በመንፈሳዊው ዓለም ውስጥ ያሉ ገዥዎች
ዓለምን የሚገዛው ማን ነው? የሰውን ልጆች በበላይነት የሚቆጣጠር አካል ይኖር ይሆን? ወይስ አምላክ የሰው ልጆች ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ ትቷቸዋል? ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት እስቲ በኢየሱስ ክርስቶስ ምድራዊ አገልግሎት ወቅት ስለ ተከሰቱ ሁኔታዎች በመጀመሪያ እንመርምር።
ኢየሱስ ተጠምቆ ብዙም ሳይቆይ ሰይጣን ዲያብሎስ በሚባል በዓይን በማይታይ በአንድ መንፈሳዊ ፍጡር ተፈተነ። መጽሐፍ ቅዱስ ከፈተናዎቹ መካከል አንዱን ሲጠቅስ “ደግሞ ዲያብሎስ እጅግ ረጅም ወደ ሆነ ተራራ [ኢየሱስን] ወሰደው፣ የዓለምንም መንግሥታት ሁሉ ክብራቸውንም” አሳየው በማለት ይናገራል። (ማቴዎስ 4:8) ከዚያም ሰይጣን “ይህ ሥልጣን ሁሉ ክብራቸውም ለእኔ ተሰጥቶአል ለምወደውም ለማንም እሰጠዋለሁና ለአንተ እሰጥሃለሁ፤ ስለዚህ አንተ በእኔ ፊት ብትሰግድ፣ ሁሉ ለአንተ ይሆናል አለው።”—ሉቃስ 4:6, 7
ሰይጣን በዚህ ዓለም በሚገኙ መንግሥታት ወይም መስተዳድሮች ላይ በሙሉ ሥልጣን እንዳለው ተናግሯል። ኢየሱስ ይህንን አባባል አስተባብሏልን? አላስተባበለም። እንዲያውም ኢየሱስ በሌላ ወቅት ሰይጣን “የዚህ ዓለም ገዥ” መሆኑን በመግለጽ ይህንን አባባል አጠናክሮታል።—ዮሐንስ 14:30
በመጽሐፍ ቅዱስ አገላለጽ መሠረት ሰይጣን ትልቅ ኃይል ያለው ክፉ መልአክ ነው። ክርስቲያኑ ሐዋርያ ጳውሎስ ሰይጣንን “ከክፋት መንፈሳውያን ሠራዊት” ጋር ከማዛመዱም በላይ እነዚህ ክፉ መንፈሳውያን ሠራዊት የዚህ የጨለማ ዓለም ገዥዎች መሆናቸውን ተናግሯል። (ኤፌሶን 6:11, 12) ከዚህም በላይ ሐዋርያው ዮሐንስ “ዓለምም በሞላው በክፉው” ተይዟል በማለት ገልጿል። (1 ዮሐንስ 5:19) የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የራእይ መጽሐፍ ሰይጣንን “ዓለሙንም ሁሉ የሚያስተው” በማለት ይገልጸዋል። (ራእይ 12:9) በተጨማሪም የራእይ መጽሐፍ ሰይጣንን በዘንዶ በመመሰል በዓለም ላይ ለሚገኘው የፖለቲካ ሥርዓት “ኃይሉንና ዙፋኑን ትልቅም ሥልጣን” እንደሰጠው በምሳሌ ገልጾታል።—ራእይ 13:2
በተጨማሪም የሰው ልጆችን ለመጉዳት እየተንቀሳቀሰ ያለ አንድ ክፉ ኃይል እንዳለ በዓለም ላይ እየተከሰቱ ያሉት ሁኔታዎች ያረጋግጣሉ። ሰብዓዊ መስተዳድሮች ሰላም ማስፈን ያቃታቸው በሌላ በምን ምክንያት ነው? ሰዎች እርስ በእርሳቸው እንዲጠላሉና እንዲተራረዱ የሚያነሳሳቸው ማን ሊሆን ይችላል? በእርስ በርስ ጦርነት በደረሰው እልቂትና ሞት ያዘኑ አንዲት የዓይን ምሥክር “ይህ አሠቃቂ ግፍ እንዴት ሊደርስ እንደቻለ አላውቅም። ይህ እንዲሁ ጥላቻ ብቻ አይደለም። እነዚህ ሰብዓዊ ፍጡራን እንዲጠፋፉ እየተጠቀመባቸው ያለው አንድ ክፉ መንፈስ ነው።”
