የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w93 11/1 ገጽ 18-23
  • ታላቁ መስፍን ሚካኤል የሚቀዳጀው የመጨረሻ ድል

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ታላቁ መስፍን ሚካኤል የሚቀዳጀው የመጨረሻ ድል
  • መጠበቂያ ግንብ—1993
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • “በፍጻሜ ዘመንም”
  • ‘ግብጽ አታመልጥም’
  • የሰሜኑ ንጉሥ የመጨረሻ ዘመቻ
  • ከምሥራቅ የሚመጣ ወሬ
  • ከሰሜን የሚመጣ ወሬ
  • ሦስተኛ ንጉሥ
  • ባላንጣዎቹ ነገሥታት ፍጻሜያቸው ቀርቧል
    የዳንኤልን ትንቢት በትኩረት ተከታተል!
  • በዛሬው ጊዜ ‘የሰሜኑ ንጉሥ’ ማን ነው?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2020
  • ‘የሰሜኑ ንጉሥ’ በፍጻሜው ዘመን
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2020
  • አንድ ንጉሥ የይሖዋን መቅደስ አረከሰ
    መጠበቂያ ግንብ—1993
ለተጨማሪ መረጃ
መጠበቂያ ግንብ—1993
w93 11/1 ገጽ 18-23

ታላቁ መስፍን ሚካኤል የሚቀዳጀው የመጨረሻ ድል

“በዚያም ዘመን ስለ ሕዝብህ ልጆች የሚቆመው ታላቁ አለቃ ሚካኤል ይነሣል።” — ዳንኤል 12:​1

1. የይሖዋን ጽንፈ ዓለማዊ ሉዓላዊነት በተመለከተ ብዙዎቹ የዓለም መሪዎች ምን ዓይነት ዝንባሌ አሳይተዋል? የሰሜኑ ንጉሥስ በዚህ ረገድ የተለየ ያልሆነው እንዴት ነው?

“ቃሉን እሰማ ዘንድ እስራኤልንስ እለቅቅ ዘንድ ይሖዋ ማን ነው?” (ዘጸአት 5:​2 አዓት) እነዚህ ፈርዖን ለሙሴ የተናገራቸው የግድድር ቃላት ነበሩ። ከሁሉ የሚበልጠውን የይሖዋን የአምላክነት ሥልጣን አምኖ ለመቀበል አሻፈረኝ በማለት ፈርዖን እስራኤላውያንን በባርነት ይዞ ለመቆየት ቆርጦ ነበር። ሌሎች ገዥዎችም፣ በዳንኤል ትንቢት ላይ የተጠቀሱትንም ጨምሮ፣ በይሖዋ ላይ ተመሳሳይ ንቀት አሳይተዋል። (ኢሳይያስ 36:​13–20) ይባስ ብሎ የሰሜኑ ንጉሥ ንቀቱን ከልክ ያለፈ አደረገው። መልአኩ “ራሱንም ከፍ ከፍ ያደርጋል፣ በአማልክትም አምላክ ላይ በትዕቢት ይናገራል፤ . . . የአባቶቹንም አምላክ የሴቶችንም ምኞት አይመለከትም፤ ራሱንም ከሁሉ በላይ ያደርጋልና አማልክትን ሁሉ አይመለከትም [አስወግዷል አዓት]” ብሏል። — ዳንኤል 11:​36, 37

2, 3. የሰሜኑ ንጉሥ “የአባቶቹን አምላክ” ትቶ እንግዳ “አምላክ” የተከተለው በምን መንገድ ነው?

2 እነዚህን ትንቢታዊ ቃላት በመፈጸም የሰሜኑ ንጉሥ “የአባቶቹን አምላክ” (ወይም “የቅድመ አያቶቹን አማልክት” ዘ ኒው ኢንግሊሽ ባይብል )፣ የሮማውያን አረመኔያዊ አማልክትም ይሁኑ የሕዝበ ክርስትና ሥላሴያዊ መለኮት፣ አስወግዷል። ሂትለር ሕዝበ ክርስትናን ዓላማውን ለማሳካት ሲጠቀምባት እሷን አንድ አዲስ በሆነ ጀርመናዊ ቤተ ክርስቲያን ሊተካት እንዳሰበ ማስረጃዎቹ ያረጋግጣሉ። በእሱ እግር የተተካው የሰሜን ንጉሥም ፊት ለፊት አምላክ የለም የሚል አቋም ይዟል። በዚህ ዓይነት የሰሜኑ ንጉሥ ‘ራሱን ከሁሉ በላይ ከፍ ከፍ በማድረግ’ ራሱን አምላክ አድርጓል።

