የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w93 12/1 ገጽ 28-31
  • የ“በጎ ስጦታ ሁሉ” ሰጭ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • የ“በጎ ስጦታ ሁሉ” ሰጭ
  • መጠበቂያ ግንብ—1993
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የአምላክ ምሳሌ
  • ስጦታ ለመስጠት የሚያነሣሱ ምክንያቶች
  • የምንካፈልባቸው መንገዶች
  • አንዳንዶች ለመንግሥቱ ስብከት ሥራ እርዳታ የሚሰጡበት መንገድ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1994
  • “ገንዘቡ የሚገኘው ከየት ነው?”
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
  • ‘ይሖዋን ከሀብትህ አክብር’—እንዴት?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1997
  • ለይሖዋ የምንሰጠው ለምንድን ነው?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1996
ለተጨማሪ መረጃ
መጠበቂያ ግንብ—1993
w93 12/1 ገጽ 28-31

የ“በጎ ስጦታ ሁሉ” ሰጭ

“በአንድ ወቅት የሪፎርምድ ቤተ ክርስቲያን አገልጋይ የሆነ አንድ ሰው አነጋግሮኝ ነበር። ቤተ ክርስቲያኔን እንዴት እንደማስተዳድር ለማወቅ ፈልጎ ነበር። እኔም ‘ደሞዝ አንከፍልም፤ ሰዎችን እርስ በርሳቸው እንዲጣሉ የሚያደርግ ምንም ነገር የለም። ገንዘብ አንሰበስብም ’ አልኩት። ‘ታዲያ ለሥራ የሚያስፈልጋችሁን ገንዘብ ከየት ታገኛላችሁ? ’ ብሎ ጠየቀ። ‘ዶክተር — ፣ እውነቱን ብነግርህ አታምነኝም። ሰዎች ስለዚህ መንገድ የማወቅ ፍላጎት እንዳደረባቸው በአፍንጫቸው ሥር ሙዳየ ምጽዋት አይዞርላቸውም። ይሁን እንጂ ወጪዎች እንደሚኖሩ ይገነዘባሉ። ስለዚህም “ይህ አዳራሽ ገንዘብ ያስፈልገዋል . . . ታዲያ ለዚህ ወጪ መሸፈኛ የሚሆን ገንዘብ ሣጥን ውስጥ መጨመር እችኢየሱስ ላለሁን? ” ’ ብለው ያስባሉ። ‘ሞኝ መሰልኩህ እንዴ? ’ የሚል በሚመስል አስተያየት ትኩር ብሎ ተመለከተኝ። እኔም ‘አየህ ዶክተር — ግልጽ የሆነውን እውነት ነው የነገርኩህ። . . . አንድ ሰው ከተባረከና የሚሰጠው ነገር ካገኘ ይህን ንብረቱን ለጌታ አገልግሎት ሊጠቀምበት ይፈልጋል። ምንም ነገር ከሌለው ግን አምጣ ብለን ለምን እንጎተጉተዋለን? ’ አልኩት። ”

— ቻርልስ ቲ ራስል፣ የመጀመሪያው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ፕሬዘዳንት፤ የእንግሊዝኛ “መጠበቂያ ግንብ ” ሐምሌ 15, 1915

የምንሰጠው የመጀመሪያው ሰጭ ይሖዋ አምላክ ስለሆነ ነው። እሱ መስጠት የጀመረው ቁጥር ስፍር ከሌለው ዘመን በፊት “አንድያ ልጁን” በመፍጠር የፍጥረት ሥራውን በጀመረ ጊዜ ነበር። (ዮሐንስ 3:​16) በፍቅር ተነሣስቶ ለሌሎች የሕይወትን ስጦታ ሰጣቸው።

