ጦርነቶች ሊቀሩ የማይችሉ ናቸውን?
ጦርነት አስከፊ ነው። ደግሞም የየዕለቱ ዜና ዋና ክፍል ነው ለማለት ይቻላል። ስለ ጭካኔ የሚያወሩ መጽሔቶች እንደሚያሸብሩህ አያጠራጥርም። ምናልባትም የብዙ አለመግባባቶች መፍትሔ የግድ የጦር መሣሪያ የሆነበት ምክንያት ምንድን ነው? ብለህ እንድታስብ አድርገውህ ሊሆን ይችላል። ሰዎች በሰላም መኖርን ፈጽሞ አይማሩም ማለት ነው?
ለኤድስ መድኃኒት ከማግኘት ይልቅ ለጦርነት መቅሰፍት መፍትሔ ማስገኘት ሕልም መስሎ ይታያል። በ20ኛው መቶ ዘመን በተለያዩ አገሮች መላው ሕዝብ ለጦርነት እንዲንቀሳቀስ ተደርጓል። በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ለጦርነት ተማግደዋል፤ በመቶዎች የሚቆጠሩ ከተሞችም ወድመዋል። እልቂቱ ማቆሚያ ያለው አይመስልም። ከፍተኛ ትርፍ የሚያስገኘው ዓለም አቀፍ የጦር መሣሪያዎች ንግድ በዓለም ያሉ የጦር ሠራዊቶችና ሽምቅ ተዋጊዎች በጭካኔ መዋጋታቸውን የሚቀጥሉ ለመሆናቸው ማረጋገጫ ነው።
የጦር መሣሪያዎች በይበልጥ አጥፊ እየሆኑ ሲመጡ በውጊያ ላይ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥርም በጣም ጨምሯል። በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በውጊያው ከተሳተፉት 65 ሚልዮን ወታደሮች ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ተገድለዋል ወይም ቆስለዋል። ከዚያ 30 ዓመታት ያህል ቆይቶ ሁለት የአቶም ቦምቦች ብቻ ከ150,000 በላይ የሚሆኑ የጃፓንን ሰላማዊ ነዋሪዎች ሕይወት አጥፍተዋል። ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ አብዛኞቹ ግጭቶች በአገሮች መካከል ብቻ የተወሰኑ ሆነዋል። ያም ሆኖ ግን ጦርነቶቹ በተለይ ሰላማዊ ነዋሪዎችን የሚገድሉ ሲሆን በውጊያ ላይ ከሚሞቱት ሰዎች ውስጥ 80 በመቶዎቹ ሰላማውያን ሰዎች ናቸው።
ነገሩ በጣም የሚያስገርም ነው፤ ምክንያቱም ይህ በጅምላ የሚደረግ ፍጅት የተከሰተው ጦርነት በብሔራት መካከል ያሉ አለመግባባቶች የሚፈቱበት መንገድ መሆኑ እንዲቀር ታይቶ የማይታወቅ ጥረት እየተደረገ ባለበት ዘመን ውስጥ ነው። በቅርቡ ቀዝቃዛው ጦርነት ባበቃበት ጊዜ አዲስና ሰላማዊ የዓለም ሥርዓት ይመጣል የሚል ከፍተኛ ተስፋ ተደርጎ ነበር። ይሁን እንጂ ዓለም አቀፉ ሰላም እንደ ወትሮው ሁሉ ሕልም ብቻ ሆኖ ቀረ። ለምን?
የሥነ ሕይወት ግዴታ ነውን?