3 ትንቢቱ በመቀጠል “በእነዚህ ፋንታ ግን የአምባዎቹን አምላክ ያከብራል፤ አባቶቹም ያላወቁትን አምላክ በወርቅና በብር በዕንቁና በከበረ ነገር ያከብረዋል” ይላል። (ዳንኤል 11:​38) እንደ እውነቱ ከሆነ የሰሜኑ ንጉሥ ተስፋውን የጣለው ‘በአምባዎቹ አምላክ’ ላይ ማለትም ዘመናዊ በሆነው ሳይንሳዊ የውትድርና ስልት ላይ ነው። ይህ የፍጻሜ ዘመን ከገባ ጀምሮ በዚህ “አምላክ” አማካኝነት መዳንን ለማግኘት በመሻት እጅግ ብዙ የሆነ ሀብት በዚህ አምላክ መሠዊያ ላይ አፍስሷል።

4. የሰሜኑ ንጉሥ እስከ አሁን ድረስ ምን ምን ነገሮች ተሳክተውለታል?

4 “በእንግዳም አምላክ እርዳታ በጽኑ አምባ ላይ ያደርጋል፤ ለሚያውቁት ክብር ይበዛላቸዋል፣ በብዙም ላይ ያስገዛቸዋል፣ ምድርንም በዋጋ ይከፍላል” ወይም ይሸነሽናል። (ዳንኤል 11:​39) የሰሜኑ ንጉሥ በወታደራዊው “እንግዳ አምላክ” በመታመን “በመጨረሻው ቀን” አስፈሪ ወታደራዊ ኃይል ያለው በመሆን ‘በተሳካ ሁኔታ’ ተከናውኖለታል። (2 ጢሞቴዎስ 3:​1) የሱን ፍልስፍና የሚከተሉ መንግሥታት የፖለቲካ፣ የገንዘብና አንዳንድ ጊዜም ወታደራዊ ድጋፍ በማግኘት ወሮታቸውን ይቀበሉ ነበር።

“በፍጻሜ ዘመንም”

5, 6. የደቡቡ ንጉሥ ‘የተጋፋው’ እንዴት ነው? የሰሜኑ ንጉሥስ በዚህ ተበሳጭቶ ምን አደረገ?

5 ዳንኤል 11:​40 “በፍጻሜ ዘመንም የደቡብ ንጉሥ ከእርሱ ጋር ይዋጋል [ይጋፋል አዓት]” ይላል። ይህ እና የሚቀጥሉት ጥቅሶች በፊታችን ባሉት ጊዜያት እንደሚፈጸሙ ተደርገው ታይተው ነበር። ይሁን እንጂ እዚህ ላይ የተጠቀሰው “የፍጻሜ ዘመን” በዳንኤል 12:​4, 9 ላይ ከተጠቀሰው ጋር አንድ ዓይነት ከሆነ በፍጻሜው ዘመን ሁሉ ሲከናወን እንደቆየ አድርገን መረዳት ይገባናል። በዚህ ጊዜ ውስጥ የደቡቡ ንጉሥ የሰሜኑን ንጉሥ ‘ሲጋፋው’ ቆይቷልን? አዎን፣ ሲጋፋው ቆይቷል። ከአንደኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ጀርመንን ለመቅጣት ታስቦ የተፈረመው የሰላም ውል ስምምነት ለበቀል የሚያነሣሳ ‘ግፊያ’ ነበር። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ድሉን ከተቀዳጀ በኋላ የደቡቡ ንጉሥ በተቀናቃኙ መንግሥት ላይ አስፈሪ የሆነ የኑክሌር መሣሪያዎችን በማነጣጠር ኔቶ በመባል የሚታወቀውን ኃይለኛ የሆነ ወታደራዊ ግንባር አደራጅቷል። ዓመታቱ እየገፉ ሲሄዱ ‘ግፊያው’ የተራቀቀ የስለላ ቴክኖሎጂ እንዲሁም ዲፕሎማሲያዊና ወታደራዊ ጥቃት ማድረስን የሚጨምር ሆነ።