ይሖዋ ለእኛ ከሰጣቸው ስጦታዎች ሁሉ የሚበልጠው ስጦታ የአምላክ ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ነገር ግን የአምላክ ልጅ ራሱ የመጨረሻው የአምላክ ስጦታ አልሆነም። ሐዋርያው ጳውሎስ ‘በቃላት ሊገለጽ የማይችለውን የአምላክ ነፃ ስጦታ’ ‘የሚበልጠው የአምላክ ጸጋ’ በማለት ጠርቶታል። (2 ቆሮንቶስ 9:​14, 15) ይህ የጸጋ ስጦታ አምላክ በኢየሱስ በኩል ለሕዝቦቹ የዘረጋውን ጥሩነትና ፍቅራዊ ደግነት እንደሚያጠቃልል ግልጽ ነው። ይህን የመሰለው የማይገባ ደግነት የሰው አንደበት በቃላት ሊገልጸው ወይም ሊያስረዳው የማይችል እጅግ አስደናቂ ነገር ነው። ሆኖም የአምላክ ስጦታ በዚህ ብቻ የተወሰነ አይደለም።

ከረጅም ጊዜ በፊት አንድ ንጉሥ ጥበብና ትሕትና በሞላበት መንገድ ምንም ዓይነት ውድ ስጦታ ቢሰጥ ከይሖዋ ያገኘውን መልሶ እንደሚሰጥ አምኗል። እንዲህም አለ:- “በሰማይና በምድር ያለው ሁሉ የአንተ ነውና . . . አቤቱ፣ መንግሥት የአንተ ነው፣ አንተም በሁሉ ላይ ከፍ ከፍ ያልህ ራስ ነህ። . . . ሁሉ ከአንተ ዘንድ ነውና፣ ከእጅህም የተቀበልነውን ሰጥተንሃልና ይህን ያህል ችለን ልናቀርብልህ እኔ ማን ነኝ? ሕዝቤስ ማን ነው?” — 1 ዜና መዋዕል 29:​11–14

የአምላክ ምሳሌ

የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዝሙር የነበረው ያዕቆብ ይሖዋ አምላክ በሁሉም ረገድ መልካም ለሆነ ለማንኛውም ነገር ምንጭ እንደሆነ አውቆ ነበር። ከእርሱ የሚገኙት ሁሉ ፍጹም ስጦታዎች ናቸው። ያዕቆብ “መልካም ስጦታና ፍጹም በረከት ሁሉ ከእግዚአብሔር ነው፤ ይህም የሚመጣው እንደ ጥላ መዘዋወር ወይም መለዋወጥ ከሌለበት የብርሃን ሁሉ አባት ከሆነው ከእግዚአብሔር ነው” በማለት ጽፏል። — ያዕቆብ 1:​17 የ1980 ትርጉም

ስጦታ በመስጠት ረገድ አምላክ ከሰው በጣም የተለየ መሆኑን ያዕቆብ ተገንዝቧል። ሰዎች ጥሩ ስጦታዎችን ሊሰጡ ቢችሉም የሚሰጡት ሁልጊዜ አይደለም። በተጨማሪም ስጦታ የሚሰጡት የስስት ፍላጎት ኖሯቸው ወይም አንድን ሰው መጥፎ ነገር እንዲሠራ ለማድረግ ሊሆን ይችላል። ይሖዋ ግን የመለዋወጥ ባሕርይ የለበትም። ከዚህም የተነሣ ስጦታዎቹ አይለዋወጡም። ሁልጊዜ ንጹሕ ናቸው። ምንጊዜም የሰውን ልጅ ደኅንነትና ደስታ የሚያራምዱ ናቸው። ደግነት የሞላባቸውና ጠቃሚ ናቸው እንጂ ጎጂዎች አይደሉም።

