የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w94 2/1 ገጽ 4-7
  • የክፋት ጠንሳሾች

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • የክፋት ጠንሳሾች
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1994
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የመጀመሪያው ዓመፀኛ
  • ሌሎችም መላእክት ዓመፁ
  • የሰው ልጅ ጠላቶች
  • የሚፈቀድላቸው እስከ መቼ ድረስ ነው?
  • በመንፈሳዊው ዓለም ውስጥ የተነሳ ዓመፅ
    የሙታን መናፍስት—ሊረዱህ ወይም ሊጎዱህ ይችላሉን? ደግሞስ በእርግጥ አሉን?
  • በመንፈሳዊው ዓለም ውስጥ ያሉ ገዥዎች
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
  • የአንባቢያን ጥያቄዎች
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2004
  • የዘላለም ሕይወት ጠላት
    በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1994
w94 2/1 ገጽ 4-7

የክፋት ጠንሳሾች

መጽሐፍ ቅዱስ አጋንንት በሰው ጉዳዮች ውስጥ ስላላቸው ሚና የሚሰጠው ማብራሪያ ክፋትን በተመለከተ ለሚነሱት መሠረታዊ ጥያቄዎች መልስ ያስገኛል። ለእነዚህ ጥያቄዎች ከሌላ ምንጭ መልስ ማግኘት አይቻልም። እስቲ ለምሳሌ ከኢንተርናሽናል ሄራልድ ትሪብዩን ላይ በቦልካን አገሮች እየተደረገ ስላለው ጦርነት የተሰጠውን መግለጫ ተመልከት፦ “[ወታደሮቹ] 20,000 የሚያክሉ እስላም ሴቶችና ልጃገረዶችን አስገድደው እንዳስነወሩ የአውሮፓ ማኅበረሰብ የላከው የመርማሪዎች ቡድን አረጋግጧል። . . . ይህም ሰዎች ተደናግጠውና ሞራላቸው ወድቆ ከትውልድ አካባቢያቸው እንዲሸሹ ለማድረግ ከወጠኑት የማስጨነቂያ ፖሊሲያቸው አንዱ ክፍል ነው።”

ታይም በተባለ መጽሔት ላይ የወጣ አንድ ጽሑፍ ስለ ሁኔታው ለማመን በሚያዳግት መንገድ ለማብራራት ሞክሯል፦ “ወጣት ወንዶች አንዳንድ ጊዜ በጦርነት ላይ ሲሰለፉ ሴቶችን አስገድደው የሚያስነውሩት ታላላቆቻቸውንና የጦር አዛዦቻቸውን ለማስደሰትና የአባትና የልጅ ያህል የተቀራረበ ተወዳጅነት ለማግኘት ሲሉ ነው። ሴት አስገድዶ ማስነወር የተሰለፉበት ጦር አስፈሪ ሆኖ እንዲታይ ጠንካራ ፍላጎት ያላቸው መሆኑን የሚያረጋግጡበት መንገድ ነው። አንድ ወጣት ከማያወላውለው የቡድኑ ዓላማ ጋር ለመስማማት ሲል አሰቃቂ ነገሮች ለማድረግ ፈቃደኛ በመሆን የራሱን ኅሊና ይክዳል። ታማኝነቱን የሚያረጋግጠው የጭካኔ ድርጊት በመፈጸም ነው።”

ይሁን እንጂ “የማያወላውለው የቡድኑ ዓለማ” ከያንዳንዱ አባል ኅሊና ይበልጥ የተበላሸ የሆነው ለምንድን ነው? ማንም ሰው በግለሰብ ደረጃ ከጎረቤቱ ጋር ተስማምቶ ለመኖር ይፈልጋል ማለት ይቻላል። ታዲያ በጦርነት ጊዜ ሰዎች ሴቶችን አስገድደው የሚያስነውሩት፣ ሌሎችን የሚያሰቃዩትና እርስ በርስ የሚጋደሉት ለምንድን ነው? ዋናው ምክንያት የአጋንንታዊ ኃይሎች ተፅዕኖ ስላለ ነው።