6 ታዲያ የሰሜኑ ንጉሥ ይህ ሁሉ ሲደርስበት ምን አደረገ? “የሰሜንም ንጉሥ ከሰረገሎችና ከፈረሰኞች ከብዙም መርከቦች ጋር እንደ አውሎ ነፋስ ይመጣበታል፤ ወደ አገሮችም ይገባል፣ ይጐርፍማል፣ ያልፍማል።” (ዳንኤል 11:​40) የመጨረሻዎቹ ቀኖች የታሪክ ማህደር የሰሜኑን ንጉሥ የመስፋፋት ፖሊሲ ጎላ አድርጎ ይዘግባል። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ናዚው “ንጉሥ” ከድንበሩ አልፎ በአካባቢው ያሉትን አገሮች ሁሉ አጥለቅልቋቸው ነበር። ያ ጦርነት ካበቃ በኋላ ተተኪው “ንጉሥ” ከግዛት ክልሉ ውጭ ኃይለኛ ግዛት ገንብቶ ነበር። በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት የሰሜኑ ንጉሥ ከተቀናቃኙ ጋር በተዘዋዋሪ መንገድ ማለትም በሰሜኑና በደቡቡ ንጉሥ በሚደገፉ አገሮች መካከል በተደረጉት ጦርነቶችና በአፍሪካ፣ በእስያና በላቲን አሜሪካ አገሮች ውስጥ ዓመፅ በማነሣሳት ተዋግቷል። እውነተኛ ክርስቲያኖችን አሳድዷል። ሥራቸውንም ገድቧል (ይሁን እንጂ በምንም መንገድ አላስቆመውም)። እንዲሁም ወታደራዊና ፖለቲካዊው ጥቃቱ ብዙ አገሮችን በቁጥጥሩ ሥር እንዲውሉ አድርጓቸዋል። ይህ ሁኔታ የተፈጸመው “ወደ መልካሚቱም ምድር [የአምላክ ሕዝብ መንፈሳዊ ርስት] ይገባል፣ ብዙ አገሮችም ይወድቃሉ” በማለት መልአኩ አስቀድሞ በትክክል እንደተናገረው ነው። — ዳንኤል 11:​41

7. የሰሜኑ ንጉሥ መስፋፋት ውስን ሆኖ የቀረው እንዴት ነው?

7 ሆኖም ከተቀናቃኙ ኃይል አመለካከት አንጻር ሲታይ የሰሜኑ ንጉሥ አመጣጥ አስፈሪ ቢመስልም ዓለም አቀፋዊ ድል ሊጎናጸፍ አልቻለም። “ነገር ግን ኤዶምያስና ሞአብ ከአሞንም ልጆች የበለጡት ከእጁ ይድናሉ።” (ዳንኤል 11:​41) በጥንት ዘመን ኤዶም፣ ሞአብና አሞን ከሞላ ጎደል በግብጽና በሶሪያ መካከል የሚገኙ ግዛቶች ነበሩ። እነዚህም በዛሬው ጊዜ የሰሜኑ ንጉሥ ቢያነጣጥርባቸውም በእርሱ ተጽእኖ ሥር ሊያደርጋቸው ያልቻላቸውን መንግሥታትና ድርጅቶች እንደሚያመለክቱ አድርጎ መውሰድ ይቻላል።

‘ግብጽ አታመልጥም’

8, 9. የሰሜኑ ንጉሥ ተጽእኖ ለቀንደኛ ተቀናቃኙ ሳይቀር የተሰማው እንዴት ነበር?

8 መልአኩ በመቀጠል “እጁን በአገሮች ላይ ይዘረጋል፣ የግብጽም ምድር አታመልጥም። በወርቅና በብርም መዝገብ ላይ፣ በከበረችም በግብጽ ዕቃ ሁሉ ላይ ይሠለጥናል፤ የልብያና የኢትዮጵያ ሰዎችም ይከተሉታል” አለ። (ዳንኤል 11:​42, 43) “ግብጽ” ተብሎ የተጠራው የደቡቡ ንጉሥም እንኳ የሰሜኑ ንጉሥ በያዘው የመስፋፋት ፖሊሲ ሳይነካ አላለፈም። ለምሳሌ የደቡቡ ንጉሥ በቬትናም በደረሰበት ሽንፈት በጣም ተጎድቷል። “የልብያና የኢትዮጵያ ሰዎች” ስለተባለው ምን ሊባል ይቻላል? እነዚህ የጥንቷ ግብጽ አጎራባች አገሮች በዘመናችን ለምትገኘው “ግብጽ” በጂኦግራፊያዊ አቀማመጣቸው ጎረቤት ለሆኑት መንግሥታት ጥላ ሊሆኑ ይችላሉ። እነርሱም አንዳንድ ጊዜ የሰሜኑን ንጉሥ ‘ፈለግ’ ተከትለዋል።