ስጦታ ለመስጠት የሚያነሣሱ ምክንያቶች

በያዕቆብ ዘመን እውቅ የሆኑ የሃይማኖት መሪዎች ስጦታ ይሰጡ የነበረው በሰዎች ዘንድ ለመታየት ብለው ነበር። ለመስጠት የሚነሣሱበት ምክንያት መጥፎ ነበር። የሰዎችን አድናቆት ለማትረፍ አጥብቀው ሲፈልጉ የጽድቅ ሕግጋትን ተላልፈዋል። ክርስቲያኖች ግን ከእነዚህ የተለዩ መሆን ነበረባቸው። ኢየሱስ እንዲህ በማለት መክሯቸዋል:- “እንግዲህ ምጽዋት ስታደርግ፣ ግብዞች በሰው ዘንድ ሊከበሩ በምኵራብ በመንገድም እንደሚያደርጉ በፊትህ መለከት አታስነፋ፤ እውነት እላችኋለሁ፣ ዋጋቸውን ተቀብለዋል። አንተ ግን ምጽዋት ስታደርግ ምጽዋትህ በስውር እንዲሆን ቀኝህ የምትሠራውን ግራህ አትወቅ፤ በስውር የሚያይ አባትህም በግልጥ ይከፍልሃል።” — ማቴዎስ 6:​2–4

አንድ ክርስቲያን ስጦታ የሚሰጥበት ምክንያት ሌሎች ችግራቸውን እንዲወጡበት ወይም ደስ እንዲላቸው ለማድረግ ወይም እውነተኛ አምልኮን ለማስፋፋት በማሰብ ነው እንጂ ለመመስገን ብሎ አይደለም። የይሖዋ ዓይኖች በልባችን ውስጥ የተደበቀውን እንኳ ጠልቀው ለማየት የሚችሉ ናቸው። የምሕረት ስጦታ እንድንሰጥ ያነሣሳንን ውስጣዊ ዝንባሌ ለመመልከት ይችላል።

የይሖዋ ምስክሮች ስጦታ በመስጠት ረገድ የይሖዋንና የልጁን ምሳሌ ለመከተል ይፈልጋሉ። ካላቸው ንብረት ከፍለው ይሰጣሉ። ከንብረታቸው አንዱ የመንግሥቱ ምሥራች ነው። ይህንንም ሌሎች እንዲባረኩበት ይሰጣሉ። ምሳሌ 3:​9 “እግዚአብሔርን ከሀብትህ አክብር፣ ከፍሬህም ሁሉ በኩራት” ብሎ እንደሚናገር ያውቃሉ። እያንዳንዱ ቅርንጫፍ ቢሮ፣ ጉባኤና ግለሰብ ለሌሎች ደኅንነት የበኩሉን አስተዋጽኦ ለማድረግ ከልብ ስለሚጥር ጠቅላላው የወንድማማች ማኅበር በመንፈሳዊ ጠንካራና የበለጸገ ለመሆን ችሏል። ቁሳዊ ብልጽግና መንፈሳዊ ብልጽግና አያስገኝም። መንፈሳዊ ብልጽግና ግን ለይሖዋ ሥራ የሚያስፈልገውን ቁሳዊ ብልጽግና ያስገኛል።

የምንካፈልባቸው መንገዶች

እያንዳንዱ ሰው በግሉ ምሥራቹን ለመደገፍ አስተዋጽኦ ማድረግ የሚችልባቸው ብዙ መንገዶች አሉ። አስተዋጽኦ ከሚደረግባቸው መንገዶች አንዱ የመንግሥት አዳራሾችን ይመለከታል። የጉባኤው አባሎች በሙሉ በመንግሥት አዳራሹ ይጠቀማሉ። ለሕንፃው ማሠሪያ፣ ወይም መከራያ፣ ለመብራትና ለጥገና ገንዘብ ወጥቷል። እያንዳንዱ አባል በዚህ ረገድ ጉባኤውን መደገፉ አስፈላጊ ስለሆነ በመንግሥት አዳራሹ ውስጥ የመዋጮ ሣጥኖች ይቀመጡና በፈቃደኝነት የተለገሰው ገንዘብ የጉባኤውን ወጪዎች ለመሸፈን ያገለግላል። ከዚህ የሚተርፈው ገንዘብ ጉባኤው በወሰነው መሠረት ለአካባቢው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ቅርንጫፍ ቢሮ ይላካል።