አንድ ሕያው ፍጡር አምላክን ተቃወመ
ዛሬ ብዙ ሰዎች ሰይጣን ዲያብሎስ መኖሩን አያምኑም። ይሁን እንጂ አንዳንዶች እንደሚያምኑት እርሱ በሰው ዘር ውስጥ ተንሰራፍቶ የሚኖር ክፋት አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስም ሆነ የዓለም ሁኔታዎች እርሱ እውን አካል እንደሆነ ያሳያሉ። ከዚህም በላይ ሰይጣን ይሖዋ አምላክን በጽኑ የሚቃወም ነው። እርግጥ ነው ሰይጣን ከአምላክ ጋር እኩል አይደለም። ይሖዋ ሁሉን ማድረግ የሚያስችል ኃይል ያለው ፈጣሪ ስለሆነ በሁሉም ፍጥረታት ላይ የመግዛት መብት አለው።—ራእይ 4:11
አምላክ እሱን ራሱን የሚቃወም ክፉ ፍጥረት አልፈጠረም። ከዚህ ይልቅ ከመላእክታዊ ‘የአምላክ ልጆች’ መካከል አንዱ ለይሖዋ የሚገባውን እውነተኛ አምልኮ ለራሱ እንዲሰጠው በመፈለግ የራስ ወዳድነት ምኞት አሳደረ። (ኢዮብ 38:7፤ ያዕቆብ 1:14, 15) ይህ ምኞት አምላክን በመቃወም የዓመፀኝነት ጎዳና ወደ መጀመር መራው። ይህ መንፈሳዊ ፍጡር በማመፅ ራሱን ሰይጣን (ማለትም “ተቃዋሚ”) እና ዲያብሎስ (ማለትም “ስም አጥፊ”) አደረገ። ይህንን ሁሉ ስትመለከት ሰይጣን ዓለምን እንዲገዛ ለምን እንደተፈቀደለት ሳያስገርምህ አይቀርም።
ሰይጣን እንዲገዛ የተፈቀደለት ለምንድን ነው?
በምድር ላይ ስለ መግዛት ሰይጣን ለኢየሱስ ምን እንዳለው ታስታውሳለህ? ሰይጣን “ይህ ሥልጣን ሁሉ . . . ለእኔ ተሰጥቶአል . . . ለአንተ እሰጥሃለሁ” በማለት ተናሯግል። (ሉቃስ 4:6) ሰይጣን ዲያብሎስ ሥልጣን የሚኖረው በአምላክ ፈቃድ ብቻ እንደሆነ ይህ ዓረፍተ ነገር ያሳያል። ይሁን እንጂ አምላክ ሰይጣንን የታገሠው ለምንድን ነው?
የዚህ ጥያቄ መልስ ሰይጣን የዓለም ገዥ በመሆን ሥራውን በጀመረበት በኤደን ገነት ውስጥ ከተከሰተው ሁኔታ ጋር የተዛመደ ነው። እዚያም አምላክ ለመጀመሪያዎቹ ወንድና ሴት ለአዳምና ለሔዋን ጥሩ የሆነ ነገር በመንፈግ በመጥፎ መንገድ እየገዛቸው ነው በማለት ሰይጣን ሐሳብ አቀረበ። እንደ ሰይጣን አባባል አምላክ የከለከላቸውን ፍሬ ቢበሉ ነፃ ይወጣሉ። አዳምና ሔዋን ከይሖዋ አገዛዝ ነፃ ሆነው ራሳቸውን በራሳቸው ይመራሉ። እንዲያውም እንደራሱ እንደ አምላክ ይሆናሉ!—ዘፍጥረት 2:16, 17፤ 3:1–5
በዚህ መንገድ በመዋሸትና ሔዋንን በማሳሳት እንዲሁም በእርሷ አማካኝነት አዳምን የአምላክን ሕግ እንዲጥስ በማግባባት ሰይጣን የመጀመሪያዎቹን ሰብዓዊ ባልና ሚስት በእርሱ አለቅነትና ቁጥጥር ሥር አደረጋቸው። ከዚያም ዲያብሎስ የይሖዋ ተቃዋሚ በመሆን አምላካቸው ሆነ። ይሁን እንጂ ነፃነት ከማግኘት ይልቅ አዳምና ሔዋን የሰይጣን፣ የኃጢአትና የሞት ባሪያዎች ሆኑ።—ሮሜ 6:16፤ ዕብራውያን 2:14, 15