9 የሰሜኑ ንጉሥ ‘በከበረችም በግብጽ ዕቃ ሁሉ ላይ ሠልጥኗልን’? የደቡቡን ንጉሥ ድል አላደረገውም፤ እንዲያውም እስከ 1993 ድረስ ያለው የዓለም ሁኔታ እንደሚያሳየው የሚያሸንፈውም አይመስልም። ነገር ግን የደቡቡ ንጉሥ የገንዘብ አወጣጡን እጅግ በጣም ሊነካበት በሚችል መንገድ ኃይለኛ ተጽእኖ አሳድሮበታል። ተቀናቃኙን ኃይል በመፍራት የደቡቡ ንጉሥ አስፈሪ የሆነ የጦር ሠራዊት፣ የባሕር ኃይልና የአየር ኃይል ይዞ ለመቆየት እንዲችል በየዓመቱ እጅግ ብዙ ሀብት አፍስሷል። የሰሜኑ ንጉሥ የደቡቡን ንጉሥ እስከዚህ ደረጃ ሊያደርሰው ከቻለ የገንዘብ አወጣጡን ተቆጣጥሯል፣ ‘ገዝቷል’ ሊባል ይቻላል።

የሰሜኑ ንጉሥ የመጨረሻ ዘመቻ

10. መልአኩ በሁለቱ ነገሥታት መካከል ያለውን ፉክክር ፍጻሜ በምን መንገድ ነው የገለጸው?

10 የሁለቱ ነገሥታት ፉክክር ፍጻሜ ለሌለው ጊዜ ይቀጥላልን? አይቀጥልም። መልአኩ ለዳንኤል “ከምሥራቅና ከሰሜን ግን ወሬ [የሰሜኑን ንጉሥ] ያውከዋል፤ ብዙ ሰዎችንም ይገድል ዘንድና ፈጽሞ ያጠፋ ዘንድ በታላቅ ቁጣ ይወጣል። ንጉሣዊ ድንኳኑንም በባሕርና በተቀደሰው ተራራ መካከል ይተክላል፤ ወደ ፍጻሜው ግን ይመጣል፣ ማንም አይረዳውም” በማለት ነግሮታል። — ዳንኤል 11:​44, 45

11, 12. በሰሜኑ ንጉሥና በደቡቡ ንጉሥ መካከል ባለው ፉክክር ረገድ በአሁኑ ጊዜ ያለው ፖለቲካዊ ሁኔታ ምንድን ነው? ወደፊት የምናውቀው ነገር ምንድን ነው?

11 እነዚህ ሁኔታዎች ገና ወደፊት የሚፈጸሙ ነገሮች ናቸው። ስለሆነም ትንቢቱ እንዴት ሆኖ እንደሚፈጸም በዝርዝር ለመናገር አንችልም። በቅርቡ ሁለቱን ነገሥታት የሚመለከተው የፖለቲካ ሁኔታ ተለውጧል። በአሜሪካና በምሥራቅ አውሮፓ አገሮች መካከል የነበረው መራራ ፉክክር ጋብ ብሏል። ከዚህም በላይ ሶቪየት ሕብረት ከ1991 ጀምሮ ፈራርሳ ከሕልውና ውጭ ሆናለች። — የመጋቢት 1, 1992 መጠበቂያ ግንብ እትም ገጽ 4, 5ን ተመልከት።

12 ታዲያ በአሁኑ ወቅት የሰሜኑ ንጉሥ ማን ነው? ከቀድሞዋ የሶቪየት ሕብረት አገሮች በአንዷ የሚወከል ተደርጎ ሊጠቀስ ይችላልን? ወይም ከዚህ በፊት ደጋግሞ እንዳደረገው ማንነቱን ፈጽሞ እየለወጠ ነውን? ይህ ነው ብለን መናገር አንችልም። ዳንኤል 11:​44, 45 በሚፈጸምበት ወቅት የሰሜን ንጉሥ የሚሆነው ማን ነው? የሁለቱ ነገሥታት ፉክክር እንደገና ይቀሰቀስ ይሆንን? በብዙ አገሮች አሁንም ስለሚገኘው የኑክሌር መሣሪያ ክምችትስ ምን ሊባል ይቻላል? ጊዜ እያለፈ ሲሄድ ለእነዚህ ጥያቄዎች የሚሆኑትን መልሶች እናገኛለን።

13, 14. ስለ ሁለቱ ነገሥታት የወደፊት ሁኔታ ምን የምናውቀው ነገር አለ?