ማኅበሩ ለሥልጠናና የምሥራቹ ለአብዛኛው ሕዝብ ባልተዳረሰባቸው የዓለም ክፍሎች ሄደው የሚያገለግሉትን ሚስዮናውያንና ልዩ አቅኚዎች ለመደገፍ እንዲጠቀምበት ለማኅበሩ ቅርንጫፍ ቢሮ በቀጥታ መዋጮ መላክ ይቻላል። ምሥራቹን ለማስፋፋት በሚደረገው ሥራ የሚወጡት ሌሎች ወጪዎች ከተጓዥ የበላይ ተመልካቾች ሥራ ጋር የተያያዘ ነው። በመጀመሪያው መቶ ዘመን ለተጓዥ የበላይ ተመልካችነት ሥራ ጥሩ ምሳሌ የተወው ሐዋርያው ጳውሎስ የፊልጵስዩስን ጉባኤ “አንድ ጊዜና ሁለት ጊዜ ያስፈለገኝን ሰዳችሁልኝ ነበርና” በማለት አመስግኗቸዋል። (ፊልጵስዩስ 4:​14–16) እነዚህ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ገጽታዎች ከሚጠይቁት የሁሉም ቅርንጫፍ ቢሮዎች ወጪ በተጨማሪ ለእያንዳንዱ የቤቴል መኖሪያ ቤትና በዚያ ለሚኖሩና ለሚሠሩ የሚያስፈልግ ወጪ አለ። ያማረውን የምሥራቹን መልእክት ይዘው የሚወጡትን ጽሑፎች መጻፍና ማተም ከአምላክ የተሰጠ መብት ነው። ቢሆንም እነዚህን ጽሑፎች ማሰራጨት አስፈላጊ ከመሆኑም በላይ በርካታ ወጪ የሚጠይቅ ነው። በተጨማሪም የክልልና የወረዳ ስብሰባዎችን የሚመለከት ወጪ አለ። ይህም ‘ምሥራቹን በሕግ ለመከላከልና እንዲቋቋም ለማድረግ’ የተደረጉት የፍርድ ቤት ሙግቶች የጠየቁትን ወጪ ሳንጠቅስ ነው። — ፊልጵስዩስ 1:​7

እያንዳንዱ የይሖዋ አገልጋይ ምሥራቹን ለመስበክ የሚያጠፋው ሰዓትም ሆነ በቁሳዊ መንገድ የሚያደርገው ስጦታ በበጎ ፈቃድ የሚሰጥ ነው። የእውነተኛን አምልኮ መስፋፋት ለመደገፍ ቋሚ የሆነ ገንዘብ መመደብ እንደሚያስፈልግ ሐዋርያው ጳውሎስ የሰጠው ምክር አለ። “ለቅዱሳን ገንዘብ ስለ ማዋጣት፣ . . . ከእናንተ እያንዳንዱ በየሳምንቱ በፊተኛው ቀን እንደ ቀናው መጠን እያስቀረ በቤቱ ያስቀምጥ” ብሏል። — 1 ቆሮንቶስ 16:​1, 2

አንድ ሰው መዋጮ ሲያደርግ የሰጠው ገንዘብ በምን መንገድ ሥራ ላይ እንደሚውል ላያውቅ ቢችልም በመንግሥቱ ስብከት ሥራ መስፋፋት ላይ የሚያስገኘውን ውጤት ሊመለከት ይችላል። የ1993 የይሖዋ ምስክሮች የዓመት መጽሐፍ የመንግሥቱ ምሥራች ከ200 በሚበልጡ አገሮችና ደሴቶች ላይ ከ4,500,000 በላይ በሆኑ ክርስቲያን አገልጋዮች እየተሰበከ መሆኑን ያሳያል። እነዚህ ሪፖርቶች በጣም የሚያስደስቱ ናቸው። የስጦታው መጠን ምንም ያህል ቢሆን ምሥራቹን በዓለም ዙሪያ ለማስፋፋት ይረዳል።