ፍጹም ከሆነው ፍትሑ ጋር በመስማማት ይሖዋ ሰይጣንንና ሁለቱን አዲስ ተከታዮቹን በቅጽበት ሊያጠፋቸው ይችል ነበር። (ዘዳግም 32:4) ይሁን እንጂ የሥነ ምግባር ጥያቄ ተነስቶ ነበር። ሰይጣን የይሖዋን አገዛዝ ትክክለኛነት ጥያቄ ውስጥ አስገብቶታል። አምላክ ከእርሱ ተነጥሎ ራስን በራስ መምራት ጥፋት እንደሚያመጣ ማረጋገጥ እንዲቻል በጥበቡ ተጠቅሞ የተወሰነ ጊዜ እንዲያልፍ ፈቀደላቸው። ይሖዋ ዓመፀኞቹ ለተወሰነ ጊዜ እንዲኖሩ ፈቀደ። ይህም አዳምና ሔዋን ልጆች እንዲወልዱ አስቻላቸው።—ዘፍጥረት 3:14–19
ምንም እንኳ አብዛኞቹ የአዳም ዘሮች ለይሖዋ አገዛዝ ራሳቸውን ባያስገዙም አምላክ ከአምላኪዎቹ ጋር በሚያደርገው ግንኙነት የእርሱ አገዛዝ ከሁሉ የበለጠ እንደሆነ እያሳየ ነው። ለይሖዋ ሥልጣን ተገቢ የሆነ እውቅና መስጠት ደስታና እውነተኛ ደህንነት ያመጣል። በሌላው በኩል ግን በሰይጣን ተጽእኖ ሥር ያለው ሰብዓዊ አገዛዝ ውጤቱ ሥቃይና ሥጋት ሆኗል። አዎን፣ “ሰው ሰውን የሚገዛው ለጉዳቱ ነው።” (መክብብ 8:9 አዓት) በዚህ በሰይጣን ኃይል ሥር በወደቀው ዓለም ውስጥ ሰዎች በሰብዓዊ አገዛዝ አማካኝነት እውነተኛ ደህንነትና ዘላቂ ደስታ አላገኙም። ይሁን እንጂ ወደፊት ጥሩ ጊዜ ይመጣል ብለን የምንጠብቅበት በቂ ምክንያት አለን።
ሰይጣን የቀረው ጊዜ አጭር ነው!
ሰይጣን በምድር ላይ ያለው ተጽእኖ ጊዜያዊ ነው። ይሖዋ ሰይጣናዊ አገዛዝን ከእንግዲህ ወዲህ ለረጅም ጊዜ አይታገሥም! በቅርቡ ዲያብሎስ በቁጥጥር ሥር ይውላል። አምላክ ራሱ የመረጠው ጻድቅ ንጉሥ ማለትም አንድ አዲስ ገዥ ምድርን ይቆጣጠራል። ያም ንጉሥ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። በሰማይ የሚያገኘውን ንግሥና አስመልክቶ የራእይ መጽሐፍ “የዓለም መንግሥት ለጌታችንና [ለይሖዋ] ለእርሱ ለክርስቶስ ሆነች” በማለት ይናገራል። (ራእይ 11:15) የመጽሐፍ ቅዱስ የዘመን አቆጣጠርና የቅዱሳን ጽሑፎች ትንቢት ፍጻሜ ይህ ሁኔታ በ1914 እንደተከናወነ ያረጋግጣሉ።—ማቴዎስ 24:3, 6, 7
በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ በዙፋን ላይ ከተቀመጠ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ምን እንደተፈጸመ ይገልጻል። እንዲህ ይላል፦ “በሰማይም ሰልፍ ሆነ፤ ሚካኤልና መላእክቱ ዘንዶውን ተዋጉ። ዘንዶውም ከመላእክቱ ጋር ተዋጋ አልቻላቸውምም፣ ከዚያም ወዲያ በሰማይ ስፍራ አልተገኘላቸውም። ዓለሙንም ሁሉ የሚያስተው፣ ዲያብሎስና ሰይጣን የሚባለው ታላቁ ዘንዶ እርሱም የቀደመው እባብ ተጣለ፤ ወደ ምድር ተጣለ መላእክቱም ከእርሱ ጋር ተጣሉ።”—ራእይ 12:7–9
