በክፉ መናፍስት የሚያምኑ እነማን ናቸው?
የማይታዩ መናፍስት በሕይወትህ ላይ ተፅዕኖ ሊያሳድሩ እንደሚችሉ ታምናለህን? ብዙዎች ድምፃቸውን ከፍ አድርገው አናምንም በማለት ይመልሱ ይሆናል። በአምላክ መኖር ቢያምኑም ከሰው በላይ በሆነ ኃይል የሚፈጸሙ የክፋት ድርጊቶች አሉ በሚለው ሐሳብ ግን ያሾፋሉ።
በምዕራቡ ዓለም በመናፍስት አለማመን የተስፋፋው ምድር የምትገኘው በሰማይና ከምድር በታች ባለ እሳታማ ሲኦል መሐል ስለሆነ የጽንፈ ዓለም እምብርት ነች ብላ ለብዙ መቶ ዘመናት ስታስተምር በቆየችው ሕዝበ ክርስትና ምክንያት ነው። በዚህ ትምህርት መሠረት መላእክት በሰማይ በደስታና በተድላ ሲኖሩ አጋንንት ደግሞ በሲኦል ውስጥ የሚካሄዱትን ነገሮች ይቆጣጠራሉ።
በሳይንስ መስክ የተገኙት አዳዲስ ግኝቶች ሰዎች ስለ ጠፈር አቀማመጥ ያሏቸውን የተሳሳቱ አስተሳሰቦች እንዲተዉ ስላደረጓቸው በመንፈሳዊ ፍጡራን ማመንም ዘመን ያለፈበት ነገር ሆነ። ዘ ኒው ኢንሳይክሎፒድያ ብሪታኒካ እንዲህ ሲል ይገልጻል፦ “ምድር መነሻና መድረሻ በሌለው ጠፈር ውስጥ የሚገኝ የአንድ የከዋክብት ረጨት (ጋላክሲ) እጅግ በጣም አነስተኛ ክፍል የሆነች አንዲት ተራ ፕላኔት እንጂ የጽንፈ ዓለም እምብርት አለመሆኗን ከገለጸው የ16ኛው መቶ ዘመን ኮፐርኒካዊ አብዮት (ፖላንዳዊ የከዋክብት ተመራማሪ በነበረው በኮፐርኒከስ ጽንሰ ሐሳብ ላይ የተመሠረተ ነው) በኋላ ስለ መላእክትም ሆነ ስለ አጋንንት የሚገልጸው ሐሳብ ስህተት መሰለ።”
ብዙዎች የክፉ መናፍስትን መኖር የማያምኑ ቢሆንም የክፉ መናፍስትን መኖር የሚያምኑ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አሉ። በጥንት ጊዜም ይሁን በዚህ በአሁኑ ዘመን ባሉት ብዙ ሃይማኖቶች ኃጢአት የሠሩ መላእክት ትልቅ ቦታ ተሰጥቷቸዋል። እነዚህ ክፉ መላእክት የመንፈሳዊነት አጥፊዎች ከመሆንም አልፎ እንደ ጦርነት፣ ረሃብና የመሬት መንቀጥቀጥ ላሉ አደጋዎች መንስዔዎች እንዲሁም በሽታን፣ የአእምሮ መቃወስንና ሞትን የሚያስፋፉ እንደሆኑ ይታመናል።
በክርስትናና በአይሁድ ሃይማኖቶች ውስጥ ቀንደኛ ርኩስ መንፈስ በመሆን የሚታወቀው ሰይጣን ዲያብሎስ በእስላሞች ዘንድ ኢብሊስ ተብሎ ይጠራል። የጥንቶቹ ፋርሳውያን ሃይማኖት በነበረው በዞሮአስትሬይኒዝም ውስጥ አንግራ ማይንዩ በመባል ይታወቃል። በሁለተኛውና በሦስተኛው መቶ ዘመን እዘአ ተስፋፍቶ በነበረው የግኖስቲክ ሃይማኖት ደግሞ ዴሚዮርግ ይባል ነበር። ዴሚዮርግ አብዛኛው የሰው ልጅ ካለማወቅ የተነሳ የሚያመልከው ቀናተኛ የሆነ አነስተኛ አምላክ ነበር።
በምሥራቅ ሃይማኖቶች ደግሞ ዋነኛ ቦታ የተሰጠው አነስተኛ ደረጃ ላላቸው ክፉ መናፍስት ነው። ሂንዱዎች አሱራዎች (አጋንንት) ዲቫዎችን (አማልክትን) ይቀናቀናሉ ብለው ያምናሉ። ከአሱራስ ደግሞ ይበልጥ የሚፈሩት በመቃብሮች አካባቢ ተሰውረው የሚዘዋወሩት ራክቻሳዎች ናቸው።
ቡድሂስቶች አጋንንት ሰው ወደ ኒርቫና ማለትም ማንኛውም ፍላጎት ወደሚጠፋበት ሁኔታ እንዳይገባ የሚከለክሉ የየራሳቸው ስብዕና ያላቸው ኃይሎች ናቸው ብለው ያምናሉ። ከነርሱም ውስጥ ዋነኛው ፈታኝ ማራ ሲሆን ራቲ (ፍላጎት)፣ ራጋ (ተድላ) እና ታንሃ (መቁነጥነጥ) የተባሉ ሦስት ሴቶች ልጆች አሉት።
ቻይናውያን አምላኪዎች ራሳቸውን ከግዋ ወይም ከተፈጥሮ አጋንንት ለመከላከል በእሳት፣ በችቦዎችና ድምፅ በሚያሰሙ ርችቶች ይጠቀማሉ። ጃፓናውያን ሃይማኖተኞች ደግሞ ብዙ አጋንንት እንዳሉ ያምናሉ። ከነዚህም ውስጥ ሰዎችን የሚቆራኙ ቴንጉ የተባሉ አስፈሪ መናፍስት ይገኛሉ። እነዚህ መናፍስት ቄስ ካላወጣቸው በቀር የያዙትን ሰው አይለቁም።
መሃይማን በሚከተሏቸው በእስያ፣ በአፍሪካ፣ በኦሺንያና በሁለቱ አሜሪካዎች ውስጥ በሚገኙት ሃይማኖቶች መንፈሳዊ ፍጡራን እንደ ሁኔታውና እንደ ስሜታቸው ሊጠቅሙ ወይም ሊጎዱ እንደሚችሉ ይታመናል። ሰዎች ራሳቸውን ከመቅሰፍት ለመጠበቅና የመናፍስቱን በረከት ለማግኘት ሲሉ ያመልኳቸዋል።
በነዚህ ሁሉ ላይ በጣም የተስፋፋውን የአስማትና የመናፍስትነት ሥራ ስንጨምር በክፉ መናፍስት ማመን ለረዥም ጊዜ የቆየና በሰፊው የታወቀ ታሪክ እንዳለው ግልጽ ይሆናል። ሆኖም እንዲህ ዓይነት ፍጡራን አሉ ብሎ ማመኑ ምክንያታዊ ነውን? መጽሐፍ ቅዱስ ክፉ መናፍስት አሉ ይላል። ታዲያ ክፉ መናፍስት ካሉ በሰው ሕይወት ላይ ጎጂ ተፅዕኖ እንዲያሳድሩ አምላክ የፈቀደላቸው ለምንድን ነው?