ይህ ሥራ የገንዘብ ድጋፍ የሚያገኘው ሁሉም የሰጡት አንድ ላይ ተዳምሮ ነው። አንዳንዶች ብዙ ለመስጠት ይችላሉ፤ ይህም የስብከቱን ሥራ በከፍተኛ ደረጃ ያግዘዋል። ሌሎች ደግሞ ጥቂት ይሰጣሉ። አነስተኛ መዋጮ የሚያደርጉ ሊያፍሩ ወይም የነሱ መዋጮ ምንም ቁም ነገር እንደማይሠራ ሆኖ ሊሰማቸው አይገባም። ይሖዋ እንደዚህ እንደማይሰማው እርግጠኛ ነገር ነው። ይህንንም ኢየሱስ ሲያረጋግጥ ይሖዋ የመበለቲቱን የነሐስ ሳንቲሞች ምን ያህል እንደሚያደንቅ ተናግሯል። “አንዲትም ድሀ መበለት ሁለት ሳንቲም በዚያ ስትጥል አየና:- እውነት እላችኋለሁ፣ ይህች ድሀ መበለት ከሁሉ ይልቅ አብልጣ ጣለች፤ እነዚህ ሁሉ ከትርፋቸው ወደ እግዚአብሔር መዝገብ ጥለዋልና፤ ይህች ግን ከጉድለትዋ የነበራትን ትዳርዋን ሁሉ ጣለች።” — ሉቃስ 21:​2–4

የገንዘብ አቅማችን ምንም ያህል ቢሆን ይሖዋን ደስ የሚያሰኝ ስጦታ ለማቅረብ እንችላለን። መዝሙራዊው ለንጉሣችንና ለፈራጃችን እንዴት ክብር ልንሰጥ እንደምንችል ጥሩ አድርጎ ገልጿል። እንዲህም አለ:- “ለስሙ የሚገባ ክብርን ለእግዚአብሔር አምጡ፤ ቁርባን [ስጦታ አዓት] ያዙ ወደ አደባባዮችም ግቡ።” (መዝሙር 96:​8) ስለዚህ ደስተኛ ሰጪዎች በመሆን የሰማያዊ አባታችንን ፍቅራዊ ምሳሌ እንከተል። በመጀመሪያ የሰጠን እርሱ ነውና።

[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

አንዳንዶች ለዓለም አቀፉ የስብከት ሥራ እርዳታ የሚሰጡበት መንገድ

◻ ለዓለም አቀፉ የስብከት ሥራ የሚደረግ መዋጮ:- ብዙዎች “ለማኅበሩ ዓለም አቀፍ ሥራ የሚደረግ መዋጮ — ማቴዎስ 24:​14” ተብሎ የተለጠፈባቸው ሣጥኖች ውስጥ የሚያስገቡትን የተወሰነ የገንዘብ መጠን ይመድባሉ ወይም ወጪ ያደርጋሉ። ጉባኤዎች ይህን ገንዘብ በየወሩ በብሩክሊን ኒው ዮርክ ወዳለው ዋና መሥሪያ ቤት ወይም በአቅራቢያቸው ወደሚገኝ ቅርንጫፍ ቢሮ ይልካሉ።

◻ ስጦታዎች:- በፈቃደኛነት የሚደረጉ የገንዘብ እርዳታዎች በቀጥታ Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania, 25 Columbia Hieghts, Brooklyn, New York 11201 በሚለው አድራሻ ወይም በአቅራቢያው ወደሚገኝ የማኅበሩ ቅርንጫፍ ቢሮ ሊላክ ይችላል። ጌጣጌጦች ወይም ሌሎች ውድ ዕቃዎችም በእርዳታ ሊሰጡ ይችላሉ። የተላከው ነገር ስጦታ መሆኑን የሚገልጽ አጭር ደብዳቤም አብሮ መላክ ይኖርበታል።