አጋንንት የሚጫወቱትን ሚና መረዳት አንዳንዶች “የቲኦሎጂያውያን እንቆቅልሽ” የሚሉትን ጥያቄ ለመፍታትም ያስችላል። ጥያቄው (1) አምላክ ኃይል አለው (2) አምላክ አፍቃሪ ነው እና (3) መጥፎ ነገሮች እየተፈጸሙ ነው፣ የሚሉትን ሦስት ነገሮች እንዴት ማስማማት ይቻላል የሚል ነው። አንዳንዶች ከሦስቱ ሁለቱን ማስማማት ቢቻልም ሦስቱን ግን በፍጹም ማስማማት አይቻልም የሚል አመለካከት አላቸው። የአምላክ ቃል ራሱ መልሱን ይሰጠናል፤ የሚሰጠውም መልስ የክፋት ጠንሳሾች የሆኑትን የማይታዩ መናፍስት የሚመለከት ነው።

የመጀመሪያው ዓመፀኛ

መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ራሱ መንፈስ መሆኑን ይነግረናል። (ዮሐንስ 4:24) እርሱም በሚልዮን የሚቆጠሩ ሌሎች መንፈሳዊ ፍጡራን ማለትም መላእክታዊ ልጆች ፈጠረ። የአምላክ አገልጋይ የነበረው ዳንኤል በመቶ ሚልዮን የሚቆጠሩ መላእክት በራእይ ተመልክቷል። ይሖዋ የፈጠራቸው መንፈሳዊ አካሎች በሙሉ ጻድቃንና ከፈቃዱ ጋር ተስማምተው የሚኖሩ ነበሩ።—ዳንኤል 7:10፤ ዕብራውያን 1:7

ከጊዜ በኋላ አምላክ ‘ምድርን በመሠረተ ጊዜ’ እነዚህ የአምላክ መላእክታዊ ልጆች ‘በአንድነት በመዘመር’ ‘እልል’ ብለው ነበር። (ኢዮብ 38:4–7) ይሁን እንጂ ከመካከላቸው አንዱ ለፈጣሪ የሚገባውን አምልኮ ለራሱ የመውሰድ ምኞት አደረበት። ይህ መልአክ በአምላክ ላይ ዓመፀና ራሱን ሰይጣን (ማለትም “ተቃዋሚ”) እና ዲያብሎስ (ማለትም “ስም አጥፊ”) አደረገ።—ከሕዝቅኤል 28:13–15 ጋር አወዳድር።

ሰይጣን የመጀመሪያዋን ሴት ሔዋንን ለማናገር በእባብ ተጠቀመና በገነት ውስጥ ያለውን የአንድ ዛፍ ፍሬ እንዳይበሉ አምላክ የሰጣቸውን ቀጥተኛ ትዕዛዝ እንድትጥስ አግባባት። በኋላም ባሏ ተባበራት። በዚህ መንገድ የመጀመሪያዎቹ ሰብዓዊ ባልና ሚስት በይሖዋ ላይ ካመፀው መልአክ ጋር ተባበሩ።—ዘፍጥረት 2:17፤ 3:1–6

በኤደን የተፈጸመው ነገር ታዛዥነትን በሚመለከት የማያሻማ ትምህርት የሚሰጥ ሊመስል ቢችልም ሰይጣን ሁለት አከራካሪ የሞራል ጥያቄዎች አስነስቶ ነበር። ሰይጣን በመጀመሪያ ይሖዋ ፍጥረታቱን የሚገዛው በጽድቅና እነሱን በሚጠቅም መንገድ ስለ መሆኑ ክርክር አስነሳ። ምናልባት ሰዎች ራሳቸውን ቢያስተዳድሩ ይበጃቸዋል አለ። ሰይጣን የማሰብ ችሎታ ያለው ማንኛውም ፍጡር ቁሳዊ ጥቅሞች ባያገኝ ኖሮ ለአምላክ ታማኝ ሆኖ ከእርሱ ጎን አይቆምም ነበር የሚል ሁለተኛ ጥያቄ አስነሳ።a

