም እርስ በርስ በሚደረጉ የጎሳና የዘር ግጭቶች አሁንም የሌሎች ሕይወት ለሞት ተዳርጓል።
አብዛኞቹ ሰዎች እንደነዚህ ባሉ ዓመፆች ይሰቀቃሉ፤ ጎረቤቶቻቸውን ለመጉዳት ብለው ምንም ነገር አያደርጉም። እንዲያውም በጀርመን የሚካሄደውን በዘር ላይ የተመሠረተ አምባጓሮ የሚያወግዙ ትላልቅ ሰላማዊ ሰልፎች በዚያው አገር ተደርገዋል። ይሁንና ዘ ኒው ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ እንዲህ ይላል:- “በዓለም ዙሪያ የተለያዩ ማኅበረሰብ አባላት የሆኑ ሰዎች የራሳቸውን የሕይወት መንገድ አጠገባቸው ካሉት ጎረቤቶቻቸው የላቀ እንደሆነ አድርገው ይመለከታሉ።” እንዲህ የመሰሉ አመለካከቶች ለጎረቤት ፍቅር ጋሬጣ ናቸው። ኢየሱስ ሕይወት ማግኘታችን የተመካው ለአምላክና ለጎረቤቶቻችን ባለን ፍቅር ላይ እንደሆነ ተናግሯል። ታዲያ ለዚህ ነገር መፍትሄ ሊኖረው ይችላልን?
[በገጽ 2 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
Cover: Jules Pelcog/Die Heilige Schrift
[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
The Good Samaritan/The Dore Bible illustrations /Dover Publications, Inc.