13 አንድ የምናውቀው ነገር አለ። በቅርቡ የሰሜኑን ንጉሥ “ከምሥራቅና ከሰሜን ግን ወሬ ያውከዋል፤” በዚህም ተነሣስቶ የማጥቃት ዘመቻ ያደርጋል። ይህ ዘመቻ ‘የፍጻሜው’ ዋዜማ ይሆናል። ሌሎቹን የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ከመረመርን ስለዚህ “ወሬ” ብዙ ልንማር እንችላለን።

14 በመጀመሪያ ደረጃ እዚህ ላይ የሰሜኑ ንጉሥ የሚወስደው እርምጃ በደቡቡ ንጉሥ ላይ የሚሰነዘር ነው እንዳልተባለ ልብ በል። በታላቅ ተቀናቃኙ እጅ ወደ ፍጻሜው አይመጣም። በተመሳሳይም የደቡቡ ንጉሥ በሰሜኑ ንጉሥ አይደመሰስም። በአንድ አውሬ ላይ ብቅ ያለው የመጨረሻ ቀንድ እንደሆነ ተደርጎ የተገለጸው የደቡቡ ንጉሥ “ያለ [ሰው] እጅም” በአምላክ መንግሥት ይጠፋል። (ዳንኤል 7:​26፤ 8:​25) እርግጥ ነው፣ ሁሉም ምድራዊ ነገሥታት በአምላክ መንግሥት አማካኝነት በመጨረሻው በአርማጌዶን ጦርነት ይጠፋሉ። በግልጽ ማየት እንደምንችለው በሰሜኑ ንጉሥ ላይ የሚደርሰውም ይኸው ነው። (ዳንኤል 2:​44፤ 12:​1፤ ራእይ 16:​14, 16) ዳንኤል 11:​44, 45ም ወደዚህ የመጨረሻ ፍልሚያ የሚያደርሱትን ሁኔታዎች ገልጿል። የሰሜኑ ንጉሥ ፍጻሜው ላይ ሲመጣ “ማንም አይረዳውም” መባሉ አያስደንቅም!

15. ልንወያይባቸው የሚገቡ ምን ዐበይት ጥያቄዎች ይቀራሉ?

15 የሰሜኑን ንጉሥ “ብዙ ሰዎችን ያጠፋ ዘንድ” ስለሚያንቀሳቅሰው “ወሬ” የእውቀት ብርሃን የሚያበሩልን ሌሎች ትንቢቶችስ የትኞቹ ናቸው? ሊያጠፋቸው የሚፈልጋቸው “ብዙ ሰዎች” የተባሉት እነማን ናቸው?

ከምሥራቅ የሚመጣ ወሬ

16. (ሀ) ከአርማጌዶን በፊት ምን ከፍተኛ ነገር መከናወን አለበት? (ለ) “ከፀሐይም መውጫ ለሚመጡ ነገሥታት” የተባሉት እነማን ናቸው?

16 የእውነተኛ አምልኮ ቀንደኛ ጠላት ማለትም ዓለም አቀፍ የሐሰት ሃይማኖት ግዛት የሆነችው ጋለሞታይቱ ታላቋ ባቢሎን ከመጨረሻው ጦርነት ከአርማጌዶን በፊት መጥፋት አለባት። (ራእይ 18:​3–8) በምሳሌያዊው የኤፍራጥስ ወንዝ ላይ እንዲፈስ የተደረገው ስድስተኛው የአምላክ የቁጣው ጽዋ ለእሷ መጥፋት ጥላ ነው። “ከፀሐይም መውጫ ለሚመጡ ነገሥታት መንገድ እንዲሰናዳላቸው” ወንዙ ደረቀ። (ራእይ 16:​12) እነዚህ ነገሥታት እነማን ናቸው? ከይሖዋ አምላክና ከኢየሱስ ክርስቶስ ሌላ ማንም ሊሆን አይችልም!a

17. (ሀ) መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ታላቋ ባቢሎን መጥፋት ምን የሚነግረን ነገር አለ? (ለ) “ከምሥራቅ” የሚመጣ ወሬ የተባለው ምን ሊሆን ይችላል?