በኤደን የተነሱትን አከራካሪ ጥያቄዎች በግልጽ መረዳታችንና የይሖዋን ጠባዮች ማወቃችን “ለቲኦሎጂያውያን እንቆቅልሽ” መልስ ለማግኘት ያስችለናል። ይኸውም የክፋትን መኖር ከአምላክ የኃይልና የፍቅር ባሕርያት ጋር ለማስማማት እንድንችል ይረዳናል። ይሖዋ ወሰን የለሽ ኃይል ያለውና ፍቅር ቢሆንም የጥበብና የፍትሕም አምላክ ነው። እነዚህን አራቱንም ባሕርያት የሚያሳየው በፍጹም ሚዛናዊነት ነው። ስለዚህ ማንም ሊቋቋመው የማይቻለውን ኃይሉን ሦስቱን ዓመፀኞች ወዲያውኑ ለማጥፋት አልተጠቀመበትም። ወዲያው ቢያጠፋቸው ድርጊቱ ፍትሐዊ ሊሆን ይችላል፤ ጥበብና ፍቅር ያለበት ግን አይሆንም። ከዚህም ሌላ ብዙዎች ፍቅራዊ አማራጭ ነው ብለው እንደሚያስቡት ጥፋታቸውን ይቅር ብሎ አልተወም። እንዲህ ቢያደርግ ኖሮ ጥበብም ፍትሕም የጎደለው ውሳኔ ይሆን ነበር።

ሰይጣን ያስነሳቸውን አከራካሪ ጥያቄዎች ለመፍታት ጊዜ ያስፈልግ ነበር። ሰዎች ከአምላክ ተለይተው ራሳቸውን በራሳቸው በትክክል ማስተዳደር ይችሉና አይችሉ እንደሆነ ለማረጋገጥ ጊዜ ይወስዳል። ይሖዋ ሦስቱ ዓመፀኞች ለተወሰነ ጊዜ በሕይወት እንዲኖሩ በማድረጉ ፍጥረታት በአስቸጋሪ ሁኔታዎችም ሥር እየኖሩ አምላክን በታማኝነት በማገልገል የሰይጣን ክስ ሐሰት መሆኑን የሚያረጋግጡበትን አጋጣሚ አስገኝቷል።b

ይሖዋ ለአዳምና ለሔዋን ከተከለከለው ፍሬ ቢበሉ እንደሚሞቱ በግልጽ ነግሯቸው ነበር። ሰይጣን ሔዋንን አትሞችም ብሎ ቢያሳምናትም ልክ አምላክ እንዳለው ሞቱ። ሰይጣንም የሞት ፍርድ ተፈርዶበታል። እስከዚያው ድረስ ግን የሰውን ልጆች ማሳሳቱን ቀጥሏል። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ ‘ዓለምም በሞላው በክፉው ተይዟል’ ይላል።—1 ዮሐንስ 5:19፤ ዘፍጥረት 2:16, 17፤ 3:4፤ 5:5

ሌሎችም መላእክት ዓመፁ

በኤደን ከተፈጸመው ሁኔታ ብዙም ሳይቆይ ሌሎችም መላእክት በይሖዋ ሉዓላዊነት ላይ በተደረገው ዓመፅ ተባበሩ። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ በማለት ይገልጻል፦ “እንዲህም ሆነ፤ ሰዎች በምድር ላይ መብዛት በጀመሩ ጊዜ ሴቶች ልጆች ተወለዱላቸው፤ የእግዚአብሔር ልጆችም የሰውን ሴቶች ልጆች መልካሞች እንደ ሆኑ አዩ፤ ከመረጡአቸውም ሁሉ ሚስቶችን ለራሳቸው ወሰዱ።” በሌላ አባባል እነዚህ መላእክት ‘ትክክለኛ መኖሪያቸውን [ሰማይን] ትተው’ ወደ ምድር በመምጣት የሰው አካል ለብሰው ከሴቶች ጋር ሩካቤ ሥጋ ፈጸሙ።—ዘፍጥረት 6:1, 2፤ ይሁዳ 6