ሰይጣን ከሰማይ መባረሩ ምን ውጤት አስከትሏል? በሰማይ ያሉት ሊደሰቱ ችለዋል። ይሁን እንጂ በምድር የሚኖሩትስ? “ለምድርና ለባሕር ወዮላቸው፣ ዲያብሎስ ጥቂት ዘመን እንዳለው አውቆ በታላቅ ቁጣ ወደ እናንተ ወርዶአልና” በማለት ራእይ 12:12 ይናገራል። በእርግጥም የሰይጣን ከሰማይ መባረር በምድር ላይ ወዮታ አምጥቷል። “ምዕራቡ ዓለም ሥልጣኔን ራሱ ካመጣው ድንቁርና ወይም መጥፎ ግፊት መጠበቅ እንዳልቻለ . . . ከ1914–1918 በተደረገው የአራት ዓመት ጦርነት የደረሰው ታላቅ ጥፋት ያሳያል። የምዕራቡ ዓለም የሞራል ጥንካሬ በዚያን ጊዜ ከደረሰበት ስብራት ፈጽሞ ሊያገግም አልቻለም” በማለት ዘ ኮሎምቢያ ሂስትሪ ኦቭ ዘ ዎርልድ ዘግቧል።
የዚህ ትውልድ ወዮታዎች ተለይተው የሚታወቁት በደረሰባቸው የመንፈስ መንኮታኮት ብቻ አይደለም። ኢየሱስ “ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣልና፣ ራብም ቸነፈርም የምድርም መናወጥ በልዩ ልዩ ስፍራ ይሆናል” በማለት ተንብዮአል። (ማቴዎስ 24:7, 8፤ ሉቃስ 21:11) ከዚህም በላይ በሰይጣን የነገሮች ሥርዓት “በመጨረሻ ቀን” ውስጥ ብዙዎች “ራሳቸውን የሚወዱ፣ . . . ገንዘብን የሚወዱ፣ . . . ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፣ . . . ዕርቅን የማይሰሙ . . . ይሆናሉ” በማለት መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። በተጨማሪም ሰዎች “ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ ይሆናሉ።”—2 ጢሞቴዎስ 3:1–5
እንደ ጦርነት፣ ቸነፈር፣ የምግብ እጥረት፣ የመሬት መናወጥና የሥነ ምግባር መዝቀጥ ያሉ ነገሮች ሁሉ መጽሐፍ ቅዱስ አስቀድሞ እንደተነበየው ከ1914 ጀምሮ ታይቶ በማይታወቅ መጠን ደርሰዋል። እነዚህ ነገሮች በቁጣ የነደደው የአምላክና የሰው ጠላት ሰይጣን ዲያብሎስ ወደ ምድር አካባቢ መጣሉን ያሳያሉ። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ሰይጣን ለረዥም ጊዜ እየሠራ እንዲቀጥል እንደማይፈቀድለት ያሳያል። የቀረው “ጥቂት ዘመን” ብቻ ነው።
ይህ የተወሰነ ጥቂት ዘመን ሲሟጠጥ ሰይጣን ምን ይደርስበታል? “የጥልቁንም መክፈቻና ታላቁን ሰንሰለት በእጁ የያዘ መልአክ ከሰማይ ሲወርድ አየሁ። የቀደመውንም እባብ ዘንዶውን እርሱም ዲያብሎስና ሰይጣን የተባለውን ያዘው፣ ሺህ ዓመትም አሰረው፣ ወደ ጥልቅም ጣለው . . . በእርሱ ላይ ዘግቶ ማኅተም አደረገበት” በማለት ሐዋርያው ዮሐንስ ጽፏል። (ራእይ 20:1–3) በሥቃይ ላይ ለሚገኙት የሰው ልጆች እንዴት ያለ ግልግል ይሆንላቸዋል!