አንዳንድ የታሪክ ምሑራንና ስለ ሰው ባሕርይ የሚያጠኑ ተመራማሪዎች ጦርነት በዝግመተ ለውጥ ሂደት ውስጥ ያሸነፈ እንዲኖር የሚያደርገው ትግል አንዱ ክፍል ስለሆነ ሊቀር የማይችል እንዲያውም የግድ የሚያስፈልግ ነገር ነው ባዮች ናቸው። በእንዲህ ዓይነቱ አስተሳሰብ በመመራት የወታደራዊ ጉዳዮች ተንታኝ የሆኑት ፍሬደሪክ ቮን ቤርንሃርዲ ጦርነት የሚነሳው “የሥነ ሕይወት፣ የማኅበረሰባዊና የሥነ ምግባር ዕድገት የሚፈልገው ነገር ስለሆነ ነው” ሲሉ በ1914 ተከራክረዋል። በንድፈ ሐሳቡ መሠረት ጦርነት በሕይወት ለመቀጠል ይበልጥ ተስማሚ ሆነው የተገኙት ሲቀሩ ደካማ ግለሰቦች ወይም ብሔራት ደግሞ የሚጠፉበት መንገድ ነው።
እንዲህ ዓይነቱ የመከራከሪያ ሐሳብ በጦርነት ምክንያት ባሎቻቸው የሞቱባቸውን ሴቶችና ወላጅ አልባ የሆኑትን ልጆች አያጽናናቸውም። ይህ አስተሳሰብ በሥነ ምግባር አኳያ ዘግናኝ ከመሆኑም ሌላ የዘመናዊ ጦርነቶችን አሰቃቂ እውነታዎች ችላ የሚል ነው። ጠመንጃ በሕይወት ለመቀጠል ይበልጥ ተስማሚ የሆኑትን አይምርም፤ ቦምብም ቢሆን ደካማውንም ጠንካራውንም የሚያጠፋው አንድ ላይ ነው።
የመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ያስተማረውን አሳዛኝ ትምህርት ከምንም ባለመቁጠር አዶልፍ ሂትለር በጦርነት አሸንፎ ከሁሉ የላቀ ዘር ለመፍጠር አልሞ ነበር። ሚን ካምፕፍ (የኔ ትግል) በተሰኘው መጽሐፉ ውስጥ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “የሰው ልጅ ዘላለማዊ በሆነው ትግል ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል፤ ትግሉን ሊያጠፋው የሚችለው ዘላለማዊ ሰላም ብቻ ነው። . . . ኃይለኛው ደካማውን መግዛት አለበት፤ ከርሱ ጋር ተቀላቅሎ መኖር የለበትም።” ሆኖም ሂትለር የሰውን ዘር የጥራት ደረጃ ከፍ ከማድረግ ይልቅ በሚልዮን የሚቆጠር ሕይወት እንዲሠዋና አንድ አህጉር ሙሉ እንዲፈራርስ አድርጓል።
ጦርነት የሥነ ሕይወት ግዴታ ካልሆነ ታዲያ የሰው ልጅ ራሱን በራሱ እንዲያጠፋ የሚገፋፋው ምንድን ነው? ብሔራት ይህን “የአረመኔዎች ሥራ” እንዲሠሩ የሚገፋፏቸው ምን ዓይነት ኃይለኛ ግፊቶች ናቸው?a ሰላምን ለማምጣት የሚሞክሩ ሰዎች የሚያደርጉትን ጥረት ሁሉ የሚያሰናክሉባቸውን አንዳንድ ዋና ዋና ምክንያቶች የያዘ ዝርዝር ከዚህ ቀጥሎ ይገኛል።
የጦርነት መንስዔዎች
ብሔረተኝነት። የፖለቲካ ሰዎችና ጄነራሎች አዘውትረው የሚቀሰቅሱት ብሔረተኝነት ጦርነትን ከሚያስነሱት ዋነኛ ምክንያቶች አንዱ ነው። ብዙ ጦርነቶች የሚከፈቱት “የአገርን ጥቅም ለማስጠበቅ” ሲባል ወይም “የአገርን ክብር” ላለማስደፈር ተብሎ ነው። ትክክልም ይሁን ስህተት አገሬ የምትወስደውን እርምጃ እደግፋለሁ የሚል አስተሳሰብ እስካለ ድረስ ግልጽ ለሆነውም ወረራ ሰበብ አይጠፋም። ጠላት መሣሪያውን አንስቶ እንዳይወጋን ኃይሉን ለማዳከም የተወሰደ እርምጃ ነው ብሎ በማመካኘት ወረራ ይካሄዳል።