17 የታላቋ ባቢሎን ጥፋት በራእይ መጽሐፍ ውስጥ ሥዕላዊ በሆነ መንገድ እንደሚከተለው ተገልጿል:- “ያየሃቸውም አሥር ቀንዶችና [በፍጻሜው ዘመን የሚገዙት ‘ነገሥታትና’] አውሬው [የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን የሚያመለክተው ቀይ አውሬ] ጋለሞታይቱን ይጣላሉ፤ ባዶዋንና ራቁትዋንም ያደርጓታል፣ ሥጋዋንም ይበላሉ፣ በእሳትም ያቃጥሉአታል።” (ራእይ 17:​16) በእውነትም እነዚህ መንግሥታት ‘ብዙ ሥጋ ያጠፋሉ!’ (ዳንኤል 7:​5) ይሁን እንጂ የብሔራት ገዥዎች፣ የሰሜኑም ንጉሥ ጭምር፣ ታላቋ ባቢሎንን የሚያጠፉት ለምንድን ነው? ምክንያቱም ‘አምላክ አሳቡን እንዲያደርጉ በልባቸው ስላገባ’ ነው። (ራእይ 17:​17) ከምሥራቅ የሚመጣው ወሬ እርሱ በመረጠው መንገድ ታላቋን ሃይማኖታዊ አመንዝራ እንዲያጠፉ በሰብአውያን መሪዎች ልብ ውስጥ ይሖዋ አሳቡን ያስቀመጠበትን ይህንን የአምላክ እርምጃ ሊያመለክት ይችላል። — ዳንኤል 11:​44

ከሰሜን የሚመጣ ወሬ

18. የሰሜኑ ንጉሥ ምን ሌላ የጥቃት ዒላማ አለው? ወደ ፍጻሜው በሚመጣበት ጊዜስ ይህ ሁኔታው የት ቦታ ላይ እንዲቆም ያደርገዋል?

18 ለሰሜኑ ንጉሥ ቁጣ ዒላማ የሆነ ሌላም ነገር አለ። መልአኩ “ንጉሣዊ ድንኳኑንም በባሕርና በከበረው በቅዱሱ ተራራ መካከል ይተክላል” በማለት ተናግሯል። (ዳንኤል 11:​45) በዳንኤል ዘመን ታላቁ ባሕር የሜዲትራኒያን ባሕር ሲሆን ቅዱሱ ተራራ ደግሞ የአምላክ ቤተ መቅደስ የነበረበት የጽዮን ተራራ ነው። እንግዲያው በትንቢቱ ፍጻሜ በቁጣ የተሞላው የሰሜን ንጉሥ በአምላክ ሕዝቦች ላይ ወታደራዊ የጥቃት ዘመቻ ያካሂዳል ማለት ነው። ከአምላክ ጋር ከተጣላው የሰው ዘር “ባሕር” ወጥተው ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በሰማያዊቱ የጽዮን ተራራ የመግዛት ተስፋ ያላቸው የአምላክ ቅቡዓን አገልጋዮች መንፈሳዊ ርስት ዛሬ እሱን በመንፈሳዊ አባባል “በታላቁ ባሕርና በከበረው በቅዱሱ ተራራ መካከል” እንዲቆም ያደርገዋል። — ኢሳይያስ 57:​20፤ ዕብራውያን 12:​22፤ ራእይ 14:​1

19. በሕዝቅኤል ትንቢት ላይ እንደተመለከተው የጎግን ጥቃት የሚያነሣሳውን ወሬ እንዴት ለይተን ለማወቅ እንችላለን? (የግርጌ ማስታወሻውን ተመልከት።)

19 ዳንኤል በነበረበት ዘመን ይኖር የነበረው ሕዝቅኤል “በኋለኛው ዘመን” በአምላክ ሕዝቦች ላይ ስለሚሰነዘረው ጥቃት ትንቢት ተናግሮ ነበር። ጥቃቱ የሚቀሰቀሰው ሰይጣን ዲያብሎስን በሚያመለክተው በማጎጉ ጎግ እንደሆነ ይናገራል። (ሕዝቅኤል 38:​16) በምሳሌያዊ አባባል ጎግ የሚመጣው ከየትኛው አቅጣጫ ነው? ይሖዋ በሕዝቅኤል በኩል “ከሰሜንም ዳርቻ ከስፍራችሁ ትመጣላችሁ” በማለት ይናገራል። (ሕዝቅኤል 38:​15) ስለዚህ “ከሰሜን” የሚመጣው ወሬ የሰሜኑን ንጉሥና ሌሎቹን ነገሥታት የይሖዋን ሕዝቦች እንዲያጠቁ የሚያነሳሳውን የሰይጣንን ፕሮፓጋንዳ ሊያመለክት ይችላል።b — ከራእይ 16:​13, 14፤ 17:​14 ጋር አወዳድር።

20, 21. (ሀ) ጎግ መንግሥታትንና የሰሜኑን ንጉሥ የአምላክን ሕዝቦች እንዲያጠቁ የሚያነሣሳቸው ለምንድን ነው? (ለ) የማጥቃት እርምጃው ይሳካለታለን?