◻ ተመላሽ ሊሆን የሚችል ገንዘብ ለመስጠት የሚያስችል ዝግጅት:- አንድ ሰው ለመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የሰጠውን ገንዘብ ሊጠቀምበት በሚፈልግበት ጊዜ ሊመለስለት የሚያስችል ዝግጅት በማድረግ እስኪሞት ድረስ ማኅበሩ በአደራ መልክ እንዲይዘው ሊሰጥ ይችላል።

◻ ኢንሹራንስ:- የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የአንድ የሕይወት ዋስትና ኢንሹራንስ ፖሊሲ ወይም የጡረታ ክፍያ ተጠቃሚ እንዲሆን ስም ሊዛወርለት ይችላል። እንዲህ ዓይነት ዝግጅት ሲደረግ ለማኅበሩ ማስታወቅ ይገባል።

◻ የባንክ ሒሳብ:- የባንክ ሒሳቦች፣ ገንዘብ መቀመጡን የሚገልጽ የምስክር ወረቀት ወይም ተናጠል የሆኑ የጡረታ ሒሳቦች የአካባቢው ባንክ በሚፈቅደው መሠረት በአደራ ወይም በሞት ጊዜ የሚከፈል መሆኑ ተገልጾ ለመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ሊሰጥ ይችላል። ማንኛውም እንዲህ ዓይነቱ ዝግጅት መደረጉን ለማኅበሩ ማስታወቅ ይገባል።

◻ አክሲዮኖችና ቦንዶች:- አክሲዮኖችና ቦንዶች በይፋ ስጦታነትም ሆነ ወይም ገቢው ለሰጩ በተከታታይ እንዲመለስለት ዝግጅት ተደርጎ ለመጠበቂያ ግንብ ማኅበር በእርዳታ ሊሰጥ ይችላል።

◻ የማይንቀሳቀሱ ንብረቶች:- ሊሸጡ የሚችሉ የማይንቀሳቀሱ ንብረቶች በይፋ ስጦታነት ወይም ሰጪው በሕይወት እስካለ ድረስ በንብረቱ በመተዳደር እንዲቀጥል መብቱን በማስጠበቅ ለማኅበሩ በእርዳታ ሊሰጥ ይችላል። አንድ ሰው ማንኛውንም የማይንቀሳቀስ ንብረት ለማኅበሩ ከማስተላለፉ አስቀድሞ ከማኅበሩ ጋር መገናኘት ይኖርበታል።

◻ ኑዛዜዎችና አደራዎች:- ለፔንሲልቫንያው የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር ንብረት ወይም ገንዘብ በሕግ ፊት ተፈጻሚነት ባለው ኑዛዜ አማካኝነት በውርሻ ሊሰጥ ወይም ማኅበሩ በአደራ የተሰጠው ንብረት ተጠቃሚ እንደሆነ ስም ሊተላለፍለት ይችላል። አንድ የሃይማኖት ድርጅት እንዲጠቀምበት በአደራ የተሰጠ ንብረት በቀረጥ ረገድ አንዳንድ ጥቅሞች አሉት። የኑዛዜው ወይም ንብረት በአደራ የተሰጠበት ስምምነት ቅጂ ለማኅበሩ ሊላክ ይገባል።

እንዲህ ዓይነት ጉዳዮችን በተመለከተ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት Treasurer’s Office, Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania, 25 Columbia Heights, Brooklyn, New York 11201 በሚለው አድራሻ ወይም በአቅራቢያው ለሚገኝ የማኅበሩ ቅርንጫፍ ቢሮ መጻፍ ይቻላል።

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የምትሰጠው እርዳታ ሥራ ላይ የሚውልባቸው መንገዶች:-

1. ለቤቴል ፈቃደኛ ሠራተኞች

2. ለቅርንጫፍ ቢሮ ግንባታ

3. በተፈጥሮ አደጋዎች የተጎዱትን ለመርዳት

4. ለመንግሥት አዳራሾች

5. ለሚስዮናውያን

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