በዘፍጥረት 6:4 ላይ ታሪኩ እንዲህ በማለት ይቀጥላል፦ “በነዚያም ወራት ኔፊሊም በምድር ላይ ነበሩ፤ ደግሞም ከዚያ በኋላ የእግዚአብሔር ልጆች የሰውን ሴቶች ልጆች ባገቡ ጊዜ ልጆችን ወለዱላቸው እነርሱም በዱሮ ዘመን ስማቸው የታወቀ ኃያላን ሆኑ።” ከሴቶቹ የተወለዱት የመላእክት ዲቃሎች ከተለመደው በላይ ጥንካሬ ያላቸው “ኃያላን” ሆኑ። እነርሱ የዓመፅ ሰዎች ወይም ኔፊሊም ነበሩ። ኔፊሊም የተባለው የዕብራይስጥ ቃል “ሌሎችን አንስተው የሚያፈርጡ” የሚል ትርጉም አለው።

ይህ ታሪክ በተለያዩ የጥንት ሥልጣኔዎች አፈ ታሪኮች ውስጥ ተተርኮ ይገኛል። ለምሳሌ ያህል 4,000 ዓመት ዕድሜ ያለው የባቢሎናውያን የጀግንነት ግጥም ኃያል፣ ጨካኝና አምላክ አከል የነበረው ጊልጋሜሽ የተባለ ሰው ስለፈጸመው ጀብዱ ይገልጻል። ይህ ኃያል ሰው “ዘማዊ ስለነበረ አንዲትም ልጃገረድ ለፍቅረኛዋ ድንግልናዋን ጠብቃ እንድትቆይ አያደርግም ነበር።” በግሪኮች አፈ ታሪክ ውስጥ ያለው ሌላው ምሳሌ እጅግ በጣም ኃያል የነበረው ሄርኩለስ (ወይም ሄራክለስ) ነው። አልስሜኔ ከተባለች ሴት እና ዚየስ ከተባለ አምላክ የተወለደው ሄርኩለስ በድንገት አብዶ ሚስቱንና ልጆቹን ከገደለ በኋላ ብዙ የጭካኔ ድርጊቶች ፈጽሟል። ምንም እንኳን እንዲህ ዓይነቶቹ ተረቶች ከትውልድ ወደ ትውልድ በሚተላለፉበት ጊዜ የተበረዙና የተከለሱ ቢሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ ከሚናገርላቸው ኔፊሊሞችና አባቶቻችው ከሆኑት ጋር ዝምድና አላቸው።

ምድር በዓመፅ እንድትሞላ ካደረጉት ምክንያቶች አንዱ እነዚህ ክፉ መላእክትና ኃያላን ልጆቻቸው በመሆናቸው ይሖዋ ዓለምን በታላቅ የውኃ ማጥለቅለቅ ሊያጠፋት ወሰነ። ኔፊሊሞችና ለአምላክ አክብሮት የሌላቸው ሰዎች ጠፉ። ከጥፋቱ የተረፉት ጻድቁ ኖህና ቤተሰቡ ብቻ ነበሩ።—ዘፍጥረት 6:11፤ 7:23

ክፉዎቹ መላእክት ግን አልሞቱም። ለጊዜው ለብሰውት የነበረውን ሥጋዊ አካላቸውን በመተው ወደ መንፈሳዊው ዓለም ተመለሱ። ባለ መታዘዛቸው ምክንያት ጻድቅ ከሆነው የአምላክ መላእክት ቤተሰብ ጋር እንደገና እንዲቀየጡም ሆነ በኖህ ዘመን እንዳደረጉት ዳግመኛ የሰው ሥጋ እንዲለብሱ አልተፈቀደላቸውም። አሁንም ቢሆን ‘የአጋንንት አለቃ’ በሆነው በሰይጣን ዲያብሎስ ሥልጣን ሥር በመሆን የሰው ልጆች በሚያደርጓቸው ነገሮች ላይ አፍራሽ ተፅዕኖ ያሳድራሉ።—ማቴዎስ 9:34፤ 2 ጴጥሮስ 2:4፤ ይሁዳ 6

የሰው ልጅ ጠላቶች

ሰይጣንና አጋንንቱ ምንጊዜም ቢሆን ነፍሰ ገዳዮችና ጨካኞች ናቸው። ሰይጣን በተለያዩ መንገዶች የኢዮብ ከብቶች እንዲወሰዱ አድርጓል፤ አገልጋዮቹንም ገድሏል። ቀጥሎም የኢዮብ አሥር ልጆች የነበሩበት ቤት “በዐውሎ ነፋስ” ተመትቶ እንዲፈርስ በማድረግ ገድሏቸዋል። ከዚያ በኋላ ሰይጣን “ኢዮብንም ከእግሩ ጫማ ጀምሮ እስከ አናቱ ድረስ በክፉ ቁስል መታው።”—ኢዮብ 1:7–19፤ 2:3, 7