የጎሣ ጥላቻ። ብዙ ክልላዊ ጦርነቶች የሚጫሩት ከዚያም የሚቀጣጠሉት በዘሮች ወይም በጎሳዎች መካከል ለረጅም ጊዜ በቆዩ ጥላቻዎች ምክንያት ነው። በቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ፣ በላይቤርያና በሶማሊያ ያሉት አሳዛኝ የርስበርስ ጦርነቶች የቅርብ ምሳሌዎች ናቸው።
የኢኮኖሚና የጦር ኃይል ፉክክር። ከአንደኛው የዓለም ጦርነት በፊት በነበሩት ሰላማዊ ይመስሉ በነበሩት ዘመናት የአውሮፓ ኃያላን መንግሥታት ግዙፍ የጦር ሠራዊት በመገንባት ላይ ነበሩ። ጀርመንና ታላቋ ብሪታንያ የጦር መርከብ የመሥራት ውድድር ውስጥ ገብተው ነበር። ዕልቂት ባስከተለው ጦርነት ውስጥ የገቡት ታላላቅ አገሮች በሙሉ ቀደም ሲል በነበረው ጊዜ፣ ጦርነት ቢነሳ ኃይላቸውን እንደሚጨምርላቸውና ብዙ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እንደሚያስገኝላቸው እምነት ስለነበራቸው ለግጭት ሁኔታዎቹ ተመቻችተው ነበር።
ሃይማኖታዊ ቂም በቀል። ሃይማኖታዊ ልዩነቶች በተለይ የዘር ክፍፍል ከታከለባቸው አደገኛ ሊሆኑ ይችላሉ። በሊባኖስና በሰሜናዊ አየርላንድ የነበሩት ግጭቶች እንዲሁም በሕንድና በፓኪስታን መካከል የተደረጉት ጦርነቶች መንስዔያቸው ሃይማኖታዊ ጥላቻ ነው።
ጦርነት ቆስቋሽ የሆነ በዓይን የማይታይ ኃይል። “የዚህ ዓለም አምላክ” የሆነው ሰይጣን ዲያብሎስ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ሁኔታ እየተንቀሳቀሰ እንዳለ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ይናገራል። (2 ቆሮንቶስ 4:4) ‘ጥቂት ጊዜ’ ስለቀረውና በኃይል ስለተቆጣ የዓለምን መከራ የሚያባብሱ የተለያዩ ሁኔታዎችን፣ ጦርነቶችንም ጭምር እየቆሰቆሰ ነው።—ራእይ 12:12
እነዚህን ዋና ዋና የጦርነት መንስዔዎች ማስወገድ ቀላል አይደለም። ከ2,000 ዓመታት በፊት ፕላቶ “ጦርነት ሲጠፋ ያዩ የሞቱ ብቻ ናቸው” ብሎ ነበር። ይህ ተስፋ አስቆራጭ ግምገማው ልንቀበለው የሚገባን መራራ እውነታ ነውን? ወይስ ጦርነት የሌለበት ዓለም አንድ ቀን ይመጣ ይሆናል ብለን ተስፋ ለማድረግ የሚያስችል ምክንያት አለን?
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ጦርነትን “የአረመኔዎች ሥራ” ብሎ የገለጸው ናፖሊዮን ነበር። ትልቅ ሰው ከሆነ በኋላ አብዛኛውን ሕይወቱን በጦርነት በማሳለፍና ወደ 20 ለሚጠጉ ዓመታት የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ በመሆን ስለሠራ የጦርነትን አረመኔያዊነት ራሱ አይቶታል።
[በገጽ 2 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
ሽፋኑ: John Singer Sargent’s painting Gassed (detail), Imperial War Museum, London
[በገጽ 2 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
Instituto Municipal de Historia, Barcelona