በአምላክ መንግሥት ግዛት ሥር መደሰት
ሰይጣን ፈጽሞ ስለሚወገድ በኢየሱስ ክርስቶስ የሚገዛው የአምላክ መንግሥት የሰው ዘር ጉዳዮችን ሙሉ ለሙሉ በቁጥጥሩ ውስጥ ያስገባል። በምድር ላይ በነበሩት ብዙ መንግሥታት ፋንታ በመላው ዓለም ላይ አንድ ሰማያዊ መንግሥት ብቻ ይገዛል። ጦርነት አይኖርም። ሰላም በሁሉም ቦታ ይሰፍናል። በአምላክ መንግሥት ግዛት ሥር ሁሉም ሰዎች የሚዋደዱ ወንድማማች ሆነው በአንድነት ይኖራሉ።—መዝሙር 72:7, 8፤ 133:1፤ ዳንኤል 2:44
ኢየሱስ እንዴት ያለ ንጉሥ ይሆናል? ምድር በነበረበት ጊዜ ለሰዎች የጠለቀ ፍቅር አሳይቷል። ኢየሱስ የተራቡ ሰዎችን በርኅራኄ ተገፋፍቶ መግቧቸዋል። በሽተኞችን ፈውሷል፣ ለታወሩት ብርሃን፣ ለዱዳዎች መናገርን፣ ለሽባዎች የተሟላ እጅና እግር ሰጥቷቸዋል። እንዲያውም ኢየሱስ የሞቱትን ወደ ሕይወት መልሷል! (ማቴዎስ 15:30–38፤ ማርቆስ 1:34፤ ሉቃስ 7:11–17) እነዚህ ተዓምራቶች ንጉሥ ሆኖ ወደፊት ለሚያደርጋቸው አስደናቂ ነገሮች መቅድም ናቸው። እንዲህ ያለ ገዥ ማግኘት እንዴት መታደል ነው!
ለይሖዋ ሉዓላዊነት ራሳቸውን የሚያስገዙ ማለቂያ የሌለው በረከት ያገኛሉ። ቅዱሳን ጽሑፎች “በዚያን ጊዜም የዕውሮች ዓይን ይገለጣል የደንቆሮችም ጆሮ ይከፈታል። በዚያን ጊዜ አንካሳ እንደ ሚዳቋ ይዘልላል፣ የድዳም ምላስ ይዘምራል” በማለት ተስፋ ይሰጣሉ። (ኢሳይያስ 35:5, 6) ያንን ታላቅ ቀን በማመልከት ሐዋርያው ዮሐንስ “ታላቅም ድምፅ ከሰማይ፦ እነሆ፣ የእግዚአብሔር ድንኳን በሰዎች መካከል ነው ከእነርሱም ጋር ያድራል፣ እነርሱም ሕዝቡ ይሆናሉ እግዚአብሔርም እርሱ ራሱ ከእነርሱ ጋሮ ሆኖ አምላካቸው ይሆናል፤ እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፣ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ ኃዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና ብሎ ሲና ገር ሰማሁ” በማለት ጽፏል።—ራእይ 21:3, 4
በሰይጣን ቁጥጥር ሥር ያለው የአሁኑ የነገሮች ሥርዓት ሊያደርስብን የሚችለው ማንኛውም ሥቃይ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ የሚተዳደረው የይሖዋ መንግሥት ከሚያመጣቸው አስደሳች በረከቶች ጋር ሲነፃፀር ሥቃዩ ኢምንት ነው። አምላክ ተስፋ በሰጠው አዲስ ዓለም ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ‘ገዥው ማን ነው?’ በማለት ግራ አይጋቡም። (2 ጴጥሮስ 3:13) በመንፈሳዊ ዓለም በሚኖሩ በይሖዋ አምላክና በኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅራዊ አገዛዝ ሥር ያሉ ምድራዊ ተገዥ የሰው ልጆች ደስተኞችና ሥጋት የሌለባቸው ይሆናሉ። ከተገዥዎቻቸው መካከል ለመሆን የአንተም ፍላጎት ነውን?
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በአምላክ መንግሥት ሥር ያሉ ምድራዊ ተገዥ የሰው ልጆች ያለ ስጋት ይኖራሉ
[ምንጭ]
NASA photo