አጋንንትም ቢሆኑ ተመሳሳይ የሆነ የክፋት ባሕርይ ያሳያሉ። በኢየሱስ ዘመን የሰዎችን ልሳን ይዘጉ ዓይናቸውንም ያጠፉ ነበር። አንድ ሰው ራሱን ከድንጋይ ጋር እንዲያጋጭ አድርገውት ነበር። አንድን ልጅ ደግሞ ‘መሬት ላይ ወድቆ እንዲንፈራፈር’ አድርገውታል።—ሉቃስ 9:42፤ ማቴዎስ 9:32, 33፤ 12:22፤ ማርቆስ 5:5

ከዓለም ዙሪያ የሚመጡ ሪፖርቶች ሰይጣንና አጋንንቱ ከምንጊዜውም ይበልጥ ጨካኞች እንደሆኑ ያሳያሉ። አንዳንድ ሰዎችን በበሽታ ያሰቃያሉ። ሌሎችን እንቅልፍ በማሳጣት ወይም የሚያስፈሩ ሕልሞችን በማሳየት ወይም በጾታ በመገናኘት ይረብሻሉ። ሌሎችን ደግሞ ያሳብዳሉ፤ እንዲሁም ሌሎችን ወይም ራሳቸውን እንዲገድሉ ያደርጋሉ።

የሚፈቀድላቸው እስከ መቼ ድረስ ነው?

ሰይጣንና አጋንንቱ እስከ ዘላለም በዚህ ሥራቸው እንዲቀጥሉ አይፈቀድላቸውም። ይሖዋ እስከ ዘመናችን ድረስ እንዲኖሩ የፈቀደላቸው ጥሩ ምክንያት ስላለው ነው፤ አሁን ግን የቀራቸው ጊዜ አጭር ነው። በዚህ መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ እንቅስቃሴያቸውን የሚገድብ አንድ ትልቅ እርምጃ ተወስዷል። የራእይ መጽሐፍ እንዲህ በማለት ይገልጻል፦ “በሰማይም ሰልፍ ሆነ፤ ሚካኤልና [ትንሣኤ ያገኘው ኢየሱስ ክርስቶስና] መላእክቱ ዘንዶውን [ሰይጣንን] ተዋጉ። ዘንዶውም ከመላእክቱ ጋር ተዋጋ አልቻላቸውምም፣ ከዚያም ወዲያ በሰማይ ስፍራ አልተገኘላቸውም። ዓለሙንም ሁሉ የሚያስተው፣ ዲያብሎስና ሰይጣን የሚባለው ታላቁ ዘንዶ እርሱም የቀደመው እባብ ተጣለ፤ ወደ ምድር ተጣለ መላእክቱም ከእርሱ ጋር ተጣሉ።”—ራእይ 12:7–9

ውጤቱስ ምን ሆነ? ዘገባው እንዲህ በማለት ይቀጥላል፦ “ስለዚህ፣ ሰማይና በውስጡ የምታድሩ ሆይ፣ ደስ ይበላችሁ።” ጻድቅ የሆኑት መላእክት ሰይጣንና አጋንንቱ ከዚያ በኋላ በሰማይ ስለማይኖሩ ሊደሰቱ ችለዋል። በምድር ያሉ ሰዎችስ? መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ለምድርና ለባሕር ወዮላቸው፣ ዲያብሎስ ጥቂት ዘመን እንዳለው አውቆ በታላቅ ቁጣ ወደ እናንተ ወርዶአልና።”—ራእይ 12:12