20 ጎግ ይህንን አጠቃላይ ግፍ የተሞላበት ጥቃት የሚያደራጀው የእሱ ዓለም ክፍል ባልሆኑት “በእግዚአብሔር እስራኤል” እና ከእነርሱ ጋር በተባበሩት የሌሎች በጎች ክፍል በሆኑት እጅግ ብዙ ሰዎች መንፈሳዊ ብልጽግና የተነሣ ነው። (ገላትያ 6:​16፤ ዮሐንስ 10:​16፤ 17:​15, 16፤ 1 ዮሐንስ 5:​19) ጎግ “ከአሕዛብ የተሰበሰበ፣ [መንፈሳዊ] ሀብትና ንብረትንም ያከማቸውን ሕዝብ” የጎሪጥ ይመለከታል። (ሕዝቅኤል 38:​12 አዓት፤ ራእይ 5:​9፤ 7:​9) በእነዚህ ቃሎች ፍጻሜ መሠረት የይሖዋ ሕዝቦች ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ እየበለጸጉ ነው። ከዚህ በፊት ሥራቸው ታግዶ በነበረባቸው በብዙዎቹ የአውሮፓ፣ የአፍሪካና የእስያ አገሮች ውስጥ አሁን በነፃነት አምልኮታቸውን እያከናወኑ ነው። በ1987 እና በ1992 መካከል ከአንድ ሚልዮን በላይ የሆኑ ‘የተመረጡ ዕቃዎች’ ከአሕዛብ መካከል ወጥተው እውነተኛ አምልኮ ወደሚከናወንበት ወደ ይሖዋ ቤት መጥተዋል። በመንፈሳዊ ሀብታሞችና ሰላም የሞላባቸው ናቸው። — ሐጌ 2:​7፤ ኢሳይያስ 2:​2–4፤ 2 ቆሮንቶስ 8:​9

21 የክርስቲያኖችን መንፈሳዊ ርስት በቀላሉ ድል ሊደረጉ እንደሚችሉ ‘ቅጥር የሌላቸው መንደሮች’ አድርጎ በመቁጠር ጎግ የሰውን ዘር ሙሉ በሙሉ እንዳይቆጣጠር ጋሬጣ የሆነበትን ይህንን ሕዝብ ጠራርጎ ለማጥፋት ከፍተኛ ጥረት ያደርጋል። (ሕዝቅኤል 38:​11) ነገር ግን አይሳካለትም። የምድር ነገሥታት በይሖዋ ሕዝብ ላይ ጥቃት ሲሰነዝሩ ‘ወደ ፍጻሜያቸው ይመጣሉ።’ እንዴት?

ሦስተኛ ንጉሥ

22, 23. ጎግ የጥቃት እርምጃ በሚሰነዝርበት ጊዜ ለአምላክ ሕዝቦች የሚነሣላቸው ማን ነው? ከምንስ ውጤት ጋር?

22 ይህ የጎግ ጥቃት ለሕዝቦቹ ሲል እንዲነሣና የጎግን ሠራዊት “በእስራኤል ተራሮች ላይ” እንዲያጠፋ ለይሖዋ አምላክ ምልክት እንደሚሆነው ሕዝቅኤል ይነግረናል። (ሕዝቅኤል 38:​18፤ 39:​4) ይህ ሁኔታ መልአኩ ለዳንኤል የነገረውን አንድ ነገር ያስታውሰናል:- “በዚያም ዘመን ስለ ሕዝብህ ልጆች የሚቆመው ታላቁ አለቃ ሚካኤል ይነሣል፤ ሕዝብም ከሆነ ጀምሮ እስከዚያ ዘመን ድረስ እንደ እርሱ ያለ ያልሆነ የመከራ ዘመን ይሆናል፤ በዚያም ዘመን በመጽሐፉ ተጽፎ የተገኘው ሕዝብህ ሁሉ እያንዳንዱ ይድናል።” — ዳንኤል 12:​1

