የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ሪፖርት
“ጥበብን የሚያገኝ ሰው ምስጉን [ደስተኛ አዓት] ነው”
ይህ ምሳሌ በአሁኑ ጊዜ ቁጥራቸው ከ71,000 በላይ የሆኑ የይሖዋ ምስክሮች በሚገኙባት በኮሪያ ምን ያህል እውነት እንደሆነ ተረጋግጧል። (ምሳሌ 3:13) እስቲ አስበው፣ ከእነዚህ ምስክሮች ውስጥ 42 በመቶ የሚሆኑት በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ላይ የተሠማሩ ናቸው! ደስታ ጥበብን የሚፈልጉ ሰዎች ዕጣ መሆኑን የሚቀጥለው ተሞክሮ ያሳያል።
ፑዛን በተባለ ከተማ የምትኖር ሴት ከሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት በአንዱ ለ16 ዓመታት ተሰብስባ ነበር። በቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ ከቅዱስ ጽሑፉ ጋር የማይስማሙ ብዙ ልማዶችን ተመለከተችና አምላክ ሊኖር አይችልም ብላ አሰበች። በሌላው በኩል ደግሞ የአምላክን ሕልውና መካድ አልቻለችም። ከዚህም የተነሣ እውነተኛ ቤተ ክርስቲያን ካለ እሱን እንድታገኝ እንዲረዳት ከልብ ወደ አምላክ ጸለየች። እዚህ ደረጃ ላይ ስትደርስ የይሖዋ ምስክሮች ትዝ አሏትና እንዲያውም የነበረችበት ቤተ ክርስቲያን ይንቃቸው እንደነበረና ምስክሮቹ በሥላሴ፣ በእሳታማ ሲኦልና በሌሎች የሕዝበ ክርስትና መሠረተ ትምህርቶች ስለማያምኑ የቤተ ክርስቲያን ተሳላሚዎቹን ማስጠንቀቁንም አስታወሰች። ምናልባት እውነተኛው ቤተ ክርስቲያን እነሱ ሊሆኑ ይችሉ ይሆንን? በጎረቤቷ እርዳታ የመንግሥት አዳራሹ የት እንደሚገኝ አወቀች። በሚቀጥለው ቀንም በስብሰባ ላይ ተገኘች።
በስብሰባዎቹ ሥርዓታማነት በጣም ተገረመች። በቤተ ክርስቲያኗ ይደረግ እንደነበረው ያለ የአጉል አክራሪነት ጩኸት ወይም ስሜታዊ የሆኑ መዝሙሮች አላጋጠማትም። ከእሷ ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ፈቃደኛ ከሆነች አንዲት ምስክር ጋር ተዋወቀችና ብዙ ጥያቄዎች ስለነበሯት የመጀመሪያው ጥናት ሦስትና አራት ሰዓት ያህል ፈጀ። በሁለተኛው ጥናት ከቤተ ክርስቲያኗ እንደምትሰናበትና የይሖዋ ምስክር ለመሆን የወሰነች መሆኗን ተናገረች። ለምታስጠናት እኅትም በስብሰባ ላይ ብቻ መገኘቱ እንደሚበቃትና ከዚህ በላይ ማጥናት እንደማያስፈልጋት ነገረቻት። ይሁን እንጂ ስብሰባዎች ላይ ከመገኘት በተጨማሪ የግል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ያለውን ጥቅም እንድታስተውል ተደረገች። የቀረበላትን ሐሳብ ተቀበለችና ጥናቷን ቀጠለች፣ ከጊዜ በኋላም ተጠመቀች።
አሁን የእውነተኛውን አምላክ የይሖዋን ጥበብ ስላገኘች ደስተኛ ናት። በአምላክ አዲስ ዓለም ለዘላለም የመኖር ተስፋም አግኝታለች።
ጡረታ የወጣ ጄኔራል እውነትን ተማረ
የአንድ የጦር ጄኔራል ሚስት በ1962 ተጠመቀች። ባልዋ መጀመሪያ ላይ ይቃወማት ነበር። ነገር ግን መቃወሙን አቆመና ለሚቀጥሉት 28 ዓመታት ያዝ ለቀቅ እያደረገ ከተለያዩ ወንድሞች ጋር በማጥናት ለእውነት ፍላጎት እንዳለው ለማሳየት ይሞክር ነበር። አንዳንድ ስብሰባዎችንና ትልልቅ ስብሰባዎችን ተካፍሏል። እውነትን በቁም ነገር ከማይዙት ሰዎች መካከል አንዱ ነበር። በ1990 እሱና ሚስቱ አንድ የወረዳ ስብሰባ ለመካፈል ወደ ጃፓን ሄዱ። በዚህ አጋጣሚ ከዚህ በፊት አድርጎት በማያውቀው መንገድ በስብሰባዎቹ የቀረቡትን ንግግሮች በትኩረት አዳመጠ። የሐሰት ሃይማኖትን የሚያጋልጡት ድፍረት የተሞላባቸው ንግግሮች ቢያስደነግጡትም የሕዝበ ክርስትናን ግብዝነት አጥርቶ ለማየት ዓይኖቹን ከፈቱለት። በኮሪያ ካየው ጋር ተመሳሳይ በሆነ መንገድ በጃፓን የሚገኙት የአምላክ ሕዝቦች ሥርዓታማነታቸውና ደስተኛነታቸው ልቡን ነካው። ወደ ኮሪያ ሲመለስ ጠበቅ አድርጎ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ጀመረ፤ በመጨረሻም ተጠመቀ።
ታዲያ ከተጠመቀ በኋላ ምን ማድረግ ይገባዋል? የአንድ የታወቀ የቱሪስቶች ሆቴል ፕሬዘዳንት ሆኖ ከሚሠራበት ቦታ በፈቃዱ ለቀቀና ከሚስቱ ጋር በሙሉ ጊዜ አገልግሎቱ ሥራ ተባበረ። እያመነታ ያባከነውን 28 ዓመት ለማካካስ ያለው ግሩም መንገድ የዘወትር አቅኚ ሆኖ ማገልገል ነው የሚል ስሜት አድሮበታል።
“ጥበብን የሚያገኝ ሰው ምስጉን [ደስተኛ አዓት] ነው” የሚለው ምሳሌ በእሱም ላይ እንደሚሠራ አሁን ተገንዝቧል።