ሰይጣንና በሥሩ የሚተዳደሩት መላእክት የማይቀረው ጥፋታቸው ከመምጣቱ በፊት የሚችሉትን ያህል ወዮታ ለማምጣት ቆርጠዋል። በዚህ መቶ ዘመን ሁለት የዓለም ጦርነቶችና ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ከ150 በላይ የሚሆኑ አነስተኛ ጦርነቶች ተደርገዋል። “የጀርም ጦርነት (ጀርም ዎር ፌር)፣” “እልቂት (ዘ ሆሎከስት)፣” “የግድያ ሜዳ (ኪሊንግ ፊልድስ)፣” “ሴቶች ተገድደው በጾታ የሚደፈሩባቸው ካምፖች (ሬፕ ካምፕስ)፣” “አከታትሎ ገዳዮች (ሲሪያል ኪለርስ)፣” እንዲሁም “ቦምብ” የሚሉትን የመሳሳሉ የዚህን ትውልድ ጭካኔ የሚያንጸባርቁ ሐረጎች በመነጋገሪያ ቃላታችን ውስጥ ተጨምረዋል። ዜና ስለ ዕፅ፣ ስለ ግድያ፣ በቦምብ ስለመደብደብ፣ የአእምሮ ሕመም ያለባቸው ሰዎች የሰውን ሥጋ ስለመብላታቸው፣ ስለ እልቂት፣ ስለ ረሀብና ስለ ሥቃይ በሚናገሩ ወሬዎች የተሞላ ነው።

እነዚህ ነገሮች ጊዜያዊ መሆናቸውን ማወቅ በጣም ያስደስታል። በቅርቡ አምላክ በሰይጣንና በአጋንንቱ ላይ እንደገና እርምጃ ይወስዳል። ሐዋርያው ዮሐንስ ከአምላክ ስለመጣለት ራእይ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “የጥልቁንም መክፈቻና ታላቁን ሰንሰለት በእጁ የያዘ መልአክ ከሰማይ ሲወርድ አየሁ። የቀደመውንም እባብ ዘንዶውን እርሱም ዲያብሎስና ሰይጣን የተባለውን ያዘው፣ ሺህ ዓመትም አሰረው፣ ወደ ጥልቅም ጣለው አሕዛብንም ወደ ፊት እንዳያስት ሺህ ዓመት እስኪፈጸም ድረስ በእርሱ ላይ ዘግቶ ማኅተም አደረገበት።”—ራእይ 20:1–3

ከዚያ በኋላ ሰይጣንና አጋንንቱ ‘ለጥቂት ጊዜ ይፈታሉ፤’ ከዚያም ለዘላለም ይደመሰሳሉ። (ራእይ 20:3, 10) ያ ጊዜ እንዴት ያለ አስደሳች ጊዜ ይሆናል! ሰይጣንና አጋንንቱ ለዘላለሙ ይጠፋሉ። ይሖዋ ‘ለሁሉም ሁሉንም ነገር ይሆናል።’ በተጨማሪም ሁሉም ‘በብዙ ሰላም ደስ ይላቸዋል።’—1 ቆሮንቶስ 15:28 አዓት፤ መዝሙር 37:11

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ይህም ከጊዜ በኋላ ሰይጣን የአምላክ አገልጋይ የነበረውን ኢዮብን በተመለከተ “ቁርበት ስለ ቁርበት ነው፤ ሰው ያለውን ሁሉ ስለ ሕይወቱ ይሰጣል። ነገር ግን አሁን እጅህን ዘርግተህ አጥንቱንና ሥጋውን ዳብስ በእውነት በፊትህ ይሰድብሃል” ባለ ጊዜ ግልጽ ሆኗል።—ኢዮብ 2:4, 5

b አምላክ ክፋትን ስለፈቀደበት ምክንያት ዝርዝር ማብራሪያ ለማግኘት በኒው ዮርኩ የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመውን በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ የተባለውን መጽሐፍ ተመልከት።

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ለእንደነዚህ ዓይነቶቹ ነገሮች ተጠያቂው ሰው ብቻ ነው ወይስ አንድ የማይታይ ክፉ ኃይልም በነገሩ ተወቃሽ ነው?

[ምንጭ]

Oil wells burning in Kuwait, 1991: Chamussy/Sipa press

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አጋንንት የሰውን ልጅ ማወካቸውን ሲያቆሙ እንዴት ደስ የሚል ጊዜ ይሆናል!

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