23 በ1914 ኢየሱስ ማለትም ሰማያዊው ጦረኛ ሚካኤል በሰማያዊቱ የአምላክ መንግሥት ላይ ንጉሥ ሆኗል። (ራእይ 11:​15፤ 12:​7–9) ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ‘ለዳንኤል ሕዝብ ልጆች’ ቆሟል። በቅርቡ ደግሞ “እግዚአብሔርን የማያውቁትን ለጌታችንም ለኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል የማይታዘዙትን” በመበቀል የማይበገር ጦረኛ ንጉሥ ሆኖ በይሖዋ ስም “ይነሣል።” (2 ተሰሎንቄ 1:​8) የምድር መንግሥታት ሁሉ በዳንኤል ትንቢት ላይ የተጠቀሱት ነገሥታትም ጭምር “ዋይ ዋይ” እያሉ ራሳቸውን ይመታሉ። (ማቴዎስ 24:​30) ‘በዳንኤል ሕዝቦች’ ላይ ያላቸውን ክፉ አሳብ በልባቸው እንደያዙ ‘በታላቁ መስፍን በሚካኤል’ እጅ ለዘላለም ይደመሰሳሉ። — ራእይ 19:​11–21

24. የዳንኤልን ትንቢት የሚመለከተው ይህ ጥናት በእኛ ላይ ምን ውጤት ሊኖረው ይገባል?

24 ይህንን የሚካኤልና የአምላኩን የይሖዋን ታላቅ ድል ለመመልከት አንጓጓምን? ያ ድል ለእውነተኛ ክርስቲያኖች “መዳን” ወይም ከጥፋት መትረፍ ማለት ይሆንላቸዋል። (ከሚልክያስ 4:​1–3 ጋር አወዳድር።) እንግዲያው የወደፊቱን ጊዜ በታላቅ ጉጉት እየተጠባበቅን “ቃሉን ስበክ፣ በደህናውም ጊዜ ይሁን በአስቸጋሪ ጊዜ በጥድፊያ ስሜት ይህን አከናውን” የሚሉትን የሐዋርያው ጳውሎስን ቃላት እናስታውስ። (2 ጢሞቴዎስ 4:​2 አዓት) ደህናው ጊዜ እያለ የይሖዋን በጎች በትጋት እየፈለግን የሕይወትን ቃል አጥብቀን እንያዝ። ለሕይወት የሚደረገው ሩጫ ሊያበቃ በተቃረበበት ጊዜ ላይ እንገኛለን። ሽልማቱ ቅርብ ነው። ሁላችንም እስከ መጨረሻ ለመጽናት ቆርጠን በመነሣት ከሚድኑት መካከል የምንሆን ያድርገን። — ማቴዎስ 24:​13፤ ዕብራውያን 12:​1

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ራእይ — ታላቁ መደምደሚያው ደርሷል የተባለውን በኒው ዮርክ የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመውን መጽሐፍ ገጽ 229–230 ተመልከት።

b ነገሩን ከሌላም አንጻር ብናየው ለጎግ ከተናገረው ቃሉ አኳያ ስንመለከተው “ከሰሜን” የሚመጣው ወሬ ከይሖዋ የመነጨ ነው ልንልም እንችላለን:- “እመልስህማለሁ በመንጋጋህም ልጓም አገባብሃለሁ . . . አወጣሃለሁ።” “እነዳህማለሁ፣ ከሰሜንም ዳርቻ እጎትትሃለሁ፣ ወደ እስራኤልም ተራሮች አመጣሃለሁ።” — ሕዝቅኤል 38:​4፤ 39:​2፤ ከመዝሙር 48:​2 ጋር አወዳድር።

ትረዳዋለህን?

◻ በፍጻሜው ዘመን ሁሉ የደቡቡ ንጉሥ የሰሜኑን ንጉሥ በየጊዜው የተጋፋው እንዴት ነው?

◻ ስለ ሁለቱ ነገሥታት ፉክክር መጨረሻ ገና ወደፊት የምናውቀው ምን ነገር ይኖራል?

◻ ከአርማጌዶን በፊት የሚከናወኑ ምን ሁለት ነገሮች የሰሜኑን ንጉሥ ይመለከታሉ?

◻ ‘ታላቁ መስፍን ሚካኤል’ የአምላክን ሕዝቦች የሚከላከልላቸው እንዴት ነው?

◻ የዳንኤልን ትንቢት ማጥናታችን እንዴት ዓይነት እርምጃ እንድንወስድ ሊያደርገን ይገባል?

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የሰሜኑ ንጉሥ ከእርሱ በፊት የነበሩት ካመለኳቸው አማልክት የተለየ አምላክ አምልኳል

[ምንጭ]

ከላይ በስተግራ እና መካከል ላይ:- UPI/Bettmann፣ ከታች በስተግራ:- Reuters/Bettmann; ከታች በስተቀኝ:- Jasmin/Gamma Liaison

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